በትዕግሥት ‘የመጠበቅ’ ዝንባሌ አለህ?
በትዕግሥት ‘የመጠበቅ’ ዝንባሌ አለህ?
“የእግዚአብሔርን ቀን መምጣት እየጠበቃችሁና እያስቸኰላችሁ፣ በቅዱስ ኑሮ እግዚአብሔርንም በመምሰል እንደ ምን ልትሆኑ ይገባችኋል?”—2 ጴጥሮስ 3:11, 12
1, 2. የይሖዋን ቀን በትዕግሥት ‘የመጠበቅን’ አስፈላጊነት እንዴት በምሳሌ ማስረዳት እንችላለን?
ለእራት የጋበዟቸውን እንግዶች በጉጉት የሚጠባበቁ የአንድ ቤተሰብ አባላትን በዓይነ ሕሊናህ ለመመልከት ሞክር። እንግዶቹ የሚመጡበት ሰዓት እየተቃረበ ነው። ሚስትዬዋ የቀሩትን ነገሮች ለመጨራረስ ሽር ጉድ ትላለች። ባለቤቷና ልጆቻቸውም ሁሉም ነገር ቦታ ቦታውን መያዙን ለማረጋገጥ ወዲያ ወዲህ እያሉ ነው። ሁሉም ለጉዳዩ ትኩረት ሰጥተዋል። አዎን፣ መላው ቤተሰብ እንግዶቹ መጥተው ጣፋጭ የሆነውን ምግብ አብረው ለመመገብና ከእነርሱ ጋር በመጫወት አስደሳች ጊዜ ለማሳለፍ በጉጉት እየጠበቀ ነው።
2 ክርስቲያኖች እንደመሆናችን መጠን ከዚህ ይበልጥ ትልቅ ቦታ የሚሰጠው ነገር እንጠብቃለን። ይህ ምንድን ነው? ‘የይሖዋ ቀን’ ነዋ! ያ ቀን እስኪመጣ ድረስ “እኔ ግን እግዚአብሔርን ተስፋ አደርጋለሁ፤ አዳኜ የሆነውን አምላክ እጠብቃለሁ” ሲል የተናገረው የነቢዩ ሚክያስ ዓይነት ዝንባሌ መያዝ ይኖርብናል። (ሚክያስ 7:7 አ.መ.ት) እንዲህ ሲባል እጅ አጣጥፎ መጠበቅ ማለት ነውን? በፍጹም። ብዙ የምንሠራው ነገር አለ።
3. በ2 ጴጥሮስ 3:11, 12 መሠረት ክርስቲያኖች ምን ዓይነት ዝንባሌ ሊኖራቸው ይገባል?
3 ሐዋርያው ጴጥሮስ የይሖዋን ቀን ስንጠብቅ ትክክለኛ ዝንባሌ እንዲኖረን የሚረዳ ምክር ሰጥቶናል። “የእግዚአብሔርን ቀን መምጣት እየጠበቃችሁና እያስቸኰላችሁ፣ በቅዱስ ኑሮ እግዚአብሔርንም በመምሰል እንደ ምን ልትሆኑ ይገባችኋል?” ብሏል። (2 ጴጥሮስ 3:11, 12) እዚህ ላይ ጴጥሮስ እንዴት ዓይነት ሰዎች መሆን እንዳለብን ጥያቄ እያቀረበ እንዳልሆነ ልብ ማለት ይገባል። በአምላክ መንፈስ አነሳሽነት በጻፋቸው ሁለት ደብዳቤዎች ላይ ክርስቲያኖች እንዴት ዓይነት ሰዎች መሆን እንዳለባቸው ገልጿል። ከዚህም በላይ “በቅዱስ ኑሮ እግዚአብሔርንም በመምሰል” እንዲመላለሱ አሳስቧቸዋል። ኢየሱስ ክርስቶስ “የዓለም መጨረሻ” ምልክት የሚሆኑትን ነገሮች ከነገራቸው 30 ዓመታት ያለፉ ቢሆንም ክርስቲያኖች ጊዜውን በንቃት መጠበቃቸውን መቀጠል ነበረባቸው። (ማቴዎስ 24:3) የይሖዋን ቀን መምጣት ‘እየጠበቁና እያስቸኰሉ’ መኖር ይገባቸው ነበር።
4. ‘የይሖዋን ቀን መምጣት ማስቸኰል’ ሲባል ምን ማለት ነው?
