በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

በፈተና መጽናት ለይሖዋ ክብር ያመጣል

በፈተና መጽናት ለይሖዋ ክብር ያመጣል

በፈተና መጽናት ለይሖዋ ክብር ያመጣል

“መልካም አድርጋችሁ መከራን ስትቀበሉ ብትታገሡ፣ ይህ ነገር በእግዚአብሔር ዘንድ ምስጋና ይገባዋል።”​—⁠1 ጴጥሮስ 2:20

1. እውነተኛ ክርስቲያኖች ከውሳኔያቸው ጋር ተስማምተው ለመኖር ስለሚፈልጉ ትኩረት መስጠት ያለባቸው ለየትኛው ጥያቄ ነው?

 ክርስቲያኖች ሕይወታቸውን ለይሖዋ የወሰኑ ሲሆን ፈቃዱን ማድረግም ይፈልጋሉ። ይህን ውሳኔያቸውን ለማክበር ሲሉ እንደ ምሳሌ የሚያዩትን የኢየሱስ ክርስቶስን ፈለግ ለመከተልና ለእውነት ለመመሥከር አቅማቸው የሚፈቅደውን ሁሉ ያደርጋሉ። (ማቴዎስ 16:​24፤ ዮሐንስ 18:​37፤ 1 ጴጥሮስ 2:​21) ይሁን እንጂ ኢየሱስና ሌሎች ታማኝ ክርስቲያኖች ለእምነታቸው ሲሉ ሕይወታቸውን አሳልፈው በመስጠት በሰማዕትነት ሞተዋል። እንደዚህ ሲባል ታዲያ ሁሉም ክርስቲያኖች ለእምነታቸው ሲሉ እንደሚሞቱ መጠበቅ አለባቸው ማለት ነው?

2. ክርስቲያኖች ለፈተናና ለስደት ምን አመለካከት አላቸው?

2 ክርስቲያኖች እንደመሆናችን መጠን እስከ ሞት ድረስ ታማኝነታችንን እንድንጠብቅ ማበረታቻ ተሰጥቶናል። ሆኖም ለእምነታችን ስንል የግድ መሞት አለብን ማለት አይደለም። (2 ጢሞቴዎስ 4:7፤ ራእይ 2:10) ለእምነታችን ስንል መከራ ለመቀበል አስፈላጊ ከሆነም ለመሞት ፈቃደኛ ብንሆንም እንኳ ይህ እንዲደርስብን እንፈልጋለን ማለት ግን አይደለም። ከመከራ፣ ከሥቃይ ወይም ከውርደት የምናገኘው ደስታ የለም። ይሁን እንጂ ፈተናና ስደት ሊደርስብን እንደሚችል ስለምንጠብቅ እንዲህ ዓይነት ሁኔታ በሚያጋጥመን ጊዜ ምን ማድረግ እንዳለብን ከወዲሁ በጥሞና መመርመር ይኖርብናል።

በፈተና ወቅት ታማኝ መሆን

3. ስደትን በመቋቋም ረገድ የትኞቹን የመጽሐፍ ቅዱስ ምሳሌዎች መጥቀስ ትችላለህ? (በሚቀጥለው ገጽ ላይ የሚገኘውን “የደረሰባቸውን ስደት የተቋቋሙት እንዴት ነው?“ የሚለውን ሣጥን ተመልከት።)

3 መጽሐፍ ቅዱስ በጥንት ዘመን የኖሩ የአምላክ አገልጋዮች ለሕይወት አስጊ የሆኑ ሁኔታዎች ሲያጋጥሟቸው ምን እንዳደረጉ የሚገልጹ በርካታ ዘገባዎች ይዟል። ሁኔታዎቹን የተወጡባቸው የተለያዩ መንገዶች በዛሬው ጊዜ ያሉ ክርስቲያኖች ተመሳሳይ ፈተናና ስደት ቢያጋጥማቸው ምን ማድረግ እንዳለባቸው መመሪያ ይሆኗቸዋል። “የደረሰባቸውን ስደት የተቋቋሙት እንዴት ነው?” በሚለው ሣጥን ውስጥ የቀረቡትን ዘገባዎች በማንበብ ትምህርት ማግኘት ትችላለህ።

4. ኢየሱስም ሆነ ሌሎች ታማኝ አገልጋዮች ፈተና ሲደርስባቸው የሰጡትን ምላሽ በተመለከተ ምን ማለት ይቻላል?

