“አትፍሩ፣ አትደንግጡም”
“አትፍሩ፣ አትደንግጡም”
“እግዚአብሔርም ከእናንተ ጋር ነውና አትፍሩ፣ አትደንግጡም።”—2 ዜና መዋዕል 20:17
1. ሽብርተኝነት በሰዎች ላይ ምን አስከትሏል? ሰዎች መፍራታቸው ሊያስደንቀን የማይገባው ለምንድን ነው?
ሽብርተኝነት! ቃሉ ራሱ በሰው ልብ ውስጥ ፍርሃትንና ስጋትን ይጭራል። ድንጋጤ፣ ሐዘንና ቁጣ የተቀላቀለበት ስሜት ይቀሰቅሳል። እንዲሁም ብዙዎች ለመጪዎቹ ብዙ ዓመታት በሰው ልጆች ላይ ሰቆቃ ያስከትላል ብለው የሚፈሩትን እኩይ ተግባር የሚገልጽ ቃል ነው። አንዳንድ አገሮች ለብዙ ዓመታት ሽብርተኝነትን ሲታገሉ ቢቆዩም እምብዛም ውጤት አለማግኘታቸው ለዚህ ፍርሃት መባባስ መንስኤ ሆኗል።
2. የይሖዋ ምሥክሮች ሽብርተኝነት ስለሚያስከትለው አስከፊ ሁኔታ ምን አመለካከት አላቸው? ይህስ የትኞቹን ጥያቄዎች ያስነሳል?
2 የሆነ ሆኖ ሁኔታው ተስፋ አስቆራጭ አይደለም እንድንል የሚያደርግ በቂ ምክንያት አለ። በ234 አገሮችና ግዛቶች ውስጥ ምሥራቹን በትጋት የሚሰብኩት የይሖዋ ምሥክሮች ሁኔታው ይለወጣል የሚል ብሩሕ ተስፋ አላቸው። ሽብርተኝነት ፈጽሞ ሊወገድ አይችልም ብለው አይፈሩም፤ ከዚህ ይልቅ በቅርቡ እንደሚወገድ ሙሉ ትምክህት አላቸው። እንዲህ ያለ ተስፋ ለማሳደር የሚያስችል ምን ምክንያት አለ? ይህን እኩይ ተግባር ከዓለም ላይ ማስወገድ የሚችለው ማን ነው? እንዴትስ? ዓይነቱ ይለያይ እንጂ ሁላችንም በአንድ ዓይነት የዓመፅ ድርጊት ተነክተን ሊሆን ስለሚችል ሽብርተኝነት ይወገዳል ብለን እንድናምን የሚያደርገንን ምክንያት መመርመራችን የተገባ ነው።
3. ሰዎችን በፍርሃት እንዲዋጡ የሚያደርጓቸው አንዳንድ ሁኔታዎች ምንድን ናቸው? የምንገኝበትን ጊዜ በተመለከተ ምን ትንቢት ተነግሮ ነበር?
3 በዛሬው ጊዜ ሰዎች በተለያዩ ምክንያቶች የተነሳ ፍርሃትና ስጋት ያድርባቸዋል። እስቲ ለአንድ አፍታ በዕድሜ መግፋት ሳቢያ ራሳቸውን መርዳት ስለማይችሉት፣ በማይድን በሽታ ምክንያት አቅም ስላጡት እንዲሁም የዕለት ጉርስ ለማግኘት ደፋ ቀና ስለሚሉት ቤተሰቦች አስብ። ሕይወት ራሱ ምን ያህል አስተማማኝ እንዳልሆነም አስብ! በድንገተኛ ወይም በተፈጥሮ አደጋ ምክንያት የሚከሰተው ሞት የምንወዳቸውን ከጉያችን ለመንጠቅ አድብቶ የሚጠባበቅ ይመስላል። እንዲህ ያለው ፍርሃትና ጭንቀት በዕለት ተዕለት ሕይወታችን ከሰዎች ጋር ከሚያጋጥመን አለመግባባትና ቅሬታ ጋር ተዳምሮ ሐዋርያው ጳውሎስ “በመጨረሻው ቀን የሚያስጨንቅ ዘመን እንዲመጣ ይህን እወቅ። ሰዎች ራሳቸውን የሚወዱ ይሆናሉና፣ . . . ፍቅር የሌላቸው፣ ዕርቅን የማይሰሙ፣ ሐሜተኞች፣ ራሳቸውን የማይገዙ፣ ጨካኞች፣ መልካም የሆነውን የማይወዱ” በማለት በተናገረለት ዘመን ውስጥ እንደምንኖር ያሳያሉ።—2 ጢሞቴዎስ 3:1-3
4. የጊዜውን አስከፊነት ጎላ አድርጎ የሚገልጸው 2 ጢሞቴዎስ 3:1-3 ምን የተስፋ ጭላንጭል ይፈነጥቃል?
