በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ይሖዋ ትሑት ሰዎችን ወደ እውነት ያመጣቸዋል

ይሖዋ ትሑት ሰዎችን ወደ እውነት ያመጣቸዋል

የሕይወት ታሪክ

ይሖዋ ትሑት ሰዎችን ወደ እውነት ያመጣቸዋል

አሳኖ ኮሲኖ እንደተናገረችው

በ1949፣ ሁለተኛው የዓለም ጦርነት ካበቃ ከጥቂት ዓመታት በኋላ መሆኑ ነው ቁመናው ዘለግ ያለ አንድ ተግባቢ የሆነ የውጭ አገር ዜጋ በኮቤ ከተማ ተቀጥሬ እሠራበት የነበረውን ቤተሰብ ሊጠይቅ መጣ። ይህ ሰው ወደ ጃፓን የመጣ የመጀመሪያው የይሖዋ ምስክሮች ሚስዮናዊ ነበር። የእርሱ መምጣት የመጽሐፍ ቅዱስን እውነት እንድሰማ አጋጣሚ ከፍቶልኛል። መጀመሪያ ግን እስቲ ስለ አስተዳደጌ ልንገራችሁ።

በ1926 በሰሜናዊ ኦካያማ ግዛት በአንዲት ትንሽ መንደር ውስጥ ተወለድኩ። ከስምንት ልጆች መካከል አምስተኛዋ ነበርኩ። አባቴ በአካባቢያችን በሚገኘው የሺንቶ ቤተ መቅደስ ለሚመለከው አምላክ ያደረ ነበር። በመሆኑም ልጆች እያለን፣ በዓመቱ ውስጥ የሚኖሩትን ሃይማኖታዊ በዓላት ማክበርና ከዘመድ አዝማድ ጋር መገናኘት ያስደስተን ነበር።

እያደግሁ ስሄድ ሕይወትን የሚመለከቱ ብዙ ጥያቄዎች የነበሩኝ ሲሆን ይበልጡን የሚያሳስበኝ ግን የሞት ጉዳይ ነበር። በባሕሉ መሠረት ሰው ሊሞት ሲል ቤቱ እንዲሆንና ልጆች በሟቹ አጠገብ እንዲገኙ ይደረጋል። ሴት አያቴ እንዲሁም አንድ ዓመት እንኳ ያልሞላው ታናሽ ወንድሜ በመሞታቸው ከባድ ሐዘን ተሰማኝ። ወላጆቼም አንድ ቀን ይሞታሉ የሚለው ሐሳብ በጣም ያስጨንቀኝ ነበር። ‘ሕይወት ማለት በቃ ይኸው ነው? ሕይወት ከዚህ የተሻለ ትርጉም ይኖረው ይሆን?’ እነዚህ ጥያቄዎች ይከነክኑኝ ነበር።

በ1937 የስድስተኛ ክፍል ተማሪ ሳለሁ በቻይናና በጃፓን መካከል ጦርነት ተጀመረ። ወንዶች እየተመለመሉ ለውጊያ ወደ ቻይና ይላኩ ነበር። ተማሪዎች ለንጉሠ ነገሥቱ ረዥም ዕድሜ እንደሚመኙ ለመግለጽ “ባንዛይ!” የሚል መፈክር እያሰሙ አባቶቻቸውን ወይም ወንድሞቻቸውን ይሸኙ ነበር። ጃፓናውያን እንደ አምላክ የሚታይ ንጉሠ ነገሥት ያላትና በአምላክ የምትገዛው አገራቸው ድል እንደምትቀዳጅ እርግጠኞች ነበሩ።

ብዙም ሳይቆይ ቤተሰቦች በጦር ሜዳ የሞቱ ዘመዶቻቸው መርዶ ይደርሳቸው ጀመር። እነዚህ ቤተሰቦች ከሐዘናቸው መጽናናት አልቻሉም። ልባቸው በጥላቻ ስለተሞላ የጠላት ሠራዊት ከባድ እልቂት ሲደርስበት በደስታ ይፈነድቁ ነበር። ይሁን እንጂ ‘በጠላት ወገን ያሉ ሰዎችም እኮ ዘመዶቻቸው ሲሞቱ ልክ እንደኛው ማዘናቸው አይቀርም’ ብዬ አሰብኩ። የአንደኛ ደረጃ ትምህርቴን ባጠናቀቅኩበት ጊዜ በቻይና ጦርነቱ ተባብሶ ነበር።