4 ኢየሱስም ሆነ ሌሎች ታማኝ የአምላክ አገልጋዮች ስደት ሲደርስባቸው እንደ አመጣጡ የተለያየ ምላሽ የሰጡ ቢሆንም ሕይወታቸውን ሳያስፈልግ ለአደጋ እንዳላጋለጡ የታወቀ ነው። አደገኛ ሁኔታ ሲደቀንባቸው ድፍረት የተሞላበት ሆኖም ጥንቃቄ የታከለበት ምላሽ ይሰጡ ነበር። (ማቴዎስ 10:​16, 23) ዋናው ግባቸው የስብከቱን ሥራ ማስፋፋትና ከይሖዋ ጎን በታማኝነት መቆም ነበር። የተለያየ ሁኔታ ሲያጋጥማቸው የሰጡት ምላሽ በዛሬው ጊዜ ፈተናና ስደት የሚደርስባቸው ክርስቲያኖች ምን ማድረግ እንዳለባቸው ምሳሌ ሊሆናቸው ይችላል።

5. በ1960ዎቹ በማላዊ ምን ዓይነት ስደት ተነስቶ ነበር? ምሥክሮቹስ ምን ምላሽ ሰጡ?

5 በዚህ ዘመን የይሖዋ ሕዝቦች በጦርነት፣ በተጣለባቸው እገዳ ወይም ስደት ሳቢያ እጅግ አስከፊ ለሆነ መከራና ችግር ተዳርገዋል። ለምሳሌ ያህል በ1960ዎቹ በማላዊ የነበሩ የይሖዋ ምሥክሮች ከባድ ስደት ደርሶባቸዋል። የመሰብሰቢያ አዳራሻቸው፣ መኖሪያ ቤታቸው፣ እርሻቸውና የንግድ ሥራቸው በሌላ አባባል የነበራቸው ንብረት በሙሉ ወድሞባቸዋል ማለት ይቻላል። ድብደባና ሌሎች አሰቃቂ ሁኔታዎች ደርሰውባቸዋል። በዚህ ጊዜ ወንድሞች ምን አደረጉ? በሺዎች የሚቆጠሩ አካባቢያቸውን ጥለው ለመሸሽ ተገድደዋል። አብዛኞቹ ጫካ ውስጥ መኖር የጀመሩ ሲሆን ሌሎች ደግሞ አጎራባች አገር ወደሆነችው ወደ ሞዛምቢክ ለተወሰነ ጊዜ ተሰድደዋል። ብዙ ታማኝ የይሖዋ ምሥክሮች ሕይወታቸውን አጥተዋል። ሌሎች ደግሞ ከአደጋው ቀጠና ለመሸሽ የመረጡ ሲሆን ይህም በዚህ ዓይነት ሁኔታ ሥር ሊወስዱ የሚችሉት ምክንያታዊ እርምጃ ነበር። እንዲህ በማድረግ እነዚህ ወንድሞች ኢየሱስና ጳውሎስ የተዉትን ምሳሌ ተከትለዋል።

6. የማላዊ ወንድሞች ኃይለኛ ስደት ቢደርስባቸውም ምን ከማድረግ ወደኋላ አላሉም?

6 የማላዊ ወንድሞች አካባቢያቸውን ጥለው ለመሸሽ ወይም መደበቅ ወደሚችሉበት ቦታ ለመሄድ ቢመርጡም እንኳ ቲኦክራሲያዊ አመራር ለማግኘት ጥረት ከማድረጋቸውም በላይ የሚሰጣቸውን መመሪያ ይከተሉ ነበር። እንዲሁም ሁኔታው በሚፈቅድላቸው መጠን ክርስቲያናዊ እንቅስቃሴዎቻቸውን በድብቅ ማካሄዳቸውን ቀጥለዋል። ምን ውጤት ተገኘ? በ1967 እገዳው ከመጣሉ በፊት 18, 519 የደረሰ ከፍተኛ የአስፋፊዎች ቁጥር ሊገኝ ችሏል። በ1972 ገና በእገዳ ሥር እያሉና ብዙዎች ወደ ሞዛምቢክ ሸሽተው እያለ አዲስ ከፍተኛ ጭማሪ አግኝተው የአስፋፊዎች ቁጥር 23, 398 ደርሶ ነበር። በየወሩ በአማካይ ከ16 ሰዓት በላይ በአገልግሎት ያሳልፉ ነበር። በእርግጥም፣ የወሰዱት እርምጃ ይሖዋን ያስከበረው ከመሆኑም በላይ እርሱም በዚያ አስጨናቂ ወቅት እነዚያን ታማኝ ወንድሞች ባርኳቸዋል። a

7, 8. አንዳንዶች የሚደርስባቸው ተቃውሞ ችግር ቢያስከትልባቸውም አገራቸውን ጥለው ላለመሄድ የመረጡት በየትኞቹ ምክንያቶች የተነሳ ነው?

