በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ዝም ብላችሁ ቁሙ፣ የይሖዋንም ማዳን ተመልከቱ!

ዝም ብላችሁ ቁሙ፣ የይሖዋንም ማዳን ተመልከቱ!

ዝም ብላችሁ ቁሙ፣ የይሖዋንም ማዳን ተመልከቱ!

“ተሰለፉ፣ ዝም ብላችሁ ቁሙ፣ የሚሆነውንም የእግዚአብሔርን መድኃኒት እዩ።”—⁠2 ዜና መዋዕል 20:17

1, 2. ‘የማጎጉ ጎግ’ በቅርቡ የሚሰነዝረው ጥቃት ከዓለም አቀፋዊ አሸባሪነት ይበልጥ አደገኛ ነው ሊባል የሚችለው ለምንድን ነው?

 አንዳንዶች ሽብርተኝነትን በዓለም ኅብረተሰብ አልፎ ተርፎም በሥልጣኔ ላይ እንደተሰነዘረ ጥቃት አድርገው ገልጸውታል። እንዲህ ዓይነቱ አደጋ በቸልታ መታለፍ እንደሌለበት አያጠያይቅም። በሌላ በኩል ግን ከዚህ የበለጠ ክብደት ያለው ሆኖም የዓለምን ኅብረተሰብ ትኩረት ያላገኘ ሌላ ጥቃት እያንዣበበ ነው። ይህ ጥቃት ምንድን ነው?

2 በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ በሕዝቅኤል ምዕራፍ 38 ላይ የተነገረለት ‘የማጎጉ ጎግ’ ጥቃት ነው። ይህ ጥቃት ዓለም አቀፋዊ አሸባሪነት ካስከተለው ስጋት የበለጠ አደገኛ ነው ቢባል ማጋነን ይሆናል? በፍጹም! ምክንያቱም የጎግ ጥቃት በሰብዓዊ መንግሥታት ላይ ከሚሰነዘር ጥቃት የከፋ ነው። የጎግ ጥቃት ያነጣጠረው በሰማያዊው የአምላክ መንግሥት ላይ ነው! ይሁን እንጂ ፈጣሪ በኅብረተሰቡ ላይ የሚሰነዘረውን ጥቃት ለመቋቋም የሚያስችል ብቃት ከሌላቸው የሰው ልጆች በተለየ መልኩ የጎግን ጥቃት ለመመከት ሙሉ ብቃት አለው።

በአምላክ መንግሥት ላይ የተሰነዘረ ጥቃት

3. ከ1914 ጀምሮ የዓለም መንግሥታት ምን እንዲያደርጉ ተነግሯቸው ነበር? እነርሱስ ምን ምላሽ ሰጡ?

3 በ1914 የአምላክ መንግሥት በሰማይ ከተቋቋመበት ጊዜ አንስቶ አምላክ በሾመው ንጉሥና በሰይጣን ክፉ ሥርዓት መካከል ውጊያ ሲደረግ ቆይቷል። በዚያን ጊዜ ሰብዓዊ ገዥዎች ራሳቸውን በአምላክ ለተሾመው ንጉሥ እንዲያስገዙ ማሳሰቢያ ተሰጥቷቸው ነበር። እነርሱ ግን “የምድር ነገሥታት ተነሡ፣ አለቆችም በእግዚአብሔርና በመሢሑ ላይ እንዲህ ሲሉ ተማከሩ:- ማሰርያቸውንም እንበጥስ፣ ገመዳቸውንም ከእኛ እንጣል” በሚለው ትንቢት ላይ እንደተነገረው ለመገዛት ፈቃደኛ ሳይሆኑ ቀርተዋል። (መዝሙር 2:1-3) የማጎጉ ጎግ የሚከፍተው ጥቃት በመንግሥቱ አገዛዝ ላይ የሚሰነዘረው ተቃውሞ የመጨረሻው ከፍተኛ ደረጃ ላይ እንደደረሰ ያሳያል።

4, 5. ሰዎች በዓይን ከማይታየው የአምላክ ሰማያዊ መንግሥት ጋር ሊዋጉ የሚችሉት እንዴት ነው?

