በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ይሖዋ ምንጊዜም ይንከባከበናል

ይሖዋ ምንጊዜም ይንከባከበናል

የሕይወት ታሪክ

ይሖዋ ምንጊዜም ይንከባከበናል

ኤኔሌስ ምዛንግ እንደተናገረችው

የማላዊ የወጣቶች ማኅበር አባላት የሆኑ አሥር ወጣት ወንዶች ቤታችንን በርግደው በመግባት በአቅራቢያው ወደሚገኝ አንድ የሸንኮራ ማሳ እየጎተቱ ወሰዱኝ። ክፉኛ ከደበደቡኝ በኋላ የሞትኩ መስሏቸው ጥለውኝ ሄዱ። ይህ የሆነው በ1972 ነበር።

በማላዊ የሚገኙ በርካታ የይሖዋ ምሥክሮች እንዲህ ያለ ጭካኔ የተሞላበት ጥቃት ተፈጽሞባቸዋል። ስደት የደረሰባቸው ለምንድን ነው? እንዲጸኑ የረዳቸውስ ምንድን ነው? እስቲ የቤተሰቤን ታሪክ ላውጋችሁ።

የተወለድኩት ታኅሣሥ 31, 1921 ሲሆን ቤተሰቦቼ ሃይማኖተኛ ነበሩ። አባቴ የሴንትራል ፕሪስባይቴሪያን ቤተ ክርስቲያን ቄስ ነበር። ያደግኩት የማላዊ ዋና ከተማ በሆነችው በሊሎንግዌ አቅራቢያ በምትገኘው ኧንግኮም የተባለች ትንሽ ከተማ ውስጥ ነው። በ15 ዓመቴ ኤማስ ምዛንግን አገባሁ።

አንድ ቀን የአባቴ ጓደኛ የሆነ ቄስ ሊጠይቀን መጣ። በሠፈራችን ውስጥ የይሖዋ ምሥክሮች እንዳሉ ስላወቀ ከእነሱ ጋር ምንም ዓይነት ግንኙነት እንዳንመሠርት አስጠነቀቀን። የይሖዋ ምሥክሮች ጋኔን እንዳለባቸውና ካልተጠነቀቅን እኛም በአጋንንት ልንያዝ እንደምንችል ነገረን። ሁኔታው በጣም ስላስፈራን ቤት ቀይረን ወደ ሌላ መንደር የተዛወርን ሲሆን ባለቤቴም በዚያ በሚገኝ አንድ መደብር ውስጥ ተቀጥሮ ይሠራ ጀመር። ብዙም ሳይቆይ ግን በዚያ መንደር ውስጥም የይሖዋ ምሥክሮች እንዳሉ ተረዳን!

ይሁን እንጂ ከጥቂት ጊዜ በኋላ ኤማስ ለመጽሐፍ ቅዱስ ከፍተኛ ፍቅር ስለነበረው ከአንድ የይሖዋ ምሥክር ጋር ተነጋገረ። ኤማስ ለነበሩት በርካታ ጥያቄዎች አጥጋቢ መልስ በማግኘቱ ምሥክሮቹ መጽሐፍ ቅዱስን ከእነርሱ ጋር እንዲያጠና ያቀረቡለትን ሐሳብ ተቀበለ። መጀመሪያ ላይ ሳምንታዊ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቱን ያደርጉ የነበረው በሥራ ቦታው ሲሆን ከጊዜ በኋላ ግን በመኖሪያ ቤታችን ማጥናት ጀመሩ። የይሖዋ ምሥክሮችን እፈራቸው ስለነበረ ባለቤቴን ለማስጠናት በመጡ ቁጥር ቤቱን ለቅቄ እሄድ ነበር። ይሁንና ኤማስ በጥናቱ ገፋበት። ለስድስት ወራት ገደማ ካጠና በኋላ ሚያዝያ 1951 ተጠመቀ። ይሁን እንጂ ይህን ካወቀች ትዳራችን ሊፈርስ ይችላል ብሎ ስለሰጋ መጠመቁን ሳይነግረኝ ቀረ።

ፈታኝ ሳምንታት

ይሁንና አንድ ቀን የቅርብ ጓደኛዬ የሆነችው ኤለን ካድዛሌሮ ባለቤቴ መጠመቁን ነገረችኝ። ይህን ስሰማ በንዴት ተቃጠልኩ! ከዚያን ጊዜ አንስቶ አኮረፍኩት፤ ምግብም ከለከልሁት። በተጨማሪም ገላውን የሚታጠብበት ውኃ ቀድቶ ማምጣትና ማሞቅ አቆምኩ። በባሕላችን መሠረት አንዲት ሚስት ይህን ማድረግ ይጠበቅባት ነበር።