7 በአንጻሩ ደግሞ ተቃውሞ የተለያዩ ችግሮች በሚያስከትልባቸው አገሮች ውስጥ የሚኖሩ አንዳንድ ወንድሞች አገሩን ጥለው መውጣት የሚችሉ ቢሆኑም እዚያው ለመቅረት ይመርጡ ይሆናል። ወደ ሌላ አገር መሄድ ለአንዳንድ ችግሮች መፍትሔ ሊያስገኝ ቢችልም ሌሎች ተፈታታኝ ሁኔታዎችም ሊያስከትል ይችላል። ለምሳሌ ያህል፣ በመንፈሳዊ ሁኔታ ተገልለው እንዳይቀሩ በዚያ ካሉት ክርስቲያን ወንድሞቻቸው ጋር መገናኘት ይችላሉ? በሄዱበት ቦታ፣ ምናልባትም ይበልጥ የበለጸገ ወይም በቁሳዊ ሀብት ማደግ የሚቻልበት አገር ውስጥ ኑሮውን ለመላመድ በሚያደርጉት ትግል መንፈሳዊ ልማዳቸውን ጠብቀው መኖር ይችላሉ?​—⁠1 ጢሞቴዎስ 6:​9

8 ሌሎች ደግሞ የወንድሞቻቸው መንፈሳዊ ደህንነት ስለሚያሳስባቸው ወደ ሌላ አገር ላለመሄድ ይመርጣሉ። ምሥራቹን በትውልድ አገራቸው መስበካቸውን ለመቀጠልና ለአምልኮ ባልንጀሮቻቸው የብርታት ምንጭ ለመሆን ሲሉ እዚያው ቀርተው የመጣውን ለመጋፈጥ መርጠዋል። (ፊልጵስዩስ 1:​14) እንዲህ ዓይነት ምርጫ ያደረጉ አንዳንድ ወንድሞች በአገራቸው በፍርድ ጉዳዮች አንዳንድ ድሎች እንዲገኙ አስተዋጽኦ የማበርከት አጋጣሚ አግኝተዋል። b

9. አንድ ሰው በስደት ምክንያት አካባቢውን ጥሎ ለመሄድ ወይም እዚያው ለመቅረት ሲወስን የትኞቹን ጉዳዮች ግምት ውስጥ ማስገባት አለበት?

9 ባሉበት መቅረትም ሆነ ወደ ሌላ አገር መሄድ ሙሉ በሙሉ ለእያንዳንዱ ግለሰብ የተተወ ውሳኔ ነው። እርግጥ እንዲህ ዓይነት ውሳኔ ከማድረጋችን በፊት የይሖዋን አመራር በጸሎት መጠየቅ አለብን። ውሳኔያችን ምንም ይሁን ምን ሐዋርያው ጳውሎስ “እያንዳንዳችን ስለ ራሳችን ለእግዚአብሔር መልስ እንሰጣለን” ሲል የተናገረውን ሐሳብ ግምት ውስጥ ማስገባት ይኖርብናል። (ሮሜ 14:12) ቀደም ሲል እንደተጠቀሰው ይሖዋ ከሁሉም አገልጋዮቹ የሚጠብቀው በማንኛውም ሁኔታ ሥር ታማኝ ሆነው እንዲገኙ ነው። አንዳንድ አገልጋዮቹ በአሁኑ ጊዜ ፈተናና ስደት እየደረሰባቸው ነው፤ ሌሎች ደግሞ ወደፊት ሊደርስባቸው ይችላል። በዚህም ሆነ በዚያ ሁሉም ፈተና ይደርስባቸዋል። በመሆኑም ማንም ሰው ቢሆን ፈተና ሳይነካኝ እኖራለሁ ብሎ መጠበቅ የለበትም። (ዮሐንስ 15:​19, 20) ራሳችንን የወሰንን የይሖዋ አገልጋዮች እንደመሆናችን መጠን የይሖዋን ስም መቀደስና የሉዓላዊነቱን መረጋገጥ የሚያካትተውን በአጽናፈ ዓለም ላይ የተነሳውን አከራካሪ ጉዳይ መሸሽ አንችልም።​—⁠ሕዝቅኤል 38:​23፤ ማቴዎስ 6:​9, 10