ከአንዲት የውጭ ዜጋ ጋር ተገናኘሁ

ቤተሰባችን የሚተዳደረው በግብርና ስለነበር ከድህነት ተላቅቀን አናውቅም። ሆኖም አባቴ ክፍያ የማይጠይቅ እስከሆነ ድረስ ትምህርቴን እንድገፋበት ፈቀደልኝ። ስለዚህም በ1941፣ መቶ ኪሎ ሜትር ርቆ በሚገኘው በኦካያማ ሲቲ ባለ የልጃገረዶች ትምህርት ቤት ገባሁ። ትምህርት ቤቱ ልጃገረዶች ባለሞያ ሚስቶችና እናቶች እንዲሆኑ የሚያስችል ሥልጠና ለመስጠት ታስቦ የተከፈተ ነው። በመሆኑም ተማሪዎቹ የቤት አያያዝ ልምድ እንዲያገኙ በከተማው ካሉ ሀብታም ቤተሰቦች ጋር እንዲኖሩ ይመድባቸዋል። ተማሪዎቹ ጠዋት ጠዋት በሚኖሩበት ቤት ውስጥ የተለያዩ ሥራዎች በመሥራት ሥልጠና የሚያገኙ ሲሆን ከሰዓት በኋላ ደግሞ ወደ ትምህርት ቤት ይሄዳሉ።

ለተማሪዎቹ የሚደረገው የአቀባበል ሥነ ሥርዓት ሲያበቃ የጃፓናውያን ባሕላዊ ልብስ የለበሰችው አስተማሪዬ ወደ አንድ ትልቅ ቤት ወሰደችኝ። ሆኖም የቤቱ እመቤት እኔ ባላወቅሁት ምክንያት ሳትቀበለኝ ቀረች። አስተማሪዬ “እንግዲያው ወደ ወይዘሮ ኮዳ ቤት እንሂድ ይሆን?” ብላ ጠየቀች። በምዕራባውያን ንድፍ ወደ ተሠራ ቤት ወሰደችኝና የበሩን ደወል ደወለች። ከጥቂት ቆይታ በኋላ አንዲት ረዘም ያሉ ሸበቶ ወይዘሮ በሩን ከፈቱ። ገና ሳያቸው በጣም ደነገጥኩ! ሴትየዋ ጃፓናዊት አይደሉም፤ እኔ ደግሞ ፈረንጅ አይቼ አላውቅም ነበር። አስተማሪዬ ከወይዘሮ ሞድ ኮዳ ጋር አስተዋወቀችኝና ወዲያው ተመለሰች። ሻንጣዬን እየጎተትኩ ስፈራ ስቸር ወደ ቤት ገባሁ። በኋላ ላይ ወይዘሮ ኮዳ አሜሪካዊት እንደሆኑና ባለቤታቸው በዩናይትድ ስቴትስ የተማሩ ጃፓናዊ እንደሆኑ አወቅሁ። ወይዘሮ ኮዳ በንግድ ትምህርት ቤቶች እንግሊዝኛ ያስተምሩ ነበር።

ከማግስቱ ጠዋት አንስቶ በሥራ ተጠመድኩ። የወይዘሮ ኮዳ ባለቤት የሚጥል በሽታ ስለነበረባቸው እርሳቸውን በመንከባከብ አግዛቸው ነበር። እንግሊዝኛ ምንም ስለማላውቅ ትንሽ ተጨንቄ ነበር። ወይዘሮ ኮዳ በጃፓንኛ ሲያናግሩኝ ጭንቀቱ ለቀቀኝ። እርስ በርሳቸው በእንግሊዝኛ ሲነጋገሩ በየቀኑ እሰማ ስለነበር ቀስ በቀስ ቋንቋውን እየለመድኩት መጣሁ። በቤቱ ውስጥ ያለውን ደስ የሚል ሁኔታ ወደድኩት።

