የሰዎችን መልካም ጎን ተመልከቱ
የሰዎችን መልካም ጎን ተመልከቱ
“አምላኬ ሆይ፣ በመልካም አስበኝ።”—ነህምያ 13:31
1. ይሖዋ ለሰዎች ሁሉ ደግነት የሚያሳየው እንዴት ነው?
ለበርካታ ቀናት ደመናማና ጭጋጋማ ሆኖ ከቆየ በኋላ ፀሐይ ስትወጣ ማየት ያስደስታል። በዚህ ጊዜ ሰዎች መንፈሳቸው የሚነቃቃ ሲሆን ደስ የሚል ስሜትም ይሰማቸዋል። በተመሳሳይ ለረጅም ጊዜ የዘለቀ ኃይለኛ የፀሐይና የሙቀት ወቅት አልፎ ዝናብ ሲዘንብ የመንፈስ መታደስና እረፍት ያስገኛል። አፍቃሪው ፈጣሪያችን ይሖዋ ምድር እንዲህ ዓይነት የተለያየ የአየር ጠባይ እንዲኖራት በማድረግ ግሩም ስጦታ ሰጥቶናል። ኢየሱስ “በሰማያት ላለ አባታችሁ ልጆች ትሆኑ ዘንድ ጠላቶቻችሁን ውደዱ፣ . . . ስለሚያሳድዱአችሁም ጸልዩ፤ እርሱ በክፉዎችና በበጎዎች ላይ ፀሐይን ያወጣልና፣ በጻድቃንና በኃጢአተኞችም ላይ ዝናቡን ያዘንባልና” ብሎ ሲያስተምር የአምላክን ለጋስነት ገልጿል። (ማቴዎስ 5:43-45) አዎን፣ ይሖዋ ለሰው ሁሉ ደግነት ያሳያል። አገልጋዮቹ የሌሎችን መልካም ጎን በመመልከት እርሱን ለመኮረጅ መጣር አለባቸው።
2. (ሀ) ይሖዋ ደግነት እንዲያሳይ የሚያደርገው ምንድን ነው? (ለ) ይሖዋ ላሳየን ደግነት የምንሰጠውን ምላሽ በተመለከተ ምን ማወቅ ይፈልጋል?
2 ይሖዋ ደግነት እንዲያሳይ የሚያደርገው ምንድን ነው? አዳም ኃጢአት ላይ ከወደቀበት ጊዜ አንስቶ ይሖዋ የሰዎችን መልካም ጎን ከመመልከት ተቆጥቦ አያውቅም። (መዝሙር 130:3, 4) ታዛዥ የሰው ልጆችን በገነት ውስጥ የማኖር ዓላማ አለው። (ኤፌሶን 1:9, 10) ይገባናል በማንለው ደግነቱ ተስፋ በተሰጠበት ዘር አማካኝነት ከኃጢአትና ከአለፍጽምና ነፃ የምንሆንበት አጋጣሚ ሰጥቶናል። (ዘፍጥረት 3:15፤ ሮሜ 5:12, 15) የቤዛውን ዝግጅት መቀበል ወደ ፍጽምና ደረጃ የምንደርስበትን መንገድ ይከፍትልናል። ይሖዋ እያንዳንዳችንን የሚመለከትበት አንዱ ምክንያት ለልግስናው የምንሰጠውን ምላሽ ለማየት ስለሚፈልግ ነው። (1 ዮሐንስ 3:16) ላሳየን ደግነት ያለንን አድናቆት ለመግለጽ የምናደርገውን ማንኛውንም ነገር ከፍ አድርጎ ይመለከተዋል። ሐዋርያው ጳውሎስ “እግዚአብሔር፣ . . . ያደረጋችሁትን ሥራ ለስሙም ያሳያችሁትን ፍቅር ይረሳ ዘንድ ዓመፀኛ አይደለምና” በማለት ጽፏል።—ዕብራውያን 6:10
3. ለየትኛው ጥያቄ ትኩረት መስጠት ይገባናል?
