በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የይሖዋ ቀን በቀረበ መጠን ለሰዎች ምን አመለካከት ሊኖረን ይገባል?

የይሖዋ ቀን በቀረበ መጠን ለሰዎች ምን አመለካከት ሊኖረን ይገባል?

የይሖዋ ቀን በቀረበ መጠን ለሰዎች ምን አመለካከት ሊኖረን ይገባል?

“ጌታ ስለ ተስፋ ቃሉ አይዘገይም፣ ነገር ግን ሁሉ ወደ ንስሐ እንዲደርሱ እንጂ ማንም እንዳይጠፋ ወዶ ስለ እናንተ ይታገሣል።”—2 ጴጥሮስ 3:9

1, 2. (ሀ) ይሖዋ በዛሬው ጊዜ ላሉ ሰዎች ምን ዓይነት አመለካከት አለው? (ለ) ራሳችንን ምን ብለን መጠየቅ አለብን?

 የይሖዋ አገልጋዮች ‘አሕዛብን ሁሉ ደቀ መዛሙርት እንዲያደርጉ’ ተልእኮ ተሰጥቷቸዋል። (ማቴዎስ 28:19) ይህን ተልእኮ እየፈጸምን ‘ታላቁን የይሖዋን ቀን’ ስንጠባበቅ ሰዎችን በይሖዋ ዓይን መመልከት ይኖርብናል። (ሶፎንያስ 1:14) ይሖዋ ለሰዎች ምን ዓይነት አመለካከት አለው? ሐዋርያው ጴጥሮስ እንዲህ ብሏል:- “ለአንዳንዶች የሚዘገይ እንደሚመስላቸው ጌታ ስለ ተስፋ ቃሉ አይዘገይም፣ ነገር ግን ሁሉ ወደ ንስሐ እንዲደርሱ እንጂ ማንም እንዳይጠፋ ወዶ ስለ እናንተ ይታገሣል።” (2 ጴጥሮስ 3:9) አምላክ ሰዎችን የሚመለከተው ንስሐ ሊገቡ እንደሚችሉ ግለሰቦች አድርጎ ነው። ‘ሰዎች ሁሉ እንዲድኑና እውነቱን ወደ ማወቅ እንዲደርሱ’ ይፈልጋል። (1 ጢሞቴዎስ 2:3, 4) ሌላው ቀርቶ ይሖዋ ‘ኃጢአተኛ ከመንገዱ ተመልሶ በሕይወት ሲኖር’ ማየት ያስደስተዋል!—ሕዝቅኤል 33:11

2 እኛስ በግላችን ይሖዋ ለሰዎች ያለው ዓይነት አመለካከት አለን? የይሖዋን አመለካከት በመያዝ ከተለያየ ዘርና ብሔር የመጡ ሰዎች ‘የማሰማርያው በጎች’ ሊሆኑ እንደሚችሉ ይሰማናል? (መዝሙር 100:3፤ ሥራ 10:34, 35) የአምላክ ዓይነት አመለካከት ማዳበር አስፈላጊ የሆነበትን ምክንያት የሚያጎሉ ሁለት ምሳሌዎች እንመልከት። በሁለቱም አጋጣሚዎች ጥፋት ቀርቦ የነበረ ሲሆን ይህንንም የይሖዋ አገልጋዮች አስቀድመው እንዲያውቁ ተደርገዋል። የይሖዋን ታላቅ ቀን በምንጠባበቅበት በአሁኑ ወቅት እነዚህን ምሳሌዎች መመልከታችን በጣም አስፈላጊ ነው።

አብርሃም የይሖዋ ዓይነት አመለካከት ነበረው

3. ይሖዋ ለሰዶምና ለገሞራ ነዋሪዎች ምን ዓይነት አመለካከት ነበረው?