ሞድ ታማሚ ለሆኑት ባለቤታቸው የሚያደርጉላቸው እንክብካቤ አስገረመኝ። ባለቤታቸው መጽሐፍ ቅዱስ ማንበብ ይወድዳሉ። እነዚህ ባልና ሚስት መለኮታዊው የዘመናት እቅድ የተሰኘውን መጽሐፍ የጃፓንኛ እትም ከአሮጌ መጽሐፍ መሸጫ እንደገዙና በርከት ላሉ ዓመታት የመጠበቂያ ግንብ መጽሔት ኮንትራት በእንግሊዝኛ ሲደርሳቸው እንደቆየ አወቅሁ።

አንድ ቀን መጽሐፍ ቅዱስ በስጦታ ተሰጠኝ። የራሴ መጽሐፍ ቅዱስ ያገኘሁት በሕይወቴ ለመጀመሪያ ጊዜ በመሆኑ በጣም ደስ አለኝ። ትምህርት ቤት ስሄድና ስመለስ በመንገድ ላይ አነብበው ነበር፤ ቢሆንም እምብዛም አይገባኝም። ያደግሁት በጃፓን የሺንቶ ሃይማኖት ውስጥ ስለሆነ ስለ ኢየሱስ ክርስቶስ የማውቀው ነገር አልነበረም። ይህም ስለ ሕይወትና ስለ ሞት ላሉኝ ጥያቄዎች መልስ የሚሰጠኝን የመጽሐፍ ቅዱስን እውነት ወደ መቀበል እንደሚያመራኝ አልተገነዘብኩም ነበር።

ሦስት አሳዛኝ ክስተቶች

የሁለት ዓመት የሥልጠና ጊዜዬ በፍጥነት አለፈና ቤተሰቡን ተሰናብቼ የምሄድበት ጊዜ ደረሰ። ትምህርቴን ስጨርስ በፈቃደኝነት የሚሠሩ ወጣት ሴቶች ማኅበር ውስጥ ገብቼ የባሕር ኃይል የደንብ ልብስ በማዘጋጀት ሥራ ተሰማራሁ። የአሜሪካ ቢ-29 ጄቶች የቦምብ ድብደባ ጀመሩ። ነሐሴ 6, 1945 በሂሮሽማ ላይ አቶሚክ ቦምብ ተጣለ። ከጥቂት ቀናት በኋላ እናቴ በጠና መታመሟን የሚገልጽ የቴሌግራም መልእክት ደረሰኝ። መጀመሪያ ባገኘሁት ባቡር ተሳፍሬ ወደቤት ሄድኩ። ከባቡሩ ስወርድ አንድ ዘመዴ ተቀበለኝና እናቴ ማረፏን ነገረኝ። የሞተችው ነሐሴ 11 ነበር። ለዓመታት ስፈራው የነበረው ነገር ደረሰ! በቃ ከእንግዲህ ልታናግረኝ አትችልም፤ ፊቷንም አላይም ማለት ነው።

ነሐሴ 15 ጃፓን መሸነፏ ተረጋገጠ። ስለዚህ በአሥር ቀናት ውስጥ ሦስት አሳዛኝ ክስተቶች ደረሱብኝ:- የአቶሚክ ቦምብ ፍንዳታ፣ የእናቴ መሞትና ጃፓን የደረሰባት ታሪካዊ ሽንፈት። ቢያንስ ቢያንስ ጦርነቱ ስላበቃ በውጊያ የሚሞቱ ሰዎች እንደማይኖሩ ማወቁ የሚያጽናና ነበር። ልቤ በሐዘን ተሞልቶ ሥራዬን ትቼ ወደ ትውልድ መንደሬ ተመለስኩ።

እውነትን ሰማሁ

አንድ ቀን በኦካያማ ከሚኖሩት ከወይዘሮ ሞድ ኮዳ ያልተጠበቀ ደብዳቤ ደረሰኝ። የእንግሊዝኛ ትምህርት ቤት ሊከፍቱ ስላሰቡ እንደገና ተመልሼ በቤት ውስጥ ሥራ ልረዳቸው እችል እንደሆነ ጠየቁኝ። ምን ባደርግ እንደሚሻል ግራ ቢገባኝም በመጨረሻ ለመሄድ ወሰንኩ። ከጥቂት ዓመታት በኋላ ከዚህ ቤተሰብ ጋር ወደ ኮቤ ተዛወርኩ።

