በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ሳናቋርጥ መጸለይ ያለብን ለምንድን ነው?

ሳናቋርጥ መጸለይ ያለብን ለምንድን ነው?

ሳናቋርጥ መጸለይ ያለብን ለምንድን ነው?

“ሳታቋርጡ ጸልዩ፤ በሁሉ አመስግኑ።”—1 ተሰሎንቄ 5:17, 18

1, 2. ዳንኤል ለጸሎት መብት አድናቆት እንዳለው ያሳየው እንዴት ነበር? ይህስ ከአምላክ ጋር የነበረውን ዝምድና ያጠናከረለት እንዴት ነው?

 ነቢዩ ዳንኤል በቀን ሦስት ጊዜ ወደ አምላክ የመጸለይ ልማድ ነበረው። በእልፍኙ ውስጥ በኢየሩሳሌም ትይዩ ወዳለው መስኮት ፊቱን አዙሮ ይንበረከክና ይጸልይ ነበር። (1 ነገሥት 8:46-49፤ ዳንኤል 6:10) ወደ ሜዶናዊው ንጉሥ ዳርዮስ ካልሆነ በስተቀር ወደ ማንም ልመና ማቅረብን የሚከለክል የንጉሥ ትእዛዝ በወጣ ጊዜም እንኳ ዳንኤል ወደ አምላኩ ለመጸለይ ቅንጣት ታክል አላመነታም። ይህ የጸሎት ሰው ለሕይወቱ የሚያሰጋው ቢሆንም እንኳ ወደ ይሖዋ መጸለዩን አላቋረጠም።

2 ይሖዋ ለዳንኤል ምን አመለካከት ነበረው? መልአኩ ገብርኤል ጸሎቱ እንደተሰማለት ለዳንኤል ለመንገር በመጣ ጊዜ ነቢዩን “እጅግ የተወደድህ” በማለት ጠርቶታል። (ዳንኤል 9:20-23) ይሖዋ በሕዝቅኤል ትንቢት ውስጥ ዳንኤል ጻድቅ እንደሆነ መስክሮለታል። (ሕዝቅኤል 14:14, 20) ዳንኤል በሕይወት ዘመኑ የጸሎት ልማድ የነበረው መሆኑ ከአምላኩ ጋር የጠበቀ ዝምድና ለመመሥረት እንዳስቻለው ግልጽ ነው። ዳርዮስ እንኳን ይህንን ሐቅ ተገንዝቦ ነበር።—ዳንኤል 6:16

3. ጸሎት ታማኝነታችንን ለመጠበቅ እንደሚረዳን የአንድ ሚስዮናዊ ተሞክሮ የሚያሳየው እንዴት ነው?

3 አዘውትሮ መጸለይ ከባድ ፈተናዎችን ለመቋቋም ያስችለናል። ለምሳሌ ያህል በቻይና ለአምስት ዓመታት ያህል ለብቻው ተገልሎ የታሰረውን ሃሮልድ ኪንግ የተባለ ሚስዮናዊ ተመልከት። ወንድም ኪንግ ተሞክሮውን ሲናገር እንዲህ ብሏል:- “ከሰው ሊያገልሉኝ ይችሉ ይሆናል፤ ከአምላክ ግን ማንም ሊለየኝ አይችልም። . . . በመሆኑም በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የተጠቀሰውን ዳንኤልን በማስታወስ በታሰርኩበት ክፍል አጠገብ የሚያልፉ ሰዎች እያዩኝ በቀን ሦስት ጊዜ በጉልበቴ ተንበርክኬ ከፍ ባለ ድምፅ እጸልይ ነበር። . . . እንዲህ በማደርግበት ጊዜ አእምሮዬ ይበልጥ ጠቃሚ በሆኑ ጉዳዮች ላይ እንዲያተኩር የአምላክ መንፈስ የሚረዳኝ ሲሆን እንድረጋጋም ያደርገኛል። ጸሎት ያስገኘልኝ ማበረታቻና ማጽናኛ ወደር የለውም!”

4. በዚህ ርዕስ ውስጥ ጸሎትን በተመለከተ የትኞቹን ጥያቄዎች እንመረምራለን?

