በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ዘዴኛ የመሆንን ጥበብ ማዳበር

ዘዴኛ የመሆንን ጥበብ ማዳበር

ዘዴኛ የመሆንን ጥበብ ማዳበር

ፔጊ ልጅዋ ታናሽ ወንድሙን ሲያመናጭቀው ተመለከተች። “ወንድምህን እንዲህ ብለህ መናገርህ ተገቢ ነው? እንዴት እንደተበሳጨ ተመልከት!” አለችው። እንዲህ ያለችው ለምን ነበር? ልጅዋ በንግግሩ ዘዴኛ እንዲሆንና ለሌሎች ስሜት አሳቢነት እንዲያሳይ እያሠለጠነችው ነበር።

ሐዋርያው ጳውሎስ በዕድሜ የሚያንሰውን የሥራ ባልደረባውን ጢሞቴዎስን ‘ለሰው ሁሉ ገር እንዲሆን [ወይም “ሰዎችን በዘዴ እንዲይዝ”]’ አበረታቶታል። ጢሞቴዎስ ይህንን ምክር ተግባራዊ በማድረግ የሌሎችን ስሜት ከመጉዳት መቆጠብ ይችላል። (2 ጢሞቴዎስ 2:24) ዘዴኛ መሆን ሲባል ምን ማለት ነው? በዚህ ረገድ ማሻሻያ ማድረግ የምትችለው እንዴት ነው? ሌሎች ይህንን ችሎታ እንዲያዳብሩ እንዴት መርዳት ትችላለህ?

ዘዴኛ መሆን ምን ማለት ነው?

ዘዴኛ መሆን በጥንቃቄ መያዝ ያለበትን ሁኔታ ተገንዝቦ ደግነት የተሞላበት ወይም ተገቢ የሆነ ነገር የማድረግ ወይም የመናገር ችሎታ ነው። ዘዴኛ የሆነ ሰው የሌሎችን ስሜት የሚረዳ ከመሆኑም በላይ ንግግሩ ወይም ድርጊቱ በሰዎች ላይ ምን ስሜት ሊያሳድር እንደሚችል ይገነዘባል።

የኤልሳዕ አገልጋይ ስለሆነው ስለ ግያዝ የሚናገረው የመጽሐፍ ቅዱስ ዘገባ ዘዴኛ ስላልሆነ ሰው የሚገልጽ ምሳሌ ይዟል። ልጅዋ በእቅፏ እያለ የሞተባት አንዲት ሱነማዊት ሴት መጽናኛ ለማግኘት ወደ ኤልሳዕ መጣች። የመጣችው በደኅና መሆኑን ስትጠየቅ “ደኅና ነው” የሚል መልስ ሰጠች። ሆኖም ወደ ነቢዩ ስትቀርብ “ግያዝ ሊያርቃት ቀረበ።” ኤልሳዕ ግን “ነፍስዋ አዝናለችና ተዋት” አለው።—2 ነገሥት 4:17-20, 25-27

ግያዝ እንደዚህ ያለ የችኮላና አሳቢነት የጎደለው እርምጃ የወሰደው ለምን ነበር? እርግጥ ሴትዮዋ ምን እንዳጋጠማት ስትጠየቅ ጉዳዩን አውጥታ አልተናገረችም። ደግሞም ብዙ ሰዎች የደረሰባቸውን ነገር ላገኙት ሰው ሁሉ መናገር አይፈልጉም። ይሁንና ስሜቷን ከፊቷ ማንበብ እንደሚቻል የታወቀ ነው። ከሁኔታው ማየት እንደሚቻለው ኤልሳዕ ስሜቷን ተረድቶላታል፤ ግያዝ ግን አልተረዳላትም አሊያም ሆን ብሎ ችላ ብሏል። ይህ ታሪክ አብዛኞቻችን አሳቢነት የጎደለው ድርጊት ወደመፈጸም የሚያመራንን ነገር ይጠቁመናል። አንድ ሰው ትኩረቱ ያረፈው ሥራው ላይ ብቻ ከሆነ የሌሎችን ፍላጎት መገንዘብ ወይም ማሟላት ሊሳነው ይችላል። ሁኔታው በሰዓቱ ለመድረስ ከመቸኮሉ የተነሳ መንገደኞችን ለመጫን ሳያቆም ከሚሄድ የአውቶቡስ ሹፌር ጋር ይመሳሰላል።

የሰዎችን ስሜት በትክክል ማወቅ ያስቸግራል። በመሆኑም እንደ ግያዝ ዘዴኛነት የጎደለው ድርጊት እንዳንፈጽም ደግነት ለማሳየት መጣር ይኖርብናል። የአንድን ሰው ስሜት ሊጠቁሙ የሚችሉ ሁኔታዎችን ለማስተዋልና ደግነት በተሞላበት ቃል ወይም ድርጊት ምላሽ ለመስጠት ምንጊዜም ንቁ መሆን ይገባናል። በዚህ ረገድ ችሎታህን ማሻሻል የምትችለው እንዴት ነው?

