እምነትና ድፍረት የሚገነባ ታሪክ—የይሖዋ ምሥክሮች በዩክሬን
እምነትና ድፍረት የሚገነባ ታሪክ—የይሖዋ ምሥክሮች በዩክሬን
በመጀመሪያው መቶ ዘመን እንደነበሩት ክርስቲያኖች ሁሉ ዛሬ ያሉ የአምላክ ሕዝቦችም ስደት ደርሶባቸዋል። (ማቴዎስ 10:22፤ ዮሐንስ 15:20) ለረጅም ጊዜ የዘለቀና ከባድ ስደት ካጋጠማቸው ጥቂት አገሮች አንዷ የመንግሥቱ ስብከት ሥራ ለ52 ዓመታት የታገደባት ዩክሬን ናት።
የ2002 የይሖዋ ምሥክሮች የዓመት መጽሐፍ በዚያች አገር የአምላክ ሕዝቦች ያሳለፉትን ታሪክ ዘግቧል። መራራ የሆነ ስደት ቢያጋጥማቸውም እምነት፣ ድፍረትና የመንፈስ ጥንካሬ ያሳዩበት ታሪክ ነው። በዩክሬን የሚገኘው የይሖዋ ምሥክሮች ቅርንጫፍ ቢሮ ከደረሱት የአድናቆት መግለጫዎች መካከል ጥቂቶቹ ቀጥሎ ቀርበዋል:-
“የ2002 የዓመት መጽሐፍን አንብቤ መጨረሴ ነው። በዩክሬን ስላከናወናችሁት መንፈሳዊ እንቅስቃሴ ሳነብብ እንባዬን መቆጣጠር አልቻልኩም። ቅንዓታችሁና ጠንካራ እምነታችሁ ምን ያህል እንዳበረታታኝ ልገልጽላችሁ እወዳለሁ። የአንድ መንፈሳዊ ቤተሰብ አባላት በመሆናችን ኩራት ይሰማኛል። ልባዊ ምስጋናዬ ይድረሳችሁ!”—አንድሬ፣ ፈረንሳይ
“ስለ 2002 የዓመት መጽሐፍ ለእናንተም ሆነ ለይሖዋ ያደረብኝን የአመስጋኝነት ስሜት ለመግለጽ ቃላቶች ያጥሩኛል። የወጣትነት ዕድሜያቸውን በወኅኒ ቤቶችና በማጎሪያ ካምፖች ያሳለፉትን የበርካታ ወንድሞች ተሞክሮ ሳነብብ ዓይኖቼ እንባ አቅርረው ነበር። ድፍረታቸውን አደንቃለሁ። የይሖዋ ምሥክር ከሆንኩ 27 ዓመታት ያለፉ ቢሆንም እንኳ ከእነዚህ ወንድሞችና እህቶች ተሞክሮ ትምህርት አግኝቻለሁ። በሰማይ በሚኖረው አባታችን በይሖዋ ላይ ያለኝን እምነት አጠናክረውልኛል።”—ቬራ፣ ከቀድሞዋ ዩጎዝላቪያ
“በእነዚያ ሁሉ ዓመታት የደረሰባችሁን ስደት በመቋቋም ግሩም የሆነ የጽናትና የታማኝነት ምሳሌ ስለተዋችሁ ይህንን ደብዳቤ ስጽፍላችሁ ደስታ ይሰማኛል። በይሖዋ ሙሉ በሙሉ በመታመናችሁና ታማኝነታችሁን ለመጠበቅ በወሰዳችሁት ቆራጥ አቋም ልትከበሩ ይገባል። ከዚህም በላይ በፈተናዎች ወቅት ያሳያችሁት ትሕትና ይሖዋ ሕዝቡን እንደማይተው ያለኝን ጽኑ እምነት አጠናክሮልኛል። በድፍረት፣ በታማኝነትና በጽናት ረገድ የተዋችሁት ግሩም ምሳሌ የሚያጋጥሙንን አነስተኛ ችግሮች በጸጋ እንድንቀበል ያስችለናል።”—ቱቴሪሂኣ፣ ፍሬንች ፖሊኔዥያ
