በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ይሖዋን መታመኛችሁ አድርጉት

ይሖዋን መታመኛችሁ አድርጉት

ይሖዋን መታመኛችሁ አድርጉት

“አቤቱ፣ አንተ ተስፋዬ ነህና፣ እግዚአብሔር ሆይ፣ ከታናሽነቴ ጀምረህ መታመኛዬ ነህና።”—⁠መዝሙር 71:5

1. ወጣቱ እረኛ ዳዊት የተጋፈጠው ሁኔታ ምንድን ነው?

 የሰውየው ቁመት ወደ ሦስት ሜትር ይጠጋል። ለውጊያ የተሰለፉት የእስራኤል ወታደሮች በሙሉ ከዚህ ሰው ጋር ለመጋጠም መፍራታቸው አያስገርምም! ጎልያድ የተባለው ይህ ግዙፍ ፍልስጤማዊ ከእርሱ ጋር ሊጋጠም የሚችል ወታደር መርጠው እንዲልኩ በመገዳደር ለበርካታ ሳምንታት ጠዋትና ማታ በእስራኤል ጦር ሠራዊት ላይ ሲሳለቅ ቆየ። በመጨረሻም አንድ ተራ ወጣት ከእርሱ ጋር ለመጋጠም ቀረበ። እረኛ የሆነው ዳዊት ከጎልያድ ጋር ሲነጻጸር አንድ ፍሬ ልጅ ይመስላል። ለነገሩ የጎልያድ ትጥቅና የጦር መሣሪያ ብቻ እንኳ ከዳዊት የበለጠ ሳይመዝን አይቀርም። ያም ሆኖ ወጣቱ ከዚህ ግዙፍ ሰው ጋር የተጋጠመ ሲሆን ባሳየው ድፍረት እስከ ዛሬ ድረስ በምሳሌነት ይጠቀሳል።​—⁠1 ሳሙኤል 17:1-51

2, 3. (ሀ) ዳዊት ጎልያድን በድፍረት ሊጋፈጥ የቻለው ለምን ነበር? (ለ) ይሖዋን መታመኛችን ለማድረግ የሚረዱንን የትኞቹን ሁለት እርምጃዎች እንመረምራለን?

2 ዳዊት ይህንን ድፍረት ከየት አመጣው? ዓመታት ካለፉ በኋላ የጻፋቸውን ቃላት ተመልከት:- “አቤቱ፣ አንተ ተስፋዬ ነህና፣ እግዚአብሔር ሆይ፣ ከታናሽነቴ ጀምረህ መታመኛዬ ነህና።” (መዝሙር 71:5) አዎን፣ ዳዊት ከወጣትነቱ ጀምሮ በይሖዋ ላይ ሙሉ በሙሉ ይታመን ነበር። ከፍልሚያው በፊት ጎልያድን እንዲህ ብሎት ነበር:- “አንተ ሰይፍና ጦር ጭሬም ይዘህ ትመጣብኛለህ፤ እኔ ግን ዛሬ በተገዳደርኸው በእስራኤል ጭፍሮች አምላክ ስም በሠራዊት ጌታ በእግዚአብሔር ስም እመጣብሃለሁ።” (1 ሳሙኤል 17:45) ጎልያድ የተመካው በከፍተኛ ጥንካሬውና በጦር መሣሪያዎቹ ሲሆን ዳዊት ግን የታመነው በይሖዋ ነበር። ዳዊት የአጽናፈ ዓለሙ ሉዓላዊ ጌታ ከእርሱ ጎን እስከሆነ ድረስ የቱንም ያህል ግዙፍና በሚገባ የታጠቀ ቢሆንም አንድን ተራ ሰው የሚፈራበት ምን ምክንያት አለው?

3 የዳዊትን ታሪክ ስታነብ እኔም እንደ እርሱ በይሖዋ ላይ ጠንካራ ትምክህት በኖረኝ የሚል ምኞት ያድርብሃል? አብዛኞቻችን እንደዚህ ይሰማናል። እንግዲያው ይሖዋን መታመኛችን ለማድረግ ልንወስዳቸው የሚገቡ ሁለት እርምጃዎችን እንመልከት። በመጀመሪያ በይሖዋ እንዳንታመን እንቅፋት የሚሆንብንን ነገር መወጣት ይኖርብናል። በሁለተኛ ደረጃ በይሖዋ መታመን ምን ነገሮችን እንደሚያካትት መማር ያስፈልገናል።

በይሖዋ እንዳንታመን የሚያደርገንን እንቅፋት መወጣት

4, 5. ብዙ ሰዎች በአምላክ መታመን የሚከብዳቸው ለምንድን ነው?

