ሌሎችን ማገልገል የራሴን ሥቃይ አስታግሶልኛል
የሕይወት ታሪክ
ሌሎችን ማገልገል የራሴን ሥቃይ አስታግሶልኛል
ሁልያን አርያስ እንደተናገረው
በ1988 የ40 ዓመት ጎልማሳ ሳለሁ አስተማማኝ ሥራ እንዳለኝ አድርጌ አስብ ነበር። በበርካታ አገሮች ውስጥ ቢሮዎች ባሉት በአንድ ትልቅ ኩባንያ ውስጥ የቅርንጫፍ ቢሮ አስተዳዳሪ ነበርኩ። መሥሪያ ቤቴ ዘመናዊ መኪና እንዲሁም በስፔይን፣ ማድሪድ ውስጥ የሚያምር ቢሮ የሰጠኝ ከመሆኑም በላይ ዳጎስ ያለ ደመወዝ ይከፈለኝ ነበር። እንዲያውም የኩባንያው አስተዳዳሪዎች በስፔይን የሚገኙት ቅርንጫፍ ቢሮዎች ኃላፊ ሊያደርጉኝ እንደሚፈልጉ ፍንጭ ሰጥተውኝ ነበር። ይሁን እንጂ ከጥቂት ጊዜ በኋላ በሕይወቴ ውስጥ ከፍተኛ ለውጥ ይከሰታል የሚል ግምት አልነበረኝም።
በዚያው ዓመት አንድ ቀን መልቲፕል ስክሌሮሲስ በተባለ ፈውስ አልባ በሽታ መያዜን ሐኪም ነገረኝ። ሰማይ የተደፋብኝ መሰለኝ። በሽታው በአንድ ሰው ላይ ምን ሊያስከትል እንደሚችል የሚገልጹ ጽሑፎችን ሳነብብ ደግሞ በፍርሃት ተዋጥኩ። a በቀሪው የሕይወት ዘመኔ ከባድ አደጋ ያንዣበበብኝ ያህል ሆኖ ተሰማኝ። ባለቤቴን ሚላግሮስንና የሦስት ዓመት ልጄን እስማኤልን እንዴት ላስተዳድራቸው ነው? ይህን ችግር በተሳካ ሁኔታ መቋቋም የምችለውስ እንዴት ነው? ለእነዚህ ጥያቄዎች መልስ ለማግኘት እየታገልኩ ሳለ ሌላ አሳዛኝ ሁኔታ አጋጠመኝ።
ዶክተሩ ስለ በሽታው ከነገረኝ ከአንድ ወር ገደማ በኋላ የሥራ ኃላፊዬ ወደ ቢሮው ጠራኝና መሥሪያ ቤቱ የሚፈልገው “ጥሩ ቁመና” ያላቸውን ሰዎች እንደሆነ ነገረኝ። ቀስ በቀስ ለአካል ጉዳተኝነት በሚዳርግ በሽታ የተያዘ ሰው ደግሞ ገና በሽታው ባይጠናበትም እንኳን የሚፈለገውን ዓይነት ጥሩ ቁመና ሊኖረው እንደማይችል ገልጾ ከሥራ መባረሬን ነገረኝ። አስተማማኝ ይመስል የነበረውን ሥራዬን በድንገት አጣሁ!
