በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

“የጠቢብ ትምህርት” የሕይወት ምንጭ ናት

“የጠቢብ ትምህርት” የሕይወት ምንጭ ናት

“የጠቢብ ትምህርት” የሕይወት ምንጭ ናት

ሐዋርያው ጳውሎስ “የእግዚአብሔር ባለ ጠግነትና ጥበብ እውቀቱም እንዴት ጥልቅ ነው፤ ፍርዱ እንዴት የማይመረመር ነው፣ ለመንገዱም ፍለጋ የለውም” በማለት ተናግሯል። (ሮሜ 11:33) እንዲሁም ታማኙ ኢዮብ ይሖዋ አምላክ “ልቡ ጠቢብ” እንደሆነ ተናግሯል። (ኢዮብ 9:4) አዎን፣ የሰማይና የምድር ፈጣሪ በጥበቡ አቻ የለውም። ይህ ፈጣሪ ስለሰጠን ሕግ ወይም በጽሑፍ ስለሰፈረው ቃሉስ ምን ለማለት ይቻላል?

መዝሙራዊው እንዲህ ሲል ዘምሯል:- “የእግዚአብሔር ሕግ ፍጹም ነው፤ ነፍስን ይመልሳል፤ የእግዚአብሔር ምስክር የታመነ ነው ሕፃናትን ጠቢባን ያደርጋል። የእግዚአብሔር ሥርዓት ቅን ነው፣ ልብንም ደስ ያሰኛል፤ የእግዚአብሔር ትእዛዝ ብሩህ ነው፣ ዓይንንም ያበራል።” (መዝሙር 19:7, 8) የጥንት እስራኤላውያን ንጉሥ የነበረው ሰሎሞን የእነዚህን ቃላት እውነተኝነት ስለተገነዘበ እንዲህ ብሏል:- “የጠቢብ ትምህርት የሕይወት ምንጭ ናት፤ ሰውን በሞት ወጥመድ እንዳይያዝ ታደርገዋለች።” (ምሳሌ 13:14 አ.መ.ት) ሰሎሞን ከምሳሌ 13:14 በፊት ባሉት 13 ቁጥሮች ላይ በአምላክ ቃል ውስጥ የሚገኘው ምክር ሕይወታችንን ለማሻሻልና ከአደጋ ለመጠበቅ እንዴት እንደሚረዳን ተናግሯል።

ለመማር ፈቃደኞች ሁኑ

ምሳሌ 13:1 “ባለ አእምሮ ልጅ የአባቱን ተግሣጽ ይሰማል፤ ፌዘኛ ግን ተግሣጽን አይሰማም” ይላል። የአባት ተግሣጽ ቀላል ወይም ከባድ ሊሆን ይችላል። በመጀመሪያ በምክር መልክ የሚሰጥ ሲሆን ይህ ውጤት ካላስገኘ ግን ቅጣት ይከተላል። የአባቱን ተግሣጽ የሚሰማ ልጅ ግን ጠቢብ ይሆናል።

መጽሐፍ ቅዱስ ይሖዋ “የሚወደውን ይቀጣዋልና፣ የሚቀበለውንም ልጅ ሁሉ ይገርፈዋል” በማለት ይናገራል። (ዕብራውያን 12:5, 6) በሰማይ የሚኖረው አባታችን እኛን የሚገሥጽበት አንደኛው መንገድ በጽሑፍ በሰፈረው ቃሉ ማለትም በመጽሐፍ ቅዱስ አማካኝነት ነው። ቃሉን በአክብሮት የምናነብና ያነበብነውን በሥራ ላይ የምናውል ከሆነ ቃሉ ይገሥጸናል ሊባል ይችላል። ይሖዋ የሚነግረን የሚረባንን ስለሆነ ቃሉን በማንበባችን የምንጠቀመው እኛው ነን።—ኢሳይያስ 48:17

