በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የጋብቻን ሰንሰለት ማጠናከር የሚቻለው እንዴት ነው?

የጋብቻን ሰንሰለት ማጠናከር የሚቻለው እንዴት ነው?

የጋብቻን ሰንሰለት ማጠናከር የሚቻለው እንዴት ነው?

ለረጅም ጊዜ እድሳት ሳይደረግለት በመቅረቱ በጣም ያረጀ ቤት በዓይነ ሕሊናህ ተመልከት። ቀለሙ ተላልጧል፤ ጣሪያው ተበሳስቷል እንዲሁም ግቢውን ሣርና ሙጃ ወርሶታል። ቤቱ ለብዙ ዓመታት ፀሐይና ዝናብ ሲፈራረቁበት እንደቆየና ምንም እድሳት እንዳልተደረገለት ያስታውቃል። ይህንን ቤት ከናካቴው ማፍረስ ይሻላል ወይስ ማደስ? መሠረቱ ጠንካራ ከሆነና መዋቅሩም በጥሩ ሁኔታ ላይ የሚገኝ ከሆነ የግድ መፍረስ አያስፈልገውም። እድሳት ተደርጎለት ወደ መጀመሪያ ይዞታው ሊመለስ ይችላል።

የዚህ ቤት ሁኔታ ስለ ትዳርህ አስታውሶህ ይሆን? ለበርካታ ዓመታት የተለያዩ ዓይነት ከባድ ችግሮች በትዳርህ ላይ ተፈራርቀውበት ሊሆን ይችላል። ከሁለት አንዳችሁ ወይም ሁለታችሁም ትዳራችሁን በተወሰነ መጠን ቸል ብላችሁ ሊሆን ይችላል። አንተም ለ15 ዓመታት በትዳር ዓለም እንደቆየችው እንደ ሳንዲ ይሰማህ ይሆናል። እንዲህ ብላለች:- “እኔና ባለቤቴን ያስተሳሰረን ባልና ሚስት የሚለው መጠሪያ ብቻ ነበር። ይህ ደግሞ ብቻውን በቂ አልነበረም።”

ያንተም ትዳር እዚህ ደረጃ ላይ ቢደርስ እንኳን መፍትሔው ፍቺ ነው ብለህ ለመደምደም አትቸኩል። የጋብቻህን ሰንሰለት ማጠናከር ትችላለህ። ይህ በአብዛኛው የተመካው አንተም ሆንክ የትዳር ጓደኛህ ቃል ኪዳናችሁን ለመጠበቅ ባላችሁ ቁርጠኝነት ላይ ነው። ቃል ኪዳንህን ለማክበር ያለህ ቁርጠኝነት ችግሮች በሚያጋጥሙበት ጊዜም እንኳን ትዳርህን ከመፍረስ ሊጠብቀው ይችላል። ይሁን እንጂ ቃል ኪዳንን ለማክበር ቁርጠኛ መሆን ሲባል ምን ማለት ነው? መጽሐፍ ቅዱስ በዚህ ረገድ ሊረዳህ የሚችለው እንዴት ነው?

ቃል ኪዳን ግዴታ ያስከትላል

አንድ መዝገበ ቃላት በሰጠው ፍቺ መሠረት ቃል ኪዳን “ግዴታ ወይም ኃላፊነት ውስጥ መግባት” ተብሏል። አንዳንድ ጊዜ ቃሉ ከጋብቻ ውጪ እንደ ንግድ ስምምነት ላሉ ሌሎች ግንኙነቶችም ይሠራል። ለምሳሌ ያህል አንድ የሕንጻ ተቋራጭ አንድን ቤት ለመሥራት የገባውን ውል የመፈጸም ግዴታ እንዳለበት ይሰማው ይሆናል። ቤቱን የሚያሠራውን ግለሰብ ግን በግል ላያውቀው ይችላል። ቢሆንም የገባውን ቃል የመፈጸም ግዴታ እንዳለበት ይገነዘባል።

