በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ተራ ሰዎች መጽሐፍ ቅዱስን ተረጎሙ

ተራ ሰዎች መጽሐፍ ቅዱስን ተረጎሙ

ተራ ሰዎች መጽሐፍ ቅዱስን ተረጎሙ

በ1835 ሄንሪ ኖት የተባለ እንግሊዛዊ ግንበኛና ጆን ዴቪስ የተባለ የዌልስ ተለማማጅ የግሮሠሪ ሠራተኛ ጀምረውት የነበረውን ከባድ ሥራ አጠናቀቁ። ከ30 ዓመት የሚበልጥ ጊዜ ከፈጀ አድካሚ ሥራ በኋላ መላውን መጽሐፍ ቅዱስ በታሂቲ ቋንቋ ተርጉመው ጨረሱ። እነዚህ ተራ ሰዎች እንዴት ያሉ ችግሮች አጋጥመዋቸው ነበር? በፍቅር ተነሳስተው ያደረጉት ጥረት ምን ውጤት አስገኘ?

“ታላቁ ንቃት”

በ18ኛው መቶ ዘመን ሁለተኛ አጋማሽ ላይ ታላቁ ንቃት ወይም ንቃት ተብሎ የሚጠራ የፕሮቴስታንቶች እንቅስቃሴ አባላት በብሪታንያ በሚገኙ የመንደር አደባባዮች፣ በማዕድን ማውጫዎችና በፋብሪካዎች ይሰብኩ ነበር። ዓላማቸው ስብከታቸውን ለሠርቶ አደሮች ማድረስ ነበር። የንቃት ሰባኪዎች በጋለ ስሜት የመጽሐፍ ቅዱስን ስርጭት ያበረታቱ ነበር።

የዚህ እንቅስቃሴ መሥራችና የባፕቲስት ቤተ ክርስቲያን አባል የሆነው ዊልያም ካሪ በ1795 ለተቋቋመው የለንደን ሚስዮናውያን ማኅበር (ኤል ኤም ኤስ) መመሥረት አስተዋጽኦ አድርጓል። የለንደን ሚስዮናውያን ማኅበር የአገሬውን ቋንቋ ተምረው በደቡባዊ ፓስፊክ አካባቢዎች በሚስዮናዊነት ለማገልገል ፈቃደኛ የሆኑ ሰዎችን ያሠለጥን ነበር። የእነዚህ ሚስዮናውያን ግብ ወንጌልን በአካባቢው ሕዝቦች ቋንቋ መስበክ ነበር።

በቅርቡ የተገኘችው የታሂቲ ደሴት ለለንደን ሚስዮናውያን ማኅበር የስብከት እንቅስቃሴ የመጀመሪያዋ መስክ ሆነች። ለንቃት እንቅስቃሴ አባላት የታሂቲ ደሴቶች አረማዊነት የነገሠባቸውና በመከርነት ለመሰብሰብ ዝግጁ ሆነው የሚጠባበቁ ‘የጨለማ’ ደሴቶች ነበሩ።

ተራዎቹ ሰዎች አንድ አስቸጋሪ ሥራ ተወጡ

መከሩን ለመሰብሰብ በቂ ዝግጅት ያልነበራቸውና በችኮላ የተመረጡ 30 የሚያክሉ ሰዎች በለንደን ሚስዮናውያን ማኅበር በተገዛች ደፍ የተባለች መርከብ ላይ ተሳፈሩ። አንድ ሪፖርት የተሳፋሪዎቹን ዝርዝር ሲገልጽ “አራት የክህነት ሥልጣን የተሰጣቸው ቄሶች [መደበኛ ሥልጠና ያልወሰዱ]፣ ስድስት አናጺዎች፣ ሁለት ጫማ ሠሪዎች፣ ሁለት ግንበኞች፣ ሁለት ሸማኔዎች፣ ሁለት ልብስ ሠፊዎች፣ አንድ ባለሱቅ፣ አንድ ኮርቻ ሠሪ፣ አንድ የቤት ሠራተኛ፣ አንድ አትክልተኛ፣ አንድ ሐኪም፣ አንድ አንጥረኛ፣ አንድ የበርሜል ሠራተኛ፣ አንድ የጥጥ አምራች፣ አንድ የባርኔጣ ሠሪ፣ አንድ ጨርቅ አምራች፣ አንድ ሣጥን ሠራተኛ፣ አምስት ሚስቶችና ሦስት ሕፃናት ነበሩ” ይላል።