4 መጽሐፍ ቅዱስ “ሳታቋርጡ ጸልዩ፤ በሁሉ አመስግኑ” ይላል። (1 ተሰሎንቄ 5:17, 18) ከዚህ ምክር አኳያ እስቲ የሚከተሉትን ጥያቄዎች እንመርምር:- ለጸሎታችን ይዘት ትኩረት መስጠት ያለብን ለምንድን ነው? ወደ ይሖዋ አዘውትረን እንድንጸልይ የሚገፋፉ ምን ምክንያቶች አሉን? በፈጸምነው ስህተት የተነሳ ወደ አምላክ ለመጸለይ ብቃቱ እንደሌለን በሚሰማን ጊዜስ ምን ማድረግ ይኖርብናል?

በጸሎት አማካኝነት ወዳጅነት መሥርቱ

5. ጸሎት ምን ዓይነት ልዩ ወዳጅነት ለመመሥረት ያስችለናል?

5 ይሖዋ እንደ ወዳጁ አድርጎ ቢመለከትህ ምን ይሰማሃል? ይሖዋ አብርሃም ወዳጁ እንደሆነ ተናግሮለታል። (ኢሳይያስ 41:8፤ ያዕቆብ 2:23) እኛም ከእርሱ ጋር እንዲህ ያለ ወዳጅነት እንድንመሠርት ይፈልጋል። እንዲያውም ወደ እርሱ እንድንቀርብ ጋብዞናል። (ያዕቆብ 4:8) ይህ ግብዣ ልዩ ስለሆነው የጸሎት መብታችን በጥሞና እንድናስብበት ሊያደርገን አይገባም? አንድን ከፍተኛ የመንግሥት ባለ ሥልጣን ወዳጅ ማድረግ ይቅርና ለአንድ ጊዜ እንኳን ቀጠሮ ማስያዝ ምን ያህል አስቸጋሪ እንደሆነ እናውቃለን። ሆኖም የአጽናፈ ዓለሙ ፈጣሪ በፈለግነው ጊዜ በጸሎት ወደ እርሱ በነጻነት እንድንቀርብ ያበረታታናል። (መዝሙር 37:5) ሳናቋርጥ መጸለያችን ከይሖዋ ጋር የጠበቀ ወዳጅነት ለመመሥረት ያስችለናል።

6. ‘ተግቶ በመጸለይ’ ረገድ ከኢየሱስ ምን እንማራለን?

6 ይሁን እንጂ የጸሎት ልማዳችንን በቀላሉ ልንዘነጋው እንችላለን። የየዕለቱ የኑሮ ውጣ ውረድ በራሱ ትኩረታችንን ስለሚበታትንብን አዘውትረን ወደ አምላክ መጸለይ እናቆም ይሆናል። ኢየሱስ ደቀ መዛሙርቱን “ትጉና ጸልዩ” በማለት አበረታቷቸዋል። እርሱም ራሱ ያለማቋረጥ ይጸልይ ነበር። (ማቴዎስ 26:41) ከጠዋት እስከ ማታ በተለያዩ እንቅስቃሴዎች ተጠምዶ የሚውል ቢሆንም በሰማይ ከሚኖረው አባቱ ጋር የሚነጋገርበት ጊዜ መድቦ ነበር። አንዳንድ ጊዜ ‘ማለዳ ተነሥቶ ገና ሌሊት ሳለ’ ለመጸለይ ይወጣ ነበር። (ማርቆስ 1:35) በሌሎች ጊዜያት ደግሞ አመሻሹ ላይ ብቻውን ጭር ወዳለ አካባቢ ሄዶ ወደ ይሖዋ ይጸልይ ነበር። (ማቴዎስ 14:23) ኢየሱስ ሁልጊዜ ለጸሎት ጊዜ ይመድብ ነበር፤ እኛም እንዲሁ ማድረግ ይገባናል።—1 ጴጥሮስ 2:21

7. በሰማይ ወዳለው አባታችን በየዕለቱ እንድንጸልይ የሚገፋፉን ሁኔታዎች የትኞቹ ናቸው?

