በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ኢየሱስ ክርስቶስ በምድር ላይ እንደኖረ የሚያረጋግጥ ማስረጃ

ኢየሱስ ክርስቶስ በምድር ላይ እንደኖረ የሚያረጋግጥ ማስረጃ

ኢየሱስ ክርስቶስ በምድር ላይ እንደኖረ የሚያረጋግጥ ማስረጃ

አልበርት አንስታይን የሚባል ሰው እንደነበረ ታምናለህን? እንዴታ ብለህ ትመልስ ይሆናል። ግን ለምን? አብዛኞቹ ሰዎች አልበርት አንስታይንን እንዳላዩት ግልጽ ነው። ሆኖም ስለሠራቸው ነገሮች የሚገልጹት ተዓማኒነት ያላቸው ዘገባዎች በአንድ ወቅት የነበረ ሰው መሆኑን ይመሠክራሉ። ሳይንሳዊ ግኝቶቹም ይህንኑ ሳንጠራጠር እንድንቀበል ያደርጉናል። ለምሳሌ ያህል ብዙዎች በኑክሌር ኃይል አማካኝነት ከሚመነጭ የኤሌክትሪክ ኃይል ይጠቀማሉ። ይህንንም የኑክሌር ኃይል ወደ ኤሌክትሪክ ኃይል መለወጥ የተቻለው አልበርት አንስታይን ያገኘውን የሒሳብ ቀመር መሠረት በማድረግ ነው።

አልበርት አንስታይን በምድር ላይ ኖሯል እንድንል የሚያደርገን ይህ ምክንያት በታሪክ ውስጥ ትልቅ ቦታ ለሚሰጠው ለኢየሱስ ክርስቶስም ይሠራል። ስለ እርሱ የተጻፉት ጽሑፎችም ሆኑ በሰዎች ሕይወት ላይ ያሳደረው ከፍተኛ ተጽዕኖ ኢየሱስ በምድር ላይ እንደኖረ የሚያረጋግጡ ጠንካራ ማስረጃዎች ናቸው። በቀደመው ርዕስ ላይ የተጠቀሰው በቅርቡ የተገኘው ታሪካዊ ቅርስ የሁላችንንም ትኩረት ሊስብ የሚችል ቢሆንም ኢየሱስ በአንድ ወቅት በምድር ላይ እንደኖረ በማረጋገጥ ረገድ ይህም ሆነ ሌላ ታሪካዊ ቅርስ ወሳኝ ነው ማለት አይደለም። የታሪክ ምሁራን ስለ ኢየሱስና ስለ ተከታዮቹ ከጻፏቸው ዘገባዎች ኢየሱስ በምድር ላይ እንደኖረ የሚገልጹ ማስረጃዎችን ማግኘት እንችላለን።

የታሪክ ምሁራን የሰጡት ምሥክርነት

ለምሳሌ ያህል በመጀመሪያው መቶ ዘመን ይኖር የነበረው ፈሪሳዊው ታሪክ ጸሐፊ ፍላቪዬስ ጆሴፈስ የሰጠውን ምሥክርነት እንመልከት። ጁዊሽ አንቲኩዊቲስ በተባለው መጽሐፉ ውስጥ ስለ ኢየሱስ ክርስቶስ ጠቅሷል። ጆሴፈስ ስለ ኢየሱስ መሢሕነት ያሰፈረውን የመጀመሪያ ዘገባ ትክክለኛነት አንዳንዶች የሚጠራጠሩ ቢሆንም ሁለተኛውን የጆሴፈስ ዘገባ ግን ብዙዎች እንደሚቀበሉት የዮሺቫ ዩኒቨርሲቲ ባልደረባ የሆኑት ፕሮፌሰር ሉዊ ፌልድማን ተናግረዋል። በሁለተኛው ዘገባ ላይ ጆሴፈስ እንዲህ ሲል አስፍሯል:- “[ሊቀ ካህናቱ ሐና] የሳንሄድሪንን ዳኞች ሰብስቦ ያዕቆብ የሚባል ሰው በፊታቸው አቀረበ። ይህ ሰው ክርስቶስ እየተባለ የሚጠራው የኢየሱስ ወንድም ነው።” (ጁዊሽ አንቲኩዊቲስ XX, 200) አዎን፣ ኢየሱስን በጽኑ ይቃወም የነበረው ሃይማኖት አባል የሆነው ፈሪሳዊ “የኢየሱስ ወንድም ያዕቆብ” በወቅቱ የነበረ ሰው መሆኑን አምኖ ጽፏል።

