በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

መከራ ሲደርስባችሁ ሙሉ በሙሉ በይሖዋ ታመኑ

መከራ ሲደርስባችሁ ሙሉ በሙሉ በይሖዋ ታመኑ

መከራ ሲደርስባችሁ ሙሉ በሙሉ በይሖዋ ታመኑ

“አምላካችን መጠጊያችንና ኃይላችን፣ ባገኘን በታላቅ መከራም ረዳታችን ነው።”—⁠መዝሙር 46:1

1, 2. (ሀ) በአምላክ እታመናለሁ ማለት ብቻ በቂ እንዳልሆነ የትኛው ምሳሌ ያሳያል? (ለ) በይሖዋ እንደምንታመን በሥራ ማሳየት ያለብን ለምንድን ነው?

 በአምላክ እንደምንታመን በተግባር ማሳየት የመናገሩን ያህል ቀላል አይደለም። ለምሳሌ ያህል በዩናይትድ ስቴትስ የብር ኖቶችና ሳንቲሞች ላይ “በአምላክ እንታመናለን” የሚለው አባባል መታተም ከጀመረ ረጅም ዘመን አስቆጥሯል። a በ1956 የዩናይትድ ስቴትስ ምክር ቤት ይህ አባባል የአገሪቱ ብሔራዊ መርሕ እንዲሆን በሕግ ደነገገ። የሚያስገርመው ግን በዩናይትድ ስቴትስ ብቻ ሳይሆን በዓለም ዙሪያ የሚኖሩ ብዙ ሰዎች ከአምላክ ይልቅ በገንዘብና በቁሳዊ ሀብት ይበልጥ ይታመናሉ።​—⁠ሉቃስ 12:​16-21

2 እውነተኛ ክርስቲያኖች ለአፋችን ያህል በይሖዋ እንታመናለን ከማለት የበለጠ ነገር ማድረግ አለብን። “ከሥራ የተለየ እምነት የሞተ” እንደሆነ ሁሉ በተግባር እስካልተደገፈ ድረስ በአምላክ እንታመናለን ብለን መናገራችንም ዋጋ የለውም። (ያዕቆብ 2:26) በፊተኛው ርዕስ ላይ ወደ ይሖዋ በጸሎት በመቅረብ፣ ከቃሉ መመሪያ በመፈለግና ድርጅቱ የሚሰጠንን አመራር በመከተል በይሖዋ መታመናችንን ማሳየት እንደምንችል ተምረናል። አሁን ደግሞ መከራ በሚያጋጥመን ጊዜ እነዚህን ሦስት እርምጃዎች እንዴት መውሰድ እንደምንችል እንመልከት።

ከሥራ ስንቀነስ ወይም ገቢያችን ዝቅተኛ ሲሆን

3. የይሖዋ አገልጋዮች በዚህ “የሚያስጨንቅ ዘመን” ውስጥ ምን ኢኮኖሚያዊ ችግሮች ያጋጥሟቸዋል? አምላክ እኛን ለመርዳት ፈቃደኛ እንደሆነስ እንዴት እናውቃለን?

3 በዚህ “የሚያስጨንቅ ዘመን” ውስጥ እንደ ሌሎች ሰዎች ሁሉ እኛም የኢኮኖሚ ችግር ያጋጥመናል። (2 ጢሞቴዎስ 3:​1) በመሆኑም በድንገት ከሥራ ልንቀነስ እንችላለን። ወይም ደግሞ ለትንሽ ክፍያ ብለን ለረጅም ሰዓት ለመሥራት እንገደድ ይሆናል። በእንደዚህ ዓይነት ሁኔታዎች ሥር ሆነን ‘ለራሳችን ለሆኑት’ የሚያስፈልጉትን ነገሮች ለማሟላት እንቸገር ይሆናል። (1 ጢሞቴዎስ 5:​8) የሁሉም የበላይ የሆነው አምላክ በዚህ ጊዜ እኛን ለመርዳት ፈቃደኛ ነው? ምንም ጥያቄ የለውም! እርግጥ ነው፣ ይሖዋ በዚህ ሥርዓት ውስጥ ሊያጋጥሙን ከሚችሉት የሕይወት ውጣ ውረዶች በሙሉ አይሰውረንም። ሆኖም በእርሱ ከታመንን የመዝሙር 46:​1 ቃላት ይፈጸሙልናል:- “አምላካችን መጠጊያችንና ኃይላችን፣ ባገኘን በታላቅ መከራም ረዳታችን ነው።” ይሁን እንጂ ገንዘብ ነክ ችግር ሲያጋጥመን ሙሉ በሙሉ በይሖዋ እንደምንታመን እንዴት ማሳየት እንችላለን?

4. ገንዘብ ነክ በሆኑ ጉዳዮች ረገድ ችግሮች ሲያጋጥሙን ምን ብለን መጸለይ እንችላለን? ይሖዋ ለእንዲህ ዓይነት ጸሎቶች ምላሽ የሚሰጠው እንዴት ነው?