4 የይሖዋን ቀን ቃል በቃል ‘ማስቸኰል’ እንደማንችል የታወቀ ነው። ሌላው ቀርቶ ኢየሱስ ክርስቶስ የአባቱን ጠላቶች ለማጥፋት የሚመጣበትን ‘ቀንና ሰዓት አናውቅም።’ (ማቴዎስ 24:36፤ 25:13) “እያስቸኰላችሁ” የሚለው ቃል የተመሠረተበት ግስ በዚህ አገባቡ “ማጣደፍ” የሚል ትርጉም ያለው ሲሆን ይህም “‘ቅንዓት ከማሳየት፣ ንቁ ከመሆን፣ ለአንድ ነገር ትኩረት ከመስጠት’ ጋር በጣም የተዛመደ እንደሆነ” አንድ የማመሳከሪያ ጽሑፍ ይናገራል። በመሆኑም ጴጥሮስ የእምነት ባልንጀሮቹ የይሖዋን ቀን መምጣት በከፍተኛ ጉጉት እንዲጠብቁ ማሳሰቡ ነበር። ይህን ማድረግ የሚችሉት ምንጊዜም ቀኑን በአእምሯቸው በመያዝ ነው። (2 ጴጥሮስ 3:11, 12) “ታላቁና የሚያስፈራው የእግዚአብሔር ቀን” በጣም በቀረበበት በአሁኑ ወቅት እኛም ተመሳሳይ አስተሳሰብ ሊኖረን ይገባል።—ኢዩኤል 2:31
“በቅዱስ ኑሮ” እየተመላለሱ መጠበቅ
5. ‘የይሖዋን ቀን’ በከፍተኛ ጉጉት እንደምንጠብቅ ማሳየት የምንችለው እንዴት ነው?
5 የይሖዋን ቀን በሕይወት የማለፍ ከፍተኛ ጉጉት ካለን ይህንን “በቅዱስ ኑሮ እግዚአብሔርንም በመምሰል” በተጨባጭ እናሳያለን። “በቅዱስ ኑሮ” የሚለው አገላለጽ የሚከተለውን የጴጥሮስን ምክር ያስታውሰን ይሆናል:- “እንደሚታዘዙ ልጆች ባለማወቃችሁ አስቀድሞ የኖራችሁበትን ምኞት አትከተሉ። ዳሩ ግን:- እኔ ቅዱስ ነኝና ቅዱሳን ሁኑ ተብሎ ስለ ተጻፈ የጠራችሁ ቅዱስ እንደ ሆነ እናንተ ደግሞ በኑሮአችሁ ሁሉ ቅዱሳን ሁኑ።”—1 ጴጥሮስ 1:14-16
6. ቅዱስ ለመሆን ምን ማድረግ አለብን?
6 ቅዱስ ለመሆን አካላዊ፣ አእምሯዊ፣ ሥነ ምግባራዊና መንፈሳዊ ንጽሕናችንን መጠበቅ አለብን። በይሖዋ ስም የምንጠራ ግለሰቦች እንደመሆናችን መጠን ቅድስናችንን በመጠበቅ ‘ለይሖዋ ቀን’ እየተዘጋጀን ነው? የዓለም የሥነ ምግባር የአቋም ደረጃ ከጊዜ ወደ ጊዜ እያሽቆለቆለ በመሆኑ በዛሬው ጊዜ እንዲህ ዓይነት ንጽሕና ጠብቆ መኖር ቀላል አይደለም። (1 ቆሮንቶስ 7:31፤ 2 ጢሞቴዎስ 3:13) የሥነ ምግባር አቋምን በተመለከተ በእኛና በዓለም መካከል ያለው ልዩነት እየሰፋ ነውን? ካልሆነ ጉዳዩን ልናስብበት ይገባል። የግል የአቋም ደረጃችን ዓለም ከሚከተለው የላቀ ቢሆንም እንኳ ከጊዜ ወደ ጊዜ እያሽቆለቆለ ይሆን? ሁኔታው እንደዚህ ከሆነ አምላክን ለማስደሰት እንድንችል አቋማችንን ለማስተካከል እርምጃ መውሰድ ይኖርብናል።
7, 8. (ሀ) ‘በቅዱስ ኑሮ’ የመመላለስን አስፈላጊነት ልንዘነጋ የምንችለው እንዴት ነው? (ለ) አቋማችንን ለማስተካከል ምን እርምጃ መውሰድ ይኖርብናል?