ስለ መንፈሳዊ ደህንነታችን የሚያስቡ የእምነት ባልንጀሮቻችንም በእርማት መልክ ተግሣጽ ሊሰጡን ይችላሉ። አንድ ሰው ከአምላክ ቃል ጋር የሚስማማ ጠቃሚ ምክር ቢሰጠን ሐሳቡን እርሱ እንዳመነጨው ሳይሆን ከታላቁ የእውነት ምንጭ ከይሖዋ እንደመጣ አድርገን ልንመለከተው እንችላለን። እንዲህ ካደረግንና ምክሩ አስተሳሰባችንን እንዲቀርጽልን፣ ስለ ቅዱሳን ጽሑፎች ያለንን ግንዛቤ እንዲያሰፋልን እንዲሁም አካሄዳችንን እንዲያስተካክልልን የምንፈቅድ ከሆነ ከተግሣጹ የምንጠቀም ከመሆናችንም በላይ ጠቢባን እንሆናለን። ከክርስቲያናዊ ስብሰባዎችና በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ ከተመሠረቱ ጽሑፎችም ተመሳሳይ ጥቅሞችን ማግኘት እንችላለን። በጽሑፍ ለሰፈሩትም ሆነ በቃል ለምናገኛቸው ትምህርቶች ተግባራዊ ምላሽ መስጠት ራሳችንን መገሠጽ የምንችልበት ግሩም መንገድ ነው።

በአንጻሩ ግን ፌዘኛ የሆነ ሰው የሚሰጠውን ተግሣጽ ለመቀበል ፈቃደኛ አይደለም። አንድ የማመሳከሪያ ጽሑፍ “ከማንም የተሻለ እውቀት እንዳለው ስለሚሰማው ከሌሎች ለመማር ፈቃደኛ አይደለም” ይላል። ከበድ ያለ ተግሣጽ ቢሰጠው እንኳን አይሰማም። የይሖዋ ተግሣጽ ትክክል እንዳልሆነ ማረጋገጥ ይችላል? ይሖዋ በፍጹም ተሳስቶ አያውቅም፤ ወደፊትም አይሳሳትም። ፌዘኛ ሰው ተግሣጽን አልቀበልም በማለቱ በራሱ ላይ ይፌዝበታል። ሰሎሞን ለመማር ፈቃደኛ መሆን የሚያስገኘውን ጥቅም በጥቂት የተመረጡ ቃላት ግሩም አድርጎ ገልጾታል።

አንደበታችሁን ጠብቁ!

የእስራኤል ንጉሥ ሰሎሞን አነጋገራችንን በአምላክ ቃል መምራት ያለውን አስፈላጊነት ለማሳየት አፍን ፍሬ ከሚያፈራ ዛፍ ጋር በማመሳሰል እንዲህ ብሏል:- “ሰው ከአፉ ፍሬ መልካምን ይበላል፤ የዓመፀኞች ነፍስ ግን ግፍን ትሻለች።” (ምሳሌ 13:2) የአፍ ፍሬ የተባሉት የምንናገራቸው ቃላት ናቸው። በመሆኑም ሰው በአንደበቱ የሚዘራውን መልሶ ያጭዳል። አንድ ምሑር እንዲህ ብለዋል:- “አንድ ሰው ከጎረቤቶቹ ጋር ወዳጃዊ የሆነ ቅርርብ ለመመሥረት ሲል በቅን መንፈስ የሚናገር ከሆነ መልካምን ይበላል፤ ማለትም ከጎረቤቶቹ ጋር አስደሳችና ሰላማዊ የሆነ ግንኙነት ይኖረዋል።” የዓመፀኛ ሰው ሁኔታ ግን ከዚህ የተለየ ነው። ግፍ ለመፈጸምና ሌሎችን ለመጉዳት ይፈልጋል። ምንጊዜም የሚያስበው ዓመፅን ስለሆነ ዓመፅን መልሶ ያጭዳል። በደጁ የሞት ወጥመድ ተጠምዷል።

ሰሎሞን ሲቀጥል “አፉን የሚጠብቅ ነፍሱን ይጠብቃል፤ ከንፈሩን የሚያሞጠሙጥ ግን ጥፋት ያገኘዋል” በማለት ይናገራል። (ምሳሌ 13:3) ሳያስቡ የሞኝነት ንግግር መናገር መጥፎ ስም ያሰጣል፣ ስሜት ይጎዳል፣ ከሌሎች ጋር ያለንን ዝምድና ያበላሻል አልፎ ተርፎም አካላዊ ጉዳት ሊያስከትል ይችላል። እያንዳንዱ ሰው ስለሚናገራቸው ቃላት በአምላክ ፊት ስለሚጠየቅ አንደበታችንን ካልተቆጣጠርነው የአምላክን ሞገስ ሊያሳጣን ይችላል። (ማቴዎስ 12:36, 37) በእርግጥም አንደበታችንን መግራት ከጥፋት ያድነናል። ታዲያ አንደበታችንን መቆጣጠር የምንችለው እንዴት ነው?