በዚህ ሁኔታ ለሦስት ሳምንታት ያህል ከዘለቅን በኋላ ኤማስ ስለ ጉዳዩ እንድንነጋገር በትሕትና ጠየቀኝና የይሖዋ ምሥክር ለመሆን የወሰነበትን ምክንያት ገለጸልኝ። እንደ 1 ቆሮንቶስ 9:​16 ያሉ ጥቅሶችን እያነበበ አስረዳኝ። ይህ ስሜቴን በጥልቅ የነካው ከመሆኑም በላይ እኔም ምሥራቹን መስበክ እንዳለብኝ ተሰማኝ። በመሆኑም ከይሖዋ ምሥክሮች ጋር መጽሐፍ ቅዱስ ለማጥናት ወሰንኩ። በዚያው ምሽት ለአፍቃሪው ባለቤቴ ቆንጆ እራት ሠራሁለት።

እውነትን ለቤተሰብና ለጓደኞች ማካፈል

ወላጆቻችን ከይሖዋ ምሥክሮች ጋር መገናኘት እንደጀመርን ሲሰሙ አጥብቀው ተቃወሙን። ቤተሰቦቼ ሁለተኛ አጠገባቸው ድርሽ እንዳንል የሚያስጠነቅቅ ደብዳቤ ጻፉልን። እንዲህ ያለ አቋም መውሰዳቸው ቢያሳዝነንም ኢየሱስ ብዙ መንፈሳዊ ወንድሞች፣ እህቶች፣ አባቶችና እናቶች እንደምናገኝ በሰጠው ተስፋ ላይ እምነት ነበረን።​—⁠ማቴዎስ 19:​29

የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቴን በትጋት በመከታተል ባለቤቴ በተጠመቀ በሦስት ወር ተኩል ጊዜ ውስጥ ነሐሴ 1951 ተጠመቅኩ። የመጽሐፍ ቅዱስን እውነት ለጓደኛዬ ለኤለን ማካፈል እንዳለብኝ ተሰማኝ። መጽሐፍ ቅዱስን እንድታጠና ያቀረብኩላትን ሐሳብ መቀበሏ አስደሰተኝ። ኤለን ግንቦት 1952 ተጠምቃ መንፈሳዊ እህቴ ሆነች። ይህም በመካከላችን ያለውን ወዳጅነት ይበልጥ አጠነከረው። አሁንም የልብ ወዳጆች ነን።

በ1954 ኤማስ ጉባኤዎችን እንዲጎበኝ የወረዳ የበላይ ተመልካች ሆኖ ተሾመ። በዚያን ጊዜ ስድስት ልጆች ወልደን ነበር። በወቅቱ ቤተሰብ ያለው ተጓዥ የበላይ ተመልካች አንድ ሳምንት ጉባኤዎችን ከጎበኘ በኋላ ቀጣዩን ሳምንት ከሚስቱና ከልጆቹ ጋር ያሳልፍ ነበር። ይሁን እንጂ ኤማስ ጉባኤዎችን በሚጎበኝበት ጊዜ ሁሉ የቤተሰብ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናታችንን እንድመራ ያደርግ ነበር። የቤተሰብ ጥናታችን ለልጆቻችን አስደሳች እንዲሆንላቸው የተቻለንን ጥረት እናደርግ ነበር። ለይሖዋና በቃሉ ላይ ለሰፈረው እውነት ያለንን ፍቅር ከልብ በመነጨ ስሜት እንገልጽላቸው የነበረ ከመሆኑም በላይ አብረን እናገለግላለን። ልጆቻችን እንዲህ ያለ መንፈሳዊ ሥልጠና ማግኘታቸው እምነታቸውን ያጠነከረላቸው ሲሆን በኋላ ለመጣው ስደት ዝግጁ እንዲሆኑ ረድቷቸዋል።

