በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

በፊትና አሁን—ለመለወጥ የሚያስችል ኃይል አገኘች

በፊትና አሁን—ለመለወጥ የሚያስችል ኃይል አገኘች

“ወደ እግዚአብሔር ቅረቡ ወደ እናንተም ይቀርባል”

በፊትና አሁን—ለመለወጥ የሚያስችል ኃይል አገኘች

በሜክሲኮ የምትኖረው ሳንድራ ከቤታቸው አስቸጋሪ ልጅ እንደነበረች ትናገራለች። በሌሎች ዘንድ ተቀባይነት ማጣቷና ፍቅር መነፈጓ የወጣትነት ዕድሜዋን አበላሽቶባታል። “በወጣትነት ዕድሜዬ ሁልጊዜ የባዶነት ስሜት ያጠቃኝ ነበር። ከዚህም በላይ የምኖረው ለምንድን ነው? የሕይወት ዓላማ ምንድን ነው? እንደሚሉት ያሉ በርካታ ጥያቄዎች ነበሩኝ” ስትል ተናግራለች።

ሳንድራ የሁለተኛ ደረጃ ተማሪ እያለች አባቷ ቤት ውስጥ ያስቀመጠውን ወይን ትጠጣ ነበር። ከጊዜ በኋላም ራሷ እየገዛች መጠጣት የጀመረች ሲሆን ውሎ አድሮም የአልኮል ሱሰኛ ሆነች። “መኖር አስጠልቶኝ ነበር” በማለት በግልጽ ትናገራለች። ሳንድራ ካደረባት የተስፋ መቁረጥ ስሜት የተነሳ አደገኛ ዕፆች መውሰድ ጀመረች። “ችግሮቼን ለመርሳት እንዲረዳኝ የምወስደው የአልኮል መጠጥ፣ አደገኛ መድኃኒት ወይም ማሪዋና በቦርሳዬ እይዝ ነበር” ትላለች።

ሳንድራ የሕክምና ትምህርቷን ካጠናቀቀች በኋላ ይበልጥ በአልኮል ሱስ እየተዘፈቀች ሄደች። ራሷን ለመግደል ሙከራ ብታደርግም በሕይወት ተረፈች።

ሳንድራ መንፈሳዊ እርዳታና ስሜታዊ ድጋፍ ለማግኘት ወደ ተለያዩ ሃይማኖቶች ብትሄድም ያደረገችው ጥረት ምንም አላስገኘላትም። ካደረባት የተስፋ መቁረጥና የከንቱነት ስሜት የተነሳ “አምላክ ሆይ፣ የት ነህ? ለምንስ አትረዳኝም?” በማለት ደጋግማ ትጸልይ ነበር። በከፍተኛ የዋጋ ቢስነት ስሜት ተውጣ እያለ አንዲት የይሖዋ ምሥክር መጥታ አነጋገረቻት። ያደረጉት ውይይት ከይሖዋ ምሥክሮች ጋር የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት እንድትጀምር ገፋፋት። ሳንድራ ‘ይሖዋ ልባቸው ለተሰበረ ቅርብ እንደሆነ’ ስታውቅ ስሜቷ በጥልቅ ተነካ።—መዝሙር 34:18

መጽሐፍ ቅዱስን የምታስጠናት ሴት ከአዳም በወረስነው ኃጢአትና አለፍጽምና ምክንያት በቀላሉ ልንሳሳት እንደምንችል ይሖዋ አምላክ እንደሚያውቅ እንድትገነዘብ ረዳቻት። አምላክ የጽድቅ መሥፈርቶቹን ሙሉ በሙሉ ማሟላት እንደማንችል እንደሚረዳ አወቀች። (መዝሙር 51:5፤ ሮሜ 3:23፤ 5:12, 18) ይሖዋ በድክመቶቻችን ላይ እንደማያተኩርና ከአቅማችን በላይ እንደማይጠብቅብን ስትማር በጣም ተደሰተች። መዝሙራዊው “አቤቱ፣ ኃጢአትንስ ብትጠባበቅ፣ አቤቱ፣ ማን ይቆማል?” በማለት ጠይቋል።—መዝሙር 130:3

ሳንድራ ስለ ኢየሱስ ክርስቶስ ቤዛዊ መሥዋዕት የሚገልጸውን የመጽሐፍ ቅዱስ እውነት ስትማር ከፍተኛ የአመስጋኝነት ስሜት አደረባት። ይሖዋ ታዛዥ የሆኑ የሰው ልጆች ፍጽምና ቢጎድላቸውም በዚህ ቤዛዊ መሥዋዕት አማካኝነት የጽድቅ አቋም እንዲያገኙ የሚያስችል የምሕረት ዝግጅት አድርጓል። (1 ዮሐንስ 2:2፤ 4:9, 10) አዎን፣ ‘ለበደላችን ስርየት’ በማግኘት ማንኛውንም የከንቱነት ስሜት ማሸነፍ የምንችልበት እርዳታ አለን።—ኤፌሶን 1:7

