በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ታስታውሳለህን?

ታስታውሳለህን?

ታስታውሳለህን?

በቅርቡ የወጡትን የመጠበቂያ ግንብ እትሞች አንብበሃቸዋልን? እስቲ የሚከተሉትን ጥያቄዎች ለመመለስ ሞክር:-

ሩት የላቀ ምሳሌ የተወችው በምን በምን ነገሮች ነው?

ሩት ለይሖዋ ባላት ፍቅር፣ ለኑኃሚን ባሳየችው ደግነት፣ በታታሪነቷና በትሕትናዋ የላቀ ምሳሌ ትታለች። በሰዎች ዘንድ “ምግባረ መልካም ሴት” የሚል ስም ማትረፏ የተገባ ነው። (ሩት 3:11)—4/15 ገጽ 23-6

• ይሖዋ ተራ ለሆኑ ሰዎችም እንደሚያስብ እንዴት እናውቃለን?

በግብጽ በጭቆና ቀንበር ሥር ለነበሩት እስራኤላውያን ድሆችን እንዳያንገላቱ ነግሯቸው ነበር። (ዘጸአት 22:21-24) አባቱን ለመምሰል ይጥር የነበረው ኢየሱስ ተራ ለሆኑ ሰዎች ከልብ ያስብላቸው ነበር። ሐዋርያቱ እንዲሆኑ የመረጣቸው ሰዎችም “ያልተማሩ ተራ ሰዎች” ነበሩ። (ሥራ 4:13 አ.መ.ትማቴዎስ 9:36) እኛም ወጣቶችን ጨምሮ ለሌሎች ሰዎች አሳቢነት በማሳየት አምላክን መምሰል እንችላለን።—4/15 ገጽ 28-31

• ይሖዋ የምናደርገውን በቁም ነገር ይመለከተዋል ብለን እንድናምን የሚያደርጉ ምን ማስረጃዎች አሉ?

ይሖዋ ሰዎች የሚያደርጉትን በቁም ነገር እንደሚመለከት የመጽሐፍ ቅዱስ ዘገባዎች ያሳያሉ። አቤል ያቀረበውን መሥዋዕት በአድናቆት የተመለከተው ሲሆን እኛም የምናቀርበውን ‘የምሥጋና መሥዋዕት ማለትም የከንፈሮች ፍሬ’ ከፍ አድርጎ ይመለከታል። (ዕብራውያን 13:15) ይሖዋ፣ ሔኖክ አኗኗሩን ንጹሕ በማድረግና ሥነ ምግባሩን በመጠበቅ እርሱን ለማስደሰት ያደረገውን ጥረት በሚገባ ተመልክቷል። በሰራፕታ ከተማ የምትኖር ከአሕዛብ ወገን የሆነች አንዲት መበለት የነበራትን በጣም አነስተኛ ምግብ ለነቢዩ ኤልያስ በማካፈል ያሳየችውን ደግነት አምላክ በቁም ነገር ተመልክቶታል። እኛም የምናከናውነውን የእምነት ሥራ በቁም ነገር ይመለከተዋል።—5/1 ገጽ 28-31

በ33 እዘአ ከተከበረው የጰንጠቆስጤ በዓል በኋላ የተጠመቁ አይሁዳውያን በግለሰብ ደረጃ ራሳቸውን ለአምላክ መወሰን ያስፈለጋቸው ለምን ነበር?

በ1513 ከዘአበ የጥንት እስራኤላውያን ለአምላክ የተወሰኑ ሕዝብ ሆነው ነበር። (ዘጸአት 19:3-8) ተተኪዎቹ የአይሁድ ትውልዶች በሙሉ የተወለዱት ራሱን ለአምላክ በወሰነ ብሔር ውስጥ ነበር። ይሁን እንጂ ይሖዋ በ33 እዘአ የሕጉን ቃል ኪዳን በክርስቶስ ሞት አማካኝነት አስወገደው። (ቆላስይስ 2:14) ከዚያ በኋላ አምላክን ተቀባይነት ባለው መንገድ ለማምለክ የሚፈልጉ አይሁዳውያን ሁሉ ራሳቸውን ለእርሱ መወሰንና በኢየሱስ ክርስቶስ ስም መጠመቅ ነበረባቸው።—5/15 ገጽ 30-1

በዘመናችን ዕጣን ማጤስ በእውነተኛው አምልኮ ውስጥ ቦታ አለው?

