በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ስለ መንፈሳዊ ነገሮች መወያየት ያንጻል

ስለ መንፈሳዊ ነገሮች መወያየት ያንጻል

ስለ መንፈሳዊ ነገሮች መወያየት ያንጻል

“ለሚሰሙት ጸጋን ይሰጥ ዘንድ፣ እንደሚያስፈልግ ለማነጽ የሚጠቅም ማናቸውም በጎ ቃል እንጂ ክፉ ቃል ከአፋችሁ ከቶ አይውጣ።”—ኤፌሶን 4:29

1, 2. (ሀ) የመናገር ችሎታ ውድ ስጦታ ነው የምንለው ለምንድን ነው? (ለ) የይሖዋ አገልጋዮች አንደበታቸውን መጠቀም የሚኖርባቸው እንዴት ነው?

 “የመናገር ችሎታ ለሰው ልጅ ምስጢር ነው፤ መለኮታዊ ስጦታ እንዲሁም ተአምር ነው።” እንዲህ በማለት የጻፉት የመዝገበ ቃላት አዘጋጅ የሆኑት ሉትቪክ ከእለር ናቸው። ከአምላክ ያገኘነው ይህ የመናገር ችሎታ ምን ያህል ውድ ስጦታ እንደሆነ ያን ያህል አስበንበት አናውቅ ይሆናል። (ያዕቆብ 1:17) ሆኖም አንድ የምንወደው ሰው በድንገተኛ ሕመም የተነሳ መናገር ቢሳነው ምን ያህል ትልቅ ነገር እንደምናጣ አስበው። ጆአን የተባለች አንዲት ሴት በቅርቡ ባለቤቷ በአንጎሉ ውስጥ ደም በመፍሰሱ ምክንያት የመናገር ችሎታውን ባጣበት ወቅት የተሰማትን ስትናገር እንዲህ ትላለች:- “ጥሩ የሐሳብ ግንኙነት ስለነበረን በጣም እንቀራረብ ነበር። እንደቀድሞው የልባችንን አውጥተን ማውራት አለመቻላችን ብዙ ነገር እንደቀረብኝ እንዲሰማኝ አድርጎኛል።”

2 ከሌሎች ጋር የምናደርገው ጭውውት ወዳጅነትን ያጠናክራል፣ አለመግባባትን ለመፍታት ያስችላል፣ ያዘኑትን ያጽናናል፣ እምነት ያጠነክራል እንዲሁም ሕይወትን አስደሳች ያደርጋል። ሁሉም ዓይነት ጭውውት እንዲህ ያለ ውጤት ያስገኛል ማለት ግን አይደለም። ጠቢቡ ንጉሥ ሰሎሞን “እንደሚዋጋ ሰይፍ የሚለፈልፍ ሰው አለ፤ የጠቢባን ምላስ ግን ጤና ነው” በማለት ተናግሮ ነበር። (ምሳሌ 12:18) የይሖዋ አገልጋዮች እንደመሆናችን መጠን የምንናገራቸው ቃላት ሌሎችን የሚጎዱ ወይም የሚያቆስሉ ሳይሆን የሚፈውሱና የሚያንጹ እንዲሆኑ እንፈልጋለን። እንዲሁም በአገልግሎታችንም ሆነ ከሌሎች ጋር በምንጫወትበት ጊዜ አንደበታችንን ይሖዋን ለማወደስ ልንጠቀምበት እንሻለን። መዝሙራዊው “ሁልጊዜ በእግዚአብሔር እንከብራለን፣ ስምህንም ለዘላለም እናመሰግናለን” ሲል ዘምሯል።—መዝሙር 44:8

3, 4. (ሀ) ከአንደበት አጠቃቀም ጋር በተያያዘ ሁላችንም ምን ችግር አለብን? (ለ) ስለምንናገረው ነገር ጠንቃቆች መሆን ያለብን ለምንድን ነው?