ሳንድራ ሐዋርያው ጳውሎስ ከተወው ምሳሌ ጠቃሚ ትምህርት አግኝታለች። ጳውሎስ ቀድሞ የሠራውን ጥፋት በነፃ ይቅር በማለትና ከጊዜ ወደ ጊዜ ብቅ የሚሉ ድክመቶቹን ለማሸነፍ በሚያደርገው ብርቱ ትግል ድጋፍ በመስጠት አምላክ ላሳየው ደግነት ከፍተኛ አድናቆት አድሮበታል። (ሮሜ 7:15-25፤ 1 ቆሮንቶስ 15:9, 10) ጳውሎስ አኗኗሩን ያስተካከለ ሲሆን በአምላክ ዘንድ ተቀባይነት ባለው መንገድ መመላለሱን ለመቀጠል ‘ሥጋውን እየጎሰመ አስገዝቷል።’ (1 ቆሮንቶስ 9:27) የኃጢአት ዝንባሌዎቹ እንደ ባሪያ እንዲገዙት አልፈቀደም።

ሳንድራ መጥፎ ልማዶቿ ያስቸግሯት የነበረ ቢሆንም ተስፋ ቆርጣ እጅ አልሰጠችም። ይሖዋ ድክመቶቿን ለማሸነፍ እንዲረዳትና ይቅር እንዲላት አጥብቃ ትጸልይ ነበር። (መዝሙር 55:22፤ ያዕቆብ 4:8) አምላክ በግለሰብ ደረጃ እንደሚያስብላት ማወቋ ሕይወቷን ለመለወጥ አስቻላት። “በሙሉ ጊዜ አገልግሎት ተሰማርቼ ሌሎችን መጽሐፍ ቅዱስ እያስተማርኩ መሆኑ ያስደስተኛል” ብላለች። ሳንድራ ታላቅና ታናሽ እህቶቿ ይሖዋን እንዲያውቁ መርዳት ችላለች። በይሖዋ ምሥክሮች የአውራጃ ስብሰባ ላይ ባላት የሕክምና ሙያ ለማገልገል ፈቃደኛ በመሆንም ተጨማሪ ‘መልካም ነገር ታደርጋለች።’—ገላትያ 6:10

ሳንድራ ያስቸግሯት የነበሩትን ሱሶች ማሸነፍ ችላ ይሆን? “አእምሮዬ ለሱስ ተገዢ መሆኑ አክትሟል። መጠጣት፣ ማጨስ ወይም አደገኛ ዕፅ መውሰድ አቁሜያለሁ። አሁን እነዚህ ነገሮች አያስፈልጉኝም። ስፈልገው የነበረውን ነገር አግኝቻለሁ” በማለት በልበ ሙሉነት ተናግራለች።

[በገጽ 9 ላይ የሚገኝ ሣጥን]

የመጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ ሥርዓቶች ያላቸው ኃይል

ብዙዎች ከሚያረክሱ ሱሶች እንዲላቀቁ የረዷቸው አንዳንድ የመጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ ሥርዓቶች ቀጥሎ ቀርበዋል:-

“ሥጋንና መንፈስን ከሚያረክስ ሁሉ ራሳችንን እናንጻ።” (2 ቆሮንቶስ 7:1) የአምላክን በረከት የሚያገኙት የሚያረክሱ ልማዶችን በማስወገድ ራሳቸውን ያነጹ ሰዎች ናቸው።

“እግዚአብሔርን መፍራት ክፋትን ይጠላል።” (ምሳሌ 8:13) አንድ ሰው ለአምላክ አክብሮታዊ ፍርሃት ማሳደሩ አደገኛ ዕፆችን መውሰድን ጨምሮ ከመጥፎ ልማዶች ለመላቀቅ ያስችለዋል። እንደዚህ በማድረጉ ይሖዋን ከማስደሰቱም በላይ አስፈሪ ከሆኑ በሽታዎች ይጠበቃል።

‘ለገዦችና ለባለ ሥልጣኖች የሚገዙና የሚታዘዙ ይሁኑ።’ (ቲቶ 3:1) በበርካታ አገሮች ውስጥ አንዳንድ ዕፆችን ይዞ መገኘት ወይም መጠቀም በሕግ የተከለከለ ነው። እውነተኛ ክርስቲያኖች በሕግ የታገዱ ዕፆችን ከመግዛት ወይም ከመጠቀም ይርቃሉ።

[በገጽ 9 ላይ የሚገኝ የተቀነጨበ ሐሳብ]

“ስፈልገው የነበረውን ነገር አግኝቻለሁ”