የአንባቢያን ጥያቄዎች
የአንባቢያን ጥያቄዎች
በዕብራውያን 2:14 ላይ ሰይጣን “በሞት ላይ ሥልጣን” እንዳለው ተደርጎ የተገለጸው ለምንድን ነው?
በአጭሩ ጳውሎስ እንዲህ ሲል ሰይጣን በቀጥታ ወይም ወኪሎቹን በመጠቀም ሰዎች እንዲሞቱ ማድረግ ይችላል ማለቱ ነበር። ኢየሱስም ከዚህ ጋር በሚስማማ መንገድ ሰይጣን “ከመጀመሪያ ነፍሰ ገዳይ ነበረ” በማለት ተናግሯል።—ዮሐንስ 8:44
አንዳንድ ትርጉሞች ዕብራውያን 2:14ን ሰይጣን “በሞት ላይ ሥልጣን” ወይም “በሞት ላይ ኃይል” እንዳለው አድርገው ስለተረጎሙት ጥቅሱን በትክክል መረዳት ሊያስቸግር ይችላል። (የ1954 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ፣ አዲሱ መደበኛ ትርጉም፣ ኪንግ ጄምስ ቨርሽን፣ ጀሩሳሌም ባይብል) እንዲህ ዓይነቱ አተረጓጎም ሰይጣን የፈለገውን የመግደል ያልተገደበ ችሎታ ያለው ሊያስመስል ይችላል። ይሁን እንጂ ለማለት የተፈለገው እንደዚያ እንዳልሆነ ግልጽ ነው። ምክንያቱም ሰይጣን እንዲህ የማድረግ ችሎታ ቢኖረው ኖሮ የይሖዋን አምላኪዎች ገና ድሮ ከምድር ገጽ ጠራርጎ አጥፍቷቸው ነበር።—ዘፍጥረት 3:15
በአንዳንድ ትርጉሞች ላይ “በሞት ላይ ሥልጣን ያለው” በአዲሲቱ ዓለም ትርጉም ላይ ደግሞ “የመግደል ችሎታ ያለው” ተብሎ የተተረጎመው የግሪክኛ ሐረግ “ክራቶስ ቱ ታናቱ” የሚል ነው። ቱ ታናቱ “ሞት” ማለት ሲሆን ክራቶስ ደግሞ “ኃይል፣ አቅም፣ ችሎታ” ማለት ነው። ቲኦሎጂካል ዲክሽነሪ ኦቭ ዘ ኒው ቴስታመንት ቃሉ “ኃይል ወይም አቅም መኖሩን እንጂ ይህን ኃይል መጠቀምን አያመለክትም” በማለት ይናገራል። በዚህ መሠረት ጳውሎስ በዕብራውያን 2:14 ላይ ሰይጣን በሞት ላይ ፍጹም ሥልጣን አለው ማለቱ ሳይሆን ሰዎችን የመግደል ችሎታ ወይም ብቃት እንዳለው መግለጹ ነበር።
ሰይጣን ሰዎችን የመግደል ችሎታውን የሚጠቀምበት እንዴት ነው? በኢዮብ መጽሐፍ ውስጥ ጥሩ ምሳሌ ሊሆን የሚችል አንድ ታሪክ ይገኛል። ዘገባው ሰይጣን በአውሎ ነፋስ ተጠቅሞ የኢዮብ ልጆች እንዲሞቱ እንዳደረገ ይናገራል። ይሁን እንጂ አምላክ ባይፈቅድለት ኖሮ ሰይጣን እንዲህ ማድረግ እንደማይችልና አምላክ የፈቀደለትም ለአንድ ወሳኝ ጥያቄ መፍትሔ ለማስገኘት እንደሆነ ልብ በል። (ኢዮብ 1:12, 18, 19) ደግሞም ሰይጣን ኢዮብን መግደል አልተፈቀደለትም ነበር። (ኢዮብ 2:6) ምንም እንኳ አንዳንድ ጊዜ ሰይጣን ታማኝ የሆኑ የሰው ልጆች እንዲሞቱ ያደረገ ቢሆንም በፈለገ ጊዜ ሊያጠፋን እንደሚችል በማሰብ መፍራት እንደሌለብን ይህ ታሪክ ያስገነዝበናል።