4 ሰዎች በዓይን ከማይታይ ሰማያዊ መንግሥት ጋር እንዴት ውጊያ ሊገጥሙ ይችላሉ? ብለን እንጠይቅ ይሆናል። መጽሐፍ ቅዱስ እንደሚያሳየው ይህ መንግሥት ‘ከምድር የተዋጁትን መቶ አርባ አራት ሺህ’ ሰዎችና ‘በበግ’ የተመሰለውን ኢየሱስ ክርስቶስን ያቀፈ ነው። (ራእይ 14:1, 3፤ ዮሐንስ 1:29) ይህ መንግሥት በሰማይ የሚገኝ በመሆኑ “አዲስ ሰማይ” ተብሎ የተጠራ ሲሆን ምድራዊ ተገዢዎቹም “አዲስ ምድር” የሚል ስያሜ ማግኘታቸው ምክንያታዊ ነው። (ኢሳይያስ 65:17፤ 2 ጴጥሮስ 3:13) የክርስቶስ ተባባሪ ገዥዎች ከሆኑት 144,000 ሰዎች መካከል አብዛኞቹ ምድራዊ ሕይወታቸውን በታማኝነት ጨርሰዋል። በመሆኑም በሰማይ የሚሰጣቸውን አዲስ የሥራ ምድብ ለመቀበል ብቃት እንዳላቸው አስመስክረዋል።

5 ይሁን እንጂ ጥቂቶቹ አሁንም በምድር ላይ ይገኛሉ። በ2002 በተከበረው የጌታ እራት ላይ ከተገኙት ከ15, 000, 000 የሚበልጡ ተሰብሳቢዎች መካከል ለሰማያዊው ተስፋ እንደተመረጡ የገለጹት 8, 760 የሚያህሉት ብቻ ናቸው። ማንም በምድር ላይ የቀሩትን የመንግሥቱን እጩ አባላት ለማጥቃት ቢነሳ የአምላክን መንግሥት ለማጥቃት እንደሞከረ ይቆጠራል።​—⁠ራእይ 12:17

ንጉሡ ጦርነቱን በድል ያጠናቅቃል

6. በአምላክ ሕዝብ ላይ የሚሰነዘረውን ተቃውሞ ይሖዋና ክርስቶስ እንዴት ይመለከቱታል?

6 ይሖዋ በመንግሥቱ ላይ የሚሰነዘረውን ተቃውሞ እንዴት እንደሚመለከተው ቀጥሎ ያለው ትንቢት ያሳያል:- “በሰማይ የሚኖር እርሱ ይሥቃል፣ ጌታም ይሣለቅባቸዋል። በዚያን ጊዜ በቁጣው ይናገራቸዋል፣ በመዓቱም ያውካቸዋል። እኔ ግን ንጉሤን ሾምሁ በተቀደሰው ተራራዬ በጽዮን ላይ።” (መዝሙር 2:4-6) ክርስቶስ በይሖዋ አመራር ሥር ሆኖ የመጨረሻውን ድል የሚቀዳጅበት ጊዜ ተቃርቧል። (ራእይ 6:2) ይሖዋ የመጨረሻው ድል በተቃረበበት ወቅት በሕዝቡ ላይ የሚሰነዘረውን ተቃውሞ እንዴት ይመለከተዋል? በቀጥታ በእርሱና እርሱ በሾመው ንጉሥ ላይ እንደተሰነዘረ ጥቃት አድርጎ ይመለከተዋል። እንዲያውም ‘የሚነካችሁ የዓይኔን ብሌን የሚነካ ነውና’ በማለት ተናግሯል። (ዘካርያስ 2:8) ኢየሱስ ሰዎች ለቅቡዓን ወንድሞቹ ያደረጉትን ለእርሱ እንዳደረጉት እንዲሁም እነርሱን የነፈጓቸውን እርሱን እንደነፈጉት አድርጎ እንደሚመለከተው በአጽንዖት ተናግሯል።​—⁠ማቴዎስ 25:​40, 45

7. ጎግ በራእይ 7:9 ላይ በተገለጹት “እጅግ ብዙ ሰዎች” ላይ ጥቃት የሚሰነዝረው ለምንድን ነው?