ሃይማኖታዊ ስደት ተቀጣጠለ

በ1964 ማላዊ ነፃነቷን ተቀዳጀች። የገዢው ፓርቲ ባለ ሥልጣናት ከፖለቲካ ገለልተኞች እንደሆንን ሲያውቁ የፓርቲ አባልነት ካርድ እንድንገዛ ያስገድዱን ጀመር። a እኔና ኤማስ ካርዱን ለመግዛት ፈቃደኞች ባለመሆናችን የወጣቶች ማኅበር አባላት ለቀጣዩ ዓመት ቀለብ ይሆነናል ብለን ያሰብነውን የበቆሎ እርሻችንን አወደሙብን። የማኅበሩ አባላት እርሻችንን ባወደሙበት ወቅት “የካሙዙን ፓርቲ ካርድ አንገዛም ያሉ ሁሉ የበቆሎ እርሻቸው በምስጥ ተበልቶ ለልቅሶና ለዋይታ ይዳረጋሉ” እያሉ ያንጎራጉሩ ነበር። እህላችን በዚህ መንገድ ቢወድምም በሐዘን አልተደቆስንም። ይሖዋ ተንከባክቦናል፤ እንዲሁም ችግሩን መቋቋም የምንችልበት ኃይል ሰጥቶናል።​—⁠ፊልጵስዩስ 4:​12, 13

ነሐሴ 1964 አንድ ቀን ሌሊት ቤት ውስጥ ብቻዬን ከልጆቹ ጋር ነበርኩ። ተኝተን የነበረ ቢሆንም ከሩቅ የሚሰማ የመዝሙር ድምፅ ከእንቅልፌ ቀሰቀሰኝ። ዘማሪዎቹ ጉሌዋምኩሉ ተብለው የሚጠሩ በጭፈራቸው የሚታወቁና እጅግ የሚፈሩ የአንድ ምስጢራዊ ማኅበር አባላት ነበሩ። እነዚህ ሰዎች የቀድሞ አባቶች መናፍስት መስለው በመቅረብ በሌሎች ላይ ጥቃት የማድረስ ልማድ አላቸው። አመጣጣቸው በእኛ ላይ ጥቃት ለመፈጸም ሲሆን ይህን እንዲያደርጉ የላካቸው የወጣቶች ማኅበሩ ነበር። ድምፃቸውን እንደሰማሁ ልጆቹን ቀሰቀስኩና እኛ ጋር ከመድረሳቸው በፊት ማሳ ውስጥ ገብተን ተደበቅን።

በተደበቅንበት ቦታ እንዳለን ቦግ ያለ ብርሃን ተመለከትን። ሰዎቹ የሣር ክዳን ያለውን ቤታችንን በእሳት አያያዙት። ቤቱም ሆነ በውስጡ የነበረን ንብረት ሙሉ በሙሉ ወደመ። ጥቃቱን ካደረሱ በኋላ አካባቢውን ለቅቀው በሚሄዱበት ጊዜ “ያ የይሖዋ ምሥክር እንዲሞቀው ጥሩ እሳት አያይዘንለታል” ብለው ሲያሾፉ ሰማን። አስቀድመን ወጥተን በመትረፋችን ይሖዋን እጅግ አመሰገንነው! ንብረታችንን በሙሉ ቢያወድሙብንም በሰው ከመታመን ይልቅ በይሖዋ ለመታመን የወሰድነውን ቁርጥ አቋም አላዳከሙብንም።​—⁠መዝሙር 118:​8

የጉሌዋምኩሉ አባላት በአካባቢያችን በሚኖሩ ሌሎች አምስት የይሖዋ ምሥክሮች ቤተሰቦች ላይ ተመሳሳይ ጥቃት መፈጸማቸውን ሰማን። በአቅራቢያችን በሚገኙ ጉባኤዎች ያሉ ወንድሞች ያደረጉልን እርዳታ ልባችንን በጥልቅ ነካው! ቤታችንን መልሰው የገነቡልን ከመሆኑም በላይ በርከት ላሉ ሳምንታት የሚያስፈልገንን ቀለብ ሰጥተውናል።

ስደቱ ተፋፋመ

መስከረም 1967 በመላ አገሪቱ የሚገኙትን የይሖዋ ምሥክሮች በሙሉ ለማፈስ ዘመቻ ተካሄደ። ጨካኝና ኃይለኛ የሆኑ የወጣቶች ማኅበርና የማላዊ ወጣት ዘማቾች አባላት ቆንጨራ ታጥቀው በየቤቱ እየገቡ የይሖዋ ምሥክሮችን ማደን ጀመሩ። ምሥክሮቹን ሲያገኙ የፖለቲካ ፓርቲ ካርድ እንዲገዙ ይጠይቋቸው ነበር።

