በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ብዙ ጥያቄዎች—ጥቂት አጥጋቢ መልሶች

ብዙ ጥያቄዎች—ጥቂት አጥጋቢ መልሶች

ብዙ ጥያቄዎች​—ጥቂት አጥጋቢ መልሶች

ኅዳር 1, 1755 የቅዱሳን ቀን በሚከበርበት ዕለት ጠዋት አብዛኞቹ የሊዝበን ነዋሪዎች ቤተ ክርስቲያን እያሉ ከተማዋ በኃይለኛ የመሬት መንቀጥቀጥ ተመታች። በሺዎች የሚቆጠሩ ሕንፃዎች ወደሙ፤ በአሥር ሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ደግሞ ለሕልፈተ ሕይወት ተዳረጉ።

አደጋው ከደረሰ ከጥቂት ጊዜ በኋላ ፈረንሳዊው ጸሐፊ ቮልቴር ፖኤም ሱር ለ ዴዛስትር ደ ሊስቦን (በሊዝበን የደረሰውን አደጋ በተመለከተ የተጻፈ ግጥም ) በሚል ርዕስ በጻፈው ግጥም ላይ አደጋው ሰዎቹ በሠሩት ኃጢአት ምክንያት የመጣ መለኮታዊ ቅጣት ነው የሚለውን አባባል ውድቅ አድርጓል። ቮልቴር እንዲህ ዓይነት አሳዛኝ ክስተቶች ከሰው የመረዳት አቅም በላይ መሆናቸውን በመግለጽ እንዲህ ሲል ጽፏል:-

ተፈጥሮ አፍ የላት፣ መልስ አትሰጠን፤

ጥያቄያችንን የሚመልስ አምላክ እንሻለን።

እርግጥ አምላክን የሚመለከት ጥያቄ በማንሳት ረገድ ቮልቴር የመጀመሪያው ሰው አይደለም። በሰው ልጅ የታሪክ ዘመናት በሙሉ የደረሱት አሰቃቂ ክስተቶችና አደጋዎች በሰዎች አእምሮ ላይ ጥያቄ ፈጥረዋል። ልጆቹን በሙሉ በሞት አጥቶ ብዙም ሳይቆይ በከባድ በሽታ የተመታው ኢዮብ ከብዙ ሺህ ዓመታት በፊት እንዲህ ሲል ጠይቆ ነበር:- ‘አምላክ በመከራ ላሉት ብርሃን፣ ነፍሳቸው ለተማረረች ሕይወት ለምን ሰጠ?’ (ኢዮብ 3:​20 አ.መ.ት ) በዛሬው ጊዜም ብዙ ሰዎች ይህ ሁሉ መከራና ግፍ እያለ ደግና አፍቃሪ የሆነ አምላክ እንዴት ዝም ብሎ ያያል ብለው ይጠይቃሉ።

ረሃብ፣ ጦርነት፣ በሽታና ሞት ባለበት ዓለም ውስጥ ለሰው ልጆች የሚያስብ አምላክ አለ የሚለውን ሐሳብ ብዙዎች አይቀበሉትም። በአምላክ መኖር የማያምን አንድ ፈላስፋ እንዲህ ሲል ተናግሯል:- “አምላክ የለም ልንል ካልሆነ በስተቀር . . . በሕፃናት ላይ ሥቃይ እንዲደርስ የሚፈቅድበት ምንም ምክንያት የለም።” በሁለተኛው የዓለም ጦርነት ወቅት ናዚዎች ያደረሱትን እልቂት የመሳሰሉ የብዙዎችን ሕይወት የቀጠፉ ክስተቶች ሰዎች አምላክ የለም የሚል መደምደሚያ ላይ እንዲደርሱ አድርገዋቸዋል። አንድ አይሁዳዊ በአንድ ጋዜጣ ላይ ያሰፈረውን ሐሳብ ተመልከት:- “በኦሽዊትዝ ለተፈጸመው ሰቆቃ ሊቀርብ የሚችለው ምክንያት በሰው ልጆች ጉዳይ ጣልቃ የሚገባ አምላክ የለም የሚል ነው።” አብዛኛው ሕዝብ የካቶሊክ እምነት ተከታይ በሆነባት በፈረንሳይ በ1997 በተካሄደ ጥናት መሠረት በዓለም ላይ በተከሰቱት የዘር ማጥፋት ወንጀሎች የተነሳ (ለምሳሌ ያህል በ1994 በሩዋንዳ የደረሰው) 40 በመቶ የሚያህሉ ፈረንሳውያን የአምላክን መኖር ይጠራጠራሉ።

በአምላክ ለማመን እንቅፋት ይሆናል?