“ለማንም ስለ ክፉ ፈንታ ክፉን አትመልሱ”

10. ኢየሱስና ሐዋርያቱ ፈተናና ተቃውሞ ሲደርስብን ልንወስደው የሚገባውን እርምጃ በተመለከተ ምን ጠቃሚ ምሳሌ ትተውልናል?

10 ኢየሱስና ሐዋርያቱ ፈተና ሲደርስባቸው ከሰጡት ምላሽ የምንማረው ሌላው ጉልህ መሠረታዊ ሥርዓት አሳዳጆቻችንን ፈጽሞ መበቀል የሌለብን መሆኑን ነው። ኢየሱስ ወይም ተከታዮቹ የሚያሳድዷቸውን ሰዎች ለማጥቃት የሽምቅ እንቅስቃሴ ወይም የኃይል እርምጃ መውሰድ እንደጀመሩ የሚገልጽ ሐሳብ መጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ በየትኛውም ቦታ አናገኝም። ከዚህ ይልቅ ሐዋርያው ጳውሎስ ክርስቲያኖችን “ለማንም ስለ ክፉ ፈንታ ክፉን አትመልሱ” ሲል መክሯቸዋል። “ተወዳጆች ሆይ፣ ራሳችሁ አትበቀሉ፣ ለቊጣው ፈንታ ስጡ እንጂ፤ በቀል የእኔ ነው፣ እኔ ብድራቱን እመልሳለሁ ይላል ጌታ ተብሎ ተጽፎአልና።” ከዚህም በላይ “ክፉውን በመልካም አሸንፍ እንጂ በክፉ አትሸነፍ።”​—⁠ሮሜ 12:17-21፤ መዝሙር 37:1-4፤ ምሳሌ 20:22

11. የቀድሞዎቹ ክርስቲያኖች ለመንግሥት የነበራቸውን አመለካከት በተመለከተ አንድ ታሪክ ጸሐፊ ምን ብለዋል?

11 የቀድሞዎቹ ክርስቲያኖች ይህን ምክር በቁም ነገር ተመልክተውታል። ታሪክ ጸሐፊው ሲሰል ጄ ካዱ ዚ ኧርሊ ቸርች ኤንድ ዘ ዎርልድ (የጥንቱ ቤተ ክርስቲያንና ዓለም) በተባለው መጽሐፋቸው ላይ ከ30-70 እዘአ በነበረው ጊዜ ውስጥ ክርስቲያኖች ለመንግሥት የነበራቸውን አመለካከት ሲገልጹ እንዲህ በማለት ጽፈዋል:- “በዚያ ዘመን የነበሩ ክርስቲያኖች የሚደርስባቸውን ስደት በኃይል ለመቋቋም ጥረት እንዳደረጉ የሚገልጽ ማስረጃ የለም። በዚህ ረገድ አደረጉ የሚባለው ትልቁ ነገር ገዥዎቻቸውን ማውገዝ ወይም ከአካባቢው በመሰወር እነርሱን ግራ ማጋባት ነበር። ክርስቲያኖች ስደት ሲደርስባቸው የሚሰጡት የተለመደው ምላሽ ለክርስቶስ ያላቸውን ታዛዥነት እንደሚያስጥሳቸው የሚያምኑበትን መንግሥት የሚሰጣቸውን ትእዛዝ ፈጽሞ እንደማይቀበሉ በአክብሮት ከመግለጽ አልፎ አይሄድም።”

12. መከራ ሲደርስብን ከመበቀል ይልቅ በትዕግሥት ማሳለፍ የተሻለ የሆነው ለምንድን ነው?