የኢየሱስ ተከታዮች ያደረጉት እንቅስቃሴ ኢየሱስ በአንድ ወቅት በምድር ላይ የነበረ ሰው መሆኑን ያሳያል። ሐዋርያው ጳውሎስ በ59 እዘአ ገደማ ሮም ታስሮ በነበረበት ጊዜ የአይሁድ ታላላቅ ሰዎች “ስለዚህ ወገን በየስፍራው ሁሉ እንዲቃወሙ በእኛ ዘንድ ታውቆአል” በማለት ተናግረውታል። (ሥራ 28:17-22) እነዚህ የአይሁድ ታላላቅ ሰዎች የኢየሱስን ደቀ መዛሙርት “ወገን” ወይም ኑፋቄ ብለው ጠርተዋቸዋል። በየቦታው ስለ እነርሱ ክፉ ወሬ የሚወራ ከሆነ የዓለም ታሪክ ጸሐፊዎች ስለ እነዚህ ሰዎች መዘገባቸው የማይቀር ነው።

በ55 እዘአ ገደማ የተወለደውና ከዓለም ታላላቅ ታሪክ ጸሐፊዎች አንዱ እንደሆነ የሚነገርለት ታሲተስ ባሰፈረው ዜና ታሪክ ላይ ስለ ክርስቲያኖች ጠቅሷል። ኔሮ በ64 እዘአ በሮም የተነሳውን ከባድ ቃጠሎ በክርስቲያኖች ላይ እንዳሳበበ የሚገልጸውን ታሪክ ሲጽፍ እንዲህ ብሏል:- “ኔሮ አደጋውን በብዙኃኑ ዘንድ ክርስቲያን ተብለው በሚጠሩ ሰዎች ላይ ካሳበበ በኋላ ዘግናኝ የሆነ ቅጣት ፈጸመባቸው። ክርስቲያን ለሚለው ስም መገኛ የሆነው ክራይስቱስ በጢባርዮስ የንግሥና ዘመን ከአስተዳዳሪዎቻችን አንዱ በነበረው በጴንጤናዊው ጲላጦስ እጅ ከፍተኛ ቅጣት ተቀብሏል።” ይህ ዝርዝር ዘገባ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ከሚገኘው ስለ ኢየሱስ ከሚናገረው ታሪክ ጋር ይስማማል።

ስለ ኢየሱስ ተከታዮች የጻፈው ሌላው ሰው ደግሞ የቢታንያ ገዥ የነበረው ታናሹ ፕሊኒ ነው። ፕሊኒ በ111 እዘአ ክርስቲያኖችን በተመለከተ ምን ማድረግ እንዳለበት መመሪያ ለመጠየቅ ወደ ንጉሥ ትራጃን ደብዳቤ ጽፎ ነበር። ክርስቲያን ናችሁ ተብለው በሐሰት የተከሰሱ ሰዎች ለአማልክቶቹ በመጸለይና ለትራጃን ሐውልት በመስገድ ክርስቲያን አለመሆናቸውን እንዲያረጋግጡ ይደረጉ ነበር። በመቀጠል ፕሊኒ “እውነተኛ ክርስቲያን የሆኑትን ግን አስገድዶ ይህን እንዲፈጽሙ ማድረግ አይቻልም ነበር” ብሏል። በእርሱ ላይ ለነበራቸው እምነት ሲሉ ሕይወታቸውን እንኳ ሳይቀር ለመስጠት ፈቃደኞች የሆኑ ሰዎች መኖራቸው ክርስቶስ በእርግጥ በሕይወት የኖረ ሰው መሆኑን የሚያረጋግጥ ማስረጃ ነው።

በመጀመሪያውና በሁለተኛው መቶ ዘመን የነበሩ ታሪክ ጸሐፊዎች ስለ ኢየሱስ ክርስቶስና ስለተከታዮቹ ያሰፈሩትን ዘገባ ጠቅለል አድርጎ ካቀረበ በኋላ ዘ ኢንሳይክሎፒዲያ ብሪታኒካ (2002 እትም) እንዲህ በማለት ይገልጻል:- “በጥንት ዘመን የነበሩ የክርስትና ተቃዋሚዎች እንኳ ኢየሱስ በትክክል በታሪክ የነበረ ሰው መሆኑን ተጠራጥረው እንደማያውቁ እነዚህ ገለልተኛ የታሪክ ማስረጃዎች ያረጋግጣሉ። ሰዎች የኢየሱስን ታሪክ እርግጠኝነት አለበቂ ምክንያት መጠራጠር የጀመሩት በ18ኛው መቶ ዘመን መጨረሻ፣ በ19ኛው መቶ ዘመንና በ20ኛው መቶ ዘመን መጀመሪያ ላይ ነው።”