እኛም ቤት መጥተው የፓርቲ ካርድ መግዛት አለመግዛታችንን ጠየቁን። “አልገዛሁም፤ አሁንም ሆነ ወደፊት አልገዛም” አልኳቸው። በዚህ ጊዜ እኔንና ባለቤቴን ምንም ነገር ሳንይዝ ባዶ እጃችንን አንጠልጥለው ፖሊስ ጣቢያ ወሰዱን። ልጆቻችን ከትምህርት ቤት ሲመለሱ ቤት ስላጡን በጣም ተረበሹ። ሆኖም ትልቁ ልጃችን ዳንኤል ከጥቂት ጊዜ በኋላ ወደ ቤት ሲመለስ የደረሰውን ሁኔታ አንድ ጎረቤታችን ነገረው። ወዲያውኑ ታናናሽ ወንድሞቹንና እህቶቹን ይዞ ወደ ፖሊስ ጣቢያው መጣ። ልጆቻችን ፖሊሶች ወደ ሊሎንግዌ ሊወስዱን በከባድ መኪናዎች ላይ እየጫኑን ሳለ ደረሱና አብረውን ተጓዙ።

ሊሎንግዌ ከደረስን በኋላ በፖሊስ ዋና መሥሪያ ቤት ለይስሙላ በተሰየመ ችሎት ፊት ቀረብን። ባለ ሥልጣናቱ “አሁንም እምነታችሁን አትተዉም?” ሲሉ ጠየቁን። አቋማችን የሰባት ዓመት እስር ሊያስፈርድብን እንደሚችል ብናውቅም “አንተውም” የሚል መልስ ሰጠን። የድርጅቱ “መሪዎች” ናቸው ተብለው የሚታሰቡ ወንድሞች ደግሞ የ14 ዓመት እስር ይፈረድባቸው ነበር።

ሌሊቱን ምንም እህል ሳንቀምስና ሳንተኛ ካሳለፍን በኋላ በማውል ወደሚገኝ እስር ቤት ወሰዱን። ማረፊያ ክፍሎቹ ከሚገባው በላይ በሰው ተጨናንቀው ስለነበር ወለሉ ላይ የምንተኛበት ቦታ እንኳ አልነበረም! በእያንዳንዱ ክፍል ውስጥ ከተቀመጠው ባልዲ በስተቀር ለመጸዳጃነት የሚያገለግል ምንም ነገር የለም። የሚሰጠን ምግብ በጣም ትንሽ ከመሆኑም በላይ እንደ ነገሩ የተዘጋጀ ነበር። ከሁለት ሳምንታት በኋላ የእስር ቤቱ ኃላፊዎች ሰላማዊ ሰዎች መሆናችንን በመገንዘባቸው በቅጥር ግቢው ውስጥ ወደሚገኘውና የአካል ብቃት እንቅስቃሴ ለመሥራት ወደሚያገለግለው ቦታ መውጣት እንድንችል ፈቀዱልን። በእስር ቤቱ ውስጥ በርካታ የይሖዋ ምሥክሮች እንገኝ ስለነበር በየዕለቱ እርስ በርስ ለመበረታታትና ለሌሎች እስረኞች ምሥክርነት ለመስጠት ጥሩ አጋጣሚ አግኝተናል። በማላዊ መንግሥት ላይ ዓለም አቀፍ ጫና በመደረጉ ከሦስት ወራት በኋላ መለቀቃችን ፈጽሞ ያልጠበቅነው ነገር ነበር።

የፖሊስ መኮንኖቹ ወደየቤታችን እንድንመለስ ቢያሳስቡንም በማላዊ የይሖዋ ምሥክሮች የታገዱ መሆናቸውን ሳይጠቁሙን አላለፉም። በይሖዋ ምሥክሮች ላይ የተጣለው እገዳ ለ26 ዓመታት ያህል ማለትም ከጥቅምት 20, 1967 እስከ ነሐሴ 12, 1993 ድረስ ዘልቋል። እነዚህ ዓመታት በጣም ፈታኝ የነበሩ ቢሆንም በይሖዋ እርዳታ ገለልተኝነታችንን ጠብቀን መኖር ችለናል።

እንደ እንስሳ ታደንን

ጥቅምት 1972 መንግሥት ሌላ አዋጅ በማውጣቱ አዲስ የስደት ማዕበል ተቀሰቀሰ። አዋጁ የይሖዋ ምሥክሮች በሙሉ ከሥራ ገበታቸው እንዲባረሩና በገጠር መንደሮች የሚኖሩት ደግሞ ከቀዬአቸው እንዲፈናቀሉ የሚያዝ ነበር። የይሖዋ ምሥክሮች እንደ እንስሳ በመታደን ላይ ነበሩ።