4 ሰዎች በአምላክ እንዳይታመኑ እንቅፋት የሚሆንባቸው ምንድን ነው? አብዛኛውን ጊዜ ሰዎች ክፉ ነገሮች የሚደርሱት ለምን እንደሆነ ግራ ይጋባሉ። ብዙዎች በሰው ልጆች ላይ መከራ የሚያመጣው አምላክ እንደሆነ ይነገራቸዋል። ቀሳውስት በአንድ ዓይነት አደጋ ሰዎች ሲሞቱ ሰለባዎቹን አምላክ ከእርሱ ጋር እንዲሆኑ ወደ ሰማይ “እንደወሰዳቸው” ይናገራሉ። ከዚህም በላይ በርካታ የሃይማኖት መሪዎች በዚህ ዓለም ላይ የሚደርሰው እያንዳንዱ አሳዛኝ ሁኔታም ሆነ የክፋት ድርጊት አምላክ አስቀድሞ የወሰነው እንደሆነ ያስተምራሉ። እንደዚህ ባለው ጨካኝ አምላክ መታመን በጣም ያስቸግራል። የማያምኑትን ሐሳብ የሚያሳውረው ሰይጣን እንዲህ ዓይነቱን “የአጋንንት ትምህርት” ለማስፋፋት ከፍተኛ ጥረት ያደርጋል።​—⁠1 ጢሞቴዎስ 4:1፤ 2 ቆሮንቶስ 4:4

5 ሰይጣን ሰዎች በይሖዋ ላይ ያላቸውን እምነት እንዲያጡ ይፈልጋል። ይህ የአምላክ ጠላት በሰው ልጆች ላይ መከራ የሚደርሰው ለምን እንደሆነ እንድናውቅ አይፈልግም። መከራ የሚደርሰው ለምን እንደሆነ መጽሐፍ ቅዱስ የሚሰጠውን ሐሳብ የምናውቅ ከሆነ ደግሞ ከአእምሯችን እንዲጠፋ ለማድረግ ይጥራል። በመሆኑም በዓለም ላይ ለሚደርሰው መከራ መንስኤ የሆኑትን ሦስት መሠረታዊ ምክንያቶች በየጊዜው መከለሳችን ተገቢ ነው። እንዲህ ማድረጋችን በሕይወታችን ውስጥ ለሚያጋጥሙን ችግሮች ተጠያቂው ይሖዋ እንዳልሆነ እንድናስታውስ ስለሚረዳን ማጽናኛ ማግኘት እንችላለን።​—⁠ፊልጵስዩስ 1:9, 10

6. አንደኛ ጴጥሮስ 5:​8 በሰው ልጆች ላይ መከራ የሚደርስበትን አንደኛውን ምክንያት የሚገልጸው እንዴት ነው?

6 በሰው ልጆች ላይ መከራ የሚደርስበት አንዱ ምክንያት ሰይጣን የይሖዋ ታማኝ አገልጋዮች አቋማቸውን እንዲያጎድፉ ስለሚፈልግ ነው። ሰይጣን፣ ኢዮብ ንጹህ አቋሙን እንዲያጎድፍ ለማድረግ ሞክሯል። ያን ጊዜ ባይሳካለትም ተስፋ ቆርጦ እጅ አልሰጠም። የዚህ ዓለም ገዥ እንደመሆኑ መጠን የአምላክን ታማኝ አገልጋዮች ‘ለመዋጥ’ ይጥራል። (1 ጴጥሮስ 5:8) ሁላችንም የጥቃቱ ዒላማዎች ነን! ሰይጣን ይሖዋን ማገልገላችንን ለማስቆም ይፈልጋል። በዚህም ምክንያት አብዛኛውን ጊዜ ስደት እንዲነሳ ያደርጋል። እንደዚህ ዓይነቱ ስደት ሥቃይ የሚያስከትል ቢሆንም እንድንጸና የሚያደርገን አጥጋቢ ምክንያት አለን። በዚህ መንገድ የሰይጣንን ውሸታምነት የምናጋልጥ ከመሆኑም በላይ ይሖዋን እናስደስታለን። (ኢዮብ 2:4፤ ምሳሌ 27:11) ይሖዋ የሚደርስብንን ስደት በጽናት እንድንወጣ የሚያስችል ኃይል በሰጠን መጠን በእርሱ ላይ ያለን ትምክህት ያድጋል።​—⁠መዝሙር 9:9, 10

7. ለመከራ ምክንያት የሚሆነው በገላትያ 6:​7 ላይ የተገለጸው ነገር ምንድን ነው?