7 ጎግ ቅቡዓን ቀሪዎችን ከልብ በሚደግፉትም ላይ ጥቃት እንደሚሰነዝር የታወቀ ነው። እነዚህ የአምላክ “አዲስ ምድር” እጩ አባላት በቁጥር “እጅግ ብዙ ሰዎች” ሲሆኑ “ከሕዝብና ከነገድ ከወገንም ከቋንቋም” የተውጣጡ መሆናቸው ተገልጿል። (ራእይ 7:9) “ነጭ ልብስም ለብሰው . . . በዙፋኑና በበጉ ፊት” እንደቆሙ ተነግሯል። ይህም የአምላክንና የኢየሱስ ክርስቶስን ሞገስ ማግኘታቸውን ያሳያል። “የዘንባባንም ዝንጣፊዎች በእጆቻቸው ይዘው” በዙፋኑ ላይ በተቀመጠውና “የእግዚአብሔር በግ” ተብሎ በተጠራው በኢየሱስ ክርስቶስ የተወከለውን የጽንፈ ዓለሙን ሉዓላዊ ገዢ ይሖዋን ያወድሳሉ።​—⁠ዮሐንስ 1:29, 36

8. ጎግ ጥቃት ሲሰነዝር ክርስቶስ ምን እርምጃ ይወስዳል? ውጤቱስ ምን ይሆናል?

8 ጎግ ጥቃት ሲሰነዝር በአምላክ የተሾመው ንጉሥ እርምጃ በመውሰድ የአርማጌዶንን ጦርነት ያስጀምራል። (ራእይ 16:14, 16) የይሖዋን ሉዓላዊነት ለመቀበል ፈቃደኛ ያልሆኑት ሰዎች ጥፋት ይደርስባቸዋል። በተቃራኒው ለአምላክ መንግሥት ታማኝ በመሆናቸው ምክንያት መከራ የደረሰባቸው ሁሉ ዘላቂ እፎይታ ያገኛሉ። ሐዋርያው ጳውሎስ ይህን አስመልክቶ እንዲህ በማለት ጽፏል:- “ስለ እርሱ ደግሞ መከራ ለምትቀበሉለት ለእግዚአብሔር መንግሥት የምትበቁ ሆናችሁ ትቈጠሩ ዘንድ፣ ይህ የእግዚአብሔር ቅን ፍርድ ምልክት ነው። ጌታ ኢየሱስ ከሥልጣኑ መላእክት ጋር ከሰማይ በእሳት ነበልባል ሲገለጥ፣ መከራን ለሚያሳዩአችሁ መከራን፣ መከራንም ለምትቀበሉ ከእኛ ጋር ዕረፍትን ብድራት አድርጎ እንዲመልስ በእግዚአብሔር ፊት በእርግጥ ጽድቅ ነውና። እግዚአብሔርን የማያውቁትን፣ ለጌታችንም ለኢየሱስ ክርስቶስ ወንጌል የማይታዘዙትን ይበ​ቀላል።”​—⁠2 ተሰሎንቄ 1:5-8

9, 10. (ሀ) የይሁዳ ነዋሪዎች ብርቱ ጠላት በመጣባቸው ጊዜ ይሖዋ ድል ያጎናጸፋቸው እንዴት ነበር? (ለ) በዛሬው ጊዜ ክርስቲያኖች ምን ማድረጋቸውን መቀጠል አለባቸው?