በዚህ ጊዜ አንድ ወጣት ክርስቲያን ወንድም ለኤማስ በጣም አስቸኳይ የሆነ መልእክት ይዞ በመምጣት ‘የወጣቶች ማኅበሩ አባላት አንገትህን በመቅላት ጭንቅላትህን ምሰሶ ላይ ሰቅለው ለመንደሩ ሹማምንት ለመስጠት ሴራ ጠንስሰዋል’ አለው። ኤማስ ሁላችንም ማምለጥ የምንችልበትን ሁኔታ ካመቻቸ በኋላ ወዲያውኑ ቤቱን ለቅቆ ጠፋ። ምንም ጊዜ ሳላጠፋ ልጆቹን ሰደድኳቸው። ከዚያ እኔም ቤቱን ጥዬ ልሄድ ስል አሥር የወጣት ማኅበሩ አባላት ኤማስን ፍለጋ መጡ። ቤታችንን በርግደው ቢገቡም ኤማስን ሊያገኙት አልቻሉም። ወጣቶቹ በጣም ስለተናደዱ በአቅራቢያችን ወዳለው የሸንኮራ ማሳ እየጎተቱ ወሰዱኝና በሸንኮራ አገዳ እንክት አድርገው ደበደቡኝ። ከዚያም የሞትኩ ስለመሰላቸው ትተውኝ ሄዱ። አቅሌን ስቼ ከቆየሁ በኋላ ራሴን ሳውቅ እንደ ምንም እየተሳብኩ ወደ ቤት ገባሁ።

የዚያን ቀን ማታ ኤማስ በሕይወቱ ቆርጦ በጨለማ እኔን ፍለጋ መጣ። ከፍተኛ ጉዳት እንደደረሰብኝ ሲያውቅ መኪና ካለው አንድ ጓደኛው ጋር ሆነው በቀስታ ተሸክመው መኪናው ላይ ጫኑኝ። ከዚያም በሊሎንግዌ ወደሚኖር አንድ ወንድም ቤት ወሰዱኝና ከቀን ወደ ቀን እያገገምኩ ሄድኩ። በዚህ ጊዜ ኤማስ አገሪቱን ለቅቀን መውጣት የምንችልበትን መንገድ ያፈላልግ ጀመር።

ማረፊያ ያጡ ስደተኞች

ሴት ልጃችን ዲኔስና ባለቤቷ አንድ ትልቅ የጭነት መኪና ነበራቸው። በአንድ ወቅት የማላዊ ወጣት ዘማቾች አባል የነበረ አንድ ሹፌር ቀጠሩ። ይህ ሰው በደረሰብን ሁኔታ እጅግ በማዘኑ እኛንም ሆነ ሌሎች የይሖዋ ምሥክሮችን ለመርዳት ፈቃደኛ ነበር። ለተወሰኑ ቀናት ማታ ማታ ወንድሞችን የተደበቁበት ቦታ ድረስ እየሄደ በመጫን በርካታ የፍተሻ ጣቢያዎችን አልፎ ወደ ዛምቢያ ድንበር አሻገራቸው። ወንድሞችን በሚያመላልስበት ጊዜ የማላዊ ወጣት ዘማቾች አባል እያለ የተሰጠውን የደንብ ልብስ ይለብስ የነበረ ሲሆን በመቶዎች የሚቆጠሩ የይሖዋ ምሥክሮችን ለመርዳት የራሱን ሕይወት አደጋ ላይ ጥሏል።

ከጥቂት ወራት በኋላ የዛምቢያ ባለ ሥልጣናት ወደ ማላዊ መለሱን። ይሁንና ወደ ቀድሞ መንደራችን ተመልሰን መኖር አልቻልንም። እዚያ ትተነው የሄድነው ንብረት በሙሉ፣ የቤታችን ጣሪያ እንኳ ሳይቀር ተዘርፎ ቆየን። ራሳችንን የምናስጠጋበት ቦታ በማጣታችን ወደ ሞዛምቢክ ተሰድደን በምላንጌኒ የስደተኞች ካምፕ ለሁለት ዓመት ተኩል ተቀመጥን። ይሁን እንጂ በሞዛምቢክ ሥልጣን የያዘው አዲስ መንግሥት ሰኔ 1975 የስደተኞቹን ካምፕ ዘግቶ ወደ ማላዊ እንድንመለስ አስገደደን። በማላዊ የነበረው ሁኔታ ግን አልተለወጠም ነበር። በመሆኑም በድጋሚ ወደ ዛምቢያ ከመሰደድ ሌላ ምንም አማራጭ አልነበረንም። እዚያ ከደረስን በኋላ ወደ ቺጉሙኪር የስደተኞች ካምፕ ገባን።