በቤተሰቤ ፊት ችግሩን በድፍረት የተጋፈጥኩት ለማስ
መሰል እጥር የነበረ ቢሆንም ብቻዬን ሆኜ ስለደረሰብኝ ሁኔታና ስለ ወደፊቱ ሕይወቴ ለማሰብ እፈልግ ነበር። የሚሰማኝን የጭንቀት ስሜት ለመቋቋም ከፍተኛ ትግል አደርግ ነበር። ከሁሉም በላይ ቅስሜን የሰበረው በአንድ ጀምበር እንደማልረባ ተቆጥሬ ከሥራ መባረሬ ነበር።ከድካሜ ኃይል ማግኘት
ደስ የሚለው በዚህ ተስፋ አስቆራጭ ወቅት ከበርካታ ምንጮች ብርታት ማግኘት ችዬ ነበር። ከ20 ዓመታት በፊት የይሖዋ ምሥክር ሆኜ ነበር። ስለዚህ ውስጣዊ ስሜቴንና የወደፊቱን ጊዜ በተመለከተ የሚሰማኝን ስጋት በመግለጽ ወደ ይሖዋ ከልብ ጸለይኩ። የይሖዋ ምሥክር የሆነችው ባለቤቴ ትልቅ የብርታት ምንጭ የሆነችልኝ ሲሆን አንዳንድ የቅርብ ወዳጆቼ ያሳዩኝ ደግነትና ርኅራኄም በጣም ጠቅሞኛል።—ምሳሌ 17:17
ሌሎችን የመርዳት ኃላፊነት እንዳለብኝ ማወቄም ረድቶኛል። ልጄን በአግባቡ ማሳደግ፣ ማስተማር፣ አብሬው መጫወትና በስብከቱ ሥራ ማሠልጠን እፈልግ ነበር። ስለዚህ ተስፋ ቆርጬ እጄን መስጠት አልነበረብኝም። ከዚህም በተጨማሪ በይሖዋ ምሥክሮች ጉባኤ ውስጥ በሽምግልና ስለማገለግል ክርስቲያን ወንድሞቼና እህቶቼ የእኔ ድጋፍ ያስፈልጋቸው ነበር። በደረሰብኝ ችግር የተነሳ እምነቴ እንዲላላ ከፈቀድኩ ምን ዓይነት ምሳሌ ልሆናቸው እችላለሁ?
በሕይወቴ ውስጥ አካላዊም ሆነ ኢኮኖሚያዊ ለውጥ መከሰቱ አልቀረም፤ አንዳንዶቹ ለውጦች በሕይወቴ ላይ መጥፎ ውጤት ያስከተሉ ሲሆን ሌሎቹ ግን ጠቅመውኛል። በአንድ ወቅት አንድ ዶክተር “በበሽታ መያዝ ሰውን ይለውጠዋል እንጂ ጨርሶ አያጠፋውም” ሲል ሰምቼ ነበር። ሁሉም ለውጦች መጥፎ እንዳልሆኑም ከራሴ ሕይወት ተምሬያለሁ።
በመጀመሪያ ደረጃ “የሥጋዬ መውጊያ” ሌሎች ያለባቸውን የጤና እክል በተሻለ ሁኔታ እንድረዳና ርኅራኄ እንዳሳያቸው አስችሎኛል። (2 ቆሮንቶስ 12:7) “በፍጹም ልብህ በእግዚአብሔር ታመን፣ በራስህም ማስተዋል አትደገፍ” የሚለው የምሳሌ 3:5 ጥቅስ ከመቼውም ጊዜ ይበልጥ ትርጉም ያለው ሆኖልኛል። ከሁሉም በላይ በሕይወት ውስጥ ትልቁን ቦታ ሊይዝ የሚገባውና የእርካታና የዋጋማነት ስሜት የሚያስገኘው ምን እንደሆነ በሕይወቴ ላይ ከደረሰው ለውጥ ለማስተዋል ችያለሁ። በይሖዋ ድርጅት ውስጥ ብዙ ላከናውነው የምችለው ሥራ ነበር። ኢየሱስ “ከሚቀበል ይልቅ የሚሰጥ ብፁዕ ነው” በማለት የተናገረው ሐሳብ ትክክል መሆኑን ተገንዝቤያለሁ።—ሥራ 20:35