3 ደቀ መዝሙሩ ያዕቆብ “አንደበትን ሊገራ ማንም ሰው አይችልም” በማለት ተናግሯል። እንዲሁም “ሁላችን በብዙ ነገር እንሰናከላለንና፤ በቃል የማይሰናከል ማንም ቢኖር እርሱ ሥጋውን ሁሉ ደግሞ ሊገታ የሚችል ፍጹም ሰው ነው” ሲል ያሳስበናል። (ያዕቆብ 3:2, 8) ማናችንም ብንሆን ፍጹማን አይደለንም። በመሆኑም በንግግራችን ሌሎችን ለማነጽ ወይም ፈጣሪያችንን ለማወደስ ብንፈልግም እንኳን ሁልጊዜ ላይሳካልን ይችላል። ስለሆነም ስለምንናገረው ነገር ጠንቃቆች መሆን ይኖርብናል። ከዚህም በላይ ኢየሱስ “ሰዎች ስለሚናገሩት ስለ ከንቱ ነገር ሁሉ በፍርድ ቀን መልስ ይሰጡበታል፤ ከቃልህ የተነሣ ትጸድቃለህና ከቃልህም የተነሣ ትኰነናለህ” ብሏል። (ማቴዎስ 12:36, 37) አዎን፣ አንደበታችንን የምንጠቀምበት መንገድ በእውነተኛው አምላክ ፊት ያስጠይቀናል።

4 ጎጂ አነጋገርን ማስወገድ የሚቻልበት ከሁሉ የተሻለው መንገድ መንፈሳዊ ነገሮችን አንስቶ የመወያየትን ልማድ ማዳበር ነው። በዚህ ርዕስ ውስጥ ይህን እንዴት ማድረግ እንደምንችል፣ ስለ የትኞቹ መንፈሳዊ ጉዳዮች መነጋገር እንደምንችል እንዲሁም የሚያንጽ ውይይት በማድረጋችን ምን ጥቅም እንደምናገኝ ይብራራል።

ምሳሌያዊ ልባችንን የሞላው ምንድን ነው?

5. ጭውውታችን የሚያንጽ እንዲሆን በማድረግ ረገድ ልባችን ምን ወሳኝ ሚና ይጫወታል?

5 የሚያንጹ ውይይቶችን የማድረግ ልማድን ለማዳበር በመጀመሪያ ደረጃ በአፋችን የምንናገረው በልባችን ያለውን መሆኑን መገንዘብ ይኖርብናል። ኢየሱስ “በልብ ሞልቶ ከተረፈው አፍ ይናገራል” ብሏል። (ማቴዎስ 12:34) በመሠረቱ ብዙውን ጊዜ የምንናገረው ትኩረታችንን ስለሳበው ጉዳይ ነው። እንግዲያው ራሳችንን እንዲህ እያልን መጠየቅ ይኖርብናል:- ‘የምናገረው ነገር ስለ ልቤ ሁኔታ ምን ይገልጣል? ከቤተሰቤ ወይም ከሌሎች ክርስቲያኖች ጋር ስሆን የማወራው ስለ መንፈሳዊ ነገሮች ነው? ወይስ ስለ ስፖርት፣ ስለ ልብስ፣ ስለ ፊልም፣ ስለ ምግብ፣ በቅርብ ስለገዛኋቸው ዕቃዎች ወይም ፍሬከርስኪ ስለሆኑ ነገሮች?’ ምናልባት አኗኗራችንም ሆነ አስተሳሰባችን ቅድሚያ ልንሰጣቸው በማይገቡ ነገሮች ላይ አተኩሮ ይሆናል። ቅድሚያ በምንሰጣቸው ነገሮች ላይ ማስተካከያ ማድረጋችን ጭውውታችን በመንፈሳዊ ነገሮች ላይ እንዲያተኩር ከመርዳቱም በላይ የተሻለ ሕይወት እንድንመራ ያስችለናል።—ፊልጵስዩስ 1:9, 10

6. ማሰላሰል ጭውውታችን በመንፈሳዊ ጉዳዮች ላይ ያተኮረ እንዲሆን የሚረዳን እንዴት ነው?