7 “ሰው የሚዘራውን ሁሉ ያንኑ ደግሞ ያጭዳልና” የሚለው የመጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ ሥርዓት በሰዎች ላይ መከራ የሚደርስበትን ሁለተኛውን ምክንያት ግልጽ ያደርግልናል። (ገላትያ 6:7) አንዳንድ ጊዜ ሰዎች ጥበብ የጎደለው ምርጫ በማድረግ መዝራታቸው የሚያስከትልባቸውን መከራ ለማጨድ ይገደዳሉ። ጥንቃቄ በጎደለው መንገድ በማሽከርከራቸው አደጋ ሊያጋጥማቸው ይችላል። ብዙዎች ሲጃራ ማጨሳቸው የልብ ወይም የሳንባ ካንሰር ያስከትልባቸዋል። የጾታ ብልግና የሚፈጽሙ ሰዎች ቤተሰባቸው ሊፈርስ፣ ለራሳቸው አክብሮት ሊያጡ እንዲሁም በጾታ ግንኙነት ለሚተላለፉ በሽታዎችና ላልተፈለገ እርግዝና ሊጋለጡ ይችላሉ። ሰዎች እንዲህ ዓይነት መከራ ሲደርስባቸው ተጠያቂው አምላክ እንደሆነ ይናገሩ ይሆናል። እንደ እውነቱ ከሆነ ግን መከራ ሊደርስባቸው የቻለው መጥፎ ውሳኔ በማድረጋቸው ነው።​—⁠ምሳሌ 19:3

8. በመክብብ 9:​11 ላይ በተገለጸው መሠረት ሰዎች መከራ የሚደርስባቸው ለምንድን ነው?

8 በሰዎች ላይ መከራ የሚደርስበት ሦስተኛው ምክንያት በመክብብ 9:​11 ላይ ተመዝግቦ ይገኛል:- “እኔም ተመለስሁ፣ ከፀሐይ በታችም ሩጫ ለፈጣኖች፣ ሰልፍም ለኃያላን፣ እንጀራም ለጠቢባን፣ ባለጠግነትም ለአስተዋዮች፣ ሞገስም ለአዋቂዎች እንዳልሆነ አየሁ፤ ጊዜና እድል [“አጋጣሚ፣” NW ] ግን ሁሉን ይገናኛቸዋል።” አንዳንድ ጊዜ ሰዎች መከራ የሚያጋጥማቸው ባልሆነ ቦታ በአጉል ሰዓት በመገኘታቸው ብቻ ሊሆን ይችላል። በአካላዊ ሁኔታችን ጠንካሮችም ሆንን ደካሞች ሁላችንም ባልጠበቅነው ጊዜ ለመከራና ለሞት ልንዳረግ እንችላለን። ለምሳሌ ያህል በኢየሱስ ዘመን ኢየሩሳሌም ውስጥ 18 ሰዎች ግንብ ተደርምሶባቸው ሞተዋል። ሰዎቹ የሞቱት ከዚያ በፊት ለፈጸሙት ኃጢአት አምላክ ስለቀጣቸው እንዳልሆነ ኢየሱስ ገልጿል። (ሉቃስ 13:4) ለእንደዚህ ዓይነቱ መከራ ይሖዋ ተጠያቂ አይደለም።

9. መከራን በተመለከተ ብዙዎች ግልጽ ያልሆነላቸው ነገር ምንድን ነው?

9 በሰዎች ላይ መከራ እንዲደርስ ምክንያት የሚሆኑትን አንዳንድ ነገሮች ማወቁ ጠቃሚ ነው። ይሁን እንጂ ብዙዎች ለመረዳት አስቸጋሪ የሚሆንባቸው ከጉዳዩ ጋር የተያያዘ አንድ ነገር አለ። ይህም ይሖዋ አምላክ በሰዎች ላይ መከራ እንዲደርስ የሚፈቅደው ለምንድን ነው? የሚለው ነው።

ይሖዋ በሰዎች ላይ መከራ እንዲደርስ የሚፈቅደው ለምንድን ነው?