አዲስ ሕይወት
በበሽታው መያዜ ከታወቀ ብዙም ሳይቆይ ማድሪድ ውስጥ በሚሰጥ ሴሚናር ላይ እንድገኝ ተጋበዝኩ። የሴሚናሩ ዓላማ በሐኪሞችና የይሖዋ ምሥክር በሆኑ ሕሙማን መካከል የትብብር መንፈስ ለመፍጠር የሚረዱ ፈቃደኛ የሆኑ ክርስቲያኖችን ማሠልጠን ነበር። ከዚያም እነዚህ ፈቃደኛ ክርስቲያኖች የሆስፒታል አገናኝ ኮሚቴዎች ሆነው እንዲሠሩ ተደረገ። ሴሚናሩ የተካሄደው በጣም በሚያስፈልገኝ ወቅት ላይ ነበር። ገንዘብ ከሚያስገኝ ከማንኛውም ሥራ ይበልጥ እርካታ የሚሰጥ የተሻለ ሥራ አገኘሁ።
አዲስ የተቋቋሙት የሆስፒታል አገናኝ ኮሚቴዎች ሥራቸው ወደተለያዩ ሆስፒታሎች በመሄድ ዶክተሮችን ማነጋገርና ለጤና ባለሞያዎች አቋማችንን ማስረዳት እንደሆነ በሴሚናሩ ላይ ተገለጸልን። ዓላማውም በሐኪሞችና የይሖዋ ምሥክር በሆኑ ሕሙማን መካከል አላስፈላጊ ውዝግቦችን በማስቀረት የትብብር መንፈስ መፍጠር ነው። ኮሚቴዎቹ ያለ ደም ሕክምና ለመስጠት ፈቃደኛ የሆኑ ዶክተሮችን በማፈላለግ የይሖዋ ምሥክሮችን ይረዳሉ። እርግጥ ስለ ሕክምና ብዙም እውቀት ስላልነበረኝ የሕክምና ቃላትንና የሕክምና ሥነ ምግባርን እንዲሁም የሆስፒታል አደረጃጀትን በሚመለከት ብዙ ነገሮች መማር ነበረብኝ። ቢሆንም ሴሚናሩ ሲጠናቀቅ ወደ ቤቴ የተመለስኩት በአዲስ መንፈስ ሲሆን ከፊቴ የሚጠብቀኝን ሥራ ለመጀመር ጉጉት አድሮብኝ ነበር።
በኮሚቴው ውስጥ መሥራት እርካታ አስገኝቶልኛል
ምንም እንኳን የያዘኝ በሽታ ቀስ በቀስ አቅም እያሳጣኝ ቢመጣም የሆስፒታል አገናኝ ኮሚቴ አባል ሆኜ የማከናውናቸው
ኃላፊነቶች ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመሩ ይሄዱ ነበር። በሕመሜ ምክንያት መሥራት ስለማልችል መንግሥት የገንዘብ ድጎማ ያደርግልኝ ነበር። ይህም ወደ ሆስፒታሎች እየሄድኩ ዶክተሮችን ለማነጋገር የምችልበት ሰፊ ጊዜ ሰጥቶኛል። አንዳንድ ጊዜ ቅር የሚያሰኝ ሁኔታ ቢያጋጥመኝም ሥራው ከጠበቅሁት በላይ ቀላልና አስደሳች ሆኖ አግኝቼዋለሁ። ምንም እንኳን አሁን ያለ ተሽከርካሪ ወንበር መንቀሳቀስ የማልችል ቢሆንም አንድ የኮሚቴው አባል ሁልጊዜ አብሮኝ ስለሚሄድ ይህ ብዙም እንቅፋት አልፈጠረብኝም። ዶክተሮች በተሽከርካሪ ወንበር የሚንቀሳቀሱ ሰዎችን ማነጋገር እንግዳ አይሆንባቸውም፤ እነርሱን ለማግኘት ያደረግሁትን ጥረት ሲመለከቱ ደግሞ በአክብሮት ያዳምጡኛል።