በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ዕጣን ማጤስ—በእውነተኛው አምልኮ ውስጥ አስፈላጊ ነውን?

ዕጣን ማጤስ—በእውነተኛው አምልኮ ውስጥ አስፈላጊ ነውን?

ዕጣን ማጤስ—በእውነተኛው አምልኮ ውስጥ አስፈላጊ ነውን?

የጥንቶቹ ግብጻውያን “አማልክት መልካም መዓዛ ይወዳሉ” የሚል የተለመደ አባባል ነበራቸው። ዕጣን ማጤስ በአምልኳቸው ውስጥ ትልቅ ቦታ ነበረው። ግብጻውያኑ አማልክቱ ቅርብ እንደሆኑ ያምኑ ስለነበር በቤተ መቅደሶቻቸው፣ በቤታቸው ውስጥ ባሉት መሠዊያዎች እንዲሁም ሥራ ሲሠሩም ጭምር በየዕለቱ ዕጣን ያጤሱ ነበር። ሌሎች ሕዝቦችም ተመሳሳይ ልማድ ነበራቸው።

ዕጣን ምንድን ነው? ዕጣን የሚዘጋጀው እንደ በለሳን ከመሰሉ ጥሩ መዓዛ ካላቸው ሙጫዎች ነው። እነዚህ ንጥረ ነገሮች ከተፈጩ በኋላ እንደ ቅመም፣ የዛፍ ቅርፊትና አበባ ከመሳሰሉ ነገሮች ጋር ይቀላቀሉና ለየት ላለ ዓላማ የሚውል ግሩም መዓዛ እንዲኖራቸው ተደርገው ይዘጋጃሉ።

በጥንት ጊዜ ዕጣን በጣም ተፈላጊና ከፍተኛ ዋጋ የሚያወጣ ሸቀጥ ስለነበር ዕጣን ለመሥራት የሚያገለግሉት ንጥረ ነገሮች ጥሩ ገበያ ነበራቸው። ነጋዴዎች እነዚህን ሸቀጦች ርቀው ከሚገኙ አገሮች በከብት ጭነው ያመጡ ነበር። የያዕቆብ ልጅ ዮሴፍ ‘በግመሎቻቸው ሽቱ፣ በለሳንና ከርቤ ጭነው ከገለዓድ ወደ ግብጽ ለሚጓዙ’ እስማኤላውያን ነጋዴዎች መሸጡን ታስታውስ ይሆናል። (ዘፍጥረት 37:25) ዕጣን በጣም ተፈላጊ ሸቀጥ ከመሆኑ የተነሳ በእስያና በአውሮፓ መካከል የንግድ መስመር የተከፈተ ሲሆን ይህንንም ያስጀመሩት የዕጣን ነጋዴዎች እንደሆኑ ይታመናል።

ዛሬ ያሉ በርካታ ሃይማኖቶችም በበዓላቶቻቸውና በሃይማኖታዊ ሥርዓቶቻቸው ወቅት ዕጣን ያጤሳሉ። ከዚህም በላይ ቁጥራቸው እየጨመረ የመጣ ሰዎች ለአስደሳች መዓዛው ሲሉ ቤታቸው ውስጥ ዕጣን ያጤሳሉ። ክርስቲያኖች ዕጣን ስለማጤስ ሊኖራቸው የሚገባው አመለካከት ምንድን ነው? ከአምልኮ ጋር በተያያዘ ለአምላክ ቢቀርብ ተቀባይነት ይኖረዋልን? መጽሐፍ ቅዱስ በዚህ ጉዳይ ላይ የሚሰጠውን ሐሳብ እንመልከት።

“ለእግዚአብሔር የተቀደሰ”

ጥንት በእስራኤላውያን ዘመን በመገናኛው ድንኳን በሚቀርበው የክህነት አገልግሎት ውስጥ ዕጣን ማጤስ ጉልህ ቦታ ነበረው። የማክሊንቶክና ስትሮንግ ሳይክሎፔዲያ እንዲህ ይላል:- “ዕብራውያኑ ዕጣን ማጤስን እንደ ትልቅ የአምልኮ ሥርዓት ወይም ቅዱስ መሥዋዕት አድርገው ይመለከቱት ስለነበረ ይመስላል ለሌላ ለምንም ነገር እንደተጠቀሙበት የሚገልጽ ማስረጃ የለም።”