መጥፎ ነገሮች እንዳይከሰቱ ለማድረግ አምላክ ጣልቃ የማይገባው ለምንድን ነው? አንድ የካቶሊክ ታሪክ ጸሐፊ ብዙዎች “በአምላክ እንዳያምኑ የሚያደርጋቸው ትልቁ እንቅፋት” ይህ ጥያቄ ነው ብለዋል። “በሚሊዮን የሚቆጠሩ ንጹሐን ዜጎች ሲሞቱና ሰዎች በዘራቸው ምክንያት ሲጨፈጨፉ ዝም ብሎ ከማየት ሌላ ለማስቆም ምንም ጥረት በማያደርግ አምላክ እውን ማመን ይቻላል?” ሲሉ ጠይቀዋል።

ላ ክርዋ በተባለው የካቶሊክ ጋዜጣ ላይ የወጣ አንድ ርዕስ እንዲህ የሚል ተመሳሳይ ሐሳብ አቅርቧል:- “በጥንት ዘመን የተፈጸሙ አደጋዎች፣ የዘመኑ ቴክኖሎጂ የፈጠራቸው ክስተቶች፣ የተፈጥሮ አደጋዎች፣ በተደራጀ መልክ የሚፈጸሙ ወንጀሎችም ሆኑ የሚወዱትን ሰው በሞት ማጣት የትኛውም ሁኔታ ቢሆን በድንጋጤ የተዋጡ ሰዎች ወደ ፈጣሪ እንዲመለከቱ ያደርጋቸዋል። አምላክ የት አለ? ብለው ይጠይቃሉ። ዝም ብሎ የሚመለከተው ለእኛ ግድ ባይሰጠውና ባያስብልን አይደለም?”

ሊቀ ጳጳስ ጆን ፖል ዳግማዊ በ1984 ባስተላለፉት ሳልቪፊኪ ዶሎሪስ በሚባለው ሐዋርያዊ መልእክት ላይ ስለዚህ ጉዳይ ሐሳብ ሰጥተዋል። እንዲህ ሲሉ ጽፈዋል:- “ግዑዙ ዓለም ሰዎች የአምላክን መኖር፣ ጥበቡን፣ ኃይሉንና ታላቅነቱን እንዲገነዘቡ ያስቻለ ቢሆንም ክፋትና መከራ በተለይ በየዕለቱ ተንሰራፍቶ የሚታየው ግፍ እንዲሁም ሰዎች ለፈጸሙት በደል ተገቢውን ቅጣት ሳያገኙ መታለፋቸው አንዳንድ ጊዜ እነዚህ የአምላክ ባሕርያት እንዳይታዩአቸው ይጋርዱባቸዋል።”

መጽሐፍ ቅዱስ እንደሚገልጸው አፍቃሪና ሁሉን ቻይ የሆነ አምላክ አለ የሚለውን ሐሳብ በሰው ልጆች ላይ ከሚደርሰው ሥቃይና መከራ ጋር ማስታረቅ ይቻላል? በግለሰቦችም ሆነ በጅምላ በሰዎች ላይ የሚደርሱትን አሳዛኝ ክስተቶች ለማስቆም ጣልቃ ይገባል? በዛሬው ጊዜ ለእኛ ብሎ የሚያደርግልን ነገር ይኖራል? ቮልቴር እንደተናገረው “ጥያቄያችንን የሚመልስልን አምላክ” አለ? መልሱን ለማግኘት የሚቀጥለውን ርዕስ እንድታነብ እንጋብዝሃለን።

[በገጽ 3 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

በ1755 በሊዝበን ከደረሰው ጥፋት በመነሳት ቮልቴር እንዲህ ዓይነት ክስተቶች ከሰው የመረዳት አቅም በላይ ናቸው ብሏል

[ምንጭ]

ቮልቴር:- ግሬት ሜን ኤንድ ፌመስ ዉሜን ከተባለው መጽሐፍ የተወሰደ፤ ሊዝበን:- J.P. Le Bas, Praça da Patriarcal depois do terramoto de 1755. ፎቶ:- Museu da Cidade/Lisboa

[በገጽ 4 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ብዙዎች በሩዋንዳ እንደተከሰተው ዓይነት አሰቃቂ የዘር ማጥፋት ወንጀል መፈጸሙ የአምላክን መኖር እንዲጠራጠሩ አድርጓቸዋል

[ምንጭ]

AFP PHOTO

[በገጽ 2 ላይ የሚገኝ የሥዕል ምንጭ]

COVER, children: USHMM, courtesy of Main Commission for the Prosecution of the Crimes against the Polish Nation