3 የመጀመሪያው ምሳሌ ታማኙን የእምነት አባት አብርሃምንና በክፋት ድርጊታቸው የታወቁትን የሰዶምና የገሞራን ከተሞች የተመለከተ ነው። ይሖዋ ‘የሰዶምና የገሞራን ጩኸት’ እንደሰማ ከተሞቹንና ነዋሪዎቹን ወዲያው አላጠፋቸውም። በመጀመሪያ ሁኔታውን በሚገባ ተመልክቷል። (ዘፍጥረት 18:20, 21) ሁለት መላእክት ወደ ሰዶም የተላኩ ሲሆን ያረፉት በጻድቁ ሎጥ ቤት ነበር። መላእክቱ በመጡበት ምሽት “የዚያች ከተማ . . . ሰዎች” ከመላእክቱ ጋር ግብረ ሰዶም ለመፈጸም በመፈለግ “ከብላቴናው ጀምሮ እስከ ሽማግሌው ድረስ፣ በየስፍራው ያለው ሕዝብ ሁሉ፣ ቤቱን ከበቡት።” የነዋሪዎቿ ወራዳ ተግባር ከተማዋ መጥፋት እንዳለባት በግልጽ ያሳያል። ያም ሆኖ መላእክቱ ሎጥን “ከዚህ ሌላ ማን አለህ? አማችም ቢሆን ወንድ ልጅም ቢሆን ወይም ሴት ልጅ ብትሆን በከተማይቱ ያለህን ሁሉ ከዚህ ስፍራ አስወጣቸው” አሉት። ይሖዋ ከዚያች ከተማ ነዋሪዎች መካከል የተወሰኑት መትረፍ የሚችሉበት አጋጣሚ ቢሰጣቸውም ከጥፋቱ የተረፉት ሎጥና ሁለት ሴቶች ልጆቹ ብቻ ነበሩ።—ዘፍጥረት 19:4, 5, 12, 16, 23-26

4, 5. አብርሃም የሰዶም ነዋሪዎች እንዳይጠፉ ልመና ያቀረበው ለምን ነበር? እርሱ ለሰዎች የነበረው አመለካከት ከይሖዋ አመለካከት ጋር የሚስማማ ነበርን?

4 ይሖዋ የሰዶምንና የገሞራን ከተሞች በቅርብ ለመመልከት እንዳሰበ በተናገረ ጊዜ የነበረውን ሁኔታ እስቲ መለስ ብለን እንመልከት። አብርሃም እንዲህ በማለት ይሖዋን የተማጸነው በዚህ ወቅት ነበር:- “አምሳ ጻድቃን በከተማይቱ ውስጥ ቢገኙ በው[ኑ] ሁሉን ታጠፋለህን? ከተማይቱንስ በእርስዋ ስለሚገ[ኙ] አምሳ ጻድቃን አትምርምን? ይህ ከአንተ ይራቅ፤ ጻድቁን ከኃጢአተኛ ጋር ትገድል ዘንድ፣ ጻድቁም እንደ ኃጢአተኛ ይሆን ዘንድ፣ እንደዚህ ያለው አድራጎት ከአንተ ይራቅ። የምድር ሁሉ ፈራጅ በቅን ፍርድ አይፈርድምን?” አብርሃም “ከአንተ ይራቅ” በማለት ሁለት ጊዜ ተናግሯል። አብርሃም ከዚህ ቀደም ከሚያውቀው ነገር በመነሳት ይሖዋ ጻድቁን ከኃጢአተኛው ጋር እንደማያጠፋ ተገንዝቦ ነበር። ይሖዋ “በከተማይቱ ውስጥ አምሳ ጻድቃን” ቢገኙ ሰዶምን እንደማያጠፋ ሲናገር አብርሃም ደረጃ በደረጃ ቁጥሩን በመቀነስ ወደ አሥር አደረሰው።—ዘፍጥረት 18:22-33

5 አብርሃም ያቀረበው ልመና ከእርሱ አመለካከት ጋር የሚስማማ ባይሆን ኖሮ ይሖዋ ያዳምጠው ነበር? እንደማያደርገው የታወቀ ነው። አብርሃም ‘የይሖዋ ወዳጅ’ እንደመሆኑ መጠን የይሖዋን አመለካከት ሳያውቅና ተመሳሳይ አመለካከት ሳያዳብር አልቀረም። (ያዕቆብ 2:23) ይሖዋ ሰዶምና ገሞራን ለማጥፋት ባሰበበት ወቅት አብርሃም ላቀረበው ልመና ትኩረት ለመስጠት ፈቃደኛ ሆኗል። ይህን ያደረገው ለምን ነበር? በሰማይ የሚኖረው አባታችን ‘ሁሉ ወደ ንስሐ እንዲደርሱ እንጂ ማንም እንዲጠፋ’ ስለማይፈልግ ነው።

ዮናስ ለሰዎች የነበረው ፈጽሞ የተለየ አመለካከት

6. የነነዌ ሰዎች የዮናስን መልእክት ሲሰሙ ምን አደረጉ?