4 ምንም እንኳ ይህ ጥቅስ የጊዜውን አስከፊነት የሚያጎላ ቢሆንም የተስፋ ጭላንጭልም ይፈነጥቃል። እንዲህ ያለው አስጨናቂ ሁኔታ አሁን በምንኖርበት ክፉ የሰይጣን ሥርዓት ‘የመጨረሻ ቀን’ ላይ እንደሚከሰት ልብ በል። ይህም ክፉው የሰይጣን ዓለም ኢየሱስ ተከታዮቹ እንዲጸልዩለት ባስተማራቸው የአምላክ መንግሥት አገዛዝ የሚተካበትና ከዚህ አስከፊ ሁኔታ እፎይ የምንልበት ጊዜ ሩቅ እንዳልሆነ የሚጠቁም ነው። (ማቴዎስ 6:9, 10) ይህ መንግሥት ‘ለዘላለም የማይፈርሰው’ የአምላክ ሰማያዊ መስተዳድር ሲሆን ነቢዩ ዳንኤል “እነዚያንም [ሰብዓዊ] መንግሥታት ሁሉ ትፈጫቸዋለች ታጠፋቸውማለች፣ ለዘላለምም ትቆማለች” በማለት ተናግሮለታል።—ዳንኤል 2:44
ገለልተኛ ክርስቲያኖች ስለ ሽብርተኝነት ያላቸው አቋም
5. በቅርቡ መንግሥታት በዓለማችን ላይ ያጠላውን የሽብርተኝነት አደጋ ለማስወገድ ምን አድርገዋል?
5 ለብዙ ዓመታት ሽብርተኝነት በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎችን ሕይወት ሲቀጥፍ ቆይቷል። ብዙዎች ሽብርተኝነት አደገኛ መሆኑን ይበልጥ የተገነዘቡት ግን መስከረም 11, 2001 በኒው ዮርክ ሲቲና በዋሽንግተን ዲ ሲ ከተፈጸመው ጥቃት በኋላ ነው። ከችግሩ ስፋትና ዓለም አቀፋዊነት አኳያ በዓለም ዙሪያ ያሉ መንግሥታት ሽብርተኝነትን በጋራ ለመዋጋት ኃይላቸውን አስተባብረዋል። ለምሳሌ ያህል፣ መገናኛ ብዙኃን እንደዘገቡት ታኅሣሥ 4, 2001 “ከአውሮፓ፣ ከሰሜን አሜሪካና ከመካከለኛው እስያ የተውጣጡ 55 የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች” ጥረታቸውን ለማስተባበር የሚያስችላቸውን “ዕቅድ በአንድ ድምፅ አጽድቀዋል።” አንድ ከፍተኛ የአሜሪካ ባለሥልጣን ይህ እርምጃ ሽብርተኝነትን ለመዋጋት በሚደረገው ጥረት “ትልቅ እመርታ” እንደሆነ በመግለጽ አወድሰውታል። በመቶ ሚልዮኖች የሚቆጠሩ ሰዎች ዘ ኒው ዮርክ ታይምስ ማጋዚን “መጠነ ሰፊ ለሆነ ጦርነት መጀመሪያ” ብሎ በጠራው ዘመቻ ውስጥ ሳይታወቃቸው ገብተዋል። ይህ ጥረት ምን ያህል ስኬታማ እንደሚሆን ጊዜ የሚያሳየን ይሆናል። ይሁን እንጂ በሽብርተኝነት ላይ የታወጀው ይህ ጦርነት የሚያስከትለው መዘዝ ብዙዎችን ለፍርሃትና ለጭንቀት ዳርጓቸዋል። በይሖዋ የሚታመኑ ሰዎች ግን ከዚህ ስጋት ነጻ ናቸው።
6. (ሀ) አንዳንዶች የይሖዋ ምሥክሮች የሚከተሉትን የገለልተኝነት አቋም ለመቀበል የሚከብዳቸው ለምንድን ነው? (ለ) ኢየሱስ የፖለቲካ ጉዳዮችን በሚመለከት ለተከታዮቹ ምን ምሳሌ ትቶላቸዋል?