3 እንግዲያው የሌሎችን መልካም ጎን በመመልከት ረገድ ይሖዋን መምሰል የምንችለው እንዴት ነው? የዚህን ጥያቄ መልስ ከሚከተሉት አራት የሕይወት ዘርፎች አኳያ እንመልከት:- (1) በክርስቲያናዊ አገልግሎት፣ (2) በቤተሰብ፣ (3) በጉባኤ እና (4) ከሌሎች ጋር ባለን ግንኙነት።
በስብከቱና ደቀ መዛሙርት በማድረጉ ሥራ
4. በክርስቲያናዊ አገልግሎት መካፈል የሌሎችን መልካም ጎን ለማየት እንደምንጥር የሚያሳየው እንዴት ነው?
4 ኢየሱስ ስለ ስንዴውና እንክርዳዱ የተናገረውን ምሳሌ እንዲተረጉምላቸው ደቀ መዛሙርቱ ላቀረቡለት ጥያቄ በሰጠው መልስ ላይ “እርሻውም ዓለም ነው” ሲል ተናግሮ ነበር። የክርስቶስ ደቀ መዛሙርት እንደመሆናችን መጠን በአገልግሎት ስንካፈል የዚህን አባባል እውነተኝነት እንገነዘባለን። (ማቴዎስ 13:36-38፤ 28:19, 20) የመስክ አገልግሎታችን ስለ እምነታችን ለሕዝብ የምንሰጠውን ምሥክርነት ይጨምራል። የይሖዋ ምሥክሮች ከቤት ወደ ቤትና በመንገድ ላይ በሚያከናውኑት አገልግሎት በሚገባ የታወቁ መሆናቸው በራሱ የመንግሥቱ መልእክት የሚገባቸውን ሰዎች ሁሉ በመፈለግ ረገድ በትጋት እንደምንሠራ ያረጋግጣል። ደግሞም ኢየሱስ “በምትገቡባትም በማናቸይቱም ከተማ ወይም መንደር፣ በዚያ የሚገባው ማን እንደ ሆነ በጥንቃቄ መርምሩ” የሚል መመሪያ ሰጥቷል።—ማቴዎስ 10:11፤ ሥራ 17:17፤ 20:20
5, 6. ለሰዎች ምሥራቹን ለማካፈል በተደጋጋሚ ወደ ቤታቸው የምንሄደው ለምንድን ነው?
5 ሰዎችን ቤታቸው ሄደን ስናነጋግራቸው ለመልእክታችን የተለያየ ምላሽ ይሰጣሉ። አንዳንድ ጊዜ አንድ የቤተሰብ አባል በትኩረት ሲያዳምጠን ሌላው “አንፈልግም” በማለቱ ውይይቱ የሚቋረጥበት ሁኔታ ያጋጥመናል። አንድ ሰው ተቃዋሚ መሆኑ ወይም ፍላጎት ማጣቱ ሌላው ሰው በሚሰጠው ምላሽ ላይ ተጽዕኖ የሚያሳድር መሆኑ በጣም ያሳዝናል! ታዲያ የሰዎችን መልካም ጎን ለማየት ጥረት ማድረጋችንን መቀጠል የምንችለው እንዴት ነው?
6 በሌላ ጊዜ በዚያ አካባቢ ስናገለግል በድጋሚ ወደዚያ ቤት መሄዳችን በመጀመሪያው ቀን ውይይቱን ያስቆመውን ሰው ለማነጋገር አጋጣሚ ይፈጥርልን ይሆናል። በዚያን ጊዜ የተሰጠንን ምላሽ ማስታወሳችን ከዚያ አንጻር ዝግጅት እንድናደርግ ይረዳናል። ግለሰቡ ውይይቱን ያስቆመው የቤተሰቡ አባል መልእክታችንን እንዳይሰማ መከልከል እንዳለበት ተሰምቶት በቅን ልቦና ሊሆን ይችላል። ምናልባት እንዲህ ዓይነት አመለካከት የያዘው ስለ ስብከት ሥራችን የተሳሳተ ወሬ ሰምቶ ይሆናል። ይሁን እንጂ ይህ እንደገና ወደ እዚያ ቤት ሄደን ምሥራቹን ከመስበክ የማያግደን ከመሆኑም በላይ ግለሰቡ የተሳሳተ አስተሳሰቡን እንዲያርም በጥበብ ጥረት እናደርጋለን። ፍላጎታችን ሁሉም ሰው ስለ አምላክ ትክክለኛ እውቀት እንዲያገኝ መርዳት ነው። እንዲህ ካደረግን ይሖዋም ግለሰቡን ወደ ራሱ ይስበው ይሆናል።—ዮሐንስ 6:44፤ 1 ጢሞቴዎስ 2:4
7. ለሰዎች ምሥራቹን ስንናገር አዎንታዊ አመለካከት እንዲኖረን ሊረዳን የሚችለው ምንድን ነው?
