በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ለጽድቅ ሲባል መሰደድ

ለጽድቅ ሲባል መሰደድ

ለጽድቅ ሲባል መሰደድ

“ስለ ጽድቅ የሚሰደዱ ብፁዓን ናቸው።”—ማቴዎስ 5:10

1. ኢየሱስ ጴንጤናዊው ጲላጦስ ፊት የቀረበው ለምን ነበር? ምን ብሎስ ተናግሯል?

 “እኔ ለእውነት ልመሰክር ስለዚህ ተወልጃለሁ ስለዚህም ወደ ዓለም መጥቻለሁ።” (ዮሐንስ 18:37) ኢየሱስ ይህን የተናገረው በሮማዊው የይሁዳ ገዥ በጴንጤናዊው ጲላጦስ ፊት ቀርቦ በነበረበት ወቅት ነው። ኢየሱስ በዚያ ሊገኝ የቻለው በራሱ ፍላጎት ሄዶ ወይም ደግሞ ጲላጦስ ጥሪ አቅርቦለት አይደለም። ከዚህ ይልቅ ጲላጦስ ፊት የቀረበው የአይሁድ ሃይማኖታዊ መሪዎች በሞት የሚያስቀጣው ጥፋት ሠርቷል ብለው በሐሰት ስለወነጀሉት ነው።​—⁠ዮሐንስ 18:​29-31

2. ኢየሱስ ምን አደረገ? በመጨረሻስ ምን ደረሰበት?

2 ጲላጦስ ሊፈታውም ሆነ ሊገድለው ሥልጣን እንዳለው ኢየሱስ አሳምሮ ያውቅ ነበር። (ዮሐንስ 19:​10) ይሁንና ለጲላጦስ ስለ አምላክ መንግሥት በድፍረት ከመናገር ወደኋላ አላለም። ኢየሱስ ሕይወቱ አደጋ ላይ የወደቀ ቢሆንም አጋጣሚውን ተጠቅሞ በይሁዳ ላለው ከፍተኛ የመንግሥት ባለ ሥልጣን ምሥክርነት ሰጥቷል። ኢየሱስ ስለ አምላክ መንግሥት ቢመሠክርም እንደ ጥፋተኛ ተቆጥሮ በመከራ እንጨት ላይ በአሰቃቂ ሁኔታ ሰማዕት ሆኖ ሞቷል።​—⁠ማቴዎስ 27:​24-26፤ ማርቆስ 15:​15፤ ሉቃስ 23:​24, 25፤ ዮሐንስ 19:​13-16

ምሥክር ወይስ ሰማዕት?

3. “ሰማዕት” የሚለው ቃል ምን ትርጉም ነበረው? በዛሬው ጊዜስ ምን ትርጉም ይዟል?

3 በዛሬው ጊዜ ብዙ ሰዎች ለአንድ ዓላማ ሰማዕት የሚሆንን ሰው አክራሪ ወይም ጽንፈኛ እንደሆነ አድርገው ይቆጥሩታል። ላመኑበት ነገር በተለይ ደግሞ ለሃይማኖታዊ እምነታቸው ለመሞት ፈቃደኛ የሚሆኑ ሰዎች አብዛኛውን ጊዜ አሸባሪዎች ወይም ደግሞ ለኅብረተሰቡ ጠንቅ እንደሆኑ ተደርገው በጥርጣሬ ዓይን ይታያሉ። ይሁን እንጂ ሰማዕት የሚለው ቃል ከግዕዝ (ሰምዐ) የተገኘ ሲሆን “መሰከረ” የሚል ትርጉም ነበረው። ቃሉ፣ የሚያምንበት ነገር እውነት መሆኑን ምናልባትም ችሎት ፊት ቀርቦ ሊሆን ይችላል የምስክርነት ቃል የሚሰጥን ሰው ያመለክታል። ከጊዜ በኋላ ግን ሰማዕት የሚለው ቃል “ምሥክርነት በመስጠቱ ምክንያት ሕይወቱን አሳልፎ የሚሰጥ ሰው” ወይም ደግሞ ሕይወቱን መሥዋዕት በማድረግ ምሥክርነት የሚሰጥ የሚል ትርጉም ያዘ።

4. ኢየሱስ ሰማዕት ነው ሊባል የሚችልበት ዋነኛው መንገድ ምንድን ነው?