ባለፉት አሥር ዓመታት በመቶዎች የሚቆጠሩ ዶክተሮችን አነጋግሬያለሁ። አንዳንዶቹ ገና ከመጀመሪያው ሊተባበሩን ፈቃደኞች ይሆናሉ። የታካሚዎችን ፍላጎት ማክበር የሚያስደስታቸው ክዋን ድዋርቴ የተባሉ ማድሪድ ውስጥ የሚሠሩ የልብ ቀዶ ሐኪም ያለ ደም ሕክምና ለመስጠት ምንም ሳያቅማሙ ፈቃደኝነታቸውን ገለጹልን። ከዚያን ጊዜ አንስቶ ከተለያዩ የስፔይን ክፍላተ አገራት ለመጡ ከ200 የሚበልጡ የይሖዋ ምሥክር ታካሚዎች ያለ ደም ቀዶ ሕክምና አድርገዋል። ዓመታት እያለፉ ሲሄዱ ያለ ደም ቀዶ ሕክምና የሚያደርጉት ዶክተሮች ቁጥር ጨምሯል። ለዚህ በከፊል አስተዋጽኦ ያደረገው ከዶክተሮች ጋር የምናደርገው ውይይት ቢሆንም በሕክምናው መስክ የተገኘው እድገትና ያለ ደም በሚደረግ ቀዶ ሕክምና የተገኙ ጥሩ ውጤቶች ያበረከቱት ድርሻም ሳይጠቀስ የሚታለፍ አይደለም። ከዚህም በላይ ይሖዋ ጥረታችንን እንደባረከው ይሰማናል።
በተለይ በልጆች ሕክምና ዘርፍ ባለሞያ የሆኑ አንዳንድ የልብ ቀዶ ሐኪሞች የሚሰጡት ምላሽ በጣም ያበረታታኛል። ለሁለት ዓመታት ያህል ሁለት ቀዶ ሐኪሞችንና ሰመመን የሚሰጡ ባለሞያዎችን ካቀፈ አንድ ቡድን ጋር ተደጋጋሚ ውይይት እናደርግ ነበር። በመስኩ የተሰማሩ ሌሎች ዶክተሮች ምን እንደሚያደርጉ የሚገልጹ የሕክምና ጽሑፎችን እንሰጣቸው ነበር። የልብና የደም ቧንቧ ችግር ላለባቸው ልጆች የሚሰጥ ቀዶ ሕክምናን አስመልክቶ በ1999 ስብሰባ በተካሄደበት ወቅት የጥረታችንን ውጤት ማየት ችለናል። ሁለቱ ዶክተሮች ያለ ደም ሕክምና ለማድረግ ፈቃደኛ በሆነ ከለንደን በመጣ ቀዶ ሐኪም እየተመሩ በደም ቅዳ ቧንቧው ላይ ማስተካከያ ለሚያስፈልገው የይሖዋ ምሥክር ወላጆች ያሉት አንድ ሕፃን ልጅ በጣም ውስብስብ የሆነ ቀዶ ሕክምና አደረጉለት። b አንደኛው ሐኪም ከቀዶ ሕክምናው ክፍል ወጥቶ ቀዶ ሕክምናው በተሳካ ሁኔታና በቤተሰቡ ፍላጎት መሠረት መከናወኑን ሲነግረን እኔም ሆንኩ ወላጆቹ በጣም ተደሰትን። በአሁኑ ወቅት እነዚህ ሁለት ዶክተሮች ከመላው ስፔይን ለሚመጡ የይሖዋ ምሥክር ታካሚዎች ሕክምና ይሰጣሉ።