7 ኢየሱስ ለደቀ መዛሙርቱ በሰጣቸው መመሪያ ላይ የቤተሰብ ተቃውሞ እንደሚያጋጥምም ተናግሯል። “ሰውን ከአባቱ፣ ሴት ልጅንም ከእናትዋ፣ ምራትንም ከአማትዋ እለያይ ዘንድ መጥቻለሁና፤ ለሰውም ቤተ ሰዎቹ ጠላቶች ይሆኑበታል” በማለት ነግሯቸዋል። (ማቴዎስ 10:35, 36) ይሁንና የሰዎች ሁኔታና አመለካከት ይለወጣል። ሰዎች በድንገት ሲታመሙ፣ የቅርብ ዘመድ በሞት ሲለያቸው፣ አደጋ ሲደርስባቸው፣ የስሜት መቃወስ እንዲሁም ሌሎች የተለያዩ ነገሮች ሲያጋጥሟቸው ለምሥራቹ የሚሰጡት ምላሽ ሊለወጥ ይችላል። የምናነጋግራቸው ሰዎች መቼም ቢሆን ለምሥራቹ ፍላጎት አያሳዩም የሚል አፍራሽ አመለካከት ካለን የሰዎችን መልካም ጎን ለማየት እየጣርን ነው ለማለት እንችላለን? በሌላ አጋጣሚ ሄደን ለምን ወዳጃዊ በሆነ መንፈስ አናነጋግራቸውም? ከበፊቱ የተለየ ምላሽ ይሰጡን ይሆናል። አንዳንድ ጊዜ የሰዎችን አመለካከት የሚለውጠው የምንናገረው ነገር ብቻ ሳይሆን የምንናገርበት መንገድም ነው። አገልግሎታችንን ከመጀመራችን በፊት ወደ ይሖዋ ከልብ መጸለያችን አዎንታዊ አመለካከት እንዲኖረንና የመንግሥቱን መልእክት ለሁሉም በሚስብ መንገድ ማቅረብ እንድንችል እንደሚረዳን እሙን ነው።—ቆላስይስ 4:6፤ 1 ተሰሎንቄ 5:17
8. ክርስቲያኖች አማኝ ያልሆኑ ዘመዶቻቸው ያሏቸውን መልካም ጎኖች ለማየት መጣራቸው ምን ሊያስገኝ ይችላል?
8 በአንዳንድ ጉባኤዎች ውስጥ የአንድ ቤተሰብ አባላት የሆኑ በርካታ ሰዎች ይሖዋን ሲያገለግሉ ይታያል። አብዛኛውን ጊዜ የሥጋ ዘመዳቸው የሆነ በዕድሜ የጎለመሰ አንድ ክርስቲያን የሚያሳየው ጽናት ወጣቶቹ ለእርሱ የአድናቆትና የአክብሮት ስሜት እንዲያድርባቸው ያደርጋል። ይህ ክርስቲያን ከቤተሰቡ አባላትና ከትዳር ጓደኛው ጋር ያለው ጥሩ ዝምድና የወጣቶቹ የልብ ዝንባሌ እንዲለወጥ ያስችላል። ብዙ ክርስቲያን ሚስቶች ሐዋርያው ጴጥሮስ የሰጠውን ምክር መከተላቸው ባሎቻቸውን “ያለ ትምህርት” ለመለወጥ አስችሏቸዋል።—1 ጴጥሮስ 3:1, 2
በቤተሰብ ውስጥ
9, 10. ያዕቆብም ሆነ ዮሴፍ የቤተሰብ አባሎቻቸውን መልካም ጎን ተመልክተዋል ሊባል የሚችለው እንዴት ነው?