እነዚህ ሚስዮናውያን ከአንድ ግሪክኛ-እንግሊዝኛ መዝገበ ቃላትና ከአንድ የዕብራይስጥ መዝገበ ቃላት ካሉት መጽሐፍ ቅዱስ ሌላ ከመጀመሪያዎቹ የመጽሐፍ ቅዱስ ቋንቋዎች ጋር የሚያስተዋውቃቸው መሣሪያ አልነበራቸውም። ሚስዮናውያኑ በባሕር ላይ በመጓዝ ባሳለፏቸው ሰባት ወራት ቀደም ሲል ደሴቲቱን ጎብኝተው የነበሩና በአብዛኛው ባውንቲ የተባለችውን መርከብ ከድተው የተመለሱ እንግሊዛውያን ካዘጋጁት የቃላት ዝርዝር አንዳንድ የታሂቲ ቃሎችን በቃል አጠኑ። በመጨረሻ ደፍ መጋቢት 7, 1797 ታሂቲ ደረሰችና ሚስዮናውያኑ ከመርከባቸው ወረዱ። ይሁን እንጂ ከአንድ ዓመት በኋላ አብዛኞቹ ተስፋ ቆርጠው ወደ አገራቸው በመመለሳቸው ሰባት ሚስዮናውያን ብቻ ቀሩ።

ከሰባቱ መካከል አንዱ የ23 ዓመቱ ግንበኛ ሄንሪ ኖት ነበር። ከጻፋቸው የመጀመሪያ ደብዳቤዎች መረዳት እንደሚቻለው ከመደበኛ ትምህርት ያለፈ እውቀት አልነበረውም። ሆኖም ገና ከጅምሩ የታሂቲን ቋንቋ በመማር ረገድ ልዩ ተሰጥኦ እንዳለው ያስታውቅ ነበር። ደስ የሚል፣ ቀልደኛና ከልቡ የሚሠራ ሰው እንደነበር ተገልጿል።

በ1801 ኖት አዲስ ለመጡ ዘጠኝ ሚስዮናውያን የታሂቲን ቋንቋ እንዲያስተምር ተመረጠ። ከእነዚህ መካከል ጎበዝ ተማሪና ትጉህ ሠራተኛ የነበረው የ28 ዓመቱ የዌልስ ተወላጅ፣ ጆን ዴቪስ ይገኝ ነበር። ጆን ዴቪስ ሆደ ሠፊና ለጋስ ሰው ነበር። ብዙም ሳይቆይ እነዚህ ሁለት ሰዎች መጽሐፍ ቅዱስን ወደ ታሂቲ ቋንቋ ለመተርጎም ወሰኑ።

ከባድ ሥራ

ይሁን እንጂ የታሂቲ ቋንቋ ፊደል ስላልነበረው የትርጉም ሥራው ቀላል ሆኖ አልተገኘም። ሚስዮናውያኑ ቋንቋውን በማዳመጥ ብቻ መማር ነበረባቸው። መዝገበ ቃላትም ሆነ የሰዋስው መጽሐፍ አልነበራቸውም። ቋንቋው የድምፅ መፈጠሪያ አካላትን በመክፈትና በመዝጋት በሚወጣ የተቆራረጠ ድምፅ የሚነገር፣ በርካታ አናባቢዎችና በጣም ጥቂት ተነባቢዎች ያሉት መሆኑ ለሚስዮናውያኑ ገና ከጅምሩ ተስፋ አስቆራጭ ሆነባቸው። “አብዛኞቹ ቃላት የተዋቀሩት በአናባቢ ብቻ ሲሆን እያንዳንዱ አናባቢ ደግሞ የራሱ የሆነ ድምፅ አለው” በማለት አማርረዋል። “የቃላቱን ድምፅ በትክክል መያዝ አልቻልንም” ብለዋል። እንዲያውም ጨርሶ የሌለ ድምፅ የሰሙ ይመስላቸው ነበር።

