በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ከአእዋፍ የምናገኘው ትምህርት

ከአእዋፍ የምናገኘው ትምህርት

ከአእዋፍ የምናገኘው ትምህርት

“ወደ ሰማይ ወፎች ተመልከቱ፤ አይዘሩም አያጭዱምም በጎተራም አይከቱም፣ የሰማዩ አባታችሁም ይመግባቸዋል፤ እናንተ ከእነርሱ እጅግ አትበልጡምን?” (ማቴዎስ 6:26) ኢየሱስ ክርስቶስ ይህን የተናገረው በገሊላ ባሕር አጠገብ በሚገኝ ተራራ ላይ ሆኖ በሰጠው በሰፊው በሚታወቀው ስብከቱ ላይ ነው። ስብከቱን ያዳመጡት ተከታዮቹ ብቻ አልነበሩም። ከተለያዩ የአገሪቱ ክፍል የመጡ ወደፊት የእርሱ ደቀ መዛሙርት ሊሆኑ የሚችሉ ብዙ ሰዎች ተገኝተዋል። አብዛኞቹ ድሆች ሲሆኑ ኢየሱስ እንዲፈውሳቸው የታመሙ ሰዎችንም ይዘው መጥተው ነበር።​—⁠ማቴዎስ 4:​23 እስከ 5:​2፤ ሉቃስ 6:​17-20

ኢየሱስ የታመሙትን በሙሉ ከፈወሰ በኋላ ይበልጥ አሳሳቢ ለሆነው ለመንፈሳዊ ፍላጎታቸው ትኩረት ሰጠ። ከትምህርቶቹ መካከል ከላይ የተጠቀሰው ይገኝበታል።

የሰማይ ወፎች ከተፈጠሩ ረጅም ዘመናት ተቆጥረዋል። አንዳንዶቹ የሚመገቡት ነፍሳትን ሲሆን ሌሎቹ ደግሞ ፍራፍሬና ጥራጥሬ ይመገባሉ። አምላክ ለወፎች ይህን የመሰለ የተትረፈረፈ ዝግጅት ካደረገላቸው ሰብዓዊ አገልጋዮቹም የዕለት እንጀራቸውን እንዲያገኙ መርዳት እንደሚችል የታወቀ ነው። ይህን የሚያደርግበት አንደኛው መንገድ ምግብ ለመግዛት የሚያስፈልጋቸውን ገንዘብ ማግኘት የሚችሉበትን ሥራ እንዲያገኙ በመርዳት ነው። ወይም የራሳቸውን ምግብ ማምረት እንዲችሉ በማድረግ ይረዳቸው ይሆናል። ድንገተኛ ችግር በሚከሰትበት ጊዜ ደግሞ አምላክ ደግ የሆኑ ጎረቤቶችንና ወዳጆችን ልባቸውን በማነሳሳት ያላቸውን ምግብ በችግር ላይ ላሉት እንዲያካፍሉ ማድረግ ይችላል።

የወፎችን ሕይወት በጥሞና በመመልከት ሌላም ብዙ ትምህርት ማግኘት እንችላለን። አምላክ ወፎችን ሲፈጥር ጫጩቶቻቸውን የሚያሳድጉበት ጎጆ መሥራት የሚያስችላቸውን አስገራሚ የተፈጥሮ ችሎታ ሰጥቷቸዋል። እስቲ ሁለት የተለያዩ ዓይነት የወፍ ጎጆዎችን እንመልከት። በግራ በኩል ያለው ጨረባ የሚባለው ወፍ ጎጆ ነው። ጎጆው የሚሠራው በዓለት ላይ ወይም በቤት ግድግዳ ላይ ነው። እንዲህ ዓይነት ጎጆዎች ከበላያቸው ሾጠጥ ብሎ የወጣ ድንጋይ ወይም በሥዕሉ ላይ እንደሚታየው የቤት ክዳን ክፈፍ እንደ ጣሪያ ሆኖ ያገለግላቸዋል። የጎጆው ወለል አንድ ላይ በተጣበቁ ትናንሽ ድቡልቡል ጭቃዎች የተሠራ ሲሆን የኩባያ ቅርጽ አለው። ጭቃዎቹን ለመሰብሰብ ወንዱም ሆነ ሴቷ በትጋት የሚሠሩ ሲሆን ጎጆውን ሠርተው ለመጨረስ ከአንድ ወር በላይ ሊፈጅባቸው ይችላል። ከዚያም ውስጠኛውን ክፍል በሣርና በላባ ይሸፍኑታል። ጫጩቶቻቸውን መመገብ የሁለቱም ሥራ ነው። ከታች የሚታየው ደግሞ ቢጫ ወፍ የተባለው ተባዕታይ ወፍ የሚሠራው ጎጆ ነው። ይህ በአፍሪካ ውስጥ የሚገኝ ታታሪ ወፍ ጎጆውን የሚሠራው በሣር ወይም በሌሎች ዕፅዋት ቅጠል ነው። በአንድ ቀን ውስጥ ጎጆውን ሠርቶ የሚጨርስ ሲሆን በተወሰነ ወቅት ውስጥ ደግሞ ከ30 በላይ ጎጆዎች መሥራት ይችላል።

ከዚህ ምን ትምህርት እናገኛለን? አምላክ ለወፎች እንዲህ ዓይነት ችሎታና ጎጆዋቸውን የሚሠሩበት በቂ ቁሳቁስ የሚሰጣቸው ከሆነ ሰብዓዊ አገልጋዮቹ የሚያስፈልጋቸውን መኖሪያ እንዲያገኙ ሊረዳቸው እንደሚችል የተረጋገጠ ነው። ይሁን እንጂ ይሖዋ አምላክ የሚያስፈልጉንን ቁሳዊ ነገሮች እንዲያሟላልን ከፈለግን ማድረግ ያለብን ነገር እንዳለ ኢየሱስ ተናግሯል። “አስቀድማችሁ የእግዚአብሔርን መንግሥት ጽድቁንም ፈልጉ፣ ይህም ሁሉ ይጨመርላችኋል” ብሏል። (ማቴዎስ 6:33) ‘የአምላክን መንግሥት ማስቀደም ምን ማለት ነው?’ ብለህ ትጠይቅ ይሆናል። ይህን መጽሔት የሚያሰራጩት የይሖዋ ምሥክሮች የዚህን ጥያቄ መልስ እንድታገኝ በደስታ ይረዱሃል።