4 ኢየሱስ በዋነኝነት ሰማዕት የነበረው ቃሉ ቀደም ሲል በነበረው ትርጉም መሠረት ነው። ለጲላጦስ እንደነገረው ወደ ምድር የመጣው ‘ለእውነት ለመመስከር’ ነበር። እርሱ ላቀረበው ምሥክርነት ሰዎች የተለያየ ምላሽ ሰጥተዋል። ከተራው ሕዝብ መካከል አንዳንዶች በሰሙትና ባዩት ነገር በጥልቅ በመነካታቸው በኢየሱስ ላይ እምነት አሳድረዋል። (ዮሐንስ 2:​23፤ 8:​30) በአንጻሩ ደግሞ ሕዝቡን በአጠቃላይ በተለይ ደግሞ የሃይማኖት መሪዎቹን በቁጣ እንዲነሳሱ አድርጓቸዋል። ኢየሱስ መሲሕነቱን አንቀበልም ያሉ የስጋ ዘመዶቹን “ዓለም እናንተን ሊጠላ አይቻለውም፤ እኔ ግን ሥራው ክፉ መሆኑን እመሰክርበታለሁና እኔን ይጠላኛል” ብሏቸዋል። (ዮሐንስ 7:7) ኢየሱስ እውነትን በመመሥከሩ ከብሔሩ መሪዎች ጥላቻ ያተረፈ ከመሆኑም በላይ በመጨረሻም ለሞት ተዳርጓል። በእርግጥም “የታመነውና እውነተኛው ምስክር (ሰምዐ)” ነበር።​—⁠ራእይ 3:​14

“የተጠላችሁ ትሆናላችሁ”

5. ኢየሱስ አገልግሎቱን በጀመረበት ወቅት ስደትን በተመለከተ ምን ተናግሯል?

5 ኢየሱስ ራሱ ከባድ ስደት የደረሰበት ከመሆኑም በላይ ተከታዮቹም ተመሳሳይ ነገር እንደሚያጋጥማቸው አስቀድሞ አስጠንቅቋቸዋል። አገልግሎቱን በጀመረበት ወቅት በተራራ ስብከቱ ላይ ተከታዮቹን እንዲህ ብሏቸው ነበር:- “ስለ ጽድቅ የሚሰደዱ ብፁዓን ናቸው፣ መንግሥተ ሰማያት የእነርሱ ናትና። ሲነቅፉአችሁና ሲያሳድዱአችሁ በእኔም ምክንያት ክፉውን ሁሉ በውሸት ሲናገሩባችሁ ብፁዓን ናችሁ። ዋጋችሁ በሰማያት ታላቅ ነውና ደስ ይበላችሁ፣ ሐሤትም አድርጉ።”​—⁠ማቴዎስ 5:10-12

6. ኢየሱስ 12 ሐዋርያቱን በላከበት ጊዜ ምን በማለት አስጠንቅቋቸዋል?

6 ከጊዜ በኋላ ኢየሱስ 12 ሐዋርያቱን ሲልክ እንዲህ ብሏቸው ነበር:- “ወደ ሸንጎ አሳልፈው ይሰጡአችኋል፣ በምኵራቦቻቸውም ይገርፉአችኋልና ከሰዎች ተጠበቁ፤ ለእነርሱና ለአሕዛብም ምስክር እንዲሆን፣ ስለ እኔ ወደ ገዥዎች ወደ ነገሥታትም ትወሰዳላችሁ።” ሆኖም ደቀ መዛሙርቱን የሚያሳድዷቸው የሃይማኖት መሪዎች ብቻ አይደሉም። ኢየሱስ እንዲህ ብሎም ተናግሯል:- “ወን​ድምም ወንድሙን አባትም ልጁን ለሞት አሳልፎ ይሰጣል፣ ልጆችም በወላጆቻቸው ላይ ይነሣሉ ይገድሉአቸውማል። በሁሉም ስለ ስሜ የተጠላችሁ ትሆናላችሁ፤ እስከ መጨረሻ የሚጸና ግን እርሱ ይድናል።” (ማቴዎስ 10:17, 18, 21, 22) በመጀመሪያው መቶ ዘመን የነበሩ ክርስቲያኖች ታሪክ ኢየሱስ የተናገረው ነገር እውነት መሆኑን አረጋግጧል።

በታማኝነት በመጽናት ያስመዘገቡት ታሪክ

7. እስጢፋኖስን ለሰማዕትነት ያበቃው ምንድን ነው?