6 የጭውውታችንን ይዘት ማሻሻል የምንችልበት ሌላው መንገድ የታሰበበት ማሰላሰል ማድረግ ነው። ስለ መንፈሳዊ ነገሮች ለማሰብ ከልብ ጥረት ካደረግን ከሌሎች ጋር በምንሆንበት ጊዜ መንፈሳዊ ጉዳዮችን አንስቶ መወያየት ይቀናናል። ይህን የተገነዘበው ንጉሥ ዳዊት “አቤቱ፣ . . . የአፌ ቃልና የልቤ አሳብ በፊትህ ያማረ ይሁን” በማለት ተቀኝቷል። (መዝሙር 19:14) መዝሙራዊው አሳፍ ደግሞ “ሥራህን ሁሉ አሰላስላለሁ፤ ድንቅ ሥራህን ሁሉ አውጠነጥናለሁ” ብሏል። (መዝሙር 77:12 አ.መ.ት) ልባችንና አእምሯችን በአምላክ ቃል ውስጥ በሚገኘው እውነት ላይ የሚያሰላስል ከሆነ ከአንደበታችን የሚወጣው ሌሎችን የሚያንጽ መሆኑ አይቀርም። ኤርምያስ ከይሖዋ ስለተማራቸው ነገሮች ላለመናገር ቢወስንም እንኳን ዝም ማለት አልቻለም። (ኤርምያስ 20:9) እኛም ዘወትር በመንፈሳዊ ጉዳዮች ላይ የምናሰላስል ከሆነ ስለ መንፈሳዊ ነገሮች መወያየት ቀላል ይሆንልናል።—1 ጢሞቴዎስ 4:15

7, 8. የሚያንጽ ጭውውት ለማድረግ የሚያስችሉን የትኞቹ ርዕሰ ጉዳዮች ናቸው?

7 ጥሩ መንፈሳዊ ልማድ ማዳበር የሚያንጹ ጭውውቶች ለማድረግ የሚያስችሉ በርካታ ርዕሰ ጉዳዮች ያስገኝልናል። (ፊልጵስዩስ 3:16) ከጉባኤና ከትልልቅ ስብሰባዎች፣ ከወቅታዊ ጽሑፎች እንዲሁም ከዕለት ጥቅስና አብሮት ከቀረበው ሐሳብ ላይ ለሌሎች የምናካፍላቸው መንፈሳዊ ሀብቶች እናገኛለን። (ማቴዎስ 13:52) በክርስቲያናዊ አገልግሎት ስንካፈል የምናገኛቸው ተሞክሮዎች ደግሞ በመንፈሳዊ የሚያነቃቁ ናቸው።

8 ንጉሥ ሰሎሞን በእስራኤል ባያቸው የተለያዩ ዓይነት ዛፎች፣ እንስሳት፣ አእዋፋትና ዓሣዎች በእጅጉ ተደንቆ ነበር። (1 ነገሥት 4:33) ስለ አምላክ የፍጥረት ሥራዎች ማውራት ያስደስተው ነበር። እኛም እንዲሁ ማድረግ እንችላለን። የይሖዋ አገልጋዮች ስለተለያዩ ነገሮች መወያየት ቢያስደስታቸውም መንፈሳዊ ዝንባሌ ያላቸው ሰዎች እንደመሆናቸው መጠን ይበልጥ ማውራት የሚፈልጉት ስለ መንፈሳዊ ጉዳዮች ነው።—1 ቆሮንቶስ 2:13

“እነዚህን አስቡ”

9. ጳውሎስ በፊልጵስዩስ ጉባኤ ለሚገኙ ክርስቲያኖች ምን ማሳሰቢያ ሰጥቷቸዋል?

9 የምንነጋገርበት ርዕሰ ጉዳይ ምንም ይሁን ምን ሌሎችን ማነጽ የምንችለው ሐዋርያው ጳውሎስ በፊልጵስዩስ ጉባኤ ውስጥ ለሚገኙ ክርስቲያኖች የሰጠውን ማሳሰቢያ ተግባራዊ የምናደርግ ከሆነ ነው። ጳውሎስ እንዲህ ሲል ጽፏል:- “ወንድሞች ሆይ፣ እውነተኛ የሆነውን ነገር ሁሉ፣ ጭምትነት ያለበትን ነገር ሁሉ፣ ጽድቅ የሆነውን ነገር ሁሉ፣ ንጹሕ የሆነውን ነገር ሁሉ፣ ፍቅር ያለበትን ነገር ሁሉ፣ መልካም ወሬ ያለበትን ነገር ሁሉ፣ በጎነት ቢሆን ምስጋናም ቢሆን፣ እነዚህን አስቡ።” (ፊልጵስዩስ 4:8) ጳውሎስ የዘረዘራቸው ጉዳዮች በጣም አስፈላጊ በመሆናቸው ‘እነዚህን አስቡ’ ብሏል። ልባችንንና አእምሯችንን በእነዚህ ነገሮች መሙላት ይገባናል። ጳውሎስ ለጠቀሳቸው ለእነዚህ ስምንት ነጥቦች ትኩረት መስጠታችን ውይይታችንን እንዴት የሚያንጽ እንደሚያደርገው እስቲ እንመልከት።