የሌሎችን ስሜት መረዳት

ኢየሱስ የሰዎችን ስሜት በመረዳትና ከሁሉ በተሻለ መንገድ ደግነት ሊያሳያቸው የሚችለው እንዴት እንደሆነ በማስተዋል ረገድ የላቀ ችሎታ ነበረው። በአንድ ወቅት ስምዖን በተባለ ፈሪሳዊ ቤት በማዕድ ተቀምጦ እያለ “በዚያች ከተማ ኃጢአተኛ የነበረች” አንዲት ሴት ወደ እርሱ ቀረበች። እንደ ሱነማዊቷ ሴት ሁሉ ይህቺ ሴትም ምንም የተናገረችው ነገር አልነበረም። ሆኖም ከአድራጎቷ በመነሳት ብዙ ማወቅ ይቻላል። “ሽቱ የሞላበት የአልባስጥሮስ ቢልቃጥ አመጣች። በስተ ኋላውም [በኢየሱስ እግር] አጠገብ ቆማ እያለቀሰች በእንባዋ እግሩን ታርስ ጀመረች፣ በራስ ጠጒርዋም ታብሰው እግሩንም ትስመው ሽቱም ትቀባው ነበረች።” ኢየሱስ ይህንን ሁሉ ያደረገችው ለምን እንደሆነ ተገንዝቦ ነበር። ከዚህም በላይ ስምዖን አፍ አውጥቶ ባይናገርም “ይህስ ነቢይ ቢሆን፣ ይህች የምትዳስሰው ሴት ማን እንደ ሆነች እንዴትስ እንደ ነበረች ባወቀ ነበር፣ ኃጢአተኛ ናትና” በማለት በልቡ እንዳሰበ ኢየሱስ አውቋል።—ሉቃስ 7:37-39

ኢየሱስ ሴትዮዋን አባርሯት ቢሆን ወይም ስምዖንን “አንተ የማታስተውል! ንስሐ እንደገባች አትመለከትም?” ብሎት ቢሆን ኖሮ ምን ያህል ስሜታቸውን ይጎዳው እንደነበረ መገመት ትችላለህ? ከዚህ ይልቅ ኢየሱስ አንደኛው ብዙ፣ ሌላው ደግሞ ትንሽ ዕዳ የነበረባቸውን ሁለት ሰዎች በነፃ ስለተወላቸው አበዳሪ የሚገልጽ ምሳሌ ለስምዖን ነገረው። ከዚያም “ከእነርሱ አብልጦ የሚወደው ማንኛው ነው?” ብሎ ጠየቀው። በዚህ መንገድ ኢየሱስ ስምዖንን ከመንቀፍ ይልቅ ለሰጠው ትክክለኛ ምላሽ ሊያመሰግነው ችሏል። ቀጥሎም የሴትዮዋን እውነተኛ ስሜትና ንስሐ መግባቷን የሚያሳዩትን በርካታ ሁኔታዎች እንዲገነዘብ በደግነት ረዳው። ኢየሱስ ወደ ሴትዮዋ በመዞር ስሜቷን እንደተረዳላት በደግነት ገለጸላት። ኃጢአቷ እንደተሰረየላት ከነገራት በኋላ “እምነትሽ አድኖሻል፤ በሰላም ሂጂ አላት።” አሳቢነት የተንጸባረቀባቸው እነዚህ ቃላት ሴትዮዋ ትክክል የሆነውን ነገር ለማድረግ የወሰደችውን አቋም ምንኛ አጠናክረውላት ይሆን! (ሉቃስ 7:40-50) ኢየሱስ ሰዎችን በዘዴ በመያዝ ረገድ ሊሳካለት የቻለው የሰዎችን ስሜት ይረዳና ርኅራኄ ያሳያቸው ስለነበረ ነው።