6 አሁን ደግሞ ስለ ዮናስ የሚናገረውን ሁለተኛውን ምሳሌ ተመልከት። በዚህ ወቅት ጥፋት የተበየነባት ከተማ ነነዌ ነበረች። ነቢዩ ዮናስ የከተማዋ ክፋት ‘ወደ ይሖዋ ፊት መውጣቱን’ እንዲያውጅ ተነግሮት ነበር። (ዮናስ 1:2) ነነዌ በዳርቻዋ ያሉትን መንደሮች ጨምሮ “የሦስት ቀን መንገድ ያህል” የምታስኬድ ታላቅ ከተማ ነበረች። ዮናስ ከኰበለለበት አቅጣጫ ተመልሶ የተሰጠውን መመሪያ በመታዘዝ ወደ ነነዌ ከሄደ በኋላ “ነነዌ በአርባ ቀን ውስጥ ትገለበጣለች” [አ.መ.ት] ብሎ አወጀ። በዚህ ጊዜ “የነነዌም ሰዎች እግዚአብሔርን አመኑ፤ ለጾም አዋጅ ነገሩ፣ ከታላቁም ጀምሮ እስከ ታናሹ ድረስ ማቅ ለበሱ።” የነነዌ ንጉሥም እንኳ ሳይቀር ንስሐ ገብቷል።—ዮናስ 3:1-6

7. ይሖዋ የነነዌ ሰዎች ያሳዩትን የንስሐ ዝንባሌ የተመለከተው እንዴት ነበር?

7 ይህ የሰዶም ነዋሪዎች ከሰጡት ምላሽ ፈጽሞ የተለየ ነበር! ይሖዋ ንስሐ የገቡትን የነነዌ ሰዎች እንዴት ተመለከታቸው? ዮናስ 3:10 “እግዚአብሔርም ያደርግባቸው ዘንድ በተናገረው ክፉ ነገር ተጸጽቶ አላደረገውም” ይላል። ይሖዋ ‘ተጸጸተ’ ሊባል የሚችለው የነነዌ ሰዎች አካሄዳቸውን በማስተካከላቸው ምክንያት ሊያመጣባቸው ያሰበውን ጥፋት በመተዉ ነው። የአምላክ አቋም የማይለወጥ ቢሆንም ይሖዋ የነነዌ ሰዎች ንስሐ መግባታቸውን ሲመለከት ውሳኔውን ለውጧል።—ሚልክያስ 3:6

8. ዮናስ ቅሬታ የተሰማው ለምን ነበር?

8 ዮናስ ነነዌ እንደማትጠፋ ሲያውቅ ሁኔታውን ከይሖዋ አመለካከት አንጻር ተመልክቶት ይሆን? መጽሐፍ ቅዱስ “ይህም ዮናስን ከቶ ደስ አላሰኘውም፣ እርሱም ተቆጣ” ስለሚል ዮናስ የይሖዋ ዓይነት አመለካከት እንዳልነበረው ማወቅ እንችላለን። ዮናስ ከዚህ ሌላ ያደረገው ነገር ይኖር ይሆን? ዘገባው እንዲህ ይላል:- “ወደ እግዚአብሔርም ጸለየና:- አቤቱ፣ እለምንሃለሁ፤ በአገሬ ሳለሁ የተናገርሁት ይህ አልነበረምን? አንተ ቸርና ይቅር ባይ፣ ታጋሽም፣ ምሕረትህም የበዛ፣ ከክፉው ነገርም የተነሣ የምትጸጸት አምላክ እንደ ሆንህ አውቄ ነበርና ስለዚህ ወደ ተርሴስ ለመኰብለል ፈጥኜ ነበር።” (ዮናስ 4:1, 2) ዮናስ የይሖዋን ባሕርያት ያውቅ ነበር። ሆኖም በዚህ ጊዜ አምላክ ንስሐ ለገቡት የነነዌ ሰዎች የነበረው ዓይነት አመለካከት ስላልነበረው ቅሬታ ተሰምቶታል።

9, 10. (ሀ) ይሖዋ ለዮናስ የሰጠው ትምህርት ምንድን ነው? (ለ) ከጊዜ በኋላ ዮናስ፣ ይሖዋ ለነነዌ ሰዎች የነበረው ዓይነት አመለካከት አዳብሮ ሊሆን ይችላል የምንለው ለምንድን ነው?