አንደኛው ቀላል መንገድ ብዙ አለማውራት ነው። መጽሐፍ ቅዱስ “በቃል ብዛት ውስጥ ኃጢአት ሳይኖር አይቀርም” ይላል። (ምሳሌ 10:19) ሌላው መንገድ ደግሞ ከመናገር በፊት ማሰብ ነው። አንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ጸሐፊ “እንደሚዋጋ ሰይፍ የሚለፈልፍ ሰው አለ” በማለት ተናግሯል። (ምሳሌ 12:18) አንድ ሰው ሳያስብ ዝም ብሎ የሚናገር ከሆነ እሱም ሆነ አድማጮቹ ሊጎዱ ይችላሉ። ስለሆነም መጽሐፍ ቅዱስ ‘የጻድቅ ልብ መልሱን ያስባል’ የሚል ጠቃሚ ምክር ይሰጠናል።—ምሳሌ 15:28

ትጉ ሠራተኞች ሁኑ

ሰሎሞን “የታካች ሰው ነፍስ ትመኛለች፤ አንዳችም አታገኝም፤ የትጉ ነፍስ ግን ትጠግባለች” ይላል። (ምሳሌ 13:4) አንድ የማመሳከሪያ ጽሑፍ እንዲህ ይላል:- “[ይህ ምሳሌ] ምኞት ብቻውን ከንቱ መሆኑንና ውጤት የሚያስገኘው ተግቶ መሥራት እንደሆነ ያሳያል። ሰነፍ ሰዎች የምኞታቸው ምርኮኞች ስለሆኑ ምንም የረባ ነገር አያገኙም።” የትጉህ ሰው ነፍስ ግን የፈለገችውን ስለምታገኝ ትጠግባለች።

ከተጠያቂነት ለመሸሽ ሲሉ ራሳቸውን ለይሖዋ ወስነው ከመጠመቅ ወደ ኋላ ስለሚሉ ሰዎችስ ምን ለማለት ይቻላል? በአምላክ አዲስ ዓለም ውስጥ ለመኖር ይመኙ ይሆናል። ይህን ምኞታቸውን ለማሳካት ግን ምን አድርገዋል? “ከታላቁ መከራ” በሕይወት የሚተርፉት በኢየሱስ ቤዛዊ መሥዋዕት የሚያምኑ፣ ራሳቸውን ለይሖዋ የወሰኑና ይህን ውሳኔያቸውን ለማሳየት የተጠመቁ ሰዎች ናቸው።—ራእይ 7:14, 15

እንዲሁም በጉባኤ ውስጥ በበላይ ተመልካችነት ለማገልገል ምን ብቃቶችን ማሟላት እንደሚያስፈልግ ተመልከት። ለዚህ መልካም ሥራ ለመብቃት መመኘት የሚያስመሰግን ከመሆኑም በላይ በቅዱሳን ጽሑፎች ውስጥ ተበረታቷል። (1 ጢሞቴዎስ 3:1) ይሁን እንጂ ምኞት ብቻውን በቂ አይደለም። ለዚህ ኃላፊነት ለመብቃት ተገቢውን ባሕርይና ችሎታ ማዳበር የሚያስፈልግ ሲሆን ይህ ደግሞ ትጋት የተሞላበት ጥረት ማድረግን ይጠይቃል።

ጽድቅ ጥበቃ ይሆናል

ጻድቅ ሰው አምላክን የሚያስደስቱ ባሕርያትን የሚያንጸባርቅ ከመሆኑም በላይ እውነትን ይናገራል። ውሸት በይሖዋ ሕግ የተከለከለ እንደሆነ ያውቃል። (ምሳሌ 6:16-19፤ ቆላስይስ 3:9) በዚህ ረገድ ሰሎሞን እንዲህ ይላል:- “ጻድቅ ሐሰትን ይጠላል፤ ኀጥእ ግን ያሳፍራል ያስነውራልም።” (ምሳሌ 13:5) ጻድቅ ሰው ውሸት ባለመናገሩ ብቻ አይረካም፤ ውሸትን አጥብቆ ይጠላል። የቱንም ያህል በቅን ልቦና የተነገረ ቢሆን ውሸት በሰዎች መካከል ያለውን ግንኙነት እንደሚያበላሽ ያውቃል። በተጨማሪም ውሸት የሚናገር ሰው ተአማኒነቱን ያጣል። ክፉ ሰው ውሸት በመናገር ወይም ተገቢ ያልሆኑ ሌሎች ነገሮችን በማድረግ በራሱ ላይ ውርደት ያመጣል።