7 ወሲባዊ ሥዕሎች በኢንተርኔት የሚቀርቡ በመሆኑና ማንም ሳያውቅ መመልከት ስለሚቻል ከዚህ ቀደም እንዲህ ዓይነት ከሥነ ምግባር ውጪ የሆነ ነገር የማግኘት አጋጣሚ ያልነበራቸው አንዳንዶች አሁን “በወሲብ ዙሪያ የሚቀርቡ ነገሮችን በገፍ” እንደሚያገኙ አንድ የሕክምና ዶክተር ተናግረዋል። እንደነዚህ ያሉት ወራዳ ድርጊቶች የሚተላለፉባቸውን የኢንተርኔት ሥርጭቶች የምንመለከት ከሆነ “ርኩስን ነገር አትንኩ” የሚለውን የመጽሐፍ ቅዱስ ትእዛዝ እየጣስን መሆኑ ግልጽ ነው። (ኢሳይያስ 52:11) በእርግጥ ‘የይሖዋን ቀን መምጣት እያስቸኰልን’ ነው ማለት ይቻላል? ወይስ ርካሽ በሆኑ ነገሮች አእምሯችንን እያቆሸሽነው ቢሆንም ንጹሕ አቋም ለመያዝ በቂ ጊዜ አለን በሚል ቀኑን በሐሳባችን አርቀነው ይሆን? በዚህ ረገድ ድክመት ካለብን ‘ከንቱ ነገርን ከማየት ዓይኖቻችንን እንዲመልስና በመንገዱ ሕያው እንዲያደርገን’ ይሖዋን መማጸናችን እጅግ አጣዳፊ ነው!—መዝሙር 119:37
8 ወጣቶችም ሆኑ አረጋውያን አብዛኞቹ የይሖዋ ምሥክሮች ከፍ ያሉትን የአምላክ የሥነ ምግባር የአቋም ደረጃዎች በመጠበቅ ከዚህ ዓለም የብልግና ማባበያዎች ርቀዋል። የጊዜያችንን አጣዳፊነት በመገንዘብና ጴጥሮስ ‘የጌታ ቀን እንደ ሌባ ሆኖ ይመጣል’ ሲል የሰጠውን ማስጠንቀቂያ በመከተል ‘በቅዱስ ኑሮ’ መመላለሳቸውን ይቀጥላሉ። (2 ጴጥሮስ 3:10) ድርጊታቸው ‘የይሖዋን ቀን መምጣት እንደሚጠብቁና እንደሚያስቸኩሉ’ ያረጋግጣል። a
‘እግዚአብሔርን በመምሰል’ እየተመላለሱ መጠበቅ
9. ለአምላክ የማደር ባሕርይ ምን እንድናደርግ ሊያነሳሳን ይገባል?
9 የይሖዋ ቀን ከአእምሯችን እንዳይጠፋ ለማድረግ ‘አምላክን በመምሰል’ ይኸውም ለአምላክ ያደርን በመሆን መኖራችንም በጣም አስፈላጊ ነው። ለአምላክ ያደሩ መሆን ለአምላክ አክብሮታዊ ፍርሃት ማሳየትን የሚጨምር ሲሆን ይህም እርሱን የሚያስደስተውን ነገር እንድናደርግ ይገፋፋናል። ከይሖዋ ጋር በታማኝነት መጣበቃችን ለአምላክ ያደርን መሆናችንን የሚያሳዩ ድርጊቶች እንድንፈጽም ያነሳሳናል። ይሖዋ ‘ሰዎች ሁሉ እንዲድኑና እውነቱን ወደ ማወቅ እንዲደርሱ’ ይፈልጋል። (1 ጢሞቴዎስ 2:3, 4) አምላክ ‘ሁሉ ወደ ንስሐ እንዲደርሱ እንጂ ማንም እንዲጠፋ’ አይፈልግም። (2 ጴጥሮስ 3:9) እንግዲያው ለአምላክ ማደራችን ሰዎች ስለ ይሖዋ እንዲማሩና እርሱን እንዲመስሉ በመርዳት ረገድ የበለጠ እንድንሠራ ሊያነሳሳን አይገባምን?—ኤፌሶን 5:1
10. ‘በባለጠግነት ላለመታለል’ መጠንቀቅ የሚኖርብን ለምንድን ነው?