9 ዮናስ ከነነዌ ወጣና “ከተማይቱን የሚያገኛትን እስኪያይ ድረስ” ለራሱ ዳስ ሠርቶ ከጥላው ሥር ተቀመጠ። ይሖዋ አንድ የቅል ተክል በማሳደግ ለዮናስ ጥላ አዘጋጀ። ሆኖም በቀጣዩ ቀን ተክሉ ደረቀ። ዮናስ በሁኔታው በተናደደ ጊዜ ይሖዋ እንዲህ አለው:- “አንተ . . . ለደረቀችው ቅል አዝነሃል። እኔስ ቀኛቸውንና ግራቸውን የማይለዩ ከመቶ ሀያ ሺህ የሚበልጡ ሰዎችና ብዙ እንስሶች ላሉባት ለታላቂቱ ከተማ ለነነዌ አላዝንምን?” (ዮናስ 4:5-11) ይሖዋ ለሰዎች ስላለው አመለካከት ዮናስ ከዚህ ሁኔታ ትልቅ ትምህርት ሊያገኝ ይገባል!

10 አምላክ ለነነዌ ሰዎች ያሳየውን ርኅራኄ አስመልክቶ ለሰጠው ትምህርት ዮናስ ምን ምላሽ እንደሰጠ መጽሐፍ ቅዱስ አይናገርም። ሆኖም ነቢዩ ንስሐ ለገቡት የነነዌ ሰዎች የነበረውን አመለካከት እንዳስተካከለ ግልጽ ነው። ይሖዋ በመንፈስ አነሳሽነት ይህንን ዘገባ እንዲጽፍ በዮናስ መጠቀሙ እዚህ መደምደሚያ ላይ እንድንደርስ ያስችለናል።

አንተስ ምን ዓይነት አመለካከት አለህ?

11. አብርሃም ዛሬ በሕይወት ቢኖር ኖሮ ለሰዎች ምን አመለካከት ይኖረው ነበር?

11 ዛሬም ከፊታችን ሌላ ጥፋት ተደቅኗል፤ ይህ ክፉ ሥርዓት በታላቁ የይሖዋ ቀን ይጠፋል። (ሉቃስ 17:26-30፤ ገላትያ 1:4፤ 2 ጴጥሮስ 3:10) አብርሃም ዛሬ በሕይወት ቢኖር ኖሮ ሊጠፋ በተቃረበው ዓለም ውስጥ ላሉት ሰዎች ምን አመለካከት ይኖረው ነበር? ‘የመንግሥቱን ወንጌል’ ላልሰሙት ሰዎች ያስብ እንደነበር ምንም ጥርጥር የለውም። (ማቴዎስ 24:14) አብርሃም በሰዶም ሊኖሩ የሚችሉ ጻድቅ ሰዎችን በተመለከተ ይሖዋን ደጋግሞ ተማጽኗል። እኛስ ንስሐ የመግባትና አምላክን የማገልገል አጋጣሚ ቢሰጣቸው በሰይጣን ቁጥጥር ሥር የሚገኘውን የዚህን ዓለም አካሄድ ሊተዉ ለሚችሉ ሰዎች በግል እናስብላቸዋለን?—1 ዮሐንስ 5:19፤ ራእይ 18:2-4

12. በአገልግሎት ላይ ለምናገኛቸው ሰዎች የዮናስ ዓይነት አመለካከት ልናንጸባርቅ የምንችለው እንዴት ነው? ይህንንስ ለማስወገድ ምን ማድረግ እንችላለን?

