መለኮታዊ ጣልቃ ገብነት—ምን መጠበቅ እንችላለን?
መለኮታዊ ጣልቃ ገብነት—ምን መጠበቅ እንችላለን?
በስምንተኛው መቶ ዘመን ከዘአበ የ39 ዓመቱ የይሁዳ ንጉሥ ሕዝቅያስ ለሞት በሚያደርስ በሽታ መያዙን አወቀ። ሕዝቅያስ ይህን ሲያውቅ ከፍተኛ ሐዘን ስለተሰማው አምላክ እንዲያድነው በጸሎት ተማጸነ። አምላክ በነቢዩ አማካኝነት “ጸሎትህን ሰምቻለሁ፣ እንባህንም አይቻለሁ፤ እነሆ፣ በዕድሜህ ላይ አሥራ አምስት ዓመት እጨምራለሁ” የሚል መልስ ሰጠው።—ኢሳይያስ 38:1-5
አምላክ በዚህ ወቅት ጣልቃ የገባው ለምንድን ነው? ከበርካታ መቶ ዓመታት በፊት ይሖዋ ለጻድቁ ንጉሥ ዳዊት እንዲህ ሲል ቃል ገብቶለት ነበር:- “ቤትህና መንግሥትህም በፊቴ ለዘላለም ይጠነክራል፣ ዙፋንህም ለዘላለም ይጸናል።” አምላክ መሲሑ በዳዊት መሥመር እንደሚመጣም ገልጿል። (2 ሳሙኤል 7:16፤ መዝሙር 89:20, 26-29፤ ) ሕዝቅያስ በታመመበት ወቅት ገና ወንድ ልጅ አልወለደም። በመሆኑም በዳዊት በኩል የመጣው የንግሥና መሥመር የመቋረጥ አደጋ ተደቅኖበት ነበር። ሕዝቅያስ ባጋጠመው ሁኔታ አምላክ ጣልቃ መግባቱ መሲሑ የሚመጣበት የዘር ሐረግ እንዳይቋረጥ አስችሏል። ኢሳይያስ 11:1
ይሖዋ የገባውን ቃል ለመፈጸም ሲል ከክርስትና በፊት በነበረው ዘመን ሁሉ ስለ ሕዝቡ ሆኖ ጣልቃ የገባባቸው በርካታ አጋጣሚዎች ነበሩ። ሙሴ እስራኤላውያን ከግብፅ ባርነት ነፃ ከመውጣታቸው ጋር በተያያዘ እንዲህ ብሏል:- “እግዚአብሔር ስለ ወደዳችሁ ለአባቶቻችሁም የማለላቸውን መሐላ ስለ ጠበቀ፣ ስለዚህ እግዚአብሔር በጽኑ እጅ አወጣችሁ።”—ዘዳግም 7:8
በመጀመሪያው መቶ ዘመንም መለኮታዊ ጣልቃ ገብነት የአምላክን ዓላማዎች ለማራመድ አገልግሏል። ለምሳሌ ያህል ሳውል የተባለ አንድ አይሁዳዊ ወደ ደማስቆ እየተጓዘ ሳለ የክርስቶስን ደቀ መዛሙርት ማሳደዱን ለማስቆም ተአምራዊ የሆነ ራእይ እንዲመለከት ተደረገ። በኋላ ሐዋርያው ጳውሎስ ተብሎ የተጠራው የዚህ ሰው መለወጥ ምሥራቹ ለአሕዛብ እንዲዳረስ ከፍተኛ አስተዋጽኦ አበርክቷል።—ሥራ 9:1-16፤ ሮሜ 11:13
አምላክ ሁልጊዜ ጣልቃ ይገባል?