6 የይሖዋ ምሥክሮች ከፖለቲካ ጉዳዮች ገለልተኛ መሆናቸው በብዙዎች ዘንድ የሚታወቅ ነው። ብዙ ሰዎች በሰላም ወቅት ይህን አቋማቸውን ለመቀበል ፈቃደኛ ቢሆኑም ያልተጠበቁ ሁኔታዎች በሚያጋጥሙበት ጊዜ ግን ለመቀበል ይቸግራቸዋል። ብዙውን ጊዜ ጦርነት የሚያስከትለው ፍርሃትና አለመረጋጋት ብሔራዊ ስሜት በከፍተኛ ሁኔታ እንዲቀጣጠል ያደርጋል። በዚህ ምክንያት አንዳንዶች ከፍተኛ ተቀባይነት ያገኙ ብሔራዊ እንቅስቃሴዎችን መደገፍ የማይፈልጉ ሰዎች መኖራቸውን መቀበል ይከብዳቸዋል። የሆነ ሆኖ እውነተኛ ክርስቲያኖች ‘የዓለም ክፍል’ እንዳይሆኑ ኢየሱስ የሰጣቸውን ትእዛዝ መከተል እንደሚገባቸው ያውቃሉ። (ዮሐንስ 15:19፤ 17:14-16፤ 18:36፤ ያዕቆብ 4:4) ይህ ደግሞ በፖለቲካም ሆነ በማኅበራዊ ጉዳዮች ገለልተኛ መሆንን ይጠይቃል። በዚህ ረገድ ኢየሱስ ራሱ ትክክለኛውን ምሳሌ ትቶልናል። እንደ ፍጹም ጥበቡና የላቀ ችሎታው ቢሆን ኖሮ በዘመኑ የነበሩትን ሰብዓዊ ችግሮች ለመቅረፍ ግሩም አስተዋጽኦ ባደረገ ነበር። ሆኖም በፖለቲካ ጉዳዮች እጁን ከማስገባት ተቆጥቧል። አገልግሎቱን በጀመረበት አካባቢ በዓለም መንግሥታት ሁሉ ላይ እንዲገዛ ሰይጣን ያቀረበለትን ግብዣ ያለምንም ማመንታት ውድቅ አድርጎታል። ከጊዜ በኋላም ሕዝቡ የፖለቲካ ሥልጣን ሊሰጠው በፈለገ ጊዜ ለመቀበል ፈቃደኛ ሳይሆን ቀርቷል።—ማቴዎስ 4:8-10፤ ዮሐንስ 6:14, 15
7, 8. (ሀ) የይሖዋ ምሥክሮች የሚከተሉት የገለልተኝነት አቋም እንደምን ተደርጎ ሊቆጠር አይገባም? ለምንስ? (ለ) ሮሜ 13:1, 2 መንግሥትን በመቃወም በሚደረጉ የዓመፅ እንቅስቃሴዎች መሳተፍ እንደሌለብን የሚያሳየው እንዴት ነው?
