በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የአንባብያን ጥያቄዎች

የአንባብያን ጥያቄዎች

የአንባብያን ጥያቄዎች

በበሽታ እየተሰቃየ ያለ ወይም በጣም ያረጀ የቤት እንስሳን መግደል ስህተት ነውን?

ብዙ ሰዎች ለእንስሳት ፍቅር ያላቸው ከመሆኑም በላይ ከእነርሱ ጋር መሆን ያስደስታቸዋል። እንዲሁም አንዳንዶች ቤት ውስጥ የሚያሳድጓቸው ለማዳ እንስሳት እንደ ጓደኛ ሆነውላቸዋል። ለምሳሌ ያህል ውሾች ባለቤቶቻቸውን ሙሉ በሙሉ እንደሚታዘዙና እንደሚወዱ ይታወቃል። በመሆኑም ሰዎች በተለይ ለረጅም ጊዜ አብሯቸው ለኖረ የቤት እንስሳ የጠበቀ ፍቅር ቢኖራቸው የሚያስገርም አይሆንም።

ይሁን እንጂ የአብዛኞቹ የቤት እንስሳት የሕይወት ዘመን ያን ያህል ረጅም አይደለም። ውሻና ድመት እንደ ዝርያቸው ዓይነት ከ10 እስከ 15 ዓመት ገደማ ሊኖሩ ይችላሉ። የቤት እንስሳት ሲያረጁ በሽታ ሊያጠቃቸውና አካለ ስንኩል ሊሆኑ ይችላሉ። ይህም እንስሶቹ ከማርጀታቸው በፊት እንደፈለጉ ይንቀሳቀሱ የነበሩበትን ጊዜ ለሚያስታውሱት ባለቤቶቻቸው እጅግ አሳዛኝ ሊሆንባቸው ይችላል። እንደዚህ ያሉትን እንስሳት ከሥቃያቸው እንዲገላገሉ መግደል ስህተት ነው?

አንድ ክርስቲያን እንስሳትን የሚይዝበት መንገድ ከአምላክ ፈቃድ ጋር የተስማማ እንዲሆን ይፈልጋል። መጽሐፍ ቅዱስ “ጻድቅ ሰው ለእንስሳው ነፍስ ይራራል” ስለሚል እንስሳትን ማሰቃየት የአምላክን ፈቃድ እንደሚቃረን ምንም ጥያቄ የለውም። (ምሳሌ 12:​10) ይህ ማለት ግን አምላክ እንስሳትንና ሰዎችን በእኩል ዓይን ይመለከታቸዋል ማለት አይደለም። አምላክ ሰዎችን ሲፈጥር በእነርሱና በእንስሳት መካከል የማያሻማ ልዩነት መኖሩን አሳይቷል። ለምሳሌ ያህል ለሰዎች የዘላለም ሕይወት ተስፋ የሰጣቸው ሲሆን ለእንስሳት ግን እንደዚህ አላደረገም። (ሮሜ 6:​23፤ 2 ጴጥሮስ 2:​12) ፈጣሪ እንደመሆኑ መጠን በሰዎችና በእንስሳት መካከል ሊኖር ስለሚገባው ተገቢ ግንኙነት የመወሰን መብት አለው።

ዘፍጥረት 1:​28 በሁለቱ መካከል ያለውን ግንኙነት ይገልጽልናል። አምላክ ለመጀመሪያዎቹ ባልና ሚስት እንዲህ ብሏቸዋል:- “የባሕርን ዓሦችና የሰማይን ወፎች በምድር ላይ የሚንቀሳቀሱትንም ሁሉ ግዙአቸው።” በተመሳሳይ መዝሙር 8:​6-8 አምላክ ለሰው የሰጠውን ሥልጣን ሲገልጽ እንዲህ ይላል:- “ሁሉን ከእግሮቹ በታች አስገዛህለት፣ በጎችንም ላሞችንም ሁሉ፣ ደግሞም የምድረ በዳውን እንስሶች፣ የሰማይንም ወፎች የባሕርንም ዓሦች፣ በባሕር መንገድ የሚሄደውንም ሁሉ።”

ሰዎች እንስሳትን አግባብ ባለው መንገድ ሊጠቀሙባቸውና ለምግብነት ሊያርዷቸው እንደሚችሉ አምላክ በግልጽ ተናግሯል። ለምሳሌ ያህል ቆዳቸው ለልብስነት ሊያገለግል ይችላል። ከዚህም በላይ አምላክ ከኖኅ የጥፋት ውኃ በኋላ ሰዎች የእንስሳትን ሥጋ እንዲበሉ ፈቅዶላቸዋል። ይህም መጀመሪያ ላይ ለምግብነት በተሰጧቸው ዕፅዋት ላይ ተጨማሪ ምግብ ይሆናቸዋል ማለት ነው።​—⁠ዘፍጥረት 3:​21፤ 4:​4፤ 9:​3

እንዲህ ሲባል ግን ሰዎች እንስሳትን በስፖርት ስም እንዳሻቸው መግደል ይችላሉ ማለት አይደለም። መጽሐፍ ቅዱስ በዘፍጥረት 10:​9 ላይ ናምሩድ “ኃያል አዳኝ” እንደነበር ይገልጻል። ይሁን እንጂ እዚያው ጥቅስ ላይ ይህ አድራጎቱ ‘የይሖዋ ተቃዋሚ’ [NW ] እንዳደረገው ይናገራል።

በመሆኑም የሰው ልጅ እንስሳትን የመግዛት ሥልጣን ቢሰጠውም ይህን ሥልጣን አላግባብ ሊጠቀምበት አይገባም። በአምላክ ቃል ውስጥ ከሚገኘው መሠረታዊ ሥርዓት ጋር በሚስማማ መንገድ ሊሠራበት ይገባል። ይህም አንድ የቤት እንስሳ በጣም በማርጀቱ፣ በደረሰበት ከባድ ጉዳት ወይም ለሞት በሚዳርግ በሽታ ሲሰቃይ ዝም ብሎ አለማየትን ሊጨምር ይችላል። እንዲህ ዓይነት ሁኔታ ሲያጋጥም ምን መደረግ እንዳለበት የመወሰኑ ኃላፊነት ለእያንዳንዱ ክርስቲያን የተተወ ነው። ግለሰቡ አንድ የቤት እንስሳ የመዳን ተስፋ እስከሌለው ድረስ እየተሰቃየ ከሚኖር ቢያርፍ እንደሚሻል ከተሰማው እንዲገደል ይወስን ይሆናል።