10, 11. (ሀ) በሮሜ 8:​19-22 መሠረት “ፍጥረት ሁሉ” ለምን ተዳርጓል? (ለ) ፍጥረትን ለከንቱነት ያስገዛው ማን እንደሆነ እንዴት ማወቅ እንችላለን?

10 ሐዋርያው ጳውሎስ ለሮሜ ክርስቲያኖች በጻፈው ደብዳቤ ላይ የተጠቀሰ አንድ ሐሳብ ይህንን አሳሳቢ ጉዳይ እንድንገነዘብ ይረዳናል። ጳውሎስ እንዲህ ሲል ጽፏል:- “የፍጥረት ናፍቆት የእግዚአብሔርን ልጆች መገለጥ ይጠባበቃልና። ፍጥረት ለከንቱነት ተገዝቶአልና፣ በተስፋ ስላስገዛው ነው እንጂ በፈቃዱ አይደለም፤ ተስፋውም ፍጥረት ራሱ ደግሞ ከጥፋት ባርነት ነፃነት ወጥቶ ለእግዚአብሔር ልጆች ወደሚሆን ክብር ነፃነት እንዲደርስ ነው። ፍጥረት ሁሉ እስከ አሁን ድረስ አብሮ በመቃተትና በምጥ መኖሩን እናውቃለንና።”​—⁠ሮሜ 8:19-22

11 ይህ ጥቅስ የሚያስተላልፈውን ሐሳብ ለመረዳት በመጀመሪያ ለአንዳንድ ቁልፍ ጥያቄዎች መልስ ማግኘት ይኖርብናል። ለምሳሌ ያህል፣ ፍጥረትን ለከንቱነት ያስገዛው ማን ነው? አንዳንድ የሃይማኖት አስተማሪዎች ሰይጣን እንደሆነ ሲናገሩ ሌሎች ደግሞ አዳም ነው ይላሉ። ይሁን እንጂ ሁለቱም ይህንን ማድረግ አይችሉም። ለምን? ምክንያቱም ፍጥረትን ለከንቱነት ያስገዛው አካል ይህንን የሚያደርገው “በተስፋ” በመሆኑ ነው። በእርግጥም፣ ታማኝ ሰዎች ከጊዜ በኋላ ‘ከጥፋት ባርነት ነፃ እንደሚወጡ’ ተስፋ ሰጥቷል። አዳምም ሆነ ሰይጣን እንዲህ ዓይነት ተስፋ ሊሰጡ አይችሉም። ይህንን ማድረግ የሚችለው ይሖዋ ብቻ ነው። በመሆኑም ፍጥረትን ለከንቱነት ያስገዛው እርሱ መሆኑን በግልጽ መረዳት ይቻላል።

12. አንዳንዶች “ፍጥረት ሁሉ” ስለሚለው አባባል ምን አመለካከት አላቸው? ትክክለኛውን ትርጉም ማወቅ የሚቻለውስ እንዴት ነው?

12 ሆኖም በዚህ ጥቅስ ላይ የሚገኘው “ፍጥረት ሁሉ” የሚለው አባባል ምን ያመለከታል? አንዳንዶች “ፍጥረት ሁሉ” የሚለው እንስሳትንና እፅዋትን ጨምሮ በዚህ ዓለም ላይ የሚገኘውን ፍጥረት በሙሉ ያመለክታል ይላሉ። ይሁን እንጂ እንስሳትና እፅዋት “ለእግዚአብሔር ልጆች ወደሚሆን ክብር ነፃነት” ለመድረስ ተስፋ ያደርጋሉን? በፍጹም። (2 ጴጥሮስ 2:12) እንግዲያው “ፍጥረት ሁሉ” የሚለው አባባል ከሰው ልጆች በስተቀር ማንንም ሊያመለክት አይችልም። በኤደን በተነሳው ዓመፅ ምክንያት ኃጢአትና ሞት የወረሰው፣ በተስፋ የሚቃትተው ፍጥረት ይህ ነው።​—⁠ሮሜ 5:12

13. በኤደን የተቆሰቆሰው ዓመፅ በሰው ልጆች ላይ ምን አስከትሏል?