12 ክፋት እንዲወገድ መጓጓታችን ተገቢ ነው። (ዕንባቆም 1:2, 3) ሆኖም ንስሐ ሊገቡ ለሚችሉ ሰዎች ደህንነት ባለማሰብ በቀላሉ እንደ ዮናስ ዓይነት አመለካከት ልናዳብር እንችላለን። በተለይ ከቤት ወደ ቤት እየሄድን የመንግሥቱን መልእክት ስንሰብክ ግድየለሽ፣ ተቃዋሚ አልፎ ተርፎም ለዱላ የሚጋበዙ ሰዎች በተደጋጋሚ የሚያጋጥሙን ከሆነ እንደዚህ ዓይነት አመለካከት ልናዳብር እንችል ይሆናል። ይሖዋ ከዚህ ክፉ ሥርዓት ለሚሰበስባቸው ሰዎች ትኩረት ላንሰጥ እንችላለን። (ሮሜ 2:4) ራሳችንን ስንመረምር ዮናስ ለነነዌ ሰዎች መጀመሪያ ላይ የነበረው ዓይነት አመለካከት በመጠኑም ቢሆን እንዳለን ከተገነዘብን ይሖዋ የእርሱ ዓይነት አመለካከት ለማዳበር እንዲረዳን መጸለይ ይኖርብናል።

13. ይሖዋ በዛሬው ጊዜ ላሉ ሰዎች ያስባል የምንለው ለምንድን ነው?

13 ይሖዋ የእርሱ አገልጋይ ሊሆኑ ለሚችሉ ሰዎች የሚያስብ ከመሆኑም በላይ ራሳቸውን ለእርሱ የወሰኑ ሕዝቦቹ የሚያቀርቡትን ልመናም ያዳምጣል። (ማቴዎስ 10:11) ለምሳሌ ያህል ለጸሎታቸው ምላሽ በመስጠት “ይፈርድላቸዋል።” (ሉቃስ 18:7, 8) ከዚህም በላይ ይሖዋ ቃል የገባቸውን ነገሮችና ዓላማዎቹን በወሰነው ጊዜ ይፈጽማል። (ዕንባቆም 2:3) ይህም የነነዌ ነዋሪዎች ወደ ክፉ ድርጊታቸው ሲመለሱ ከተማዋን እንዳጠፋ ሁሉ ክፋትን ከምድር ላይ ጠራርጎ ማስወገድን ይጨምራል።—ናሆም 3:5-7

14. የይሖዋን ታላቅ ቀን ስንጠባበቅ ምን ማድረግ ይኖርብናል?

14 ይህ ክፉ ሥርዓት በታላቁ የይሖዋ ቀን እስኪወገድ ድረስ የአምላክን ፈቃድ በመፈጸሙ ሥራ ራሳችንን በማስጠመድ በትዕግሥት መጠበቃችንን እንቀጥላለን? የይሖዋ ቀን ከመምጣቱ በፊት የስብከቱ ሥራ ምን ያህል መከናወን እንዳለበት በዝርዝር ባናውቅም መጨረሻው ከመምጣቱ በፊት አምላክ ሥራው ይቁም እስኪል ድረስ የመንግሥቱ ምሥራች በምድር ዙሪያ መሰበክ እንዳለበት እናውቃለን። ደግሞም ይሖዋ ቤቱን በክብር ሲሞላ ስለሚሰበሰቡት ‘የተመረጡ ዕቃዎች’ ልናስብ እንደሚገባ ጥርጥር የለውም።—ሐጌ 2:7

አመለካከታችን በሥራችን ይገለጣል

15. የስብከቱን ሥራ አስፈላጊነት ይበልጥ እንድንገነዘብ የሚረዳን ምንድን ነው?