9 በቤተሰብ አባላት መካከል ያለው የቅርብ ትስስር የሌሎችን መልካም ጎን ለመመልከት የምንችልበት ሌላው ዘርፍ ነው። ያዕቆብ ከልጆቹ ጋር ከነበረው ግንኙነት ትምህርት ማግኘት እንችላለን። መጽሐፍ ቅዱስ በዘፍጥረት ምዕራፍ 37 ቁጥር 3 እና 4 ላይ ያዕቆብ ለዮሴፍ የተለየ ፍቅር እንደነበረው ይናገራል። በዚህም የተነሳ የዮሴፍ ወንድሞች ቅንዓት ያደረባቸው ሲሆን ይህም ወንድማቸውን ለመግደል እስከ ማሴር አድርሷቸዋል። ይሁን እንጂ ከጊዜ በኋላ ያዕቆብና ዮሴፍ የነበራቸውን አስተሳሰብ ተመልከት። ሁለቱም የቤተሰባቸው አባላት የነበሯቸውን መልካም ጎኖች ለመመልከት ጥረት አድርገዋል።
10 ዮሴፍ በረሃብ በተጠቃችው በግብፅ ዋና የምግብ አስተዳዳሪ ሆኖ ያገለግል በነበረበት ወቅት ወንድሞቹን በጥሩ ሁኔታ ተቀብሏቸዋል። ማንነቱን በቶሎ ባይገልጥላቸውም የሚያስፈልጋቸው ነገር እንዲሟላላቸውና በዕድሜ ለገፋው አባታቸው ይዘው የሚሄዱት ምግብ እንዲሰጣቸው አድርጓል። አዎን፣ በጥላቻ ተነሳስተው መጥፎ ነገር ቢያደርጉበትም ዮሴፍ መልካም ነገር አድርጎላቸዋል። (ዘፍጥረት 41:53 እስከ 42:8፤ 45:23) በተመሳሳይም ያዕቆብ መሞቻው ተቃርቦ ሳለ ወንዶች ልጆቹን በሙሉ ባርኳቸዋል። መጥፎ ተግባራቸው አንዳንድ መብቶችን ቢያሳጣቸውም እንኳ ከመካከላቸው በምድሪቱ ውስጥ ርስት የተከለከለ የለም። (ዘፍጥረት 49:3-28) ያዕቆብ ለልጆቹ ያሳየው እንዴት ያለ ጽኑ ፍቅር ነው!
11, 12. (ሀ) የቤተሰብ አባሎችን መልካም ጎን የመመልከትን አስፈላጊነት የሚያጎላው የትኛው ትንቢታዊ ምሳሌ ነው? (ለ) ኢየሱስ ስለ አባካኙ ልጅ በተናገረው ምሳሌ ላይ አባትየው ከተወው አርዓያ የምናገኘው ትምህርት ምንድን ነው?