እንደዚህ ዓይነት ሁኔታዎች ሲፈጠሩ ይበልጥ የሚያስደስተኝ ክርስቲያን ወንድሞቼን መርዳት መቻሌ ነው። ብዙውን ጊዜ ወንድሞች የሆስፒታል አገናኝ ኮሚቴውን እርዳታ የሚጠይቁት በሕይወታቸው ውስጥ በጣም ከባድ የሚባል ችግር ሲያጋጥማቸው ነው። ቀዶ ሕክምና ማድረግ ያስፈልጋቸዋል፤ በአካባቢያቸው ባለው ሆስፒታል ውስጥ የሚሠሩት ዶክተሮች ደግሞ ያለ ደም ቀዶ ሕክምና ሊያደርጉላቸው ፈቃደኝነቱም ሆነ ችሎታው የላቸውም። ይሁን እንጂ ወንድሞች ማድሪድ ውስጥ በማንኛውም የሕክምና መስክ ያለ ደም ቀዶ ሕክምና ለማድረግ ፈቃደኛ የሚሆኑ ሐኪሞች መኖራቸውን ሲያውቁ ከፍተኛ እፎይታ ይሰማቸዋል። አንድ ወንድም እኛ በሆስፒታሉ ውስጥ በመገኘታችን ብቻ ጭንቀቱ ተወግዶ መንፈሱ ሲረጋጋ ተመልክቻለሁ።
ዳኞችና የሕክምና ሥነ ምግባር
ከቅርብ ዓመታት ወዲህ የሆስፒታል አገናኝ ኮሚቴ አባላት ዳኞችንም ማነጋገር ጀምረዋል። በእነዚህ ውይይቶች ወቅት ስለ ደም ያለንን አቋምና ያለ ደም የሚደረጉ የሕክምና አማራጮችን በተመለከተ ዳኞች ግንዛቤ እንዲኖራቸው ለማድረግ የተዘጋጀ ፋሚሊ ኬር ኤንድ ሜዲካል ማኔጅመንት ፎር ጀሆቫስ ዊትነስስ የተባለ ጽሑፍ እንሰጣቸው ነበር። ከዚያ በፊት ስፔይን ውስጥ ዳኞች ያለ ሕመምተኛው ፈቃድ ዶክተሩ ደም እንዲሰጠው ማዘዛቸው የተለመደ ስለነበር ከዳኞች ጋር ተገናኝቶ መነጋገሩ በጣም አስፈላጊ ነበር።
ዳኞች ሥራቸውን የሚያከናውኑባቸው ክፍሎች ግርማ ሞገስ የተላበሱ ከመሆናቸው የተነሳ በመጀመሪያው ቀን በተሽከርካሪ ወንበሬ በኮሪደሩ ላይ ስጓዝ እዚያ ቦታ ላይ መገኘት እንደማይገባኝ ተሰምቶኝ ነበር። ይባስ ብሎ ደግሞ ትንሽ ተደነቃቀፍንና ከተሽከርካሪ ወንበሬ ላይ ወደቅሁ። ይህንን የተመለከቱ ጥቂት ዳኞችና ጠበቆች በደግነት መጥተው ረዱኝ፤ ቢሆንም በእነርሱ ፊት እንዲህ ዓይነት ሁኔታ ስላጋጠመኝ እፍረት ተሰማኝ።
ዳኞቹ ልናነጋግራቸው የፈለግንበት ምክንያት ግልጽ ባይሆንላቸውም አብዛኞቹ በደግነት ተቀበሉን። በመጀመሪያ ያነጋገርኩት ዳኛ ስለ አቋማችን ቀደም ብሎ ሲያስብበት ስለነበር ሰፋ ያለ ጊዜ ወስደን እንድንወያይ እንደሚፈልግ ገለጸልን። በቀጣዩ ቀጠሯችን ተሽከርካሪ ወንበሬን ራሱ እየገፋ ወደ ክፍሉ ያስገባኝ ከመሆኑም በላይ ሐሳባችንን ስንናገር በጥሞና አዳመጠን። ይህ ውይይት ያስገኘው መልካም ውጤት እኔም ሆንኩ ሌሎች የኮሚቴው አባላት የነበረንን ፍርሃት እንድናሸንፍ የረዳን ሲሆን ብዙም ሳይቆይ ተጨማሪ መልካም ውጤቶች አግኝተናል።