15 በምንኖርበት አካባቢ ብዙ ሰዎች ለምሥራቹ ፍላጎት አይኖራቸው ይሆናል። እኛ ደግሞ የመንግሥቱ ሰባኪዎች ይበልጥ ወደሚያስፈልጉበት አካባቢ ለመሄድ ሁኔታችን አይፈቅድልን ይሆናል። መጨረሻው ከመምጣቱ በፊት ፍላጎት ያላቸው አሥር ሰዎች በክልላችን ሊገኙ የሚችሉ ቢሆን እነዚህን ሰዎች ለመፈለግ ጥረት ማድረጉ ተገቢ እንደሆነ ይሰማናል? ኢየሱስ “ብዙ ሕዝብም ባየ ጊዜ፣ እረኛ እንደ ሌላቸው በጎች ተጨንቀው ተጥለውም ነበርና አዘነላቸው።” (ማቴዎስ 9:36) መጽሐፍ ቅዱስን በማጥናትና መጠበቂያ ግንብ እና ንቁ! መጽሔቶችን ትኩረት ሰጥተን በማንበብ ይህ ዓለም ስለሚገኝበት አሳዛኝ ሁኔታ የበለጠ ማወቅ እንችላለን። ይህ ደግሞ ምሥራቹን መስበክ ምን ያህል አስፈላጊ እንደሆነ ይበልጥ እንድንገነዘብ ያደርገናል። ከዚህም በላይ “ታማኝና ልባም ባሪያ” የሚያዘጋጃቸውን መጽሐፍ ቅዱሳዊ ጽሑፎች አድናቆታችንን በሚያሳይ መንገድ መጠቀማችን በተደጋጋሚ በተሠራባቸው ክልሎች ውስጥ ስናገለግል ይበልጥ አሳማኝ በሆነ መልኩ መስበክ እንድንችል ይረዳናል።—ማቴዎስ 24:45-47፤ 2 ጢሞቴዎስ 3:14-17

16. በአገልግሎታችን ይበልጥ ውጤታማ መሆን የምንችለው እንዴት ነው?

16 ሕይወት ለሚያስገኘው የመጽሐፍ ቅዱስ መልእክት ምላሽ ሊሰጡ ለሚችሉ ሰዎች ያለን አሳቢነት በተለያዩ ጊዜያትና መንገዶች ሰዎችን ለማነጋገር እንድንነሳሳ ያደርገናል። ከቤት ወደ ቤት ስናገለግል አብዛኞቹን ሰዎች ቤታቸው አናገኛቸውም? ከሆነ በተለያዩ ጊዜያትና ቦታዎች በማገልገል ይበልጥ ውጤታማ መሆን እንችል ይሆናል። ዓሣ አጥማጆች ወደ ሥራ የሚሰማሩት ብዙ ዓሣ ማግኘት በሚችሉበት ሰዓት ነው። እኛስ በመንፈሳዊው ዓሣ የማጥመድ ሥራ እንዲሁ ማድረግ እንችል ይሆን? (ማርቆስ 1:16-18) በምሽት አገልግሎት ለመካፈል አሊያም በምትኖርበት አካባቢ በሕግ የተከለከለ ካልሆነ በስልክ ለመመሥከር ለምን አትሞክርም? አንዳንዶች የቆመ መኪና ውስጥ ለሚገኙ ሰዎች፣ አውቶቡስ ተራ እንዲሁም በገበያ ቦታዎች መመሥከር ውጤታማ ሆኖ አግኝተውታል። መደበኛ ያልሆነ ምሥክርነት ለመስጠት የሚያስችሉንን አጋጣሚዎች በመጠቀምም ለሰዎች እንደ አብርሃም ዓይነት አመለካከት እንዳለን እናሳያለን።

17. ከአገራቸው ውጪ የሚያገለግሉ ሚስዮናውያንንና ሌሎች የሙሉ ጊዜ አገልጋዮችን በምን መንገዶች ማበረታታት እንችላለን?

17 የመንግሥቱ መልእክት ገና ያልደረሳቸው በሚልዮን የሚቆጠሩ ሰዎች አሉ። ከስብከቱ ሥራችን በተጨማሪ ቤታችን ሆነን ለእነዚህ ሰዎች እንደምናስብላቸው ማሳየት እንችል ይሆን? በሌላ አገር የሚያገለግሉ የምናውቃቸው ሚስዮናውያን ወይም የሙሉ ጊዜ አገልጋዮች አሉ? ከሆነ ለሚያከናውኑት ሥራ አድናቆታችንን በመግለጽ ደብዳቤ ብንጽፍላቸው ጠቃሚ ሊሆን ይችላል። እንደዚህ ማድረጋችን ለሰዎች ሁሉ እንደምናስብ የሚያሳየው እንዴት ነው? የጻፍንላቸው የማበረታቻና የምስጋና ደብዳቤ ሚስዮናውያኑ በተመደቡበት አገር እንዲቀጥሉ ሊያበረታታቸው የሚችል ሲሆን ይህ ደግሞ ተጨማሪ ሰዎች እውነትን እንዲያውቁ አጋጣሚ ይከፍትላቸዋል። (መሳፍንት 11:40) ከዚህም በተጨማሪ ሚስዮናውያኑንና በሌሎች አገሮች የሚገኙ እውነትን የተጠሙ ሰዎችን በጸሎታችን ልናስባቸው እንችላለን። (ኤፌሶን 6:18-20) የይሖዋ ምሥክሮች በዓለም ዙሪያ ለሚያከናውኑት ሥራ የገንዘብ መዋጮ በማድረግም አሳቢነታችንን እናሳያለን።—2 ቆሮንቶስ 8:13, 14፤ 9:6, 7