10 የአምላክን መንግሥት የምናስቀድም ከሆነ ለአምላክ ያደርን መሆናችንን የሚያሳዩ ድርጊቶችን እንፈጽማለን። (ማቴዎስ 6:33) ይህም ለቁሳዊ ነገሮች ሚዛናዊ አመለካከት መያዝን ይጨምራል። ኢየሱስ “የሰው ሕይወት በገንዘቡ ብዛት አይደለምና ተጠንቀቁ፣ ከመጐምጀትም ሁሉ ተጠበቁ” የሚል ማሳሰቢያ ሰጥቷል። (ሉቃስ 12:15) በፍቅረ ነዋይ ልንታወር እንደምንችል ማሰቡ የማይሆን ነገር ሊመስል ቢችልም ‘የዚህ ዓለም አሳብና የባለጠግነት መታለል ’ የአምላክን ‘ቃል ሊያንቅ’ እንደሚችል ልብ ማለታችን ተገቢ ነው። (ማቴዎስ 13:22) መተዳደሪያ ማግኘት ቀላል ላይሆን ይችላል። በዚህም ምክንያት በአንዳንድ አገሮች ብዙዎች ሕይወታቸውን ለማሻሻል ምናልባትም ለተወሰኑ ዓመታት ከቤተሰባቸው ተለይተው ወደ በለጸጉ አገሮች መሄድ እንዳለባቸው ይሰማቸዋል። አንዳንድ የአምላክ አገልጋዮችም እንዲህ ዓይነት አመለካከት አላቸው። ወደ ሌላ አገር በመሄዳቸው ቤተሰባቸው ዘመናዊ ዕቃዎች እንዲኖረው ማድረግ ይችሉ ይሆናል። ይሁን እንጂ የቤተሰባቸው መንፈሳዊ ሁኔታስ? ቤት ውስጥ ተገቢውን አመራር የሚሰጥ የቤተሰብ ራስ ከሌለ የይሖዋን ቀን በሕይወት ለማለፍ የሚያስችል መንፈሳዊ አቋም መያዝ ይችላሉ?
11. ሥራ ፍለጋ ወደ ሌላ አገር የሄደ አንድ ሰው ከገንዘብ ይልቅ ለአምላክ የማደር ባሕርይ ይበልጥ አስፈላጊ መሆኑን በተግባር ያሳየው እንዴት ነው?
11 ሥራ ፍለጋ ከፊሊፒንስ ወደ ጃፓን የሄደ አንድ ሰው እዚያ እያለ የመጽሐፍ ቅዱስን እውነት ከይሖዋ ምሥክሮች ተማረ። የቤተሰብ ራስ መሆን ምን ቅዱስ ጽሑፋዊ ኃላፊነቶች እንደሚያስከትል ሲያውቅ ቤተሰቡ የይሖዋ አምላኪዎች እንዲሆኑ የመርዳት ግዴታ እንዳለበት ተገነዘበ። (1 ቆሮንቶስ 11:3) በፊሊፒንስ የምትኖረው ባለቤቱ አዲስ የያዘውን እምነት አጥብቃ ተቃወመች፤ ቤተሰቡን መጽሐፍ ቅዱስ ለማስተማር ወደ አገሩ ከመመለስ ይልቅ እዚያው ሆኖ ገንዘብ እንዲልክላቸው ፈልጋ ነበር። እርሱ ግን የጊዜውን አጣዳፊነት ስለተገነዘበና የቤተሰቡ ሁኔታ ስላሳሰበው ወደ አገሩ ተመለሰ። የቤተሰቡን አባላት ፍቅራዊ በሆነ መንገድ በትዕግሥት መርዳቱ ወሮታ አስገኝቶለታል። ከጊዜ በኋላ ቤተሰቡ እውነተኛውን አምልኮ የተቀበለ ከመሆኑም በላይ ባለቤቱ የሙሉ ጊዜ አገልግሎት ጀመረች።
12. በሕይወታችን ውስጥ ለመንፈሳዊ ጉዳዮች ቅድሚያ መስጠት ያለብን ለምንድን ነው?