ከሁለት ወራት በኋላ በርከት ያሉ አውቶቡሶችና ትልልቅ የወታደር መኪናዎች መጥተው ዋናው መንገድ ላይ ከቆሙ በኋላ በመቶዎች የሚቆጠሩ የታጠቁ የዛምቢያ ወታደሮች ካምፑን ከበቡት። ቆንጆ ቆንጆ ቤቶች እንደተሠሩልን በመግለጽ እዚያ ሊወስዱን እንደመጡ ነገሩን። ይህ እኛን ለማታለል ብለው ያደረጉት ነገር እንደሆነ አላጣነውም። ወታደሮቹ ሰዉን እየገፈታተሩ ወደ መኪኖቹ መውሰድ ሲጀምሩ ከፍተኛ ሽብር ተፈጠረ። ወታደሮቹ አከታትለው ወደ ሰማይ ሲተኩሱ በሺዎች የሚቆጠሩ ወንድሞችና እህቶች በድንጋጤ በየአቅጣጫው ተበታተኑ።

በዚህ ትርምስ መሃል ኤማስ ተገፍትሮ በመውደቁ ተረጋገጠ። ይሁንና አንድ ወንድም ከወደቀበት አነሳው። ታላቁ መከራ የጀመረ ሆኖ ተሰማን። ስደተኞቹ በሙሉ ወደ ማላዊ መሸሽ ጀመሩ። እዚያው ዛምቢያ ውስጥ እያለን አንድ ወንዝ አጠገብ ስንደርስ ሁሉም ሰው በደህና ማቋረጥ እንዲችል ወንድሞች በሰልፍ ሆነው እጅ ለእጅ በመያያዝ ተሻገሩ። ይሁንና ወንዙን እንደተሻገርን የዛምቢያ ወታደሮች ከበቡንና አስገድደው ወደ ማላዊ ላኩን።

ማላዊ ከደረስን በኋላ መሄጃ አልነበረንም። በፖለቲካ ስብሰባዎችና በጋዜጦች ላይ ሕዝቡ ወደ መንደሩ የሚገቡ “ጸጉረ ልውጥ” ሰዎችን ማለትም የይሖዋ ምሥክሮችን በንቃት እንዲከታተል ማስጠንቀቂያ እንደተሰጠው ሰማን። በመሆኑም ሰዎች በቀላሉ እንዳይለዩን ስንል ወደ ዋና ከተማው ለመሄድ ወሰንን። አንድ ትንሽ ቤት ተከራየንና ኤማስ እንደ ቀድሞው ተጓዥ የበላይ ተመልካች ሆኖ ጉባኤዎችን በድብቅ መጎብኘት ጀመረ።

በጉባኤ ስብሰባዎች ላይ መገኘት

ታማኝነታችንን ጠብቀን እንድንኖር የረዳን ምንድን ነው? የጉባኤ ስብሰባ ነው! በሞዛምቢክና በዛምቢያ የስደተኞች ካምፕ ውስጥ እያለን የሳር ክዳን ባላቸው የመሰብሰቢያ አዳራሾች ውስጥ በነፃነት እንሰበሰብ ነበር። በማላዊ ስብሰባዎችን ማድረግ በጣም አደገኛና አስቸጋሪ የነበረ ቢሆንም ከስብሰባዎች ባለመቅረታችን እጅግ ተጠቅመናል። እንዳንያዝ ስንል አብዛኛውን ጊዜ የጉባኤ ስብሰባዎቻችንን የምናደርገው በጣም ከመሸ በኋላ ከከተማ ወጣ ብለን ነበር። የአካባቢውን ሰዎች ትኩረት ላለመሳብ ለተናጋሪዎች አድናቆታችንን የምንገልጸው በማጨብጨብ ሳይሆን እጃችንን እርስ በርስ በማፋተግ ነበር።

የጥምቀት ሥነ ሥርዓት የሚካሄደው ማታ በጨለማ ነበር። ወንድ ልጃችን አቢዩድ የተጠመቀው በእንዲህ ያለ ሁኔታ ነው። የጥምቀት ንግግር ከተሰጠ በኋላ እሱና ሌሎች የጥምቀት እጩዎች በአንድ ረግረጋማ አካባቢ በተቆፈረ ጉድጓድ ውስጥ ተጠመቁ።

