በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ዩሲቢየስ “የቤተ ክርስቲያን ታሪክ አባት” ነውን?

ዩሲቢየስ “የቤተ ክርስቲያን ታሪክ አባት” ነውን?

ዩሲቢየስ “የቤተ ክርስቲያን ታሪክ አባት” ነውን?

የሮማው ንጉሠ ነገሥት ቆስጠንጢኖስ በ325 እዘአ ጳጳሳትን በሙሉ ለስብሰባ ጠራ። ስብሰባው የሚደረገው በኒቂያ ነበር። ስብሰባ የጠራበት ዓላማ ምን ነበር? በአምላክና በልጁ መካከል ያለውን ዝምድና በተመለከተ ለተነሳው ውዝግብ እልባት ለማስገኘት ነበር። በዘመኑ እንደ ታላቅ ምሑር ይታይ የነበረው የቂሳሪያው ዩሲቢየስም በስብሰባው ላይ ተገኝቷል። ዩሲቢየስ መጽሐፍ ቅዱስን በሚገባ ያጠና ከመሆኑም በላይ በአንድ አምላክ ስለሚያምነው የክርስትና እምነት ይሟገት ነበር።

የኒቂያ ጉባኤን በማስመልከት ኢንሳይክሎፒዲያ ብሪታኒካ እንዲህ ሲል ጽፏል:- “ቆስጠንጢኖስ ራሱ ስብሰባውን በሊቀ መንበርነት መርቷል። በጉዳዩ ላይ የጦፈ ክርክር እንዲካሄድ ከማድረጉም በላይ . . . ጉባኤው ያስተላለፈውንና ክርስቶስና እግዚአብሔር አንድ አካል መሆናቸውን የገለጸውን ድንጋጌ ጉባኤው እንዲያጸድቀው ሐሳብ ያቀረበው እርሱ ራሱ ነው። . . . ከሁለት ጳጳሳት በስተቀር ጳጳሳቱ በሙሉ ንጉሡን በመፍራት አለፍላጎታቸው ድንጋጌውን በፊርማቸው አረጋገጡ።” ካልፈረሙት ሁለት ሰዎች አንዱ ዩሲቢየስ ነውን? እርሱ ከወሰደው አቋም ምን ትምህርት ልናገኝ እንችላለን? የዩሲቢየስን የኋላ ታሪክ ማለትም የቀሰመውን ትምህርትና ያከናወናቸውን ሥራዎች እንመልከት።

እውቅ የጽሑፍ ሥራዎቹ

ዩሲቢየስ በጳለስጢና ምድር በ260 እዘአ ገደማ እንደተወለደ ይገመታል። ዩሲቢየስ ቂሳሪያ የሚገኘው ቤተ ክርስቲያን ኃላፊ ከነበረው ከፓምፊለስ ጋር የተዋወቀው ገና በልጅነቱ ነበር። ፓምፊለስ ባቋቋመው የሃይማኖት ትምህርት ቤት ገብቶ ትምህርቱን በትጋት መከታተል ጀመረ። የፓምፊለስ ቤተ መጻሕፍት ለሚከታተለው ትምህርት ትልቅ እገዛ አድርጎለታል። ዩሲቢየስ ለትምህርቱ በተለይ ደግሞ በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ ለሚያደርገው ምርምር ትልቅ ትኩረት ሰጥቶ ነበር። ከፓምፊለስ ጋር ጥብቅ ወዳጅነት ከመመሥረቱም በላይ ራሱን “የፓምፊለስ ልጅ ዩሲቢየስ” ብሎ ጠርቷል።

ዩሲቢየስ ስለ ወደፊት ራእዩ እንዲህ በማለት ጽፏል:- “ዓላማዬ ባለፉት ዘመናት ተራ በተራ ስለተነሱት ቅዱስ ሐዋርያትና ከመድኃኒታችን ጊዜ አንስቶ እስከ ዘመናችን ድረስ ስላለፉት ጊዜያት መዘገብ፣ በቤተ ክርስቲያን ታሪክ ውስጥ ተፈጽመዋል ስለሚባሉ ታላላቅ ክንውኖች መተረክ እንዲሁም በታወቁ ደብሮች በሚገኙ አብያተ ክርስቲያናት አስተዳዳሪ ሆነው ስላገለገሉ ሰዎችና ባለፉት ትውልዶች ሁሉ በቃልም ይሁን በጽሑፍ የአምላክን ቃል ስላስተላለፉ ሰዎች ማስፈር ነው።”

