“እግዚአብሔር ፍቅር ነው”
“እግዚአብሔር ፍቅር ነው”
“ፍቅር የሌለው እግዚአብሔርን አያውቅም፣ እግዚአብሔር ፍቅር ነውና።”—1 ዮሐንስ 4:8
1-3. (ሀ) መጽሐፍ ቅዱስ ስለ ይሖዋ ፍቅር ምን ይላል? ይህን አባባል ልዩ የሚያደርገው ምንድን ነው? (ለ) መጽሐፍ ቅዱስ “እግዚአብሔር ፍቅር ነው” የሚለው ለምንድን ነው?
ሁሉም የይሖዋ ባሕርያት ወደር የማይገኝላቸው፣ ፍጹምና ማራኪ ናቸው። ሆኖም ከይሖዋ ባሕርያት መካከል ይበልጥ ማራኪ የሆነው ፍቅር ነው። የፍቅሩን ያህል ወደ እርሱ እንድንቀርብ የሚገፋፋን ሌላ ባሕርይ የለም። ደስ የሚለው ደግሞ ፍቅር የይሖዋ ዋነኛ ባሕርይ መሆኑ ነው። ይህን እንዴት እናውቃለን?
2 መጽሐፍ ቅዱስ ስለ ሌሎቹ የይሖዋ ባሕርያት የማይናገረው ስለ ፍቅር ግን የሚናገረው አንድ ነገር አለ። ቅዱሳን ጽሑፎች አምላክ ኃይል ነው ወይም አምላክ ፍትሕ ነው ወይም አምላክ ጥበብ ነው አይሉም። ይሖዋ እነዚህ ባሕርያት አሉት። እርሱ የእነዚህ ባሕርያት የመጨረሻው ከፍተኛ ምንጭ ነው። ስለ ፍቅር ግን በ1 ዮሐንስ 4:8 ላይ ጥልቀት ያለው ሐሳብ ተገልጿል። ጥቅሱ ‘እግዚአብሔር ፍቅር ነው’ ይላል። አዎን፣ ይሖዋ ሁለንተናው ፍቅር ነው። ፍቅር የይሖዋ ዋነኛው መለያ ባሕርይ ነው። በጥቅሉ እንዲህ ብለን ልናስብ እንችላለን:- የይሖዋ ኃይል አንድ ነገር እንዲያከናውን ያስችለዋል። አንድን ጉዳይ ለማከናወን ፍትሑንና ጥበቡን ይጠቀማል። ፍቅሩ ግን አንድ ዓይነት እርምጃ እንዲወስድ ያነሳሳዋል። ሌሎቹን ባሕርያቱን የሚጠቀምባቸው ፍቅሩን በሚያንጸባርቅ መንገድ ነው።
3 ብዙውን ጊዜ ይሖዋ የፍቅር ተምሳሌት እንደሆነ ተደርጎ ይነገራል። በመሆኑም ስለ ፍቅር ለማወቅ ከፈለግን ስለ ይሖዋ መማራችን የግድ ነው። እንግዲያው ወደር የማይገኝለትን የይሖዋ ፍቅር አንዳንድ ገጽታዎች እንመርምር።
ከሁሉ የላቀው የፍቅር መግለጫ
4, 5. (ሀ) በታሪክ ዘመናት ከታዩት የፍቅር መግለጫዎች በሙሉ አቻ የማይገኝለት የትኛው ነው? (ለ) በይሖዋ አምላክና በልጁ መካከል ያለው ፍቅር ከሁሉ የላቀ ነው የምንለው ለምንድን ነው?
4 ይሖዋ ፍቅሩን በተለያዩ መንገዶች አሳይቷል። ፍቅሩ የታየበት አንደኛው መንገድ ግን ከሁሉም የሚበልጥ ነው። ይህ ምንድን ነው? ይሖዋ ልጁን በመላክ ለእኛ ብሎ እንዲሠቃይና እንዲሞት ማድረጉ ነው። እንዲያውም ይህ ድርጊት በታሪክ ዘመናት ከታዩት የፍቅር መግለጫዎች ሁሉ አቻ የማይገኝለት ነው ብለን በእርግጠኝነት መናገር እንችላለን። እንዲህ የምንለው ለምንድን ነው?