ይባስ ብሎ ደግሞ በየጊዜው አንዳንድ ቃላት እንደ ነውር ይቆጠሩ ስለነበረ በሌሎች ቃላት መተካት ነበረባቸው። ሌላው ራስ ምታት ደግሞ ተመሳሳይ ቃላት መብዛታቸው ነው። “ጸሎት” ለሚለው ቃል በታሂቲ ቋንቋ ከ70 የሚበልጡ ተመሳሳይ ትርጉም ያላቸው ቃላት አሉ። በታሂቲ ቋንቋ ዓረፍተ ነገሮች የሚቀናበሩበት ሥርዓት ከእንግሊዝኛ ፈጽሞ የተለየ መሆኑ ሌላው ከባድ ችግር ነበር። እነዚህ ሁሉ ችግሮች ቢኖሩም ሚስዮናውያኑ ቀስ በቀስ በርካታ ቃላትንና ትርጉማቸውን ለማሰባሰብ በመቻላቸው ዴቪስ ከ50 ዓመታት በኋላ ባለ 10, 000 ቃላት መዝገበ ቃላት ሊያሳትም ችሏል።

ከዚህ ሁሉ በተጨማሪ የታሂቲን ቋንቋ በጽሑፍ የማስፈር ችግር ተደቀነባቸው። ሚስዮናውያኑ የታወቀውን የእንግሊዝኛ የአጻጻፍ ስልት ለመጠቀም ሞክረው ነበር። ይሁን እንጂ እንግሊዝኛ የሚጠቀምበት የላቲን ፊደል ከታሂቲ ድምፆች ጋር ሊጣጣም አልቻለም። በዚህም ምክንያት በሥነ ጽሑፍና በሥነ ድምፅ ላይ ማለቂያ የሌለው የሚመስል ውይይት ተደረገ። ሚስዮናውያኑ በደቡባዊ ደሴቶች ለንግግር ብቻ የሚጠቀሙበትን ቋንቋ ወደ ጽሑፍ ቋንቋነት ለመለወጥ የመጀመሪያዎቹ ስለሆኑ አዳዲስ ሆሄያትን መፈልሰፍ ነበረባቸው። የእነርሱ ሥራ የኋላ ኋላ ለብዙዎቹ የደቡብ ፓስፊክ ቋንቋዎች በናሙናነት ያገለግላል ብለው አላሰቡም ነበር።

የመሣሪያ እጥረት ቢኖርባቸውም የበለጸገ የፈጠራ ችሎታ ነበራቸው

ተርጓሚዎቹ የነበሯቸው የማመሳከሪያ ጽሑፎች በጣም ጥቂት ነበሩ። የለንደን ሚስዮናውያን ማኅበር ለትርጉም ሥራቸው መሠረት እንዲያደርጉ መመሪያ የሰጣቸው የላቲኑን ቴክስቱስ ሪሰፕቱስ እና የኪንግ ጄምስን ትርጉም ነበር። ኖት የለንደን ሚስዮናውያን ማኅበር ተጨማሪ የዕብራይስጥና የግሪክኛ መዝገበ ቃላት እንዲሁም በሁለቱም ቋንቋዎች መጽሐፍ ቅዱስ እንዲልክላቸው ጠየቀ። እነዚህ መጻሕፍት ደርሰውት ይሁን አይሁን በትክክል አይታወቅም። ዴቪስ ግን ከዌልስ ወዳጆቹ አንዳንድ ምሑራዊ መጻሕፍት አግኝቷል። ቢያንስ አንድ የግሪክኛ መዝገበ ቃላት፣ አንድ የዕብራይስጥ መጽሐፍ ቅዱስ፣ አንድ የግሪክኛ አዲስ ኪዳንና የሰፕቱጀንት ትርጉም እንደነበሩት መዛግብት ያሳያሉ።