ዩሲቢየስ የቤተ ክርስቲያን ታሪክ በተባለው ዝነኛ የጽሑፍ ሥራው ይታወቃል። በ324 እዘአ ገደማ ያሳተማቸው ባለ አሥር ጥራዝ መጻሕፍት ከመካከለኛው መቶ ዘመን በፊት ስለነበረው የቤተ ክርስቲያን ታሪክ የሚዘግቡ ታላላቅ የጽሑፍ ሥራዎች እንደሆኑ ተደርገው ይታያሉ። በዚህም ምክንያት ዩሲቢየስ የቤተ ክርስቲያን ታሪክ አባት በመባል ሊታወቅ ችሏል።

የቤተ ክርስቲያን ታሪክ ከተባለው መጽሐፉ በተጨማሪ ሌሎች ታሪኮችን በሁለት ጥራዝ ጽፏል። የመጀመሪያው ጥራዝ ስለ ዓለም ታሪክ አጠር ባለ መንገድ የሚተርክ ነው። ይህ መጽሐፍ በአራተኛው መቶ ዘመን የዓለም ታሪክን በተመለከተ እንደ ዋና የማመሳከሪያ ጽሑፍ ተደርጎ ይታይ ነበር። ሁለተኛው ጥራዝ ታላላቅ ታሪኮች የተፈጸሙባቸውን ጊዜያት የሚገልጽ ነው። ዩሲቢየስ በብዙ አገሮች በተለያዩ ወቅቶች የተፈራረቁ ነገሥታትን በሁለት ረድፍ ዘርዝሮ አስቀምጧል።

ዩሲቢየስ የጳለስጢና ምድር ሰማዕታት እና የቆስጠንጢኖስ የሕይወት ታሪክ የተባሉ ሁለት የታሪክ መጻሕፍትን ጽፏል። የመጀመሪያው መጽሐፍ ከ303 እስከ 310 እዘአ ያለውን ጊዜ የሚሸፍን ሲሆን በዚህ ዘመን ውስጥ ስለተሠዉ ሰማዕታት ይዘግባል። እነዚህ ሁኔታዎች በእርሱ የሕይወት ዘመን የተፈጸሙ ሊሆኑ ይችላሉ። ንጉሠ ነገሥት ቆስጠንጢኖስ በ337 እዘአ ከሞተ በኋላ በአራት መጻሕፍት ተከፋፍሎ የተዘጋጀው ሁለተኛ መጽሐፉ ጠቃሚ የሆኑ ዝርዝር ታሪካዊ መረጃዎችን ይዟል። ይህ መጽሐፍ በቀጥታ ታሪክን ከመዘገብ ይልቅ ንጉሠ ነገሥቱን በሚያወድሱ ቃላት የተሞላ ነው።

የክርስትናን እምነት ለመደገፍ የጻፋቸው ጽሑፎች በዘመኑ ሮማዊው ገዥ ሃይሮክለስ የሰነዘረውን ሐሳብ በመቃወም ያሰፈረውን መልስ የሚጨምሩ ነበሩ። ሃይሮክለስ የክርስትናን እምነት በመንቀፍ በጻፈ ጊዜ ዩሲቢየስ ለዚህ ነቀፋ የመቃወሚያ ሐሳብ ጽፏል። ከዚህም በተጨማሪ ዩሲቢየስ መጽሐፍ ቅዱስን ያስጻፈው አምላክ ነው የሚለውን ሐሳብ የሚደግፉ 35 መጻሕፍትን ጽፏል። እነዚህ መጻሕፍት በብዙ ድካም የተዘጋጁና በዓይነታቸው ልዩ የሆኑ መጻሕፍት እንደሆኑ ተደርገው ይታያሉ። ከእነዚህ ውስጥ የመጀመሪያዎቹ 15 መጻሕፍት ክርስቲያኖች የዕብራይስጥ ቅዱሳን ጽሑፎችን እንደሚቀበሉ የሚገልጹ ማስረጃዎችን የያዙ ናቸው። የቀሩት 20 መጻሕፍት ደግሞ ክርስቲያኖች የአይሁድን ልማድ ትተው አዳዲስ መሠረታዊ መመሪያዎችንና ልማዶችን መከተል መጀመራቸው ትክክል መሆኑን የሚያረጋግጡ ናቸው። ያም ሆነ ይህ ሠላሳ አምስቱም መጻሕፍት ዩሲቢየስ በወቅቱ በነበረው ግንዛቤ መሠረት የክርስትናን እምነት በመደገፍ የተጻፉ ናቸው።