አንተስ ወደ ሌላ ቦታ መዛወር ትችላለህ?

18. አንዳንድ ክርስቲያኖች በአገራቸው ውስጥ የመንግሥቱን ምሥራች ለማስፋፋት ምን አድርገዋል?

18 የመንግሥቱ ሰባኪዎች ይበልጥ ወደሚያስፈልጉባቸው ቦታዎች የተዛወሩ የይሖዋ ምሥክሮች የራሳቸውን ጥቅም መሥዋዕት በማድረጋቸው ተባርከዋል። ሌሎች ክርስቲያኖች ደግሞ እዚያው አገራቸው ውስጥ ሆነው የውጭ አገር ዜጎችን በመንፈሳዊ ለመርዳት በማሰብ ሌላ ቋንቋ ተምረዋል። በእርግጥም ያደረጉት ጥረት ጥሩ ውጤት አስገኝቶላቸዋል። ለምሳሌ ያህል በዩ ኤስ ኤ፣ ቴክሳስ ውስጥ በምትገኝ ከተማ ለቻይናውያን ለመመሥከር ጥረት የሚያደርጉ ሰባት የይሖዋ ምሥክሮች በ2001 በተከበረው የክርስቶስ ሞት መታሰቢያ በዓል ላይ 114 ሰዎች በመገኘታቸው ተደስተዋል። እንዲህ ዓይነት ቡድኖችን የሚረዱ ክርስቲያኖች ከመስኩ ብዙ ፍሬ ማግኘት ችለዋል።—ማቴዎስ 9:37, 38

19. ተጨማሪ የመንግሥቱ ሰባኪዎች ወደሚያስፈልጉበት ቦታ ለመዛወር የምታስብ ከሆነ ምን ማድረግህ ጠቃሚ ነው?

19 ምናልባት አንተና ቤተሰብህ የምሥራቹ ሰባኪዎች ይበልጥ ወደሚያስፈልጉበት ቦታ ለመዛወር የሚያስችል ሁኔታ እንዳላችሁ ይሰማችሁ ይሆናል። እርግጥ በቅድሚያ ‘ተቀምጦ ኪሳራውን መቁጠር’ የጥበብ እርምጃ ነው። (ሉቃስ 14:28) በተለይ አንድ ሰው ወደ ሌላ አገር ለመዛወር የሚያስብ ከሆነ እንደዚህ ማድረጉ አስፈላጊ ነው። ይህን ለማድረግ የሚያስብ ማንኛውም ሰው የሚከተሉትን ጥያቄዎች ቢጠይቅ ጥሩ ይሆናል:- ‘የቤተሰቤን ቁሳዊ ፍላጎት ማሟላት እችላለሁን? አስፈላጊውን የይለፍ ፈቃድ ማግኘት እችላለሁ? የአገሩን ቋንቋ መናገር እችላለሁ አሊያም ለመማር ፈቃደኛ ነኝ? የአየሩን ሁኔታና የሕብረተሰቡን ባሕል ግምት ውስጥ አስገብቻለሁ? በዚያ አገር ለሚኖሩ የእምነት ባልንጀሮቼ ሸክም ከመሆን ይልቅ “የብርታት ምንጭ” እሆንላቸዋለሁን?’ (ቆላስይስ 4:10, 11 NW) ለመሄድ ባሰብክበት አገር የምሥራቹ ሰባኪዎች ያስፈልጉ እንደሆነ ለማወቅ በዚያ አካባቢ ያለውን የስብከት እንቅስቃሴ በበላይነት ለሚመለከተው የይሖዋ ምሥክሮች ቅርንጫፍ ቢሮ መጻፉ ተገቢ ነው። a

20. አንድ ወጣት ክርስቲያን ወደ ሌላ አገር ሄዶ በዚያ የሚኖሩ የእምነት ባልንጀሮቹንም ሆነ ሌሎችን ለመጥቀም ምን አድርጓል?

