ደግነትን ይወድድ ነበር
ደግነትን ይወድድ ነበር
የአስተዳደር አካል አባል ሆኖ ለረጅም ዓመታት ያገለገለው ወንድም ሚልተን ጂ ሄንሽል በተወለደ በ82 ዓመቱ ቅዳሜ፣ መጋቢት 22, 2003 ምድራዊ ሕይወቱን አጠናቅቋል።
ወንድም ሄንሽል በይሖዋ ምሥክሮች ዋና መሥሪያ ቤት መሥራት የጀመረው ገና በወጣትነቱ ሲሆን ከ60 ለሚበልጡ ዓመታት በታማኝነት አገልግሏል። በአስተዋይነቱና ለስብከቱ ሥራ ባለው ቅንዓት ለመታወቅ ብዙም ጊዜ አልፈጀበትም። በ1939 ብሩክሊን በሚገኘው የይሖዋ ምሥክሮች የኅትመት ክፍል የበላይ ተመልካች ለነበረው ለወንድም ናታን ኤች ኖር ጸሐፊ ሆነ። ወንድም ኖር በ1942 የይሖዋ ምሥክሮችን ዓለም አቀፋዊ ሥራ በበላይነት መምራት ሲጀምር ወንድም ሄንሽልን ረዳቱ አደረገው። ወንድም ሄንሽል በ1956 ሉሴል ቤኔት የምትባል እህት ያገባ ሲሆን አስደሳች ጊዜያትንም ሆነ ተፈታታኝ ሁኔታዎችን አብረው አሳልፈዋል።
ወንድም ኖር በ1977 እስከሞተበት ጊዜ ድረስ ወንድም ሄንሽል ከእርሱ ጋር ተቀራርቦ ይሠራ ነበር። ወንድም ሄንሽል አብዛኛውን ጊዜ ከወንድም ኖር ጋር በመሆን በዓለም ዙሪያ የሚገኙ የይሖዋ ምሥክሮችን በተለይም ደግሞ ሚስዮናውያንንና በቅርንጫፍ ቢሮዎች ውስጥ የሚሠሩ የሙሉ ጊዜ አገልጋዮችን ለማበረታታት ከ150 ወደሚበልጡ አገሮች ተጉዟል። ከእነዚህ ጉዞዎች ውስጥ አንዳንዶቹ አስቸጋሪ ብሎም አደገኛ ነበሩ። በ1963 ወንድም ሄንሽል በላይቤሪያ በተደረገ አንድ የአውራጃ ስብሰባ ላይ በተገኘበት ወቅት ለባንዲራ ሰላምታ ለመስጠት ፈቃደኛ ባለመሆኑ ምክንያት ከባድ እንግልት ደርሶበት ነበር። a ወንድም ሄንሽል በዚህ ሳይበገር በላይቤሪያ ለሚገኙ የይሖዋ ምሥክሮች የአምልኮ ነጻነት ለማስገኘት ከአገሪቱ ፕሬዚዳንት ጋር ለመነጋገር ከጥቂት ወራት በኋላ ወደዚያ ሄዷል።
ወንድም ሄንሽል የሚያጋጥሙትን አስቸጋሪ ሁኔታዎችና ፈተናዎች በመወጣት ረገድ ቆራጥ፣ ከሁኔታዎች ጋር ራሱን የሚያስማማና ምክንያታዊ ሰው በመሆኑ ይታወቃል። አብረውት የሚሠሩት ሁሉ ሥርዓታማነቱንና ትሕትናውን እንዲሁም ቀልደኛነቱን ያደንቁለታል። አስገራሚ የማስታወስ ችሎታ የነበረው ወንድም ሄንሽል በዓለም ዙሪያ ካሉ ሚስዮናውያን ጋር በሚገናኝበት ወቅት በስማቸው በመጥራት እንዲሁም በአገሬው ቋንቋ አንድ ወይም ሁለት ሐረጎችን ወይም የቀልድ አባባሎችን ጣል በማድረግ ያስደስታቸው ነበር።
ሚክያስ 6:8 ይሖዋ አምላክ ‘ደግነትን እንድንወድድ’ እንደሚፈልግ ይናገራል። በዚህ ረገድ ወንድም ሄንሽል ግሩም ምሳሌ ይሆነናል። ያለበት ኃላፊነት ከባድ ቢሆንም የሚቀረብ፣ ረጋ ያለና ደግ ነበር። ወንድም ሄንሽል “አንድን ሁኔታ እንዴት እንደምትወጣው ግራ ከገባህ ትክክለኛው ነገር ደግ የሆነው ነገር እንደሆነ አስታውስ” የሚል አባባል ነበረው። ይህን ወንድማችንን በማጣታችን ብናዝንም እስከ መጨረሻው በታማኝነት በመጽናቱ “የሕይወትን አክሊል” እንደተቀበለ እርግጠኞች ስለሆንን እንደሰታለን።—ራእይ 2:10
[የግርጌ ማስታወሻ]
a የ1977 የይሖዋ ምሥክሮች የዓመት መጽሐፍ (እንግሊዝኛ) ገጽ 171-7 ተመልከት።
[በገጽ 31 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ሚልተን ጂ ሄንሽል ከናታን ኤች ኖር ጋር
[በገጽ 31 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ከባለቤቱ ከሉሴል ጋር