13 ይህ ዓመፅ በሰው ዘር ላይ ምን አስከትሏል? ጳውሎስ ውጤቱን ከንቱነት በሚለው ቃል ገልጾታል። አንድ የማመሳከሪያ ጽሑፍ እንደገለጸው ቃሉ “ለታቀደለት ዓላማ መዋል ባለመቻሉ ከንቱ የሆነን ዕቃ” ያመለክታል። ሰዎች የተፈጠሩት ፍጹምና አንድነት ያለው ቤተሰብ ሆነው ገነት የሆነችውን ምድር በጋራ እየተንከባከቡ ለዘላለም እንዲኖሩ ነበር። ከዚህ በተቃራኒ ሕይወታቸው አጭር፣ በመከራ የተሞላና በአብዛኛው ተስፋ አስቆራጭ ሆኗል። ኢዮብ እንደተናገረው “ከሴት የተወለደ ሰው የሕይወቱ ዘመን ጥቂት ቀን ነው፣ መከራም ይሞላዋል።” (ኢዮብ 14:1) በእርግጥም የሰው ዘር ለከንቱነት ተገዝቷል!

14, 15. (ሀ) ይሖዋ በሰው ዘር ላይ የበየነው ፍርድ ፍትሐዊ መሆኑን የሚያሳይ ምን ማስረጃ አለ? (ለ) ጳውሎስ ፍጥረት ለከንቱነት የተገዛው “በፈቃዱ” አይደለም ያለው ለምንድን ነው?

14 አሁን ደግሞ “የምድር ሁሉ ፈራጅ” የሰው ዘር ይህን የመሰለ ሥቃይ የሞላበትና ተስፋ አስቆራጭ ሕይወት እንዲመራ ያደረገው ለምንድን ነው? የሚለው አቢይ ጥያቄ ይነሳል። (ዘፍጥረት 18:25) እንዲህ ማድረጉ ፍትሐዊ ነውን? የመጀመሪያዎቹ ወላጆቻችን ያደረጉትን ነገር መለስ ብለን እንመልከት። በአምላክ ላይ በማመፃቸው በይሖዋ ሉዓላዊነት ላይ ከፍተኛ ግድድር ካስነሳው ከሰይጣን ጎን ተሰልፈዋል። የሰው ልጅ ከይሖዋ አገዛዝ ወጥቶ በአንድ ዓመፀኛ መንፈሳዊ ፍጡር እየተመራ ራሱን ቢያስተዳድር የተሻለ ሕይወት ያገኛል የሚለውን አባባል በወሰዱት እርምጃ ደግፈዋል። ይሖዋ በዓመፀኞቹ ላይ ባስተላለፈው ፍርድ የጠየቁትን ነገር ሰጥቷቸዋል። የሰው ልጅ በሰይጣን ተጽዕኖ ሥር ሆኖ ራሱን እንዲገዛ ፈቅዷል። ከሁኔታዎቹ አንጻር የሰው ልጅ ተስፋ ኖሮት ለከንቱነት እንዲገዛ ከማድረግ የተሻለ ምን ፍትሐዊ እርምጃ ሊኖር ይችላል?

15 እርግጥ ነው፣ ፍጥረት ለከንቱነት የተገዛው “በፈቃዱ” አይደለም። የኃጢአትና የጥፋት ባሪያዎች ሆነን የተወለድነው ያለ ምርጫችን ነው። ይሁን እንጂ ይሖዋ አዳምና ሔዋንን ወዲያው ከማጥፋት ይልቅ በሕይወት እንዲኖሩና ልጆች እንዲወልዱ በምሕረቱ ፈቅዶላቸዋል። የአዳምና የሔዋን ዘሮች በመሆናችን የኃጢአትና የሞት ባሪያዎች ብንሆንም እነርሱ ሳያደርጉ የቀሩትን ነገር የማድረግ አጋጣሚ አለን። ይሖዋን ማዳመጥና የእርሱ ሉዓላዊ አገዛዝ ጽድቅ የሰፈነበት እንዲሁም እንከን የለሽ መሆኑን መማር እንችላለን። በአንጻሩ ግን የሰው ልጅ ከይሖዋ ርቆ ራሱን ለመግዛት ያደረገው ጥረት ያስገኘው ነገር ቢኖር ሥቃይ፣ ተስፋ መቁረጥና ከንቱነት መሆኑን እንገነዘባለን። (ኤርምያስ 10:23፤ ራእይ 4:11) ሰይጣን የሚያሳድረው ተጽዕኖ ደግሞ ነገሮችን ከማባባስ ሌላ የሚፈይደው ነገር የለም። የሰው ዘር ታሪክ ይህ እውነት መሆኑን ያረጋግጣል።​—⁠መክብብ 8:9

16. (ሀ) ዛሬ በዓለማችን ላይ ለሚታየው መከራ ተጠያቂው ይሖዋ እንዳልሆነ እንዴት እናውቃለን? (ለ) ይሖዋ ታማኝ ለሆኑ ሰዎች ምን ተስፋ ሰጥቷቸዋል?