9 በአርማጌዶን በሚደመደመው በመጪው ታላቅ መከራ ወቅት ክርስቶስ ከክፋት ኃይሎች ጋር ይዋጋል። ከ2, 900 ከሚበልጡ ዓመታት በፊት በሁለቱ ነገድ የይሁዳ መንግሥት ላይ ጥቃት በተሰነዘረበት ወቅት ነዋሪዎቹ መዋጋት እንዳላስፈለጋቸው ሁሉ የክርስቶስ ተከታዮችም መዋጋት አያስፈልጋቸውም። ጦርነቱ የይሖዋ ስለሆነ እርሱ ድል ያጎናጽፋቸዋል። መጽሐፍ ቅዱስ እንዲህ ይላል:- “ይሁዳን ሊወጉ በመጡት በአሞንና በሞዓብ ልጆች በሴይርም ተራራ ሰዎች ላይ እግዚአብሔር ድብቅ ጦርን አመጣባቸው፤ እነርሱም ተመቱ። የአሞንና የሞዓብ ልጆችም በሴይር ተራራ በሚኖሩት ላይ ፈጽመው ይገድሉአቸው ዘንድ፣ ያጠፉአቸውም ዘንድ ተነሥተውባቸው ነበር፤ በሴይርም የሚኖሩትን ካጠፉ በኋላ እያንዳንዱ ባልንጀራውን ለማጥፋት ተረዳዳ። የይሁዳም ሰዎች ወደ ምድረ በዳ ግንብ በመጡ ጊዜ ሕዝቡን አዩ፤ እነሆም፣ በምድሩ ሁሉ ሬሳ ሞልቶ ነበር፣ ያመለጠም ሰው አልነበረም።”​—⁠2 ዜና መዋዕል 20:​22-​24

10 ይሖዋ “እናንተ በዚህ ሰልፍ የምትዋጉ አይደላችሁም” በማለት ያስነገረው ትንቢት በትክክል ፍጻሜውን አግኝቷል። (2 ዜና መዋዕል 20:17) ይህ ታሪክ ኢየሱስ ክርስቶስ ‘ድል ለመንሣት በሚወጣበት’ ጊዜ ክርስቲያኖች ምን ማድረግ እንደሚኖርባቸው የሚያሳይ ግሩም ምሳሌ ይሆናቸዋል። እስከዚያው ድረስ ግን በሥጋዊ ጦር መሣሪያ አይሁን እንጂ በመንፈሳዊ መሣሪያ ክፋትን መዋጋታቸውን ይቀጥላሉ። በዚህ መንገድ ‘ክፉውን በመልካም ያሸንፋሉ።’​—⁠ሮሜ 6:​13፤ 12:​17-​21፤ 13:​12፤ 2 ቆሮንቶስ 10:​3-5

ጎግ ጥቃት የሚሰነዝረው ማንን ተጠቅሞ ነው?

11. (ሀ) ጎግ ጥቃት ለመሰንዘር በእነማን ይጠቀማል? (ለ) በመንፈሳዊ ንቁ ሆኖ መኖር ምን ማድረግን ይጨምራል?

11 የማጎጉ ጎግ የተባለው በ1914 ከሰማይ የተባረረው ሰይጣን ዲያብሎስ ነው። መንፈሳዊ አካል እንደመሆኑ መጠን በቀጥታ ራሱ ጥቃት መሰንዘር ስለማይችል ሰብዓዊ ወኪሎችን እንደ መሣሪያ አድርጎ ይጠቀማል። እነዚህ ሰብዓዊ ወኪሎች እነማን ይሆናሉ? መጽሐፍ ቅዱስ ይህን በሚመለከት ዝርዝር መግለጫ ባይሰጥም የእነዚህን የሰይጣን ወኪሎች ማንነት ለመረዳት የሚያስችል ፍንጭ ይጠቁመናል። የመጽሐፍ ቅዱስ ትንቢቶች ፍጻሜያቸውን እያገኙ ሲሄዱ የእነዚህ ኃይሎች ማንነት ይበልጥ ግልጽ ይሆንልናል። የይሖዋ ሕዝቦች ግምታዊ አስተያየቶችን ከመሰንዘር የሚቆጠቡ ሲሆን የመጽሐፍ ቅዱስ ትንቢት ፍጻሜ የሆኑ ፖለቲካዊና ሃይማኖታዊ ሁኔታዎችን በትኩረት በመከታተል በመንፈሳዊ ነቅተው መኖራቸውን ይቀጥላሉ።