12 አንድ ሰው የሚደርስበትን ስደት ዝም ብሎ መቀበሉ በእርግጥ ያዋጣልን? እንዲህ ዓይነት ምላሽ የሚሰጥ ማንኛውም ሰው እነርሱን ጠራርገው ለማጥፋት ቆርጠው በተነሱ ወገኖች በቀላሉ አይጠቃም? ራስን መከላከል የጥበብ እርምጃ አይደለም? ነገሩን በሰብዓዊ ዓይን ስናየው እንዲህ ሊመስል ይችላል። ይሁን እንጂ የይሖዋ አገልጋዮች እንደመሆናችን መጠን በማንኛውም ዓይነት ሁኔታ ሥር የእርሱን መመሪያ መከተል ከሁሉ የተሻለ አካሄድ እንደሆነ እርግጠኞች ነን። ጴጥሮስ “መልካም አድርጋችሁ መከራን ስትቀበሉ ብትታገሡ፣ ይህ ነገር በእግዚአብሔር ዘንድ ምስጋና ይገባዋል” ሲል የተናገረውን አንዘነጋም። (1 ጴጥሮስ 2:20) ይሖዋ ሁኔታውን ጠንቅቆ እንደሚያውቅና ዝም ብሎ እንዲቀጥል እንደማይፈቅድ እርግጠኞች ነን። ለዚህ ምን ማረጋገጫ አለን? ይሖዋ በባቢሎን ግዞተኞች ለነበሩት ሕዝቦቹ “የሚነካችሁ የዓይኑን [“የዐይኔን፣” የ1980 ትርጉም ] ብሌን የሚነካ ነውና” ብሏቸው ነበር። (ዘካርያስ 2:8) የዓይኑ ብሌን ሲነካ ዝም ብሎ የሚያይ ማን አለ? ይሖዋ በተገቢው ጊዜ እረፍት ይሰጠናል። ይህን የምንጠራጠርበት ምንም ምክንያት የለም።​—⁠2 ተሰሎንቄ 1:​5-8

13. ኢየሱስ ምንም ሳያንገራግር በጠላቶቹ እጅ የተያዘው ለምን ነበር?

13 በዚህ ረገድ ኢየሱስን ምሳሌ አድርገን መመልከት እንችላለን። በጌቴሴማኒ መናፈሻ ጠላቶቹ ሲይዙት ዝም ብሎ ያየው ራሱን መከላከል ስላቃተው አልነበረም። እንዲያውም ደቀ መዛሙርቱን እንዲህ ብሏቸው ነበር:- “አባቴን እንድለምን እርሱም አሁን ከአሥራ ሁለት ጭፍሮች የሚበዙ መላእክት እንዲሰድልኝ የማይቻል ይመስልሃልን? እንዲህ ከሆነስ:- እንደዚህ ሊሆን ይገባል የሚሉ መጻሕፍት እንዴት ይፈጸማሉ?” (ማቴዎስ 26:53, 54) ኢየሱስ መከራ የሚያስከትልበት ቢሆንም እንኳ የይሖዋን ፈቃድ መፈጸም ከምንም ነገር በላይ በጣም አስፈላጊ እንደሆነ ተሰምቶታል። “ነፍሴን በሲኦል አትተዋትምና፣ ቅዱስህንም መበስበስን ያይ ዘንድ አትተወውም” በሚለው የዳዊት ትንቢት አዘል መዝሙር ላይ ሙሉ ትምክህት ነበረው። (መዝሙር 16:10) ከበርካታ ዓመታት በኋላ ሐዋርያው ጳውሎስ ስለ ኢየሱስ እንዲህ ብሏል:- “እርሱ ነውርን ንቆ በፊቱም ስላለው ደስታ በመስቀል ታግሦ በእግዚአብሔር ዙፋን ቀኝ ተቀምጦአልና።”​—⁠ዕብራውያን 12:1, 2

የይሖዋን ስም ማስቀደስ የሚያስገኘው ደስታ

14. ኢየሱስ የደረሰበትን መከራ በሙሉ እንዲቋቋም ያስቻለው ደስታ ምንድን ነው?

