በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

“የነበረብኝን የባዶነት ስሜት አስወግዶልኛል”

“የነበረብኝን የባዶነት ስሜት አስወግዶልኛል”

“የነበረብኝን የባዶነት ስሜት አስወግዶልኛል”

አንዲት የይሖዋ ምሥክር “ቀናተኛ የመንግሥቱ አዋጅ ነጋሪዎች” በሚል ርዕስ በ2002/03 በተደረገው የአውራጃ ስብሰባ ላይ ስለወጣው ባለ 320 ገጽ መጽሐፍ እንዲህ የሚል አስተያየት ሰጥታለች:- “ ወደ ይሖዋ ቅረቡ የተባለውን ግሩም መጽሐፍ አዘጋጅታችሁ ስለሰጣችሁን ከልብ አመሰግናችኋለሁ። የነበረብኝን የባዶነት ስሜት አስወግዶልኛል፤ ይሖዋ እንደሚወደኝና ከፍ አድርጎ እንደሚመለከተኝ እንዲሰማኝ አድርጎኛል። አሁን ከይሖዋና ከውድ ልጁ ጋር ይበልጥ እንደተቀራረብኩ ይሰማኛል። ስለዚህ መጽሐፍ ለሰው ሁሉ ብናገርና መጽሐፉን ለምወዳቸው ሁሉ ብሰጥ ደስ ይለኛል።” የዚህን አዲስ መጽሐፍ አንዳንድ ገጽታዎችና መጽሐፉ የተዘጋጀበትን ዓላማ እንመልከት።

የአዲሱ መጽሐፍ አንዳንድ ገጽታዎች

ይህ አዲስ መጽሐፍ በውስጡ ምን ይዞልናል? በዚህ መጽሔት ሁለት የጥናት ርዕሶች ውስጥ የሚገኙትን ትምህርቶችና ሌሎች ተጨማሪ ሐሳቦችን ይዟል! መጽሐፉ 31 ምዕራፎች ያሉት ሲሆን እያንዳንዱ ምዕራፍ በመጠበቂያ ግንብ ላይ የሚጠናውን ክፍል የሚያህል ርዝመት አለው። ከመቅድሙና ከመጀመሪያዎቹ ሦስት ምዕራፎች በኋላ መጽሐፉ አራት ክፍሎች ያሉት ሲሆን እያንዳንዱ ክፍል ከአራቱ ዋና ዋና የይሖዋ ባሕርያት መካከል በአንዱ ላይ ያተኩራል። እያንዳንዱ ክፍል ስለ አንዱ ባሕርይ ጠቅለል ያለ ሐሳብ በሚሰጥ ምዕራፍ ይጀምራል። ከዚያም ቀጣዮቹ ምዕራፎች ይሖዋ ይህን ባሕርይ እንዴት እንዳንጸባረቀ ያብራራሉ። በተጨማሪም እያንዳንዱ ክፍል ስለ ኢየሱስ የሚናገር አንድ ምዕራፍ አለው። ለምን? ኢየሱስ “እኔን ያየ አብን አይቶአል” በማለት ተናግሯል። (ዮሐንስ 14:​9) ኢየሱስ የይሖዋ ፍጹም ነጸብራቅ እንደመሆኑ የአምላክ ባሕርያት በእርሱ ላይ ሕያው በሆነ መንገድ ተንጸባርቀዋል። እያንዳንዱ ክፍል በውስጡ የተብራራውን ባሕርይ በማንጸባረቅ ረገድ ይሖዋን እንዴት ልንመስለው እንደምንችል በሚያስተምር ምዕራፍ ይደመደማል። ይህ አዲስ መጽሐፍ ስለ ይሖዋ ባሕርያት ማብራሪያ በሚሰጥበት ጊዜ ከሁሉም የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍሎች ይጠቅሳል።

ወደ ይሖዋ ቅረቡ የተባለው ይህ አዲስ መጽሐፍ ሌሎች ገጽታዎችም አሉት። ከምዕ ራፍ 2 ጀምሮ በሁሉም ምዕራፎች ውስጥ “ለማሰላሰል የሚረዱ ጥያቄዎች” የሚል ርዕስ ያለው ሣጥን ይገኛል። በሣጥኖቹ ውስጥ ያሉት ጥቅሶችና ጥያቄዎች ምዕራፉን ለመከለስ ተብለው የቀረቡ አይደሉም። ከዚህ ይልቅ በመጽሐፍ ቅዱስ ተጠቅመህ በርዕሰ ትምህርቱ ላይ በጥልቀት እንድታሰላስል ለመርዳት ታስበው የተዘጋጁ ናቸው። እያንዳንዱን ጥቅስ በጥንቃቄ እንድታነብብ ሐሳብ እናቀርብልሃለን። ከዚያም በጥያቄው ላይ በማሰላሰል በግል ሕይወትህ በሥራ ላይ ለማዋል ጥረት አድርግ። በዚህ መንገድ ማሰላሰልህ ወደ ይሖዋ ይበልጥ እንድትቀርብ ይገፋፋሃል።​—⁠መዝሙር 19:14

ወደ ይሖዋ ቅረቡ የተባለው መጽሐፍ ታስቦባቸው የተዘጋጁ ትምህርት ሰጪና ለሥራ የሚያንቀሳቅሱ ሥዕላዊ መግለጫዎችንም አካትቷል። አሥራ ሰባቱ ምዕራፎች የመጽሐፍ ቅዱስ ታሪኮችን የሚያሳዩ ሙሉ ገጽ የሚሸፍኑ ማራኪ ሥዕላዊ መግለጫዎች ይዘዋል።

መጽሐፉ የተዘጋጀበት ዓላማ

ወደ ይሖዋ ቅረቡ የተባለው መጽሐፍ የተዘጋጀው ለምንድን ነው? ይህ መጽሐፍ የተዘጋጀበት ዋነኛ ዓላማ ይሖዋን ይበልጥ አውቀነው ከእርሱ ጋር ጠንካራ የሆነ የግል ዝምድና መመሥረት እንድንችል መርዳት ነው።

ወደ ይሖዋ ቅረቡ የተባለውን መጽሐፍ ቢያነብ ሊጠቀም ይችላል ብለህ የምታስበው የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ወይም በመንፈሳዊ የደከመ ክርስቲያን ይኖር ይሆናል። አንተስ ይህንን አዲስ መጽሐፍ ማንበብ ጀምረሃል? ካልሆነ ይህንን መጽሐፍ ለማንበብ አሁኑኑ ለምን ፕሮግራም አታወጣም? ባነበብከው ላይ ለማሰላሰል ጊዜ መድብ። ይህ አዲስ መጽሐፍ ወደ ይሖዋ አምላክ ይበልጥ እንድትቀርብና የመንግሥቱን ምሥራች በከፍተኛ ደስታና ቅንዓት እንድታውጅ የሚረዳህ እንዲሆን እንመኛለን!