4 በይሖዋ እንደምንታመን የምናሳይበት አንዱ መንገድ በጸሎት ወደ እርሱ በመቅረብ ነው። ይሁን እንጂ ምን ብለን መጸለይ እንችላለን? ገንዘብ ነክ በሆኑ ጉዳዮች ረገድ ችግር ሲያጋጥመን ከምን ጊዜውም የበለጠ ጥበብ ያስፈልገን ይሆናል። እንግዲያው ይሖዋ ጥበብ እንዲሰጠን መጸለያችን የተገባ ነው! የይሖዋ ቃል ይህን ዋስትና ይሰጠናል:- “ከእናንተ ግን ማንም ጥበብ ቢጐድለው፣ ሳይነቅፍ በልግስና ለሁሉ የሚሰጠውን እግዚአብሔርን ይለምን፣ ለእርሱም ይሰጠዋል።” (ያዕቆብ 1:5) አዎን፣ ጥሩ ውሳኔና ትክክለኛ ምርጫ ማድረግ እንድትችሉ እውቀትን፣ ማስተዋልንና የማመዛዘን ችሎታን በሚገባ ለመጠቀም የሚያስችላችሁን ጥበብ እንዲሰጣችሁ ጠይቁት። በሰማይ የሚኖረው አፍቃሪ አባታችን እንደዚህ ያሉትን ጸሎቶች እንደሚሰማ ማረጋገጫ ሰጥቶናል። በፍጹም ልባቸው በእርሱ ለሚታመኑ ሰዎች መንገዳቸውን ለማቅናት ምንጊዜም ዝግጁ ነው።​—⁠መዝሙር 65:​2፤ ምሳሌ 3:​5, 6

5, 6. (ሀ) ኢኮኖሚያዊ ችግሮችን ለመቋቋም የሚያስችል እርዳታ ለማግኘት የአምላክን ቃል መመልከታችን ተገቢ የሆነው ለምንድን ነው? (ለ) ከሥራ ስንቀነስ ጭንቀታችንን ለማቃለል ምን ማድረግ እንችላለን?

5 በይሖዋ እንደምንታመን የምናሳይበት ሌላው መንገድ መመሪያ ለማግኘት የአምላክን ቃል በማንበብ ነው። መጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሚገኘው ጥበብ የተሞላበት ማሳሰቢያው “እጅግ የታመነ ነው።” (መዝሙር 93:​5) ይህ በመንፈስ አነሳሽነት የተጻፈ መጽሐፍ ተጽፎ ካበቃ ከ1, 900 ዓመታት በላይ ያለፉ ቢሆንም ኢኮኖሚያዊ ችግሮችን በተሻለ መልኩ ለመቋቋም እንድንችል የሚረዳን አስተማማኝ ምክርና ጥልቅ ማስተዋል ይገኝበታል። በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ከሚገኙት ጥበብ አዘል ምክሮች ጥቂቶቹን ተመልከት።

6 ጠቢቡ ንጉሥ ሰሎሞን ከረጅም ጊዜ በፊት እንዲህ ብሎ ነበር:- “እጅግ ወይም ጥቂት ቢበላ የሠራተኛ እንቅልፍ ጣፋጭ ነው የባለጠጋ ጥጋብ ግን እንቅልፍን ይከለክለዋል።” (መክብብ 5:12) ያሉንን ንብረቶች መጠገን፣ በንጽሕና መያዝ እንዲሁም ከብልሽትና ከአደጋ መጠበቅ ጊዜና ገንዘብ ይጠይቃል። በመሆኑም ከሥራ ስንቀነስ የግድ የሚያስፈልጉንንና እምብዛም የማይጠቅሙንን ነገሮች ለይተን ለማወቅ አኗኗራችንን መለስ ብለን መገምገም ሊያስፈልገን ይችላል። አላስፈላጊ ጭንቀትን ለመቀነስ አንዳንድ ለውጦች ማድረጉ ጥበብ ይሆናል። ለምሳሌ ያህል አነስ ወዳለ ቤት በመዛወር ወይም የማያስፈልጉንን ዕቃዎች በማስወገድ ኑሯችንን ማቅለል እንችል ይሆን?​—⁠ማቴዎስ 6:​22

7, 8. (ሀ) ኢየሱስ ፍጹማን ያልሆኑ ሰዎች ለቁሳዊ ነገሮች ከልክ በላይ የመጨነቅ ዝንባሌ ያላቸው መሆኑን እንደሚያውቅ ያሳየው እንዴት ነው? (የግርጌ ማስታወሻውንም ተመልከት።) (ለ) ኢየሱስ አላስፈላጊ ጭንቀትን ማስወገድን በተመለከተ ምን ጥበብ ያዘለ ምክር ሰጥቷል?