7 ከኢየሱስ ሞት በኋላ ብዙም ሳይቆይ እስጢፋኖስ ለእውነት በመመሥከሩ ምክንያት ለመሞት የመጀመሪያው ክርስቲያን ሆኗል። “ጸጋንና ኃይልን ተሞልቶ በሕዝቡ መካከል ድንቅንና ታላቅ ምልክትን ያደርግ ነበር።” ሃይማኖታዊ ጠላቶቹ “ይናገርበት የነበረውንም ጥበብና መንፈስ ይቃወሙ ዘንድ አልቻሉም።” (ሥራ 6:8, 10) ካደረባቸው ቅንዓት የተነሳ እስጢፋኖስን የአይሁዶች ከፍተኛ ፍርድ ቤት በሆነው በሳንሄድሪን አቀረቡት። በፍርድ ቤቱ በሐሰት የወነጀሉትን ሰዎች የተጋፈጠ ከመሆኑም በላይ ኃይለኛ መልእክት ያለው ምሥክርነት ሰጠ። በመጨረሻ ግን የእስጢፋኖስ ጠላቶች ይህን ታማኝ ምሥክር ገደሉት።​—⁠ሥራ 7:​59, 60

8. በኢየሩሳሌም የነበሩ ደቀ መዛሙርት ከእስጢፋኖስ ሞት በኋላ ለደረሰባቸው ስደት ምን ምላሽ ሰጡ?

8 የእስጢፋኖስን መገደል ተከትሎ “በኢየሩሳሌም ባለች ቤተ ክርስቲያን ላይ ታላቅ ስደት ሆነ፤ ሁሉም ከሐዋርያትም በቀር ወደ ይሁዳና ወደ ሰማርያ አገሮች ተበተኑ።” (ሥራ 8:1) ስደት ክርስቲያኖች መስበካቸውን እንዲያቆሙ አድርጓቸዋል? ከዚህ በተቃራኒ “የተበተኑትም ቃሉን እየሰበኩ ዞሩ” በማለት ዘገባው ይናገራል። (ሥራ 8:4) ከዚያ ቀደም ሐዋርያው ጴጥሮስ “ከሰው ይልቅ ለእግዚአብሔር ልንታዘዝ ይገባል” ሲል የተናገረው ዓይነት አቋም ነበራቸው። (ሥራ 5:29) እነዚያ ታማኝና ደፋር ደቀ መዛሙርት ስደት ቢደርስባቸውም ለእውነት መመሥከራቸውን አላቆሙም። ይህን ያደረጉት እውነትን መመሥከራቸው የባሰ ሥቃይ ሊያስከትልባቸው እንደሚችል እያወቁ ነው።​—⁠ሥራ 11:​19-21

9. በኢየሱስ ተከታዮች ላይ የሚደርሰው ስደት የቀጠለው እንዴት ነው?

9 በእርግጥም የሚደርስባቸው ስደት ፈጽሞ ጋብ አላለም። በመጀመሪያ፣ የእስጢፋኖስን በድንጋይ መወገር የደገፈውና የዓይን ምሥክር የነበረው ሳውል “የጌታን ደቀ መዛሙርት እንዲገድላቸው ገና እየዛተ ወደ ሊቀ ካህናት ሄደ፣ በዚህ መንገድ ያሉትንም ሰዎች ወንዶችንም ሴቶችንም ቢያገኝ፣ እያሰረ ወደ ኢየሩሳሌም ያመጣቸው ዘንድ በደማስቆ ላሉት ምኵራቦች ደብዳቤ ከእርሱ ለመነ” የሚል ዘገባ ሰፍሯል። (ሥራ 9:1, 2) ከዚያ በመቀጠል ደግሞ በ44 እዘአ ገደማ “ንጉሡ ሄሮድስ መከራ ያጸናባቸው ዘንድ ከቤተ ክርስቲያኑ በአንዳንዶቹ ላይ እጁን ጫነባቸው። የዮሐንስንም ወንድም ያዕቆብን በሰይፍ ገደለው።”​—⁠ሥራ 12:1, 2

10. ክርስቲያኖች ስለደረሰባቸው ስደት የሐዋርያት ሥራ እና የራእይ መጻሕፍት ምን ዘገባ ይዘዋል?