5 መጽሐፍ ቅዱስ ኢየሱስን “ከፍጥረት ሁሉ በፊት በኵር” ብሎ ይጠራዋል። (ቆላስይስ 1:15) እስቲ አስበው፣ የይሖዋ ልጅ ግዑዙ ጽንፈ ዓለም ከመፈጠሩ በፊትም በሕይወት ነበር። ታዲያ አባትና ልጅ አብረው የኖሩት ለምን ያህል ጊዜ ነው? አንዳንድ ሳይንቲስቶች አጽናፈ ዓለም የ13 ቢልዮን ዓመታት ዕድሜ እንዳለው ይገምታሉ። ይህ ግምት ትክክል ነው ብንል እንኳ የይሖዋን የበኩር ልጅ ዕድሜ ይህን ያህል ብቻ ነው ብሎ መናገር አይቻልም። ኢየሱስ በእነዚህ ሁሉ ዓመታት ምን ይሠራ ነበር? “ዋና ሠራተኛ” በመሆን አባቱን በደስታ ያገለግል ነበር። (ምሳሌ 8:30፤ ዮሐንስ 1:3) ይሖዋና ኢየሱስ ሌሎች ነገሮችን ለመፍጠር በአንድነት ሠርተዋል። እንዴት ያለ አስደሳች ጊዜ አሳልፈው ይሆን! በዚህን ያህል ረጅም ጊዜ ውስጥ ምን ያህል የጠበቀ ወዳጅነት ሊመሠርቱ እንደሚችሉ መረዳት አዳጋች ይሆንብናል። በግልጽ ማየት እንደሚቻለው በይሖዋ አምላክና በልጁ መካከል ያለው ፍቅር አለ ከሚባል ከማንኛውም ፍቅር የላቀ ነው።
6. ኢየሱስ በተጠመቀ ጊዜ ይሖዋ ስለ ልጁ የነበረውን ስሜት የገለጸው እንዴት ነው?
6 ያም ሆኖ ይሖዋ ልጁ ሰው ሆኖ እንዲወለድ ወደ ምድር ላከው። ይህም ለሦስት አሥርተ ዓመታት ያህል በጣም ከሚወደው ልጁ ጋር ተለያይቶ መኖር ጠይቆበታል። ይሖዋ ሰማይ ሆኖ ፍጹም ሰው የነበረውን የኢየሱስን እድገት በትኩረት ይከታተል ነበር። ኢየሱስ 30 ዓመት ሲሆነው ተጠመቀ። በዚህ ጊዜ አባቱ ከሰማይ ሆኖ “በእርሱ ደስ የሚለኝ የምወደው ልጄ ይህ ነው” በማለት ተናገረ። (ማቴዎስ 3:17) ኢየሱስ በትንቢት የተነገረውንና እንዲያደርግ የሚጠበቅበትን በሙሉ በታማኝነት ሲያከናውን ሲመለከት አባቱ ምንኛ ተደስቶ ይሆን!—ዮሐንስ 5:36፤ 17:4
7, 8. (ሀ) ኒሳን 14, 33 እዘአ ኢየሱስ ምን ደረሰበት? ይህስ ሰማያዊ አባቱ ምን እንዲሰማው አድርጓል? (ለ) ይሖዋ ልጁ እንዲሠቃይና እንዲሞት የፈቀደው ለምንድን ነው?