ትንሹ ቤታችን የጽሑፍ ማከፋፈያ ሆኖ አገልግሏል

በእገዳ ሥር ባሳለፍናቸው የመጨረሻዎቹ ዓመታት በሊሎንግዌ የነበረው ቤታችን በድብቅ ጽሑፎችን ለማከፋፈል እንደ ማዕከል ሆኖ አገልግሏል። ከዛምቢያ ቅርንጫፍ ቢሮ የሚላክ ደብዳቤና ጽሑፍ በድብቅ ወደ ቤታችን ይመጣ ነበር። ጽሑፎችን በብስክሌት እየጫኑ የሚያጓጉዙ ወንድሞች ወደ ቤታችን በመምጣት ከዛምቢያ የሚላከውን ደብዳቤና ጽሑፍ በመላ አገሪቱ ያሰራጫሉ። የመጠበቂያ ግንብ መጽሔቶቹ የሚታተሙት በስስ ወረቀት ስለነበር ብዙም ክብደት አልነበራቸውም። ይህም ወንድሞች በአንድ ጊዜ በርካታ መጽሔቶችን ጭነው እንዲወስዱ ምቹ ሁኔታ ፈጥሮላቸዋል። ከዚህም በተጨማሪ እነዚህ ወንድሞች በጉባኤ የሚጠኑ ርዕሶችን ብቻ የያዙ በአነስተኛ መጠን የተዘጋጁ የመጠበቂያ ግንብ መጽሔቶችን ያሰራጩ ነበር። እነዚህ ትናንሽ መጽሔቶች የሚዘጋጁት በአንዲት ወረቀት ላይ በመሆኑ በሸሚዝ ኪስ ውስጥ በቀላሉ መደበቅ ይቻላል።

እነዚህ ወንድሞች ነፃነታቸውንና ሕይወታቸውን አደጋ ላይ በመጣል በብስክሌቶቻቸው ላይ የታገዱ ጽሑፎችን የያዙ ካርቶኖችን ጭነው በጥሻ ውስጥ ይጓዙ ነበር። አንዳንድ ጊዜም በጨለማ ለመጓዝ የሚገደዱባቸው ሁኔታዎች ነበሩ። የፍተሻ ጣቢያዎችና ሌሎች አደገኛ ሁኔታዎች የነበሩ ቢሆንም የትኛውም የአየር ሁኔታ ሳይበግራቸው ለወንድሞቻቸው መንፈሳዊ ምግብ ለማድረስ በርካታ ኪሎ ሜትሮች ይጓዛሉ። እነዚህ ውድ ወንድሞች በእርግጥም ከፍተኛ ድፍረት አሳይተዋል!

ይሖዋ መበለቶችን ይንከባከባል

ታኅሣሥ 1992 ኤማስ በአንድ ጉባኤ የወረዳ የበላይ ተመልካች ሆኖ ንግግር እየሰጠ ሳለ በአንጎሉ ውስጥ ደም በመርጋቱ ራሱን ስቶ ወደቀ። በዚህም ምክንያት የመናገር ችሎታውን አጣ። ከተወሰነ ጊዜ በኋላ ተመሳሳይ የጤና እክል አጋጠመውና ግማሽ ጎኑ ሽባ ሆነ። የደረሰበትን የጤና ችግር መቋቋም ከብዶት የነበረ ቢሆንም የጉባኤያችን ወንድሞች ያደረጉልን ፍቅራዊ ድጋፍ የተሰማኝን ጥልቅ ሐዘን አቅልሎልኛል። ባለቤቴ ኅዳር 1994 በ76 ዓመቱ እስከሞተበት ጊዜ ድረስ ቤት ውስጥ አስታምሜዋለሁ። ለ57 ዓመታት በትዳር ዓለም አብረን ያሳለፍን ሲሆን ኤማስ በሕይወት እያለ እገዳው ሲነሳልን ለማየት በቅቷል። ይሁንና ታማኝ አጋሬን ማጣቴ ያስከተለብኝ ሐዘን አሁንም አልወጣልኝም።

