በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

በፊትና አሁን—መጽሐፍ ቅዱስ የዚህን ሰው ሕይወት ለወጠው

በፊትና አሁን—መጽሐፍ ቅዱስ የዚህን ሰው ሕይወት ለወጠው

“ወደ እግዚአብሔር ቅረቡ ወደ እናንተም ይቀርባል”

በፊትና አሁን—መጽሐፍ ቅዱስ የዚህን ሰው ሕይወት ለወጠው

በሮልፍ ሚካኤል ሕይወት ውስጥ ትልቁን ቦታ የያዘው ሙዚቃ ነበር። አደገኛ ዕፅ ደግሞ ከምንም ነገር በላይ ይወድ ነበር። በወጣትነቱ በጀርመን በነበረበት ወቅት የአልኮል መጠጦችን ከመጠን በላይ ይጠጣ የነበረ ከመሆኑም በላይ ኤል ኤስ ዲ፣ ኮኬይንና ሃሺሽ የሚባሉትን ጨምሮ ሌሎች አደገኛ ዕፆችን በብዛት ይወስድ ነበር።

ሮልፍ ሚካኤል ወደ አንድ የአፍሪካ አገር አደገኛ ዕፆችን በድብቅ ለማስገባት ሲሞክር ተያዘና ለ13 ወራት ታሰረ። በእስር ቤት ያሳለፈው ጊዜ ስለ ሕይወት ዓላማ በጥሞና እንዲያስብ አደረገው።

ሮልፍ ሚካኤልና ባለቤቱ ኡርሱላ የሕይወትን ዓላማ እንዲሁም እውነትን አጥብቀው መፈለግ ጀመሩ። ክርስቲያን ነን ለሚሉ ሃይማኖቶች ጥሩ አመለካከት ባይኖራቸውም አምላክን ለማወቅ በእጅጉ ይፈልጉ ነበር። ለነበሯቸው በርካታ ጥያቄዎች መልስ ለማግኘት ወደተለያዩ ሃይማኖታዊ ቡድኖች ቢሄዱም አጥጋቢ ምላሽ ለማግኘት አልቻሉም። በተጨማሪም ከእነዚህ ሃይማኖቶች ሕይወታቸውን እንዲለውጡ የሚገፋፋቸው ተጨባጭ ምክንያት አላገኙም።

ከጊዜ በኋላ ሮልፍ ሚካኤልና ኡርሱላ ከይሖዋ ምሥክሮች ጋር ተገናኙ። መጽሐፍ ቅዱስን ማጥናት ከጀመሩ በኋላ ሮልፍ ሚካኤል “ወደ እግዚአብሔር ቅረቡ ወደ እናንተም ይቀርባል” በሚለው የመጽሐፍ ቅዱስ ምክር በጣም ተነካ። (ያዕቆብ 4:8) ‘ፊተኛ ኑሮውን በማሰብ አሮጌውን ሰው ለማስወገድና ለእውነትም በሚሆኑ ጽድቅና ቅድስና እንደ እግዚአብሔር ምሳሌ የተፈጠረውን አዲሱን ሰው ለመልበስ’ ቁርጥ ውሳኔ አደረገ።—ኤፌሶን 4:22-24

ሮልፍ ሚካኤል አዲሱን ሰው መልበስ የሚችለው እንዴት ይሆን? የይሖዋ ምሥክሮች አንድ ሰው በትክክለኛው ‘እውቀት’ አማካኝነት ፈጣሪውን ይሖዋ አምላክን ለመምሰል ‘አዲሱን ሰው መልበስ’ እንደሚችል ከመጽሐፍ ቅዱስ ላይ አሳዩት።—ቆላስይስ 3:9-11

ሮልፍ ሚካኤል ትክክለኛውን እውቀት እየቀሰመ ሲሄድ ሕይወቱን ከአምላክ ቃል መሠረታዊ ሥርዓቶች ጋር ለማስማማት ጥረት ማድረግ ጀመረ። (ዮሐንስ 17:3) ከነበረበት የዕፅ ሱስ መላቀቅ አስቸጋሪ ሆኖበት የነበረ ቢሆንም ሮልፍ ሚካኤል ይሖዋ እንዲረዳው ወደ እርሱ መጸለይ ያለውን አስፈላጊነት ተገነዘበ። (1 ዮሐንስ 5:14, 15) የአምላክን ፈቃድ ለመፈጸም ከሚጥሩት ከይሖዋ ምሥክሮች ጋር የቀረበ ወዳጅነት መመሥረቱም ረድቶታል።