12, 13. ነቢዩ ዳንኤል በአምላክ ሕዝቦች ላይ የሚሰነዘረውን የመጨረሻ ጥቃት በሚመለከት ምን ትንቢት ተናግሯል?

12 ነቢዩ ዳንኤል በአምላክ ሕዝቦች ላይ ስለሚሰነዘረው የመጨረሻ ጥቃት ተጨማሪ መረጃ ሲሰጥ እንዲህ በማለት ጽፏል:- “[የሰሜንም ንጉሥ] ብዙ ሰዎችንም ይገድል ዘንድና ፈጽሞ ያጠፋ ዘንድ በታላቅ ቁጣ ይወጣል። ንጉሣዊ ድንኳኑንም በባሕርና [“በታላቁ ባሕርና፣” NW ] በከበረው በቅዱሱ ተራራ መካከል ይተክላል።”​—⁠ዳንኤል 11:44, 45

13 በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ‘ታላቁ ባሕር’ ተብሎ የተጠራው የሜዲትራኒያን ባሕር ሲሆን ‘ቅዱሱ ተራራ’ የተባለው ደግሞ ይሖዋ “እኔ ግን ንጉሤን ሾምሁ በተቀደሰው ተራራዬ በጽዮን ላይ” በማለት የተናገረለት የጽዮን ተራራ ነው። (መዝሙር 2:6፤ ኢያሱ 1:4) በመሆኑም ‘በታላቁ ባሕርና በቅዱሱ ተራራ’ መካከል ያለው ሥፍራ በመንፈሳዊ ሁኔታ ሲታይ ቅቡዓን ክርስቲያኖች ያሉበትን መንፈሳዊ ብልጽግና ያመለክታል። ቅቡዓን ክርስቲያኖች ከአምላክ ከራቀውና በባሕር ከተመሰለው የሰው ዘር ራሳቸውን የለዩ ሲሆን ከኢየሱስ ክርስቶስ ጋር በሰማያዊው መንግሥት የሚነግሡበትን ጊዜ በጉጉት ይጠባበቃሉ። በግልጽ ለማየት እንደሚቻለው በዳንኤል ትንቢት ፍጻሜ መሠረት የሰሜኑ ንጉሥ ኃይለኛ ጥቃት በሚሰነዝርበት ወቅት የተቀቡት የአምላክ አገልጋዮችና በታማኝነት ከጎናቸው የቆሙት እጅግ ብዙ ሰዎች ዋነኛ ዒላማው ይሆናሉ።​—⁠ኢሳይያስ 57:20፤ ዕብራውያን 12:22፤ ራእይ 14:1

የአምላክ አገልጋዮች ምን ማድረግ አለባቸው?

14. የአምላክ ሕዝቦች ጥቃት ሲሰነዘርባቸው ምን ሦስት ነገሮችን ያደርጋሉ?

14 የአምላክ አገልጋዮች የጎግ ጥቃት ሲሰነዘርባቸው ምን ማድረግ ይጠበቅባቸዋል? በኢዮሣፍጥ ዘመን የነበሩ የአምላክ ሕዝቦች ጥቃት ሲሰነዘርባቸው የወሰዱት እርምጃ በዛሬው ጊዜ ለሚገኙት የአምላክ አገልጋዮች ምሳሌ ይሆናል። የይሁዳ ሕዝብ ሦስት ነገሮችን እንዲያደርጉ ታዝዘው እንደነበር ልብ በል። (1) ተሰለፉ፣ (2) ዝም ብላችሁ ቁሙ እንዲሁም (3) የይሖዋን ማዳን እዩ የሚል ትእዛዝ ተሰጥቷቸው ነበር። በዛሬው ጊዜ የአምላክ ሕዝቦች በእነዚህ ቃላት መሠረት ምን እንዲያደርጉ ይጠበቅባቸዋል?​—⁠2 ዜና መዋዕል 20:17

15. መሰለፍ ምን ማድረግን የሚጠይቅ ነው?