7 ይሁን እንጂ፣ ኒሳን 14, 33 እዘአ ይሁዳ ኢየሱስን አሳልፎ ሲሰጠው እንዲሁም ጠላቶቹ ሲያፌዙበት፣ ሲተፉበትና ሲጎስሙት ይሖዋ ምን ያህል ተሰምቶት ይሆን? ጀርባው እስኪተለተል ሲገረፍ፣ እጅና እግሩ በእንጨት ላይ በምስማር ሲቸነከርና ተሰቅሎ እያለ አላፊ አግዳሚው ሲሰድበው አባቱ ምን ተሰምቶት ይሆን? በጣም የሚወደው ልጁ በጭንቀት እያጣጣረ ወደ እርሱ ሲጮህ፣ የመጨረሻውን እስትንፋሱን ስቦ በሞት ሲያንቀላፋ ማለትም ከተፈጠረበት ጊዜ ጀምሮ ለመጀመሪያ ጊዜ ከህልውና ውጪ ሲሆን ይሖዋ እንዴት ተሰምቶት ይሆን?—ማቴዎስ 26:14-16, 46, 47, 56, 59, 67፤ 27:26, 38-44, 46፤ ዮሐንስ 19:1
8 ይሖዋ ስሜት ያለው እንደመሆኑ መጠን ልጁ ሲሞት የተሰማው ሥቃይ በቃላት ልንገልጸው ከምንችለው በላይ ነው። ልንገልጸው የምንችለው ነገር ቢኖር፣ ይሖዋ ይህ ሁሉ በልጁ ላይ እንዲደርስ የፈቀደበትን ውስጣዊ ግፊት ብቻ ነው። አብ እንዲህ ያለው ሥቃይ በራሱ ላይ እንዲደርስ የፈቀደው ለምንድን ነው? ይሖዋ በዮሐንስ 3:16 ላይ አንድ አስደናቂ ሐሳብ ገልጦልናል። ይህ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅስ ካዘለው ከፍተኛ ቁምነገር የተነሳ የወንጌል ጭብጥ ተብሎ ይጠራል። ጥቅሱ እንዲህ ይላል:- “በእርሱ የሚያምን ሁሉ የዘላለም ሕይወት እንዲኖረው እንጂ እንዳይጠፋ እግዚአብሔር አንድያ ልጁን እስኪሰጥ ድረስ ዓለሙን እንዲሁ ወዶአልና።” ስለዚህ አምላክ ይህን እርምጃ እንዲወስድ የገፋፋው ፍቅር ነው። ይህ ከዚህ ቀደም ከታዩት የፍቅር መግለጫዎች ሁሉ የላቀ ነው።
ይሖዋ እንደሚወደን ያረጋገጠልን እንዴት ነው?
9. ሰይጣን፣ ይሖዋ ለእኛ ባለው አመለካከት ረገድ ምን ብለን እንድናስብ ይፈልጋል? ይሁን እንጂ ይሖዋ ምን ማረጋገጫ ሰጥቶናል?
9 ይሁን እንጂ አምላክ በግለሰብ ደረጃ ይወደናልን? የሚል ጥያቄ ይነሳል። አንዳንዶች ዮሐንስ 3:16 እንደሚለው አምላክ የሰውን ዘር በአጠቃላይ እንደሚወድ ይቀበሉ ይሆናል። ይህን ሲሉ ‘አምላክ እኔን በግለሰብ ደረጃ አይወደኝም’ ብለው የሚናገሩ ያህል ነው። ሰይጣን፣ ይሖዋ አይወደኝም እንዲሁም ከቁብ አይቆጥረኝም ብለን እንድናስብ ይፈልጋል። ሆኖም እኛ እንደማንወደድ ወይም በእርሱ ፊት ዋጋ እንደሌለን አድርገን ብናስብም እንኳ ይሖዋ እያንዳንዱ ታማኝ አገልጋዩ በእርሱ ዘንድ ከፍተኛ ዋጋ እንዳለው ማረጋገጫ ሰጥቶናል።
10, 11. ኢየሱስ ስለ ድንቢጦች የተናገረው ምሳሌ በይሖዋ ፊት ዋጋ እንዳለን የሚያሳየው እንዴት ነው?
