በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ማርቲን ሉተርና ትቶት ያለፈው ቅርስ

ማርቲን ሉተርና ትቶት ያለፈው ቅርስ

ማርቲን ሉተርና ትቶት ያለፈው ቅርስ

“በታሪክ ውስጥ ከኢየሱስ ክርስቶስ ቀጥሎ የማርቲን ሉተርን ያህል ብዙ መጽሐፍ የተጻፈለት ሰው እንደሌለ ይነገራል።” ይህ አስተያየት የወጣው በታይም መጽሔት ላይ ነበር። ሉተር የተናገራቸው ቃላትና ያደረጋቸው ነገሮች “በሰው ዘር ታሪክ ውስጥ ታላቅ አብዮት” የተባለው ሃይማኖታዊ የተሃድሶ እንቅስቃሴ እንዲቀጣጠል በማድረግ ትልቁን ሚና ተጫውተዋል። በዚህም በአውሮፓ የነበረውን ሃይማኖታዊ ገጽታ ለመለወጥና አህጉሩን የሸፈነውን የድንቁርና መጋረጃ ለመግፈፍ አስተዋጽኦ አድርጓል። በተጨማሪም ሉተር ለጀርመን የሥነ ጽሑፍ ቋንቋ እድገት ጥሩ መሠረት ጥሏል። የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉሙ በጀርመንኛ ከተተረጎሙት ሌሎች መጽሐፍ ቅዱሶች ሁሉ ይበልጥ ተወዳጅነት አለው።

ማርቲን ሉተር ምን ዓይነት ሰው ነበር? በአውሮፓውያን ሕይወት ላይ ይህን ያህል ለውጥ ሊያመጣ የቻለው እንዴት ነው?

ሉተር ምሑር ለመባል በቃ

ማርቲን ሉተር ኅዳር 1483 በአይስሌበን፣ ጀርመን ተወለደ። አባቱ የመዳብ ቁፋሮ ሠራተኛ ቢሆኑም ማርቲንን ትምህርት ቤት ለመላክ እጅ አላጠራቸውም። ማርቲን በ1501 ኢርፈርት ዩኒቨርሲቲ ገባ። ለመጀመሪያ ጊዜ መጽሐፍ ቅዱስን ያነበበው በዚህ ዩኒቨርሲቲ ቤተ መጻሕፍት ውስጥ ነበር። በወቅቱ የተሰማውን ሲናገር እንዲህ ብሏል:- “መጽሐፉን በጣም ወደድኩት። አንድ ቀን ተሳክቶልኝ የራሴ መጽሐፍ ቅዱስ ይኖረኛል ብዬ ተስፋ አደረግሁ።”

ሉተር በ22 ዓመቱ ኢርፈርት በሚገኘው አውጉስቲን ገዳም ገባ። ከጊዜ በኋላ በዊትንበርግ ዩኒቨርሲቲ መንፈሳዊ ትምህርት ተከታትሎ የዶክትሬት ዲግሪ ያዘ። ሉተር የአምላክ ሞገስ እንደማይገባው አድርጎ ራሱን ይቆጥር የነበረ ሲሆን አንዳንድ ጊዜ ሕሊናው ስለሚወቅሰው የመንፈስ ጭንቀት ያድርበት ነበር። ሆኖም የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት፣ ጸሎትና ማሰላሰል አምላክ ኃጢአተኞችን እንዴት እንደሚመለከት የተሻለ ግንዛቤ እንዲኖረው ረድቶታል። ሉተር የአምላክ ሞገስ በራስ ጥረት የሚገኝ ሳይሆን አምላክ ለሚያምኑ ሁሉ የሚሰጠው የጸጋ ስጦታ እንደሆነ ተገነዘበ።—ሮሜ 1:16፤ 3:23, 24, 28

ሉተር ይህ አዲሱ ግንዛቤው ትክክል ነው ወደሚል መደምደሚያ ላይ ሊደርስ የቻለው እንዴት ነበር? በጥንታዊ የቤተ ክርስቲያን ታሪክና በአዲስ ኪዳን የቃላት ምርምር ፕሮፌሰር የሆኑት ኩርት አላንት እንዲህ ሲሉ ጽፈዋል:- “ይህ አዲስ እውቀቱ ከሌሎች የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍሎች ጋር ይስማማ እንደሆነ ለማረጋገጥ በመላው መጽሐፍ ቅዱስ ላይ ያሰላስል የነበረ ሲሆን ሁሉም የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍሎች ይህን ሐሳቡን የሚደግፉ ሆነው አግኝቷቸዋል።” መዳን የሚገኘው በሥራ ወይም ሱባዔ በመግባት ሳይሆን በእምነት ነው የሚለው መሠረተ ትምህርት ለሉተር ትምህርቶች እንደ ምሰሶ ነበር።

