ፍቅር መተኪያ የለውም
ፍቅር መተኪያ የለውም
ዕድሜ፣ ባሕል፣ ቋንቋ ወይም ዘር ሳይል ሁሉም ሰው ፍቅርን ይሻል። የሰው ልጅ ይህ ፍላጎቱ ካልተሟላለት ደስተኛ ሊሆን አይችልም። አንድ የሕክምና ተመራማሪ እንዲህ በማለት ጽፈዋል፦ “ፍቅር ስናጣ እንታመማለን፣ ፍቅር ስናገኝ ጤናማ እንሆናለን፤ ፍቅር ስናጣ እናዝናለን፣ ፍቅር ስናገኝ እንደሰታለን፤ ፍቅር ስናጣ እንሠቃያለን፣ ፍቅር ስናገኝ እንፈወሳለን። አንድ ሐኪም ለሁሉም በሽታ ፍቱን የሆነ መድኃኒት ቢያገኝ ለበሽተኞቹ እንደሚያዝዝ የታወቀ ነው። ይህን መድኃኒት ሳያዝዝ ቢቀር የሞያ ግዴታውን እንዳልተወጣ ተደርጎ ይታያል።”
ሆኖም ዛሬ ያለው ኅብረተሰብ በተለይም የመገናኛ ብዙኃንና ታዋቂ ሰዎች ከፍተኛ ግምት የሚሰጡት ለሰዎች እጅግ አስፈላጊ ለሆነው ለፍቅር ሳይሆን ለሃብት፣ ለሥልጣን፣ ለዝናና ለፆታ ነው። ብዙ ምሁራን የአንድ ሰው ስኬታማነት የሚለካው በኑሮ ደረጃው ነው ብለው ስለሚያስቡ ሰዎች አንድ ደረጃ ላይ ለመድረስ እንዲፍጨረጨሩ ያበረታታሉ። መማርና ተሰጥዖን ማዳበር ስህተት ባይሆንም አንድ ሰው ከቤተሰቡና ከጓደኞቹ ጋር አብሮ ለመሆን የሚያስችለው ጊዜ እስኪያጣ ድረስ በእነዚህ ነገሮች መጠመድ ይኖርበታልን? የተማረና የሰዎችን ባሕርይ ጥሩ አድርጎ የሚያውቅ አንድ የጥንት ጸሐፊ የተፈጥሮ ችሎታ የታደለን ሆኖም ፍቅር የሌለውን ሰው ‘ከሚጮኽ ናስ ወይም ከሚንሽዋሽዋ ጸናጽል’ ጋር አመሳስሎታል። (1 ቆሮንቶስ 13:1) እንደነዚህ ያሉ ሰዎች ሃብታም አልፎ ተርፎም ዝነኛ ሊሆኑ ይችላሉ። ሆኖም በፍጹም ደስተኛ ሊሆኑ አይችሉም።
ሰዎችን ጥሩ አድርጎ የሚያውቀውና ለሰዎች ልዩ ፍቅር ያለው ኢየሱስ ክርስቶስ ትምህርቱ በዋነኝነት ያተኮረው ለአምላክና ለሰዎች ፍቅር በማሳየት ላይ ነበር። እንዲህ ሲል ተናግሯል፦ “ጌታ አምላክህን በፍጹም ልብህ በፍጹም ነፍስህም በፍጹም አሳብህም ውደድ። . . . ባልንጀራህን እንደ ነፍስህ ውደድ።” (ማቴዎስ 22:37-39) በእርግጥም እውነተኛ የኢየሱስ ተከታዮች ይህንን መመሪያ የሚከተሉ ብቻ ናቸው። ስለሆነም “እርስ በርሳችሁ ፍቅር ቢኖራችሁ፣ ደቀ መዛሙርቴ እንደ ሆናችሁ ሰዎች ሁሉ በዚህ ያውቃሉ” በማለት ተናግሯል።—ዮሐንስ 13:35
ታዲያ አንድ ሰው ፍቅር በሌለው በዚህ ዓለም ውስጥ እየኖረ ፍቅርን ማዳበር የሚችለው እንዴት ነው? እንዲሁም ወላጆች ለልጆቻቸው ፍቅርን ማስተማር የሚችሉት እንዴት ነው? የሚከተለው ርዕስ ለእነዚህ ጥያቄዎች መልስ ይሰጣል።
[በገጽ 3 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ስግብግብነት በተጠናወተው በዚህ ዓለም ውስጥ ፍቅርን ማዳበር አስቸጋሪ ነው