የአንባብያን ጥያቄዎች
የአንባብያን ጥያቄዎች
ከ33 እስከ 36 እዘአ ድረስ የተጠመቁትን አይሁዳውያን በሚመለከት ከዚህ ቀደም የነበረው ግንዛቤ በግለሰብ ደረጃ ራሳቸውን ለአምላክ መወሰን አያስፈልጋቸውም የሚል ሆኖ ሳለ የሚያዝያ 1, 2002 መጠበቂያ ግንብ ገጽ 11 አንቀጽ 7 ላይ በ33 እዘአ በጰንጠቆስጤ ዕለት አዳዲስ አይሁዳውያን አማኞች በውኃ መጠመቃቸው “በክርስቶስ አማካኝነት በግለሰብ ደረጃ ለአምላክ ያደረጉትን ውሳኔ” እንደሚያሳይ የሚናገረው ለምንድን ነው?
በ1513 ከዘአበ ይሖዋ አምላክ እስራኤላውያን ‘ቃሉን የሚሰሙና ቃል ኪዳኑን የሚጠብቁ’ ከሆነ ለእርሱ የተቀደሰ ሕዝብ እንደሚሆኑ ነገራቸው። እነርሱም “እግዚአብሔር የተናገራቸውን ቃሎች ሁሉ እናደርጋለን” ብለው መለሱ።—ዘጸአት 19:3-8፤ 24:1-8
እስራኤላውያን የሙሴን ሕግ ቃል ኪዳን ለመጠበቅ በመስማማት ራሳቸውን ለአምላክ ወስነው ነበር። ተተኪዎቹ የአይሁድ ትውልዶች የተወለዱት ራሱን ለአምላክ በወሰነ ብሔር ውስጥ ነበር። ይሁን እንጂ በ33 እዘአ ከተከበረው የጰንጠቆስጤ በዓል በኋላ የኢየሱስ ተከታዮች የሆኑት አይሁዳውያን በውኃ መጠመቃቸው ለአምላክ የተወሰነ ብሔር አባል አድርገው ራሳቸውን ማቅረባቸውን የሚያመለክት ሳይሆን በክርስቶስ በኩል ከይሖዋ አምላክ ጋር አዲስ ዝምድና ለመመሥረት ራሳቸውን ለእርሱ መወሰናቸውን የሚያሳይ ነው። እንዲህ የምንለው ለምንድን ነው?
በ33 እዘአ በጰንጠቆስጤ ዕለት ኢየሩሳሌም በሚገኝ ደርብ ላይ በተሰበሰቡ 120 የሚያክሉ ደቀ መዛሙርት ላይ መንፈስ ቅዱስ ከወረደባቸው በኋላ ሐዋርያው ጴጥሮስ ስለተፈጸመው ሁኔታ ለማወቅ ለመጡት አይሁዳውያንና ወደ ይሁዲነት የተለወጡ አሕዛብ መስበክ ጀመረ። ጴጥሮስ ሰፊ ምሥክርነት ከሰጣቸው በኋላ በድርጊታቸው የተጸጸቱትን አይሁዳውያን “ንስሐ ግቡ፣ ኃጢአታችሁም ይሰረይ ዘንድ እያንዳንዳችሁ በኢየሱስ ክርስቶስ ስም ተጠመቁ” በማለት አሳሰባቸው። የጴጥሮስን ምክር ሰምተው “ቃሉንም የተቀበሉ ተጠመቁ፣ በዚያም ቀን ሦስት ሺህ የሚያህል ነፍስ ተጨመሩ።”—ሥራ 2:1-41
የጴጥሮስን ማሳሰቢያ ሰምተው የተጠመቁት እነዚህ አይሁዳውያን ቀድሞውኑ ለአምላክ የተወሰነ ብሔር አባላት አልነበሩምን? ራሳቸውን ወስነው ከአምላክ ጋር ዝምድና መሥርተው አልነበረምን? አልነበረም። ሐዋርያው ጳውሎስ ‘አምላክ ሕጉን በመከራ እንጨት ላይ ቸንክሮ ከመንገድ እንዳስወገደው’ ጽፏል። (ቆላስይስ 2:14 አ.መ.ት ) ይሖዋ አምላክ ከእስራኤላውያን ጋር የነበረው ዝምድና የተመሠረተበትን የሕጉን ቃል ኪዳን በ33 እዘአ በክርስቶስ ሞት አማካኝነት አስወገደው። የአምላክን ልጅ አልቀበልም ያለው ብሔር በአምላክ ዘንድ ተቀባይነት አጣ። ‘በሥጋ እስራኤል የሆነው’ ሕዝብ ለአምላክ የተወሰነ ብሔር መሆኑ አከተመ።—1 ቆሮንቶስ 10:18፤ ማቴዎስ 21:43
የሕጉ ቃል ኪዳን በ33 እዘአ ቢወገድም አይሁዳውያን የአምላክን ሞገስ ወዲያውኑ አላጡም። a ጴጥሮስ ፈሪሃ አምላክ ለነበረው ለኢጣሊያዊው ቆርኔሌዎስና ለቤተሰቡ እንዲሁም ለሌሎች አሕዛብ እስከሰበከበት እስከ 36 እዘአ ድረስ ይሖዋ አይሁዳውያንን በተለየ ዓይን መመልከቱን ቀጥሎ ነበር። (ሥራ 10:1-48) ይሖዋ እስከዚያ ጊዜ ድረስ ሞገሱን ያልነፈጋቸው ለምን ነበር?