የኢየሱስ ተከታዮች የሰጡት ምሥክርነት

“አዲስ ኪዳን ስለ ኢየሱስ ሕይወትና ስለገጠመው ሁኔታ እንዲሁም እርሱን በተመለከተ ጥንት ስለተሰጡ የክርስትና ትምህርቶች በቂ መረጃ ይሰጣል” በማለት ዘ ኢንሳይክሎፒዲያ አሜሪካና ይናገራል። መጽሐፍ ቅዱስ ስለ ኢየሱስ ሕልውና የሚሰጠውን መረጃ የማይቀበሉ ሰዎች ሊኖሩ ይችላሉ። ኢየሱስ በምድር ላይ እንደኖረ የሚያረጋግጡ በቅዱሳን ጽሑፎች ላይ የተመሠረቱ ሁለት ጠንካራ ማስረጃዎችን እንመልከት።

አንስታይን የፈለሰፈው ንድፈ ሐሳብ በአንድ ወቅት በሕይወት የኖረ ሰው መሆኑን እንደሚያረጋግጥ ቀደም ብለን ተመልክተናል። በተመሳሳይም ኢየሱስ ያስተማራቸው ትምህርቶች በአንድ ወቅት በምድር ላይ እንደኖረ ያረጋግጡልናል። የታወቀውን የኢየሱስን የተራራ ስብከት እንደ ምሳሌ አድርገን እንውሰድ። (ማቴዎስ ምዕራፍ 5-7) ሐዋርያው ማቴዎስ የተራራውን ስብከት ያዳመጡ ሰዎች የተሰማቸውን ስሜት በተመለከተ እንዲህ ሲል ጽፏል:- “ሕዝቡ በትምህርቱ ተገረሙ፤ . . . እንደ ባለ ሥልጣን ያስተምራቸው ነበርና።” (ማቴዎስ 7:28, 29) ፕሮፌሰር ዲተር ቤትስ ይህ የተራራ ስብከት ባለፉት ዘመናት በሰዎች ላይ ያሳደረውን በጎ ተጽዕኖ በተመለከተ እንዲህ ሲሉ ጽፈዋል:- “የተራራው ስብከት ከአይሁድና ከክርስትና እምነት አልፎ እስከ ምዕራቡ ዓለም ባሕል ድረስ ዘልቆ ገብቷል።” አክለውም ይህ የተራራ ስብከት “በየትኛውም የምድር ክፍል ተቀባይነት አግኝቷል ለማለት ይቻላል” ሲሉ ተናግረዋል።

በዚህ የተራራ ስብከት ላይ የተነገሩትን አጭር ሆኖም ከፍተኛ ቁምነገር ያዘሉና ጥበብ የሞላባቸውን የሚከተሉትን ቃላት እንመልከት። “ቀኝ ጉንጭህን በጥፊ ለሚመታህ ሁሉ ሁለተኛውን ደግሞ አዙርለት።” “ለሰዎች ትታዩ ዘንድ ምጽዋታችሁን በፊታቸው እንዳታደርጉ ተጠንቀቁ።” “ነገ ለራሱ ይጨነቃልና ለነገ አትጨነቁ፤ ለቀኑ ክፋቱ ይበቃዋል።” “ዕንቈቻችሁንም በእሪያዎች ፊት አትጣሉ።” “ለምኑ፣ ይሰጣችሁማል።” “ሰዎች ሊያደርጉላችሁ የምትወዱትን ሁሉ እናንተ ደግሞ እንዲሁ አድርጉላቸው።” “በጠበበው ደጅ ግቡ።” “ከፍሬያቸው ታውቋቸዋላችሁ።” “መልካም ዛፍ ሁሉ መልካም ፍሬ ያደርጋል።”​—⁠ማቴዎስ 5:39፤ 6:1, 34፤ 7:6, 7, 12, 13, 16, 17