12 ያለንበት ሁኔታ በእሳት እየጋየ ባለ ሕንፃ ውስጥ ከሚገኙ ሰዎች ጋር ሊመሳሰል ይችላል። ሊወድቅ ከተቃረበው ሕንፃ ውስጥ አንዳንድ ዕቃዎችን ለማትረፍ መሯሯጡ ጥበብ ይሆናልን? ከዚህ ይልቅ የራሳችንን፣ የቤተሰባችንንና በሕንፃው ውስጥ ያሉትን የሌሎች ሰዎች ሕይወት ማዳኑ ይበልጥ የተሻለ አይሆንም? ከዚህ ባልተለየ ይህ ክፉ ሥርዓት በፍጥነት ወደ ጥፋት እያመራ ሲሆን የብዙዎች ሕይወት አደጋ ላይ ወድቋል። ይህንን በመገንዘብ ለመንፈሳዊ ነገሮች ቅድሚያ መስጠትና ሕይወት አድን በሆነው የመንግሥቱ ስብከት ሥራ በቅንዓት መካፈል እንዳለብን የተረጋገጠ ነው።—1 ጢሞቴዎስ 4:16
“ያለ ነውር” መሆን አለብን
13. የይሖዋ ቀን ሲጀምር ምን ዓይነት አቋም ይዘን መገኘት እንፈልጋለን?
13 ጴጥሮስ “ወዳጆች ሆይ፣ ይህን እየጠበቃችሁ ያለ ነውርና ያለ ነቀፋ ሆናችሁ በሰላም [በአምላክ] እንድትገኙ ትጉ” በማለት በትዕግሥት የመጠበቅን አስፈላጊነት አበክሮ ገልጿል። (2 ጴጥሮስ 3:14) በቅዱስ ኑሮ እንድንመላለስና ለአምላክ ያደርን እንድንሆን ከማሳሰብ በተጨማሪ በይሖዋ ዘንድ በኢየሱስ ክቡር ደም ነጽቶ የመገኘትን አስፈላጊነት ጎላ አድርጎ ገልጿል። (ራእይ 7:9, 14) ይህም አንድ ሰው በኢየሱስ መሥዋዕት ላይ እምነት እንዲያሳድርና ራሱን ወስኖ የተጠመቀ የይሖዋ አገልጋይ እንዲሆን ይጠይቅበታል።
14. “ያለ ነውር” መሆን ምን ነገሮችን ያጠቃልላል?
14 ጴጥሮስ “ያለ ነውር” ሆነን ለመገኘት የምንችለውን ሁሉ እንድናደርግ አሳስቦናል። ክርስቲያናዊ ምግባራችንንና ማንነታችንን የሚያመለክተው ምሳሌያዊ ልብሳችን ከቆሻሻ የጸዳ እንዲሆን ይኸውም ዓለም እንዳይበክልብን ጥረት እያደረግን ነውን? በልብሳችን ላይ ትንሽ ቆሻሻ ብንመለከት ወዲያውኑ ለማጽዳት የቻልነውን እናደርጋለን። በተለይ ደግሞ በጣም የምንወደው ልብስ ከሆነ በከፍተኛ ጥንቃቄ እናጸዳዋለን። በባሕርያችን ወይም በምግባራችን ላይ አንድ ዓይነት ጉድለት በመኖሩ ምክንያት በምሳሌያዊ አነጋገር ክርስቲያናዊ ልብሳችን ከቆሸሸ ተመሳሳይ ስሜት ይሰማናል?