10 ለምሳሌ ያህል፣ ኢየሱስ በማቴዎስ 10:29-31 ላይ ምን እንዳለ ተመልከት። ኢየሱስ ደቀ መዛሙርቱ ምን ያህል ዋጋ እንዳላቸው በምሳሌ ሲያስረዳ እንዲህ አለ:- “ሁለት ድንቢጦች በአምስት ሳንቲም ይሸጡ የለምን? ከእነርሱም አንዲቱ ያለ አባታችሁ ፈቃድ በምድር ላይ አትወድቅም። የእናንተስ የራሳችሁ ጠጉር እንኳ ተቈጥሮአል። እንግዲህ አትፍሩ፤ ከብዙ ድንቢጦች እናንተ ትበልጣላችሁ።” እነዚህ ቃላት በመጀመሪያው መቶ ዘመን ለነበሩት የኢየሱስ አድማጮች ምን ትርጉም እንደነበራቸው እንመርምር።
11 ኢየሱስ በኖረበት ዘመን ድንቢጥ ለምግብነት ከሚሸጡት ወፎች በሙሉ በጣም ርካሿ ነበረች። አንድ ሰው አነስተኛ መጠን ባለው አምስት ሳንቲም ሁለት ድንቢጦች መግዛት ይችል ነበር። ሆኖም ኢየሱስ ቆየት ብሎ ሉቃስ 12:6, 7 ላይ እንደተናገረው አንድ ሰው በአሥር ሳንቲም አራት ድንቢጦች ሳይሆን አምስት ድንቢጦች መግዛት ይችል ነበር። አንዷ ድንቢጥ ምንም ዋጋ የሌላት ይመስል ምራቂ ተደርጋ ትሰጣለች። በምርቃት መልክ የሚሰጡት ወፎች በሰዎች ዘንድ ምንም ዋጋ እንደሌላቸው ተደርገው ይታዩ ይሆናል። ፈጣሪስ የሚያያቸው እንዴት ነው? ኢየሱስ “ከእነርሱም አንዲቱ ስንኳ [በምርቃት የምትሰጠውም ብትሆን] በእግዚአብሔር ፊት አትረሳም” ብሏል። አሁን ኢየሱስ ምን ለማለት እንደፈለገ ግልጽ ሳይሆንልን አይቀርም። ይሖዋ አንዲትን ድንቢጥ ይህን ያህል ከፍ አድርጎ የሚመለከታት ከሆነ የሰው ልጅማ ምን ያህል ከፍ ያለ ቦታ ይኖረው! ኢየሱስ እንደተናገረው ይሖዋ በደንብ ያውቀናል። ሌላው ቀርቶ የራሳችን ፀጉር እንኳ የተቆጠረ ነው!
12. ኢየሱስ የራሳችን ፀጉር የተቆጠረ እንደሆነ ሲናገር ማጋነኑ እንዳልነበረ እርግጠኞች መሆን የምንችለው ለምንድን ነው?
12 አንዳንዶች ኢየሱስ እዚህ ላይ እንዳጋነነ ይሰማቸው ይሆናል። እስቲ ስለ ትንሣኤ ለአንድ አፍታ አስብ። ይሖዋ እኛን ዳግመኛ የሚፈጥረን ምን ያህል ቢያውቀን እንደሆነ መገመት ትችላለህ! ከፍ አድርጎ የሚመለከተን በመሆኑ ውስብስብ በሆነው ጂናችን ውስጥ የሚገኘውን ኮድና በሕይወት ዘመናችን ያካበትናቸውን ትዝታዎች እንዲሁም ተሞክሮዎች ጨምሮ እያንዳንዱን ዝርዝር ያስታውሳል። ከዚህ አንጻር ሲታይ በአማካይ 100, 000 የሚሆነውን ፀጉራችንን መቁጠር ለእርሱ በጣም ቀላል ነው። እነዚህ የኢየሱስ ቃላት ይሖዋ በግለሰብ ደረጃ ስለ እያንዳንዳችን እንደሚያስብ ማረጋገጫ ይሰጡናል።
13. ፍጹማን ባንሆንም እንኳን ይሖዋ በጎ ጎናችንን እንደሚመለከት የንጉሥ ኢዮሣፍጥ ታሪክ የሚያሳየው እንዴት ነው?
13 መጽሐፍ ቅዱስ ይሖዋ እንደሚወደን የሚያረጋግጥልን ሌላ ተጨማሪ ማስረጃም ይሰጠናል። ይሖዋ መልካም ጎናችን ላይ የሚያተኩር ሲሆን ይህንንም ከፍ አድርጎ ይመለከተዋል። ጥሩ ንጉሥ የነበረውን ኢዮሣፍጥን እንደ ምሳሌ እንውሰድ። ንጉሡ የሞኝነት እርምጃ በወሰደ ጊዜ የይሖዋ ነቢይ “ስለዚህም ነገር ከእግዚአብሔር ዘንድ ቁጣ ሆኖብሃል” አለው። እንዴት ያለ ጠንካራ መልእክት ነው! ሆኖም የይሖዋ መልእክት በዚህ ብቻ አላበቃም። ነቢዩ ቀጥሎ “መልካም ነገር ተገኝቶብሃል” አለው። (2 ዜና መዋዕል 19:1-3) የይሖዋ የጽድቅ ቁጣ ኢዮሣፍጥ ያደረገውን “መልካም ነገር” ከመመልከት አላገደውም። ፍጹማን ባንሆንም አምላካችን በጎ ጎናችንን እንደሚመለከት ማወቃችን የሚያጽናና አይደለም?
