በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ኢየሱስ በምድር ላይ እንደኖረ የሚያረጋግጥ የአርኪኦሎጂ ማስረጃ?

ኢየሱስ በምድር ላይ እንደኖረ የሚያረጋግጥ የአርኪኦሎጂ ማስረጃ?

ኢየሱስ በምድር ላይ እንደኖረ የሚያረጋግጥ የአርኪኦሎጂ ማስረጃ?

“ኢየሱስ በምድር ላይ እንደኖረ የሚያረጋግጥ በድንጋይ ላይ የተጻፈ ማስረጃ።” ይህን የተናገረው ቢብሊካል አርኪኦሎጂ ሪቪው (ኅዳር/ታኅሣሥ 2002) የተባለው መጽሔት ሲሆን በሽፋኑም ላይ በእስራኤል አገር የተገኘ ከኖራ ድንጋይ የተሠራ አንድ የአፅም ማስቀመጫ ሣጥን ፎቶ ግራፍ ይታያል። ከ1 ከዘአበ እስከ 70 እዘአ በነበሩት ዓመታት አይሁዳውያን የሞተ ሰው አፅም በሣጥን ውስጥ የማስቀመጥ ልማድ ነበራቸው። ይህን ሣጥን ከሌሎች ልዩ ያደረገው በአንድ ጎኑ ላይ ተጽፎ የሚገኘው የአረማይክ ጽሑፍ ነው። ምሁራን ጽሑፉ “የኢየሱስ ወንድም የዮሴፍ ልጅ ያዕቆብ” የሚል እንደሆነ ይናገራሉ።

መጽሐፍ ቅዱስ የናዝሬቱ ኢየሱስ ያዕቆብ የሚባል ወንድም እንደነበረው ይናገራል። ያዕቆብ ደግሞ ዮሴፍ ከማርያም የወለደው እንደሆነ ግልጽ ነው። ኢየሱስ ባደገበት ከተማ ሲያስተምር በትምህርቱ የተገረሙት አድማጮቹ “ይህ የጸራቢ ልጅ አይደለምን? እናቱስ ማርያም ትባል የለምን? ወንድሞቹስ ያዕቆብና ዮሳ ስምዖንም ይሁዳም አይደሉምን? እኅቶቹስ ሁሉ በእኛ ዘንድ ያሉ አይደሉምን?” ሲሉ ጠይቀዋል​—⁠ማቴዎስ 13:54-56፤ ሉቃስ 4:22፤ ዮሐንስ 6:42

በሣጥኑ ላይ የሰፈረው ጽሑፍ ሰዎቹ ስለ ናዝሬቱ ኢየሱስ ከሰጡት መግለጫ ጋር ይስማማል። በሣጥኑ ላይ የተጠቀሰው ያዕቆብ የኢየሱስ ክርስቶስን ግማሽ ወንድም የሚያመለክት ከሆነ የጥንታዊ ቅርሶች ተመራማሪና ቢብሊካል አርኪኦሎጂ ሪቪው በተባለው መጽሔት ላይ የወጣውን ከላይ ያለውን ሐሳብ የጻፉት አንድሬ ለሜር እንዳሉት “ይህ ከመጽሐፍ ቅዱስ ውጭ ከሚገኙት ስለ ኢየሱስ ከሚናገሩ ማስረጃዎች ሁሉ ጥንታዊው ይሆናል ማለት ነው።” የመጽሔቱ አዘጋጅ የሆኑት ኸርሼል ሻንክስ ይህ ሣጥን “እስከ ዛሬ ከኖሩት ሁሉ የሚበልጠው ታላቅ ሰው በምድር ላይ ስለነበረበት ጊዜ የሚገልጽ ተጨባጭ ማስረጃ ነው” በማለት ተናግረዋል።

ሆኖም በሣጥኑ ላይ የሚገኙት ሦስቱም ስሞች በመጀመሪያው መቶ ዘመን የተለመዱ ስሞች ነበሩ። ስለሆነም ከኢየሱስ ክርስቶስ ቤተሰብ ሌላ ያዕቆብ፣ ዮሴፍ እና ኢየሱስ በሚሉት ስሞች የሚጠሩ ሰዎች ያሉት ቤተሰብ ሊኖር እንደሚችል ግልጽ ነው። ለሜር “ከ70 እዘአ በፊት በኢየሩሳሌም በነበሩት ሁለት ትውልዶች ውስጥ . . . ‘የኢየሱስ ወንድም የዮሴፍ ልጅ ያዕቆብ’ የሚባሉ 20 የሚያህሉ ሰዎች ሊኖሩ እንደሚችሉ” ግምታዊ አስተያየታቸውን ሰጥተዋል። የሆነ ሆኖ በሣጥኑ ላይ የተጠቀሰው ያዕቆብ የሚያመለክተው 90 በመቶ የኢየሱስን ግምሽ ወንድም ያዕቆብን ሊሆን እንደሚችል ይሰማቸዋል።