7 በየዕለቱ ችግሮች ሲያጋጥሙን፣ ፈተና ሲደርስብን እንዲሁም ውሳኔ ማድረግ ሲያስፈልገን በግል ወደ ይሖዋ መጸለይ እንችላለን። (ኤፌሶን 6:18) በሁሉም የሕይወት ዘርፎች የአምላክን መመሪያ ለማግኘት ጥረት የምናደርግ ከሆነ ከእርሱ ጋር ያለን ወዳጅነት እንደሚጠናከር የታወቀ ነው። ሁለት ጓደኛሞች የሚያጋጥሟቸውን ችግሮች በጋራ የሚጋፈጡ ከሆነ በመካከላቸው ያለው ወዳጅነት ይበልጥ ይጠናከራል። (ምሳሌ 17:17) እኛም ይሖዋ እንዲረዳን ጠይቀነው እንደረዳን ሲሰማን ከእርሱ ጋር ያለን ወዳጅነት ይበልጥ ይጠናከራል።—2 ዜና መዋዕል 14:11

8. በግል የምናቀርበውን ጸሎት በተመለከተ ከነህምያ፣ ከኢየሱስና ከሐና ምን እንማራለን?

8 አምላክ ወደ እርሱ የምናቀርበውን ጸሎት ርዝመትና ብዛት አለመገደቡን ማወቃችን በጣም የሚያስደስት ነው። ነህምያ ለፋርስ ንጉሥ ልመናውን ከማቅረቡ በፊት በልቡ አጭር ጸሎት አቅርቦ ነበር። (ነህምያ 2:4, 5) ኢየሱስ አልዓዛርን ከሞት ለማስነሳት ኃይል እንዲሰጠው ይሖዋን ሲጠይቅ ያቀረበው ጸሎት አጭር ነበር። (ዮሐንስ 11:41, 42) በሌላ በኩል ግን ሐና የልቧን አውጥታ ለይሖዋ በተናገረች ጊዜ ያቀረበችው ጸሎት ረዥም ነበር። (1 ሳሙኤል 1:12, 15, 16) እኛም በግል የምናቀርበው ጸሎት እንደሚያስፈልገን ነገርና እንደ ሁኔታው አጭር ወይም ረዥም ሊሆን ይችላል።

9. ይሖዋ ላደረገልን ነገር በጸሎት ልናወድሰውና ልናመሰግነው የሚገባን ለምንድን ነው?

9 በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ተመዝግበው የሚገኙት አብዛኞቹ ጸሎቶች የይሖዋን የበላይነትና ያከናወናቸውን ድንቅ ሥራዎች የሚገልጹ ናቸው። (ዘጸአት 15:1-19፤ 1 ዜና መዋዕል 16:7-36፤ መዝሙር 145) ሐዋርያው ዮሐንስ በሰማይ ቦታቸውን የያዙ ቅቡዓን ክርስቲያኖችን የሚወክሉት 24ቱ ሽማግሌዎች “ጌታችንና አምላካችን ሆይ፣ አንተ ሁሉን ፈጥረሃልና ስለ ፈቃድህም ሆነዋልና ተፈጥረውማልና ክብር ውዳሴ ኃይልም ልትቀበል ይገባሃል” እያሉ ይሖዋን ሲያወድሱ በራእይ ተመልክቷል። (ራእይ 4:10, 11) እኛም ፈጣሪን ዘወትር እንድናወድስ የሚያደርጉን በቂ ምክንያቶች አሉን። ወላጆች ልጃቸው ስላደረጉለት ነገር ከልቡ ሲያመሰግናቸው በጣም ይደሰታሉ። ይሖዋ ስላደረገልን ደግነት በአድናቆት ማሰላሰላችንና ልባዊ ምስጋናችንን መግለጻችን የጸሎታችንን ይዘት ማሻሻል የምንችልበት አንዱ ግሩም መንገድ ነው።

‘ሳናቋርጥ መጸለይ’ ያለብን ለምንድን ነው?

10. ጸሎት እምነታችንን በማጠናከር ረገድ ምን ሚና ይጫወታል?