10 የተቀረው የሐዋርያት ሥራ መጽሐፍ በፊት አሳዳጅ የነበረው በኋላ ግን ሐዋርያ የሆነውን ጳውሎስን የመሳሰሉ ታማኝ ክርስቲያኖች በጽናት የተወጡትን ፈተና፣ እስራትና ስደት የሚዘግብ የማይፋቅ ታሪክ ይዟል። ጳውሎስ በሮማው ንጉሠ ነገሥት በኔሮ ትእዛዝ በ65 እዘአ ሰማዕት ሆኖ እንደተገደለ ይገመታል። (2 ቆሮንቶስ 11:​23-27፤ 2 ጢሞቴዎስ 4:​6-8) በመጨረሻም፣ አረጋዊው ሐዋርያ ዮሐንስ “ስለ እግዚአብሔር ቃልና ስለ ኢየሱስ ምስክር” ፍጥሞ በምትባል ደሴት ታስሮ እንደነበር በመጀመሪያው መቶ ዘመን መገባደጃ በተጻፈው የራእይ መጽሐፍ ላይ ተገልጿል። በተጨማሪም የራእይ መጽሐፍ በጴርጋሞን ‘ስለተገደለው ስለታመነው ምስክር ስለ አንቲጳስ’ ይናገራል።​—⁠ራእይ 1:​9፤ 2:​13

11. ኢየሱስ ስደትን በተመለከተ የተናገረው ሐሳብ ትክክል መሆኑን የመጀመሪያዎቹ ክርስቲያኖች ሕይወት የሚያረጋግጠው እንዴት ነው?

11 ይህ ሁሉ ኢየሱስ ለደቀ መዛሙርቱ “እኔን አሳደውኝ እንደ ሆኑ እናንተን ደግሞ ያሳድዱአችኋል” ሲል የተናገረው ቃል እውነት መሆኑን ያረጋግጣል። (ዮሐንስ 15:20) የቀድሞዎቹ ታማኝ ክርስቲያኖች ጌታቸው ኢየሱስ ክርስቶስ “በኢየሩሳሌምም በይሁዳም ሁሉ በሰማርያም እስከ ምድር ዳርም ድረስ ምስክሮቼ ትሆናላችሁ” በማለት የሰጣቸውን ተልእኮ ለመፈጸም ሲሉ ለመደብደብም ሆነ ለአውሬ ለመሰጠት ወይም በሌላ በማንኛውም መንገድ ከሁሉ የከፋውን ፈተና ለመጋፈጥ ማለትም ለመሞት ፈቃደኛ ነበሩ።​—⁠ሥራ 1:8

12. በክርስቲያኖች ላይ የሚደርሰው ስደት አብቅቷል ብለን ማሰብ የሌለብን ለምንድን ነው?

12 ማንኛውም ሰው ቢሆን በኢየሱስ ተከታዮች ላይ የደረሰው እንዲህ ዓይነቱ ግፍ ድሮ ቀርቷል ብሎ የሚያስብ ከሆነ በጣም ተሳስቷል። ቀደም ሲል እንዳየነው ብዙ መከራ ያሳለፈው ጳውሎስ “በእውነትም በክርስቶስ ኢየሱስ እግዚአብሔርን እየመሰሉ ሊኖሩ የሚወዱ ሁሉ ይሰደዳሉ” ሲል ጽፏል። (2 ጢሞቴዎስ 3:12) ስደትን በተመለከተ ጴጥሮስ እንዲህ ብሏል:- “የተጠራችሁለት ለዚህ ነውና፤ ክርስቶስ ደግሞ ፍለጋውን እንድትከተሉ ምሳሌ ትቶላችሁ ስለ እናንተ መከራን ተቀብሎአልና።” (1 ጴጥሮስ 2:21) እስከዚህ ሥርዓት ‘የመጨረሻ ቀን’ ድረስ የይሖዋ ሕዝቦች የጥላቻና የስደት ዒላማ መሆናቸው አላቆመም። (2 ጢሞቴዎስ 3:​1) አምባገነናዊ አገዛዝ በሰፈነባቸውም ሆነ ዲሞክራሲያዊ መርሕ በሚከተሉ አገሮች፣ በየትኛውም የዓለም ክፍል የሚኖሩ የይሖዋ ምሥክሮች በሆነ ወቅት ላይ በግለሰብ ደረጃም ይሁን በቡድን ስደት ደርሶባቸዋል።

የሚጠሉትና የሚሰደዱት ለምንድን ነው?