“የዓመት መጽሐፉን ካነበብኩ በኋላ ልጽፍላችሁ ተነሳሳሁ። መጽሐፉ ላይ የወጡት የሚያበረታቱ ተሞክሮዎች በጥልቅ ነክተውኛል። በተገቢው ጊዜ ብርታት የሚሰጠው አፍቃሪና ደጋፊ አባታችን በሚመራው እንደዚህ ባለ ታማኝና አንድነት ያለው ድርጅት ውስጥ በመሆኔ ኩራት ይሰማኛል። ደፋርና ቀናተኛ የሆኑ በርካታ የይሖዋ አገልጋዮች ያን ያህል በመሰቃየታቸውና አንዳንዶቹም ሕይወታቸውን በማጣታቸው በጣም አዝኛለሁ። ይሁን እንጂ እነርሱ ባሳዩት ድፍረትና ቅንዓት የተነሳ ብዙዎች እውነትን የመማርና በሰማይ የሚኖረውን አባታችንን የማወቅ አጋጣሚ በማግኘታቸው ተደስቻለሁ።”—ኮሌት፣ ኔዘርላንድስ
“እኔና ባለቤቴ በዓመት መጽሐፍ ላይ የወጣውን የዩክሬን ተሞክሮ ስናነብ ልባችን መነካቱን ለመግለጽ ልንጽፍላችሁ እንደሚገባ ተሰማን። እናንት ታማኝ ወንድሞች ለረጅም ጊዜ የዘለቀውን ከባድ ስደት በጽናት በመወጣታችሁ ግሩም ምሳሌ ትታችሁልናል። ዲያብሎስ ምንም ያህል ግፍ ቢፈጽምባቸውም አቋማቸውን ምሳሌ 27:11 እንደሚናገረው ይሖዋን ምንኛ አስደስቶት ይሆን።”—አላን፣ አውስትራሊያ
ሳያላሉ የጸኑ በርካታ ታማኝ ወንድሞች ዩክሬን ውስጥ መኖራቸውን ማየቱ“ስለ ዩክሬን ወንድሞች ሳነብብ ዓይኖቼ እንባ አቀረሩ። ለዓመታት መታሰር፣ መደብደብ፣ ጭቆናና ከቤተሰብ ተለያይቶ መኖር የመሳሰሉ በርካታ ችግሮችን በጽናት ተቋቁመዋል። አሁን በተለያዩ ጉባኤዎች ውስጥ እያገለገሉ ያሉትን ወንድሞች በጣም እንደምወዳቸውና እንደማከብራቸው ልነግራቸው እፈልጋለሁ። ያሳዩት ድፍረትና የአቋም ጽናት በጣም አስደስቶኛል። ለዚህ ኃይል ያገኙት ከይሖዋ መንፈስ እንደሆነ አውቃለሁ። ይሖዋ ከጎናችን ነው፤ እኛን መርዳትም ይፈልጋል።”—ሰርጊዬ፣ ሩሲያ
“የ2002 የዓመት መጽሐፍን ሳነብብ አለቅስ ነበር። በጉባኤያችን ያሉ በርካታ ወንድሞችና እህቶች የእናንተን ተሞክሮ የመወያያ ርዕስ አድርገውታል። ልዩ ግምት የምንሰጣችሁ ወንድሞቻችን ናችሁ። የዚህ ትልቅ መንፈሳዊ ቤተሰብ አባል በመሆኔ ከፍተኛ ደስታ ይሰማኛል።”—ዩንሂ፣ ደቡብ ኮሪያ