ጠቢቡ ንጉሥ ሰሎሞን በአምላክ ፊት ትክክል የሆነውን ማድረግ የሚያስገኘውን ጥቅም ሲናገር እንዲህ ይላል:- “በመንገዱ ያለ ነውር የሚሄደውን ጽድቅ ይጠብቀዋል፤ ኃጢአት ግን ኃጢአተኛውን ይጥለዋል።” (ምሳሌ 13:6) ጽድቅ እንደ ምሽግ ሆኖ አንድን ሰው ከአደጋ የሚጠብቀው ሲሆን ኃጢአት ግን ለጥፋት ይዳርገዋል።

አስመሳይ አትሁኑ

የእስራኤል ንጉሥ ሰሎሞን የሰውን ባሕርይ ጠንቅቆ ስለሚያውቅ እንዲህ ይላል:- “ራሱን ባለጠጋ የሚያስመስል ሰው አለ፣ ነገር ግን አንዳች የለውም፤ ራሱን ድሃ የሚያስመስል አለ፣ ነገር ግን እጅግ ባለጠግነት አለው።” (ምሳሌ 13:7) አንድ ሰው ከላይ እንደሚታየው ሆኖ ላይገኝ ይችላል። አንዳንድ ድሃ ሰዎች የሰውን ትኩረት ለመሳብ፣ የተሳካላቸው ለማስመሰል ወይም የሌሎችን ከበሬታ ለማትረፍ ሀብታም መስለው ለመታየት ይጥሩ ይሆናል። ሀብታም የሆኑ ሰዎች ደግሞ ሀብት እንዳላቸው እንዳይታወቅ ድሃ ለመምሰል ይሞክሩ ይሆናል።

ሀብታም ለመምሰል መሞከርም ሆነ ሀብትን መደበቅ ተገቢ አይደለም። የገቢ ምንጫችን ዝቅተኛ ሆኖ ሳለ ሀብታም ለመምሰል የቅንጦት ዕቃዎችን የምንገዛ ከሆነ ለእኛም ሆነ ለቤተሰባችን አስፈላጊ ለሆነ ነገር የምናውለውን ገንዘብ ሊያሳጣን ይችላል። እንዲሁም አንድ ሰው ሀብታም ሆኖ ሳለ ድሃ ለመምሰል መጣሩ ንፉግ ሊያስብለው፣ ለራሱ ያለውን አክብሮት ሊቀንስበትና መስጠት የሚያስገኘውን ደስታ ሊያሳጣው ይችላል። (ሥራ 20:35) ራሳችንን ሆነን መኖር የተሻለ ሕይወት ያስገኝልናል።

አኗኗራችሁን ቀላል አድርጉ

ሰሎሞን “ለሰው ነፍስ ቤዛው ሀብቱ ነው፤ ድሀ ግን ተግሣጽን አይሰማም” ይላል። (ምሳሌ 13:8) ከዚህ ምሳሌ ምን ትምህርት እናገኛለን?

ሀብታም መሆን የሚያስገኛቸው ጥቅሞች ቢኖሩትም ለደስታ ዋስትና ይሆናል ማለት ግን አይደለም። በምንኖርበት አስቸጋሪ ዘመን ሀብታሞች ብዙውን ጊዜ ለገንዘባቸው ሲባል እነርሱ ራሳቸው ወይም የቤተሰባቸው አባላት ይጠለፋሉ። አንዳንድ ጊዜ ሀብታሙ ሰው ገንዘብ ከፍሎ የራሱን ወይም የቤተሰቡን ሕይወት ማዳን ይችል ይሆናል። ብዙውን ጊዜ ግን የተጠለፈው ሰው ይገደላል። ሀብታም ሰው ሕይወቱ ምንጊዜም አደጋ ያጠላበት ነው።

ብዙ ሀብት የሌለው ሰው ግን እንዲህ ያለ ሁኔታ ይደርስብኛል ብሎ አይጨነቅም። የሀብታሞችን ያህል ተመችቶትና ተንደላቅቆ ባይኖርም በአጋቾች ዓይን ውስጥ እገባለሁ ብሎ አይፈራም። ኑሯችንን ቀላል ማድረግ እንዲሁም ሀብት በማሳደድ ጊዜያችንንና ጉልበታችንን አለማባከን ያለው ጥቅም ይህ ነው።—2 ጢሞቴዎስ 2:4