13. በዚህ ዘመን ያሉ የይሖዋ አገልጋዮች ስደትን በተመለከተ መዘንጋት የሌለባቸው ነገር ምንድን ነው?

13 በዛሬው ጊዜ አብዛኞቻችን የመስበክ እንዲሁም በሰላም የመሰብሰብ አንጻራዊ ነፃነት ያለን ቢሆንም መጽሐፍ ቅዱስ “የዚች ዓለም መልክ አላፊ ነው” ሲል የሰጠውን ማሳሰቢያ ልብ ማለት አለብን። (1 ቆሮንቶስ 7:​31) ሁኔታዎች በድንገት ስለሚለወጡ በአእምሮ፣ በስሜትና በመንፈሳዊ ሁኔታ ዝግጁ ካልሆንን በቀላሉ ልንወድቅ እንችላለን። ታዲያ ራሳችንን ለመጠበቅ ምን ማድረግ እንችላለን? ትልቁ መከላከያችን ሰላም ወዳድና ሕግ አክባሪ የሆኑ ክርስቲያኖች የሚጠሉትና የሚሰደዱት ለምን እንደሆነ በአእምሯችን መያዛችን ነው።

14. ጴጥሮስ ክርስቲያኖች ስደት ይደርስባቸው የነበረው ለምን እንደሆነ ለማስረዳት ምን ብሏል?

14 ሐዋርያው ጴጥሮስ ክርስቲያኖች በመላው የሮማ ግዛት መከራና ስደት ይደርስባቸው በነበረበት ወቅት በጻፈው የመጀመሪያ ደብዳቤው ላይ (በ62-64 እዘአ ገደማ) ስለዚህ ጉዳይ ጠቅሷል። “ወዳጆች ሆይ፣ በእናንተ መካከል እንደ እሳት ሊፈትናችሁ ስለሚሆነው መከራ ድንቅ ነገር እንደ መጣባችሁ አትደነቁ” ብሏል። ጴጥሮስ ሐሳቡን ይበልጥ ግልጽ ለማድረግ አክሎ እንዲህ ብሏል:- “ከእናንተ ማንም ነፍሰ ገዳይ ወይም ሌባ ወይም ክፉ አድራጊ እንደሚሆን ወይም በሌሎች ጉዳይ እንደሚገባ ሆኖ መከራን አይቀበል፤ ክርስቲያን እንደሚሆን ግን መከራን ቢቀበል ስለዚህ ስም እግዚአብሔርን ያመስግን እንጂ አይፈር።” መከራ እየደረሰባቸው ያለው ክፉ ነገር በመሥራታቸው ሳይሆን በክርስቲያንነታቸው ምክንያት መሆኑን ተናግሯል። በአካባቢያቸው እንዳሉት ሰዎች ‘በመዳራት ብዛት’ ቢዘፈቁ ኖሮ በእነርሱ ዘንድ ተቀባይነትና ተወዳጅነት ባገኙ ነበር። እንደ እውነቱ ከሆነ ግን መከራ የደረሰባቸው የክርስቶስ ተከታዮች እንደመሆናቸው መጠን የሚጠበቅባቸውን ለማሟላት ጥረት በማድረጋቸው ነው። በዛሬው ጊዜ እውነተኛ ክርስቲያኖችም ተመሳሳይ ሁኔታ ይደርስባቸዋል።​—⁠1 ጴጥሮስ 4:​4, 12, 15, 16

15. በዛሬው ጊዜ የይሖዋ ምሥክሮች የሚያጋጥሟቸው ተቃራኒ የሆኑ ሁለት ነገሮች ምንድን ናቸው?