“ይቅር ባይ” የሆነ አምላክ
14. ኃጢአት ስንሠራ ምን ሊሰማን ይችላል? ሆኖም ይሖዋ ይቅር እንዲለን ምን ማድረግ አለብን?
14 ኃጢአት ስንሠራ የሚሰማን ሐዘን፣ ኃፍረትና የበደለኝነት ስሜት ይሖዋን ለማገልገል ብቁ አይደለሁም ብለን እንድናስብ ሊያደርገን ይችላል። ሆኖም ይሖዋ “ይቅር ባይ” አምላክ መሆኑን መዘንጋት አይኖርብንም። (መዝሙር 86:5) በእርግጥም ንስሐ የምንገባና ኃጢአቱን ላለመድገም ከፍተኛ ጥረት የምናደርግ ከሆነ ይሖዋ ይቅር ይለናል። መጽሐፍ ቅዱስ አስደናቂ ስለሆነው ስለዚህ የይሖዋ ፍቅር መግለጫ ምን እንደሚል እንመልከት።
15. ይሖዋ ኃጢአታችንን ምን ያህል ያርቅልናል?
15 መዝሙራዊው ዳዊት ‘ምሥራቅ ከምዕራብ እንደሚርቅ፣ እንዲሁ ኃጢአታችንን ከእኛ አራቀ’ በማለት የይሖዋን ይቅር ባይነት ሕያው በሆነ መንገድ ገልጾታል። (መዝሙር 103:12) ምሥራቅ ከምዕራብ ምን ያህል ይርቃል? ምሥራቅና ምዕራብ በጣም የተራራቁ በመሆናቸው መቼም ቢሆን ሊገናኙ አይችሉም። አንድ ምሑር ይህ አባባል “መገመት ከምንችለው በላይ የተራራቁ” ማለት እንደሆነ ተናግረዋል። ዳዊት በመንፈስ አነሳሽነት የጻፋቸው ቃላት ይሖዋ ይቅር ሲል ኃጢአታችንን ልናስበው ከምንችለው በላይ እንደሚያርቅልን ያሳዩናል።
16. ይሖዋ አንድ ጊዜ ኃጢአታችንን ይቅር ካለን ከዚያ በኋላ እንደ ንጹህ አድርጎ እንደሚመለከተን እርግጠኛ መሆን የምንችለው ለምንድን ነው?
16 ከነጭ ልብስ ላይ ቆሻሻ ለማስለቀቅ ሞክረህ ታውቃለህ? አንዳንድ ጊዜ የቱንም ያህል ስትፈትገው ብትውል ቆሻሻው ሙሉ በሙሉ አይለቅ ይሆናል። ይሖዋ ይቅር ለማለት ያለውን ችሎታ ምን ብሎ እንደገለጸው ተመልከት:- ‘ኃጢአታችሁ እንደ አለላ ብትሆን እንደ አመዳይ [“በረዶ፣” አ.መ.ት ] ትነጻለች፤ እንደ ደምም ብትቀላ እንደ ባዘቶ ትጠራለች።’ (ኢሳይያስ 1:18) “አለላ” ተብሎ የተተረጎመው “ስካርሌት” የሚለው የእንግሊዝኛ ቃል ደማቅ ቀይ ቀለምን ያመለክታል። a በራሳችን ጥረት የኃጢአትን እድፍ በምንም ዓይነት ማስወገድ አንችልም። ሆኖም ይሖዋ እንደ ደማቅ ቀይ ቀለም እና እንደ ደም የሆነውን ኃጢአታችንን እንደ በረዶ ወይም እንደተባዘተ ጥጥ ሊያነጣው ይችላል። በዚህም ምክንያት ይሖዋ ኃጢአታችንን አንድ ጊዜ ይቅር ካለን በቀሪው ሕይወታችን ሁሉ ከዚህ ኃጢአት እንዳልነጻን ሊሰማን አይገባም።
17. ይሖዋ ኃጢአታችንን ወደ ኋላው ይጥለዋል ሲባል ምን ማለት ነው?