ምንም እንኳን ጋብቻ ምንም ስሜታዊ ትስስር የሌለው የንግድ ስምምነት ባይሆንም ቃል የተጋቡት ግለሰቦች ቃላቸውን የመጠበቅ ግዴታ አለባቸው። አንተና የትዳር ጓደኛህ የመጣው ቢመጣ ላትለያዩ በአምላክና በሰዎች ፊት ቃል ገብታችኋል። ኢየሱስ እንዲህ ብሎ ነበር:- “ፈጣሪ በመጀመሪያ ወንድና ሴት አደረጋቸው፣ አለም:- ስለዚህ ሰው አባቱንና እናቱን ይተዋል፣ ከሚስቱም ጋር ይተባበራል።” አክሎም “እግዚአብሔር ያጣመረውን እንግዲህ ሰው አይለየው” ብሏል። (ማቴዎስ 19:4-6) እንግዲያው ችግሮች በሚከሰቱበት ጊዜ ሁለታችሁም የገባችሁትን ቃል ለማክበር ቁርጥ ውሳኔ ማድረግ አለባችሁ። a አንዲት ሚስት እንዲህ ብላለች:- “የጋብቻ ሕይወታችን መስተካከል የጀመረው ፍቺን እንደ አማራጭ አድርገን ማየት ስናቆም ነበር።”

ይሁን እንጂ ቃል ኪዳን ግዴታ ወይም ኃላፊነት ውስጥ ከመግባት የበለጠ ነገርን ይጨምራል። ይህ ምንድን ነው?

ተባብሮ መሥራት የጋብቻ ቃል ኪዳንን ያጠነክራል

አንድ ባልና ሚስት ቃል ኪዳን ተጋብተዋል ማለት በመካከላቸው አለመግባባት አይፈጠርም ማለት አይደለም። አለመግባባት በሚፈጠርበት ጊዜ ለገቡት ቃል ሲሉ ብቻ ሳይሆን በመካከላቸው ያለውን ስሜታዊ ቁርኝት ለመጠበቅ ችግሩን በሰላም ለመፍታት ልባዊ ፍላጎት ሊኖራቸው ይገባል። ኢየሱስ ባልና ሚስትን በሚመለከት “አንድ ሥጋ ናቸው እንጂ ወደ ፊት ሁለት አይደሉም” ብሏል።

ከትዳር ጓደኛህ ጋር “አንድ ሥጋ” ናችሁ ሲባል ምን ማለት ነው? ሐዋርያው ጳውሎስ “ባሎች ደግሞ እንደ ገዛ ሥጋቸው አድርገው የገዛ ሚስቶቻቸውን ሊወዱአቸው ይገባቸዋል” ሲል ጽፏል። (ኤፌሶን 5:28, 29) እንግዲያው “አንድ ሥጋ” መሆን ማለት ለራስህ ደህንነት የምትጨነቀውን ያህል ለትዳር ጓደኛህም ደህንነት ታስባለህ ማለት ነው። ባለትዳሮች ምንጊዜም “እኔ” ከማለት “እኛ” ማለትን መልመድ ይኖርባቸዋል። አንዲት የጋብቻ አማካሪ ‘ሁለቱም የትዳር ጓደኞች ነጠላ እንደሆኑ ማሰባቸውን አቁመው ራሳቸውን እንደ ባለትዳር መቁጠር መጀመር አለባቸው’ በማለት ጽፈዋል።

አንተም ሆንክ የትዳር ጓደኛህ “ራሳችሁን እንደ ባለትዳር” አድርጋችሁ ትመለከታላችሁ? አንዳንዶች ለዓመታት ተጋብተው ቢኖሩም “አንድ ሥጋ” መሆን አልቻሉ ይሆናል። እንዲህ ያለ ሁኔታ ሊፈጠር የሚችል ቢሆንም ጊቪንግ ታይም ኤ ቻንስ (ጊዜ እንዲፈታው እድል መስጠት) የተባለው መጽሐፍ እንዲህ ይላል “ትዳር ማለት ሕይወትን በጋራ ማጣጣም ማለት ነው፤ ሁለት ሰዎች ሕይወትን በጋራ ባጣጣሙ መጠን አንድነታቸውም የዚያኑ ያህል ይጠናከራል።”