ኤማስ ከሞተ በኋላ የልጄ ባል ከሚስቱና ከአምስት ልጆቹ በተጨማሪ እኔንም ማስተዳደር ጀመረ። የሚያሳዝነው ግን ለጥቂት ጊዜ ከታመመ በኋላ ነሐሴ 2000 አረፈ። ሴት ልጄ ይህ ትልቅ ቤተሰብ የሚያስፈልገውን ቀለብና መጠለያ ማቅረብ የምትችለው እንዴት ይሆን? በዚህ ጊዜም ቢሆን ይሖዋ እንደሚንከባከበንና ‘አባት ለሌላቸው ልጆች አባት፣ ለባልቴቶችም ዳኛ’ እንደሆነ ተገንዝቤያለሁ። (መዝሙር 68:5) ይሖዋ በአገልጋዮቹ አማካኝነት ቆንጆ ቤት ሰጥቶናል። እንዴት? በጉባኤያችን ያሉ ወንድሞችና እህቶች የደረሰብንን ችግር ሲመለከቱ በአምስት ሳምንታት ጊዜ ውስጥ አዲስ ቤት ሠርተው ሰጡን! በሌሎች ጉባኤዎች የሚገኙ የግንበኝነት ሙያ ያላቸው ወንድሞችም በግንባታ ሥራው ተሳትፈዋል። የሠሩልን ቤት ብዙዎቹ ወንድሞች ከሚኖሩበት ቤት የተሻለ በመሆኑ ያሳዩን ፍቅርና ደግነት ልባችንን በጥልቅ ነካው። ወንድሞች በፍቅር ተገፋፍተው ያደረጉልን ነገር ለጎረቤቶቻችን ጥሩ ምሥክርነት ሰጥቷል። ማታ ማታ አልጋዬ ላይ ሆኜ ሳስብ ገነት ውስጥ እንዳለሁ ሆኖ ይሰማኛል! አዲሱ ቤታችን በጡብና በአርማታ የተሠራ ቢሆንም ብዙዎች እንደተናገሩት ቤቱ በእርግጥም በፍቅር የተገነባ ነው።​—⁠ገላትያ 6:​10

የይሖዋ እንክብካቤ አሁንም አልተለየኝም

አልፎ አልፎ በተስፋ መቁረጥ ስሜት የተዋጥኩባቸው ጊዜያት ቢኖሩም ይሖዋ ደግፎኛል። ከዘጠኙ ልጆቼ መካከል ሰባቱ በሕይወት ያሉ ሲሆን ቤተሰቤ በአሁኑ ጊዜ 123 አባላትን ያቀፈ ሆኗል። ከእነዚህ መካከል አብዛኞቹ ይሖዋን በታማኝነት እያገለገሉ በመሆኑ እጅግ ደስተኛ ነኝ!

በአሁኑ ጊዜ 82 ዓመት የሞላኝ ሲሆን የአምላክ መንፈስ በማላዊ ያከናወነውን ነገር መለስ ብዬ ስመለከት ልቤ በሐሴት ይሞላል። ቀደም ባሉት ዓመታት በማላዊ የመሰብሰቢያ አዳራሽ ያልነበረን ሲሆን ባለፉት አራት ዓመታት ውስጥ ብቻ ከ600 በላይ አዳራሾች ተሠርተዋል። በተጨማሪም በአሁኑ ጊዜ በሊሎንግዌ አዲስ የቅርንጫፍ ቢሮ የተገነባ ከመሆኑም በላይ እምነት የሚያጠናክር መንፈሳዊ ምግብ እንደ ልብ እናገኛለን። በኢሳይያስ 54:​17 ላይ አምላክ “በአንቺ ላይ የተሠራ መሣሪያ ሁሉ አይከናወንም” ሲል የገባው ቃል ፍጻሜውን ሲያገኝ ተመልክቻለሁ። ይሖዋን በማገልገል ያሳለፍኳቸው ከ50 የሚበልጡ ዓመታት ምንም ዓይነት ፈተና ቢደርስብን ይሖዋ ምንጊዜም እንደሚንከባከበን እንድተማመን አድርገውኛል።

[የግርጌ ማስታወሻ]

a በማላዊ የሚኖሩ የይሖዋ ምሥክሮችን ታሪክ በተመለከተ ተጨማሪ መረጃ ለማግኘት በይሖዋ ምሥክሮች የተዘጋጀውን የ1999 የይሖዋ ምሥክሮች የዓመት መጽሐፍ ገጽ 149-223 ተመልከት።

[በገጽ 24 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ባለቤቴ የተጠመቀው ሚያዝያ 1951 ነው

[በገጽ 26 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ጽሑፍ ያሰራጩ የነበሩ ደፋር ወንድሞች

[በገጽ 28 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

በፍቅር የተገነባ ቤት