“ሁለት ሴቶች ቤታችንን አንኳኩ”
“ሁለት ሴቶች ቤታችንን አንኳኩ”
“ሕፃን ልጃችንን በሞት በማጣታችን ከባድ ሐዘን ላይ ከወደቅን ሁለት ዓመት አልፎናል።” በፈረንሳይ በሴንት ኤቴይን ከተማ በሚታተም ለ ፕሮግሬ በተባለ ጋዜጣ ላይ የወጣ አንድ ደብዳቤ የሚጀምረው እንዲህ በማለት ነበር።
“ልጃችን ሜሊሳ ትሪሶሚ 18 በተባለ ከባድ በሽታ የተያዘችው ገና የሦስት ወር ሕፃን ሳለች ነበር። የእርሷ ስቃይና ሞት ካስከተለብን መሪር ሐዘን መቼም ቢሆን መጽናናት የምንችል አይመስለኝም። ከልጅነታችን ጀምሮ የካቶሊክ እምነት ተከታዮች የነበርን ቢሆንም ‘አምላክ፣ በእርግጥ ካለህ እንዲህ ዓይነት መከራ ሲደርስብን ለምን ዝም ብለህ ትመለከታለህ?’ ብለን በተደጋጋሚ መጠየቃችን አልቀረም።” ደብዳቤውን የጻፈችው እናት በከባድ ሐዘን ተውጣና ተስፋ ቆርጣ እንደነበር ከዚህ መረዳት ይቻላል። ቀጥላ እንዲህ አለች:-
“ይህ ከሆነ ብዙም ሳይቆይ ሁለት ሴቶች ቤታችንን አንኳኩ። ገና ሳያቸው የይሖዋ ምሥክሮች እንደሆኑ ስለገባኝ ምንም ሳላስቀይማቸው በትሕትና ላሰናብታቸው አሰብኩ። ይሁን እንጂ በእጃቸው ላይ አንድ ብሮሹር ተመለከትሁ። ብሮሹሩ አምላክ መከራ እንዲኖር ስለፈቀደበት ምክንያት የሚናገር ነበር። ስለዚህ ወደ ቤት ላስገባቸውና አምላክ መከራን ስለፈቀደበት ምክንያት የሚናገሩት ሐሳብ ትክክል አለመሆኑን አሳምኜ ልሸኛቸው ወሰንኩ። የመከራ ጉዳይ ከተነሳ የእኛን ቤተሰብ ያህል መከራ የተፈራረቀበት እንደሌለና ‘አምላክ ሰጠ፣ አምላክ ወሰዳት’ እንደሚለው ካሉ በጣም የሰለቹን የማጽናኛ ቃላት የተለየ ነገር እንደማይነግሩኝ ተሰምቶኝ ነበር። ከምሥክሮቹ ጋር ከአንድ ሰዓት በላይ አብረን ቆየን። ስለደረሰብን ሁኔታ ስነግራቸው በአዘኔታ ያዳመጡኝ ሲሆን በመጨረሻ ሲሄዱ በተወሰነ መጠን ተጽናንቼ ስለነበር ሌላም ጊዜ እንዲመጡ ተስማማን። ይህ ከሆነ ሁለት ዓመታት አልፈዋል። የይሖዋ ምሥክር አልሆንኩም፤ ቢሆንም መጽሐፍ ቅዱስን የሚያስጠኑኝ ሲሆን የቻልኩትን ያህል በስብሰባዎቻቸው ላይ ለመገኘት ጥረት አደርጋለሁ።”