በትዳራቸው ደስተኛ ያልሆኑ አንዳንድ ባልና ሚስቶች አብረው የሚኖሩት ለልጆቻቸው ሲሉ ወይም በኢኮኖሚ ራሳቸውን መደገፍ ስለማይችሉ ነው። ሌሎች ደግሞ ፍቺን አጥብቀው ስለሚቃወሙ ወይም ብንፋታ ሰው ምን ይለናል ብለው በመፍራት ችግሮች እያሉም አብረው ይኖራሉ። ይህ የሚያስመሰግናቸው ቢሆንም ትዳር የመሠረትህበት ዋነኛው ዓላማ እንዲያው ለረዥም ጊዜ አብሮ ለመኖር ሳይሆን በፍቅር ላይ የተመሠረተ አስደሳች ትስስር ለመፍጠር መሆኑን መዘንጋት የለብህም።

ራስ ወዳድ አለመሆን የጋብቻን ቃል ኪዳን ያጠናክራል

“በመጨረሻው ቀን” ሰዎች “ራሳቸውን የሚወዱ” እንደሚሆኑ በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ በትንቢት ተነግሯል። (2 ጢሞቴዎስ 3:1, 2) በዚህ ትንቢት ፍጻሜ መሠረት በጊዜያችን ሰዎች ለራሳቸው ከአምልኮ የማይተናነስ ክብር እንደሚሰጡ በግልጽ ይታያል። በአብዛኞቹ ትዳሮች ውስጥ በአጸፋው ምንም ሳይጠብቁ ለትዳር ጓደኛ አንድ ነገር ማድረግ እንደ ድክመት ይቆጠራል። ስኬታማ በሆኑ ትዳሮች ውስጥ ግን ሁለቱም የትዳር ጓደኞች የራስን ጥቅም መሥዋዕት የማድረግን መንፈስ ያሳያሉ። አንተስ እንዲህ ማድረግ የምትችለው እንዴት ነው?

‘ከትዳሬ የማገኘው ጥቅም ምንድን ነው?’ ብለህ ከማሰብ ይልቅ ‘ትዳሬን ለማጠናከር በግል እያደረግሁ ያለሁት አስተዋጽኦ ምንድን ነው?’ በማለት ራስህን ጠይቅ። መጽሐፍ ቅዱስ “እያንዳንዳችሁ ሌሎችን የሚጠቅመውን እንጂ ራሳችሁን የሚጠቅመውን ብቻ አትመልከቱ” በማለት ክርስቲያኖችን ያሳስባል። (ፊልጵስዩስ 2:4 አ.መ.ት) ይህን የመጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ ሥርዓት በአእምሮህ ይዘህ ያለፈውን ሳምንት እንዴት እንዳሳለፍከው አስብ። የትዳር ጓደኛህን ብቻ የሚጠቅም ምን ያደረግኸው ነገር አለ? የትዳር ጓደኛህ መናገር በሚፈልግበት ጊዜ መስማት ባያሰኝህም እንኳን እርሱን ለማስደሰት ስትል ብቻ አዳምጠሃል? ከአንተ ይልቅ የትዳር ጓደኛህን በሚያስደስቱ በየትኞቹ እንቅስቃሴዎች ተካፍለሃል?

እነዚህን ጥያቄዎች እያነሳህ ራስህን በምትገመግምበት ጊዜ ያደረግሁትን ጥረት ሌላው ወገን አይረዳውም ወይም በአጸፋው ምንም አያደርግልኝም ብለህ አታስብ። አንድ የማመሳከሪያ ጽሑፍ እንዲህ ይላል:- “በአብዛኞቹ ትዳሮች ውስጥ በጎ ተግባር ሌላው ወገን አጸፌታውን እንዲመልስ ስለሚገፋፋው እናንተ ራሳችሁ መልካም ነገር በማድረግ የትዳር ጓደኛችሁን ለመልካም ነገር አነሳሱት።” የራስን ጥቅም መሥዋዕት የማድረግ መንፈስ ማሳየታችሁ ለትዳራችሁ ትልቅ ቦታ እንደምትሰጡና ዘላቂ እንዲሆን እንደምትፈልጉ ስለሚያሳይ የጋብቻችሁን ሰንሰለት ያጠናክረዋል።