ይህ በእንዲህ እንዳለ፣ የሚስዮናውያኑ የስብከት እንቅስቃሴ እምብዛም ፍሬ አላስገኘም። ሚስዮናውያኑ ለ12 ዓመታት በታሂቲ ይቆዩ እንጂ አንድም የአገሬው ሰው አልተጠመቀም። ከጊዜ በኋላ በማያባራ የእርስ በርስ ጦርነት ምክንያት ከአይበገሬው ከኖት በስተቀር ሁሉም ሚስዮናውያን ወደ አውስትራሊያ ሸሹ። ለተወሰነ ጊዜ ሶሳይቲ አይላንድስ በሚባሉት በዊንድዋርድ ደሴቶች የቀረው ሚስዮናዊ እርሱ ብቻ ነበር። ንጉሥ ፖማሪ ዳግማዊ፣ ሙሪያ ወደምትባለው አጎራባች ደሴት በሸሹ ጊዜ ግን ኖት ንጉሡን ተከትሎ ወደዚያ ሄደ።

ይሁን እንጂ የኖት ወደሌላ አካባቢ መዛወር የትርጉም ሥራውን አላቆመውም። ዴቪስ ሁለት ዓመት ያህል በአውስትራሊያ ከቆየ በኋላ ከኖት ጋር እንደገና ተገናኙ። በዚህ ጊዜ ኖት ግሪክኛና ዕብራይስጥ አጥንቶ ሁለቱንም ቋንቋዎች ችሎ ነበር። ስለዚህም አንዳንድ የዕብራይስጥ ቅዱሳን ጽሑፎች ክፍሎችን ወደ ታሂቲ ቋንቋ መተርጎም ጀመረ። ለአገሩ ሰዎች የሚጥሙና በቀላሉ ሊገቡ የሚችሉ ታሪኮችን የያዙ የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍሎችን መረጠ።

ኖት ከዴቪስ ጋር በመተጋገዝ የሉቃስን ወንጌል መተርጎም ጀመረና በመስከረም ወር 1814 ጨረሰ። እርሱ በታሂቲ ቋንቋ እንግዳ በማይመስል መንገድ ሲተረጉም ዴቪስ ከበኩረ ጽሑፎቹ ጋር እያስተያየ ያርመው ነበር። በ1817 ንጉሥ ፖማሪ ዳግማዊ የሉቃስ ወንጌልን የመጀመሪያ ገጽ እርሳቸው ራሳቸው ማተም ይችሉ እንደሆነ ሚስዮናውያኑን ጠየቋቸው። ከዚያም ንጉሡ ሚስዮናውያኑ ወደ ሙሪያ ባመጡት በእጅ የሚንቀሳቀስ ትንሽ ማተሚያ አተሙት። በእነዚህ ዓመታት ሁሉ ከሚስዮናውያኑ ጎን ሳይለይ ቋንቋውን በዝርዝር እንዲያጠኑ ያስቻላቸውን ቱዋሂን የተባለውን ታማኝ የታሂቲ ተወላጅ ሳንጠቅስ ብናልፍ የታሂቲ መጽሐፍ ቅዱስ አተረጓጎም ታሪክ የተሟላ አይሆንም።

የትርጉሙ ሥራ ተጠናቀቀ

በ1819 ከስድስት ዓመታት ልፋት በኋላ የወንጌሎች፣ የሐዋርያት ሥራና የመዝሙር መጽሐፍ ትርጉም ተጠናቀቀ። አዳዲስ ሚስዮናውያን ያመጡት የማተሚያ መሣሪያ የመጽሐፍ ቅዱሱን መጻሕፍት ኅትመትና ስርጭት ሥራ አቀላጥፏል።