ዩሲቢየስ ለ80 ዓመት ያህል (ከ260 ገደማ እስከ 340 እዘአ ገደማ) የኖረ ሲሆን ከመካከለኛው መቶ ዘመን በፊት ስለነበረው ታሪክ የዘገበ እውቅ የታሪክ ጸሐፊ ነበር። ጽሑፎቹ ከመጀመሪያዎቹ ሦስት መቶ ዘመናት አንስቶ እስከ ንጉሠ ነገሥት ቆስጠንጢኖስ ዘመን ድረስ ባሉት ጊዜያት የተፈጸሙ ታሪኮችን የያዙ ናቸው። በሕይወቱ መጨረሻ አካባቢ ከታሪክ ጸሐፊነቱ በተጨማሪ የቂሳሪያ ጳጳስ ሆኖም አገልግሏል። ምንም እንኳ ዩሲቢየስ ይበልጥ የሚታወቀው በታሪክ ጸሐፊነቱ ቢሆንም ለእምነቱ ተሟጋች፣ የካርታ አዘጋጅ፣ ሰባኪ፣ የሃይማኖት ትምህርት ገምጋሚና የሃይማኖታዊ ጽሑፎች ተንታኝ ነበር።

የነበሩት ሁለት ዓላማዎች

ዩሲቢየስ እንዲህ ያለ በዘመኑ አቻ ያልተገኘለትን ትልቅ ሥራ እንዲሠራ ያነሳሳው ምንድን ነው? ለዚህ ያነሳሳው ወደ አዲስ ዘመን በሚያሸጋግር ጊዜ ላይ እንደሚኖር የነበረው እምነት ነው። ባለፉት ትውልዶች ብዙ ታሪካዊ ክንውኖች እንደተፈጸሙና እነዚህ ታሪኮች ለቀጣዩ ትውልድ በጽሑፍ ሰፍረው መቀመጥ እንዳለባቸው ያምን ነበር።

ሌላው የዩሲቢየስ ዓላማ ለክርስትና እምነት ጥብቅና መቆም ነበር። የክርስትና እምነት መለኮታዊ ምንጭ እንዳለው ያምን ነበር። ሆኖም ይህን ሐሳብ የሚቃወሙ አንዳንድ ሰዎች ነበሩ። ዩሲቢየስ እንዲህ በማለት ጽፏል:- “በተጨማሪም ዓላማዬ አዳዲስ አመለካከቶችን በማራመድ ለትልቅ ስህተት የተዳረጉትን እንዲሁም አዲስ እውቀት አመንጪዎች ነን የሚሉትን ሆኖም እንደ ጨካኝ ተኩላ የክርስቶስን በጎች ያለ ርኅራኄ የጨፈጨፉትን ሰዎች ስምና ብዛት ማጋለጥ ነው።”

ዩሲቢየስ ራሱን ክርስቲያን አድርጎ ይቆጥር ነበርን? ክርስቶስን “መድኃኒታችን” ብሎ መጥቀሱ ራሱን እንደ ክርስቲያን ይቆጥር እንደነበር ለመገመት ያስችላል። እንዲህ በማለት ጽፏል:- “በመድኃኒታችን ላይ በማሴራቸው ምክንያት በመላው የአይሁድ ብሔር ላይ ስለደረሰው መጥፎ ነገር፣ አሕዛብ በተለያየ ጊዜና መንገድ በመለኮታዊው ቃል ላይ ጥቃት ስለመሰንዘራቸው፣ ለአምላክ ቃል ሲሉ የተለያየ መከራና ሥቃይ ቢደርስባቸውም መንፈሰ ጠንካራ ሆነው ስለተገኙ እንዲሁም በጊዜያችን እምነታቸውን ጠብቀው ስለኖሩና መድኃኒታችንም ምሕረቱንና ደግነቱን ስላፈሰሰላቸው ሰዎች በዝርዝር መጻፍ እፈልጋለሁ።”

ያደረገው ጥልቅ ምርምር

ዩሲቢየስ ያነበባቸውም ሆኑ በምንጭነት የጠቀሳቸው መጻሕፍት በጣም ብዙ ናቸው። በመጀመሪያዎቹ ሦስት መቶ ዘመናት እንደ ዘመናችን አቆጣጠር ስለኖሩ ስለብዙዎቹ የታወቁ ሰዎች የተሟላ መረጃ ማግኘት የምንችለው ዩሲቢየስ ከጻፋቸው ጽሑፎች ብቻ ነው። የጽሑፍ ሥራዎቹ በዘመኑ ይደረጉ ስለነበሩ እንቅስቃሴዎች ጠቃሚ መረጃ ይሰጣሉ። መረጃዎቹን የጻፈው አሁን ሊገኙ ከማይችሉ ምንጮች ነው።