በዚያው ዓመት በጥሩ ሁኔታ ተቀብሎ ላነጋገረን አንድ ሌላ ዳኛ ፋሚሊ ኬር የተባለውን ጽሑፍ የሰጠነው ሲሆን እርሱም እንደሚያነበው ቃል ገብቶልናል። ድንገተኛ ሁኔታ ተፈጥሮ ሊያነጋግረን ከፈለገ እንዲደውልልኝ የስልክ ቁጥሬን ሰጠሁት። ከሁለት ሳምንት በኋላ፣ በአካባቢው ባለ ሆስፒታል የሚሠራ አንድ የቀዶ ሕክምና ባለሞያ ለአንዲት የይሖዋ ምሥክር ሕመምተኛ ደም ለመስጠት የሚያስችል ማዘዣ እንዲጽፍለት እንደጠየቀው ደውሎ ነገረኝ። ዳኛው በሕመምተኛዋ ፍላጎት መሠረት ያለ ደም ሕክምና እንዲሰጣት ማድረግ የሚቻልበት መንገድ ካለ እንድንረዳው ጠየቀን። ያለ ደም ሕክምና የሚያደርጉ ዶክተሮች ያሉበት ሌላ ሆስፒታል ለማግኘት ብዙ አልተቸገርንም፤ ቀዶ ሕክምናውም በተሳካ ሁኔታ ተከናወነ። ዳኛው ውጤቱን ሲሰማ የተደሰተ ሲሆን ወደፊትም ተመሳሳይ መፍትሔዎችን እንደሚፈልግ አረጋገጠልን።
ሐኪሞች የሕመምተኛውን መብትና ሕሊና ግምት ውስጥ እንዲያስገቡ ስለምንፈልግ ብዙውን ጊዜ ከዶክተሮች
ጋር ስንወያይ የሕክምና ሥነ ምግባር ጥያቄ ይነሳል። በማድሪድ ያለ ደም ሕክምና ለመስጠት ፈቃደኛ የሆነ አንድ ሆስፒታል የሕክምና ሥነ ምግባርን አስመልክቶ ባዘጋጀው ኮርስ ላይ እንድገኝ ግብዣ አቀረበልኝ። ይህ ኮርስ በሕክምናው መስክ ለተሰማሩ በርካታ ባለሞያዎች በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ ስለተመሠረተው አቋማችን የማስረዳበት አጋጣሚ ከፈተልኝ። ከዚህም በላይ ዶክተሮች ምን ዓይነት ከባድ ውሳኔዎችን ማድረግ እንደሚጠበቅባቸው ለመገንዘብ አስችሎኛል።ከኮርሱ መምህራን አንዱ የሆኑት ፕሮፌሰር ዲያጎ ግራሲያ የሕክምና ሥነ ምግባርን በሚመለከት በስፔይን ለሚገኙ ዶክተሮች በቋሚነት ኮርስ ያዘጋጁ ነበር። እኚህ ፕሮፌሰር ደም መውሰድን በተመለከተ ሕመምተኛው ስለ ሕክምናው በቂ መረጃ ተሰጥቶት በራሱ የመወሰን መብቱ ሊከበርለት ይገባል የሚል ጽኑ እምነት ነበራቸው። c ከፕሮፌሰሩ ጋር አዘውትረን እንገናኝ ስለነበር ለድኅረ ምረቃ ተማሪዎቻቸው ደምን በሚመለከት ስላለን አቋም ማብራሪያ እንዲሰጡ በስፔይን የሚገኘው የይሖዋ ምሥክሮች ቅርንጫፍ ቢሮ ተወካዮችን ጋብዘዋቸው ነበር። ከእነዚህ ተማሪዎች አንዳንዶቹ በአገሪቱ ውስጥ አሉ ከሚባሉት ስመ ጥር ዶክተሮች መካከል የሚመደቡ ናቸው።
እውነታውን መጋፈጥ