7 የይሖዋ ምሥክሮች የገለልተኝነት አቋም መያዛቸው የዓመፅ ድርጊቶችን እንደ መደገፍ ወይም ቸል ብሎ እንደ ማለፍ ተደርጎ ሊቆጠር አይገባም። የዓመፅ ድርጊቶችን ቢደግፉ ኖሮ “የፍቅርና የሰላምም አምላክ” አገልጋዮች ነን ለማለት አያስደፍራቸውም። (2 ቆሮንቶስ 13:11) ይሖዋ ስለ ዓመፅ ምን አመለካከት እንዳለው ተምረዋል። መዝሙራዊው “እግዚአብሔር ጻድቅንና ኀጥእን ይመረምራል፤ ዓመፃን የወደዳት ግን ነፍሱን ጠልቶአል” በማለት ጽፏል። (መዝሙር 11:5) እንዲሁም ኢየሱስ “ሰይፍ የሚያነሡ ሁሉ በሰይፍ ይጠፋሉና ሰይፍህን ወደ ስፍራው መልስ” በማለት ለሐዋርያው ጴጥሮስ የሰጠውን ምክር ጠንቅቀው ያውቃሉ።—ማቴዎስ 26:52
8 ሐሰተኛ ክርስቲያኖች ብዙውን ጊዜ “ሰይፍ” ማንሳት እንደሚቀናቸው ታሪክ በግልጽ የሚያሳይ ቢሆንም የይሖዋ ምሥክሮች ግን እንዲህ አያደርጉም። ከዚህ ይልቅ እንዲህ ባለው እንቅስቃሴ ውስጥ እጃቸውን ከማስገባት ይቆጠባሉ። የይሖዋ ምሥክሮች በሮሜ 13:1, 2 ላይ የሚገኘውን የሚከተለውን ምክር በጥብቅ ይከተላሉ:- “ነፍስ ሁሉ በበላይ ላሉት [የመንግሥት] ባለ ሥልጣኖች ይገዛ። ከእግዚአብሔር ካልተገኘ በቀር ሥልጣን የለምና፤ ያሉትም ባለ ሥልጣኖች በእግዚአብሔር የተሾሙ ናቸው። ስለዚህ ባለ ሥልጣንን የሚቃወም የእግዚአብሔርን ሥርዓት ይቃወማል፤ የሚቃወሙትም በራሳቸው ላይ ፍርድን ይቀበላሉ።”
9. የይሖዋ ምሥክሮች ሽብርተኝነትን የሚዋጉባቸው ሁለት መንገዶች የትኞቹ ናቸው?
9 ሽብርተኝነት እኩይ ተግባር መሆኑ የማያጠያይቅ ከሆነ የይሖዋ ምሥክሮች ሽብርተኝነትን ለመዋጋት በሚደረገው ጥረት የበኩላቸውን አስተዋጽኦ ማድረግ አይኖርባቸውም? አዎን አለባቸው፤ ደግሞም እያደረጉ ነው። በመጀመሪያ ደረጃ፣ እነርሱ ራሳቸው በሽብር ድርጊቶች ከመካፈል ይቆጠባሉ። በሌላ በኩል ሰዎች በማንኛውም ዓይነት የዓመፅ ድርጊት መካፈላቸውን እንዲያቆሙ የሚረዱ የመጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ ሥርዓቶችን ያስተምራሉ። a ባለፈው ዓመት የይሖዋ ምሥክሮች ለሰዎች ይህንን ክርስቲያናዊ አኗኗር በማስተማር 1,202,381,302 ሰዓት አሳልፈዋል። ይህ ጊዜ በከንቱ የባከነ አልነበረም። ምክንያቱም በዚህ እንቅስቃሴያቸው የተነሳ 265, 469 የሚያህሉ ሰዎች ዓመፅን መጥላታቸውን በሕዝብ ፊት ለማሳየት ተጠምቀው የይሖዋ ምሥክሮች ሆነዋል።
10. ከዓለም ላይ ክፋትን ጠራርጎ ለማስወገድ ያለው ተስፋ ምንድን ነው?