ስርየት በገንዘብ መሸጡን ይቃወም ነበር

አምላክ ለኃጢአተኞች ስላለው አመለካከት ሉተር ያገኘው አዲስ እውቀት ከሮማ ካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ጋር አጋጭቶታል። በወቅቱ ኃጢአተኞች ከሞቱ በኋላ መንጽሔ ገብተው የተወሰነ ጊዜ በቅጣት እንደሚያሳልፉ በሰፊው ይታመን ነበር። ሆኖም ከጳጳሱ ሥልጣን ለተሰጠው ሰው ገንዘብ በመክፈል ይህን የቅጣት ጊዜ ማሳጠር ይቻላል የሚል አመለካከት ነበር። ለሜይንዝ ሊቀ ጳጳስ ለአልበርት ወኪሎች ሆነው ይሠሩ የነበሩት እንደ ዮሐንስ ቴዜል ያሉት የስርየት ሻጮች ለተራው ሕዝብ የኃጢአት ስርየት በመሸጥ ከፍተኛ መጠን ያለው ገንዘብ ይሰበስቡ ነበር። ብዙዎች በገንዘብ የሚገዙት የኃጢአት ስርየት ወደፊት ለሚሠሩት ኃጢአት ዋስትና እንደሚሆናቸው ይሰማቸው ነበር።

ሉተር ይህ ሁኔታ በጣም ያበሳጨው ነበር። ሰዎች ኃጢአታቸውን ከአምላክ ጋር በገንዘብ ሊያወራርዱ እንደማይችሉ ያውቅ ነበር። በ1517 የመከር ወራት የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን በገንዘብ፣ በመሠረተ ትምህርትና በሃይማኖታዊ አመለካከቶች ሕዝቡን እንደምታታልል በመወንጀል በብዙዎች ዘንድ የሚታወቁትን 95 የተቃውሞ ሐሳቦች ጻፈ። ከዚያም ሉተር የእነዚህን የተቃውሞ ሐሳቦች ቅጂ ለሜይንዝ ሊቀ ጳጳስ ለአልበርትና ለሌሎች ምሑራን ላከ። ይህን ያደረገው ዓመፅ ለመቀስቀስ ሳይሆን ሃይማኖታዊ ተሃድሶ እንዲደረግ ለማነሳሳት ነበር። በርካታ የታሪክ ምሑራን የተሃድሶው እንቅስቃሴ የጀመረው በዚህ ወቅት ማለት በ1517 ገደማ እንደሆነ ይናገራሉ።

የቤተ ክርስቲያኒቱን ስህተቶች ለማጋለጥ ሉተር የመጀመሪያውም የመጨረሻውም አልነበረም። ከመቶ ዓመታት ቀደም ብሎ የቼክ ሃይማኖታዊ ተሃድሶ አራማጅ የነበረው ያን ሁስ ስርየትን በገንዘብ መሸጥን አውግዞ ነበር። ከሁስ በፊትም ቢሆን እንግሊዛዊው ጆን ዋይክሊፍ ቤተ ክርስቲያኒቱ የምትከተላቸው አንዳንድ ልማዶች የመጽሐፍ ቅዱስ ድጋፍ እንደሌላቸው ገልጾ ነበር። በሉተር ዘመን የኖረው የሮተርዳሙ ኢራስመስና እንግሊዛዊው ቲንደልም ሃይማኖታዊ ተሃድሶ እንዲደረግ ግፊት አድርገዋል። ይሁን እንጂ ጀርመናዊው ዮሐንስ ጉተንበርግ ለፈለሰፈው የማተሚያ ማሽን ምሥጋና ይግባውና የሉተር ተቃውሞ ከሌሎቹ የተሃድሶ አራማጆች ይበልጥ ጎልቶ ማስተጋባት ችሏል።

