ሌሎች በእርግጥ ያስፈልጉናል?
ሌሎች በእርግጥ ያስፈልጉናል?
ታዋቂው ሳይንቲስት አልበርት አንስታይን “ሕይወታችንንና የምናደርጋቸውን ጥረቶች ልብ ብለን ስንመለከት ድርጊቶቻችንና ፍላጎቶቻችን በሙሉ ማለት ይቻላል ከሌሎች ሰዎች ሕልውና ጋር የተቆራኙ መሆናቸውን መገንዘብ አያዳግተንም” በማለት ተናግሮ ነበር። አክሎም እንዲህ ብሏል:- “ሌሎች ያመረቱትን እንመገባለን፣ ሌሎች የሰፉትን እንለብሳለን እንዲሁም ሌሎች በሠሩት ቤት ውስጥ እንኖራለን። . . . አንድ ሰው ከልደት እስከ ሞት ድረስ ሰብዓዊም ሆነ መንፈሳዊ ሕልውናው የተመሠረተበት የሰፊው ሰብዓዊ ኅብረተሰብ አካል እስካልሆነ ድረስ በግሉ ምንም ፋይዳ የለውም።”
እንስሳት በደመነፍስ እርስ በርስ ሲተጋገዙ መመልከት የተለመደ ነው። ዝሆኖች ልጆቻቸውን በትኩረት እየተከታተሉ በመንጋ ይንቀሳቀሳሉ። ሴት አንበሶች በኅብረት ያድኑና ግዳያቸውን ለወንዶቹ ያካፍላሉ። ዶልፊኖች አንድ ላይ ሆነው የሚጫወቱ ከመሆኑም በላይ አደጋ ላይ የወደቁ ሌሎች እንስሳትን ወይም ዋናተኞችን ከሞት ይታደጋሉ።
የሰው ልጆችን በተመለከተ ግን ከጊዜ ወደ ጊዜ አሳሳቢ እየሆነ የመጣ አንድ አዝማሚያ እንዳለ የማኅበራዊ ሳይንስ ባለሞያዎች አስተውለዋል። በሜክሲኮ የሚታተም አንድ ጋዜጣ እንደዘገበው አንዳንድ ሳይንቲስቶች “ለብዙ አሥርተ ዓመታት የዘለቀው ራስን የማግለል አዝማሚያና የማኅበራዊ ኑሮ መሠረት መናጋት በአሜሪካ ሕዝብ ላይ ከፍተኛ ጉዳት አስከትሏል” የሚል አመለካከት አላቸው። ጋዜጣው “የአገሪቱ ደኅንነት የተመካው ሥር ነቀል ማኅበራዊ ለውጥ በማድረግ ላይ ሲሆን ይህም ማኅበራዊ ኑሮን መልሶ መገንባትን ይጨምራል” በማለት ገልጿል።
ይህ ችግር በተለይ በበለጸጉት አገሮች ውስጥ ሥር ሰድዶ ይታያል። ራስን ከሌሎች የማግለል አዝማሚያ በፍጥነት በመስፋፋት ላይ ይገኛል። ሰዎች ‘የራሳቸውን ሕይወት ለመኖር’ የሚፈልጉ ከመሆኑም በላይ ‘ማንም እንዲደርስባቸው አይፈልጉም።’ እንዲህ ያለው ዝንባሌ ሰብዓዊውን ኅብረተሰብ ለስሜታዊ ችግሮች፣ ለመንፈስ ጭንቀት ብሎም ራስን ለመግደል እንደዳረገው ተገልጿል።
ዳንኤል ጎልማን የተባሉ ዶክተር ይህን አስመልክተው እንዲህ ብለዋል:- “ከማኅበራዊ ኑሮ መገለል በሌላ አነጋገር ውስጣዊ ስሜትን የሚያጋሩትም ሆነ አብረው ጊዜ የሚያሳልፉት ሰው አለማግኘት በበሽታ የመጠቃትንና የመሞትን አጋጣሚ በእጥፍ ያሳድገዋል።” ሳይንስ በተባለ መጽሔት ላይ የወጣ አንድ ዘገባ ከማኅበራዊ ኑሮ ራስን ማግለል ‘የሚያስከትለው ጉዳት እንደ ማጨስ፣ የደም ግፊት፣ የኮሌስትሮል መጨመር፣ ከልክ በላይ መወፈርና አካላዊ እንቅስቃሴ አለማድረግ ከመሳሰሉት ሞት የሚያስከትሉ ችግሮች ጋር ይተካከላል’ በማለት ደምድሟል።
እንግዲያው፣ በእርግጥ ሌሎች ያስፈልጉናል የምንልበት በርካታ ምክንያቶች አሉን። ሰው ያለ ሰው መኖር አይችልም። ታዲያ ከማኅበራዊ ኑሮ የመገለልን ችግር ማስወገድ የሚቻለው እንዴት ነው? ብዙዎች ሕይወታቸው እውነተኛ ትርጉም ያለው እንዲሆን የረዳቸው ምንድን ነው? የሚቀጥለው ርዕስ ለእነዚህ ጥያቄዎች መልስ ይሰጣል።
[በገጽ 3 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
“ድርጊቶቻችንና ፍላጎቶቻችን በሙሉ ማለት ይቻላል ከሌሎች ሰዎች ሕልውና ጋር የተቆራኙ” ናቸው።—አልበርት አንስታይን