10. ጭውውታችን እውነተኛ በሆኑ ነገሮች ላይ እንዲያተኩር ማድረግ የምንችለው እንዴት ነው?

10 አንድ ወሬ እውነተኛ የሚባለው ትክክል ስለሆነ ወይም ውሸት ስላልሆነ ብቻ አይደለም። በአምላክ ቃል ውስጥ እንደሚገኘው እውነት ትክክለኛና እምነት የሚጣልበት መሆን ይኖርበታል። በመሆኑም ልባችንን ስለነካው የመጽሐፍ ቅዱስ እውነት፣ በመንፈሳዊ ስለ ታነጽንበት ንግግር ወይም ጠቃሚ ሆኖ ስላገኘነው ቅዱስ ጽሑፋዊ ምክር ለሌሎች በምንናገርበት ወቅት እውነት የሆነውን ማሰባችን ነው። በአንጻሩ ግን ከላይ ሲያዩት እውነት የሚመስለውን ‘የውሸት እውቀት’ ከመናገር እንቆጠባለን። (1 ጢሞቴዎስ 6:20) እንዲሁም ሐሜትንና እውነተኝነታቸው ሊረጋገጡ የማይችሉ ተሞክሮዎችን ለሌሎች መናገር አይኖርብንም።

11. በጭውውታችን ውስጥ ጭምትነት ያለባቸውን የትኞቹን ጉዳዮች አንስተን መወያየት እንችላለን?

11 ጭምትነት ያለባቸው ነገሮች የሚባሉት ተራ ወይም የማይረቡ ወሬዎች ሳይሆኑ ቁም ነገር ያዘሉና ጨዋነት የተላበሱ ጉዳዮች ናቸው። ስለ ክርስቲያናዊ አገልግሎታችን፣ ስለምንኖርበት የመጨረሻ ዘመንና መልካም ምግባር ማሳየት አስፈላጊ ስለመሆኑ አንስቶ መወያየትንም ይጨምራሉ። እንደነዚህ ያሉ አስፈላጊ ጉዳዮችን አንስተን በምንነጋገርበት ጊዜ በመንፈሳዊ ነቅተን ለመኖር፣ ጽኑ አቋማችንን ለመጠበቅና ምሥራቹን መስበካችንን ለመቀጠል ያደረግነው ቁርጥ ውሳኔ ይበልጥ ይጠናከራል። በእርግጥም፣ ከመስክ አገልግሎት የምናገኛቸው ግሩም ተሞክሮዎችና በመጨረሻው ዘመን ውስጥ እንደምንኖር የሚያስታውሱን በጊዜያችን የሚፈጸሙ ክስተቶች የሚያንጹ ውይይቶችን ለማድረግ የሚያስችሉ ርዕሰ ጉዳዮች ናቸው።—ሥራ 14:27፤ 2 ጢሞቴዎስ 3:1-5

12. ጳውሎስ ጽድቅና ንጹሕ የሆኑ ነገሮችን ብቻ እንድናስብ በሰጠን ምክር መሠረት እንዴት ካሉ ጭውውቶች መራቅ ይኖርብናል?