16 በግልጽ ለመረዳት እንደሚቻለው ይሖዋ የሰው ዘር ለከንቱነት እንዲገዛ ያደረገበት አጥጋቢ ምክንያት አለው። እንዲህ ሲባል ታዲያ ዛሬ ሕይወታችን ትርጉም የለሽ እንዲሆንና በመከራ እንዲሞላ የሚያደርገው ይሖዋ ነው ማለት ነው? በአንድ ወንጀለኛ ላይ ፍትሐዊ የሆነ ቅጣት ስለበየነ ዳኛ አስብ። ወንጀለኛው የተፈረደበት ቅጣት ብዙ መከራ እንዲደርስበት ያደርገው ይሆናል። ሆኖም የመከራው መንስኤ ዳኛው እንደሆነ መናገሩ ትክክል ይሆናል? በፍጹም! ከዚህም በላይ የክፋት ድርጊቶች ምንጭ ይሖዋ አይደለም። ያዕቆብ 1:13 “እግዚአብሔር በክፉ አይፈተንምና፤ እርሱ ራሱስ ማንንም አይፈትንም” ይላል። እንዲሁም ይሖዋ ይህንን ፍርድ ያስተላለፈው “በተስፋ” መሆኑን መዘንጋት አይኖርብንም። ታማኝ የሆኑ የአዳምና የሔዋን ዘሮች ለከንቱነት መገዛታቸው የሚያከትምበትን ዘመን ማየትና ‘የእግዚአብሔር ልጆች በሚያገኙት ክብራማ ነፃነት’ መደሰት እንዲችሉ ፍቅራዊ ዝግጅት አድርጎላቸዋል። ታማኝ የሆኑ የሰው ዘሮች ፍጥረት ሁሉ እንደገና ለከንቱነት የሚገዛበት ሁኔታ ይፈጠር ይሆን ብለው ሳይጨነቁ ለዘላለም ይኖራሉ። ይሖዋ ለሁኔታው ፍትሐዊ የሆነ መፍትሔ ማስገኘቱ የእርሱ አገዛዝ ትክክለኛነት ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ እንዲረጋገጥ ያደርጋል።​—⁠ኢሳይያስ 25:8

17. ዛሬ በዓለም ላይ ለሚታየው መከራ ምክንያት የሚሆኑትን ነገሮች መለስ ብለን መመርመራችን ምን ጥቅም አለው?

17 በሰው ልጅ ላይ ለሚደርሰው መከራ መንስኤ የሆኑትን ነገሮች ስንከልስ ለክፋት ድርጊቶች ይሖዋን ተጠያቂ እንድናደርግ ወይም በእርሱ እንዳንታመን የሚያደርገን ምክንያት ይኖራል? ከዚህ በተቃራኒ ያደረግነው ምርምር ሙሴ በተናገራቸው በሚከተሉት ቃላት እንድንስማማ ይገፋፋናል:- “እርሱ አምላክ ነው፤ ሥራውም ፍጹም ነው፤ መንገዱም ሁሉ የቀና ነው፤ የታመነ አምላክ፣ ክፋትም የሌለበት፣ እርሱ እውነተኛና ቅን ነው።” (ዘዳግም 32:4) በእነዚህ ጉዳዮች ላይ በማሰላሰል ከላይ ላነሳናቸው ጥያቄዎች ምን መልስ እንደምንሰጥ አልፎ አልፎ ማሰባችን ጠቃሚ ነው። እንዲህ በማድረግ መከራ በሚደርስብን ጊዜ ሰይጣን በአእምሯችን ውስጥ ጥርጣሬ ለመዝራት የሚያደርገውን ጥረት መቋቋም እንችላለን። በመግቢያው ላይ ስለተጠቀሰው ስለ ሁለተኛው እርምጃስ ምን ማለት ይቻላል? በይሖዋ መታመን ምን ነገሮችን ይጨምራል?