የጉተንበርግ ማተሚያ በሜይንዝ ከተማ በሥራ ላይ የዋለው በ1455 ሲሆን በ16ኛው መቶ ዘመን መባቻ ላይ በ60 የጀርመን ከተሞችና በ12 የአውሮፓ አገሮች ማተሚያ ቤቶች ተቋቁመው ነበር። በታሪክ ውስጥ ለመጀመሪያ ጊዜ ትኩረት የሚስቡ ዜናዎችን በትኩስነታቸው ወደ ሕዝብ ጆሮ ለማድረስ ተችሎ ነበር። ምናልባት የሉተር 95 የተቃውሞ ሐሳቦች ያለ እርሱ ፈቃድ ታትመው ሳይሰራጩ አይቀሩም። በዚህ የተነሳ የተሃድሶው ጥያቄ የጥቂቶች አጀንዳ መሆኑ ቀርቶ ብዙዎችን የሚያወዛግብ ጉዳይ ሆነ። ማርቲን ሉተርም በአንድ ጀንበር ጀርመን ውስጥ በጣም ታዋቂ ሰው ለመሆን በቃ።

“ፀሐይና ጨረቃ” መልስ ሰጡ

ለበርካታ መቶ ዘመናት አውሮፓ በሁለት ኃይሎች ማለትም በታላቁ የሮማ ሥርወ መንግሥትና በሮማ ካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን መዳፍ ውስጥ ነበረች። የሉተራን ዓለም አቀፍ ፌደሬሽን የቀድሞ ፕሬዚዳንት የነበሩት ሃንስ ሊለዬ “ንጉሠ ነገሥቱና ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሱ ልክ እንደ ፀሐይና ጨረቃ የማይነጣጠሉ ነበሩ” ብለዋል። ይሁን እንጂ ማን ፀሐይ ማን ጨረቃ እንደነበር በእርግጠኝነት አይታወቅም። በ16ኛው መቶ ዘመን መጀመሪያ አካባቢ ሁለቱም ኃይሎች ሥልጣናቸው ከፍተኛ ደረጃ ላይ የደረሰ ሲሆን የለውጥ ደመናም እያንዣበበ ነበር።

ሊቀ ጳጳስ ሊዮ አሥረኛ ሉተር ተሳስቻለሁ ብሎ ይቅርታ ካልጠየቀ እንደሚያወግዙት የሚገልጽ ደብዳቤ ላኩበት። ሉተር በዚህ ሳይበገር ጳጳሱ የላኩትን የማስፈራሪያ ደብዳቤ በአደባባይ አቃጠለው። እንዲሁም ጳጳሱ ባይስማሙም እንኳ መሳፍንቱ ለሃይማኖታዊ ተሃድሶ እንዲነሱ የሚቀሰቅሱ ተጨማሪ ጽሑፎች አሳተመ። በ1521 ርዕሰ ሊቃነ ጳጳስ ሊዮ አሥረኛ ሉተርን በይፋ አወገዙት። ሉተር እንዲህ ያለው እርምጃ የተወሰደበት ጉዳዩ በተገቢው መንገድ ሳይታይለት እንደሆነ በመግለጽ ተቃውሞውን ሲያሰማ ንጉሠ ነገሥት ቻርለስ አምስተኛ በዎርምስ በሚደረገው የመሳፍንቶች ጉባኤ ላይ እንዲገኝ አስጠሩት። ሉተር በሚያዝያ 1521 ከዊትንበርግ እስከ ዎርምስ ያደረገው የ15 ቀን ጉዞ ከድል ሰልፍ ጋር ይመሳሰል ነበር ለማለት ይቻላል። ከፍተኛ የሕዝብ ድጋፍ አግኝቶ የነበረ ሲሆን በደረሰባቸው ቦታዎች ሁሉ ሰዎች ሊያዩት ይፈልጉ ነበር።

ሉተር በዎርምስ በንጉሠ ነገሥቱ፣ በመሳፍንቱና በጳጳሱ ተወካይ ፊት ቀረበ። በ1415 ያን ሁስ በኮንስታንስ በዚህ ዓይነት ጉባኤ ፊት ቀርቦ የተፈረደበት ሲሆን በእንጨት ላይ ተቃጥሏል። ሉተር በመንግሥት ባለ ሥልጣናትም ሆነ በቤተ ክርስቲያን ተጠሪዎች ፊት ተቃዋሚዎቹ መሳሳቱን ከመጽሐፍ ቅዱስ ማስረጃ እየጠቀሱ ካላሳዩት በስተቀር ተሳስቻለሁ እንደማይል በግልጽ አስታወቀ። ሆኖም በቅዱሳን ጽሑፎች እውቀቱ ማንም ሊስተካከለው አልቻለም። ጉባኤው ያሳለፈው ውሳኔ የዎርምስ አዋጅ በተሰኘው ሰነድ አማካኝነት ይፋ ተደረገ። ሰነዱ ሉተርን ሕገ ወጥ በማለት በጽሑፎቹ ላይ እገዳ የሚጥል ነበር። በጳጳሱ የተወገዘውና በንጉሠ ነገሥቱ ሕገ ወጥ የተባለው ሉተር ሕይወቱ አደጋ ላይ ወደቀ።