መለኮታዊ ጣልቃ ገብነት የሚከሰተው ሁልጊዜ ነው ወይስ አልፎ አልፎ? ሁልጊዜ የሚከሰት ነገር አለመሆኑን መጽሐፍ ቅዱስ በግልጽ ያሳያል። አምላክ ሦስቱን ወጣት ዕብራውያን ከእቶን እሳት ውስጥ፣ ነቢዩ ዳንኤልን ደግሞ ከአንበሶች ጉድጓድ ቢያድናቸውም ሌሎች ነቢያትን ከሞት ለማዳን ግን እርምጃ አልወሰደም። (2 ዜና መዋዕል 24:20, 21፤ ዳንኤል 3:21-27፤ 6:16-22፤ ዕብራውያን 11:37) ጴጥሮስ፣ ቀዳማዊ ሄሮድስ አግሪጳ አሳስሮት በነበረ ጊዜ በተአምራዊ መንገድ ከወኅኒ ቤት ተፈትቷል። ሆኖም ይኸው ንጉሥ ሐዋርያው ያዕቆብን ያስገደለው ሲሆን አምላክ ይህን ግፍ ለማስቀረት ጣልቃ አልገባም። (ሥራ 12:1-11) አምላክ ሐዋርያት የታመሙትን እንዲፈውሱና የሞቱትን ጭምር እንዲያስነሡ ኃይል ቢሰጣቸውም ሐዋርያው ጳውሎስ የነበረበትን ‘የሥጋ መውጊያ’ (አካላዊ ሕመም ሊሆን ይችላል) ለማስወገድ ግን ፈቃደኛ አልሆነም።—2 ቆሮንቶስ 12:7-9፤ ሥራ 9:32-41፤ 1 ቆሮንቶስ 12:28
አምላክ የሮማው ንጉሠ ነገሥት ኔሮ በክርስቶስ ደቀ መዛሙርት ላይ የቆሰቆሰውን የስደት ማዕበል ለማስቆም ጣልቃ አልገባም። ክርስቲያኖች ተደብድበዋል፣ ከነሕይወታቸው በእሳት ተቃጥለዋል እንዲሁም ለአራዊት ተሰጥተዋል። ይሁን እንጂ ይህ ስደት የቀድሞዎቹን ክርስቲያኖች አላስደነገጣቸውም፤ በአምላክ ሕልውና ላይ ያላቸውንም እምነት አላዳከመባቸውም። ደግሞም ኢየሱስ ለፍርድ እንደሚያቀርቧቸው እንዲሁም ለእምነታቸው ሲሉ መከራና ሞትም እንኳ ሳይቀር ለመቀበል ዝግጁ መሆን እንዳለባቸው ደቀ መዛሙርቱን አስጠንቅቋቸው ነበር።—ማቴዎስ 10:17-22
አምላክ በጥንት ዘመን እንዳደረገው ሁሉ ዛሬም አገልጋዮቹን ከአደገኛ ሁኔታዎች የማዳን ችሎታ ያለው ሲሆን የእርሱን ጥበቃ እንዳገኙ የሚናገሩ ሰዎችም ሊተቹ አይገባም። ሆኖም በእነዚህ ጊዜያት የአምላክ እጅ አለበት ወይም የለበትም ብሎ በእርግጠኝነት መናገር ያስቸግራል። በቱሉዝ፣ ፈረንሳይ በደረሰው ፍንዳታ ሳቢያ በርካታ የይሖዋ ምሥክሮች ጉዳት ደርሶባቸዋል እንዲሁም በሺዎች የሚቆጠሩ ታማኝ ምሥክሮች በናዚና በኮሚኒስት ማጎሪያ ካምፖች ወይም በሌሎች አደጋዎች ሕይወታቸውን አጥተዋል። በእነዚህ ወቅቶች አምላክ እነርሱን ለመጠበቅ ጣልቃ አልገባም። አምላክ በእርሱ ዘንድ ተቀባይነት ያላቸውን ሰዎች በሙሉ ለመጠበቅ ጣልቃ የማይገባው ለምንድን ነው?—ዳንኤል 3:17, 18