በ1949 የበጋ ወራት መጀመሪያ ላይ ቁመናው ዘለግ ያለ አንድ ተግባቢ ሰው ባልና ሚስቱን ለመጠየቅ መጣ። ዳነልድ ሃስሌት የሚባል ሲሆን ከቶኪዮ ወደ ኮቤ የመጣውም ለሚስዮናውያን የሚሆን ቤት ለማፈላለግ ነበር። ወደ ጃፓን የመጣው የመጀመሪያው የይሖዋ ምስክሮች ሚስዮናዊ ነበር። በመጨረሻም ቤት አገኘና ኅዳር 1949 በርከት ያሉ ሚስዮናውያን ኮቤ ገቡ። አንድ ቀን አምስት ሚስዮናውያን የኮዳን ቤተሰብ ለመጠየቅ የመጡ ሲሆን ሎይድ ባሪና ፐርሲ ኢዛሎብ በቤቱ ለተሰበሰቡት ሰዎች የአሥር የአሥር ደቂቃ ንግግር አቀረቡ። ሚስዮናውያኑ ወይዘሮ ሞድ የይሖዋ ምሥክር መሆናቸውን ያውቁ ነበር፤ እርሳቸውም ከእነርሱ ጋር በመገናኘታቸው ተበረታተዋል። እንግሊዝኛ ለመማር የተነሳሳሁት በዚህ ጊዜ ነበር።

በእነዚያ ቀናተኛ ሚስዮናውያን እርዳታ ቀስ በቀስ መሠረታዊ የመጽሐፍ ቅዱስ እውነቶችን መረዳት ቻልኩ። ከልጅነቴ ጀምሮ ለነበሩኝ ጥያቄዎች መልስ አገኘሁ። አዎን፣ መጽሐፍ ቅዱስ በምድር ላይ በገነት ለዘላለም የመኖር ተስፋ የያዘ ሲሆን “በመቃብር ያሉ[ት] ሁሉ” ትንሣኤ እንደሚያገኙም ይናገራል። (ዮሐንስ 5:​28, 29፤ ራእይ 21:​1, 4) ይሖዋ በልጁ በኢየሱስ ክርስቶስ ቤዛዊ መሥዋዕት አማካኝነት እንዲህ ዓይነቱን ተስፋ በማዘጋጀቱ አመሰገንኩት።

አስደሳች ቲኦክራሲያዊ እንቅስቃሴዎች

ከታኅሣሥ 30, 1949 ጀምሮ እስከ ጥር 1, 1950 ድረስ በጃፓን የመጀመሪያው የይሖዋ ምሥክሮች የአውራጃ ስብሰባ በኮቤ ባለው የሚስዮናውያን ቤት ተካሄደ። እኔም ከሞድ ጋር ወደ ስብሰባው ሄድኩ። ይህ ትልቅ ቤት በመጀመሪያ የአንድ የናዚ አባል መኖሪያ የነበረ ሲሆን ውብ የሆነውን ባሕረ ገብ መሬትና የአዋጂን ደሴት ከዚህ ቦታ ማየት ይቻላል። የነበረኝ የመጽሐፍ ቅዱስ እውቀት ውስን ስለነበር በስብሰባው ላይ ከተሰጠው ትምህርት የተረዳሁት ጥቂቱን ብቻ ነበር። ሆኖም ሚስዮናውያኑ ከጃፓናውያኑ ጋር እንደልብ መቀላቀላቸው ተአምር ሆነብኝ። በዚህ ስብሰባ ላይ የሕዝብ ንግግሩን ለማዳመጥ 101 ተሰብሳቢዎች ተገኝተው ነበር።