በይሖዋ መታመን ምን ማለት ነው?

18, 19. መጽሐፍ ቅዱስ በይሖዋ እንድንታመን የሚያበረታታን እንዴት ነው? ሆኖም አንዳንዶች በዚህ ረገድ ምን የተሳሳተ አመለካከት አላቸው?

18 የአምላክ ቃል እንዲህ ሲል ያሳስበናል:- “በፍጹም ልብህ በእግዚአብሔር ታመን፣ በራስህም ማስተዋል አትደገፍ፤ በመንገድህ ሁሉ እርሱን እወቅ፣ እርሱም ጎዳናህን ያቀናልሃል።” (ምሳሌ 3:5, 6) እነዚህ የሚያበረታቱና አስደሳች ቃላት ናቸው። በእርግጥም በአጽናፈ ዓለሙ ውስጥ የምንወደውን አባታችንን ያህል እምነት ሊጣልበት የሚችል ሌላ ማንም የለም። ያም ሆኖ በምሳሌ መጽሐፍ ውስጥ የሰፈሩትን እነዚህን ቃላት ተግባራዊ ማድረግ የማንበቡን ያህል ቀላል አይደለም።

19 ብዙዎች በይሖዋ መታመን ሲባል ምን ማለት እንደሆነ በትክክል አይረዱትም። አንዳንዶች በይሖዋ መታመን በተፈጥሮ በልባችን ውስጥ የሚያድር የደስታ ስሜት እንደሆነ ያስባሉ። ሌሎች ደግሞ በአምላክ ከታመንን ከማንኛውም ዓይነት አስቸጋሪ ሁኔታ እንደሚጠብቀን፣ ለሚያጋጥሙን ችግሮች በሙሉ መፍትሔ እንደሚሰጠን፣ በየዕለቱ የሚያጋጥሙንን ፈታኝ ሁኔታዎች እኛ በምንፈልገው መንገድ ወዲያው እንደሚፈታልን ያምናሉ። ሆኖም እንዲህ ብሎ ለማሰብ የሚያስችል መሠረት የለም። በይሖዋ መታመን ሲባል በስሜት መመራት ወይም ተጨባጭ ባልሆነ ነገር ማመን ማለት አይደለም። በዕድሜ የበሰሉ ሰዎች በአንድ ነገር ላይ ትምክህት የሚጥሉት በጥንቃቄ አስበውበት ነው።

20, 21. በይሖዋ መታመን ሲባል ምን ማለት ነው? በምሳሌ አስረዳ።

20 ምሳሌ 3:​5 ምን እንደሚል እንደገና እንመልከት። ጥቅሱ በይሖዋ መታመንና በራሳችን ማስተዋል መደገፍ ሁለት ተቃራኒ ነገሮች መሆናቸውንና ሁለቱንም ጎን ለጎን ማስኬድ እንደማንችል ያሳያል። ይህ ማለት የማስተዋል ችሎታችንን እንዳንጠቀም ተከልክለናል ማለት ነው? አይደለም። እንዲያውም ይህንን ችሎታ የሰጠን ፈጣሪያችን ይሖዋ በማስተዋል ችሎታችን ተጠቅመን እንድናገለግለው ይፈልጋል። (ሮሜ 12:1 አ.መ.ት ) ሆኖም ውሳኔ ስናደርግ የምንደገፈው ወይም የምንታመነው በምን ላይ ነው? አስተሳሰባችን ከይሖዋ አስተሳሰብ ጋር የሚጋጭ ከሆነ እርሱ ያለው ጥበብ ከእኛ በጣም የላቀ እንደሆነ በመገንዘብ እንቀበለዋለን? (ኢሳይያስ 55:8, 9) በይሖዋ መታመን ማለት የእርሱ አስተሳሰብ እንዲመራን መፍቀድ ማለት ነው።