7 ኢየሱስ በተራራ ስብከቱ ላይ “ስለ ነፍሳችሁ በምትበሉትና በምትጠጡት፣ ወይም ስለ ሰውነታችሁ በምትለብሱት አትጨነቁ” የሚል ምክር ሰጥቷል። b (ማቴዎስ 6:25) ኢየሱስ ፍጹማን ያልሆኑ ሰዎች መሠረታዊ ፍላጎቶቻቸውን ስለማሟላት መጨነቃቸው እንደማይቀር ያውቅ ነበር። ሆኖም ስለ እነዚህ ነገሮች ‘መጨነቃችንን’ ማቆም የምንችለው እንዴት ነው? ኢየሱስ “አስቀድማችሁ የእግዚአብሔርን መንግሥት . . . ፈልጉ” ብሏል። ምንም ዓይነት ችግር ቢያጋጥመን በሕይወታችን ውስጥ ለይሖዋ አምልኮ ቅድሚያ መስጠት ይኖርብናል። እንዲህ ካደረግን በሰማይ የሚኖረው አባታችን ለዕለታዊ ሕይወታችን የሚያስፈልጉንን ነገሮች ሁሉ ‘ይጨምርልናል።’ በዚህም ሆነ በዚያ የሚያስፈልጉንን ነገሮች ያሟላልናል።​—⁠ማቴዎስ 6:33

8 ኢየሱስ በማከል “ነገ ለራሱ ይጨነቃልና ለነገ አትጨነቁ” የሚል ምክር ሰጥቷል። (ማቴዎስ 6:​34 ) ነገ ምን ይመጣ ይሆን በሚል ከልክ በላይ መጨነቅ ተገቢ አይደለም። አንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ምሑር ይህን ሐሳብ ሰጥተዋል:- “ይደርሳል ብለን የጠበቅነው ነገር አብዛኛውን ጊዜ የፈራነውን ያህል አስከፊ አይሆንም።” ቅድሚያ ሊሰጣቸው ለሚገቡ ነገሮች ትኩረት እንድንሰጥ የሚያበረታታውን የመጽሐፍ ቅዱስ ምክር በትሕትና መከተላችንና ለነገ አለመጨነቃችን የማያስፈልግ ውጥረት ውስጥ እንዳንገባ ሊረዳን ይችላል።​—⁠1 ጴጥሮስ 5:​6, 7

9. የገንዘብ ችግር ሲያጋጥመን “ታማኝና ልባም ባሪያ” ከሚያዘጋጃቸው ጽሑፎች ምን እርዳታ ማግኘት እንችላለን?

9 የገንዘብ ችግር ሲያጋጥመን እርዳታ ለማግኘት “ታማኝና ልባም ባሪያ” የሚያዘጋጃቸውን ጽሑፎች በመመርመር በይሖዋ እንደምንታመን ማሳየትም እንችላለን። (ማቴዎስ 24:​45) ኢኮኖሚያዊ ችግሮችን ለመቋቋም የሚረዱ ምክሮችንና ሐሳቦችን የያዙ ርዕሶች በተለያዩ ጊዜያት በንቁ! መጽሔት ላይ ወጥተዋል። በነሐሴ 8, 1991 (እንግሊዝኛ) እትም ላይ የወጣው “ከሥራ መባረር የሚያስከትለውን ችግር መቋቋም የሚቻልባቸው መንገዶች” የሚለው ርዕስ ብዙዎች ሥራ ባጡበት ወቅት ለገንዘብ ችግርም ሆነ ለስሜት ቀውስ እንዳይጋለጡ የረዳቸውን ስምንት ተግባራዊ መመሪያዎች አስፍሮ ነበር። c እርግጥ እንዲህ ዓይነት መመሪያዎች ለገንዘብ ተገቢውን አመለካከት በመያዝ መታገዝ አለባቸው። ይህ ጉዳይ “ከገንዘብ የበለጠ አስፈላጊ የሆነ ነገር” በሚለው በዚያው እትም ላይ በወጣ ርዕስ ሥር ተብራርቷል።​—⁠መክብብ 7:​12

የጤና እክሎች ለጭንቀት ሲዳርጉን

10. በጠና ስንታመም በይሖዋ መታመናችን ተገቢ መሆኑን የንጉሥ ዳዊት ምሳሌ የሚያሳየው እንዴት ነው?