ኢየሱስ ስምዖንን እንደረዳው ሁሉ እኛም የሰዎችን ስሜት ከሁኔታቸው መረዳትን መማርና ሌሎችም ተመሳሳይ ችሎታ እንዲያዳብሩ መርዳት እንችላለን። ልምድ ያላቸው የምስራቹ ሰባኪዎች በክርስቲያናዊ አገልግሎት በሚካፈሉበት ወቅት አዲሶች ይህንን ችሎታ እንዲያዳብሩ ሊያሠለጥኗቸው ይችላሉ። ለአንድ ሰው ምስራቹን ከሰበኩ በኋላ ስለ ግለሰቡ ስሜት የሚገልጹትን ሁኔታዎች መለስ ብለው ሊያጤኑ ይችላሉ። ግለሰቡ ፍርሃት ይነበብበታል? ተጠራጣሪ ነው? ተቆጥቷል? ወይስ ሥራ በዝቶበታል? ይህንን ሰው ደግነት በተሞላበት መንገድ ልንረዳው የምንችለው እንዴት ነው? በተጨማሪም ሽማግሌዎች፣ እርስ በእርስ ባላቸው ግንኙነት ረገድ ዘዴኛ ባለመሆናቸው ምክንያት የተቀያየሙ ወንድሞችንና እህቶችን ሊረዱ ይችላሉ። አንዳቸው የሌላውን ስሜት መረዳት እንዲችሉ እርዷቸው። ግለሰቡ ዘለፋ እንደተሰነዘረበት፣ ችላ እንደተባለ ወይም ሰዎች በትክክል እንዳልተረዱት ተሰምቶታል? ደግነት ማሳየት የተሻለ ስሜት ሊያሳድርበት ይችል ይሆን?

ወላጆች ልጆቻቸው በንግግራቸውም ሆነ በድርጊታቸው ዘዴኛ እንዲሆኑ ለመርዳት የርኅራኄን ስሜት እንዲያዳብሩ ሊያሠለጥኗቸው ይገባል። በመግቢያው ላይ የተጠቀሰው የፔጊ ልጅ የታናሽ ወንድሙ ፊት መለዋወጡን፣ ማኩረፉንና፣ ዓይኖቹ እንባ ማቅረራቸውን ሲመለከት ወንድሙን እንደጎዳው ተገነዘበ። እናቱ እንደጠበቀችው በሥራው ተጸጽቶ ለውጥ ለማድረግ ወሰነ። ሁለቱም የፔጊ ልጆች በትንሽነታቸው የቀሰሙትን ይህንን ትምህርት ጥሩ አድርገው የተጠቀሙበት ሲሆን ከዓመታት በኋላ በክርስቲያን ጉባኤ ውስጥ ደቀ መዛሙርት በማድረጉ ሥራ ውጤታማ ለመሆንና በእረኝነት ለማገልገል በቅተዋል።

አመለካከታቸውን መረዳትህን ግለጽ

በአንድ ሰው ላይ ቅሬታ በሚኖርህ ጊዜ ዘዴኛ መሆንህ ይበልጥ አስፈላጊ ይሆናል። አለዚያ የግለሰቡን ክብር በቀላሉ ልትነካበት ትችላለህ። ምንጊዜም ቢሆን በቅድሚያ መልካም ጎኖቹን ማድነቅህ ተገቢ ነው። ግለሰቡን ከመውቀስ ይልቅ ችግሩ ላይ አነጣጥር። አድራጎቱ ስሜትህን እንዴት እንደነካውና እንዲያስተካክል የምትፈልገውን ነገር በግልጽ አስረዳው። ከዚያም የሚናገረውን ለማዳመጥ ፈቃደኛ ሁን። ምናልባትም ግለሰቡን በተሳሳተ መንገድ ተረድተኸው ሊሆን ይችላል።

ሰዎች በሐሳባቸው ባትስማማም እንኳ አመለካከታቸውን እንደተረዳህላቸው ማወቅ ይፈልጋሉ። ኢየሱስ የማርታን ጭንቀት እንደተረዳ በሚገልጽ መንገድ በዘዴ አናግሯታል። “ማርታ፣ ማርታ፣ በብዙ ነገር ትታወኪማለሽ” አላት። (ሉቃስ 10:41) በተመሳሳይም አንድ ሰው ችግሩን ሲያካፍልህ ጉዳዩን በሚገባ ሳትሰማ መፍትሔ ለማቅረብ ከመቸኮል ይልቅ በራስህ አባባል ችግሩን ወይም ቅሬታውን ደግመህ በመናገር ሐሳቡን መረዳትህን በዘዴ ማሳወቅ ትችላለህ። በዚህ መንገድ ሐሳቡን እንደተረዳህለት በደግነት ማሳየት ትችላለህ።

