በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

መጽሐፍ ቅዱስ ትዳራችሁ የሰመረ እንዲሆን ይረዳል

መጽሐፍ ቅዱስ ትዳራችሁ የሰመረ እንዲሆን ይረዳል

መጽሐፍ ቅዱስ ትዳራችሁ የሰመረ እንዲሆን ይረዳል

ትዳር የሚለው ቃል ለአንዳንዶች ደስ የሚል ስሜት በውስጣቸው ይፈጥርባቸዋል። ሌሎች ግን ገና ቃሉን ሲሰሙ ያንገሸግሻቸዋል። አንዲት ሚስት እንዲህ በማለት ምሬቷን ገልጻለች:- “በአካል አብረን ብንኖርም በመንፈስ ግን የተፋታን ይመስለኛል። ችላ እንደተባልኩና ብቻዬን እንደተተውኩ ሆኖ ይሰማኛል።”

በአንድ ወቅት ለመዋደድና አንዳቸው ሌላውን ለመንከባከብ ቃል የተጋቡ ሰዎች እንዲህ እንዲራራቁ የሚያደርጋቸው ምንድን ነው? አንደኛው ምክንያት ትዳር ስለሚያስከትለው ኃላፊነት ቀድሞውኑ ግንዛቤ የሌላቸው መሆኑ ነው። አንድ የሕክምና መጽሔት አዘጋጅ “ወደ ትዳር ዓለም የምንገባው ምንም እውቀቱ ሳይኖረን ነው” በማለት ተናግረዋል።

በዩናይትድ ስቴትስ፣ ኒው ጀርሲ ግዛት በረትገርስ ዩኒቨርሲቲ አስተባባሪነት ብሔራዊ የጋብቻ ፕሮጀክት ያደረገው ጥናት እንደሚያሳየው በዛሬው ጊዜ ስለ ትዳር በቂ ግንዛቤ ያላቸው ሰዎች በጣም ጥቂት ናቸው። የፕሮጀክቱ ኃላፊ እንዲህ ሲሉ ጽፈዋል:- “ጥናቱ ከተደረገባቸው መካከል ብዙዎቹ በተፋቱ ወይም ደስታ የራቀው ትዳር ባላቸው ወላጆች ያደጉ ናቸው። ያልሰመረ ትዳር ምን እንደሚመስል ጠንቅቀው ያውቃሉ። ስኬታማ የሆነ ትዳር ምን ሊመስል እንደሚችል ግን በእርግጠኝነት መናገር አይችሉም። እንዲያውም አንዳንዶቹ የሰመረ ትዳር ምን ይመስላል ቢባሉ ‘እንደወላጆቼ ትዳር ያልሆነ’ ከማለት ሌላ ብዙም የሚሉት የላቸውም።”

ክርስቲያኖች በትዳራቸው ውስጥ ችግር አያጋጥማቸውም ሊባል ይቻላል? በፍጹም። እንዲያውም በመጀመሪያው መቶ ዘመን የነበሩ አንዳንድ ክርስቲያኖች “መፋታትን አትሻ” የሚል ቀጥተኛ ምክር ተሰጥቷቸው ነበር። (1 ቆሮንቶስ 7:27) ፍጹም ባልሆኑ ሰዎች የተመሠረተ ትዳር ሳንካ ሊገጥመው እንደሚችል የታወቀ ነው። የትዳር ጓደኛሞች በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሚገኙ መመሪያዎችን ተግባራዊ በማድረግ የጋብቻ ሰንሰለታቸውን ማጠናከር ይችላሉ።

መጽሐፍ ቅዱስ የጋብቻ መመሪያ መጽሐፍ እንዳልሆነ ግልጽ ነው። ቢሆንም የጋብቻን ዝግጅት ያቋቋመው አምላክ በመንፈሱ አነሳሽነት ያስጻፈው በመሆኑ በውስጡ የሚገኙት መመሪያዎች ትዳርን የሰመረ ለማድረግ ይረዳሉ ብለን በእርግጠኝነት መናገር እንችላለን። ይሖዋ አምላክ በነቢዩ ኢሳይያስ በኩል እንዲህ በማለት ተናግሯል:- “እኔ የሚረባህን ነገር የማስተምርህ በምትሄድባትም መንገድ የምመራህ አምላክህ እግዚአብሔር ነኝ። ትእዛዜን ብትሰማ ኖሮ፣ ሰላምህ እንደ ወንዝ ጽድቅህም እንደ ባሕር ሞገድ በሆነ ነበር።”—ኢሳይያስ 48:17, 18

በአንተና በትዳር ጓደኛህ መካከል የነበረው ፍቅር እየቀዘቀዘ እንደመጣ ተሰምቶሃል? ፍቅር በጠፋበት የትዳር ሕይወት እንደታሰርክ ይሰማሃል? በትዳር ዓለም 26 ዓመታት ያሳለፈች አንዲት ሚስት እንዲህ ብላለች:- “እንዲህ ያለው የትዳር ሕይወት የሚያስከትለውን የስሜት ስቃይ በቃላት መግለጽ ያስቸግራል። ስቃዩ እፎይታ የሌለው ከመሆኑም በላይ ውስጥ ድረስ ዘልቆ የሚሰማ ነው።” ሊሻሻል አይችልም ብለህ ተስፋ ከመቁረጥ ይልቅ ለምን በትዳርህ ላይ ሕይወት ለመዝራት ቆርጠህ አትነሳም? የሚቀጥለው ርዕስ ባልና ሚስት ትዳራቸውን የሰመረ በማድረግ ረገድ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሚገኘው መመሪያ እንዴት ሊረዳቸው እንደሚችል እንመለከታለን።