10 ከባድ የጤና እክል ሲያጋጥመን በይሖዋ መታመኑ ያዋጣልን? በሚገባ! ይሖዋ በሕመም ላይ ለሚገኙ ሕዝቦቹ ያዝናል። ከዚህም በላይ እርዳታ ለመስጠት ፈቃደኛ ነው። ንጉሥ ዳዊትን እንደ ምሳሌ እንውሰድ። አምላክ ታማኝ የሆነ አገልጋዩ ቢታመም እንዴት እንደሚንከባከበው በጻፈ ጊዜ እርሱ ራሱ በጠና ታምሞ ሊሆን ይችላል። “እግዚአብሔር በደዌው አልጋ ሳለ ይረዳዋል፤ መኝታውን ሁሉ በበሽታው ጊዜ ያነጥፍለታል” ብሏል። (መዝሙር 41:​1, 3, 7, 8) ዳዊት በአምላክ ላይ ያለው እምነት ፈጽሞ አልተናጋም፤ በኋላም ከበሽታው ድኗል። ይሁን እንጂ የጤና እክሎች ለጭንቀት ሲዳርጉን በአምላክ እንደምንታመን እንዴት ማሳየት እንችላለን?

11. የጤና እክል ሲያጋጥመን በሰማይ የሚኖረው አባታችንን ምን ልንጠይቀው እንችላለን?

11 በበሽታ በምንሰቃይበት ጊዜ በይሖዋ እንደምንታመን የምናሳይበት አንዱ መንገድ ሥቃዩን ችለን ለማሳለፍ እንዲረዳን በጸሎት በመማጸን ነው። ሁኔታችን በሚፈቅደው መጠን መፍትሔ ለመፈለግ የሚያስችል ‘መልካም ጥበብ’ እንዲሰጠን ልንጠይቀው እንችላለን። (ምሳሌ 3:​21) ሕመሙን የምንቋቋምበት ትዕግሥትና ጽናት እንዲሰጠን እንጠይቀው። ከሁሉ በላይ ደግሞ ምንም ዓይነት ሁኔታ ቢያጋጥመን ለይሖዋ ታማኝ ሆነን ለመጽናትና ሚዛናችንን ለመጠበቅ የሚያስችል ኃይል እንዲሰጠን ልንለምነው እንችላለን። (ፊልጵስዩስ 4:​13) ለአምላክ ታማኝነታችንን መጠበቃችን የአሁኑን ሕይወታችንን ከማትረፍ ይበልጥ አስፈላጊ ነው። አቋማችንን ጠብቀን ከኖርን አምላካችን ፍጹም ሕይወትና ጤንነት በመስጠት ለዘላለም ያኖረናል።​—⁠ዕብራውያን 11:​6

12. የምናደርገውን የሕክምና ዓይነት ስንመርጥ ጥበብ የተሞላበት ውሳኔ እንድናደርግ የሚረዱን የመጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ ሥርዓቶች የትኞቹ ናቸው?

12 በይሖዋ መታመናችን ተግባራዊ መመሪያ ለማግኘት ቃሉን መጽሐፍ ቅዱስን እንድንመለከትም ይገፋፋናል። በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሚገኙት መሠረታዊ ሥርዓቶች ከሕክምና ጋር በተያያዘ ጥበብ ያለበት ውሳኔ ማድረግ እንድንችል ይረዱናል። ለምሳሌ ያህል መጽሐፍ ቅዱስ ‘መናፍስታዊ ሥራን’ እንደሚያወግዝ ስለምናውቅ ከመናፍስታዊ እምነት ጋር ንክኪ ካለው ከማንኛውም የጤና ምርመራ ወይም የፈውስ ሂደት እንርቃለን። (ገላትያ 5:​19-21፤ ዘዳግም 18:​10-12) የመጽሐፍ ቅዱስ ጥበብ እምነት የሚጣልበት መሆኑን ለማየት “የዋህ ቃልን ሁሉ ያምናል፤ ብልህ ግን አካሄዱን ይመለከታል” የሚለው ጥቅስ ተጨማሪ ምሳሌ ይሆነናል። (ምሳሌ 14:15) ስለዚህ አንድ ዓይነት ሕክምና ለመውሰድ ስናስብ ‘ቃልን ሁሉ ከማመን’ ይልቅ አስተማማኝ መረጃ ለማግኘት መሞከራችን ጥበብ ነው። እንዲህ ዓይነት ‘ትክክለኛ አስተሳሰብ’ መያዛችን ያሉንን አማራጮች በጥንቃቄ እንድናመዛዝንና ማስተዋል የተሞላበት ውሳኔ እንድናደርግ ይረዳናል።​—⁠ቲቶ 2:​12 NW

13, 14. (ሀ) የጤና ጉዳዮችን በተመለከተ መጠበቂያ ግንብ እና ንቁ! መጽሔቶች ላይ ምን ትምህርት ሰጪ ርዕሶች ወጥተዋል? (በገጽ 17 ላይ የሚገኘውን ሣጥን ተመልከት።) (ለ) የየካቲት 2001 ንቁ! ሥር የሰደደ የጤና እክልን ለመቋቋም የሚረዳ ምን ምክር ይዟል?