11 ይሖዋ እምነት አጉዳይ ከሆነው የእስራኤል ብሔር ጋር በነበረው ግንኙነት ያሳየው ትዕግሥት የሕዝቡን መልካም ጎኖች እንዴት እንደሚመለከት ተጨማሪ ግንዛቤ ይሰጠናል። ይሖዋ የነቢዩ ሆሴዕን ቤተሰብ እንደ ምሳሌ በመጠቀም ለሕዝቡ የነበረውን ጽኑ ፍቅር ገልጿል። የሆሴዕ ሚስት የነበረችው ጎሜር በተደጋጋሚ ምንዝር ብትፈጽምም ይሖዋ ለሆሴዕ እንዲህ የሚል መመሪያ ሰጠው:- “የእስራኤል ልጆች ወደ ሌሎች አማልክት ቢመለሱና የዘቢብ ጥፍጥፍን ቢወድዱ እንኳ፣ እግዚአብሔር እንደሚወድዳቸው አንተም ውሽማዋን የምትወድደውን አመንዝራይትን ሴት ውደድ።” (ሆሴዕ 3:1) እንዲህ እንዲያደርግ የታዘዘው ለምን ነበር? ይሖዋ ከእርሱ ጎዳና ርቆ ከነበረው ብሔር ውስጥ አንዳንድ ግለሰቦች ለትዕግሥቱ ምላሽ እንደሚሰጡ ያውቅ ነበር። ሆሴዕ እንዲህ በማለት ተናግሯል:- “ከዚያም በኋላ የእስራኤል ልጆች ተመልሰው አምላካቸውን እግዚአብሔርንና ንጉሣቸውን ዳዊትን ይፈልጋሉ፤ በኋለኛውም ዘመን ፈርተው ወደ እግዚአብሔርና ወደ በረከቱ ይመጣሉ።” (ሆሴዕ 3:5) በእርግጥም ይህ በቤተሰባችን ውስጥ ችግሮች ሲያጋጥሙን ልናስታውሰው የሚገባ ጥሩ ምሳሌ ነው። የቤተሰብህን አባላት መልካም ጎን ለመመልከት የማያቋርጥ ጥረት ማድረግህ ቢያንስ በታጋሽነት ረገድ ጥሩ አርዓያ ሊሆን ይችላል።
12 ኢየሱስ ስለ አባካኙ ልጅ የተናገረው ታሪክ ከቤተሰባችን አባላት ጋር በተያያዘ መልካም ጎናቸውን ለማየት እንዴት ጥረት ማድረግ እንደምንችል ተጨማሪ ማስተዋል ይሰጠናል። ታናሹ ልጅ በአባካኝነት ያሳለፈውን ሕይወት ከተወ በኋላ ወደ ቤት ሲመለስ አባቱ በምህረት ተቀበለው። ከቤተሰቡ ተለይቶ የማያውቀው ታላቅ ወንድሙ ቅሬታ ባሰማ ጊዜ አባትየው ምን ምላሽ ሰጠ? “ልጄ ሆይ፣ አንተ ሁልጊዜ ከእኔ ጋር ነህ፣ ለእኔም የሆነ ሁሉ የአንተ ነው” አለው። ይህ ወቀሳ ሳይሆን ልጁን እንደሚወደው የሚያሳይ ማረጋገጫ ነበር። አክሎም “ይህ ወንድምህ ሞቶ ነበረ ሕያው ስለ ሆነ ጠፍቶም ነበር ስለ ተገኘ ደስ እንዲለን ፍሥሐም እንድናደርግ ይገባናል” አለው። እኛም በተመሳሳይ የሌሎችን መልካም ጎን ለመመልከት ጥረት ማድረጋችንን መቀጠል እንችላለን።—ሉቃስ 15:11-32
በክርስቲያን ጉባኤ ውስጥ
13, 14. በክርስቲያን ጉባኤ ውስጥ የንጉሥ ሕግ የተባለውን ፍቅርን ማሳየት የምንችልበት አንደኛው መንገድ ምንድን ነው?
13 ክርስቲያኖች እንደመሆናችን መጠን የንጉሥ ሕግ የተባለውን ፍቅርን በሥራ ላይ ለማዋል ጥረት እናደርጋለን። (ያዕቆብ 2:1-9) እርግጥ ነው፣ በኑሮ ደረጃ ረገድ ከእኛ የተለየ ሁኔታ ያላቸውን በጉባኤያችን ውስጥ ያሉ ወንድሞችንና እህቶችን በእኩል ዓይን እናያቸው ይሆናል። ይሁን እንጂ ከዘር፣ ከባሕል ወይም በፊት እንከተለው ከነበረው ሃይማኖት አኳያ አድልዎ እናደርጋለን? ከሆነ የያዕቆብን ምክር ተግባራዊ ማድረግ የምንችለው እንዴት ነው?