ይሖዋ አምላክ ከአራት ንጥረ ነገሮች የተዘጋጀ ዕጣን በመገናኛው ድንኳን እንዲጤስ አዝዞ ነበር:- “ጣፋጭ ሽቱ ውሰድ፤ የሚንጠባጠብ ሙጫ፣ በዛጐል ውስጥ የሚገኝ ሽቱ፣ የሚሸትትም ሙጫ፣ ጥሩም ዕጣን ውሰድ፤ የሁሉም መጠን ትክክል ይሁን። በቀማሚ ብልሃት እንደ ተሠራ፣ በጨው የተቀመመ ንጹሕና ቅዱስ ዕጣን አድርገው። ከእርሱም ጥቂት ትወቅጣለህ፣ ታልመውማለህ፤ ከዚያም ወስደህ አንተን በምገናኝበት በመገናኛው ድንኳን ውስጥ በምስክሩ ፊት ታኖረዋለህ።” (ዘጸአት 30:34-36) በኋላ ላይ አይሁዳውያን ረቢዎች በቤተ መቅደሱ ውስጥ የሚጠቀሙበትን ዕጣን ሌሎች ነገሮችም እንደጨመሩበት አንዳንድ ምሁራን ይናገራሉ።

በመገናኛው ድንኳን ውስጥ የሚጤሰው ዕጣን የተቀደሰ በመሆኑ ለይሖዋ ለሚቀርበው አምልኮ ብቻ የሚውል ነበር። እንዲህ በማለት አዝዟቸዋል:- “እንደ እርሱ የተሠራ ዕጣን ለእናንተ አታድርጉ፤ በእናንተ ዘንድም ለእግዚአብሔር የተቀደሰ ይሁን። ሊያሸትተውም እንደ እርሱ የሚያደርግ ሰው ከሕዝቡ ተለይቶ ይጥፋ።” (ዘጸአት 30:37, 38) ካህናቱ ለዚሁ ዓላማ በተዘጋጀ መሠዊያ ላይ በቀን ሁለት ጊዜ ዕጣን ያጤሱ ነበር። (2 ዜና መዋዕል 13:11) በስርየት ቀን ደግሞ ሊቀ ካህኑ በቅድስተ ቅዱሳኑ ውስጥ ያጥናል።​—⁠ዘሌዋውያን 16:12, 13

በአምላክ ዘንድ ተቀባይነት የነበራቸው ሁሉም የዕጣን መሥዋዕቶች አይደሉም። ይሖዋ ካህናት ሳይሆኑ በትዕቢት ተነሳስተው ያጠኑ ሰዎችን ቀጥቷቸዋል። (ዘኍልቍ 16:16-18, 35-40፤ 2 ዜና መዋዕል 26:16-20) አይሁዳውያን በሐሰት አምልኮ እየተካፈሉና እጆቻቸው በደም ተጨማልቀው እያሉ የሚያቀርቡት የዕጣን መሥዋዕት በይሖዋ ዘንድ አስጸያፊ ነበር። ግብዝነታቸው ይሖዋ “ዕጣን በእኔ ዘንድ አስጸያፊ ነው” ብሎ እንዲናገር አድርጎታል። (ኢሳይያስ 1:13, 15) እስራኤላውያን ይሖዋ ለሰጣቸው የአምልኮ ሥርዓት በጣም ግድየለሾች ከመሆናቸው የተነሳ ቤተ መቅደሱን ዘግተው በሌሎች መሠዊያዎች ላይ ያጥኑ ነበር። (2 ዜና መዋዕል 28:24, 25) ከዓመታት በኋላ ደግሞ የተቀደሰውን ዕጣን ለሐሰት አማልክት ለሚቀርበው አስነዋሪ አምልኮ ሳይቀር ይጠቀሙበት ጀመር። እነዚህ ድርጊቶች በይሖዋ ዘንድ እጅግ አስጸያፊ ነበሩ።​—⁠ሕዝቅኤል 16:2, 17, 18

