በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

አረጋውያን ወንድሞችንና እህቶችን ታከብራቸዋለህ?

አረጋውያን ወንድሞችንና እህቶችን ታከብራቸዋለህ?

አረጋውያን ወንድሞችንና እህቶችን ታከብራቸዋለህ?

ከአምላክ ጋር ቃል ኪዳን ገብተው የነበሩት የጥንት እስራኤላውያን “በሽበታሙ ፊት ተነሣ፣ ሽማግሌውንም አክብር፣ አምላክህንም ፍራ” የሚል ትእዛዝ ተሰጥቷቸው ነበር። (ዘሌዋውያን 19:32) ከዚህ ለማየት እንደሚቻለው አረጋውያንን ማክበር ለአምላክ ከመገዛት ጋር የተቆራኘ መለኮታዊ ግዴታ ነበር። ዛሬ ያሉ ክርስቲያኖች በሙሴ ሕግ ሥር ባይሆኑም ለእስራኤላውያን የተሰጠው ይህ ትእዛዝ ይሖዋ አረጋውያን አገልጋዮቹን እንደሚወዳቸውና እንደሚያስብላቸው ያስገነዝበናል። (ምሳሌ 16:31፤ ዕብራውያን 7:18) እኛስ የይሖዋ ዓይነት አመለካከት አለን? አረጋውያን ወንድሞቻችንንና እህቶቻችንን እናከብራቸዋለን?

ለአረጋዊ ወዳጁ አክብሮት የነበረው ሰው

የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል በሆነው በሁለተኛ ነገሥት መጽሐፍ ላይ ለአረጋውያን አክብሮት የማሳየትን አስፈላጊነት የሚያጎላ አንድ ታሪክ ይገኛል። ታሪኩ ኤልሳዕ የተባለው ወጣት ነቢይ እንዴት በነቢዩ ኤልያስ እግር እንደተተካ ይገልጻል። ኤልያስ በአሥሩ ነገድ የእስራኤል መንግሥት ነቢይ ሆኖ ባገለገለበት የመጨረሻ ዕለት ምን እንደተከናወነ እንመልከት።

በዚያን ዕለት አረጋዊው ነቢይ ከጌልገላ ወደ ቤቴል፣ ከቤቴል ወደ ኢያሪኮ እንዲሁም ከኢያሪኮ ወደ ዮርዳኖስ ወንዝ እንዲሄድ ይሖዋ መመሪያ ሰጥቶት ነበር። (2 ነገሥት 2:1, 2, 4, 6) ወደ 50 ኪሎ ሜትር ያህል ርቀት በሚሸፍነው በዚህ ጉዞ ወቅት ኤልሳዕ ከእርሱ ተለይቶ እንዲቀር ኤልያስ ሦስት ጊዜ ለመነው። ሆኖም ከበርካታ ዘመናት በፊት ወጣቷ ሩት ኑኃሚንን የሙጥኝ ብላ አልለይም እንዳለች ሁሉ ኤልሳዕም ከአረጋዊው ነቢይ ለመለየት አልፈለገም። (ሩት 1:16, 17) ኤልሳዕ በሦስቱም ጊዜያት “ሕያው እግዚአብሔርን! በሕያው ነፍስህም እምላለሁ፣ አልለይህም” በማለት መልሶለታል። (2 ነገሥት 2:2, 4, 6) በዚህ ወቅት ኤልሳዕ ኤልያስን ለስድስት ዓመታት ያህል አገልግሎት ነበር። ያም ሆኖ እስከ መጨረሻው ድረስ ኤልያስን ለማገልገል ቆርጦ ነበር። እንዲያውም ዘገባው ‘ሲሄዱም፣ እያዘገሙም ሲጫወቱ፣ እነሆ ኤልያስ ወደ ሰማይ ወጣ’ ይላል። (ቁጥር 11) ኤልያስ በእስራኤል ያከናወነውን አገልግሎት እስካጠናቀቀበት እስከ መጨረሻዋ ሰዓት ድረስ እየተጫወቱ ነበር። ወጣቱ ነቢይ ከአረጋዊውና ልምድ ካካበተው ነቢይ በተቻለ መጠን ብዙ መመሪያና ማበረታቻ ማግኘት ፈልጎ ሊሆን ይችላል። ኤልሳዕ ለአረጋዊ ወዳጁ አክብሮት እንደነበረው ምንም አያጠራጥርም።