14 በክርስቲያናዊ ስብሰባዎች ላይ የሚገኙትን ሁሉ ሞቅ ባለ መንፈስ መቀበላችን እንግዳ ተቀባይ መሆናችንን ያሳያል። ወደ መንግሥት አዳራሹ የሚመጡ አዳዲስ ሰዎችን ቀርበን ማነጋገራችን መጀመሪያ ላይ የሚሰማቸው የፍርሃትና የባይተዋርነት መንፈስ እንዲወገድላቸው ያደርጋል። በዚህም የተነሳ ለመጀመሪያ ጊዜ በክርስቲያናዊ ስብሰባ ላይ የተገኙ ሰዎች እንዲህ ብለዋል:- “ከዚህ በፊት የሚያውቁኝ ያህል ሁሉም የተቀበሉኝ ሞቅ ባለ የወዳጅነት መንፈስ ነው። ፈጽሞ እንግድነት አልተሰማኝም።”
15. ልጆች በጉባኤ ውስጥ ላሉት አረጋውያን ትኩረት እንዲሰጡ ማበረታታት የሚቻለው እንዴት ነው?
15 በአንዳንድ ጉባኤዎች ውስጥ ስብሰባው ካለቀ በኋላ አንዳንድ ወጣቶች በዕድሜ ትላልቅ ከሆኑት ገለል ብለው በአዳራሹ ውስጥ ወይም ውጪ አንድ ላይ ይሰበሰባሉ። ይህን ልማድ ለማስቀረት ምን ማድረግ ይቻላል? የመጀመሪያው እርምጃ ወላጆች ልጆቻቸውን ለስብሰባ በማዘጋጀት በቤታቸው ሥልጠና መስጠት እንደሆነ የታወቀ ነው። (ምሳሌ 22:6) የቤተሰቡ አባላት ወደ ስብሰባው ይዘው የሚሄዱትን ጽሑፍ የማዘጋጀቱ ኃላፊነት ለልጆች ሊሰጣቸው ይችላል። ወላጆች ልጆቻቸው በስብሰባው ላይ የተገኙትን በዕድሜ የገፉና አቅመ ደካማ የሆኑ ወንድሞችና እህቶች እንዲያጫውቷቸው ማበረታታትም ይችላሉ። ልጆች እነዚህን ወንድሞችና እህቶች ማበረታታት መቻላቸው የእርካታ ስሜት እንዲሰማቸው ያደርጋል።
16, 17. በዕድሜ የጎለመሱ ክርስቲያኖች በጉባኤ ውስጥ ያሉ ወጣቶች ያሏቸውን መልካም ጎኖች መመልከት የሚችሉት እንዴት ነው?
16 በዕድሜ የጎለመሱ ወንድሞችና እህቶችም በጉባኤ ውስጥ ላሉ ልጆች ትኩረት መስጠት ይኖርባቸዋል። (ፊልጵስዩስ 2:4) ቅድሚያውን ወስደው በማነጋገር አንዳንድ የሚያበረታቱ ሐሳቦች ሊያካፍሏቸው ይችላሉ። ብዙውን ጊዜ በስብሰባው ላይ አንዳንድ ጥሩ ነጥቦች ይጠቀሳሉ። ልጆቹን በስብሰባው የተደሰቱ ስለመሆናቸውና በተለይ ከትምህርቱ ውስጥ እነርሱን የነካቸውና ተግባራዊ ሊያደርጉት የሚችሉት ሐሳብ እንዳገኙ መጠየቅ ይቻላል። እንዲሁም የጉባኤው ክፍል እንደመሆናቸው መጠን ስብሰባውን በንቃት ለመከታተል ላሳዩት ትጋትና በስብሰባው ላይ ለሰጡት ሐሳብ ወይም ክፍል በማቅረብ ላደረጉት ተሳትፎ ሊመሰገኑ ይገባል። በጉባኤው ውስጥ ካሉት በዕድሜ የጎለመሱ ወንድሞች ጋር ያላቸው ቅርርብና ቤት ውስጥ ትንንሽ ሥራዎችን የሚያከናውኑበት መንገድ እያደጉ ሲሄዱ ትልልቅ ኃላፊነቶችንም የመወጣት ብቃት ሊኖራቸው እንደሚችል ይጠቁማል።—ሉቃስ 16:10