ከዚህ በኋላ የተፋፋመ የመተርጎም፣ የማረምና የመከለስ እንቅስቃሴ ተካሄደ። ኖት 28 ዓመታት በታሂቲ ከኖረ በኋላ በ1825 ስለታመመ የለንደን ሚስዮናውያን ማኅበር ወደ እንግሊዝ እንዲመለስ ፈቀደለት። በዚህ ጊዜ ግን የግሪክኛ ቅዱሳን ጽሑፎች ትርጉም ሥራ ወደመጠናቀቅ ተቃርቦ ነበር። የቀረውን የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል በጉዞ ላይ እንዳለና በእንግሊዝ አገር ቆይታው መተርጎም ቀጠለ። ኖት በ1827 ወደ ታሂቲ ተመለሰ። ከስምንት ዓመት በኋላ በታኅሣሥ ወር 1835 ብዕሩን አስቀመጠ። ከ30 ዓመት ልፋት በኋላ መላው መጽሐፍ ቅዱስ ተተርጉሞ አለቀ።

በ1836 ኖት ሙሉውን የታሂቲ መጽሐፍ ቅዱስ በለንደን ለማሳተም ወደ እንግሊዝ ተመለሰ። ሰኔ 8 ቀን 1838 ኖት የደስታ ሲቃ እየተናነቀው የመጀመሪያውን ሙሉ የታሂቲ መጽሐፍ ቅዱስ ለንግሥት ቪክቶሪያ አቀረበ። ይህ ወቅት ከአርባ ዓመታት በፊት ደፍ በተባለች መርከብ ተሳፍሮ ለሄደውና የዕድሜ ልክ ሥራውን ለማጠናቀቅ ሲል በታሂቲ ባሕል ተውጦ ለኖረው የቀድሞ ግንበኛ ምን ያህል አስደሳች እንደሚሆን መረዳት አያስቸግርም።

ከሁለት ወራት በኋላ ኖት 3, 000 የሚያክሉ የታሂቲ መጽሐፍ ቅዱሶች በ27 ሣጥኖች ጭኖ ወደ ደቡባዊ ፓስፊክ አቀና። በሲድኒ ጥቂት ቆይታ አደረገና እንደገና ታመመ። ይሁን እንጂ ውድ ከሆኑት ሣጥኖቹ ለመለየት አልፈቀደም። ከተሻለው በኋላ በ1840 ታሂቲ ሲደርስ የአገሩ ሕዝቦች መጽሐፍ ቅዱሶቹን ተሻምተው ወሰዱ። ኖት በግንቦት ወር 1844 በ70 ዓመት ዕድሜው በታሂቲ ሞተ።

ከፍተኛ ውጤት ያስገኘ ሥራ

ይሁን እንጂ የኖት ሥራ ሕያው ሆኖ ቀጥሏል። የእርሱ ትርጉም በፖሊኔዥያ ቋንቋዎች ላይ ለረዥም ጊዜ የዘለቀ ውጤት አስከትሏል። ሚስዮናውያኑ የታሂቲ ቋንቋ በጽሑፍ እንዲሠፍር በማድረጋቸው ቋንቋው ተጠብቆ እንዲኖር አስችለዋል። አንድ ደራሲ “ኖት ጥንታዊው የታሂቲ ቋንቋና ሰዋስው ተጠብቆ እንዲኖር አስችሏል። ትክክለኛውን የታሂቲ ቋንቋ ለመማር ምንጊዜም ወደ መጽሐፍ ቅዱስ መመለስ አስፈላጊ ይሆናል” ብለዋል። እነዚህ ተርጓሚዎች ደከመኝ ሰለቸኝ ሳይሉ ያከናወኑት ሥራ በሺህ የሚቆጠሩ ቃላትን ተረስተው እንዳይቀሩ አድርጓል። ከመቶ ዓመት በኋላ አንድ ደራሲ “ኖት የተረጎመው አስደናቂ የታሂቲ መጽሐፍ ቅዱስ ከታሂቲ የሥነ ጽሑፍ ሥራዎች ሁሉ ታላቁ ነው። በዚህ የማይስማማ ሰው የለም” ብለዋል።