አንዳንዶች በሣጥኑ ላይ የተጠቀሰው ያዕቆብ የኢየሱስ ክርስቶስ ግማሽ ወንድም ነው ብለው እንዲያምኑ የሚያደርጋቸው ሌላም ተጨማሪ ማስረጃ አለ። እንዲህ ባለው የአፅም ማስቀመጫ ሣጥን ላይ የሟችን አባት ስም መጻፍ የተለመደ ቢሆንም የወንድሙን ስም መጥቀስ ግን እምብዛም ያልተለመደ ነው። ስለሆነም አንዳንድ ምሁራን እዚህ ላይ የተጠቀሰው ኢየሱስ አንድ የታወቀ ሰው መሆን አለበት የሚል እምነት ያሳደረባቸው ሲሆን እርሱም የክርስትና መሥራች የሆነው ኢየሱስ ክርስቶስ ነው ብለው እንዲያስቡ አድርጓቸዋል።

በእርግጥ ሣጥኑ ትክክለኛው ነውን?

በጥንት ዘመን በዋሻ ውስጥ የተቀበረ በድን ከበሰበሰ በኋላ አፅሙን ሰብስቦ በሣጥን ውስጥ ማስቀመጥ የተለመደ ነበር። በኢየሩሳሌም አካባቢ ከሚገኙ የመቃብር ቦታዎች አፅም የተቀመጠባቸው ሣጥኖች ይሰረቁ ነበር። የያዕቆብ ስም የተጻፈበት ሣጥን የተገኘው የከርሰ ምድር ቁፋሮ ከሚካሄድበት ቦታ ሳይሆን በቅርሶች መሸጫ መደብር ውስጥ ነው። የሣጥኑ ባለቤት በ1970ዎቹ ዓመታት ሣጥኑን በተወሰነ ብር እንደገዛው ተናግሯል። በዚህም የተነሳ ሣጥኑ ከየት እንደተገኘ የሚታወቅ ነገር የለም። “አንድ ቅርስ ከየት እንደተገኘና ላለፉት 2, 000 ዓመታት የት እንደነበረ ማወቅ ካልተቻለ በዕቃውና በዕቃው ላይ በተጠቀሱት ሰዎች መካከል ስላለው ዝምድና እንዲህ ነው ብሎ በእርግጠኝነት መናገር አይቻልም” ሲሉ ኒው ዮርክ የሚገኘው የባርድ ኮሌጅ ባልደረባ የሆኑት ፕሮፌሰር ብሩስ ቺልተን አስተያየታቸውን ሰጥተዋል።

ሣጥኑ በአርኪኦሎጂ ተመራማሪዎች በቁፋሮ የተገኘ ስላልሆነ አንድሬ ለሜር ሣጥኑን የሥነ ምድር ጥናት ወደሚካሄድበት ማዕከል ላኩት። ጥናቱን ያካሄዱት ሰዎችም ሣጥኑ በአንደኛው ወይም በሁለተኛው መቶ ዘመን እዘአ ከኖራ ድንጋይ የተሠራ መሆኑን አረጋገጡ። ሣጥኑ “በዘመናዊ መሣሪያ እንደተሠራ የሚያሳይ ምንም ዓይነት ማስረጃ እንዳላገኙ” ገልጸዋል። ዘ ኒው ዮርክ ታይምስ መጽሔት ቃለ መጠይቅ ያደረገላቸው የመጽሐፍ ቅዱስ ምሁራን “ካሉት መረጃዎችና ሁኔታዎች አንፃር በሣጥኑ ላይ የተጠቀሰው ያዕቆብ ከኢየሱስ ጋር ግንኙነት አለው ብሎ ለማመን የሚያበቃ ቢሆንም በእርግጠኝነት ለመናገር ግን አያስደፍርም” በማለት አስተያየታቸውን ሰጥተዋል።

ታይም መጽሔት “ኢየሱስ በምድር ላይ እንደኖረ የሚጠራጠሩ ምሁራን በአሁኑ ጊዜ አሉ ለማለት ያስቸግራል” ሲል አስተያየቱን ሰጥቷል። ይሁን እንጂ ብዙዎቹ ምሁራን ከመጽሐፍ ቅዱስ በተጨማሪ ኢየሱስ በምድር ላይ እንደኖረ የሚያረጋግጡ ሌሎች ማስረጃዎች መኖር አለባቸው ብለው ያስባሉ። አንድ ሰው በኢየሱስ ክርስቶስ እንዲያምን የግድ የአርኪኦሎጂ መረጃ ማግኘት ይኖርበታልን? “እስከ ዛሬ ከኖሩት ሁሉ የሚበልጠው ታላቅ ሰው” በእርግጥ በምድር ላይ እንደኖረ የሚያረጋግጥ ምን ማስረጃ አለ?

[በገጽ 3 ላይ የሚገኝ የሥዕል ምንጭ]

Left, James Ossuary: AFP PHOTO/J.P. Moczulski; right, inscription: AFP PHOTO/HO