ከዚያ ብዙም ሳይቆይ በመስክ አገልግሎት ለመካፈል ወሰንኩ። በተፈጥሮዬ ዓይን አፋር ስለነበርኩ ከቤት ወደቤት መሄድ ድፍረት ጠይቆብኝ ነበር። አንድ ቀን ጠዋት ወንድም ሎይድ ባሪ አገልግሎት ይዞኝ ለመሄድ ወደ ቤታችን መጣ። ከእህት ኮዳ ቤት አጠገብ ካለው ቤት ጀመረ። እርሱ ምስራቹን ሲናገር ከኋላው ተደብቄ ነበር ማለት እችላለሁ። ለሁለተኛ ጊዜ አገልግሎት የሄድኩት ከሁለት ሚስዮናውያን እህቶች ጋር ነበር። አንዲት በዕድሜ የገፉ ጃፓናዊት ሴት በቤታቸው ተቀብለው አዳመጡንና በኋላም ወተት አቀረቡልን። እርሳቸውም መጽሐፍ ቅዱስ ለማጥናት የተስማሙ ሲሆን ከጊዜ በኋላም የተጠመቁ እህት ሆኑ። ያደረጉትን እድገት መመልከት የሚያበረታታ ነበር።

ሚያዝያ 1951፣ ብሩክሊን በሚገኘው ዋና መሥሪያ ቤት ያገለግል የነበረው ወንድም ናታን ኤች ኖር ለመጀመሪያ ጊዜ ጃፓን መጥቶ ጎበኘን። በካንዳ፣ ቶኪዮ በሚገኘው በኪዮሪትሱ አዳራሽ ያቀረበውን የሕዝብ ንግግር ለማዳመጥ 700 የሚያህሉ ሰዎች ተገኝተው ነበር። በዚህ በዓይነቱ ልዩ የሆነ ስብሰባ ላይ የተገኙት ሁሉ በጃፓንኛ ቋንቋ መጠበቂያ ግንብ መታተም መጀመሩን ሲሰሙ በጣም ተደሰቱ። በቀጣዩ ወር ወንድም ኖር ኮቤን የጎበኘ ሲሆን በዚያ በተደረገው ልዩ ስብሰባ ላይ ሕይወቴን ለይሖዋ መወሰኔን በጥምቀት አሳየሁ።

ከአንድ ዓመት ገደማ በኋላ የሙሉ ጊዜ አገልግሎት ማለትም አቅኚነት ለመጀመር ወሰንኩ። በዚያን ጊዜ በጃፓን የነበሩት አቅኚዎች ጥቂት ነበሩ። በምን እተዳደራለሁ የሚለው ጉዳይ በጣም አሳሰበኝ። በተጨማሪም ወደፊት ትዳር የመመስረት አጋጣሚ ይኖረኝ ይሆን የሚለውም አሳስቦኝ ነበር። ሆኖም ይሖዋን ማገልገል በሕይወት ውስጥ ቅድሚያ ሊሰጠው የሚገባ ነገር እንደሆነ ስለተገነዘብኩ በ1952 የዘወትር አቅኚ ሆንኩ። በትርፍ ጊዜዬ ለእህት ኮዳ እየሠራሁ በአቅኚነት ማገልገል መቻሌ አስደሰተኝ።

በጦርነቱ ሞቷል ብዬ ያሰብኩት ወንድሜ በዚሁ ጊዜ ከቤተሰቡ ጋር ከታይዋን ተመልሶ መጣ። ቤተሰቤ ለክርስትና ምንም ፍላጎት ያልነበራቸው ቢሆንም ቀናተኛ አቅኚ ስለነበርኩ በይሖዋ ድርጅት የሚዘጋጁትን መጽሔቶችና ትናንሽ መጻሕፍት እልክላቸው ጀመር። ቆየት ብሎ ወንድሜ በሥራው ምክንያት ከቤተሰቡ ጋር ወደ ኮቤ ተዛወረ። የወንድሜን ሚስት “መጽሔቶቹን አነበብሻቸው?” ብዬ ጠየቅኳት። “አዎን፣ ወድጃቸዋለሁ” ስትለኝ ተገረምኩ። ከአንዷ ሚስዮናዊ ጋር መጽሐፍ ቅዱስን ማጥናት ጀመረች። አብራቸው ትኖር የነበረችው ታናሽ እህቴም ከእርሷ ጋር አጠናች። ከጊዜ በኋላ ሁለቱም የተጠመቁ ክርስቲያኖች ሆኑ።