እርግጥ ነው፣ የእምነት ባልንጀሮቼን ለመርዳት የማከናውነው ይህ ሥራ እርካታ የሚሰጥ ቢሆንም የግል ችግሮቼን በሙሉ አስወግዶልኛል ማለት አይደለም። የያዘኝ በሽታ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተባባሰብኝ ነው። ደስ የሚለው ግን በአእምሮዬ ላይ ምንም ችግር አላስከተለብኝም። ፈጽሞ ለማይሰለቹኝ ለባለቤቴና ለልጄ ምስጋና ይግባቸውና አሁንም ኃላፊነቶቼን መወጣት እችላለሁ። ያለ እነርሱ እርዳታና ድጋፍ ይህ ፈጽሞ የማይሞከር ነበር። ሌላው ቀርቶ ልብሴን መልበስ እንኳ አልችልም። በተለይ ቅዳሜ ቅዳሜ ከልጄ ከእስማኤል ጋር አገልግሎት መውጣት የሚያስደስተኝ ሲሆን ከቤት ወደ ቤት እየሄድኩ ሰዎችን እንዳነጋግር ተሽከርካሪ ወንበሬን በመግፋት ይረዳኛል። እንዲሁም የጉባኤ ሽማግሌ እንደመሆኔ መጠን ያሉብኝን ኃላፊነቶች አሁንም እየተወጣሁ ነው።
ባለፉት 12 ዓመታት አንዳንድ አሳዛኝ ሁኔታዎች አጋጥመውኝ ነበር። አንዳንድ ጊዜ ያለብኝ የአካል ጉዳት በቤተሰቤ ላይ ያሳደረውን ተጽዕኖ ስመለከት ሕመሜ ከሚያስከትልብኝ ሥቃይ ይበልጥ ይሰማኛል። አፍ አውጥተው አይናገሩ እንጂ እነርሱም እንደሚሠቃዩ አውቃለሁ። በቅርቡ ዓመት ባልሞላ ጊዜ ውስጥ አማቴንና አባቴን በሞት አጣሁ። በዚያው ዓመት ያለ ተሽከርካሪ ወንበር ከቦታ ቦታ መንቀሳቀስ ተሳነኝ። ከእኛ ጋር ይኖር የነበረው አባቴ የሞተው የሰውነት አካላትን ቀስ በቀስ እያጠቃ ለሞት በሚዳርግ በሽታ ነበር። አባቴን ታስታምመው የነበረችው ባለቤቴ ሚላግሮስ የእርሱ ሁኔታ ወደፊት በእኔም ላይ የሚደርሰውን ሥቃይ እንደሚጠቁም ይሰማት ነበር።
በአንጻሩ ደግሞ ችግሮቹን በጋራ መጋፈጣችን ቤተሰባችንን አንድ አድርጎታል። በአንድ ኩባንያ ውስጥ የነበረኝ የኃላፊነት ወንበር በተሽከርካሪ ወንበር ቢለወጥም ሙሉ ጊዜዬን የማሳልፈው ሌሎችን በመርዳት ስለሆነ ሕይወቴ ከበፊቱ የተሻለ ሆኗል። ሌሎችን መርዳት የራስን ሥቃይ የሚያስታግስ ሲሆን ይሖዋም በችግራችን ጊዜ ብርታት እንደሚሰጠን በገባልን ቃል መሠረት ይረዳናል። እኔም እንደ ጳውሎስ “ኀይልን በሚሰጠኝ በእርሱ ሁሉን ማድረግ እችላለሁ” ብዬ ከልቤ መናገር እችላለሁ።—ፊልጵስዩስ 4:13 አ.መ.ት
[የግርጌ ማስታወሻ]
a መልቲፕል ስክሌሮሲስ ማዕከላዊውን የነርቭ ሥርዓት የሚያጠቃ በሽታ ነው። ብዙውን ጊዜ የሰውነትን ሚዛን በመጠበቅና በእጅና እግር አጠቃቀም ላይ አንዳንድ ጊዜ ደግሞ በማየትና በመናገር እንዲሁም ሐሳብን በመረዳት ችሎታ ላይ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተባባሰ የሚሄድ እክል ያስከትላል።