17 ሕዝቅያስ ከያዘው ለሞት የሚያደርስ ሕመም ከተፈወሰ በኋላ ይሖዋን ለማመስገን ባቀናበረው ልብ የሚነካ መዝሙር ላይ ‘ኃጢአቴንም ሁሉ ወደ ኋላህ ጣልህ ’ ብሏል። (ኢሳይያስ 38:17) ይህ አባባል ይሖዋ ንስሐ የገባው በደለኛ የሠራውን ኃጢአት ዳግመኛ ላለማየትና ላለማሰብ ወደ ኋላው እንደሚጥለው የሚያሳይ ነው። አንድ የማመሳከሪያ ጽሑፍ እንደገለጸው ይህ ሐሳብ “[ኃጢአት] እንዳልፈጸምኩ ቆጠርከኝ” ብሎ የመናገር ያህል ነው። ይህ ምንኛ የሚያጽናና ሐሳብ ነው!
18. ነቢዩ ሚክያስ ይሖዋ ይቅር ሲል ኃጢአታችንን እስከ መጨረሻው እንደሚያስወግድልን የጠቆመው እንዴት ነው?
18 ነቢዩ ሚክያስ ስለ መልሶ መቋቋም በተናገረው ትንቢት ላይ ይሖዋ ንስሐ የገቡ ሕዝቦቹን ይቅር እንደሚላቸው ያለውን ትምክህት ሲገልጽ እንዲህ ብሏል:- ‘የርስቱንም ቅሬታ ዓመፅ የሚያሳልፍ እንደ አንተ ያለ አምላክ ማን ነው? . . . ኃጢአታችንንም በባሕሩ ጥልቅ ይጥለዋል።’ (ሚክያስ 7:18, 19) በዚያ ዘመን የነበሩ ሰዎች እነዚህን ቃላት ሲሰሙ ምን እንደሚሰማቸው ማሰብ ትችላለህ። ‘በጥልቅ ባሕር’ ውስጥ የተጣለን ነገር መልሶ ማግኘት ይቻላል? ሚክያስ የተናገራቸው ቃላት ይሖዋ ይቅር በሚልበት ጊዜ ኃጢአታችንን እስከ መጨረሻው እንደሚያስወግድልን ያሳያሉ።
‘ርኅሩኅ የሆነ አምላክ’
19, 20. (ሀ) “ምሕረት ማሳየት” ወይም “አዘኔታ ማሳየት” ተብሎ የተተረጎመው ራቻም የሚለው የዕብራይስጥ ግሥ ትርጉም ምንድን ነው? (ለ) መጽሐፍ ቅዱስ ይሖዋ ርኅሩኅ መሆኑን ለማስተማር ምን ምሳሌ ይጠቀማል?
19 ርኅራኄ ሌላው የይሖዋ ፍቅር መገለጫ ነው። ርኅራኄ ምንድን ነው? መጽሐፍ ቅዱስ በርኅራኄና በምሕረት መካከል የቅርብ ተዛማጅነት እንዳለ ይጠቁማል። በርካታ የዕብራይስጥና የግሪክኛ ቃላት ርኅራኄ የሚለውን ሐሳብ ያስተላልፋሉ። ለምሳሌ ያህል፣ ራቻም የሚለው ቃል ብዙውን ጊዜ “ምሕረት ማሳየት” ወይም “አዘኔታ ማሳየት” ተብሎ ተተርጉሟል። ይሖዋ የራሱን ስሜት ለመግለጽ የተጠቀመበት ይህ የዕብራይስጥ ቃል “ማኅፀን” ከሚለው ቃል ጋር ተዛማጅነት ያለው ሲሆን “የእናት ርኅራኄ” ተብሎ ሊተረጎም ይችላል።
20 መጽሐፍ ቅዱስ ይሖዋ ርኅሩኅ መሆኑን ለማስተማር እናት ለልጅዋ ያላትን ስሜት እንደ ምሳሌ ይጠቀማል። ኢሳይያስ 49:15 እንዲህ ይላል:- “በውኑ ሴት ከማኅፀንዋ ለተወለደው ልጅ እስከማትራራ [ራቻም ] ድረስ ሕፃንዋን ትረሳ ዘንድ ትችላለችን? አዎን፣ እርስዋ ትረሳ ይሆናል፣ እኔ ግን አልረሳሽም።” አንዲት እናት የሚጠባ ልጅዋን ማጥባትና መንከባከብ ትረሳለች ብሎ ማሰብ ይከብዳል። አንድ ሕፃን ልጅ ራሱን መርዳት ስለማይችል ቀን ከሌት የእናቱ እንክብካቤ ያሻዋል። የሚያሳዝነው ግን በተለይ በዚህ ‘አስጨናቂ ዘመን’ እናቶች ልጆቻቸውን ችላ እንዳሉ መስማት የተለመደ እየሆነ መጥቷል። (2 ጢሞቴዎስ 3:1, 3) ሆኖም ይሖዋ “እኔ ግን አልረሳሽም” ብሏል። ለአገልጋዮቹ የሚያሳየው ከልብ የመነጨ ርኅራኄ እናት በተፈጥሮ ለሕፃን ልጅዋ ካላት የርኅራኄ ስሜት በእጅጉ የጠነከረ ነው።
21, 22. የጥንት እስራኤላውያን በግብፅ ባርነት ሳሉ ምን ይደርስባቸው ነበር? ይሖዋ ለጩኸታቸው ምላሽ የሰጠው እንዴት ነው?