እነዚህን አባባሎች ሰምተህ ታውቅ ይሆናል። እንዲያውም በቋንቋህ ውስጥ እንደ ጥቅስ ተደርገው ይነገሩ ይሆናል። ሁሉም ኢየሱስ በተራራ ስብከቱ ከሰጠው ትምህርት የተወሰዱ ናቸው። ይህ የተራራ ስብከት በሰዎች ሕይወትና ባሕል ላይ ይህን ያህል ከፍተኛ ተጽዕኖ ያሳደረ መሆኑ “ታላቁ አስተማሪ” በአንድ ወቅት በምድር ላይ እንደኖረ የሚያረጋግጥ ማስረጃ ነው።

አንድ ሰው ኢየሱስ ክርስቶስ የሚባል አንድ ገጸ ባሕርይ ፈጥሮ ጻፈ እንበል። ይህ ሰው ኢየሱስ አስተምሯቸዋል የሚባሉትን በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሚገኙትን ትምህርቶች ማመንጨት ከቻለ ኢየሱስም ሆነ ትምህርቶቹ በተቻለ መጠን በሁሉም ሰዎች ዘንድ ተቀባይነት እንዲያገኙ ማድረግ አይችልም ነበርን? ሆኖም ሐዋርያው ጳውሎስ “መቼም አይሁድ ምልክትን ይለምናሉ የግሪክ ሰዎችም ጥበብን ይሻሉ፣ እኛ ግን የተሰቀለውን ክርስቶስን እንሰብካለን፤ ይህም ለአይሁድ ማሰናከያ ለአሕዛብም ሞኝነት ነው” በማለት ጽፏል። (1 ቆሮንቶስ 1:22, 23) አይሁድም ሆኑ አሕዛብ ስለ ተሰቀለው ክርስቶስ የሚናገረውን መልእክት አልተቀበሉትም። ሆኖም በመጀመሪያው መቶ ዘመን የነበሩት ክርስቲያኖች የሰበኩት ይህንን ክርስቶስ ነው። ክርስቶስ እንደተሰቀለ ተደርጎ የተገለጸው ለምንድን ነው? ለዚህ ጥያቄ ትክክለኛና አጥጋቢ መልስ ማግኘት የምንችለው ስለ ኢየሱስ ሕይወትና ሞት ትክክለኛ ዘገባ ካሰፈሩት ከክርስቲያን ግሪክኛ ቅዱሳን ጽሑፎች ብቻ ነው።

ኢየሱስ በአንድ ወቅት በእርግጥ የነበረ ሰው መሆኑን የሚያሳምነን ሌላው ማስረጃ ደቀ መዛሙርቱ እርሱ ያስተማራቸውን ትምህርቶች ሳይታክቱ መስበካቸው ነው። ኢየሱስ አገልግሎቱን ከጀመረ ከ30 ዓመት ገደማ በኋላ ሐዋርያው ጳውሎስ ምሥራቹ ‘ከሰማይ በታች ባለው ፍጥረት ሁሉ ዘንድ ተሰብኳል’ ብሎ ሊናገር ችሏል። (ቆላስይስ 1:23) ተቃውሞ እያለም የኢየሱስ ትምህርት በጥንቱ ዓለም በሰፊው ተሰብኮ ነበር። ክርስቲያን በመሆኑ ምክንያት ስደት የደረሰበት ጳውሎስ “ክርስቶስም ካልተነሣ እንግዲያስ ስብከታችን ከንቱ ነው እምነታችሁም ደግሞ ከንቱ ናት” በማለት ጽፏል። (1 ቆሮንቶስ 15:12-17) ትንሣኤ ስላላገኘ ክርስቶስ መስበክ ከንቱ ከሆነ ጭራሽ በሕይወት ስላልነበረ ሰው መስበክ ከዚያ ይበልጥ ከንቱ ይሆናል። ታናሹ ፕሊኒ ካሰፈረው ሪፖርት እንዳየነው የመጀመሪያው መቶ ዘመን ክርስቲያኖች በክርስቶስ ኢየሱስ ላይ ላላቸው እምነት ለመሞት እንኳን ፈቃደኞች ነበሩ። ለክርስቶስ ሲሉ ሕይወታቸውን ለመስጠት ፈቃደኛ የሆኑት የወንጌል ዘገባዎች እንደሚገልጹት በአንድ ወቅት በሕይወት የኖረ ሰው ስለሆነ ነው።