በጥንት እስራኤላውያን ዘንድ ዕጣን ማጤስ በእውነተኛው አምልኮ ውስጥ ጉልህ ቦታ ነበረው። (ዘጸአት 30:37, 38፤ ዘሌዋውያን 16:12, 13) ይሁን እንጂ ዕጣን ማጤስን ጨምሮ የሕጉ ቃል ኪዳን በክርስቶስ ሞት አክትሟል። በጊዜያችን ዕጣን ማጤስ የእውነተኛው አምልኮ ክፍል አይደለም፤ ሆኖም እያንዳንዱ ክርስቲያን ሃይማኖታዊ ላልሆነ ዓላማ ዕጣን ለማጤስ ወይም ላለማጤስ የራሱን ውሳኔ ሊያደርግ ይችላል። ይህን ውሳኔ በሚያደርግበት ጊዜ ግን ሌሎችን ላለማሰናከል የሰዎችን ስሜት ከግምት ማስገባቱ አስፈላጊ ነው።—6/1 ገጽ 28-30

ብዙዎች ኢየሱስ በምድር ላይ ኖሯል ለሚለው እውነታ ትኩረት እንዲሰጡ ያነሳሳቸው የትኛው የቅርብ ጊዜ ግኝት ነው?

በእስራኤል የተገኘ አንድ የአጽም ማስቀመጫ ሣጥን በቅርቡ የብዙዎችን ትኩረት ስቦ ነበር። ሣጥኑ በመጀመሪያው መቶ ዘመን እንደተሠራ የሚገመት ሲሆን በላዩ ላይ “የኢየሱስ ወንድም የዮሴፍ ልጅ ያዕቆብ” የሚል ጽሕፈት ተቀርጾበታል። አንዳንዶች ይህ ሣጥን ከመጽሐፍ ቅዱስ ሌላ ኢየሱስ በምድር ላይ መኖሩን ከሚያረጋግጡት “አርኪኦሎጂያዊ ማስረጃዎች ሁሉ ጥንታዊው” እንደሆነ ይናገራሉ።—6/15 ገጽ 3-4

አንድ ሰው ፍቅርን ማዳበር የሚችለው እንዴት ነው?

ሰዎች በመጀመሪያ ደረጃ ፍቅርን የሚማሩት ከወላጆቻቸው ነው። ባልና ሚስት እርስ በርሳቸው ሲዋደዱና ሲከባበሩ ልጆች ፍቅርን ሊማሩ ይችላሉ። (ኤፌሶን 5:28፤ ቲቶ 2:4) አንድ ሰው ፍቅር በሌለበት ቤተሰብ ውስጥ ቢያድግ እንኳ በይሖዋ አባታዊ መመሪያ እንዲሁም ከመንፈስ ቅዱስና ከክርስቲያን ወንድሞች በሚያገኘው ድጋፍ አማካኝነት ፍቅርን ማዳበር ይችላል።—7/1 ገጽ 4-7

ዩሲቢየስ ማን ነበር? ከእርሱ ሕይወትስ ምን ትምህርት እናገኛለን?

ዩሲቢየስ በ324 እዘአ ሂስትሪ ኦቭ ዘ ክርስቺያን ቸርች (የቤተ ክርስቲያን ታሪክ) የተባለ ባለ አሥር ጥራዝ መጽሐፍ የጻፈ ጥንታዊ ታሪክ ጸሐፊ ነው። አብ ከወልድ በፊት እንደነበር ቢያምንም በኒቂያ ጉባኤ ላይ የተደነገገውን ከዚህ የተለየ አመለካከት ደግፏል። ዩሲቢየስ ኢየሱስ ተከታዮቹ ‘የዓለም ክፍል’ መሆን እንደሌለባቸው የሰጠውን መመሪያ ቸል እንዳለ ግልጽ ነው። (ዮሐንስ 17:16)—7/15 ገጽ 29-31

ይሖዋ ከአንድ በላይ ሚስት ማግባትን በተመለከተ ያለው አቋም ተለውጧል?

ይሖዋ ከአንድ በላይ ሚስት ማግባትን በተመለከተ ያለው አቋም አልተለወጠም። (ሚልክያስ 3:6) አምላክ ለመጀመሪያው ሰው ለአዳም ያደረገው የጋብቻ ዝግጅት ‘በሚስቱ እንዲጣበቅና’ ሁለቱም አንድ ሥጋ እንዲሆኑ ነበር። (ዘፍጥረት 2:24) ኢየሱስ ያለ ዝሙት ምክንያት የትዳር ጓደኛን መፍታትና ሌላ ማግባት ምንዝር እንደሆነ ተናግሯል። (ማቴዎስ 19:4-6, 9) በመሆኑም የክርስቲያን ጉባኤ ሲቋቋም ከአንድ በላይ ሚስት ማግባት ተከልክሏል።—8/1 ገጽ 28