ከዚያ በኋላ ፈጽሞ ያልተጠበቀና አስገራሚ ሁኔታ ተከሰተ። ሉተር ወደ ዊትንበርግ ለመመለስ ጉዞ ላይ እያለ በደጉ የሳክሶኒ ንጉሥ በፍሬደሪክ በተቀነባበረ የማስመሰል ጠለፋ ተወሰደ። ከዚያ በኋላ ጠላቶቹ ፈጽሞ ሊያገኙት አልቻሉም። ሉተር በድብቅ ከከተማ ወጣ ብሎ ወደሚገኘው ቫርትቡርግ ቤተ መንግሥት የተወሰደ ሲሆን እዚያም ጢሙን አሳድጎና ማንነቱን ቀይሮ ዩንከር ዮርግ በሚል የክብር ስም መኖር ጀመረ።

ከፍተኛ ተወዳጅነትን ያተረፈው የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉሙ

ሉተር በቀጣዮቹ አሥር ዓመታት ከንጉሠ ነገሥቱና ከጳጳሱ ተሸሽጎ በቫርትቡርግ ቤተ መንግሥት ውስጥ ኖረ። ቬልቴረቤ ቫርትቡርግ የተባለው መጽሐፍ እንደገለጸው “ሉተር በቫርትቡርግ ያሳለፈው ጊዜ በሕይወቱ ውስጥ በርካታ ነገሮችን ያከናወነበትና ብዙ የፈጠራ ሥራዎችን የሠራበት ወቅት ነበር።” ሉተር ከሥራዎቹ መካከል ትልቅ ቦታ የሚሰጠውን የኢራስመስን የግሪክኛ ቅዱሳን ጽሑፎች ወደ ጀርመንኛ የመተርጎም ሥራ ያከናወነው በዚያ ነበር። በ1522 በመስከረም ወር ለሕትመት የበቃው ይህ የትርጉም ሥራ የመስከረም መጽሐፍ ቅዱስ ተብሎ የሚጠራ ሲሆን የተተረጎመው በሉተር መሆኑን ግን አይገልጽም። የአንዱ መጽሐፍ ቅዱስ ዋጋ 1 ተኩል ጊልደር የሚያህል ሲሆን ይህም አንዲት የቤት ሠራተኛ በዓመት ከምታገኘው ደሞዝ ጋር እኩል ነበር። ቢሆንም በጣም ከፍተኛ ተፈላጊነት ነበረው። በአንድ ዓመት ውስጥ በሁለት ጊዜ እትም 6,000 የሚያህሉ ቅጂዎች ሲታተሙ በቀጣዮቹ 12 ዓመታት ውስጥ ደግሞ ከ69 ለማያንስ ጊዜ ታትሟል።

በ1525 ማርቲን ሉተር መነኩሲት የነበረች ካታሪና ፎን ቦራ የምትባል ሴት አገባ። ካታሪና በቤት አያያዝ ጎበዝ የነበረች ሲሆን የባሏ ለጋስነት የሚፈጥረውን የሥራ ጫና የመወጣት ብቃት ነበራት። በሉተር ቤት ውስጥ የሚኖሩት እርሱ፣ ሚስቱና ስድስት ልጆቹ ብቻ አልነበሩም። ጓደኞቹ፣ ምሑራንና ስደተኞች በቤቱ እንዲያርፉ ይጋበዙ ነበር። ሉተር ዕድሜው እየገፋ ሲሄድ ምሑራን ስለ ተለያዩ ነገሮች ሊያማክሩት ወደ ቤቱ ይመጡ የነበረ ሲሆን ብዕርና ማስታወሻ ይዘው የሚሰጣቸውን አስተያየቶች ይጽፉ ነበር። እነዚህ ማስታወሻዎች በኋላ ላይ ተሰባስበው ሉተርስ ቲሽራደን (የሉተር የጠረጴዛ ዙሪያ ወግ) በሚል ርዕስ ታትመዋል። ይህ መጽሐፍ በጊዜው በጀርመን ውስጥ ከመጽሐፍ ቅዱስ ቀጥሎ ከፍተኛ ሥርጭት ነበረው።