10 ከዚህም በተጨማሪ የይሖዋ ምሥክሮች በራሳቸው ጥረት ብቻ ከዓለም ላይ ክፋትን ማስወገድ እንደማይችሉ ያውቃሉ። ሙሉ ትምክህታቸውን ይህን ማድረግ በሚችለው በይሖዋ አምላክ ላይ የሚጥሉት ለዚህ ነው። (መዝሙር 83:18) ሰዎች የቱንም ያህል ቢጥሩ ዓመፅን ሙሉ በሙሉ ማስወገድ አይችሉም። አንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ጸሐፊ የምንገኝበትን ‘የመጨረሻ ዘመን’ አስመልክቶ “ክፉዎች ሰዎችና አታላዮች፣ እያሳቱና እየሳቱ፣ በክፋት እየባሱ ይሄዳሉ” በማለት አስጠንቅቆናል። (2 ጢሞቴዎስ 3:1, 13) ከዚህ አኳያ ሲታይ የሰው ልጆች ከክፋት ጋር የሚያደርጉትን ውጊያ በድል መወጣት የሚችሉ አይመስልም። በሌላ በኩል ግን ዓመፅን ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ እንደሚያስወግድልን በይሖዋ ላይ መመካት እንችላለን።—መዝሙር 37:1, 2, 9-11፤ ምሳሌ 24:19, 20፤ ኢሳይያስ 60:18
መጪውን ጥቃት በድፍረት መጋፈጥ
11. ይሖዋ ዓመፅን ለማስወገድ የትኞቹን እርምጃዎች ወስዷል?
11 የሰላም አምላክ ዓመፅን ስለሚጠላ የዓመፅ ዋነኛ መንስኤ የሆነውን ሰይጣን ዲያብሎስን ለማጥፋት አንዳንድ እርምጃዎችን የወሰደበትን ምክንያት መረዳት አያዳግተንም። እንዲያውም በመላእክት አለቃ በሚካኤል ማለትም በመንግሥቱ ላይ በሾመው አዲስ ንጉሥ በኢየሱስ ክርስቶስ አማካኝነት ሰይጣንን አሳፋሪ ሽንፈት አከናንቦታል። መጽሐፍ ቅዱስ ስለዚህ ጦርነት ሲናገር እንዲህ ይላል:- “በሰማይም ሰልፍ ሆነ፤ ሚካኤልና መላእክቱ ዘንዶውን ተዋጉ። ዘንዶውም ከመላእክቱ ጋር ተዋጋ አልቻላቸውምም፣ ከዚያም ወዲያ በሰማይ ስፍራ አልተገኘላቸውም። ዓለሙንም ሁሉ የሚያስተው፣ ዲያብሎስና ሰይጣን የሚባለው ታላቁ ዘንዶ እርሱም የቀደመው እባብ ተጣለ፤ ወደ ምድር ተጣለ መላእክቱም ከእርሱ ጋር ተጣሉ።”—ራእይ 12:7-9
12, 13. (ሀ) 1914ን ልዩ ዓመት የሚያደርገው ምንድን ነው? (ለ) የሕዝቅኤል ትንቢት የአምላክን መንግሥት በሚደግፉ ሰዎች ላይ ምን እንደሚደርስባቸው ይናገራል?