ዕጣን ማጤስና የጥንቶቹ ክርስቲያኖች

ቅዱስ ዕጣን ማጠንን የሚያጠቃልለውን ክህነታዊ ሕግ ጨምሮ የሕጉ ቃል ኪዳን ክርስቶስ በ33 እዘአ አዲሱን ቃል ኪዳን ባቋቋመበት ጊዜ አክትሟል። (ቆላስይስ 2:14) የጥንቶቹ ክርስቲያኖች ለሃይማኖታዊ ዓላማ ዕጣን እንዳጤሱ የሚገልጽ ማስረጃ የለም። ይህንን በተመለከተ የማክሊንቶክና ስትሮንግ ሳይክሎፔዲያ እንዲህ ይላል:- “[የጥንቶቹ ክርስቲያኖች] ዕጣን የማጤስ ልማድ እንዳልነበራቸው የተረጋገጠ ነው። በእርግጥም ዕጣን ማጤስን የአረማዊነት ምልክት አድርገው ይመለከቱት ነበር። . . . ለእምነቱ ያደረ አንድ ሰው አረማዊ አምልኮ በሚከናወንበት መሠዊያ ላይ ዕጣን መጨመሩ አምልኮ እንዳቀረበ አድርጎ ያስቆጥረዋል።”

የጥንቶቹ ክርስቲያኖች ሞት ሊያስከትልባቸው የሚችል ቢሆንም እንኳ የሮማውን ንጉሠ ነገሥት “መለኮታዊነት” መቀበላቸውን ለማሳየት ለዚህ ዓላማ በተዘጋጀው መሠዊያ ላይ ዕጣን ለመጨመር ፈቃደኛ ሳይሆኑ ቀርተዋል። (ሉቃስ 4:8፤ 1 ቆሮንቶስ 10:14, 20) በዚያ ዘመን ዕጣን ለጣዖት አምልኮ ይውል ስለነበር የጥንት ክርስቲያኖች በዕጣን ንግድ ለመሰማራት እንኳ ፈቃደኞች አለመሆናቸው የሚያስገርም አይደለም።

ዕጣን በዛሬው ጊዜ

ዛሬ ዕጣን ለምን ዓላማ ይውላል? በአብዛኞቹ የሕዝበ ክርስትና አብያተ ክርስቲያናት ውስጥ ከበዓላትና ከአምልኮ ሥርዓቶች ጋር በተያያዘ ዕጣን ይቀርባል። እስያ ውስጥ አብዛኞቹ ቤተሰቦች ለአማልክቶቻቸው ክብር ለመስጠት ወይም ሙታንን ከክፉ ለመጠበቅ ሲሉ በቤተ መቅደሶች አሊያም በቤታቸው በሚገኝ መሠዊያ ላይ ያጥናሉ። ከሃይማኖታዊ አገልግሎት ጋር በተያያዘ ዕጣን ቤትን ለማወድ፣ ለመፈወስ፣ ለማንጻትና ጥበቃ ለማስገኘት ተሠርቶበታል።

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ዕጣን ሃይማኖት እንደሌላቸው በሚናገሩ ሰዎችም ዘንድ እንኳ እንደገና ተወዳጅ እየሆነ መጥቷል። አንዳንዶች ለማሰላሰል እንዲረዳቸው በማለት ዕጣን ያጤሳሉ። አንድ መመሪያ መጽሐፍ ከሰብዓዊው ዓለም ውጪ ያለውን የመረዳት “ለየት ያለ ንቃት” እና “ኃይል” ለማግኘት ዕጣን ማጤስን ያበረታታል። ይኸው መጽሐፍ በሕይወት ውስጥ ለሚያጋጥሙ ችግሮች መፍትሔ ለማግኘት “ከሰው በላይ ከሆኑ ፍጡራን” ጋር መገናኘትን የሚጨምር ዕጣን የማጤስ የአምልኮ ሥርዓት ጠቃሚ እንደሆነ ይገልጻል። እንደዚህ ዓይነት ልማዶች ለክርስቲያኖች ተገቢ ናቸውን?

ይሖዋ የሐሰት ሃይማኖት ልማዶችን ከንጹሕ አምልኮ ጋር ለመቀላቀል የሚሞክሩ ሰዎችን ክፉኛ ያወግዛል። ሐዋርያው ጳውሎስ የኢሳይያስን ትንቢት ጠቅሶ ክርስቲያኖች የሐሰት ሃይማኖት ከሚያሳድረው ርኩስ ተጽዕኖ መራቅ እንዳለባቸው ተናግሯል። ይሖዋ ያቀረበውን ጥሪ በተመለከተ “ከመካከላቸው ውጡና የተለያችሁ ሁኑ ርኵስንም አትንኩ ይላል፤ ሁሉንም የሚገዛ ጌታ:- እኔም እቀበላችኋለሁ” በማለት ጽፏል። (2 ቆሮንቶስ 6:17፤ ኢሳይያስ 52:11) እውነተኛ ክርስቲያኖች ከሐሰት አምልኮ ወይም ከመናፍስታዊ ድርጊቶች ጋር ንክኪ ካለው ከማንኛውም ነገር ለመራቅ ከፍተኛ ጥንቃቄ ያደርጋሉ።​—⁠ዮሐንስ 4:24