17 አንዳንድ ወጣቶች ኃላፊነቶችን ተቀብለው እድገት በማድረግ ይበልጥ ክብደት ያላቸው የሥራ ምድቦችን ለመቀበል የሚያስችሏቸውን መንፈሳዊ ባሕርያት ያዳብራሉ። በሥራ የተጠመዱ መሆናቸውም ከሞኝነት ድርጊት እንዲቆጠቡ ሊረዳቸው ይችላል። (2 ጢሞቴዎስ 2:22) እንዲህ ዓይነቶቹ የሥራ ምድቦች የጉባኤ አገልጋይ ሆነው ለማገልገል እየተጣጣሩ ላሉ ወንድሞች የብቃት ‘መፈተኛ’ ሊሆኑ ይችላሉ። (1 ጢሞቴዎስ 3:10) በስብሰባዎች ላይ የሚያደርጉት ንቁ ተሳትፎ፣ የአገልግሎት ቅንዓታቸው እንዲሁም ለጉባኤው አባላት የሚያሳዩት የአሳቢነት መንፈስ ለተጨማሪ ኃላፊነት ይበቁ እንደሆነና እንዳልሆነ ሽማግሌዎች እንዲወስኑ ያስችላቸዋል።
የሌሎችን መልካም ጎን መመልከት
18. ሽማግሌዎች በፍርድ አሰጣጥ ወቅት ምን ዓይነት ስህተት ላለመፈጸም መጠንቀቅ አለባቸው? ለምንስ?
18 ምሳሌ 24:23 “በፍርድ ታደላ ዘንድ መልካም አይደለም” በማለት ይናገራል። አምላካዊ ጥበብ ሽማግሌዎች ጉባኤ ውስጥ የፍርድ ጉዳዮችን ሲመለከቱ ከአድልዎ እንዲርቁ ይጠይቅባቸዋል። ያዕቆብ “ከሰማይ የሆነችው ጥበብ . . . በመጀመሪያ ንጽሕት ናት፣ በኋላም ሰላም ወዳድ፣ ታጋሽ፣ እሺ ባይ፣ ምሕረትና መልካም ፍሬ የሞላባት፣ አድልዎና ግብዝነት የሌለባት ናት” በማለት ተናግሯል። (ያዕቆብ 3:17 አ.መ.ት ) በግልጽ ለማየት እንደሚቻለው ሽማግሌዎች የሌሎችን መልካም ጎኖች ለመመልከት የሚጥሩ ቢሆንም በግል ዝምድና ወይም በስሜት ተመርተው የተዛባ ፍርድ እንዳይሰጡ ጥንቃቄ ማድረግ አለባቸው። መዝሙራዊው አሳፍ “እግዚአብሔር በአማልክት ማኅበር ቆመ” ሲል ጽፏል። “በአማልክትም [ወይም “በአምላክ መሰል ሰዎች” ማለትም በሰብዓዊ ፈራጆች] መካከል ይፈርዳል። እስከ መቼ ሐሰትን ትፈርዳላችሁ? እስከ መቼስ ለኃጢአተኞች ፊት ታደላላችሁ?” (መዝሙር 82:1, 2) በዚህም መሠረት ክርስቲያን ሽማግሌዎች ከጓደኛ ወይም ከቅርብ ዘመድ ጋር በተያያዙ ጉዳዮች የአድልዎ መንፈስ ከማሳየት ይርቃሉ። በዚህ መንገድ የጉባኤውን አንድነት የሚጠብቁ ከመሆኑም በላይ የይሖዋ መንፈስ በነጻነት እንዲሠራ ያስችላሉ።—1 ተሰሎንቄ 5:23
19. የሌሎችን መልካም ጎን ማየት የምንችልባቸው ተጨማሪ መንገዶች የትኞቹ ናቸው?