ማስረጃውን ተመልክተሃል

ክርስቲያኖች ለመስበክ በቅድሚያ በኢየሱስ ክርስቶስ ትንሣኤ ማመን ይኖርባቸዋል። በአሁኑ ጊዜ ኢየሱስ እየወሰደ ባለው እርምጃ ምክንያት በምድር ላይ የሚከናወኑትን ሁኔታዎች በመመልከት ትንሣኤ ያገኘውን ኢየሱስን በዓይነ ሕሊናህ መመልከት ትችላለህ።

ኢየሱስ ተሰቅሎ ከመገደሉ በፊት ዳግመኛ ስለሚገኝበት ጊዜ የሚገልጽ ሰፊ ተፈጻሚነት ያለው ትንቢት ተናግሮ ነበር። በተጨማሪም ትንሣኤ እንደሚያገኝና በጠላቶቹ ላይ እርምጃ የሚወስድበት ጊዜ እስኪደርስ ድረስ በአምላክ ቀኝ እንደሚቀመጥ ገልጿል። (መዝሙር 110:1፤ ዮሐንስ 6:62፤ ሥራ 2:34, 35፤ ሮሜ 8:34) ጊዜው ሲደርስ እርምጃ በመውሰድ ሰይጣንንና አጋንንቱን ከሰማይ ያባርራቸዋል።​—⁠ራእይ 12:7-9

ይህ ሁሉ የሚሆነው መቼ ነው? ኢየሱስ ‘መገኘቱንና የዚህን ሥርዓት መደምደሚያ የሚጠቁመውን ምልክት’ ለደቀ መዛሙርቱ ነግሯቸዋል። በማይታይ ሁኔታ መገኘቱን የሚጠቁመው ምልክት ክፍል ከሆኑት ነገሮች መካከል ታላላቅ ጦርነቶች፣ የምግብ እጥረት፣ የምድር መናወጥ፣ የሐሰተኛ ነቢያት መምጣት፣ የዓመፅ መብዛትና ቸነፈር ይገኙበታል። ሰይጣን ከሰማይ መጣሉ ‘በምድር ላይ ወዮታ’ ስለሚያስከትል እንደዚህ የመሳሰሉት አሳዛኝ ሁኔታዎች መከሰታቸው የሚጠበቅ ነው። ዲያብሎስ “ጥቂት ዘመን እንዳለው አውቆ በታላቅ ቊጣ” ወደ ምድር መጥቷል። “ለአሕዛብም ሁሉ ምስክር እንዲሆን ይህ የመ​ንግሥት ወንጌል በዓለም ሁሉ” መሰበኩ ሌላው የምልክቱ ክፍል ነው።​—⁠ማቴዎስ 24:​3-14፤ ራእይ 12:​12፤ ሉቃስ 21:7-19

ኢየሱስ የተናገረው እያንዳንዱ የምልክቱ ክፍል ፍጻሜውን አግኝቷል። አንደኛው የዓለም ጦርነት ከፈነዳበት ከ1914 ጀምሮ ኢየሱስ በማይታይ ሁኔታ መገኘቱን የሚያረጋግጡ የተለያዩ ማስረጃዎችን ተመልክተናል። በአምላክ መንግሥት ላይ ንጉሥ ሆኖ በመግዛት ላይ ሲሆን የእያንዳንዱን ሰው ሕይወት የሚነካ ከፍተኛ ሥራ በመሥራት ላይ ነው። ይህን የምታነበውን መጽሔት ማግኘትህ በአሁኑ ጊዜ የስብከቱ ሥራ እየተሠራ እንዳለ የሚያሳይ አንዱ ማስረጃ ነው።

ኢየሱስ በሰማይ እየገዛ መሆኑ ስላስከተለው ውጤት ይበልጥ ማወቅ ከፈለግህ መጽሐፍ ቅዱስን ማጥናት ይኖርብሃል። ስለ ኢየሱስ መገኘት ተጨማሪ ማብራሪያ ማግኘት የምትፈልግ ከሆነ የይሖዋ ምሥክሮችን ማነጋገር ትችላለህ።

[በገጽ 5 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ጆሴፈስ፣ ታሲተስ እና ታናሹ ፕሊኒ ስለ ኢየሱስ ክርስቶስ እና ስለ ተከታዮቹ ጽፈዋል

[ምንጭ]

ሦስቱም ምስሎች:- © Bettmann/CORBIS

[በገጽ 7 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

የጥንት ክርስቲያኖች ስለ ኢየሱስ ሕልውና ምንም ጥርጣሬ አልነበራቸውም