21 ይሖዋ ልክ እንደ አፍቃሪ ወላጅ ርኅራኄ የሚያሳየው እንዴት ነው? ይህ ባሕርይ ከጥንት እስራኤላውያን ጋር በነበረው ግንኙነት በግልጽ ታይቷል። በ16ኛው መቶ ዘመን ከዘአበ መገባደጃ ላይ በሚልዮን የሚቆጠሩ እስራኤላውያን በግብፅ ባርነት ሥር ወድቀው ከፍተኛ ጭቆና ይደርስባቸው ነበር። (ዘጸአት 1:11, 14) እስራኤላውያን ጭንቀታቸው ሲበዛ ለእርዳታ ወደ ይሖዋ ጮኹ። የርኅራኄ አምላክ የሆነው ይሖዋ ምን ምላሽ ሰጠ?
22 ይሖዋ በሁኔታው ልቡ ስለተነካ “በግብፅ ያለውን የሕዝቤን መከራ በእውነት አየሁ፣ . . . ጩኸታቸውን ሰማሁ፤ ሥቃያቸውንም አውቄአለሁ” አለ። (ዘጸአት 3:7) ይሖዋ የሕዝቡን መከራ አይቶ ወይም ጩኸታቸውን ሰምቶ ዝም ይላል ብሎ ማሰብ የሚከብድ ነገር ነው። ይሖዋ በሰዎች ላይ የሚደርሰው ችግር የሚሰማው አምላክ ነው። ይህ ባሕርይ ከርኅራኄ ጋር የቅርብ ተዛማጅነት አለው። ይሁን እንጂ ይሖዋ ለሕዝቦቹ በማዘን ብቻ ሳይወሰን እነርሱን ለመርዳት እርምጃ ወስዷል። ኢሳይያስ 63:9 “በፍቅሩና በርኅራኄውም ተቤዣቸው” ይላል። እስራኤላውያንን ‘በጸናች እጅ’ ከግብፅ አወጣቸው። (ዘዳግም 4:34) ከዚያ በኋላ ተአምራዊ በሆነ መንገድ የመገባቸው ከመሆኑም በላይ ፍሬያማ የሆነ ምድር ሰጥቷቸዋል።
23. (ሀ) የመዝሙራዊው ቃላት ይሖዋ በግለሰብ ደረጃ እንደሚያስብልን የሚያረጋግጡልን እንዴት ነው? (ለ) ይሖዋ የሚረዳን በምን መንገዶች ነው?