b ይህ ቀዶ ሕክምና የሮስ የሕክምና አሰጣጥ ዘዴ በመባል ይታወቃል።
c የየካቲት 15, 1997 መጠበቂያ ግንብ ገጽ 19-20ን ተመልከት።
[በገጽ 24 ላይ የሚገኝ ሣጥን]
ልጁ የሰጠው አስተያየት
አባቴ ያሳየው ጽናትና ያለው አዎንታዊ አመለካከት ግሩም ምሳሌ የሆነልኝ ሲሆን ተሽከርካሪ ወንበሩን እየገፋሁ ከቦታ ቦታ ስወስደው አንድ ጠቃሚ ነገር እንዳከናወንኩ ይሰማኛል። ሁልጊዜ የፈለግሁትን ነገር በፈለግኩት ጊዜ ማድረግ እንደማልችል አውቃለሁ። አሁን በአሥራዎቹ ዕድሜ ውስጥ እገኛለሁ፤ ሳድግ የሆስፒታል አገናኝ ኮሚቴ አባል ሆኜ ማገልገል እፈልጋለሁ። ሥቃይና መከራ ጊዜያዊ መሆኑን መጽሐፍ ቅዱስ ከሚሰጠው ተስፋ መገንዘብ ችያለሁ፤ ከዚህም ሌላ ከእኛ የበለጠ ሥቃይ የሚደርስባቸው በርካታ ወንድሞችና እህቶች እንዳሉ አውቃለሁ።
[በገጽ 24 ላይ የሚገኝ ሣጥን]
ባለቤቱ የሰጠችው አስተያየት
ለአንዲት ሚስት መልቲፕል ስክሌሮሲስ በተባለው በሽታ ከሚሠቃይ የትዳር ጓደኛ ጋር መኖር በጣም ከባድ ሲሆን አእምሯዊ፣ ስሜታዊና አካላዊ ችግሮች ያስከትልባታል። ለማድረግ የማቅዳቸውን ነገሮች በሚመለከት ምክንያታዊ መሆንና የወደፊቱን ጊዜ አስመልክቶ አላስፈላጊ ጭንቀቶችን ማስወገድ ጠይቆብኛል። (ማቴዎስ 6:34) ሆኖም አንድ ሰው መከራን ተቋቁሞ ሲኖር ያሉት ግሩም ባሕርያት ጎልተው ይታያሉ። ትዳራችን ከበፊቱ የበለጠ ጠንካራ ሲሆን ከይሖዋ ጋር ያለኝ ዝምድናም የጠበቀ ሆኗል። ተመሳሳይ በሆነ አስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ የሚገኙ ሰዎችን የሕይወት ታሪክ ማንበቤም በእጅጉ አበረታቶኛል። ሁልያን ወንድሞችን በመርዳት በሚያከናውነው ጠቃሚ አገልግሎት የሚያገኘው እርካታ እኔንም የሚያስደስተኝ ሲሆን በየዕለቱ አዳዲስ ችግሮች ቢያጋጥሙንም ይሖዋ ፈጽሞ እንደማይተወን ተገንዝቤያለሁ።
[በገጽ 22 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ባለቤቴ የብርታት ምንጭ ሆናልኛለች
[በገጽ 23 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ዶክተር ክዋን ድዋርቴ ከተባለው የልብ ቀዶ ሐኪም ጋር ስነጋገር
[በገጽ 25 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
እኔና ልጄ አብሮ ማገልገል ያስደስተናል