12 ጽድቅ የሚለው ቃል በአምላክ ፊት ትክክል መሆን እንዲሁም እርሱ ባወጣቸው የሥነ ምግባር መስፈርቶች መመራት ማለት ነው። ንጹሕ የሚለው ቃል በሐሳብም ሆነ በጠባይ ንጹሕ መሆንን ያመለክታል። ስም ማጥፋት፣ አስጸያፊ ቀልዶችና የብልግና ንግግሮች በጭውውታችን ውስጥ ቦታ ሊኖራቸው አይገባም። (ኤፌሶን 5:3፤ ቆላስይስ 3:8) ክርስቲያኖች በሥራ ቦታ ወይም በትምህርት ቤት እንዲህ ያሉ ጭውውቶች ሲነሱ በዘዴ ከአካባቢው ዞር ይላሉ።

13. ጭውውታችን ፍቅርና መልካም ወሬ ባለባቸው ነገሮች ላይ እንዲያተኩር ማድረግ የምንችለው እንዴት ነው?

13 ጳውሎስ ፍቅር ያለባቸውን ነገሮች አስቡ ሲል ጭውውታችን ጥላቻን፣ መራርነትንና ጠብን በሚያነሳሱ ነገሮች ላይ ሳይሆን በሚያስደስቱ ወይም ወዳጅነትን በሚያጠናክሩ ነገሮች ላይ እንዲያተኩር ማበረታታቱ ነበር። መልካም ወሬ ያለበት የተባለው ስለ ጥሩ ነገር የሚነገር ወሬ ነው። እንዲህ ያሉ መልካም ወሬዎች በመጠበቂያ ግንብ እና በንቁ! መጽሔቶች ላይ የሚወጡትን ታማኝ ስለሆኑ ወንድሞችና እህቶች የሚናገሩ የሕይወት ታሪኮችን ይጨምራሉ። እነዚህን እምነት የሚያጠነክሩ ታሪኮች ካነበብክ በኋላ የተሰማህን ስሜት ለምን ለሌሎች አትነግራቸውም? ሌሎች በመንፈሳዊ ያገኙትን ስኬት መስማት ምንኛ የሚያበረታታ ነው! እንዲህ ያሉ ጭውውቶች በጉባኤው ውስጥ ፍቅርና አንድነት እንዲሰፍን ያደርጋሉ።

14. (ሀ) በአነጋገራችን በጎነትን ማሳየት ሲባል ምን ማለት ነው? (ለ) በጭውውታችን ውስጥ አድናቆትና ምስጋናን ማከል የምንችለው እንዴት ነው?

14 ጳውሎስ “በጎነት ቢሆን” በማለት ተናግሯል። በጎነት ሲባል ጥሩነት ወይም ሥነ ምግባራዊ ንጽሕና ማለት ነው። አንደበታችንን በመጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ ሥርዓቶች መምራትና ጽድቅ፣ ንጹሕና በጎ የሆነውን ብቻ ለመናገር መጠንቀቅ ይኖርብናል። ምሥጋና ሲል ደግሞ ማድነቅ፣ ማመስገን ማለቱ ነው። አንድ ጥሩ ንግግር ካዳመጥክ ወይም በጉባኤው ውስጥ በአርአያነት የሚጠቀሱ ታማኝ ክርስቲያኖች እንዳሉ ካስተዋልክ አድናቆትህን ለግለሰቡም ሆነ ለሌሎች ንገራቸው። ሐዋርያው ጳውሎስ የእምነት ባልንጀሮቹ የነበራቸውን ግሩም ባሕርያት እየጠቀሰ በተደጋጋሚ ያመሰግናቸው ነበር። (ሮሜ 16:12፤ ፊልጵስዩስ 2:19-22፤ ፊልሞና 4-7) ደግሞም የፈጣሪያችን የእጅ ሥራዎች አድናቆት ሊቸራቸው የሚገቡ ናቸው። እነዚህን የፍጥረት ሥራዎች አንስተን የሚያንጹ ውይይቶችን ማድረግም እንችላለን።—ምሳሌ 6:6-8፤ 20:12፤ 26:2

በሚያንጹ ውይይቶች መካፈል

15. ወላጆች ከልጆቻቸው ጋር ገንቢ መንፈሳዊ ውይይቶች እንዲያደርጉ የሚያሳስበው ቅዱስ ጽሑፋዊ ትእዛዝ የትኛው ነው?