12 የመጽሐፍ ቅዱስ የዘመናት ስሌትና የዓለም ሁኔታዎች ይህ ጦርነት በሰማይ የተካሄደው በ1914 መሆኑን በግልጽ ይጠቁማሉ። ከዚያን ጊዜ አንስቶ የዓለም ሁኔታዎች እየተባባሱ መጥተዋል። ራእይ 12:12 ይህ የሆነበትን ምክንያት ሲናገር እንዲህ ይላል:- “ስለዚህ፣ ሰማይና በውስጡ የምታድሩ ሆይ፣ ደስ ይበላችሁ፤ ለምድርና ለባሕር ወዮላቸው፣ ዲያብሎስ ጥቂት ዘመን እንዳለው አውቆ በታላቅ ቊጣ ወደ እናንተ ወርዶአልና።”
13 የዲያብሎስ ቁጣ በዋነኛነት ያነጣጠረው በመንፈስ በተቀቡት የአምላክ አገልጋዮችና አጋሮቻቸው በሆኑት “ሌሎች በጎች” ላይ መሆኑ የታወቀ ነው። (ዮሐንስ 10:16፤ ራእይ 12:17) በቅርቡ ዲያብሎስ ሙሉ ተስፋቸውን በአምላክ መንግሥት ላይ በሚያደርጉትና ለዚህ መንግሥት ድጋፋቸውን በሚሰጡት ሰዎች ላይ ከባድ ጥቃት ሲሰነዝር ይህ ተቃውሞ ከፍተኛ ደረጃ ላይ ይደርሳል። ሰይጣን ያለ የሌለ ኃይሉን አሰባስቦ የሚከፍተው ይህ ጥቃት በሕዝቅኤል ምዕራፍ 38 ላይ ‘የማጎጉ ጎግ’ ጥቃት ተብሏል።
14. የይሖዋ ምሥክሮች ባለፉት ጊዜያት የማንን ከለላ አግኝተዋል? ይህ ጥበቃ ወደፊትም ይቀጥል ይሆን?
14 በራእይ 12:15, 16 ላይ በምሳሌያዊ መንገድ የተገለጹት አንዳንድ የፖለቲካ ኃይሎች ሰይጣን ከሰማይ ከተጣለ በኋላ በአምላክ ሕዝቦች ላይ ከሰነዘረው ጥቃት ከለላ የሆኑላቸው ጊዜያት ነበሩ። ሰይጣን የመጨረሻ ጥቃቱን በሚሰነዝርበት ወቅት ግን የትኛውም ሰብዓዊ ድርጅት በይሖዋ ላይ የሚታመኑትን ሰዎች እንደማይታደጋቸው መጽሐፍ ቅዱስ ይናገራል። ታዲያ ይህ ክርስቲያኖች እንዲፈሩ ወይም እንዲሸበሩ ሊያደርጋቸው ይገባል? በፍጹም!
15, 16. (ሀ) ይሖዋ በኢዮሣፍጥ ዘመን ሕዝቡን ለማረጋጋት የተናገራቸው ቃላት በዛሬው ጊዜ ለሚገኙ ክርስቲያኖች ምን ተስፋ ይሰጣሉ? (ለ) ኢዮሣፍጥና ሕዝቡ በዛሬው ጊዜ ለሚገኙ የአምላክ አገልጋዮች ምን ምሳሌ ትተዋል?
15 አምላክ በንጉሥ ኢዮሣፍጥ ዘመን ሕዝቡን እንደታደገ ሁሉ አሁንም ከሕዝቦቹ ጎን ይቆማል። መጽሐፍ ቅዱስ እንዲህ ይላል:- “ይሁዳ ሁሉ፣ በኢየሩሳሌምም የምትኖሩ፣ አንተም ንጉሡ ኢዮሣፍጥ፣ ስሙ፤ እግዚአብሔር እንዲህ ይላችኋል:- ሰልፉ የእግዚአብሔር ነው እንጂ የእናንተ አይደለምና ከዚህ ታላቅ ወገን የተነሣ አትፍሩ፣ አትደንግጡም። . . . እናንተ በዚህ ሰልፍ የምትዋጉ አይደላችሁም፤ ይሁዳና ኢየሩሳሌም ሆይ፣ ተሰለፉ፣ ዝም ብላችሁ ቁሙ፣ የሚሆነውንም የእግዚአብሔርን መድኃኒት እዩ፤ እግዚአብሔርም ከእናንተ ጋር ነውና አትፍሩ፣ አትደንግጡም፣ ነገም ውጡባቸው።”—2 ዜና መዋዕል 20:15-17