“ጊዜና አጋጣሚ”
አንድ ዓይነት አደጋ ሲከሰት ማንኛውም ሰው ሊጎዳ የሚችል ከመሆኑም በላይ ለአምላክ ታማኝ መሆን ሁልጊዜ ለውጥ ያመጣል ብለን መጠበቅ የለብንም። በቱሉዝ ከደረሰው ፍንዳታ አላን እና ሊልያን በሕይወት ተርፈዋል። ሆኖም ያጠፉት ነገር ባይኖርም 30 ሰዎች ሲሞቱ በመቶዎች የሚቆጠሩ ደግሞ ጉዳት ደርሶባቸዋል። ነገሩን ሰፋ አድርገን ስናየው ደግሞ በአሥር ሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች በወንጀል፣ ጥንቃቄ በጎደለው የመኪና አነዳድ ወይም በጦርነት ሳቢያ ሕይወታቸውን ያጡ ይሆናል። እነዚህን ለመሳሰሉ አሳዛኝ ክስተቶች አምላክ ተጠያቂ ሊሆን አይችልም። ‘ጊዜና አጋጣሚ ሁሉን እንደሚገናኛቸው’ መጽሐፍ ቅዱስ ይናገራል።—መክብብ 9:11 NW
ከዚህም በላይ ሰዎች ይታመማሉ፣ ያረጃሉ እንዲሁም ይሞታሉ። አምላክ ሕይወታቸውን በተአምር እንዳተረፈላቸው ወይም ባልተጠበቀ ሁኔታ ከበሽታ እንዳዳናቸው የሚናገሩ ሰዎች እንኳ በመጨረሻ የሞትን ጽዋ ቀምሰዋል። በሽታና ሞት የሚወገድበት እንዲሁም የሰው ልጆች ‘እንባ ከዓይናቸው የሚታበስበት’ ጊዜ የሚመጣው ገና ወደፊት ነው።—ራእይ 21:1-4
ይህ እንዲሆን ግን አልፎ አልፎ ከሚደረግ ጣልቃ ገብነት በተለየ ሰፊና ሥር ነቀል ለውጥ መምጣት አለበት። መጽሐፍ ቅዱስ “ታላቁ የእግዚአብሔር ቀን” በማለት በሚገልጸው ጊዜ ስለሚፈጸም ክንውን ይናገራል። (ሶፎንያስ 1:14) አምላክ መጠነ ሰፊ በሆነ መንገድ ጣልቃ በሚገባበት በዚህ ወቅት ክፋትን ሙሉ በሙሉ ያስወግዳል። የሰው ልጅ ‘የቀደሙት በማይታሰቡበት፣ ወደ ልብም በማይገቡበት’ ዓለም ፍጹም በሆነ ሁኔታ ለዘላለም የመኖር አጋጣሚ ይሰጠዋል። (ኢሳይያስ 65:17) ሙታን እንኳ ትንሣኤ ስለሚያገኙ በሰው ልጆች ላይ ከሚደርሰው ሁሉ አስከፊ የሆነው መከራ ይሻራል። (ዮሐንስ 5:28, 29) አምላክ ወሰን በሌለው ፍቅሩና ደግነቱ የሰው ልጆችን ችግሮች በሙሉ ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ያስወግዳል።
በዛሬው ጊዜ አምላክ ጣልቃ የሚገባው እንዴት ነው?