19 የወንድሞችንና የእህቶችን መልካም ጎን ለማየት ጥረት ስናደርግ ጳውሎስ ለተሰሎንቄ ጉባኤ እንደሚከተለው ብሎ በጻፈ ጊዜ ያሳየውን ዓይነት ዝንባሌ እናንጸባርቃለን:- “የምናዛችሁንም አሁን እንድታደርጉ ወደ ፊትም ደግሞ እንድታደርጉ ስለ እናንተ በጌታ ታምነናል።” (2 ተሰሎንቄ 3:4) የሌሎችን መልካም ጎን ለመመልከት ጥረት ስናደርግ ስህተቶቻቸውን ለማለፍ እንገፋፋለን። ነቃፊ የመሆንን መንፈስ በማስወገድ ወንድሞቻችንን ልናመሰግን የምንችልባቸውን አጋጣሚዎች እንፈልጋለን። ጳውሎስ “በመጋቢዎች ዘንድ የታመነ ሆኖ መገኘት ይፈለጋል” ሲል ጽፏል። (1 ቆሮንቶስ 4:2) ጉባኤውን የመጠበቅ አደራ የተጣለባቸውም ሆነ ሌሎች ወንድሞችና እህቶች የሚያሳዩት ታማኝነት በእኛ ዘንድ ተወዳጅ ያደርጋቸዋል። ይህም ክርስቲያናዊ ወዳጅነታችንን በማጠናከር ይበልጥ እንድንቀራረብ ያደርጋል። ጳውሎስ በጊዜው ለነበሩ ወንድሞች የተሰማው ዓይነት ስሜት ይኖረናል። እነዚህን ወንድሞችና እህቶች ‘በእግዚአብሔር መንግሥት አብረውን የሚሠሩና’ እኛንም ‘የሚያጽናኑን’ እንደሆኑ አድርገን ልንመለከታቸው ይገባል። (ቆላስይስ 4:10, 11) እንዲህ በማድረግ የይሖዋን አመለካከት እናንጸባርቃለን።
20. የሰዎችን መልካም ጎን ለመመልከት ጥረት የሚያደርጉ ምን በረከቶች ያገኛሉ?
20 ነህምያ “አምላኬ ሆይ፣ በመልካም አስበኝ” ሲል ባቀረበው ጸሎት እንደምንስማማ የታወቀ ነው። (ነህምያ 13:31) ይሖዋ የሰዎችን መልካም ጎኖች የሚመለከት መሆኑ ምንኛ ያስደስታል! (1 ነገሥት 14:13) እኛም ከሌሎች ጋር ባለን ግንኙነት ረገድ እንዲሁ እናድርግ። ይህም ከኃጢአት የመንጻትና በቅርቡ በሚመጣው አዲስ ዓለም ውስጥ ለዘላለም የመኖር ተስፋ ይሰጠናል።—መዝሙር 130:3-8
ምን ብለህ ትመልሳለህ?
• ይሖዋ ለሰዎች ሁሉ ደግነት እንዲያሳይ የሚያደርገው ምንድን ነው?
• በሚከተሉት ዘርፎች የሌሎችን መልካም ጎን ለመመልከት ጥረት ማድረግ የምንችለው እንዴት ነው:-
• በአገልግሎታችን?
• በቤተሰባችን ውስጥ?
• በጉባኤያችን ውስጥ?
• ከሰዎች ጋር ባለን ማንኛውም ግንኙነት?
[የአንቀጾቹ ጥያቄዎች]
[በገጽ 18 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ዮሴፍ ወንድሞቹ ይጠሉት የነበረ ቢሆንም መልካም ጎናቸውን ለመመልከት ጥረት አድርጓል
[በገጽ 19 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
በአገልግሎት የሚያጋጥመን ተቃውሞ ሰዎች ሁሉ እውነትን እንዲያውቁ ከመርዳት አያግደንም
[በገጽ 20 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ያዕቆብ ወንዶች ልጆቹ የሠሩትን ክፋት አስታውሶ እነርሱን ከመባረክ አልተቆጠበም
[በገጽ 21 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
በክርስቲያናዊ ስብሰባዎች ላይ ሁሉንም ሞቅ ባለ መንፈስ ተቀበሉ