10 አዘውትረን መጸለያችን ለእምነታችን በጣም አስፈላጊ ነው። ኢየሱስ ‘ሳይታክቱ ዘወትር የመጸለይን’ አስፈላጊነት በምሳሌ ካስረዳ በኋላ “የሰው ልጅ በመጣ ጊዜ በምድር እምነትን ያገኝ ይሆንን?” የሚል ጥያቄ አነሳ። (ሉቃስ 18:1-8) ከልብ የመነጨ ጸሎት እምነት ያጠነክራል። አብርሃም ዕድሜው እየገፋ ሲሄድ ልጅ አለመውለዱ ስላሳሰበው ጉዳዩን በጸሎት ለይሖዋ ነገረው። ይሖዋም ለጸሎቱ ምላሽ ሲሰጠው የሰማይን ከዋክብት እንዲመለከት ከቻለም እንዲቆጥራቸው ጠየቀው። ከዚያም “ዘርህም እንደዚሁ ይሆናል” በማለት አረጋገጠለት። ውጤቱስ ምን ነበር? አብርሃም “በእግዚአብሔር አመነ፣ ጽድቅም ሆኖ ተቈጠረለት።” (ዘፍጥረት 15:5, 6) እኛም ለይሖዋ የልባችንን በጸሎት ከነገርነው፣ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ በሰጣቸው ተስፋዎች ላይ እምነት ካሳደርን እንዲሁም ትእዛዛቱን ከጠበቅን እርሱ እምነታችንን ያጎለብትልናል።

11. ጸሎት ችግሮችን እንድናሸንፍ የሚረዳን እንዴት ነው?

11 ጸሎት ችግሮቻችንንም ለመፍታት ሊረዳን ይችላል። የዕለት ተዕለት ሕይወታችን ከብዶብን ወይም በየጊዜው የሚያጋጥሙን ችግሮች ከአቅም በላይ ሆነውብን ይሆን? መጽሐፍ ቅዱስ “ትካዜህን በእግዚአብሔር ላይ ጣል፣ እርሱም ይደግፍሃል፤ ለጻድቁም ለዘላለም ሁከትን አይሰጠውም” በማለት ያበረታታናል። (መዝሙር 55:22) ውሳኔ ማድረግ የሚጠይቅ ከባድ ጉዳይ ሲያጋጥመን የኢየሱስን ምሳሌ መኮረጅ እንችላለን። ኢየሱስ 12ቱን ሐዋርያት ከመሾሙ በፊት አንድ ሌሊት ሙሉ ሲጸልይ አድሯል። (ሉቃስ 6:12-16) እንዲሁም በሞቱ ዋዜማ “ወዙም በምድር ላይ እንደሚወርድ እንደ ደም ነጠብጣብ” እስኪፈስ ድረስ አጥብቆ ጸልዮአል። (ሉቃስ 22:44) ውጤቱስ ምን ነበር? ‘እግዚአብሔርንም ይፈራ ስለነበር ጸሎቱ ተሰማለት።’ (ዕብራውያን 5:7) አዘውትረን ከልብ የምንጸልይ ከሆነ ውጥረት የሚያስከትሉ ሁኔታዎችንና ከባድ ፈተናዎችን መቋቋም እንችላለን።

12. የጸሎት መብት ይሖዋ በግል እንደሚያስብልን የሚያሳየው እንዴት ነው?

12 በጸሎት ወደ ይሖዋ የምንቀርብበት ሌላው ምክንያት ደግሞ እርሱም ወደ እኛ ስለሚቀርብ ነው። (ያዕቆብ 4:8) ለይሖዋ የልባችንን ገልጠን ስንነግረው ችግራችንን እንደሚረዳልንና ከልብ እንደሚያስብልን ሆኖ አይሰማንም? በግለሰብ ደረጃ እንደሚወደን ይሰማናል። ይሖዋ አገልጋዮቹ የሚያቀርቡትን ጸሎት የማዳመጡን ኃላፊነት ለሌላ ለማንም አካል አልሰጠም። (መዝሙር 66:19, 20፤ ሉቃስ 11:2) እንዲሁም ‘ስለ እኛ ስለሚያስብ የሚያስጨንቀንን ሁሉ በእርሱ ላይ እንድንጥል’ ግብዣ አቅርቦልናል።—1 ጴጥሮስ 5:6, 7

13, 14. ሳናቋርጥ መጸለይ ያለብን ለምንድን ነው?