ዩሲቢየስ መረጃዎቹን በማሰባሰብ ረገድ ትጉህና ጥንቁቅ ነበር። ትክክለኛ የሆኑና ያልሆኑ መረጃዎችን ለመለየት ከፍተኛ ጥረት አድርጓል። ሆኖም ሥራው ምንም እንከን አልነበረውም ማለት አይደለም። አንዳንድ ሰዎችንና ድርጊቶቻቸውን በተሳሳተ መንገድ የተረዳባቸውና ትክክል ባልሆነ መንገድ የገለጸባቸው ጊዜያት ነበሩ። ታሪኮችን ሲመዘግብ የተፈጸሙበትን ጊዜ በተመለከተ የተሳሳተባቸው ጊዜያትም አሉ። ማራኪ የአጻጻፍ ስልትም አልነበረውም። ምንም እንኳን የጽሑፍ ሥራዎቹ አንዳንድ እንከኖች ቢኖሩባቸውም እንደ ውድ ቅርስ የሚታዩ ናቸው።

ለእውነት ፍቅር ነበረው?

ዩሲቢየስ በአብና በወልድ መካከል ያለውን ዝምድና በተመለከተ በወቅቱ ተነስቶ የነበረው ክርክር እልባት አለማግኘቱ ያሳስበው ነበር። ዩሲቢየስ ያምን እንደነበረው አብ ከወልድ በፊት ይኖር ነበርን? ወይስ ሁለቱም እኩል ዘመን ኖረዋል? “ሁለቱም እኩል ዘመን ከኖሩ አብ አባት ወልድ ደግሞ ልጅ ተብለው እንዴት ሊጠሩ ይችላሉ?” በማለት ጠይቋል። እንዲያውም ዮሐንስ 14:28 ላይ የሚገኘውን “ከእኔ አብ ይበልጣል” የሚለውንና ኢየሱስ በእውነተኛው አምላክ ‘እንደተላከ’ የሚናገረውን ዮሐንስ 17:3ን በመጥቀስ ለዚህ እምነቱ የጥቅስ ማስረጃ አቅርቧል። በቆላስይስ 1:15 እና በዮሐንስ 1:1 ላይ የሚገኘውን ሐሳብ በመጥቀስ ሎጎስ ወይም ቃል ‘የማይታየው አምላክ ምሳሌ’ ማለትም የአምላክ ልጅ እንደሆነ ተከራክሯል።

የሚያስገርመው ግን የኒቂያው ጉባኤ ሲጠናቀቅ ዩሲቢየስ ተቃራኒውን አመለካከት ደግፏል። አምላክና ክርስቶስ እኩል አይደሉም በሚለው በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ በተመሠረተው አቋሙ ከመጽናት ይልቅ የንጉሠ ነገሥቱን ውሳኔ ደግፏል።

ከዚህ የምናገኘው ትምህርት

ዩሲቢየስ ለኒቂያ ጉባኤ ውሳኔ እጅ የሰጠውና በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ ያልተመሠረተውን ሃይማኖታዊ ትምህርት የደገፈው ለምንድን ነው? ለአንድ ዓይነት ፖለቲካዊ ጥቅም ሲል ይሆን? ቀድሞውንስ በዚህ ስብሰባ ላይ ለምን ተገኘ? ለስብሰባው የተጠሩት ሁሉም ጳጳሳት ቢሆኑም እንኳ የተገኙት በጣም ጥቂት ማለትም 300 ብቻ ናቸው። ምናልባት ዩሲቢየስ የነበረውን ቦታ እንዳያጣ ፈርቶ ይሆን? ንጉሠ ነገሥት ቆስጠንጢኖስ ለእርሱ ከፍ ያለ አክብሮት እንዲኖረው ያደረገው ምንድን ነው? ዩሲቢየስ በጉባኤው ላይ ተቀምጦ የነበረው ከንጉሡ ቀኝ ነበር።

ዩሲቢየስ ኢየሱስ ተከታዮቹ ‘የዓለም ክፍል’ መሆን እንደሌለባቸው የሰጠውን መመሪያ ቸል እንዳለ ግልጽ ነው። (ዮሐንስ 17:16፤ 18:36) ደቀ መዝሙሩ ያዕቆብ “አመንዝሮች ሆይ፣ ዓለምን መውደድ ለእግዚአብሔር ጥል እንዲሆን አታውቁምን?” በማለት ጠይቋል። (ያዕቆብ 4:4) ጳውሎስ “ከማያምኑ ጋር በማይመች አካሄድ አትጠመዱ” ብሎ ምክር መስጠቱ ምንኛ ተገቢ ነው። (2 ቆሮንቶስ 6:14) አብን “በመንፈስና በእውነት” ስናመልክ ምንጊዜም ከዓለም የተለየን እንሁን።—ዮሐንስ 4:24

[በገጽ 31 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

የኒቂያን ጉባኤ የሚያሳይ ሥዕል

[ምንጭ]

Courtesy of Special Collections Library, University of Michigan

[ምንጭ]

Scala/Art Resource, NY