13 በይሖዋ እንደምንታመን ማሳየት የምንችልበት ሌላው መንገድ ታማኙ ባሪያ ያዘጋጃቸውን ጽሑፎች በመመርመር ነው። ልዩ ልዩ የጤና ችግሮችንና በሽታዎችን በተመለከተ መጠበቂያ ግንብ እና ንቁ! መጽሔቶች ትምህርት ሰጪ የሆኑ ርዕሶችን በተለያየ ጊዜ አውጥተዋል። d አንዳንድ ጊዜ እነዚህ መጽሔቶች ልዩ ልዩ የጤና ችግሮችን፣ በሽታዎችንና የአካል ጉዳቶችን እንዴት እንደተቋቋሙ የሚገልጹ ግለሰቦች የጻፏቸውን ርዕሶች ያወጣሉ። ከዚህም በላይ ከባድ የጤና እክሎችን ተቋቁሞ ለመኖር የሚረዱ ቅዱስ ጽሑፋዊ ሐሳቦችንና ተግባራዊ ምክሮችን የያዙ ርዕሶችም አሉ።

14 ለምሳሌ ያህል የየካቲት 2001 ንቁ! “ለታመሙ የሚሆን መጽናኛ” የሚል የሽፋን ርዕስ ይዞ ወጥቶ ነበር። በመጽሔቱ ላይ የወጡት ርዕሶች ጠቃሚ የሆኑ የመጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ ሥርዓቶችንና የአቅም ገደብ የሚያስከትል በሽታ ካለባቸው ግለሰቦች ጋር በተደረገ ቃለ ምልልስ የተገኙ ሐሳቦችን ይዘዋል። “ሕመምህን ተቋቁመህ መኖር​—እንዴት?” የሚለው ርዕስ እንዲህ የሚል ምክር ይሰጣል:- ስለ ሕመምህ የቻልከውን ያህል ብዙ እውቀት ሰብስብ። (ምሳሌ 24:​5) ሌሎችን እንደ መርዳት ያሉ ልትደርስባቸው የምትችላቸውን ግቦች አውጣ። ሆኖም ሌሎች ሊደርሱበት የሚችሉት ግብ ላይ አንተ መድረስ ሊያቅትህ እንደሚችል አስታውስ። (ሥራ 20:​35፤ ገላትያ 6:​4) ራስህን ከሰዎች አታግልል። (ምሳሌ 18:​1) ሌሎች አንተን መጥተው በመጠየቃቸው እንዲደሰቱ አድርግ። (ምሳሌ 17:​22) ከሁሉ በላይ ደግሞ ከይሖዋና ከጉባኤው ጋር የጠበቀ ግንኙነት ይኑርህ። (ናሆም 1:​7፤ ሮሜ 1:​11, 12) ይሖዋ በድርጅቱ በኩል ለሚሰጠን እምነት የሚጣልበት መመሪያ አመስጋኞች ልንሆን አይገባም?

ሥጋዊ ድካም ሲፈታተነን

15. ሐዋርያው ጳውሎስ ከኃጢአተኛ ሥጋው ጋር የነበረውን ትግል በአሸናፊነት መወጣት የቻለው እንዴት ነው? በዚህ ረገድ እኛስ ምን ዓይነት እርዳታ አለልን?

15 ሐዋርያው ጳውሎስ “በሥጋዬ በጎ ነገር እንዳይኖር አውቃለሁና” ሲል ጽፏል። (ሮሜ 7:18) ጳውሎስ ከኃጢአተኛ ሥጋችን ምኞቶችና ድክመቶች ጋር መታገል ምን ያህል ከባድ እንደሆነ በሕይወቱ ተመልክቷል። ይሁን እንጂ ጳውሎስ ትግሉን በአሸናፊነት መወጣት እንደሚችልም ትምክህት ነበረው። (1 ቆሮንቶስ 9:​26, 27) እንዴት? ሙሉ በሙሉ በይሖዋ በመታመን ነው። ከዚህም የተነሳ ጳውሎስ እንዲህ ሊል ችሏል:- “እኔ ምንኛ ጐስቋላ ሰው ነኝ! ለዚህ ሞት ከተሰጠ ሰውነት ማን ያድነኛል? በኢየሱስ ክርስቶስ በጌታችን ለእግዚአብሔር ምስጋና ይሁን።” (ሮሜ 7:24, 25) የእኛስ ሁኔታ እንዴት ነው? እኛም ብንሆን ከሥጋዊ ድክመቶቻችን ጋር ትግል አለብን። እነዚህን ድክመቶች ለማሸነፍ በምናደርገው ትግል መቼም ቢሆን ሊሳካልን እንደማይችል በማሰብ ትምክህታችንን በቀላሉ ልናጣ እንችላለን። ሆኖም በራሳችን ጥንካሬ ሳይሆን ልክ እንደ ጳውሎስ በይሖዋ ሙሉ በሙሉ ከተማመንን እርሱ ይረዳናል።

16. ሥጋዊ ድካም ሲታገለን ምን ዓይነት እርዳታ ለማግኘት መጸለይ ይኖርብናል? ድክመቱ ቢያገረሽብን ምን ማድረግ ይኖርብናል?