15 በበርካታ የዓለም ክፍሎች የይሖዋ ምሥክሮች በአውራጃ ስብሰባዎችና በግንባታ ሥራዎች ላይ በሚያሳዩት አንድነትና ትብብር፣ በሐቀኝነታቸውና በትጋታቸው፣ በአርዓያነት በሚጠቀሰው የሥነ ምግባር አቋማቸውና የቤተሰብ ሕይወታቸው አልፎ ተርፎም ሥርዓታማ በሆነው አለባበሳቸውና ባሕርያቸው በይፋ ይመሰገናሉ። a በአንጻሩ ደግሞ ይህ ጽሑፍ እስከተዘጋጀበት ጊዜ ድረስ 28 በሚያክሉ አገሮች ውስጥ ሥራቸው ሙሉ በሙሉ የታገደ ወይም ገደብ የተጣለበት ከመሆኑም በላይ ብዙ የይሖዋ ምሥክሮች በእምነታቸው ምክንያት አካላዊ ሥቃይና የንብረት ጥፋት ይደርስባቸዋል። በመልካም ሥነ ምግባራቸው የሚታወቁት የይሖዋ ምሥክሮች እንዲህ ዓይነት በደል የሚፈጸምባቸው ለምንድን ነው? አምላክስ ይህ እንዲደርስ የሚፈቅደው ለምንድን ነው?

16. አምላክ ሕዝቦቹ መከራ እንዲደርስባቸው የሚፈቅድበት ዋነኛ ምክንያት ምንድን ነው?

16 በመጀመሪያ ደረጃ ምሳሌ 27:​11 ላይ የሚገኙትን “ልጄ ሆይ፣ ጠቢብ ሁን፣ ልቤንም ደስ አሰኘው፣ ለሚሰድበኝ መልስ መስጠት ይቻለኝ ዘንድ” የሚሉትን ቃላት ማስታወስ ይኖርብናል። አዎን፣ ጉዳዩ ዘመናት ካስቆጠረው የአጽናፈ ዓለም ሉዓላዊ ገዥነት ጥያቄ ጋር የተያያዘ ነው። ባለፉት መቶ ዘመናት ሁሉ ይሖዋን በታማኝነት የደገፉ አገልጋዮቹ ያስመዘገቡት በጣም ብዙ ማስረጃ ቢኖርም ሰይጣን በጻድቁ ኢዮብ ዘመን እንዳደረገው ሁሉ ይሖዋን መሳደቡን አላቆመም። (ኢዮብ 1:​9-11፤ 2:​4, 5) በምድር ዙሪያ የሚገኙ ታማኝ ተገዥዎችንና ተወካዮችን ያቀፈው የአምላክ መንግሥት በተቋቋመበት በአሁኑ ጊዜ ሰይጣን የግድድሩን ትክክለኛነት ለማረጋገጥ ከመቼውም ጊዜ ይበልጥ የጠነከረ የሞት ሽረት ትግል እንደሚያደርግ ምንም ጥርጥር የለውም። የመንግሥቱ ተገዥዎች ምንም ዓይነት ስደትና መከራ ቢገጥማቸውም እስከ መጨረሻ ድረስ አምላክን በታማኝነት ይደግፉ ይሆን? ይህ እያንዳንዱ የይሖዋ አገልጋይ በግለሰብ ደረጃ መልስ ሊሰጥበት የሚገባ ጥያቄ ነው።​—⁠ራእይ 12:​12, 17

17. ኢየሱስ “ይህም ለምስክርነት ይሆንላችኋል” ሲል ምን ማለቱ ነበር?

17 ኢየሱስ ‘በሥርዓቱ መጨረሻ’ [NW ] ላይ ስለሚፈጸሙት ክንውኖች ለደቀ መዛሙርቱ በተናገረበት ወቅት ይሖዋ አገልጋዮቹ መከራ እንዲደርስባቸው የሚፈቅድበትን ተጨማሪ ምክንያት ጠቅሷል። “ወደ ነገሥታትና ወደ ገዥዎችም ይወስዱአችኋል፤ ይህም ለምስክርነት ይሆንላችኋል” ብሏል። (ማቴዎስ 24:3, 9፤ ሉቃስ 21:12, 13) ኢየሱስ ራሱ በሄሮድስና በጴንጤናዊው ጲላጦስ ፊት መሥክሯል። ሐዋርያው ጳውሎስም ቢሆን ‘ወደ ነገሥታትና ወደ ገዥዎች ተወስዷል።’ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የሚሰጠውን አመራር በመከተል ጳውሎስ በዘመኑ ለነበረው የዓለም ኃያል ገዥ የመመሥከር ዓላማ እንዳለው ሲገልጽ “ወደ ቄሣር ይግባኝ ብዬአለሁ” ብሏል። (ሥራ 23:​11፤ 25:​8-12) በተመሳሳይ ዛሬም ፈታኝ የሆኑ ሁኔታዎች በአብዛኛው ለመንግሥት ባለ ሥልጣናትም ሆነ ለሕዝብ ግሩም ምሥክርነት መስጠት የሚቻልበት አጋጣሚ አስገኝተዋል። b

