‘ሰሎሞን ከእነዚህ እንደ አንዱ አልለበሰም’
‘ሰሎሞን ከእነዚህ እንደ አንዱ አልለበሰም’
በአፍሪካ ደቡባዊ ክፍል እዚህ ላይ እንዳሉት ዓይነት ወፍ ዘራሽ አበቦች መንገድ ዳር ላይ በብዛት ይገኛሉ። አበቦቹ ኮስሞስ ተብለው የሚጠሩ ሲሆን ምንጫቸው በካንሰርና በካፕሪኮርን መስመሮች መካከል የሚገኙ አገሮች ናቸው። እነዚህን የመሰሉ ያማሩ አበቦች ስናይ ኢየሱስ የሰጠውን ትምህርት እናስታውስ ይሆናል። ትምህርቱን ያዳምጡ የነበሩ አብዛኞቹ ሰዎች ድሆች ሲሆኑ እንደ ምግብና ልብስ ለመሳሰሉት ቁሳዊ ነገሮች ይጨነቁ ነበር።
ኢየሱስ “ስለ ልብስስ ስለ ምን ትጨነቃላችሁ?” ብሎ ጠየቃቸው። “የሜዳ አበቦች እንዴት እንዲያድጉ ልብ አድርጋችሁ ተመልከቱ፤ አይደክሙም አይፈትሉምም፤ ነገር ግን እላችኋለሁ፣ ሰሎሞንስ እንኳ በክብሩ ሁሉ ከነዚህ እንደ አንዱ አልለበሰም።”—ማቴዎስ 6:28, 29
ኢየሱስ የተናገረው ስለ የትኛው ዓይነት የሜዳ አበባ ሊሆን እንደሚችል የተለያዩ ሐሳቦች ተሰንዝረዋል። ይሁን እንጂ ኢየሱስ ይህን አበባ ተራ ከሆነ የሜዳ ሣር ጋር በማመሳሰል እንዲህ ሲል ተናግሯል:- “እግዚአብሔር ግን ዛሬ ያለውን ነገም ወደ እቶን የሚጣለውን የሜዳን ሣር እንዲህ የሚያለብሰው ከሆነ፣ እናንተ እምነት የጐደላችሁ፣ እናንተንማ ይልቁን እንዴት?”—ማቴዎስ 6:30
ኮስሞስ የተባሉት አበቦች በእስራኤል ምድር ባይገኙም ኢየሱስ ለሰጠው ትምህርት ማስረጃ ተደርገው ሊወሰዱ ይችላሉ። እነዚህ አበቦች ከሩቅም ሆነ ከቅርበት ሲታዩ አስደናቂ ውበት ያላቸው ከመሆኑም በላይ የፎቶ አንሺዎችንና የሠዓሊያንን ትኩረት ይስባሉ። በእርግጥም፣ ኢየሱስ “ሰሎሞንስ እንኳ በክብሩ ሁሉ ከነዚህ እንደ አንዱ አልለበሰም” ብሎ ሲናገር ማጋነኑ አልነበረም።
ይህ ዛሬ ለእኛ ምን ትምህርት ይዟል? አምላክን የሚያገለግሉ ሰዎች በአስቸጋሪ ወቅቶችም እንኳ መሠረታዊ ፍላጎታቸውን በማሟላት ረገድ እርሱ እንደሚረዳቸው እርግጠኛ መሆን ይችላሉ። ኢየሱስ ‘የአምላክን መንግሥት ፈልጉ ይህም ሁሉ [እንደ ምግብና ልብስ ያሉት አስፈላጊ ነገሮች] ይጨመርላችኋል’ ሲል ገልጿል። (ሉቃስ 12:31) አዎን፣ የአምላክን መንግሥት ማስቀደም ተጨባጭ የሆኑ ጥቅሞች ያስገኛል። ይሁን እንጂ የአምላክ መንግሥት ሲባል ምን ማለት እንደሆነና ለሰው ልጆች ምን እንደሚያደርግላቸው ታውቃለህ? የይሖዋ ምሥክሮች መጽሐፍ ቅዱስ ለእነዚህ ጥያቄዎች የሚሰጠውን መልስ ሊያሳዩህ ፈቃደኞች ናቸው።