16 ሥጋዊ ድክመት ሲታገለን ይሖዋን በጸሎት በመማጸን በእርሱ እንደምንተማመን ማሳየት እንችላለን። ይሖዋ መንፈስ ቅዱሱን እንዲሰጠን መጠየቅ አልፎ ተርፎም መለመን ይኖርብናል። (ሉቃስ 11:​9-13) የአምላክ መንፈስ ፍሬ የሆነውን ራስን መግዛት እንዲሰጠን ለይተን መጠየቅ እንችላለን። (ገላትያ 5:​22, 23) ድክመታችን ቢያገረሽብን ምን ማድረግ ይኖርብናል? ፈጽሞ ተስፋ መቁረጥ አይኖርብንም። መሐሪ የሆነው አምላካችን ይቅር እንዲለንና እንዲረዳን ያለ መታከት በትሕትና እንጸልይ። ይሖዋ በከባድ የሕሊና ወቀሳ “የተሰበ[ረ]ውንና የተዋረደውን” ልብ አይንቅም። (መዝሙር 51:​17) ጸጸት ተሰምቶን በቅን ልቦና ከተማጸንነው ይሖዋ ፈተናዎችን እንድንቋቋም ይረዳናል።​—⁠ፊልጵስዩስ 4:​6, 7

17. (ሀ) እየታገልን ያለነውን ድካም በተመለከተ ይሖዋ ምን እንደሚሰማው ማሰባችን የሚረዳን እንዴት ነው? (ለ) ግልፍተኝነትን እንዲሁም አንደበታችንን ተገቢ ባልሆነ መንገድ ለመጠቀምና ንጹሕ ባልሆኑ መዝናኛዎች ለመሳተፍ ያለንን ዝንባሌ ለመቋቋም እየታገልን ከሆነ የትኞቹን ጥቅሶች ማስታወሳችን ይጠቅመናል?

17 በተጨማሪም እርዳታ ለማግኘት በቃሉ ላይ ምርምር በማድረግ በይሖዋ እንደምንታመን ማሳየት እንችላለን። የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅሶች ማውጫ ወይም በመጠበቂያ ግንብ እና ንቁ! መጽሔቶች በዓመቱ የመጨረሻ እትም ላይ የሚወጣውን የርዕስ ማውጫ በመጠቀም ‘እየታገልኩት ስላለው የሥጋ ድካም ይሖዋ ምን ይሰማዋል?’ ለሚለው ጥያቄ መልስ ለማግኘት መጣር እንችላለን። ይሖዋ ስለ ጉዳዩ ባለው አመለካከት ላይ ማሰላሰላችን እርሱን ለማስደሰት ያለንን ፍላጎት ያጠናክርልናል። በዚህ መንገድ እርሱ የሚጠላውን በመጥላት የእርሱ ዓይነት ስሜት ማዳበር እንችላለን። (መዝሙር 97:​10) አንዳንዶች ካለባቸው ድክመት ጋር በቀጥታ የሚዛመዱ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅሶችን በቃላቸው ማጥናቱ ጠቅሟቸዋል። የግልፍተኝነትን ባሕርይ ለማሸነፍ ትግል እያደረግን ነው? ከሆነ እንደ ምሳሌ 14:​17 እና ኤፌሶን 4:​31 ያሉትን ጥቅሶች በቃላችን መያዝ እንችላለን። አንደበታችንን መግታት ያስቸግረናል? እንደ ምሳሌ 12:​18 እና ኤፌሶን 4:​29 የመሳሰሉትን ጥቅሶች በአእምሯችን መያዝ እንችላለን። ንጹሕ ባልሆነ መዝናኛ የመካፈል ዝንባሌ አለን? ኤፌሶን 5:​3ንና ቆላስይስ 3:​5ን የመሳሰሉ ጥቅሶችን ለማስታወስ ጥረት ማድረግ እንችላለን።

18. ድክመታችንን ማሸነፍ እንድንችል ሽማግሌዎች እንዲረዱን ለመጠየቅ ማፈር የሌለብን ለምንድን ነው?