የተዋጣለት ተርጓሚና ጸሐፊ

ሉተር በ1534 የዕብራይስጥ ቅዱሳን ጽሑፎችን ተርጉሞ አጠናቀቀ። በአጻጻፍ ዘይቤና በቃላት አሰካክ የተካነ ስለነበር ተራው ሕዝብ እንኳን በቀላሉ ሊረዳው የሚችለው የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉም ማዘጋጀት ችሎ ነበር። ሉተር የአተረጓጎም ዘዴውን አስመልክቶ እንዲህ ብሎ ነበር:- “አንዲት የቤት እመቤት፣ በጎዳና ላይ የሚጫወቱ ልጆች ወይም በገበያ ቦታ ያለ ተራ ሰው እንዴት እንደሚናገሩ በጥንቃቄ አዳምጠን በእነርሱ አባባል መተርጎም ይኖርብናል።” የሉተር መጽሐፍ ቅዱስ በመላው ጀርመን ተቀባይነት ያገኘና ደረጃውን የጠበቀ የጽሑፍ ቋንቋ እንዲኖር መሠረት ጥሏል።

ሉተር የተዋጣለት ተርጓሚ ብቻ ሳይሆን ብዕሩ የማይነጥፍ ጸሐፊም ነበር። መጻፍ ከጀመረበት ጊዜ አንስቶ በየሁለት ሳምንቱ አንድ ጽሑፍ ለንባብ ያበቃ ነበር። ከእነዚህ ጽሑፎች መካከል አንዳንዶቹ ልክ እንደደራሲያቸው ኃይለኛ ነበሩ። ሉተር ከመጀመሪያው ብዕሩ የሰላ የነበረ ሲሆን ዕድሜው እየገፋ ሲሄድም የአጻጻፍ ዘይቤው ፈጽሞ አልለዘበም። እንዲያውም በመጨረሻ አካባቢ የጻፋቸው ጽሑፎች ኃይለኛ መልእክት ያዘሉ ነበሩ። ሌክሲከን ፎር ቲኦሎጂ ኡንት ኪርኽ የተባለው መዝገበ ቃላት እንዳስቀመጠው ጽሑፎቹ ሉተር በቤተ ክርስቲያኒቱ ላይ “ከመጠን ያለፈ ቁጣ” እንደነበረውና “ትሕትናና ፍቅር እንደሚጎድለው” እንዲሁም “የተነሳበትን ዓላማ ከግብ የማድረስ ቁርጠኝነት” እንዳለው ያሳያሉ።

የገበሬዎች ዓመፅ ሲቀሰቀስና አካባቢው በደም ሲታጠብ ሉተር ስለ ዓመፁ ያለውን አመለካከት ይኸውም ጭሰኞቹ በፊውዳል ገዥዎቻቸው ላይ ለማመፅ የሚያበቃ በቂ ምክንያት እንዳላቸው ተጠይቆ ነበር። ሉተር ብዙኃኑን የሚያስደስት መልስ በመስጠት የሕዝቡን አድናቆት ማትረፍ አልፈለገም። የአምላክ አገልጋዮች ለባለ ሥልጣናት መታዘዝ አለባቸው ብሎ ያምን ነበር። (ሮሜ 13:1) ሉተር ዓመፁ በኃይል መገታት እንዳለበት ለመናገር አላመነታም። “አቅም ያለው ሁሉ ሰይፍና ጦሩን መዝዞ ይግደል” በማለት ተናግሯል። ይህ መልሱ “በሕዝቡ ዘንድ የነበረውን ልዩ ተወዳጅነት” እንዳሳጣው ሃንስ ሊለዬ ተናግረዋል። ከዚህም በላይ ሉተር ወደ ክርስትና ለመለወጥ ፈቃደኛ ያልነበሩትን አይሁዳውያን አስመልክቶ ወደኋላ አካባቢ የጻፋቸው ጽሑፎች በተለይ ኦን ዘ ጂውስ ኤንድ ዜር ላይስ የተባለው ጽሑፉ በብዙዎች ዘንድ ፀረ ሴማዊ ተብሎ እንዲፈረጅ አድርጎታል።