18, 19. (ሀ) ስደትን ተቋቁሞ ማሳለፍ ምን ጥቅም ያስገኝልናል? (ለ) በሚቀጥለው ርዕስ ላይ የሚብራሩት የትኞቹ ጥያቄዎች ናቸው?

18 በመጨረሻም፣ መከራና ስደትን መቋቋም ራሳችንን ሊጠቅመን ይችላል። በምን መንገድ? ደቀ መዝሙሩ ያዕቆብ ክርስቲያን ባልንጀሮቹን እንዲህ ሲል አሳስቧቸዋል:- “ወንድሞቼ ሆይ፣ የእምነታችሁ መፈተን ትዕግሥትን እንዲያደርግላችሁ አውቃችሁ፣ ልዩ ልዩ ፈተና ሲደርስባችሁ እንደ ሙሉ ደስታ ቊጠሩት።” አዎን፣ ስደት እምነታችንን ሊያጠራልንና ጽናታችንን ሊያጠናክርልን ይችላል። በመሆኑም ስደት ሲደርስብን አንርበተበትም ወይም ደግሞ የምናመልጥበትን አሊያም እንዲቆም የምናደርግበትን ቅዱስ ጽሑፋዊ ያልሆነ መንገድ አናመቻችም። ከዚህ ይልቅ “ትዕግሥትም ምንም የሚጐድላችሁ ሳይኖር ፍጹማንና ምሉዓን ትሆኑ ዘንድ ሥራውን ይፈጽም” የሚለውን የያዕቆብን ምክር ተግባራዊ እናደርጋለን።​—⁠ያዕቆብ 1:2-4

19 መጽሐፍ ቅዱስ የአምላክ ታማኝ አገልጋዮች ለምን ስደት እንደሚደርስባቸውና ይሖዋም ለምን እንደሚፈቅድ እንድንገነዘብ የሚረዳን ቢሆንም የሚደርስብንን ስደት ለመቋቋም ቀላል ያደርግልናል ማለት አይደለም። ስደትን መቋቋም እንድንችል ጥንካሬ ማግኘት የምንችለው እንዴት ነው? ስደት ሲደርስብን ምን ማድረግ እንችላለን? እነዚህ ዐበይት ጥያቄዎች በሚቀጥለው ርዕስ ላይ ይብራራሉ።

[የግርጌ ማስታወሻ]

a መጠበቂያ ግንብ ታኅሣሥ 15, 1995 ገጽ 27-9 እና ሚያዝያ 15, 1994 ገጽ 16-17 እንዲሁም የታኅሣሥ 22, 1993 ንቁ! (እንግሊዝኛ) ገጽ 6-13 ተመልከት።

b የጥር 2003 ንቁ! ገጽ 3-11⁠ን ተመልከት።

ልታብራራ ትችላለህ?

• ኢየሱስ ሰማዕት ነው ሊባል የሚችልበት ዋነኛው መንገድ ምንድን ነው?

• በመጀመሪያው መቶ ዘመን የነበሩ ክርስቲያኖች ስደት ሲደርስባቸው ምን አድርገዋል?

• ጴጥሮስ በተናገረው መሠረት የጥንቶቹ ክርስቲያኖች ስደት የደረሰባቸው ለምንድን ነው?

• ይሖዋ አገልጋዮቹ ስደት እንዲደርስባቸው የሚፈቅደው በየትኞቹ ምክንያቶች የተነሳ ነው?

[የአንቀጾቹ ጥያቄዎች]

[በገጽ 10 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

በመጀመሪያው መቶ ዘመን የነበሩት ክርስቲያኖች ስደት የደረሰባቸው የሠሩት ጥፋት ኖሮ ሳይሆን ክርስቲያን በመሆናቸው ምክንያት ነበር

ጳውሎስ

ያዕቆብ

ዮሐንስ

አንቲጳስ

እስጢፋኖስ