13 ጸሎት ለመስክ አገልግሎት ከፍተኛ ቅንዓት እንዲያድርብን ከማድረጉም በላይ በሰዎች ግዴለሽነት ወይም ተቃውሞ የተነሳ አገልግሎታችንን የማቋረጥ መንፈስ ሲያድርብን ያበረታታናል። (ሥራ 4:23-31) በተጨማሪም ጸሎት “የዲያብሎስን ሽንገላ” እንድንቃወም ሊረዳን ይችላል። (ኤፌሶን 6:11, 17, 18) በየዕለቱ የሚያጋጥሙንን ፈተናዎች ለመቋቋም በምናደርገው ትግል ብርታት እንዲሰጠን ምንጊዜም ወደ አምላክ መጸለይ እንችላለን። ኢየሱስ ያስተማረው የናሙና ጸሎት ይሖዋ ‘ከክፉው [ከሰይጣን ዲያብሎስ] እንዲያድነን’ መለመንን ይጨምራል።—ማቴዎስ 6:13

14 በውስጣችን ያለውን የኃጢአት ዝንባሌ ለመቆጣጠር እንድንችል አዘውትረን የምንጸልይ ከሆነ ይሖዋ ይረዳናል። “ከሚቻላችሁ መጠን ይልቅ ትፈተኑ ዘንድ የማይፈቅድ እግዚአብሔር የታመነ ነው፣ ትታገሡም ዘንድ እንድትችሉ ከፈተናው ጋር መውጫውን ደግሞ ያደርግላችኋል” የሚል ማረጋገጫ ተሰጥቶናል። (1 ቆሮንቶስ 10:13) ሐዋርያው ጳውሎስም በተለያዩ አጋጣሚዎች የይሖዋን ማበረታቻ አግኝቷል። “ኃይልን በሚሰጠኝ በእርሱ ሁሉን ማድረግ እችላለሁ” በማለት ተናግሯል።—ፊልጵስዩስ 4:13፤ 2 ቆሮንቶስ 11:23-29

ድክመቶች ቢኖሩብንም በጸሎት እንጽና

15. አንዳንዶች አምላክ ያወጣቸውን የሥነ ምግባር መሥፈርቶች ሳይጠብቁ ሲቀሩ የሚወስዱት የተሳሳተ እርምጃ ምንድን ነው?

15 ይሖዋ ጸሎቶቻችንን እንዲሰማልን ከፈለግን በአምላክ ቃል ውስጥ የሚገኘውን ምክር ችላ ማለት አይኖርብንም። ሐዋርያው ዮሐንስ “ትእዛዙንም የምንጠብቅና በፊቱ ደስ የሚያሰኘውን የምናደርግ ስለ ሆንን የምንለምነውን ሁሉ ከእርሱ እናገኛለን” ሲል ጽፏል። (1 ዮሐንስ 3:22) ይሁን እንጂ አምላክ ያወጣቸውን የሥነ ምግባር መሥፈርቶች ሳንጠብቅ ብንቀርስ? አዳምና ሔዋን በኤድን ገነት ኃጢአት ከሠሩ በኋላ ተሸሽገው ነበር። እኛም “ከአምላክ ፊት” ለመሸሸግና መጸለያችንን ለማቆም እንፈልግ ይሆናል። (ዘፍጥረት 3:8) አንድ የረጅም ዓመታት ተሞክሮ ያካበተ ክላውስ የተባለ ተጓዥ የበላይ ተመልካች እንዲህ ብሏል:- “አብዛኛውን ጊዜ ለማለት ይቻላል ከይሖዋና ከድርጅቱ የራቁ ሰዎች የሚወስዱት የመጀመሪያው የተሳሳተ እርምጃ ጸሎት ማቆም እንደሆነ አስተውያለሁ።” (ዕብራውያን 2:1) የሆሴ አንከል ሁኔታ ከዚህ ጋር ይመሳሰላል። እንዲህ ይላል:- “ለስምንት ዓመታት ያህል አልፎ አልፎ ካልሆነ በስተቀር ወደ ይሖዋ ጸልዬ አላውቅም ነበር። እንደ አባቴ አድርጌ እመለከተው የነበረ ቢሆንም ከእርሱ ጋር ለመነጋገር እንደማልበቃ ይሰማኝ ነበር።”