ሉተር ትቶት ያለፈው ቅርስ

እንደ ሉተር፣ ካልቪንና ዝዊንግሊ ያሉ ሰዎች ያቀጣጠሉት የተሃድሶ እንቅስቃሴ ፕሮቴስታንት የተባለ አዲስ ሃይማኖት ብቅ እንዲል ምክንያት ሆኗል። ሉተር ለፕሮቴስታንት እምነት ያበረከተው ትልቁ አስተዋጽኦ መዳን የሚገኘው በእምነት ነው የሚለው መሠረተ ትምህርት ነው። እያንዳንዱ የጀርመን ግዛት ከፕሮቴስታንት ወይም ከካቶሊክ እምነት ጎን ተሰልፎ ነበር። የፕሮቴስታንት እምነት ወደ ስካንዲኔቪያን አገሮች፣ ስዊዘርላንድ፣ ኢንግላንድና ኔዘርላንድስ ተስፋፍቶ ሰፊ ተቀባይነት አግኝቷል። በዛሬው ጊዜ ይህ እምነት በመቶ ሚሊዮኖች የሚቆጠሩ አባላት አሉት።

ብዙ ሰዎች በሉተር ትምህርቶች ባያምኑም ለእርሱ ትልቅ አድናቆት አላቸው። አይስሌበን፣ ኢርፈርት፣ ዊትንበርግ እና ቫርትቡርግ የተባሉትን ከተሞች በግዛቱ ውስጥ ያቀፈው የቀድሞው የጀርመን ዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ በ1983 የሉተርን 500ኛ የልደት በዓል አክብሮ ነበር። ይህ ሶሻሊስታዊ መንግሥት ሉተር በጀርመን ታሪክና ባሕል ውስጥ ትልቅ ቦታ የሚሰጠው ሰው እንደሆነ አምኖ ተቀብሏል። ከዚህም በላይ በ1980ዎቹ ዓመታት አንድ የካቶሊክ ምሑር ሉተር የነበረውን ተጽዕኖ ጠቅለል አድርገው ሲገልጹ “ከዚያ በኋላ እንደ እርሱ ያለ ሰው አልተነሳም” ብለዋል። ፕሮፌሰር አላንት እንዲህ በማለት ጽፈዋል:- “ማርቲን ሉተርንና ተሃድሶውን አስመልክቶ ቢያንስ 500 የሚያህሉ አዳዲስ ጽሑፎች በየዓመቱ የሚወጡ ሲሆን በአብዛኞቹ የዓለም ታላላቅ ቋንቋዎች ታትመው ይሰራጫሉ።”

ማርቲን ሉተር ንቁ የማስተዋል ችሎታና ልዩ የማስታወስ ተሰጥኦ ያለው፣ በቃላት እውቀቱ ሀብታም የሆነ ትጉህ ሠራተኛ ነበር። እንዲሁም ትዕግሥት የለሽ፣ መተቸትና ማንቋሸሽ የሚቀናው ሰው ነበር። ግብዝነትንም አጥብቆ ይጠላ ነበር። በየካቲት 1546 በአይስሌበን ከተማ የሚሞትበት ጊዜ ተቃርቦ ሳለ ወዳጆቹ ለሌሎች ሲያስተምረው የኖረውን እምነት እስከመጨረሻው ያምንበት እንደነበር ጠየቁት። መልሱ “አዎን” የሚል ነበር። ሉተር በሞት አንቀላፍቷል፤ ብዙዎች ግን አሁንም እነዚህን እምነቶች አጥብቀው ይከተላሉ።

[በገጽ 27 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ሉተር የኃጢአት ስርየት በገንዘብ መሸጡን አጥብቆ ይቃወም ነበር

[ምንጭ]

Mit freundlicher Genehmigung: Wartburg-Stiftung

[በገጽ 28 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ሉተር ተቃዋሚዎቹ መሳሳቱን ከቅዱሳን ጽሑፎች እየጠቀሱ በማስረጃ ካላሳዩት በስተቀር ተሳስቻለሁ እንደማይል ገልጿል

[ምንጭ]

From the book The Story of Liberty, 1878

[በገጽ 29 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ሉተር በቫርትቡርግ ቤተ መንግሥት በነበረበት ወቅት መጽሐፍ ቅዱስን የተረጎመበት ክፍል

[ምንጭ]

ሁለቱም ስዕሎች:- Mit freundlicher Genehmigung: Wartburg-Stiftung

[ምንጭ]

From the book Martin Luther The Reformer, 3rd Edition, published by Toronto Willard Tract Depository, Toronto, Ontario

[ምንጭ]

From the book The History of Protestantism (Vol. I)