በዓለም አቀፋዊው ወንድማማችነት ተደነቅሁ

ብዙም ሳይቆይ በጊልያድ የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት ቤት በ22ኛው ክፍል እንድገኝ መጋበዜ ፈጽሞ ያልጠበቅሁት ነገር ሆነብኝ። ከጃፓን ለመጀመሪያ ጊዜ ወደ ትምህርት ቤቱ የተጋበዝነው ተማሪዎች እኔና ወንድም ጹቶሙ ፉካሴ ነበርን። በ1953 ትምህርት ከመጀመሩ በፊት በኒው ዮርክ፣ ያንኪ ስታዲየም በተደረገው የአዲሱ ዓለም ኅብረተሰብ የተባለ ትልቅ ስብሰባ ላይ መገኘት ችለን ነበር። በይሖዋ ሕዝቦች መካከል በሚታየው ዓለም አቀፋዊ ወንድማማችነት በእጅጉ ተደነቅሁ።

በስብሰባው አምስተኛ ቀን አብዛኞቹ ሚስዮናውያን የሆኑት ከጃፓን የመጡት ልዑካን ኪሞኖ የሚባለውን የጃፓንን ባሕላዊ ልብስ መልበስ ነበረባቸው። ከመምጣቴ አስቀድሜ የላክሁት ኪሞኖ በሰዓቱ ባለመድረሱ ከወንድም ኖር ባለቤት ተውሼ ለበስኩ። በስብሰባው ላይ እንዳለን ዝናብ መጣል በመጀመሩ ልብሱ በዝናብ እንዳይበሰብስ ተጨነቅሁ። በዚህ ጊዜ ከጀርባዬ ያለ አንድ ሰው የዝናብ ካፖርት አለበሰኝ። አጠገቤ የቆመች አንዲት እህት “ማን እንደሆነ ታውቂያለሽ?” ስትል ጠየቀችኝ። ከአስተዳደር አካል አባላት አንዱ የሆነው ወንድም ፍሬድሪክ ደብልዩ ፍራንዝ መሆኑን በኋላ ላይ አወቅሁ። የይሖዋ ድርጅት ሞቅ ያለ ፍቅር የሰፈነበት መሆኑን ማየት ችያለሁ!

22ኛው የጊልያድ ትምህርት ቤት ከ37 አገሮች የመጡ 120 ተማሪዎችን የያዘ ስለነበር በእርግጥም ዓለም አቀፋዊ ነው ሊባል ይችላል። የተለያየ ቋንቋ ስለምንናገር አንዳንድ ጊዜ መግባባት ቢቸግረንም በዓለም አቀፋዊው የወንድማማች ማኅበር በጣም ተደስተናል። የካቲት 1954 በአንድ በረዷማ ቀን ተመርቄ እዚያው ጃፓን እንዳገለግል ተመደብኩ። አብራኝ የተማረችው ኢንገር ብራንት የተባለች ስዊድናዊት እህት በናጎያ ከተማ የአገልግሎት ጓደኛዬ ሆና ተመደበች። በወቅቱ በኮሪያ ይደረግ በነበረው ጦርነት ሳቢያ ከአገሪቱ ተባርረው ወደ ናጎያ ከመጡት ሚስዮናውያን ጋር ተቀላቀልን። በሚስዮናዊነት ያሳለፍኳቸው ጥቂት ዓመታት ፈጽሞ ከአእምሮዬ አይጠፉም።

ባልና ሚስት ሆነን በደስታ ማገልገል

መስከረም 1957 በቶኪዮ ቤቴል እንዳገለግል ተጠየቅሁ። የጃፓን ቅርንጫፍ ቢሮ ባለ ሁለት ፎቅ የእንጨት ቤት ነበር። የቅርንጫፍ ቢሮው የበላይ ተመልካች የሆነውን ወንድም ባሪን ጨምሮ የቅርንጫፍ ቢሮው አባላት አራት ነበሩ። የተቀሩት የቤቴል ቤተሰብ አባላት ሚስዮናውያን ነበሩ። ከትርጉም ሥራ በተጨማሪ ጽዳት፣ ልብስ አጠባ፣ ምግብ ማብሰልና ሌሎች ሥራዎች እንድሠራ ተመደብኩ።