16, 17. አዘውትሮ መጸለይ መንፈሳዊ ድክመትን ለማሸነፍ እንደሚረዳን የሚያሳዩ ምሳሌዎችን ጥቀስ።

16 አንዳንዶቻችን በመንፈሳዊ ስንደክም ወይም ኃጢአት ስንፈጽም ወደ ይሖዋ ለመጸለይ እንደማንበቃ ይሰማናል። ይሁን እንጂ በጸሎት መብት በሚገባ መጠቀም ያለብን በዚህ ጊዜ ነው። ነቢዩ ዮናስ የተሰጠውን ተልእኮ ማከናወን ስላልፈለገ ኮብልሎ ነበር። ሆኖም ‘በመከራ ሳለ ወደ አምላኩ ወደ ይሖዋ ጮኸ፤ እርሱም ሰማው። በሲኦል ሆድ ውስጥ ሆኖ ጮኸ፤ ይሖዋም ቃሉን ሰማው።’ (ዮናስ 2:3) ዮናስ ወደ ይሖዋ ጸለየ፤ ይሖዋም ጸሎቱን ሰማው፤ ከዚያም በመንፈሳዊ ለማገገም ቻለ።

17 ሆሴ አንከልም እርዳታ ለማግኘት ከልቡ ጸልዮ ነበር። እንዲህ ይላል:- “የልቤን አውጥቼ ለይሖዋ በመንገር ይቅር እንዲለኝ ለመንሁት። እርሱም ረዳኝ። ባልጸልይ ኖሮ ወደ እውነት እመለሳለሁ ብዬ አላስብም ነበር። አሁን በየዕለቱ ወደ ይሖዋ የምጸልይ ሲሆን የምጸልይበት ሰዓት እስኪደርስ ድረስ እጓጓለሁ።” ምንጊዜም ስህተቶቻችንን ሳንደብቅ ለአምላክ በመንገር ይቅር እንዲለን በትሕትና ለመጠየቅ ነጻነት ሊሰማን ይገባል። ንጉሥ ዳዊት ኃጢአቱን በተናዘዘ ጊዜ ይሖዋ ይቅር ብሎታል። (መዝሙር 32:3-5) ይሖዋ እኛን ለመኮነን ሳይሆን ለመርዳት ይፈልጋል። (1 ዮሐንስ 3:19, 20) እንዲሁም በጉባኤ ውስጥ ያሉ ሽማግሌዎች የሚያቀርቡት ጸሎት “እጅግ ኃይል” ስላለው በመንፈሳዊ እንድንበረታ ሊረዳን ይችላል።—ያዕቆብ 5:13-16

18. የአምላክ አገልጋዮች የቱንም ያህል ከይሖዋ ቢርቁ ምን ትምክህት ሊኖራቸው ይችላል?

18 ስህተት የሠራው ልጁ ለእርዳታና ለምክር ወደ እርሱ ሲመጣ ይቅርታ ለማድረግ ፈቃደኛ የማይሆን አባት ይኖራል? ስለ ኮብላዩ ልጅ የሚናገረው ምሳሌ የቱንም ያህል በመንፈሳዊ ብንባዝን ተጸጽተን ስንመለስ በሰማይ የሚኖረው አባታችን እንደሚደሰት ያሳያል። (ሉቃስ 15:21, 22, 32) ይሖዋ ‘ይቅርታው ብዙ ስለሆነ’ በመንፈሳዊ የባዘኑት ሁሉ ወደ እርሱ እንዲመለሱ ያበረታታል። (ኢሳይያስ 55:6, 7) ዳዊት ከባድ ኃጢአቶችን በተደጋጋሚ ቢፈጽምም “አቤቱ፣ ጸሎቴን አድምጥ፣ ልመናዬንም ቸል አትበል” በማለት ወደ ይሖዋ ጸልዮ ነበር። በተጨማሪም “በማታና በጥዋት በቀትርም እናገራለሁ እጮኽማለሁ፣ ቃሌንም ይሰማኛል” ብሏል። (መዝሙር 55:1, 17) ይህ ምንኛ የሚያጽናና ነው!

19. ጸሎታችን መልስ እንዳላገኘ ሆኖ በሚሰማን ጊዜ የይሖዋን ሞገስ እንዳጣን አድርገን መደምደም የሌለብን ለምንድን ነው?