‘በብርሃን’ ደስ ይበላችሁ

ሰሎሞን ነገሮችን በይሖዋ መንገድ መሥራት ያለውን ጥቅም ሲገልጽ “ሁልጊዜ ለጻድቃን ብርሃን ነው፤ የኀጥኣን መብራት ግን ይጠፋል” ይላል።—ምሳሌ 13:9

መብራት የሕይወት ጎዳናችንን ለማብራት የምንታመንበትን መመሪያ ያመለክታል። ‘የአምላክ ቃል ለጻድቅ ሰው ለእግሩ መብራት፣ ለመንገዱም ብርሃን ነው።’ (መዝሙር 119:105) መጽሐፍ ቅዱስ የፈጣሪን የማይነጥፍ እውቀትና ጥበብ ይዟል። ስለ አምላክ ፈቃድና ዓላማ ያለን ግንዛቤ ይበልጥ በጨመረ መጠን በሕይወታችን የምንመራበት መንፈሳዊ ብርሃን እየደመቀ ይሄዳል። ይህ ደግሞ በጣም የሚያስደስት ነው! ‘በውሸት እውቀት’ በተባለው ዓለማዊ ጥበብ መታለል አይኖርብንም።—1 ጢሞቴዎስ 6:20፤ 1 ቆሮንቶስ 1:20፤ ቆላስይስ 2:8

ክፉ ሰው ግን መብራቱ ምንም ያህል ቢደምቅ ወይም የቱንም ያህል ሀብታም መስሎ ቢታይ የኋላ ኋላ መብራቱ ይጠፋል። በጨለማ ውስጥ ሲዳክር እግሮቹ መሰናከላቸው አይቀርም። ከዚህም በላይ የወደፊት ‘ተስፋ አይኖረውም።’—ምሳሌ 24:20

ይሁን እንጂ አንድ ሁኔታ ሲያጋጥመን መውሰድ ስላለብን እርምጃ እርግጠኞች ካልሆንን ምን ማድረግ ይኖርብናል? እርምጃ የመውሰዱ ኃላፊነት የእኛ መሆኑን ከተጠራጠርንስ? ምሳሌ 13:10 “በትዕቢት ጠብ ብቻ ይሆናል” በማለት ያስጠነቅቃል። ስለሁኔታው በቂ እውቀት ሳይኖረን ወይም ያለቦታችን አንድ ዓይነት እርምጃ መውሰድ የትዕቢት መግለጫ ሲሆን ይህም ከሌሎች ጋር ያለንን ግንኙነት ያሻክረዋል። እንዲህ ዓይነት ሁኔታ ሲያጋጥመን ስለ ጉዳዩ በቂ ግንዛቤና ማስተዋል ያላቸውን ሰዎች ማማከሩ የተሻለ አይሆንም? ጠቢቡ ንጉሥ ሰሎሞን “ጥበብ ግን ምክርን በሚቀበሉ ዘንድ ናት” በማለት ተናግሯል።

ከንቱ ነገርን ተስፋ አታድርጉ

ገንዘብ ለጠቃሚ ዓላማ ሊውል ይችላል። በጉስቁልና ወይም በድህነት ከመቆራመድ ይልቅ በቂ ገንዘብ እያገኙ መኖር የተሻለ ነው። (መክብብ 7:11, 12) ሕገ ወጥ በሆነ መንገድ የሚገኝ ሀብት ግን መቅኖ የለውም። ሰሎሞን “በችኰላ የምትከማች ሀብት ትጐድላለች፤ ጥቂት በጥቂት የተከማቸች ግን ትበዛለች” በማለት ያስጠነቅቃል።—ምሳሌ 13:11