ዕጣን ለሃይማኖታዊ በዓላትና ለመናፍስታዊ ድርጊቶች የሚውል በመሆኑ ዕጣን ማጤስ በአጠቃላይ ስህተት ነው ማለት ነውን? የግድ እንደዚህ ማለት አይደለም። አንድ ሰው ለመልካም መዓዛው ሲል በቤቱ ውስጥ ዕጣን ማጤስ ይፈልግ ይሆናል። (ምሳሌ 27:9) ይህም ቢሆን ግን አንድ ክርስቲያን ዕጣን ለማጤስ ሲያስብ ግምት ውስጥ ማስገባት የሚኖርበት አንዳንድ ነጥቦች ይኖራሉ። በአካባቢህ የሚኖሩ ሰዎች ዕጣን ማጤስን ከሐሰት ሃይማኖት ልማድ ጋር ያዛምዱት ይሆን? ባለህበት ኅብረተሰብ ውስጥ ዕጣን በአብዛኛው ከመናፍስታዊ ድርጊቶች ጋር የተቆራኘ ነው? ወይስ ሃይማኖታዊ ላልሆነ ዓላማ መጠቀምም የተለመደ ነው?

አንድ ግለሰብ ዕጣን ማጤስ ቢፈልግ ሕሊናው የሚነግረውንም ሆነ የሌሎችን ስሜት ግምት ውስጥ ማስገባት ይኖርበታል። (1 ቆሮንቶስ 10:29) ሐዋርያው ጳውሎስ በሮሜ ለነበሩ ክርስቲያኖች የጻፈው መልእክት አሁንም ይሠራል። “ሰላም የሚቆምበትን እርስ በርሳችንም የምንታነጽበትን እንከተል። በመብል ምክንያት የእግዚአብሔርን ሥራ አታፍርስ። ሁሉ ንጹሕ ነው፣ በመጠራጠር የተበላ እንደ ሆነ ግን ለዚያ ሰው ክፉ ነው። ሥጋን አለመብላት ወይንንም አለመጠጣት ወንድምህም የሚሰናከልበትን አለማድረግ መልካም ነው” ሲል ጽፎላቸዋል።​—⁠ሮሜ 14:19-21

“እንደ ዕጣን” የሆነ ጸሎት

እስራኤላውያን ያቀርቡት የነበረው ዕጣን በአምላክ ዘንድ ተሰሚነት ላላቸው ጸሎቶች ተስማሚ ምሳሌ ነው። በመሆኑም መዝሙራዊው ዳዊት “ጸሎቴን በፊትህ እንደ ዕጣን ተቀበልልኝ” በማለት ለይሖዋ ዘምሯል።​—⁠መዝሙር 141:2

ታማኝ እስራኤላውያን ዕጣን ማጤስን ትርጉም አልባ እንደሆነ ሃይማኖታዊ ሥርዓት አልተመለከቱትም። ዕጣኑን ይሖዋ ባዘዘው መሠረት ለማዘጋጀትና ለማጤስ ከፍተኛ ጥንቃቄ አድርገዋል። ዛሬ ክርስቲያኖች ቃል በቃል ዕጣን ከማጤስ ይልቅ በሰማይ ለሚኖረው አባታችን ጥልቅ የአመስጋኝነት ስሜትና አክብሮት የሚንጸባረቅበት ጸሎት ያቀርባሉ። በቤተ መቅደሱ ያገለግሉ የነበሩት ካህናት ያቀርቡት እንደነበረው ጣፋጭ ሽታ ያለው ዕጣን ሁሉ “የቅኖች ጸሎት . . . በእርሱ ዘንድ የተወደደ” እንደሆነ የአምላክ ቃል ያረጋግጥልናል።​—⁠ምሳሌ 15:8

[በገጽ 29 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

በመገናኛው ድንኳንም ሆነ በቤተ መቅደሱ የሚቀርበው ዕጣን ቅዱስ ነበር

[በገጽ 30 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ክርስቲያኖች ለማሰላሰል እንዲረዳቸው ብለው ዕጣን ማጤሳቸው ተገቢ ነውን?