እስከዚያ ጊዜ ድረስ ግን ፍጥረት በሥቃይ ሲቃትት ፈጣሪ በግድ የለሽነት ዝም ብሎ ይመለከታል ማለት አይደለም። 1 ጢሞቴዎስ 2:3, 4) ኢየሱስ ይህን ሁኔታ “የላከኝ አብ ከሳበው በቀር ወደ እኔ ሊመጣ የሚችል የለም” በማለት ገልጾታል። (ዮሐንስ 6:44) አምላክ አገልጋዮቹ በምድር ዙሪያ በሚያውጁት የመንግሥቱ መልእክት አማካኝነት ልበ ቅን የሆኑ ሰዎችን ወደ ራሱ ይስባቸዋል።
በዛሬው ጊዜ አምላክ ዘራቸው ወይም አስተዳደጋቸው ምንም ይሁን ምን የሰው ልጆች በሙሉ እርሱን የማወቅና ከእርሱ ጋር ዝምድና የመመሥረት አጋጣሚ እንዲያገኙ አድርጓል። (በተጨማሪም አምላክ እርሱ እንዲመራቸው ፈቃደኛ በሚሆኑ ሰዎች ሕይወት ላይ ቀጥተኛ ተጽዕኖ ያሳድራል። በመንፈስ ቅዱሱ አማካኝነት ፈቃዱን እንዲረዱና የሚጠብቅባቸውን ነገር እንዲያደርጉ ‘ልባቸውን ይከፍትላቸዋል።’ (ሥራ 16:14) አዎን፣ አምላክ እርሱን እንዲሁም ቃሉንና ዓላማውን እንድናውቅ አጋጣሚ በመስጠት ለእያንዳንዳችን ያለውን ፍቅራዊ አሳቢነት ያሳያል።—ዮሐንስ 17:3
በመጨረሻም አምላክ በተአምራዊ መንገድ ጥበቃ በማድረግ ሳይሆን የሚያጋጥማቸውን ማንኛውንም ሁኔታ መቋቋም እንዲችሉ መንፈስ ቅዱሱንና ‘ታላቅ ኃይሉን’ በመስጠት በዛሬው ጊዜ አገልጋዮቹን ይረዳቸዋል። (2 ቆሮንቶስ 4:7) ሐዋርያው ጳውሎስ “ኀይልን በሚሰጠኝ በእርሱ [በይሖዋ አምላክ] ሁሉን ማድረግ እችላለሁ” ሲል ጽፏል።—ፊልጵስዩስ 4:13 አ.መ.ት
በመሆኑም ሕይወት ስለሰጠንና ከማንኛውም ዓይነት መከራ ነፃ በሆነ ዓለም ውስጥ ለዘላለም የመኖር ተስፋ ስለዘረጋልን በእያንዳንዱ ቀን አምላክን የምናመሰግንበት በቂ ምክንያት አለን። መዝሙራዊው “ስላደረገልኝ ሁሉ ለእግዚአብሔር ምንን እመልሳለሁ?” ሲል ጠይቋል። “የመድኃኒትን ጽዋ እቀበላለሁ፣ የእግዚአብሔርንም ስም እጠራለሁ።” (መዝሙር 116:12, 13) አዘውትረህ ይህን መጽሔት ማንበብህ በአሁኑ ጊዜ ደስታ የወደፊቱን ጊዜ በተመለከተ ደግሞ የተረጋገጠ ተስፋ የሚያስገኝልህን ፈጣሪ እስካሁን ያደረገውን፣ እያደረገ ያለውንና ወደፊት የሚያደርገውን ነገር እንድታውቅ ያስችልሃል።—1 ጢሞቴዎስ 4:8
[በገጽ 6 ላይ የሚገኝ የተቀነጨበ ሐሳብ]
“የቀደሙትም አይታሰቡም፣ ወደ ልብም አይገቡም።”—ኢሳይያስ 65:17
[በገጽ 5 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
በመጽሐፍ ቅዱስ ዘመን ዘካርያስ በድንጋይ ተወግሮ ሲገደልም . . .
ሆነ ሄሮድስ ሕፃናትን ሲያስገድል ይሖዋ ጣልቃ ገብቶ አላስቆመም
[በገጽ 7 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ሥቃይና መከራ የሚያከትምበትና ሙታን ትንሣኤ የሚያገኙበት ጊዜ ቀርቧል