20 በጃፓን በይሖዋ ምሥክሮች መሰብሰቢያ አዳራሽ የግንባታ ሥራ ላይ ይካፈል የነበረ አንድ ክርስቲያን በፓራጓይ የጉባኤ አዳራሽ ለመገንባት ባለሞያ የሆኑ ሠራተኞች እንደሚያስፈልጉ ሰማ። ይህ ክርስቲያን በወጣትነት ዕድሜ ላይ የሚገኝ ነጠላ ወንድም ስለነበር ወደዚያ አገር በመሄድ ለስምንት ወራት ያህል በግንባታ ሥራው ላይ ብቸኛው የሙሉ ጊዜ አገልጋይ ሆኖ ሠርቷል። በዚያ በቆየበት ወቅት ስፓንኛ ተምሮ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቶች ይመራ ነበር። በአገሪቱ ተጨማሪ የመንግሥቱ አዋጅ ነጋሪዎች እንደሚያስፈልጉ ስለተገነዘበ ለተወሰነ ጊዜ ወደ ጃፓን ቢመለስም እንኳ ብዙም ሳይቆይ ወደ ፓራጓይ በመምጣት በዚያው የመሰብሰቢያ አዳራሽ ውስጥ የሚሰበሰቡ ሰዎችን በመፈለጉ ሥራ መካፈል ጀመረ።

21. የይሖዋን ታላቅ ቀን በምንጠብቅበት ጊዜ ለየትኛው ሥራ ትኩረት መስጠት አለብን? ምን ዓይነት አመለካከት መያዝስ ይኖርብናል?

21 አምላክ ከፈቃዱ ጋር በሚስማማ መንገድ የስብከቱ ሥራ በተሟላ መልኩ እንዲከናወን ያደርጋል። በዛሬው ጊዜ የመጨረሻውን መንፈሳዊ የመከር ሥራ እያፋጠነው ነው። (ኢሳይያስ 60:22) የይሖዋን ቀን በምንጠብቅበት ጊዜ በመከሩ ሥራ በቅንዓት እንካፈል እንዲሁም ሰዎችን አፍቃሪው አምላካችን በሚያያቸው መንገድ እንመልከታቸው።

[የግርጌ ማስታወሻ]

a የስብከቱ ሥራ ወደታገደበት አገር መሄድ ጥሩ የማይሆንባቸው ጊዜያት አሉ። እንደዚህ ማድረግ በእገዳ ሥር ሆነው ሥራውን በጥበብ የሚያካሂዱትን የመንግሥቱን አስፋፊዎች ችግር ላይ ሊጥልም ይችላል።

ታስታውሳለህን?

የይሖዋን ቀን በምንጠብቅበት ጊዜ ለሰዎች ምን ዓይነት አመለካከት ሊኖረን ይገባል?

አብርሃም በሰዶም ሊኖሩ ለሚችሉ ጻድቅ ሰዎች ምን ዓይነት አመለካከት ነበረው?

ዮናስ ንስሐ ለገቡት የነነዌ ሰዎች ምን ዓይነት አመለካከት ነበረው?

ገና ምስራቹን ያልሰሙ ሰዎችን በይሖዋ ዓይን እንደምንመለከታቸው እንዴት ልናሳይ እንችላለን?

[የአንቀጾቹ ጥያቄዎች]

[በገጽ 16 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

አብርሃም ለሰዎች የይሖዋ ዓይነት አመለካከት ነበረው

[በገጽ 17 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ዮናስ ንስሐ የገቡትን የነነዌ ሰዎች በይሖዋ ዓይን መመልከት እንዳለበት ተምሯል

[በገጽ 18 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ለሰዎች ያለን አሳቢነት በተለያየ ጊዜና መንገድ ምሥራቹን ለመስበክ ጥረት እንድናደርግ ይገፋፋናል