18 በጉባኤ ውስጥ ካሉ በመንፈስ የተሾሙ ሽማግሌዎች እርዳታ መጠየቅ በይሖዋ እንደምንታመን የምናሳይበት ሌላው መንገድ ነው። (ሥራ 20:​28) ደግሞም እነዚህ ‘ስጦታ የሆኑ ወንዶች’ ይሖዋ በጎቹን ለመጠበቅና ለመንከባከብ በክርስቶስ በኩል ያደረገልን ዝግጅት ክፍል ናቸው። (ኤፌሶን 4:​7, 8, 11-14) እርግጥ ነው፣ ድክመታችንን ለማሸነፍ የሚያስችለን እርዳታ እንዲሰጡን መጠየቅ ሊያሳፍረን ይችላል። ሽማግሌዎቹ ለእኛ ያላቸው ግምት እንዳይቀንስ በመፍራት ከመናገር ወደኋላ እንል ይሆናል። ሆኖም እነዚህ በመንፈሳዊ የጎለመሱ ወንዶች ደፍረን እርዳታ በመጠየቃችን እንደሚያከብሩን ምንም ጥርጥር የለውም። ከዚህም በላይ ሽማግሌዎች መንጋውን በሚንከባከቡበት ጊዜ የይሖዋ ዓይነት ባሕርያት ለማንጸባረቅ ይጥራሉ። ከአምላክ ቃል ላይ የሚሰጡን የሚያጽናና እንዲሁም ተግባራዊ ጠቀሜታ ያለው ምክርና መመሪያ ድክመታችንን ማሸነፍ እንድንችል ቁርጥ ውሳኔያችንን ለማጠናከር የሚያስፈልገን ነገር ሊሆን ይችላል።​—⁠ያዕቆብ 5:​14-16

19. (ሀ) ሰይጣን በዚህ ሥርዓት ውስጥ የሚገኙትን ሕይወትን ከንቱ የሚያደርጉ ነገሮች የሚጠቀምባቸው እንዴት ነው? (ለ) በይሖዋ መታመን ምን ነገሮችን ይጨምራል? ቁርጥ ውሳኔያችንስ ምን መሆን አለበት?

19 ሰይጣን የቀረው ጊዜ አጭር መሆኑን እንደሚያውቅ ፈጽሞ አንዘንጋ። (ራእይ 12:​12) በዓለም ላይ ባሉ ሕይወትን ከንቱ በሚያደርጉ ነገሮች ተጠቅሞ ተስፋ እንድንቆርጥና እጃችንን እንድንሰጥ ሊያደርገን ይፈልጋል። በሮሜ 8:​35-39 በሚገኙት ቃላት ላይ ሙሉ እምነት ይኑረን:- “ከክርስቶስ ፍቅር ማን ይለየናል? መከራ፣ ወይስ ጭንቀት፣ ወይስ ስደት፣ ወይስ ራብ፣ ወይስ ራቁትነት፣ ወይስ ፍርሃት፣ ወይስ ሰይፍ ነውን? . . . በዚህ ሁሉ ግን በወደደን በእርሱ ከአሸናፊዎች እንበልጣለን። ሞት ቢሆን፣ ሕይወትም ቢሆን፣ መላእክትም ቢሆኑ፣ ግዛትም ቢሆን፣ ያለውም ቢሆን፣ የሚመጣውም ቢሆን፣ ኃይላትም ቢሆኑ፣ ከፍታም ቢሆን፣ ዝቅታም ቢሆን፣ ልዩ ፍጥረትም ቢሆን በክርስቶስ ኢየሱስ በጌታችን ካለ ከእግዚአብሔር ፍቅር ሊለየን እንዳይችል ተረድቼአለሁ።” በይሖዋ መታመን ማለት እንዲህ ነው! ይሁን እንጂ እንዲህ ያለው መታመን እንዲያው ስሜታዊ ነገር አይደለም። ከዚህ ይልቅ በዕለት ተዕለት ሕይወታችን በምናደርጋቸው የታሰበባቸው ውሳኔዎች የሚገለጽ እምነት ነው። እንግዲያው መከራ በሚደርስብን ጊዜ ሙሉ በሙሉ በይሖዋ ለመታመን ቁርጥ ውሳኔ እናድርግ።

[የግርጌ ማስታወሻ]

a የገንዘብ ሚኒስትር የነበሩት ሳመን ፒ ቼዝ ኅዳር 20, 1861 ለዩናይትድ ስቴትስ የገንዘብ ማተሚያ ድርጅት እንዲህ የሚል ደብዳቤ ጽፈው ነበር:- “ማንኛውም አገር ቢሆን ያለ አምላክ እርዳታ ጠንካራ መሆን ወይም ያለ እርሱ ጥበቃ ደህንነት ማግኘት አይችልም። ሕዝባችን በአምላክ እንደሚታመን በአገራችን ሳንቲሞች ላይ መገለጽ አለበት።” በዚህም ምክንያት “በአምላክ እንታመናለን” የሚለው መርሕ በአሜሪካ የመገበያያ ሳንቲሞች ላይ በ1864 ለመጀመሪያ ጊዜ ወጣ።

b እዚህ ላይ የተጠቀሰው ጭንቀት “ደስታ የሚያሳጣ ከፍተኛ ስጋት” እንደሆነ ተገልጿል። የአማርኛውን ጨምሮ አንዳንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉሞች “አትጨነቁ” የሚሉ ሲሆን ይህም መጨነቅ መጀመር የለብንም የሚል ሐሳብ ያስተላልፋል። ይሁን እንጂ አንድ የማመሳከሪያ ጽሑፍ እንዲህ ይላል:- “የግሪክኛው ግስ አገባብ በሂደት ላይ ያለን አንድን ድርጊት እንዲቆም ትእዛዝ የመስጠት መልእክት ያስተላልፋል።”