ዳንኤል 9:27 [አ.መ.ት ] “አለቃው ከብዙዎች ጋር ለአንድ ሱባዔ ቃል ኪዳኑን ያጸናል” ይላል። ኢየሱስ ተጠምቆ መሲሐዊ አገልግሎቱን ከጀመረበት ከ29 እዘአ አንስቶ ለሰባት ዓመታት ወይም “ለአንድ ሱባኤ” እንዲጸና የተደረገው ቃል ኪዳን የአብርሃም ቃል ኪዳን ነበር። የዚህ ቃል ኪዳን ተካፋይ ለመሆን የአብርሃም ዘር መሆን ብቻ ይበቃ ነበር። ይህ የአንድ ወገን ቃል ኪዳን ብቻውን አንድ ሰው ከይሖዋ ጋር በግለሰብ ደረጃ ዝምድና መሥርቷል ሊያስብለው አይችልም። ስለሆነም በ33 እዘአ በጰንጠቆስጤ ዕለት የጴጥሮስን ንግግር ሰምተው የተጠመቁት አይሁዳውያን አማኞች ሥጋዊ እስራኤላውያን መሆናቸው የአምላክን ሞገስ ቢያስገኝላቸውም የሕጉ ቃል ኪዳን ከተወገደ በኋላ ግን ለአምላክ የተወሰነ ሕዝብ ተደርገው ሊቆጠሩ አይችሉም። በግለሰብ ደረጃ ለአምላክ ራሳቸውን መወሰን ይኖርባቸዋል።
በ33 እዘአ በጰንጠቆስጤ ዕለት ራሳቸውን ለጥምቀት ያቀረቡት አይሁዳውያንና ወደ ይሁዲነት የተለወጡት አሕዛብ በግለሰብ ደረጃ ራሳቸውን ለአምላክ መወሰናቸው አስፈላጊ የሆነበት ሌላም ምክንያት አለ። ሐዋርያው ጴጥሮስ ንስሐ ገብተው በኢየሱስ ስም እንዲጠመቁ አድማጮቹን አሳስቧቸው ነበር። እንዲህ ማድረጋቸው የዓለምን መንገድ ትተው ኢየሱስ ጌታ፣ መሢሕና ሊቀ ካህን መሆኑን እንዲሁም በሰማይ በአምላክ ቀኝ መቀመጡን አምነው መቀበል ይጠይቅባቸዋል። ለመዳን በኢየሱስ ክርስቶስ በኩል የይሖዋን ስም መጥራት የሚኖርባቸው ሲሆን ይህም በክርስቶስ ማመንንና እርሱን መሪያቸው አድርጎ መቀበልን ይጨምራል። ከአምላክ ጋር ወዳጅነት ለመመሥረትና የኃጢአት ይቅርታ ለማግኘት የሚቻልበት ሁኔታ ስለተለወጠ አይሁዳውያን አማኞች በግለሰብ ደረጃ ይህን አዲስ ዝግጅት መቀበል ይኖርባቸዋል። እንዴት? ለአምላክ ራሳቸውን በመወሰንና ይህን ውሳኔያቸውን በኢየሱስ ክርስቶስ ስም በውኃ ጥምቀት ለሕዝብ በማሳየት ነው። በውኃ መጠመቃቸው ለአምላክ ራሳቸውን መወሰናቸውን የሚያሳይ መግለጫ ሲሆን በኢየሱስ ክርስቶስ በኩል ከእርሱ ጋር አዲስ ዝምድና እንዲመሠርቱ ያስችላቸዋል።—ሥራ 2:21, 33–36፤ 3:19-23
[የግርጌ ማስታወሻ]
a ኢየሱስ ክርስቶስ ወደ ሰማይ አርጎ መሥዋዕት የሆነውን የሰብዓዊ ሕይወቱን ዋጋ ለይሖዋ አምላክ ሲያቀርብ የሙሴ ሕግ ቃል ኪዳን ፈረሰና በትንቢት የተነገረለት ‘የአዲሱ ቃል ኪዳን’ መሠረት ተጣለ።—ኤርምያስ 31:31-34