15 ተሰለፉ:- የአምላክ ሕዝቦች ከአቋማቸው ፍንክች ሳይሉ የአምላክን መንግሥት መደገፋቸውን ይቀጥላሉ። ክርስቲያናዊ የገለልተኝነት አቋማቸውንም ይጠብቃሉ። ‘የተደላደሉና የማይነቃነቁ’ ሆነው ይሖዋን በታማኝነት የሚያገለግሉ ከመሆኑም በላይ ስለ ፍቅራዊ ደግነቱ እርሱን በሕዝብ ፊት ማወደሳቸውን ይቀጥላሉ። (1 ቆሮንቶስ 15:58፤ መዝሙር 118:28, 29) አሁንም ሆነ ወደፊት የሚያጋጥማቸው የትኛውም ተጽዕኖ በአምላክ ፊት ሞገስ ያስገኘላቸውን ይህን አቋማቸውን እንዲያላሉ ሊያደርጋቸው አይችልም።

16. የይሖዋ አገልጋዮች ዝም ብለው የሚቆሙት እንዴት ነው?

16 ዝም ብላችሁ ቁሙ:- የይሖዋ አገልጋዮች ራሳቸውን ለማዳን ከመሞከር ይልቅ ሙሉ ትምክህታቸውን በይሖዋ ላይ ያደርጋሉ። ከዚህ ዓለም ውጥንቅጥ አገልጋዮቹን ማዳን የሚችለው እርሱ ብቻ ሲሆን እንዲህ ለማድረግም ቃል ገብቷል። (ኢሳይያስ 43:10, 11፤ 54:15፤ ሰቆቃወ ኤርምያስ 3:26) በይሖዋ መታመን ዓላማውን ከግብ ለማድረስ ከአንድ መቶ ዓመት በላይ ሲጠቀምበት በኖረው ምድራዊ ድርጅት መታመንንም ይጨምራል። ከመቼውም ጊዜ በበለጠ እውነተኛ ክርስቲያኖች ይሖዋና በመግዛት ላይ የሚገኘው ኢየሱስ ክርስቶስ አመራር እንዲሰጡ በሾሟቸው የአምልኮ አጋሮቻቸው ላይ ትምክህታቸውን መጣል አለባቸው። እነዚህ የታመኑ ወንዶች ለአምላክ ሕዝቦች አመራር ይሰጣሉ። የእነርሱን አመራር ቸል ማለት ጥፋት ያስ​ከትላል።⁠—⁠ማቴዎስ 24:45-47፤ ዕብራውያን 13:7, 17

17. የአምላክ ታማኝ አገልጋዮች የይሖዋን ማዳን ለማየት የሚታደሉት ለምንድን ነው?

17 የይሖዋን ማዳን እዩ:- ክርስቲያናዊ የአቋም ጽናታቸውን የሚጠብቁና ከሚመጣው ጥፋት እንዲታደጋቸው በይሖዋ የሚታመኑ ሁሉ ማዳኑን ለመመልከት አጋጣሚ ያገኛሉ። መጨረሻው እስኪመጣ ድረስ ግን አቅማቸው የሚፈቅድላቸውን ያህል የይሖዋ የፍርድ ቀን መቅረቡን ለሌሎች ያስታውቃሉ። ይሖዋ እውነተኛው አምላክ መሆኑንና በምድር ላይ ታማኝ አገልጋዮች እንዳሉት ፍጥረት ሁሉ ማወቅ ይኖርበታል። ከዚያ በኋላ በይሖዋ የመግዛት መብት ላይ ማንም ጥያቄ አያነሳም።​—⁠ሕዝቅኤል 33:33፤ 36:23

18, 19. (ሀ) በዘጸአት ምዕራፍ 15 ላይ የሚገኘው የድል መዝሙር ከጎግ ጥቃት በሕይወት የሚተርፉት ሰዎች የሚሰማቸውን ስሜት የሚገልጸው እንዴት ነው? (ለ) የአምላክ ሕዝቦች በአሁኑ ወቅት ምን ማድረግ ይኖርባቸዋል?

