ሰዎች የልግስና መንፈስ እያጡ ነውን?
ሰዎች የልግስና መንፈስ እያጡ ነውን?
መስከረም 11, 2001 በኒው ዮርክ ሲቲ እና በዋሽንግተን ዲ ሲ ከደረሰው ጥቃት በኋላ ሕዝቡ በአደጋው የተጎዱትን ሰዎች ለመርዳት ያደረገው ርብርብ የሚያስደንቅ ነበር። የበጎ አድራጎት ድርጅቶች በአደጋው ለተጠቁ ሰዎች ቤተሰቦች እርዳታ የተዋጣ 2.7 ቢልዮን የአሜሪካ ዶላር በአጭር ጊዜ ውስጥ ደረሳቸው። በተለያዩ ቦታዎች የሚኖሩ ሰዎች በደረሰው ከፍተኛ ጥፋት በማዘናቸው ምክንያት እርዳታ ለመለገስ ተነሳስተው ነበር።
ሆኖም ታዋቂ የሆኑ የበጎ አድራጎት ድርጅቶች በእርዳታ የተገኘውን ገንዘብ እያባከኑ መሆኑ ሲሰማ አንዳንዶች በሁኔታው አዘኑ። አንድ ትልቅ የበጎ አድራጎት ድርጅት በልግስና ካገኘው 546 ሚልዮን የአሜሪካ ዶላር ውስጥ ግማሽ የሚያህለውን ለሌላ ዓላማ የማዋል እቅድ እንዳለው መግለጹ በሕዝቡ ዘንድ ከፍተኛ ቁጣ ቀስቅሶ ነበር። ምንም እንኳ ድርጅቱ በኋላ ላይ ውሳኔውን ለውጦ ይቅርታ ቢጠይቅም አንዲት ጋዜጠኛ እንዲህ ብላለች:- “ይህ ወሳኝ እርምጃ” የተወሰደው ድርጅቱ ከጥቃቱ በፊት የነበረውን “አመኔታ መልሶ ማደስ የሚችልበት ጊዜ ካለፈበት በኋላ እንደሆነ ታዛቢዎች ተናግረዋል።” የአንተስ አመለካከት ምንድን ነው? ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በበጎ አድራጎት ድርጅቶች ላይ እምነት እያጣህ ነውን?
ከጥቅሙ ጉዳቱ ያመዝናል?
በጥቅሉ ሲታይ ለበጎ አድራጎት ድርጅቶች ገንዘብ መስጠት መልካም ተግባር እንደሆነ ይታሰባል። ይሁን እንጂ ሁሉም ሰዎች እንዲህ ዓይነት አመለካከት የላቸውም። ሳሙኤል ጆንሰን የተባሉ እንግሊዛዊ ጸሐፊ ከ200 ዓመታት በፊት እንዲህ ሲሉ ጽፈዋል:- “በእርዳታ መልክ ገንዘብ ከመስጠት ይልቅ ሥራ ለሠራልህ ሰው የድካሙን ዋጋ መክፈልህ መልካም ተግባር እንደሆነ እርግጠኛ መሆን ትችላለህ።” ዛሬም አንዳንዶች ለበጎ አድራጎት ድርጅቶች ለመስጠት እምብዛም አይነሳሱም። ለእርዳታ የተዋጣውን ገንዘብ በአግባቡ የማይዙ ወይም የሚያባክኑ ድርጅቶች እንዳሉ የሚሠራጨው ዘገባም በሕዝቡ ዘንድ ያላቸውን አመኔታ አሳጥቷቸዋል። በቅርቡ የተፈጸሙ ሁለት ምሳሌዎች ተመልከት።
በሳን ፍራንሲስኮ የአንድ ሃይማኖታዊ በጎ አድራጎት ድርጅት ኃላፊ የፕላስቲክ ቀዶ ሕክምና ያደረገበትን ወጪና ላለፉት ሁለት ዓመታት በየሳምንቱ ለምግብ ቤት ያወጣውን 500 የአሜሪካ ዶላር ለመሸፈን በድርጅቱ ገንዘብ እንደተጠቀመ ክስ ከቀረበበት በኋላ ከሥራ ተባርሯል። ብሪታንያ ውስጥ በቴሌቪዥን በሚቀርብ ፕሮግራም አማካኝነት የእርዳታ ገንዘብ የሚያሰባስብ የአንድ ታዋቂ ድርጅት አስተባባሪዎች በሩማኒያ አዳዲስ እጓለማውታ ማሳደጊያዎች ለመገንባት በተዋጣው 6.5 ሚልዮን ፓውንድ (ወደ 10 ሚልዮን የአሜሪካ ዶላር) የተገነቡት ደረጃቸውን ያልጠበቁ 12 ቤቶች ብቻ መሆናቸውንና በመቶ ሺዎች የሚቆጠር ገንዘብ
የት እንደደረሰ አለመታወቁ ይፋ ሲወጣ ሃፍረት ተከናንበዋል። እንደዚህ የመሳሰሉ ዘገባዎች አንዳንድ ለጋሾች ምን ያህል ገንዘብ እንደሚሰጡና ለማን እንደሚያስረክቡ በጥንቃቄ እንዲያስቡበት አድርጓቸዋል።ልስጥ ወይስ አልስጥ?
ይሁን እንጂ ጥቂት ግለሰቦች ወይም ድርጅቶች ባደረጉት ነገር የተነሳ ለሌሎች ልባዊ አሳቢነትና ርኅራኄ ከማሳየት ብንቆጠብ የሚያሳዝን ይሆናል። መጽሐፍ ቅዱስ እንዲህ ይላል:- “ንጹሕ የሆነ ነውርም የሌለበት አምልኮ በእግዚአብሔር አብ ዘንድ ይህ ነው፤ ወላጆች የሌላቸውን ልጆች ባልቴቶችንም በመከራቸው መጠየቅ።” (ያዕቆብ 1:27) በእርግጥም ለድሆችና ለተቸገሩ ሰዎች አሳቢነታችንን በተግባር መግለጽ የክርስትና እምነት ዐቢይ ገጽታ ነው።
ያም ሆኖ ‘ለበጎ አድራጎት ድርጅቶች የገንዘብ መዋጮ መስጠት ልቀጥል ወይስ የተቸገሩ ሰዎችን በቀጥታ ብረዳ ይሻላል?’ ብለህ ታስብ ይሆናል። አምላክ የሚቀበለው ምን ዓይነት ልግስናን ነው? የሚቀጥለው ርዕስ ለእነዚህ ጥያቄዎች መልስ ይዟል።