አላስፈላጊ የሆነ ነገር አትናገር

ንግሥት አስቴር ሐማ አይሁዳውያንን ለማጥፋት የጠነሰሰውን ሴራ እንዲያከሽፍ ባሏን መጠየቅ በፈለገች ጊዜ ባለቤቷ ዘና ያለ መንፈስ እንዲኖረው ለማድረግ በዘዴ ሁኔታዎችን አመቻቸች። ይህንን ከባድ ጉዳይ የነገረችው ከዚያ በኋላ ነበር። ይሁን እንጂ አስቴር ሳትናገር የቀረችው ነገር እንዳለ ልብ ማለቱም ጠቃሚ ነው። ለዚህ የክፋት ሴራ ባሏ ያበረከተውን አስተዋጽኦ በዘዴ ሳትጠቅስ አልፋለች።—አስቴር 5:1-8፤ 7:1, 2፤ 8:5

በተመሳሳይም አማኝ ያልሆነን የአንዲት ክርስቲያን ባል በምትጠይቁበት ጊዜ በቀጥታ የመጽሐፍ ቅዱስ ውይይት ከመጀመር ይልቅ ትኩረቱን ስለሚስቡት ነገሮች ለምን በዘዴ አትጠይቁትም? አንድ እንግዳ ሰው ለስብሰባ ተስማሚ ያልሆነ ልብስ ለብሶ ቢመጣ ወይም ረዘም ላለ ጊዜ ከስብሰባ ቀርቶ የነበረ ሰው እንደገና ቢመጣ ስለ አለባበሱ ወይም ከጉባኤ ስለመቅረቱ ከመናገር ይልቅ ሞቅ ያለ አቀባበል አድርጉለት። እንዲሁም ፍላጎት ያሳየ አንድ አዲስ ሰው የተሳሳተ አመለካከት እንዳለው ብትገነዘቡ ወዲያው ከማረም መቆጠቡ የተሻለ ሊሆን ይችላል። (ዮሐንስ 16:12) ዘዴኛ መሆን መናገር የሌለባችሁን ነገር በመገንዘብ ደግነት ማሳየትንም ይጨምራል።

ፈዋሽ የሆነ ንግግር

በንግግርህ ዘዴኛ የመሆንን ችሎታ ማዳበርህ አንድ ሰው በተሳሳተ መንገድ ቢረዳህ እንዲሁም ቢጠላህና ቢቀየምህ እንኳ ከሰዎች ጋር ሰላማዊ ግንኙነትህን ጠብቀህ ለመቀጠል ያስችልሃል። ለምሳሌ የኤፍሬም ሰዎች ጌዴዎንን ‘ጽኑ ጥል በተጣሉት’ ጊዜ የተከሰተውን ነገር በግልጽ በማስረዳትና የኤፍሬም ሰዎች ስላገኙት ድል በሐቀኝነት በመናገር በዘዴ መልስ ሰጥቷቸዋል። የተናደዱበት ምክንያት ስለገባው የሰጠው መልስ ዘዴ የተሞላበት ሲሆን ያሳየው ትሕትናም ቁጣቸውን ለማብረድ አስችሏል።—መሳፍንት 8:1–3፤ ምሳሌ 16:24

ምንጊዜም ቢሆን የምትናገረው ነገር የሌሎችን ስሜት እንዴት ሊነካ እንደሚችል ለማሰብ ሞክር። ዘዴኛ ለመሆን ጥረት ማድረግህ በምሳሌ 15:23 ላይ የተገለጸው ዓይነት ደስታ እንድታገኝ ያስችልሃል:- “ሰው በአፉ መልስ ደስ ይለዋል፤ ቃልም በጊዜው ምንኛ መልካም ነው!”

[በገጽ 31 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ወላጆች ልጆቻቸውን ለሌሎች ስሜት እንዲያስቡ ማሠልጠን ይችላሉ

[በገጽ 31 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ልምድ ያላቸው ክርስቲያን አገልጋዮች አዲሶች ዘዴኛ እንዲሆኑ ማስተማር ይችላሉ