16 የይሁዳ ሰዎች በውጊያው መካፈል እንደማያስፈልጋቸው ተነግሯቸው ነበር። በተመሳሳይም የአምላክ ሕዝቦች የማጎጉ ጎግ ጥቃት ሲሰነዝርባቸው ራሳቸውን ለመከላከል መሣሪያ አያነሱም። ከዚህ ይልቅ ‘ዝም ብለው ቆመው የይሖዋን ማዳን ይመለከታሉ።’ እርግጥ በኢዮሣፍጥ ዘመን የነበሩ የአምላክ ሕዝቦች እጃቸውን አጣምረው እንዳልቆሙ ሁሉ በአሁኑ ጊዜም ዝም ብለው ይቆማሉ ሲባል ምንም እንቅስቃሴ አያደርጉም ማለት አይደለም። መጽሐፍ ቅዱስ እንዲህ ይላል:- “ኢዮሣፍጥም በምድር ላይ ተደፋ፤ ይሁዳም ሁሉ በኢየሩሳሌምም የሚኖሩ በእግዚአብሔር ፊት ወደቁ፣ ለእግዚአብሔርም ሰገዱ። . . . [ኢዮሣፍጥ] ከሕዝቡም ጋር ተማክሮ በሠራዊቱ ፊት የሚሄዱትን:- ምሕረቱ ለዘላለም ነውና እግዚአብሔርን አመስግኑ የሚሉትንም፣ ጌጠኛ ልብስም ለብሰው የሚያመሰግኑትን፣ ለእግዚአብሔርም የሚዘምሩትን መዘምራን አቆመ።” (2 ዜና መዋዕል 20:18-21) አዎን፣ ሕዝቡ የጠላት ዒላማ ሆነው እያለም ይሖዋን ማወደሳቸውን አላቆሙም ነበር። ይህ ታሪክ የይሖዋ ምሥክሮች የጎግ ጥቃት ሲሰነዘርባቸው ምን ማድረግ እንዳለባቸው የሚያሳይ ምሳሌ ነው።
17, 18. (ሀ) የይሖዋ ምሥክሮች የጎግን ጥቃት በሚመለከት እንዴት ያለ የድፍረት አቋም ወስደዋል? (ለ) በቅርቡ ለወጣት ክርስቲያኖች ምን ማሳሰቢያ ተሰጥቷቸዋል?
17 እስከዚያው ድረስ የይሖዋ ምሥክሮች የአምላክን መንግሥት መደገፋቸውን ይቀጥላሉ። ይህ ድጋፍ ጎግ ጥቃቱን ከከፈተ በኋላም አያቋርጥም። በዓለም ዙሪያ በሚገኙ 94, 600 ጉባኤዎች አማካኝነት ማበረታቻና ጥበቃ ማግኘታቸውን ይቀጥላሉ። (ኢሳይያስ 26:20) ጊዜው ይሖዋን በድፍረት የሚያወድሱበት ወቅት ነው! ጎግ ጥቃት የሚሰነዝርበት ጊዜ መቃረቡ በፍርሃት ወደኋላ እንዲያፈገፍጉ እንደማያደርጋቸው የታወቀ ነው። ከዚህ ይልቅ የሚያቀርቡትን የምስጋና መሥዋዕት አቅማቸው በፈቀደ መጠን ከፍ ለማድረግ ያነሳሳቸዋል።—መዝሙር 146:2
18 በዓለም ዙሪያ የሚገኙ በሺዎች የሚቆጠሩ ወጣቶች በሙሉ ጊዜ አገልግሎት በመካፈል እንዲህ ያለውን የድፍረት ዝንባሌ አሳይተዋል። የሙሉ ጊዜ አገልግሎትን የሕይወት ግብ ማድረግ ከምንም ነገር የበለጠ እንደሆነ ለማጉላት በ2002 በተደረጉት የአውራጃ ስብሰባዎች ላይ ወጣቶች—በሕይወታችሁ ምን ለማድረግ አስባችኋል? የተባለ ትራክት ወጥቶ ነበር። ክርስቲያኖች ወጣትም ሆኑ አረጋውያን እንዲህ ላለው ወቅታዊ ማሳሰቢያ አመስጋኞች ናቸው።—መዝሙር 119:14, 24, 99, 119, 129, 146
19, 20. (ሀ) ክርስቲያኖች መፍራት ወይም መሸበር የማይኖርባቸው ለምንድን ነው? (ለ) የሚቀጥለው የጥናት ርዕስ ስለ ምን ነገር ያብራራል?