14 ኢየሱስ የደረሰበትን ከሁሉ የከፋ ፈተና በጽናት እንዲወጣ የረዳው ምንድን ነው? ከይሖዋ አገልጋዮች ሁሉ የአምላክ ተወዳጅ ልጅ የሆነው ኢየሱስ የሰይጣን ዋነኛ ዒላማ እንደነበር የተረጋገጠ ነው። በመሆኑም ኢየሱስ በፈተና ወቅት በአቋሙ መጽናቱ ሰይጣን በይሖዋ ላይ ለሰነዘረው ስድብ የማያዳግም መልስ ያስገኛል። (ምሳሌ 27:​11) ኢየሱስ ትንሣኤ ካገኘ በኋላ የተሰማውን ደስታና እርካታ መገመት ትችላለህ? ፍጹም ሰው በመሆን የይሖዋ ሉዓላዊነት እንዲረጋገጥና ስሙ እንዲቀደስ የተጣለበትን ኃላፊነት እንደተወጣ ሲገነዘብ ምንኛ ተደስቶ ይሆን! ከዚህ በተጨማሪ “በእግዚአብሔር ዙፋን ቀኝ” መቀመጥ ለኢየሱስ ታላቅ ክብርና የላቀ ደስታ እንደሚያስገኝለት ምንም ጥያቄ የለውም።​—⁠መዝሙር 110:​1, 2፤ 1 ጢሞቴዎስ 6:​15, 16

15, 16. በዛክሰንሃውዘን የነበሩ ምሥክሮች ምን ዓይነት አሰቃቂ ስደት አሳልፈዋል? ብርታት ያገኙትስ ከየት ነው?

15 ክርስቲያኖችም የኢየሱስን ምሳሌ ተከትለው የሚደርስባቸውን ፈተናና ስደት በጽናት በማሳለፍ ለይሖዋ ስም መቀደስ የበኩላቸውን ድርሻ ማበርከታቸው ያስደስታቸዋል። በአሰቃቂነቱ በሚታወቀው በዛክሰንሃውዘን ማጎሪያ ካምፕ ከፍተኛ ሥቃይ የደረሰባቸውና በሁለተኛው የዓለም ጦርነት ማብቂያ ላይ እጅግ አድካሚ ከሆነው የሞት ጉዞ የተረፉት የይሖዋ ምሥክሮች ተሞክሮ ለዚህ ምሳሌ ሊሆን ይችላል። በጉዞው ወቅት ከመጥፎ የአየር ጠባይ የተነሳ፣ በበሽታ፣ በረሃብ ወይም በመንገድ ላይ በኤስ ኤስ ወታደሮች በጭካኔ በመገደላቸው በሺዎች የሚቆጠሩ እስረኞች አልቀዋል። ሆኖም 230 የሚሆኑት የይሖዋ ምሥክሮች በሙሉ ምንም ሳይበታተኑ አንድ ላይ በመጓዛቸውና ሕይወታቸውን አደጋ ላይ ጥለው እርስ በርስ በመረዳዳታቸው ሊተርፉ ችለዋል።

16 እነዚህ ምሥክሮች ይህን የመሰለ ጭካኔ የተሞላበት ስደት የሚቋቋሙበት ጥንካሬ ያገኙት ከየት ነው? ልክ ነፃ እንደወጡ ባዘጋጁት “በሜክለንበርግ ሽፌሪን አቅራቢያ በሚገኝ ጫካ የተሰበሰቡ ከስድስት አገሮች የተውጣጡ 230 የይሖዋ ምሥክሮች ያወጡት የአቋም መግለጫ” በተባለው ሰነድ የተሰማቸውን ደስታና ለይሖዋ ያላቸውን አመስጋኝነት ገልጸዋል። በአቋም መግለጫው ላይ እንዲህ ብለው ነበር:- “ለረጅም ጊዜ የዘለቀ ከባድ የፈተና ጊዜ አልፎ በሕይወት ለመትረፍ የበቁት ሰዎች ከእቶን እሳት የወጡ ያህል የሚቆጠር ሲሆን የእሳት ሽታ እንኳ የለባቸውም። (ዳንኤል 3:​27ን ተመልከት።) እንዲያውም ከይሖዋ ያገኙት ብርታትና ኃይል አጠናክሯቸዋል፤ እንዲሁም ቲኦክራሲያዊ ሥራዎችን ለማስፋፋት አዳዲስ መመሪያዎችን ከንጉሡ ለመቀበል በጉጉት እየተጠባበቁ ናቸው።” c

17. በአሁኑ ጊዜ የአምላክ ሕዝቦች ምን ዓይነት ፈተናዎች ያጋጥሟቸዋል?