23 ይሖዋ ለሕዝቡ ርኅራኄ የሚያሳየው በቡድን ደረጃ ብቻ አይደለም። አፍቃሪው አምላካችን በግለሰብ ደረጃም በጥልቅ ያስብልናል። የሚደርስብንን ማንኛውንም ሥቃይና መከራ ይረዳልናል። መዝሙራዊው እንዲህ ብሏል:- “የእግዚአብሔር ዓይኖች ወደ ጻድቃን ጆሮቹም ወደ ጩኸታቸው ናቸውና። እግዚአብሔር ልባቸው ለተሰበረ ቅርብ ነው፣ መንፈሳቸው የተሰበረውንም ያድናቸዋል።” (መዝሙር 34:15, 18) ይሖዋ በግለሰብ ደረጃ የሚረዳን እንዴት ነው? ሥቃይ እንዳይደርስብን ያደርጋል ማለት አይደለም። ለእርዳታ ወደ እርሱ የሚጮኹትን ሰዎች ለመርዳት በርካታ ዝግጅቶች አድርጓል። ቃሉ ትልቅ እገዛ የሚያበረክት ተግባራዊ ምክር ይዟል። በጉባኤ ውስጥ እንደ እርሱ ለሌሎች ርኅራኄ ለማሳየት የሚጥሩ በመንፈሳዊ የጎለመሱ የበላይ ተመልካቾች አሉ። (ያዕቆብ 5:14, 15) ይሖዋ ‘ጸሎት ሰሚ’ አምላክ እንደመሆኑ መጠን ‘ለሚለምኑት መንፈስ ቅዱስን’ ይሰጣቸዋል። (መዝሙር 65:2፤ ሉቃስ 11:13) እነዚህ ሁሉ ዝግጅቶች ‘የአምላካችን ምሕረትና ርኅራኄ’ መግለጫዎች ናቸው።—ሉቃስ 1:78
24. ለይሖዋ ፍቅር ምላሽ መስጠት የምትችለው እንዴት ነው?
24 በሰማይ በሚኖረው አባታችን በይሖዋ ፍቅር ላይ ማሰላሰላችን የሚያስደስት አይደለምን? ቀደም ባለው ርዕስ ውስጥ ይሖዋ ኃይሉን፣ ፍትሑንና ጥበቡን ለእኛው ጥቅም ፍቅራዊ በሆነ መንገድ እንዳንጸባረቀ ተመልክተናል። በዚህ ርዕስ ውስጥ ደግሞ ይሖዋ በአጠቃላይ ለሰው ዘርና በግለሰብ ደረጃ ደግሞ ለእያንዳንዳችን አስደናቂ በሆነ መንገድ ፍቅሩን እንደገለጸ ተምረናል። እያንዳንዳችን ‘ለይሖዋ ፍቅር ምላሽ መስጠት የምችለው እንዴት ነው?’ ብለን ራሳችንን መጠየቅ ይኖርብናል። ይሖዋን በፍጹም ልብህ፣ ሐሳብህ፣ ነፍስህና ኃይልህ ውደደው። (ማርቆስ 12:29, 30) በየዕለቱ ሕይወትህን የምትመራበት መንገድ ወደ ይሖዋ ይበልጥ ለመቅረብ ልባዊ ፍላጎት እንዳለህ የሚያሳይ ይሁን። ፍቅር የሆነው አምላክ ወደ አንተ እንዲቀርብ ምኞታችን ነው።—ያዕቆብ 4:8
[የግርጌ ማስታወሻ]
a አንድ ምሑር እንደተናገሩት ስካርሌት “የማይለቅ ቀለም ነው። ጤዛ፣ ዝናብ፣ ተደጋጋሚ እጥበት ወይም ለረጅም ጊዜ ጥቅም ላይ መዋሉ ቀለሙን አያስለቅቀውም።”
ታስታውሳለህን?
• ፍቅር የይሖዋ ዋነኛ ባሕርይ መሆኑን በምን እናውቃለን?
• ይሖዋ ልጁን ልኮ እንዲሠቃይና እንዲሞት መፍቀዱ እስከ ዛሬ ከታዩት የፍቅር መግለጫዎች ሁሉ የላቀ ነው የምንለው ለምንድን ነው?
• ይሖዋ በግለሰብ ደረጃ እንደሚወደን ያረጋገጠልን እንዴት ነው?
• መጽሐፍ ቅዱስ ይሖዋ ይቅር ባይ መሆኑን በግልጽ ለማስረዳት በየትኞቹ ምሳሌዎች ተጠቅሟል?
[የአንቀጾቹ ጥያቄዎች]
[በገጽ 15 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
‘አምላክ አንድያ ልጁን ሰጥቷል’
[በገጽ 16, 17 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
“ከብዙ ድንቢጦች እናንተ ትበልጣላችሁ”
[ምንጭ]
© J. Heidecker/VIREO
[በገጽ 18 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
እናት ለልጅዋ ያላት ስሜት ስለ ይሖዋ ርኅራኄ ያስተምረናል