c ስምንቱ ነጥቦች የሚከተሉት ናቸው:- (1) አትደናገጥ፣ (2) አዎንታዊ አመለካከት ይኑርህ፣ (3) ማንኛውንም ሥራ ለመቀበል ዝግጁ ሁን፣ (4) እንደ ቤትህ እንጂ እንደ ጎረቤትህ ለመኖር አትሞክር፣ (5) አላስፈላጊ ዕዳ ውስጥ አትግባ፣ (6) የቤተሰብህ አንድነት እንዳይናጋ ጥረት አድርግ፣ (7) ለራስህ ያለህን ግምት ጠብቅ እና (8) ባጀት አውጣ።

d በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተመሠረቱት እነዚህ መጽሔቶች የሕክምና ምርጫ የግል ጉዳይ እንደሆነ በመገንዘብ የትኛውንም ሕክምና ደግፈው አይናገሩም። ከዚህ ይልቅ መጽሔቶቹ አንድ ዓይነት በሽታን ወይም የጤና እክልን የሚያብራሩት አንባቢዎች አሁን ካለው ግንዛቤ አንጻር ጉዳዩን እንዲመለከቱት ለመርዳት ነው።

ታስታውሳለህን?

• ኢኮኖሚያዊ ችግሮች ሲያጋጥሙን በይሖዋ እንደምንታመን ማሳየት የምንችለው በየትኞቹ መንገዶች ነው?

• የጤና እክል ሲያስጨንቀን በአምላክ እንደምንታመን ማሳየት የምንችለው እንዴት ነው?

• የሥጋ ድክመት ሲታገለን በይሖዋ እንደምንመካ እንዴት ማሳየት እንችላለን?

[የአንቀጾቹ ጥያቄዎች]

[በገጽ 17 ላይ የሚገኝ ሣጥን]

እነዚህን ርዕሶች ታስታውሳቸዋለህ?

የጤና እክል ጭንቀት ሲያስከትልብን ተመሳሳይ የጤና መታወክ፣ በሽታ ወይም የአካል ጉዳተኝነት አጋጥሟቸው በተሳካ ሁኔታ ስለተቋቋሙ ሰዎች ማንበብ ያበረታታል። ከዚህ ቀጥሎ መጠበቂያ ግንብ እና ንቁ! መጽሔቶች ላይ የወጡ አንዳንድ ርዕሶች ቀርበዋል።

“ከድክመቶቼ ጋር የማደርገው ትግል” አሉታዊ አመለካከትንና የመንፈስ ጭንቀትን ስለተቋቋመ ሰው የሚናገር ታሪክ።​—⁠መጠበቂያ ግንብ 9-111

“እንጣላለን እንጂ አንጠፋም።”​—⁠መጠበቂያ ግንብ ኅዳር 1, 1995

“ሕይወታችሁ ነገ ምን እንደሚሆን አታውቁም” ባይፖላር ዲስኦርደር የተባለውን የአእምሮ ሕመም ስለተቋቋመ ሰው የሚናገር ታሪክ።​—⁠መጠበቂያ ግንብ ታኅሣሥ 1, 2000

“ከባድ እክል ቢኖርብኝም አስደሳች ተስፋ አለኝ።”​—⁠ንቁ! መጋቢት 2000

“ሎይዳ የሐሳብ ግንኙነት ለመፍጠር ያደረገችው ትግል” ሴሬብራል ፓልሲ በተባለው የአእምሮ ጉዳት የተነሳ የሚፈጠር ችግር ያጋጠማት ወጣት ታሪክ።​—⁠ንቁ! ሐምሌ 2000

“ግቦች በማውጣት መሰናክሎችን መወጣት።”​—⁠ንቁ! የካቲት 2001

“መስማትና ማየት ባልችልም የተረጋጋ ሕይወት አግኝቻለሁ።”​—⁠ንቁ! ግንቦት 2001

“ሌሎችን ማገልገል የራሴን ሥቃይ አስታግሶልኛል።”​—⁠መጠበቂያ ግንብ ሐምሌ 1, 2003

[በገጽ 15 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ከሥራ ስንቀነስ አኗኗራችንን መለስ ብለን መመርመራችን ጥበብ ይሆናል

[በገጽ 16 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

የሎይዳ ታሪክ በይሖዋ መታመን ለመጽናት እንደሚረዳ ያሳያል (በገጽ 17 ላይ የሚገኘውን ሣጥን ተመልከት)

[በገጽ 18 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ድክመታችንን ለማሸነፍ የሚያስችል እርዳታ ከመጠየቅ ወደኋላ ማለት አይገባንም