19 ጸሎታችን ፈጣን ምላሽ ባያገኝስ? ልመናችንን በኢየሱስ ስም ማቅረባችንንና ከይሖዋ ፈቃድ ጋር የሚስማማ መሆኑን ማረጋገጥ አለብን። (ዮሐንስ 16:23፤ 1 ዮሐንስ 5:14) ደቀ መዝሙሩ ያዕቆብ አንዳንድ ክርስቲያኖች ‘በክፉ በመለመናቸው’ ጸሎታቸው እንዳልተሰማላቸው ተናግሯል። (ያዕቆብ 4:3) በሌላ በኩል ግን ጸሎታችን መልስ እንዳላገኘ ሆኖ በሚሰማን ጊዜ የይሖዋን ሞገስ እንዳጣን አድርገን ለመደምደም መቸኮል አይኖርብንም። ይሖዋ አንዳንድ ጊዜ ታማኝ አምላኪዎቹ ለሚያቀርቡት ጸሎት መልስ ከመስጠቱ በፊት በጉዳዩ ላይ በተደጋጋሚ እንዲጸልዩበት ይፈልግ ይሆናል። ኢየሱስ “ለምኑ፣ ይሰጣችሁማል” በማለት ተናግሯል። (ማቴዎስ 7:7) ስለሆነም ‘በጸሎት መጽናት’ ይኖርብናል።—ሮሜ 12:12

አዘውትራችሁ ጸልዩ

20, 21. (ሀ) በእነዚህ ‘የመጨረሻ ቀናት’ ሳናቋርጥ መጸለያችን አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው? (ለ) በየዕለቱ ወደ ይሖዋ የጸጋ ዙፋን የምንቀርብ ከሆነ ምን እናገኛለን?

20 ‘አስጨናቂ ዘመን’ ተብሎ በተገለጸው በዚህ ‘የመጨረሻ ቀን’ ውስጥ የሚያጋጥሙን ችግሮችና ተጽዕኖዎች ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመሩ ሄደዋል። (2 ጢሞቴዎስ 3:1) እንዲሁም በየጊዜው የሚያጋጥሙን ፈተናዎች አእምሯችንን በቀላሉ ሊያስጨንቁት ይችላሉ። ይሁን እንጂ ሳናቋርጥ መጸለያችን ችግሮች፣ ፈተናዎችና ተስፋ የሚያስቆርጡ ሁኔታዎች እየተባባሱ ቢሄዱም ሕይወታችን በመንፈሳዊ ነገሮች ላይ እንዲያተኩር ሊረዳን ይችላል። በየዕለቱ ለይሖዋ የምናቀርበው ጸሎት አስፈላጊውን እርዳታ ያስገኝልናል።

21 ‘ጸሎት ሰሚ’ የሆነው አምላካችን ይሖዋ እኛን ለማዳመጥ ፈጽሞ ጊዜ አያጣም። (መዝሙር 65:2) እኛም ምንም ያህል በሥራ ብንወጠር ለጸሎት ፈጽሞ ጊዜ ልናጣ አይገባም። ካለን ሀብት ሁሉ የሚበልጠው ከይሖዋ ጋር የመሠረትነው ወዳጅነት ነው። በመሆኑም ፈጽሞ አቅልለን ልንመለከተው አይገባም። “እንግዲህ ምሕረትን እንድንቀበል በሚያስፈልገንም ጊዜ የሚረዳንን ጸጋ እንድናገኝ ወደ ጸጋው ዙፋን በእምነት እንቅረብ።”—ዕብራውያን 4:16

ምን ብለህ ትመልሳለህ?

• የጸሎትን አስፈላጊነት በተመለከተ ከነቢዩ ዳንኤል ምን እንማራለን?

• ከይሖዋ ጋር ያለንን ወዳጅነት ማጠናከር የምንችለው እንዴት ነው?

• ሳናቋርጥ መጸለይ ያለብን ለምንድን ነው?

• ወደ ይሖዋ ለመጸለይ ብቃት እንደሌለን ሊሰማን የማይገባው ለምንድን ነው?

[የአንቀጾቹ ጥያቄዎች]

[በገጽ 16 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ነህምያ ንጉሡን ከመለመኑ በፊት በልቡ አጭር ጸሎት አቅርቦ ነበር

[በገጽ 17 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ሐና ‘ጸሎቷን በይሖዋ ፊት አብዝታ ነበር’

[በገጽ 18 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ኢየሱስ 12ቱን ሐዋርያት ከመሾሙ በፊት አንድ ሌሊት ሙሉ ሲጸልይ አድሯል

[በገጽ 20 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

በየዕለቱ ወደ ይሖዋ ልንጸልይ የምንችልባቸው በርካታ አጋጣሚዎች አሉ