በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

እውነተኛው አምልኮ ቤተሰብን አንድ ያደርጋል

እውነተኛው አምልኮ ቤተሰብን አንድ ያደርጋል

እውነተኛው አምልኮ ቤተሰብን አንድ ያደርጋል

ማሪያ የ13 ዓመት ልጅ ሳለች አንድ ዘመዷ ለእርሷና ለታናሽ እህቷ ለሉሲ ስለ ይሖዋ እንዲሁም ምድር ገነት እንደምትሆን ስለሚገልጸው ተስፋ ነገራቸው። ይበልጥ የማወቅ ፍላጎት ስላደረባቸው አብረውት በይሖዋ ምሥክሮች ስብሰባ ላይ ተገኙ። ማሪያ በስብሰባው ላይ በተሰጠው ትምህርት በጣም ተደነቀች። በአብዛኛው መዝሙር ከመዘመር ሌላ ብዙም ትምህርት ከማይሰጥበት ከቤተ ክርስቲያን በጣም የተለየ ሆነባት። ብዙም ሳይቆይ ማሪያና ሉሲ ከአንዲት የይሖዋ ምሥክር ጋር መጽሐፍ ቅዱስን ማጥናት ጀመሩ።

ታላቅ ወንድማቸው ሁጎ ስለ ፍልስፍናና ስለ ዝግመተ ለውጥ ይበልጥ ለማወቅ ጥረት ያደርግ የነበረ ሲሆን በአምላክ መኖር እንደማያምንም ይናገር ነበር። ይሁን እንጂ በብሔራዊ ውትድርና ግዳጅ ላይ ሳለ ሕይወት እንዴት ተገኘ? በዝግመተ ለውጥ ወይስ በፍጥረት? a የተባለውን መጽሐፍ አነበበ። የትኛውም ሃይማኖት ሊመልሳቸው ለማይችላቸው ጥያቄዎች መልስ አገኘ። ወታደራዊ ግዳጁን ካጠናቀቀ በኋላ መጽሐፍ ቅዱስን በማጥናትና ከእህቶቹ ጋር በስብሰባዎች ላይ በመገኘት ስለ አምላክ መኖር ያገኘውን እምነት ማጠናከር ጀመረ። ማሪያና ሉሲ እውነትን ከሰሙ ከሁለት ዓመት በኋላ በ1992 የተጠመቁ ሲሆን ሁጎ ደግሞ ከሁለት ዓመት በኋላ ተጠመቀ።

ይህ ሁሉ ሲሆን አጥባቂ ካቶሊክ የነበሩት ወላጆቻቸው ለመጽሐፍ ቅዱስ እውነት እምብዛም ፍላጎት አልነበራቸውም። የይሖዋ ምሥክሮችን የማይወዱ ቢሆንም እንኳ ልጆቻቸው ቤት ጋብዘው የሚያመጧቸውን ወጣት ምሥክሮች ጠባይና አለባበስ ያደንቁ ነበር። እንዲሁም ልጆቻቸው በምግብ ሰዓት በስብሰባ ላይ የተማሯቸውን ነገሮች ሲወያዩ ሲሰሙ የማወቅ ፍላጎታቸው ቀስ በቀስ እየጨመረ መጣ።

ቢሆንም ሁለቱም ወላጆች ከጥንቆላ ጋር የተያያዙ ድርጊቶች ይፈጽሙ ነበር። አባትየው ሰክሮ ሚስቱን ይደበድብ የነበረ ከመሆኑም በላይ ቤተሰቡም ሊበታተን በቋፍ ላይ ነበር። ከዚያም አባትየው ሰክሮ በመረበሹ ሁለት ሳምንታት ታሰረ። በእስር ቤት ሳለ መጽሐፍ ቅዱስን ማንበብ ጀመረ። ኢየሱስ ስለ መጨረሻው ዘመን የተናገራቸውን ምልክቶች ሲያነብ በርካታ ጥያቄዎች ፈጠረበት። በዚህም የተነሳ እርሱና ሚስቱ በመንግሥት አዳራሽ በሚደረገው ስብሰባ ላይ ተገኙና መጽሐፍ ቅዱስን እንዲያጠኑ የቀረበላቸውን ግብዣ ተቀበሉ። የመጽሐፍ ቅዱስን እውነት ሲማሩ ከጥንቆላ ጋር የተያያዙ መጽሐፎቻቸውን በሙሉ ያጠፉ ሲሆን የይሖዋን ስም በመጥራት ከአጋንንት ጥቃት ተገላገሉ። ጉልሕ የባሕርይ ለውጥም አደረጉ።

ማሪያና ሉሲ ወላጆቻቸው በ1999 በቦሊቪያ በተደረገ የአውራጃ ስብሰባ ላይ በወንድማቸው በሁጎ ሲጠመቁ ሲመለከቱ ምን ያህል እንደተደሰቱ መገመት አያዳግትህም። ማሪያና ሉሲ ስለ ይሖዋና ስለሰጣቸው ተስፋዎች ከሰሙ ዘጠኝ ዓመታት አልፈዋል። አሁን ከሁጎ ጋር የሙሉ ጊዜ አገልጋዮች ሆነዋል። ቤተሰባቸው በእውነተኛው አምልኮ ምክንያት አንድ በመሆኑ በጣም ደስተኞች ናቸው!

[የግርጌ ማስታወሻ]

a በይሖዋ ምሥክሮች የታተመ።