ምን ዋጣቸው?
ምን ዋጣቸው?
በአንድ ወቅት ታዋቂ የግብጽ ዋና ከተሞች የነበሩት ሜምፎስና ቴብስ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ኖፕ እና ኖእ ተብለው ተጠርተዋል። ኖፕ (ሜምፎስ) የምትገኘው ከናይል ወንዝ በስተ ምዕራብ ከካይሮ በስተ ደቡብ 23 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ነበር። ሆኖም ከጊዜ በኋላ ሜምፎስ የግብጽ ዋና ከተማ መሆኗ ቀረ። በ15ኛው መቶ ዘመን ከዘአበ መባቻ ላይ ከሜምፎስ በስተ ደቡብ 500 ኪሎ ሜትር ያህል ርቃ የምትገኘው ኖእ (ቴብስ) አዲሷ የግብጽ ዋና ከተማ ሆነች። በቴብስ ከተገኙት በርካታ የቤተ መቅደስ ፍርስራሾች መካከል በካርናክ የሚገኘው ግዙፍ ዓምዶች ያሉት ቤተ መቅደስ እስከ ዛሬ ከተገነቡት ሕንጻዎች ሁሉ በትልቅነቱ ተወዳዳሪ እንደሌለው ይገመታል። ቴብስና በካርናክ የሚገኘው ቤተ መቅደሷ የግብጻውያን ዋነኛ አምላክ ለሆነው ለአሞን አምልኮ የተሰጡ ነበሩ።
የመጽሐፍ ቅዱስ ትንቢት ስለ ሜምፎስና ቴብስ ምን ይላል? በግብጹ ንጉሥ በፈርዖንና በአማልክቱ በተለይም ዋነኛ አምላክ በሆነው ‘የኖእ አሞን’ ላይ ፍርድ ተበይኖባቸው ነበር። (ኤርምያስ 46:25, 26) ወደዚያ የሚጎርፉት አምላኪዎች ‘እንደሚጠፉ’ ትንቢት ተነግሮ ነበር። (ሕዝቅኤል 30:14, 15) ይህም በትክክል ተፈጽሟል። ከአሞን አምልኮ የተረፈ ነገር ቢኖር የቤተ መቅደሱ ፍርስራሽ ብቻ ነው። ዘመናዊቷ የሉክሶር ከተማ የምትገኘው ጥንታዊቷ የቴብስ ከተማ ከነበረችበት ቦታ በተወሰነው ክፍል ላይ ሲሆን በፍርስራሹ መካከል አንዳንድ ትናንሽ መንደሮችም አሉ።
በሜምፎስም ቢሆን ከመካነ መቃብሮቿ በስተቀር የተረፈ ነገር የለም። የመጽሐፍ ቅዱስ ምሁር የሆኑት ሉዊዝ ጎልዲንግ እንዲህ ብለዋል:- “ግብጽን የወረሩት አረቦች በወንዙ በሌላኛው አቅጣጫ የሠሩትን ዋና ከተማቸውን [ካይሮ] ለመገንባት ግዙፍ በሆኑት የሜምፎስ ፍርስራሾች ለበርካታ መቶ ዘመናት ተጠቅመዋል። ከተማዋ የናይል ወንዝ በሚያመጣው ደለል በመሸፈኗ እና አረቦቹም ፍርስራሾቹን በሙሉ ለቃቅመው በመውሰዳቸው በአሁኑ ወቅት የጥንቷ ከተማ በነበረችበት ሰፊ ቦታ ላይ አንድ ድንጋይ እንኳን አይታይም።” በእርግጥም መጽሐፍ ቅዱስ ሜምፎስ “ባድማ ትሆናለችና፣ . . . የሚቀመጥባትም አይገኝምና” በማለት የተናገረው ትንቢት ፍጻሜውን አግኝቷል።—ኤርምያስ 46:19
እነዚህ የመጽሐፍ ቅዱስን ትንቢቶች እውነተኝነት ከሚያረጋግጡት በርካታ ማስረጃዎች መካከል ሁለቱ ብቻ ናቸው። የቴብስና የሜምፎስ ከተሞች መጥፋት ገና ፍጻሜያቸውን ባላገኙት የመጽሐፍ ቅዱስ ትንቢቶች ላይ እምነት እንድንጥል ያደርገናል።—መዝሙር 37:10, 11, 29፤ ሉቃስ 23:43፤ ራእይ 21:3-5
[በገጽ 32 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
Photograph taken by courtesy of the British Museum