የዕድሜ ልክ ጥምረት አድርጎ መመልከት

ይሖዋ አምላክ ለታማኝነት ከፍ ያለ ቦታ ይሰጣል። መጽሐፍ ቅዱስ “ለታማኝ ሰው አንተም ታማኝ መሆንህን . . . ታሳያለህ” የሚለው በዚህ ምክንያት ነው። (2 ሳሙኤል 22:26 አ.መ.ት) ለአምላክ ታማኝ መሆን እርሱ ላቋቋመው የጋብቻ ዝግጅት ታማኝ መሆንን ይጠይቃል።—ዘፍጥረት 2:24

አንተና የትዳር ጓደኛህ እርስ በርስ ታማኞች ከሆናችሁ በመካከላችሁ ያለው ጥምረት ዘላቂ እንደሚሆን የእርግጠኝነት ስሜት ያድርብሃል። ስለ ወደፊቱ ጊዜ ስታስብ አብራችሁ እስከመጨረሻው እንደምትዘልቁ ሆኖ ይታይሃል። መፋታት የሚለው ሐሳብ ጨርሶ ወደ አእምሮህ አይመጣም። ይህ ደግሞ የጋብቻችሁን ጥምረት አስተማማኝ ያደርገዋል። አንዲት ሚስት እንዲህ ትላለች:- “በባለቤቴ ላይ በጣም በምናደድበትና በመካከላችን በተፈጠረው ሁኔታ በምበሳጭበት ጊዜ እንኳ እንፋታ ይሆን ብዬ ፈጽሞ አስቤ አላውቅም። እኔን የሚያሳስበኝ የነበረንን ሰላማዊ ግንኙነት መልሰን ማደስ የምንችለው እንዴት ነው የሚለው ነው። በወቅቱ ይህን እንዴት ማድረግ እንደምንችል ባይታየኝም መልሰን እንደምንስማማ ግን ቅንጣት ታክል ጥርጣሬ የለኝም።”

የጋብቻን ቃል ኪዳን በመጠበቅ ረገድ ትዳርን ዘላቂ ጥምረት አድርጎ መመልከቱ በጣም አስፈላጊ ቢሆንም ብዙ ባለትዳሮች ግን እንዲህ ዓይነቱ አመለካከት የላቸውም። ጭቅጭቅ በሚፈጠርበት ጊዜ አንደኛው የትዳር ጓደኛ “በቃኝ! እሄዳለሁ” ወይም “ከአንተ የተሻለ የሚወደኝና የሚያስብልኝ ሌላ ሰው አላጣም!” ብሎ በምሬት ይናገር ይሆናል። እርግጥ አብዛኞቹ እንዲህ ያሉት ማስፈራሪያዎች ከልብ የሚነገሩ አይደሉም። ያም ሆኖ ግን መጽሐፍ ቅዱስ አንደበት “የሚገድል መርዝ” ሊሆን እንደሚችል ይናገራል። (ያዕቆብ 3:8) ዛቻዎችና ማስጠንቀቂያዎች ‘ትዳራችን ዘላቂ ሆነ አልሆነ አያስጨንቀኝም፤ ባሻኝ ጊዜ ተነስቼ ውልቅ ልል እችላለሁ’ የሚል መልእክት ያስተላልፋሉ። ይህ ደግሞ የትዳር ፀር ነው።

ትዳርህን ዘላቂ አድርገህ የምትመለከተው ከሆነ ከትዳር ጓደኛህ ጋር መከራንም ሆነ ደስታን አሳልፈህ እስከ መጨረሻው እንደምትጸና ይሰማሃል። ይህ ሌላም ጥቅም አለው። አንዳችሁ የሌላውን ድክመትና ስህተት ለመቀበልና ተቻችሎ ለመኖር እንዲሁም ይቅር ለመባባል ይበልጥ ቀላል ይሆንላችኋል። (ቆላስይስ 3:13) አንድ መጽሐፍ “ስኬታማ በሆነ ትዳር ውስጥ ሁለቱም ስህተት ሊሠሩ የሚችሉ ቢሆንም ትዳራቸው ግን ጸንቶ ይኖራል” ይላል።

በሠርጋችሁ ዕለት ቃል የገባኸው ግዑዝ ለሆነው የጋብቻ ዝግጅት ሳይሆን ሕያው ለሆነው የትዳር ጓደኛህ ነው። ይህ ሐቅ በትዳር ሕይወትህ ውስጥ በአስተሳሰብህና በድርጊቶችህ ላይ ትልቅ ተጽዕኖ ሊኖረው ይገባል። ከትዳር ጓደኛህ ጋር እስከ መጨረሻው መዝለቅ ያለብህ በጋብቻ ቅዱስነት አጥብቀህ ስለምታምን ብቻ ሳይሆን የትዳር ጓደኛህን ከልብ ስለምትወደው መሆን እንዳለበት አትስማማም?