በተጨማሪም ሮልፍ ሚካኤል ይህ ዓለም አላፊ መሆኑን እንዲሁም የአምላክን ፈቃድ የሚያደርጉ ሰዎች በዚህች ምድር ላይ ለዘላለም እንደሚኖሩ ማወቁ ረድቶታል። ይህም ጊዜያዊ የሆነውን ዓለም ሳይሆን አፍቃሪ አምላክ ከሆነው ከይሖዋ ጋር የቀረበ ዝምድና መመሥረት የሚያስገኘውን ዘላለማዊ በረከት እንዲመርጥ አስችሎታል። (1 ዮሐንስ 2:15-17) ሮልፍ ሚካኤል በምሳሌ 27:11 ላይ በሚገኙት “ልጄ ሆይ፣ ጠቢብ ሁን፣ ልቤንም ደስ አሰኘው፣ ለሚሰድበኝ መልስ መስጠት ይቻለኝ ዘንድ” በሚሉት ቃላት ልቡ ተነክቶ ነበር። “ይህ ጥቅስ ይሖዋ ምን ያህል እንደሚወደን ያሳያል፤ ምክንያቱም የእርሱን ልብ የማስደሰት መብት ሰጥቶናል” በማለት የተሰማውን አድናቆት ገልጿል።

ሮልፍ ሚካኤል፣ ሚስቱና ሦስት ልጆቹ የመጽሐፍ ቅዱስን መሠረታዊ ሥርዓቶች በሥራ ላይ በማዋላቸው እንደተጠቀሙ ሁሉ በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎችም ተመሳሳይ ጥቅም አግኝተዋል። እንዲህ ዓይነት ሰዎችን በዓለም ዙሪያ በሚገኙ የይሖዋ ምሥክሮች ጉባኤዎች ውስጥ ማግኘት ይቻላል። የሚያሳዝነው ግን በአንዳንድ አገሮች ውስጥ የይሖዋ ምሥክሮች ቤተሰብን የሚበታትኑ አደገኛ ኑፋቄዎች እንደሆኑ ተደርገው በሐሰት ይወነጀላሉ። የሮልፍ ሚካኤል ተሞክሮ ግን የዚህን ውንጀላ ሐሰተኝነት ያሳያል።—ዕብራውያን 4:12

ሮልፍ ሚካኤል በሕይወታችን ውስጥ ለመንፈሳዊ ግቦች ቅድሚያ እንድንሰጥ የሚያበረታታን የማቴዎስ 6:33 ጥቅስ ቤተሰቡን በትክክለኛው አቅጣጫ የሚመራው “ኮምፓስ” እንደሆነ ይናገራል። እሱና ቤተሰቡ የይሖዋ ምሥክሮች በመሆናቸው ላገኙት በደስታ የተሞላ የቤተሰብ ሕይወት ይሖዋን ከልብ ያመሰግኑታል። “ስላደረገልኝ ሁሉ ለእግዚአብሔር ምንን እመልሳለሁ?” በማለት የዘመረውን የመዝሙራዊውን ስሜት ይጋራሉ።—መዝሙር 116:12

[በገጽ 9 ላይ የሚገኝ ሣጥን]

የመጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ ሥርዓቶች ያላቸው ኃይል

ብዙዎች አደገኛ ከሆኑ ሱሶች እንዲላቀቁ ከረዷቸው የመጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ ሥርዓቶች መካከል የሚከተሉት ይገኙበታል:-

“እግዚአብሔርን የምትወድዱ፣ ክፋትን ጥሉ።” (መዝሙር 97:10) አንድ ሰው ለሕይወት አደገኛ የሆኑ ልማዶችን መጥፎነት ከተገነዘበና ለእነርሱ ጥላቻ ካዳበረ አምላክን የሚያስደስቱ ነገሮችን ማድረግ ቀላል ይሆንለታል።

“ከጠቢባን ጋር የሚሄድ ጠቢብ ይሆናል፤ የሰነፎች ባልንጀራ ግን ክፉ መከራን ይቀበላል።” (ምሳሌ 13:20) አንድ ሰው አደገኛ ዕፆችንም ሆነ ሱስ የሚያስይዙ ሌሎች ነገሮችን መውሰዱን ለማቆም ጓደኞቹን በጥበብ መምረጥ ይኖርበታል። ይህን አቋሙን ከሚደግፉለት ከይሖዋ ምሥክሮች ጋር ወዳጅነት መመሥረቱ በእጅጉ ይረዳዋል።

“በነገር ሁሉ በጸሎትና በምልጃ ከምስጋና ጋር በእግዚአብሔር ዘንድ ልመናችሁን አስታውቁ እንጂ በአንዳች አትጨነቁ። አእምሮንም ሁሉ የሚያልፍ የእግዚአብሔር ሰላም ልባችሁንና አሳባችሁን በክርስቶስ ኢየሱስ ይጠብቃል።” (ፊልጵስዩስ 4:6, 7) እንዲህ ዓይነቱን የልብና የአእምሮ ሰላም በሌላ በምንም ነገር ማግኘት አይቻልም። ምንም ዓይነት አደገኛ ዕፅ መጠቀም ሳያስፈልግ በጸሎት አማካኝነት በይሖዋ ላይ ትምክህት መጣል የሕይወትን ችግሮች ለማሸነፍ ያስችላል።

[በገጽ 9 ላይ የሚገኝ የተቀነጨበ ሐሳብ]

አምላክ የእርሱን ልብ የማስደሰት መብት ለሰው ልጆች ሰጥቷል