ይህ አስፈላጊ የሆነ ሥራ የጠቀመው የታሂቲን ሕዝቦች ብቻ አይደለም። ለሌሎች የደቡባዊ ፓስፊክ ቋንቋዎች የትርጉም ሥራዎችም በመነሻነት አገልግሏል። ለምሳሌ የኩክና የሳሞአ ደሴቶች ተርጓሚዎች በናሙናነት ተጠቅመውበታል። አንድ ተርጓሚ “ሙሉ በሙሉ ለማለት እችላለሁ፣ የተከተልኩት በጥንቃቄ መርምሬው የነበረውን የሚስተር ኖትን ትርጉም ነው” ብለዋል። ሌላ ተርጓሚ ደግሞ ‘ከዳዊት መዝሙሮች አንዱን ወደ ሳሞአ’ የተረጎሙት ‘የዕብራይስጡን የመዝሙር መጽሐፍ እንዲሁም የእንግሊዝኛውንና የታሂቲውን ትርጉም’ እያስተያዩ እንደሆነ ተዘግቧል።

የታሂቲ ሚስዮናውያን የእንግሊዙን የንቃት እንቅስቃሴ አባላት ምሳሌ በመከተል መሠረተ ትምህርትን ለማስተማሩ ሥራ ከፍተኛ ቦታ ሰጥተዋል። እንዲያውም ለአንድ ምዕተ ዓመት ያህል የታሂቲ ሕዝብ ከታሂቲ መጽሐፍ ቅዱስ ሌላ ምንም ዓይነት መጽሐፍ አላገኘም ነበር። ስለዚህ በታሂቲ ባሕል ውስጥ ዋነኛ ቦታ ነበረው።

ከኖት የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉም ጥሩ ገጽታዎች አንዱ መለኮታዊው ስም በብዙ ቦታዎች መገኘቱ ነው። ከዚህም የተነሣ ዛሬ የይሖዋ ስም በታሂቲና በደሴቶቿ በሚገባ ሊታወቅ ችሏል። በአንዳንድ የፕሮቴስታንት አብያተ ክርስቲያናት ሳይቀር ይታያል። ይሁን እንጂ የአምላክ ስም በአሁኑ ጊዜ የሚታወቀው ከይሖዋ ምሥክሮችና ከስብከት እንቅስቃሴያቸው ጋር ተያይዞ ነው። በኖትና በተባባሪዎቹ በተተረጎመው የታሂቲ መጽሐፍ ቅዱስም በስፋት ይጠቀማሉ። እንደ ሄንሪ ኖት ያሉ ተርጓሚዎች ያሳለፉት ልፋትና ድካም ዛሬ አብዛኛው የሰው ልጅ የአምላክን ቃል በቀላሉ ለማግኘት ስላስቻለው በእጅጉ አመስጋኞች ልንሆን እንደሚገባን ያሳስበናል።

[በገጽ 26 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

የይሖዋ ስም የሚገኝበት የመጀመሪያው የታሂቲ መጽሐፍ ቅዱስ፣ 1815

የታሂቲ መጽሐፍ ቅዱስ ዋነኛ ተርጓሚ ሄንሪ ኖት (1774-1844)

[ምንጭ]

የታሂቲ መጽሐፍ ቅዱስ:- Copyright the British Library (3070.a.32)፤ ሄንሪ ኖት እና ደብዳቤው:- Collection du Musée de Tahiti et de ses Îles, Punaauia, Tahiti; catechism: With permission of the London Missionary Society Papers, Alexander Turnbull Library, Wellington, New Zealand

[በገጽ 28 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

የአምላክ ስም የሚገኝበት የታሂቲና የዌልሽ ቋንቋዎች የሃይማኖት ማስተማሪያ፣ 1801

[ምንጭ]

With permission of the London Missionary Society Papers, Alexander Turnbull Library, Wellington, New Zealand

[በገጽ 29 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

የይሖዋ ስም ከፊት ለፊት የተጻፈበት በሁዋሂኔ ደሴት በፍሬንች ፖሊኔዥያ የሚገኝ የፕሮቴስታንት ቤተ ክርስቲያን

[ምንጭ]

Avec la permission du Pasteur Teoroi Firipa