15 ዘዳግም 6:6, 7 እንዲህ ይላል:- “እኔም ዛሬ አንተን የማዝዘውን ይህን ቃል በልብህ ያዝ። ለልጆችህም አስተምረው፣ በቤትህም ስትቀመጥ፣ በመንገድም ስትሄድ፣ ስትተኛም፣ ስትነሣም ተጫወተው።” በግልጽ ለማየት እንደሚቻለው ይህ ትእዛዝ ወላጆች ከልጆቻቸው ጋር ገንቢ የሆኑ መንፈሳዊ ውይይቶችን ማድረግ እንዳለባቸው ይጠቁማል።

16, 17. ክርስቲያን ወላጆች ከይሖዋ እና ከአብርሃም ምን ትምህርት ማግኘት ይችላሉ?

16 ኢየሱስ ወደ ምድር ከመምጣቱ በፊት በሰማይ ከሚኖረው አባቱ ጋር ተልእኮውን በሚመለከት ሰፊ ውይይት አድርገው ሊሆን እንደሚችል ምንም ጥርጥር የለውም። ኢየሱስ ለደቀ መዛሙርቱ “የላከኝ አብ እርሱ የምለውን የምናገረውንም ትእዛዝ ሰጠኝ” ብሏቸው ነበር። (ዮሐንስ 12:49፤ ዘዳግም 18:18) አብርሃም፣ ይሖዋ ቤተሰቡንና አያት ቅድመ አያቶቹን እንዴት እንደባረካቸው ለልጁ ለይስሐቅ ሰፋ ያለ ጊዜ ወስዶ ነግሮት መሆን አለበት። እነዚህ ውይይቶች ኢየሱስንም ሆነ ይስሐቅን ራሳቸውን ለአምላክ ፈቃድ እንዲያስገዙ እንደረዷቸው አያጠራጥርም።—ዘፍጥረት 22:7-9፤ ማቴዎስ 26:39

17 ከልጆቻችንም ጋር የሚያንጽ ውይይት ማድረግ ያስፈልገናል። ወላጆች የቱንም ያህል ሥራ ቢበዛባቸው ከልጆቻቸው ጋር የሚጨዋወቱበት ጊዜ ሊኖራቸው ይገባል። የሚቻል ከሆነ ቢያንስ በቀን አንድ ጊዜ አብራችሁ በቤተሰብ ለመመገብ ለምን ፕሮግራም አታወጡም? እየተመገባችሁ እያለ ወይም ከምግብ በኋላ ለቤተሰቡ መንፈሳዊ ጤንነት ጠቃሚ የሆኑ ገንቢ ጭውውቶችን ማድረግ ትችላላችሁ።

18. ወላጆችና ልጆች ውይይት ማድረጋቸው ጠቃሚ እንደሆነ የሚያሳይ ተሞክሮ ተናገር።

18 በ20ዎቹ ዕድሜ መጀመሪያ ላይ የሚገኘው አሌጃንድሮ የተባለ አቅኚ ወንድም የ14 ዓመት ልጅ ሳለ በአእምሮው ውስጥ ተፈጥሮበት የነበረውን ጥርጣሬ አስታውሶ እንዲህ ይላል:- “የትምህርት ቤት ጓደኞቼና መምህራኖቼ ባሳደሩብኝ ተጽዕኖ የተነሳ የአምላክን ሕልውናና የመጽሐፍ ቅዱስን ትክክለኛነት መጠራጠር ጀምሬ ነበር። ወላጆቼ በትዕግሥት አሳማኝ ነጥቦችን እያነሱ ለብዙ ሰዓታት አነጋገሩኝ። እነዚህ ውይይቶች በወቅቱ ያደረብኝን ጥርጣሬ ለማሸነፍ ብቻ ሳይሆን በሕይወቴ ውስጥ ጥሩ ውሳኔ እንዳደርግም ረድተውኛል።” አሁንስ? አሌጃንድሮ አክሎ እንዲህ ይላል:- “አሁንም የምኖረው ከወላጆቼ ጋር ነው። ቢሆንም እኔና አባቴ ሥራ ስለሚበዛብን እንደድሮው ቁጭ ብለን ለማውራት ሰፊ ጊዜ የለንም። ስለዚህ በሳምንት አንድ ቀን አባቴ በሚሠራበት ቦታ አንድ ላይ ምሳ እንበላለን። በእነዚህ አጋጣሚዎች የምናደርጋቸው ጭውውቶች በጣም ጠቃሚ ሆነው አግኝቻቸዋለሁ።”

19. ሁላችንም ከሌሎች ጋር መንፈሳዊ ጭውውቶች ማድረግ የሚያስፈልገን ለምንድን ነው?