18 የጥንት እስራኤላውያን ቀይ ባሕርን ከተሻገሩ በኋላ እንዳደረጉት የአምላክ ሕዝቦችም በአዲስ መንፈስ ወደ አዲሲቱ ዓለም ሲገቡ የድል መዝሙር የሚዘምሩበትን ጊዜ በጉጉት ይጠባበቃሉ። ይሖዋ በግለሰብም ሆነ በቡድን ደረጃ ላደረገላቸው ጥበቃ አመስጋኝ በመሆን ከዘመናት በፊት የተዘመሩትን የሚከተሉትን ቃላት ያስተጋባሉ:- “በክብር ከፍ ከፍ ብሎአልና ለእግዚአብሔር እዘምራለሁ፤ . . . እግዚአብሔር ተዋጊ ነው፣ ስሙ እግዚአብሔር ነው፣ . . . አቤቱ፣ ቀኝህ ጠላቱን አደቀቀ። በክብርህም ብዛት የተነሡብህን አጠፋህ፤ ቁጣህን ሰደድህ፣ እንደ ገለባም በላቸው። . . . በቸርነትህ የተቤዠሃቸውን ሕዝብህን መራህ፤ በኃይልህ ወደ ቅዱስ ማደሪያህ አገባሃቸው። . . . አቤቱ፣ አንተ ታስገባቸዋለህ፣ በርስትህ ተራራም ትተክላቸዋለህ፣ አቤቱ፣ ለማደሪያህ ባደረግኸው ስፍራ፣ አቤቱ፣ እጆችህ ባዘጋጁት መቅደስ። እግዚአብሔር ለዘላለሙ እስከ ፍጻሜ ይነግሣል።”​—⁠ዘጸአት 15:1-19

19 የዘላለም ሕይወት ተስፋችን እውን የሚሆንበት ጊዜ እየቀረበ የሄደበት ይህ ያለንበት ወቅት የአምላክ አገልጋዮች ለይሖዋ ያደሩ መሆናቸውን የሚያሳዩበትና እርሱን ዘላለማዊ ንጉሣቸው አድርገው ለማገልገል ያላቸውን ቁርጠኝነት የሚያድሱበት ግሩም አጋጣሚ ነው!​—⁠1 ዜና መዋዕል 29:11-13

ልታብራራ ትችላለህ?

• ጎግ በቅቡዓኑና በሌሎች በጎች ላይ ጥቃት የሚሰነዝረው ለምንድን ነው?

• የይሖዋ ሕዝቦች የሚሰለፉት እንዴት ነው?

• ዝም ብሎ መቆም ምን ማድረግን ይጠይቃል?

• የአምላክ ሕዝቦች የይሖዋን ማዳን መመልከት የሚችሉት ምን ሲያደርጉ ነው?

[የአንቀጾቹ ጥያቄዎች]

[በገጽ 18 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ኢዮሳፍጥና ሕዝቡ ምንም መዋጋት ሳያስፈልጋቸው ይሖዋ ድል አጎናጽፏቸዋል

[በገጽ 20 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ቅቡዓኑና ሌሎች በጎች በአንድነት የይሖዋን ሉዓላዊነት ከፍ ከፍ ያደርጋሉ

[በገጽ 22 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

የጥንት እስራኤላውያን እንዳደረጉት የአምላክ ሕዝቦችም በቅርቡ የድል መዝሙር ይዘምራሉ