‘እንደ አባቶችና እንደ እናቶች’

ኤልሳዕ አረጋዊውን ነቢይ እንዲወድደው አልፎ ተርፎም እንደ መንፈሳዊ አባቱ አድርጎ እንዲመለከተው ያነሳሳው ምን እንደሆነ መረዳት አያዳግትም። (2 ነገሥት 2:12) ኤልያስ በእስራኤል ያከናወነው አገልግሎት ሊያበቃ በተቃረበበት ወቅት ኤልሳዕን “ከአንተ ሳልወሰድ አደርግልህ ዘንድ የምትሻውን ለምን” ብሎት ነበር። (ቁጥር 9) ኤልያስ እርሱን ተክቶ የሚያገለግለው ነቢይ መንፈሳዊ ደህንነትና የአምላክ ሥራ ቀጣይነት እስከ መጨረሻው ድረስ ያሳስበው እንደነበር አሳይቷል።

ዛሬም በተመሳሳይ አረጋውያን ወንድሞችና እህቶች እውቀታቸውንና ልምዳቸውን ለወጣት ክርስቲያኖች በፈቃደኝነት በማካፈል እንደ አባትና እንደ እናት እንደሚያስቡላቸው የሚያሳዩ መሆኑ ያስደስታል። ለምሳሌ ያህል፣ በይሖዋ ምሥክሮች ቅርንጫፍ ቢሮዎች ውስጥ ለረጅም ዓመታት ያገለገሉ ፈቃደኛ ሠራተኞች አዳዲስ የቤቴል ቤተሰብ አባላት አገልግሎታቸውን ለማከናወን እንዲችሉ አስፈላጊውን ሥልጠና በመስጠት በፈቃደኝነት ይረዷቸዋል። በተመሳሳይም ለብዙ ዓመታት ጉባኤዎችን ሲጎበኙ የኖሩ ተጓዥ የበላይ ተመልካቾችና ሚስቶቻቸው በዚህ ሥራ ለመሠማራት በመሠልጠን ላይ ለሚገኙት ልምዳቸውን ማካፈል ያስደስታቸዋል። ከዚህም በላይ በዓለም ዙሪያ በሚገኙት የይሖዋ ምሥክሮች ጉባኤዎች ውስጥ ለበርካታ አሥርተ ዓመታት ይሖዋን በታማኝነት ሲያገለግሉ የኖሩ አረጋውያን ወንድሞችና እህቶች እውቀታቸውንና ያገኙትን ልምድ ለአዳዲስ የጉባኤው አባላት ያካፍላሉ።​—⁠ምሳሌ 2:7፤ ፊልጵስዩስ 3:17፤ ቲቶ 2:3-5

እነዚህ አረጋውያን ክርስቲያኖች ለሌሎች የሚያሳዩት አሳቢነት ከልብ እንድንወዳቸውና እንድናከብራቸው ያነሳሳናል። እንግዲያው አረጋዊ ወንድሞችንና እህቶችን በጥልቅ በማክበር የኤልሳዕን ምሳሌ እንኮርጅ። ሐዋርያው ጳውሎስ በሰጠን ምክር መሠረት “ሽማግሌ የሆነውን . . . እንደ አባት” እንዲሁም “የሸመገሉትን ሴቶች እንደ እናቶች” እንመልከታቸው። (1 ጢሞቴዎስ 5:1, 2) እንዲህ በማድረግ ለዓለም አቀፉ የክርስቲያን ጉባኤ ዕድገት አስተዋጽኦ እናበረክታለን።

[በገጽ 30 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ኤልሳዕ እስከ መጨረሻው ድረስ ኤልያስን ለማገልገል ቆርጦ ነበር

[በገጽ 31 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ወጣቶች ከአረጋውያን ክርስቲያኖች ብዙ ይጠቀማሉ