19 ከዚህም በላይ ከእምነት ባልንጀሮቻችን ጋር ጠቃሚ መንፈሳዊ ውይይት ለማድረግ የሚያስችሉንን አጋጣሚዎች ትልቅ ቦታ ልንሰጣቸው አይገባም? በክርስቲያናዊ ስብሰባዎች፣ በመስክ አገልግሎት፣ በማኅበራዊ ግብዣዎች ወይም በጉዞ ላይ እንዲህ ያሉ መንፈሳዊ ጭውውቶችን ለማድረግ የሚያስችሉ አጋጣሚዎች እናገኛለን። ጳውሎስ በሮም ካሉ ክርስቲያኖች ጋር ተገናኝቶ የሚጫወትበትን ጊዜ ይናፍቅ ነበር። “ትጸኑ ዘንድ መንፈሳዊ ስጦታ እንዳካፍላችሁ ላያችሁ እናፍቃለሁና፤ ይህንም ማለቴ በመካከላችን ባለች በእናንተና በእኔ እምነት አብረን በእናንተ እንድንጽናና ነው” በማለት ጽፎላቸዋል። (ሮሜ 1:11, 12) ዮሐንስ የተባለ አንድ የጉባኤ ሽማግሌ እንዲህ ሲል ተናግሯል:- “ከሌሎች ክርስቲያኖች ጋር የምናደርገው መንፈሳዊ ጭውውት በጣም ጠቃሚ ነው። ልብን ደስ የሚያሰኝ ከመሆኑም በላይ በየዕለቱ የሚያጋጥመንን የኑሮ ጫና ያቀልልናል። ብዙውን ጊዜ አረጋውያንን የሕይወት ታሪካቸውንና ታማኝነታቸውን ጠብቀው እንዲጸኑ ምን እንደረዳቸው እጠይቃቸዋለሁ። ባለፉት ዓመታት ከብዙ አረጋውያን ጋር እንዲህ ዓይነቱን ጭውውት ያደረግሁ ሲሆን ከእያንዳንዳቸው ለሕይወቴ ጠቃሚ የሆነ ጥበብና እውቀት አግኝቻለሁ።”

20. አብሮን ያለው ሰው ዓይናፋር ቢሆን ምን ማድረግ እንችላለን?

20 ስለ መንፈሳዊ ነገሮች ስታነሳ አብሮህ ያለው ሰው ደስ ባይለውስ? ተስፋ አትቁረጥ። ምናልባት በሌላ ጊዜ የተሻለ አጋጣሚ ታገኝ ይሆናል። ሰሎሞን “የወርቅ እንኮይ በብር ፃሕል ላይ፤ የጊዜው ቃል እንዲሁ ነው” በማለት ተናግሯል። (ምሳሌ 25:11) ዓይናፋር የሆኑ ሰዎችን ስሜት ተረዳ። “ምክር በሰው ልብ እንደ ጠሊቅ ውኃ ነው፤ አእምሮ ያለው ሰው ግን ይቀዳዋል።” a (ምሳሌ 20:5) ከሁሉም በላይ ግን የሌሎች መንፈስ የተደሰትክባቸውን ነገሮች ከመናገር ወደ ኋላ እንድትል ሊያደርግህ አይገባም።

ስለ መንፈሳዊ ነገሮች መወያየት ይክሳል

21, 22. ጭውውቶቻችን በመንፈሳዊ ጉዳዮች ላይ እንዲያተኩሩ ማድረጋችን ምን ጥቅሞች አሉት?