19 የዓለም ሁኔታ የቱንም ያህል እየከፋ ቢሄድ ክርስቲያኖች ሊፈሩ ወይም ሊሸበሩ አይገባም። በቅርቡ የአምላክ መንግሥት ዓመፅን ከምድር ላይ ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ጠራርጎ እንደሚያስወግድ ያውቃሉ። እንዲሁም በዓመፅ ሳቢያ ሕይወታቸውን ያጡ በርካታ ሰዎች ትንሣኤ እንደሚያገኙ ማወቃቸው ያጽናናቸዋል። ይህ ተስፋ ፍጻሜውን ሲያገኝ አንዳንዶች ስለ ይሖዋ ማወቅ የሚችሉበት አጋጣሚ የሚያገኙ ሲሆን ሌሎች ደግሞ እርሱን በማገልገል የጀመሩትን ጎዳና እንዲቀጥሉ ያስችላቸዋል።—ሥራ 24:15
20 እውነተኛ ክርስቲያኖች እንደመሆናችን መጠን ክርስቲያናዊ ገለልተኝነታችንን ጠብቀን መኖር አስፈላጊ መሆኑን ከመገንዘባችንም በላይ እንዲህ ለማድረግ ቁርጥ ውሳኔ አድርገናል። ‘ዝም ብለን ቆመን የይሖዋን ማዳን እንድንመለከት’ የተሰጠንን ተስፋ እስከመጨረሻው ይዘን መቀጠል እንፈልጋለን። የሚቀጥለው ርዕስ ፍጻሜያቸውን ስላገኙት የመጽሐፍ ቅዱስ ትንቢቶች ያለንን እውቀት ደረጃ በደረጃ የሚያሳድጉልንን በጊዜያችን የተፈጸሙ ክስተቶች በማብራራት እምነታችንን ያጠነክርልናል።
[የግርጌ ማስታወሻዎች]
a የይሖዋ ምሥክሮች ለመሆን ሲሉ በዓመፅ ድርጊቶች መካፈላቸውን እርግፍ አድርገው ስለተዉ ሰዎች የሚናገሩ ምሳሌዎችን (ተሞክሮዎችን) ለማግኘት የሚከተሉትን መጽሔቶች ተመልከት። ታኅሣሥ 1999 ንቁ! ገጽ 22፤ ጥር 1, 1996 መጠበቂያ ግንብ ገጽ 5, 6 እና ነሐሴ 1, 1998 መጠበቂያ ግንብ ገጽ 5, 6።
ልታብራራ ትችላለህን?
• በዛሬው ጊዜ ብዙዎች የዓለም ሁኔታ ተስፋ አስቆራጭ የሆነባቸው ለምንድን ነው?
• የይሖዋ ምሥክሮች የወደፊቱን ጊዜ በሚመለከት ብሩሕ አመለካከት የያዙት ለምንድን ነው?
• ይሖዋ የዓመፅ መንስኤ የሆነውን ሰይጣንን ለማስወገድ ምን እርምጃ ወስዷል?
• የጎግን ጥቃት መፍራት የማይኖርብን ለምንድን ነው?
[የአንቀጾቹ ጥያቄዎች]
[በገጽ 13 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ኢየሱስ ክርስቲያናዊ ገለልተኝነትን በሚመለከት ተገቢውን ምሳሌ ትቷል
[በገጽ 16 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
በሺዎች የሚቆጠሩ ወጣት ምሥክሮች በሙሉ ጊዜ አገልግሎት በደስታ በመካፈል ላይ ይገኛሉ
[በገጽ 16 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ወጣቶች— በሕይወታችሁ ምን ለማድረግ አስባችኋል?
[በገጽ 12 ላይ የሚገኝ የሥዕል ምንጭ]
UN PHOTO 186226/M. Grafman