21 ጉዳዩን በምሳሌ ለማስረዳት መኪና ውስጥ ወላጆቹ ከፊት ተቀምጠው እርሱ በኋላኛው ወንበር ላይ የተቀመጠን አንድ ትንሽ ልጅ አስብ። መኪናውን የሚያሽከረክረው አባቱ ነው። በጉዞ ላይ እያሉ ትክክለኛውን መንገድ ስለመያዛቸው ጥያቄ ቢነሳ ወይም ከአየሩና ከመንገዱ ሁኔታ ጋር በተያያዘ ችግር ቢፈጠር ታዛዥ የሆነና በወላጆቹ የሚታመን ልጅ ምን ያደርጋል? ከኋላ ሆኖ አባቱ መኪናውን እንዴት ማሽከርከር እንዳለበት በመንገር መመሪያ ይሰጣል? ወላጆቹ የሚያደርጉትን ውሳኔ ይጠራጠራል? ወይም ደግሞ የወንበሩን ቀበቶ እንዲያስር የሚሰጡትን መመሪያ ለመቀበል አሻፈረኝ ይላል? በፍጹም። ወላጆቹ ፍጹማን ባይሆኑም እንኳን እንዲህ ዓይነት ሁኔታዎችን መወጣት እንደሚችሉ ይተማመንባቸዋል። ይሖዋ ፍጽምና የተላበሰ አባት ነው። በተለይ ፈታኝ ሁኔታዎች ሲያጋጥሙን ሙሉ በሙሉ በእርሱ መታመን አይገባንም?​—⁠ኢሳይያስ 30:21

22, 23. (ሀ) ችግሮች ሲያጋጥሙን በይሖዋ መታመን የሚኖርብን ለምንድን ነው? እንዲህ ማድረግ የምንችለውስ እንዴት ነው? (ለ) በሚቀጥለው ርዕስ ላይ የሚብራራው ምንድን ነው?

22 ይሁንና ምሳሌ 3:​6 እንደሚያሳየው ‘በመንገዳችን ሁሉ ይሖዋን ማወቅ ያለብን’ ችግሮች ሲያጋጥሙን ብቻ አይደለም። በዕለታዊ ሕይወታችን የምናደርጋቸው ውሳኔዎች በይሖዋ እንደምንታመን የሚያሳዩ መሆን አለባቸው። ችግሮች በሚከሰቱበት ጊዜ ተስፋ መቁረጥ፣ መደናገጥ ወይም ሁኔታውን ከሁሉ በተሻለ መንገድ መወጣት እንድንችል ይሖዋ የሚሰጠንን መመሪያ ገሸሽ ማድረግ የለብንም። ፈተናዎች ሲያጋጥሙን የይሖዋን ሉዓላዊነት ለመደገፍ፣ የሰይጣንን ውሸታምነት ለማጋለጥ እንዲሁም ታዛዥነትንና ይሖዋ የሚደሰትባቸውን ሌሎች ባሕርያት ለማዳበር እንደሚያስችሉ አጋጣሚዎች አድርገን ልናያቸው ይገባል።​—⁠ዕብራውያን 5:7, 8

23 ምንም ዓይነት እንቅፋት ቢደቀንብን በይሖዋ እንደምንታመን ማሳየት እንችላለን። በምናቀርበው ጸሎት እንዲሁም ከይሖዋ ቃልና ከድርጅቱ መመሪያ ለማግኘት በምናደርገው ጥረት በእርሱ እንደምንታመን እናሳያለን። ይሁን እንጂ ዛሬ የሚያጋጥሙንን አንዳንድ ችግሮች ለመወጣት በይሖዋ እንደምንታመን ማሳየት የምንችለው እንዴት ነው? የሚቀጥለው ርዕስ ይህንን ጉዳይ ያብራራል።

ምን ብለህ ትመልሳለህ?

• ዳዊት በይሖዋ እንደሚታመን ያሳየው እንዴት ነው?

• በዛሬው ጊዜ በሰዎች ላይ መከራ የሚደርሰው በየትኞቹ ሦስት ምክንያቶች የተነሳ ነው? እነዚህን ምክንያቶች አልፎ አልፎ መከለስ ጠቃሚ የሆነውስ ለምንድን ነው?

• ይሖዋ በሰው ዘር ላይ የበየነው ፍርድ ምንድን ነው? ፍርዱ ፍትሐዊ ነው የምንለውስ ለምንድን ነው?

• በይሖዋ መታመን ምን ነገሮችን ይጨምራል?

[የአንቀጾቹ ጥያቄዎች]

[በገጽ 8 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ዳዊት ይሖዋን መታመኛው አድርጓል

[በገጽ 10 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ኢየሱስ ኢየሩሳሌም ውስጥ አንድ ግንብ በተደረመሰ ጊዜ ይህንን ያደረገው ይሖዋ እንዳልሆነ ተናግሯል