15. (ሀ) እስራኤላውያን በልብሳቸው ጫፍ ዘርፍ እንዲያደርጉ የታዘዙት ለምን ነበር? (ለ) ዛሬ ያሉት የይሖዋ አገልጋዮች ከዓለም ተለይተው የሚታዩት ለምንድን ነው?
15 እስራኤላውያን “በልብሳቸው ጫፍ ዘርፍ ያደርጉ ዘንድ፣ በዘርፉም ሁሉ ላይ ሰማያዊ ፈትል ያደርጉ ዘንድ” ታዝዘው ነበር። ለምን? የይሖዋን ትእዛዛት እንዲያስቡና እንዲያከብሩ እንዲሁም ለአምላካቸው ‘ቅዱሳን መሆን’ እንዲችሉ ነው። (ዘኍልቍ 15:38-40) በዚህ ዘመን የምንኖረው የይሖዋ አገልጋዮችም የአምላክን ሕግጋትና መሠረታዊ ሥርዓቶች ስለምናከብር ከዓለም የተለየን ነን። ለምሳሌ ያህል ሥነ ምግባራዊ ንጽሕናችንን እንጠብቃለን፣ የደምን ቅድስና እናከብራለን እንዲሁም ከማንኛውም ዓይነት የጣዖት አምልኮ እንርቃለን። (ሥራ 15:28, 29) ራሳችንን ከማንኛውም እድፍ ለመጠበቅ ያደረግነው ቁርጥ ውሳኔ በብዙዎች ዘንድ አክብሮት አትርፎልናል።—ያዕቆብ 1:27
“ያለ ነቀፋ” መሆን አለብን
16. “ያለ ነቀፋ” መኖር ምን ነገሮችን ያጠቃልላል?
16 ጴጥሮስ “ያለ ነቀፋ” ሆነን መገኘት እንዳለብንም ተናግሯል። ይህን ማድረግ የምንችለው እንዴት ነው? ቆሻሻን ለማመልከት የገባው ነውር የሚለው ቃል በአብዛኛው ሊጠረግ ወይም ሊጸዳ የሚችልን ነገር የሚያመለክት ሲሆን ‘ነቀፋ’ የሚለው ቃል ግን በዚህ አገባቡ ለማስለቀቅ ይበልጥ አስቸጋሪ የሆነን ቆሻሻ ያመለክታል። ቃሉ አንድ ነገር ሥር የሰደደ እንከን ወይም ጉድለት እንዳለበት ይጠቁማል። ሐዋርያው ጳውሎስ በፊልጵስዩስ የነበሩ ክርስቲያን ባልንጀሮቹን እንዲህ በማለት መክሯቸዋል:- “በመጥፎና በጠማማ ትውልድ መካከል ያለ ነቀፋ የዋሆችም ነውርም የሌለባቸው የእግዚአብሔር ልጆች እንድትሆኑ ሳታንጐራጒሩ ክፉም ሳታስቡ [“ሳትከራከሩ፣” አ.መ.ት] ሁሉን አድርጉ፤ በእነርሱም መካከል . . . በዓለም እንደ ብርሃን ትታያላችሁ።” (ፊልጵስዩስ 2:14, 15) ይህንን ምክር ተግባራዊ ካደረግን ከማጉረምረምና ከክርክር እንርቃለን እንዲሁም አምላክን የምናገለግለው በንጹሕ ውስጣዊ ግፊት ተነሳስተን ይሆናል። ‘የመንግሥቱን ወንጌል’ ለመስበክ የሚገፋፋን ለይሖዋና ለሰዎች ያለን ፍቅር ይሆናል። (ማቴዎስ 22:35–40፤ 24:14) ከዚህም በላይ አብዛኞቹ ሰዎች ሌሎችን ስለ አምላክና ስለ ቃሉ ስለ መጽሐፍ ቅዱስ ለማስተማር ጊዜያችንን በፈቃደኝነት የምንሠዋው ለምን እንደሆነ ባይገባቸውም ምሥራቹን ማወጃችንን እንቀጥላለን።
17. በክርስቲያን ጉባኤ ውስጥ መብት ለማግኘት የምንጣጣር ከሆነ ውስጣዊ ግፊታችን ምን መሆን አለበት?