[የግርጌ ማስታወሻ]

a አንዳንድ ከአቅም በላይ የሆኑ ሁኔታዎች በሚያጋጥሙበት ጊዜ ባልና ሚስት ተለያይተው ለመኖር ይወስኑ ይሆናል። (1 ቆሮንቶስ 7:10, 11ለቤተሰብ ደስታ ቁልፉ ምንድን ነው? የተባለውን በይሖዋ ምሥክሮች የታተመ መጽሐፍ ገጽ 160-1 ተመልከት።) በተጨማሪም መጽሐፍ ቅዱስ ከሁለት አንዳቸው ምንዝር (የጾታ ብልግና) ከፈጸሙ መፋታት እንደሚችሉ ይገልጻል።—ማቴዎስ 19:9

[በገጽ 5 ላይ የሚገኝ ሣጥን]

ምን ማድረግ ትችላለህ?

የጋብቻ ቃል ኪዳንህን ለመጠበቅ ያለህ ቁርጠኝነት ምን ያህል ጠንካራ ነው? ምናልባት ማስተካከያ ልታደርግባቸው የሚገቡ ጉዳዮች ይኖሩ ይሆናል። የጋብቻ ቃል ኪዳንህን ለመጠበቅ እስቲ የሚከተሉትን ነጥቦች ተግባራዊ ለማድረግ ሞክር:-

● ራስህን መርምር። ‘አስተሳሰቤም ሆነ ድርጊቴ እንደ ባለ ትዳር ነው ወይስ ገና እንዳላገባ ሰው?’ በዚህ ረገድ የትዳር ጓደኛህ ስላንተ ምን እንደሚሰማው ጠይቀው።

● ይህን ርዕስ ከባለቤትህ ጋር ሆነህ አንብበው። ከዚያም ረጋ ብላችሁ ቃል ኪዳናችሁን ለመጠበቅ ያላችሁን ቁርጠኝነት ማጠናከር የምትችሉባቸውን መንገዶች ተወያዩ።

● የጋብቻችሁን ሰንሰለት ሊያጠናክሩ በሚችሉ እንቅስቃሴዎች አብራችሁ ተካፈሉ። ለምሳሌ ያህል:- በሠርጋችሁ ዕለት ወይም በሌሎች ልዩ ክንውኖች ላይ የተነሳችኋቸውን ፎቶግራፎች አብራችሁ ተመልከቱ። በምትጠናኑበት ወቅት ወይም በትዳራችሁ የመጀመሪያ ዓመታት በጋራ ታደርጓቸው የነበሩትን ነገሮች አድርጉ። ትዳርን በሚመለከት በመጠበቂያ ግንብ እና ንቁ! መጽሔቶች ላይ የሚወጡ በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተመሠረቱ ርዕሶችን አብራችሁ አጥኑ።

[በገጽ 6 ላይ የሚገኝ ሣጥን]

የጋብቻን ቃል ኪዳን መጠበቅ ማለት . . .

ቃልን የማክበር ግዴታ “የተሳልኸውን ፈጽመው። ተስለህ የማትፈጽም ብትሆን ባትሳል ይሻላል።”—መክብብ 5:4, 5

አብሮ መሥራት “አንድ ብቻ ከመሆን ሁለት መሆን ይሻላል። ቢወድቁ አንዱ ሁለተኛውን ያነሣዋልና።”—መክብብ 4:9, 10

የራስን ጥቅም መሠዋት “ከሚቀበል ይልቅ የሚሰጥ ብፁዕ ነው።”—ሥራ 20:35

ትዳር ዘላቂ ጥምረት እንደሆነ ማሰብ “ፍቅር . . . በሁሉ ይጸናል።”—1 ቆሮንቶስ 13:4, 7

[በገጽ 7 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

የትዳር ጓደኛችሁ ለማውራት በሚፈልግበት ጊዜ ታዳምጡታላችሁ?