በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የአንባቢያን ጥያቄዎች

የአንባቢያን ጥያቄዎች

የአንባቢያን ጥያቄዎች

ይሖዋ ጥንት አገልጋዮቹ ለነበሩት እስራኤላውያን ከአንድ በላይ እንዲያገቡ ፈቅዶላቸው ነበር። አሁን ግን ይህ ልማድ ተከልክሏል። ይህ፣ አቋሙ ተለዋዋጭ እንደሆነ ያሳያል?

ይሖዋ ከአንድ በላይ ሚስት ማግባትን በተመለከተ ያለው አቋም አልተለወጠም። (መዝሙር 19:7፤ ሚልክያስ 3:6) መጀመሪያም ቢሆን ሰዎች ከአንድ በላይ እንዲያገቡ ዓላማው አልነበረም፤ አሁንም አይደለም። ይሖዋ ለአዳም ሚስት እንድትሆነው ሔዋንን በፈጠረ ጊዜ ለአንድ ባል አንዲት ሚስት የሚል አቋም እንዳለው ገልጿል። እንዲህ አለ:- “ሰው አባቱንና እናቱን ይተዋል፣ በሚስቱም ይጣበቃል፤ ሁለቱም አንድ ሥጋ ይሆናሉ።”—ዘፍጥረት 2:24

ኢየሱስ ክርስቶስ ምድር ላይ በነበረበት ወቅት ፍቺንና እንደገና ማግባትን አስመልክቶ ለቀረበለት ጥያቄ መልስ ሲሰጥ ይህንን ደንብ በድጋሚ ጠቅሶላቸው ነበር። እንዲህ አለ:- “ፈጣሪ በመጀመሪያ ወንድና ሴት አደረጋቸው፣ አለም:- ስለዚህ ሰው አባቱንና እናቱን ይተዋል፣ ከሚስቱም ጋር ይተባበራል፣ ሁለቱም አንድ ሥጋ ይሆናሉ የሚለውን ቃል አላነበባችሁምን? ስለዚህ አንድ ሥጋ ናቸው እንጂ ወደ ፊት ሁለት አይደሉም።” አክሎም “ያለ ዝሙት ምክንያት ሚስቱን ፈትቶ ሌላዪቱን የሚያገባ ሁሉ ያመነዝራል፣ የተፈታችውንም የሚያገባ ያመነዝራል” አላቸው። (ማቴዎስ 19:4-6, 9) ከዚህ አንጻር ከአንድ በላይ ሚስት ማግባት እንደ ምንዝር እንደሚቆጠር በግልጽ መረዳት ይቻላል።

ታዲያ ጥንት ከአንድ በላይ ማግባት ተፈቅዶ የነበረው ለምንድን ነው? ይህን ልማድ ያስጀመረው ይሖዋ እንዳልሆነ ልብ በል። በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ለመጀመሪያ ጊዜ ከአንድ በላይ ሚስቶች እንደነበሩት የተገለጸው በቃየን የትውልድ መስመር የመጣው ላሜሕ ነበር። (ዘፍጥረት 4:19-24) ይሖዋ በኖኅ ዘመን የጥፋት ውኃ ባመጣበት ወቅት ኖኅ እና ሦስት ልጆቹ አንድ አንድ ሚስት ብቻ ነበሯቸው። ከአንድ በላይ ሚስት የነበራቸው ሁሉ በውኃው ጠፍተዋል።

ከብዙ መቶ ዓመታት በኋላ ይሖዋ እስራኤላውያንን ሕዝቡ አድርጎ ሲመርጣቸው በመካከላቸው ከአንድ ሚስት በላይ ያገቡ ቢኖሩም በአብዛኛው የተለመደው ግን አንድ ሚስት ብቻ ማግባት ነበር። አምላክ ከአንድ ሚስት በላይ ያገቡ ወንዶች ሚስቶቻቸውን እንዲፈቱና ቤተሰባቸው እንዲበታተን ከማድረግ ይልቅ ይህን ልማድ አስመልክቶ አንዳንድ ጥብቅ ሕጎችን ሰጣቸው።—ዘጸአት 21:10, 11፤ ዘዳግም 21:15-17

ኢየሱስ ጋብቻን በሚመለከት አምላክ ያወጣውን የመጀመሪያውን ሥርዓት አስመልክቶ የተናገረው ሐሳብ ይሖዋ ከአንድ በላይ ማግባትን የፈቀደው ለጊዜው ብቻ እንደሆነ የሚያሳይ ነው። ሐዋርያው ጳውሎስም በመንፈስ አነሳሽነት “ለእያንዳንዱ ለራሱ ሚስት ትኑረው ለእያንዳንዲቱ ደግሞ ለራስዋ ባል ይኑራት” በማለት ከዚህ ጋር የሚስማማ ሐሳብ ተናግሯል። (1 ቆሮንቶስ 7:2) በተጨማሪም ጳውሎስ በክርስቲያን ጉባኤ ውስጥ የበላይ ተመልካች ወይም የጉባኤ አገልጋይ ሆኖ የተሾመ አንድ ሰው “የአንዲት ሚስት ባል” መሆን እንዳለበት ጽፏል።—1 ጢሞቴዎስ 3:2, 12፤ ቲቶ 1:6

በመሆኑም የዛሬ 2,000 ዓመት ገደማ የክርስቲያን ጉባኤ ሲቋቋም ከአንድ በላይ ሚስት የማግባት ልማድ ተከለከለ። በዚህ ወቅት የመጀመሪያዎቹ ወንድና ሴት በተፈጠሩበት ጊዜ የነበረው አንድ ሚስት ለአንድ ባል የሚለው የጋብቻ ሥርዓት ተመልሶ በሥራ ላይ ዋለ። በአሁኑ ጊዜም በዓለም ዙሪያ የአምላክ ሕዝቦች ይህንን ሥርዓት ይከተላሉ።—ማርቆስ 10:11, 12፤ 1 ቆሮንቶስ 6:9, 10