17 እንደነዚያ 230 ታማኝ አገልጋዮች እኛም ‘ደምን እስከ ማፍሰስ ድረስ የተቃወምን’ ባይሆንም እንኳ እምነታችን ተፈትኖ ሊሆን ይችላል። (ዕብራውያን 12:​4) ሆኖም ፈተና በተለያየ መልክ ሊመጣ ይችላል። እኛ የሚደርስብን ፈተና አብረውን የሚማሩ ልጆች የሚሰነዝሩብን ፌዝ እንዲሁም የሥነ ምግባር ብልግና እንድንፈጽም ወይም ሌሎች መጥፎ ነገሮች እንድንሠራ እኩዮቻችን የሚያሳድሩብን ተጽዕኖ ሊሆን ይችላል። ከዚህ በተጨማሪ ከደም ለመራቅ ወይም በጌታ ብቻ ለማግባት ያደረግነው ቁርጥ ውሳኔ አሊያም በእምነት በተከፋፈለ ቤተሰብ ውስጥ ልጆቻችንን በአምላክ ቃል ለማሳደግ የምናደርገው ጥረት አንዳንድ ጊዜ ከፍተኛ ውጥረት ሊያስከትልብንና ፈተና ሊሆንብን ይችላል።​—⁠ሥራ 15:​29፤ 1 ቆሮንቶስ 7:​39፤ ኤፌሶን 6:​4፤ 1 ጴጥሮስ 3:​1, 2

18. በጣም ከባድ ፈተና ቢደርስብንም በጽናት መወጣት እንደምንችል የሚያሳይ ምን ማረጋገጫ አለን?

18 ምንም ዓይነት ፈተና ቢደርስብን ለመከራ የተዳረግነው ይሖዋንና መንግሥቱን በማስቀደማችን ምክንያት መሆኑን እናውቃለን። ይህን ደግሞ እንደ መብትና እንደ ደስታ እንቆጥረዋለን። ጴጥሮስ የሰጠን ማበረታቻ ድፍ​ረት ይጨምርልናል:- “ስለ ክርስቶስ ስም ብትነቀፉ የክብር መንፈስ የእግዚአብሔርም መንፈስ በእናንተ ላይ ያርፋልና ብፁዓን ናችሁ።” (1 ጴጥሮስ 4:14) ከይሖዋ መንፈስ በምናገኘው ኃይል በጣም ከባድ የሚባሉ ፈተናዎችን ጭምር መቋቋም የምንችልበት ብርታት ይኖረናል። በዚህ መንገድ ለይሖዋ ክብርና ውዳሴ እናመጣለን።​—⁠2 ቆሮንቶስ 4:​7፤ ኤፌሶን 3:​16፤ ፊልጵስዩስ 4:​13

[የግርጌ ማስታወሻ]

a በ1960ዎቹ በማላዊ የሚኖሩ የይሖዋ ምሥክሮች የደረሰባቸው ሁኔታ ከሦስት አሥርተ ዓመታት በላይ በጽናት ያሳለፉት መራራና የብዙዎችን ሕይወት የቀጠፈው ስደት መጀመሪያ ብቻ ነበር። ሙሉው ዘገባ በ1999 የይሖዋ ምሥክሮች የዓመት መጽሐፍ (እንግሊዝኛ) ገጽ 171-212 ላይ ይገኛል።

b በሚያዝያ 1, 2003 መጠበቂያ ግንብ ገጽ 11-14 ላይ የወጣውን “ጠቅላይ ፍርድ ቤት ‘በአራራት’ እውነተኛውን አምልኮ አስከበረ” የሚለውን ርዕስ ተመልከት።

c የዚህን የአቋም መግለጫ ሙሉ ቃል ለማግኘት የ1974 የይሖዋ ምሥክሮች የዓመት መጽሐፍ ገጽ 208-9ን ተመልከት። የጥር 1, 1998 መጠበቂያ ግንብ ገጽ 25-9 ላይ ከሞት ጉዞው በሕይወት የተረፈ ሰው የተናገረው የሕይወት ታሪክ ይገኛል።

ልታብራራ ትችላለህ?

• ክርስቲያኖች ለመከራና ለስደት ምን ዓይነት አመለካከት አላቸው?

• ኢየሱስም ሆነ ሌሎች ታማኝ አገልጋዮች ፈተና ሲደርስባቸው ከሰጡት ምላሽ ምን መማር እንችላለን?

• ስደት ሲደርስብን የበቀል እርምጃ መውሰዳችን ተገቢ የማይሆነው ለምንድን ነው?