ቁማርን እንደምሳሌ አድርገን እንመልከት። ቁማርተኛ ሰው የበለጠ አገኛለሁ በሚል ተስፋ ጥሮ ግሮ ያገኘውን ገንዘብ ቁማር ይጫወትበታል። ብዙውን ጊዜ ቁማርተኞች እንዲህ የሚያደርጉት ለቤተሰባቸው የሚያስፈልገውን ነፍገው ነው። ቁማርተኛው ቢያሸንፍ በገንዘቡ ምን ያደርግበታል? ያለ ድካም የተገኘ ገንዘብ ስለሆነ በአድናቆት አይመለከተውም። በተጨማሪም በቁማር ያገኘውን ገንዘብ በአግባቡ ለመጠቀም ችሎታው ላይኖረው ይችላል። ገንዘቡን ባገኘበት ፍጥነት አባክኖ ይጨርሰዋል። በአንጻሩ ግን ተግቶ በመሥራት ቀስ በቀስ የተከማቸ ሀብት እያደር እየጨመረ የሚሄድ ሲሆን ለመልካም ዓላማም ሊውል ይችላል።

ሰሎሞን “የምትዘገይ ተስፋ ልብን ታሳዝናለች፤ የተገኘች ፈቃድ ግን የሕይወት ዛፍ ናት” ይላል። (ምሳሌ 13:12) አንድ ነገር ጠብቀን ሳይፈጸም ሲቀር ከልብ እናዝናለን። እንዲህ ያለ ሁኔታ በየዕለቱ ያጋጥመናል። በመጽሐፍ ቅዱስ በተመሠረተ ተስፋ ላይ እምነት የምንጥል ከሆነ ግን እንዲህ ያለ ሁኔታ አያጋጥመንም። እነዚህ ተስፋዎች እንደሚፈጸሙ ሙሉ እምነት ሊኖረን ይችላል። የሚዘገይ ቢመስለንም እንኳን አናዝንም።

ለምሳሌ ያህል፣ የአምላክ አዲስ ዓለም በቅርቡ እንደሚመጣ እናውቃለን። (2 ጴጥሮስ 3:13) አምላክ የሰጣቸው ተስፋዎች ፍጻሜያቸውን የሚያገኙበትን ጊዜ በጉጉት እንጠባበቃለን። እስከዚያ ድረስ ግን ጊዜውን ‘በጌታ ሥራ’ ይበልጥ ለመካፈል፣ የእምነት ባልንጀሮቻችንን ለማበረታታትና ከይሖዋ ጋር ያለንን ዝምድና ለማጠናከር ብንጠቀምበትስ? እንዲህ ብናደርግ ተስፋው እንደዘገየ ተሰምቶን ከማዘን ይልቅ በደስታ እንሞላለን። (1 ቆሮንቶስ 15:58፤ ዕብራውያን 10:24, 25፤ ያዕቆብ 4:8) ለረዥም ጊዜ ተመኝተነው የተፈጸመልን ነገር እንደ ሕይወት ዛፍ የሚያበረታታና መንፈስን የሚያድስ ነው።

የአምላክ ትምህርት የሕይወት ምንጭ ነው

ምሳሌ 13:13 ለአምላክ መታዘዝ አስፈላጊ መሆኑን በምሳሌ ሲያስረዳ እንዲህ ይላል:- “ትእዛዝን የሚያቃልል በትእዛዝ ተይዞ ይጠፋል፤ ትእዛዝን የሚፈራ ግን በደኅንነት ይኖራል።” የአምላክን ትእዛዛት የማንጠብቅ ከሆነ የምናጣው ነገር ይኖራል። ይህ ምን ይሆን?

“የጠቢብ ትምህርት የሕይወት ምንጭ ናት፤ ሰውን በሞት ወጥመድ እንዳይያዝ ታደርገዋለች።” (ምሳሌ 13:14 አ.መ.ት) የጥበበኛውን አምላክ የይሖዋን ሕግ ችላ ማለት የተሻለና ረዥም ሕይወት ለመኖር የሚረዳንን መመሪያ አልቀበልም እንደማለት ይቆጠራል። ይህ ደግሞ ትልቅ ኪሳራ ነው! እንግዲያው ለአምላክ ቃል ትኩረት መስጠትና አስተሳሰባችንን፣ ንግግራችንንና ድርጊታችንን እንዲቀርጸው መፍቀድ ለሁላችንም የጥበብ እርምጃ ነው።—2 ቆሮንቶስ 10:5፤ ቆላስይስ 1:10

[በገጽ 23 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ቅዱስ ጽሑፋዊ ምክርን ተቀብለን ተግባራዊ የምናደርግ ከሆነ ራሳችንን እንደምንገስጽ ያሳያል

[በገጽ 24 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

“የጻድቅ ልብ መልሱን ያስባል”

[በገጽ 24 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

‘በጌታ ሥራ’ መጠመድ በደስታ እንድንሞላ ያደርጋል