ሰይጣን ሰብዓዊ ወኪሎቹን በመጠቀምም ሰዎችን ያስገድላል። በዚህም የተነሳ በርካታ ክርስቲያኖች በእምነታቸው ምክንያት የሞቱ ሲሆን አንዳንዶቹ በዓመፀኞች እጅ ወይም በመንግሥት ባለ ሥልጣናትና ፍትሕን በሚያዛቡ ዳኞች ትእዛዝ ያለ አግባብ ተገድለዋል።—ራእይ 2:13
በተጨማሪም ሰይጣን አንዳንድ ጊዜ ሰብዓዊ ድክመትን በመጠቀም ሰዎች እንዲሞቱ ያደርጋል። በእስራኤል ዘመን ነቢዩ በለዓም እስራኤላውያን “እግዚአብሔርን ይበድሉ ዘንድ” እንዲያስቷቸው ሞዓባውያንን መክሯቸው ነበር። (ዘኍልቍ 31:16) በዚህም ምክንያት ከ23, 000 የሚበልጡ እስራኤላውያን ሕይወታቸውን አጥተዋል። (ዘኍልቍ 25:9፤ 1 ቆሮንቶስ 10:8) ዛሬም በተመሳሳይ አንዳንዶች በሰይጣን “ሽንገላ” በመታለል የሥነ ምግባር ብልግና ወይም ሌሎች ኃጢአቶችን ይፈጽማሉ። (ኤፌሶን 6:11) እንዲህ የሚያደርጉ ሰዎች ወዲያውኑ ሕይወታቸውን እንደማያጡ የታወቀ ነው። ሆኖም ለዘላለም በሕይወት የመኖር ተስፋቸውን ስለሚያጡ ሰይጣን ሕይወታቸውን አሳጥቷቸዋል ሊባል ይችላል።
ሰይጣን ጉዳት ሊያስከትልብን እንደሚችል ብናውቅም ለእርሱ ከልክ ያለፈ ፍርሃት ሊያድርብን አይገባም። ጳውሎስ ሰይጣን ሰዎችን የመግደል ችሎታ እንዳለው ከጠቆመ በኋላ ክርስቶስ ‘[ሰይጣንን] በሞት ለመሻር፣ . . . በሕይወታቸውም ሁሉ ስለ ሞት ፍርሃት በባርነት ይታሰሩ የነበሩትን ሁሉ ነጻ ለማውጣት’ እንደሞተ ተናግሯል። (ዕብራውያን 2:14, 15) አዎን፣ ኢየሱስ ቤዛውን በመክፈል በእርሱ የሚያምኑ የሰው ልጆችን ከኃጢአትና ከሞት ባርነት ነጻ አውጥቷቸዋል።—2 ጢሞቴዎስ 1:10
ሰይጣን ሰዎችን የመግደል ችሎታ ያለው መሆኑ ሊያሳስበን እንደሚችል የታወቀ ቢሆንም ሰይጣንና ወኪሎቹ በሕዝቦቹ ላይ የሚያደርሱትን ማንኛውንም ጉዳት ይሖዋ ማስተካከል እንደሚችል ሙሉ እምነት አለን። ከሞት የተነሳው ኢየሱስ ‘የዲያብሎስን ሥራ እንደሚያፈርስ’ ይሖዋ ማረጋገጫ ሰጥቶናል። (1 ዮሐንስ 3:8) ኢየሱስ ከይሖዋ ባገኘው ኃይል ተጠቅሞ ሙታንን የሚያስነሳ ሲሆን ሞትንም ያስወግዳል። (ዮሐንስ 5:28, 29) ከዚያም ሰይጣንን ወደ ጥልቁ በመጣል አቅሙ ውስን እንደሆነ ያጋልጣል። በመጨረሻም ለዘላለም ያጠፋዋል።—ራእይ 20:1-10