“ስለ እምነታችሁ፣ ስለ ጽናታችሁና ለይሖዋና ለመንግሥቱ ስላሳያችሁት የማይናወጥ ፍቅር የሚናገረው ዘገባ በጥልቅ ነክቶኛል። አንዳንድ ጊዜ የአምልኮ ነፃነታችንንና ይሖዋ አትረፍርፎ የሚሰጠንን መንፈሳዊ ምግብ ሳናደንቅ እንቀራለን። የእናንተ ሁኔታ ግን ከዚህ የተለየ ነው። ከአምላካችን ጋር የቅርብ ዝምድና ከመሠረትን ማንኛውንም ዓይነት ፈተና ለመቋቋም የሚያስችል ጥንካሬ እንደሚሰጠን እናንተ ከተዋችሁት የእምነት ምሳሌ መገንዘብ ችለናል።”—ፓውሉ፣ ብራዚል
“በ2002 የዓመት መጽሐፍ ላይ የወጣውን ተሞክሯችሁን የማንበብ አጋጣሚ አግኝቼ ነበር። ተሞክሮዎቹ በጥልቅ የነኩኝ ሲሆን በተለይ ደግሞ የእህት ሊዲያ ኩርዳስን ልብ የሚነካ ታሪክ ሳልጠቅስ አላልፍም። ለዚህች እህት ልዩ ፍቅር አድሮብኛል።”—ኒድያ፣ ኮስታ ሪካ
“የ2002 የዓመት መጽሐፍን ዛሬ አንብቤ መጨረሴ ነው። መጽሐፉን በማንበቤ በይሖዋ ላይ ያለኝ እምነት ተጠናክሯል። በአመራር ቦታ ላይ ያሉት ወንድሞች በጥርጣሬ ዓይን እንዲታዩ የሚያደርግ ወሬ ስለመናፈሱ የሚገልጸውን ዘገባ ፈጽሞ አልረሳውም። ለሥራው አመራር የሚሰጡትን ወንድሞች ፈጽሞ መጠራጠር እንደሌለብኝ አስተምሮኛል። በጣም አመሰግናችኋለሁ! ይህ መንፈሳዊ ምግብ የሚያበረታታ ከመሆኑም በላይ እምነታችን የሚፈተንበት ጊዜ ቢመጣ እንዴት መወጣት እንደምንችል ያዘጋጀናል።”—ሌቲሲያ፣ ዩናይትድ ስቴትስ
“ግሩም ለሆነው የዓመት መጽሐፍ አመስጋኞች ነን። አብዛኞቹ አስፋፊዎች በዩክሬን ስላሉት ወንድሞቻችን መንፈሳዊ እንቅስቃሴ ሲያነቡ ይህ የመጀመሪያ ጊዜያቸው ነው። እዚህ ያሉት ወንድሞች ማበረታቻ አግኝተውበታል። አብዛኞቹ አስፋፊዎች በተለይ ወጣት የሆኑት የአገልግሎት እንቅስቃሴያቸውን አሳድገዋል። አንዳንዶች የዘወትር ወይም ረዳት አቅኚ ሆነው ማገልገል ጀምረዋል። በእገዳው ሥር ይሖዋን ስላገለገሉ ወንድሞችና እህቶች የሚናገረው ታሪክ የጉባኤያችንን አባላት በሙሉ አበረታቷቸዋል።”—በዩክሬን የሚገኝ ጉባኤ የአገልግሎት ኮሚቴ
በእርግጥም በዩክሬን የሚገኙ ወንድሞቻችን ያሳዩት ታማኝነት በዓለም ዙሪያ ለሚገኙ የይሖዋ ሕዝቦች የብርታት ምንጭ ሆኖላቸዋል። በዓመት መጽሐፍ ላይ በየዓመቱ የሚወጡትን አስደሳች ታሪኮች ማንበብ በዚህ ወሳኝ ወቅት እምነታችንንና ጽናታችንን ማጠናከር የምንችልበት ግሩም መንገድ ነው።—ዕብራውያን 12:1