17 “ያለ ነቀፋ” ሆነን ለመገኘት ስለምንፈልግ በምናደርገው ሁሉ ውስጣዊ ግፊታችን ምን እንደሆነ መመርመራችን የተገባ ነው። ዓለም በራስ ወዳድነት ስሜት እንደ ሃብትና ሥልጣን የመሳሰሉ ነገሮችን ለማግኘት የሚያደርገውን ጥረት መከተል አቁመናል። በክርስቲያን ጉባኤ ውስጥ የአገልግሎት መብት ለማግኘት ጥረት እያደረግን ከሆነ ምንጊዜም ለይሖዋና ለሰዎች ባለን ፍቅር በንጹሕ ውስጣዊ ግፊት መነሳሳት ይኖርብናል። ይሖዋንና የእምነት ባልንጀሮቻቸውን ለማገልገል በፈቃደኝነትና በትሕትና መንፈስ የበላይ ተመልካች ለመሆን የሚጣጣሩ ጥሩ መንፈሳዊ አቋም ያላቸው ወንዶች ማየታችን ያስደስተናል። (1 ጢሞቴዎስ 3:1፤ 2 ቆሮንቶስ 1:24) በእርግጥም ሽማግሌ ለመሆን ብቃቱን የሚያሟሉ ወንዶች “በእናንተ ዘንድ ያለውን የእግዚአብሔርን መንጋ [በውድ] ጠብቁ፤ . . . በበጎ ፈቃድ እንጂ መጥፎውን ረብ በመመኘት ሳይሆን ጐብኙት፤ ለመንጋው ምሳሌ ሁኑ እንጂ ማኅበሮቻችሁን በኃይል አትግዙ” የሚለውን ምክር ተግባራዊ ያደርጋሉ።—1 ጴጥሮስ 5:1-4
‘ሰላማውያን’ መሆን አለብን
18. የይሖዋ ምሥክሮች በየትኞቹ ባሕርያት ተለይተው ይታወቃሉ?
18 በመጨረሻም ጴጥሮስ “በሰላም” እንድንገኝ መክሮናል። ይህንን ብቃት ለማሟላት ከይሖዋና ከሰዎች ጋር ሰላማዊ ግንኙነት ሊኖረን ይገባል። ጴጥሮስ ‘እርስ በርስ አጥብቆ የመዋደድንና’ ከክርስቲያን ባልንጀሮቻችን ጋር በሰላም የመኖርን አስፈላጊነት ጎላ አድርጎ ገልጿል። (1 ጴጥሮስ 2:17፤ 3:10, 11፤ 4:8፤ 2 ጴጥሮስ 1:5-7) ሰላማችንን ጠብቀን ለመኖር እርስ በርሳችን መዋደድ ይኖርብናል። (ዮሐንስ 13:34, 35፤ ኤፌሶን 4:1, 2) በተለይ ብሔራት አቀፍ ስብሰባዎች በምናደርግባቸው ወቅቶች እርስ በርስ ያለን ፍቅርና ሰላም ጎልቶ ይታያል። በ1999 በኮስታ ሪካ የአውራጃ ስብሰባ በተካሄደበት ወቅት በአገሪቱ የሚኖሩ የይሖዋ ምሥክሮች አውሮፕላን ማረፊያ ተገኝተው ለስብሰባው የመጡ ልዑካንን ሲቀበሉ የአንድን ነጋዴ የገበያ ቦታ ሳያውቁ ስለሸፈኑበት ሰውዬው ተናደደ። በሁለተኛው ቀን ግን በአገሪቱ የሚኖሩት ምሥክሮች በግል ባያውቋቸውም እንኳ ለልዑካኑ በሚያደርጉላቸው ሞቅ ያለ አቀባበል የሚንጸባረቀውን ፍቅርና ሰላም አስተዋለ። በመጨረሻው ቀን ነጋዴው ከምሥክሮቹ ጋር በመሆን ለእንግዶቹ አቀባበል ያደረገላቸው ሲሆን መጽሐፍ ቅዱስ እንዲያስጠኑትም ጠይቋል።
19. ከእምነት ባልንጀሮቻችን ጋር ሰላማዊ ግንኙነት እንዲኖረን መጣራችን አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው?