21 ጳውሎስ “ለሚሰሙት ጸጋን ይሰጥ ዘንድ፣ እንደሚያስፈልግ ለማነጽ የሚጠቅም ማናቸውም በጎ ቃል እንጂ ክፉ ቃል ከአፋችሁ ከቶ አይውጣ” የሚል ምክር ሰጥቷል። (ኤፌሶን 4:29፤ ሮሜ 10:10) ጭውውታችንን የሚያንጽ እንዲሆን ማድረግ ጥረት የሚጠይቅ ቢሆንም በርካታ ጥቅሞች አሉት። ስለ መንፈሳዊ ነገሮች መወያየት እምነታችንን ለሌሎች ለማካፈልና ወንድሞቻችንን ለማነጽ ያስችለናል።

22 እንግዲያው ከአምላክ ያገኘነውን የመናገር ችሎታ ሌሎችን ለማነጽና እርሱን ለማወደስ እንጠቀምበት። እንዲህ ያሉ ውይይቶች ሌሎችን የሚያበረታቱ ከመሆናቸውም በላይ ለእኛም እርካታ ያስገኙልናል። ከሁሉም በላይ ግን የምንናገረውን ነገር ትኩረት ሰጥቶ የሚያዳምጠው ይሖዋ አንደበታችንን በተገቢው መንገድ ስንጠቀምበት ይደሰታል። (መዝሙር 139:4፤ ምሳሌ 27:11) የምንናገራቸው ነገሮች በመንፈሳዊ ጉዳዮች ላይ የሚያተኩሩ ከሆኑ ይሖዋ ፈጽሞ እንደማይረሳን እርግጠኞች መሆን እንችላለን። መጽሐፍ ቅዱስ በዘመናችን ስላሉት የይሖዋ አገልጋዮች ሲናገር እንዲህ ይላል:- “የዚያን ጊዜ እግዚአብሔርን የሚፈሩ እርስ በእርሳቸው ተነጋገሩ፤ እግዚአብሔርም አደመጠ፣ ሰማም፣ እግዚአብሔርንም ለሚፈሩ ስሙንም ለሚያስቡ የመታሰቢያ መጽሐፍ በፊቱ ተጻፈ።” (ሚልክያስ 3:16፤ 4:5) ከሌሎች ጋር የምናደርገው ጭውውት በመንፈሳዊ የሚያንጽ መሆኑ ምንኛ አስፈላጊ ነው!

[የግርጌ ማስታወሻ]

a በጥንቷ እስራኤል የነበሩ አንዳንድ የውኃ ጉድጓዶች በጣም ጥልቅ ነበሩ። የከርሰ ምድር ተመራማሪዎች በገባዖን 25 ሜትር ጥልቀት ያለው ትልቅ ውኃ ማቆሪያ ጉድጓድ አግኝተዋል። ጉድጓዱ ውስጥ ገብቶ ውኃ ለመቅዳት የሚያስችል ደረጃ አለው።

ምን ብለህ ትመልሳለህ?

• በአንደበታችን የምንናገረው ነገር ስለልባችን ሁኔታ ምን ይገልጣል?

• ስለየትኞቹ የሚያንጹ ነገሮች መወያየት እንችላለን?

• መንፈሳዊ ጭውውቶች በቤተሰብ ውስጥና በክርስቲያን ጉባኤ ውስጥ ምን ሚና ይጫወታሉ?

• የሚያንጹ ጭውውቶችን ማድረግ ምን ጥቅሞች አሉት?

[የአንቀጾቹ ጥያቄዎች]

[በገጽ 12 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

የሚያንጹ ጭውውቶች በሚከተሉት ጉዳዮች ላይ ያተኮሩ ናቸው:-

“እውነተኛ የሆነውን ነገር ሁሉ”

“ጭምትነት ያለበትን ነገር ሁሉ”

“ምስጋናም ቢሆን”

“መልካም ወሬ ያለበትን ነገር ሁሉ”

[ምንጭ]

የቪዲዮው የሽፋን ስዕል፣ ስታሊን:- U.S. Army photo; የክሪኤተር መጽሐፍ ሽፋን፣ ኢግል ኔቡላ:- J. Hester and P. Scowen (AZ State Univ.), NASA

[በገጽ 13 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

በምግብ ሰዓት መንፈሳዊ ጭውውት ለማድረግ የሚያስችል ግሩም አጋጣሚ እናገኛለን