• ኢየሱስ የደረሰበትን ፈተና በጽናት እንዲወጣ የረዳው ደስታ ምንድን ነው? ከዚህስ ምን መማር እንችላለን?

[የአንቀጾቹ ጥያቄዎች]

[በገጽ 15 ላይ የሚገኝ ሣጥን/ሥዕል]

የደረሰባቸውን ስደት የተቋቋሙት እንዴት ነው?

• የሄሮድስ ወታደሮች ዕድሜያቸው ሁለት ዓመትና ከዚያ በታች የሆኑትን ወንድ ሕፃናት በሙሉ ለመግደል ወደ ቤተ ልሔም ከመምጣታቸው በፊት ዮሴፍና ማርያም አንድ መልአክ የሰጣቸውን መመሪያ በመከተል ሕፃኑ ኢየሱስን ይዘው ወደ ግብፅ ሸሽተዋል።​—⁠ማቴዎስ 2:​13-16

• ኢየሱስ አገልግሎቱን በሚያከናውንበት ወቅት ኃይለኛ መልእክት ያዘለ ምሥክርነት በመስጠቱ ጠላቶቹ ተደጋጋሚ የግድያ ሙከራ አድርገውበታል። ኢየሱስ በእያንዳንዱ አጋጣሚ ከእጃቸው አምልጧል።​—⁠ማቴዎስ 21:​45, 46፤ ሉቃስ 4:​28-30፤ ዮሐንስ 8:​57-59

• ወታደሮችና ሎሌዎች ኢየሱስን ለመያዝ በጌቴሴማኒ ወደሚገኘው መናፈሻ በመጡ ጊዜ ኢየሱስ ከአንዴም ሁለቴ “እኔ ነኝ” በማለት ማንነቱን በግልጽ ተናግሯል። እንዲያውም ተከታዮቹ የመከላከል እርምጃ እንዳይወስዱ የከለከላቸው ከመሆኑም በላይ ሊይዙት የመጡት ሰዎች እንዲወስዱት ፈቃደኛ ሆኗል።​—⁠ዮሐንስ 18:​3-12

• ኢየሩሳሌም ውስጥ ጴጥሮስና ሌሎች ታስረዋል፣ ተገርፈዋል እንዲሁም ስለ ኢየሱስ እንዳይናገሩ ትእዛዝ ተሰጥቷቸዋል። ሆኖም ከተፈቱ በኋላ ወጥተው “ዕለት ዕለትም በመቅደስና በቤታቸው ስለ ኢየሱስ እርሱ ክርስቶስ እንደ ሆነ ማስተማርንና መስበክን አይተዉም ነበር።”​—⁠ሥራ 5:40-42

• ከጊዜ በኋላ ሐዋርያው ጳውሎስ ተብሎ የተጠራው ሳውል በደማስቆ ያሉ አይሁዶች ሊገድሉት እንዳሴሩ ባወቀ ጊዜ ወንድሞች በቅርጫት አድርገው በጨለማ ከከተማው ቅጥር በማውረድ እንዲያመልጥ አድርገውታል።​—⁠ሥራ 9:​22-25

• ከበርካታ ዓመታት በኋላ፣ አገረ ገዥው ፊስጦስና ንጉሥ አግሪጳ “እንኳንስ ለሞት ለእስራትም የሚገባ” ጥፋት ባያገኙበትም ጳውሎስ ለቄሳር ይግባኝ ለማለት መርጧል።​—⁠ሥራ 25:​10-12, 24-27፤ 26:​30-32

[በገጽ 16, 17 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

በሺዎች የሚቆጠሩ ታማኝ የማላዊ ወንድሞች ከደረሰባቸው መራራ ስደት የተነሳ ለመሸሽ ቢገደዱም ምስራቹን በደስታ መስበካቸውን ቀጥለዋል

[በገጽ 17 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

እነዚህ ታማኝ ወንድሞች የይሖዋን ስም በማስቀደሳቸው ያገኙት ደስታ የሞት ጉዞውንና በማጎሪያ ካምፖች የደረሰባቸውን ስደት በጽናት እንዲወጡ አስችሏቸዋል

[ምንጭ]

የሞት ጉዞ:- KZ-Gedenkstätte Dachau, courtesy of the USHMM Photo Archives

[በገጽ 18 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ፈተናና ስደት በተለያዩ መንገዶች ሊደርስብን ይችላል