19 ከመንፈሳዊ ወንድሞቻችንና እህቶቻችን ጋር ሰላማዊ ግንኙነት እንዲኖረን ከልባችን መጣራችን የይሖዋን ቀንና ቃል የገባውን አዲስ ዓለም ምን ያህል በጉጉት እንደምንጠብቅ ሊያሳይ ይችላል። (መዝሙር 37:11፤ 2 ጴጥሮስ 3:13) ለምሳሌ ከአንድ የእምነት ባልንጀራችን ጋር ሰላማዊ ግንኙነት ሊኖረን አልቻለም እንበል። ከዚህ ወንድም ጋር በገነት ውስጥ በሰላም አብረን ስንኖር ይታየናል? አንድ ወንድማችን በእኛ ላይ ቅሬታ ካለው ወዲያውኑ ‘ከእርሱ ጋር መታረቅ’ ይኖርብናል። (ማቴዎስ 5:23, 24) ከይሖዋ ጋር ሰላማዊ ግንኙነት እንዲኖረን ከፈለግን እንደዚህ ማድረጋችን በጣም አስፈላጊ ነው።—መዝሙር 35:27፤ 1 ዮሐንስ 4:20
20. በትዕግሥት ‘የመጠበቅ’ ዝንባሌ እንዳለን በየትኞቹ መንገዶች ማሳየት እንችላለን?
20 በግለሰብ ደረጃ ‘የይሖዋን ቀን መምጣት እየጠበቅንና እያስቸኰልን’ ነውን? በዚህ በሥነ ምግባር በተበላሸ ዓለም ውስጥ ቅድስናችንን ጠብቀን በመኖር ክፋት ተወግዶ ለማየት እንደምንጓጓ እናሳያለን። በተጨማሪም ለይሖዋ ቀን መምጣትና በመንግሥቱ አገዛዝ ሥር ለመኖር ያለን ልባዊ ጉጉት ለአምላክ የማደርን ባሕርይ በማንጸባረቃችን በግልጽ ይታያል። እንዲሁም በአሁኑ ጊዜ ከእምነት ባልንጀሮቻችን ጋር ሰላማዊ ግንኙነት እንዲኖረን ለማድረግ በመጣር ሰላም በሰፈነበት አዲስ ዓለም ውስጥ ለመኖር እንደምንጠብቅ እናሳያለን። እንደዚህ በማድረግ በትዕግሥት ‘የመጠበቅ’ ዝንባሌ እንዳለንና ‘የይሖዋን ቀን መምጣት እንደምናስቸኩል’ ማሳየት እንችላለን።
[የግርጌ ማስታወሻ]
a በዚህ ረገድ በጥር 1, 2000 መጠበቂያ ግንብ ገጽ 16 እና በ1997 የይሖዋ ምሥክሮች የዓመት መጽሐፍ ገጽ 51 ላይ ምሳሌ የሚሆኑ ተሞክሮዎች ቀርበዋል።
ታስታውሳለህን?
• ‘የይሖዋን ቀን መምጣት ማስቸኰል’ ሲባል ምን ማለት ነው?
• በትዕግሥት ‘የመጠበቅ’ ዝንባሌ እንዳለን በአኗኗራችን ማሳየት የምንችለው እንዴት ነው?
• ‘ለአምላክ የማደር’ ባሕርይ በጣም አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው?
• በይሖዋ ዘንድ ‘ያለ ነውር፣ ያለ ነቀፋና በሰላም’ ሆነን ለመገኘት ምን ማድረግ ይኖርብናል?
[የአንቀጾቹ ጥያቄዎች]
[በገጽ 11 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
በቅዱስ ኑሮ መመላለሳችን በትዕግሥት ‘የመጠበቅ’ ዝንባሌ እንዳለን ያሳያል
[በገጽ 12 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
የመንግሥቱ ስብከት ሥራ ሕይወት አድን ነው
[በገጽ 14 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
የይሖዋን ቀን ስንጠብቅ ከሌሎች ጋር በሰላም ለመኖር እንጣር