በጃፓን ሥራው እያደገ ስለነበር ተጨማሪ ወንድሞች ወደ ቤቴል ተጠሩ። ከእነርሱ መካከል አንዱ እኔ በነበርኩበት ጉባኤ የበላይ ተመልካች ሆኖ ተሾመ። በ1966 ጁንጂ ኮሲኖ ከተባለው ከዚህ ወንድም ጋር ተጋባን። ከተጋባን በኋላ ጁንጂ በወረዳ የበላይ ተመልካችነት እንዲያገለግል ተመደበ። ወደ ተለያዩ ጉባኤዎች ስንጓዝ ከብዙ ወንድሞችና እህቶች ጋር መተዋወቅ መቻላችን አስደስቶናል። የሚተረጎሙ ጽሑፎች ይሰጡኝ ስለነበር ሳምንቱን በምናሳልፍበት ቤት የትርጉም ሥራ አከናውን ነበር። በምንጓዝበት ጊዜ ከልብስ ሻንጣችንና ከሌላው ጓዛችን በተጨማሪ ከባባድ መዝገበ ቃላትን መሸከም ነበረብን።

በቤቴል ለማገልገል ከመመለሳችን በፊት በወረዳ የበላይ ተመልካችነት አራት አስደሳች ዓመታት አሳልፈናል። ድርጅቱም እየሰፋ ሲሄድ ተመልክተናል። ቅርንጫፍ ቢሮው ወደ ኑማዙ፣ ከዓመታት በኋላ ደግሞ አሁን ወደሚገኝበት ወደ ኢቢና ተዛወረ። ከዚያን ጊዜ አንስቶ እኔና ጁንጂ በቤቴል አገልግሎት እየተካፈልን ሲሆን አሁን የቤቴል ቤተሰብ አባላት 600 ያህል ሆነዋል። ግንቦት 2002 በቤቴል ያሉ ጓደኞቼ በሙሉ ጊዜ አገልግሎት ያሳለፍኩትን 50ኛ ዓመት እንዳከብር በደግነት ዝግጅት አደረጉልኝ።

ጭማሪ በማየት ተባረክሁ

በ1950 ይሖዋን ማገልገል ስጀምር በጃፓን የነበሩት አስፋፊዎች በጣት የሚቆጠሩ ነበሩ። አሁን ከ210, 000 በላይ የመንግሥቱ አስፋፊዎች አሉ። በእርግጥም ልክ እንደኔው በሺዎች የሚቆጠሩ በግ መሰል ሰዎች ወደ ይሖዋ ተስበዋል።

በ1949 እህት ኮዳ ቤት ሊጠይቁን የመጡት ሚስዮናውያን የሆኑ አራት ወንድሞችና አንዲት እህት እንዲሁም ሞድ ኮዳ ታማኝነታቸውን ጠብቀው አልፈዋል። የጉባኤ አገልጋይ የነበረው ወንድሜና ለ15 ዓመታት በአቅኚነት ያገለገለችው ባለቤቱም ታማኝነታቸውን እንደጠበቁ በሞት አንቀላፍተዋል። በልጅነቴ የወላጆቼን ሞት ሳስብ ፍርሃት ፍርሃት ይለኝ ነበር፤ የእነርሱስ ተስፋ ምንድን ነው? በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሰፈረው የትንሣኤ ትምህርት ተስፋና መጽናኛ እንዳገኝ አስችሎኛል።_​—⁠ሥራ 24:​15

ወደኋላ መለስ ብዬ ሳስበው በ1941 ከሞድ ጋር መገናኘቴ ሕይወቴ እንዲለወጥ ያደረገ አጋጣሚ እንደሆነ ይሰማኛል። በዚያን ጊዜ እርሳቸውን ባላገኛቸውና ከጦርነቱ በኋላ እነርሱ ጋር እንድሠራ ያቀረቡልኝን ሐሳብ ባልቀበል ኖሮ ርቆ በሚገኘው የገጠር መንደር በግብርና እየተዳደርኩ እዚያው ልቀርና ከሚስዮናውያኑ ጋር የመገናኘት አጋጣሚ ሊያመልጠኝ ይችል ነበር። ይሖዋ በሞድ እና በእነዚያ ቀደምት ሚስዮናውያን አማካኝነት ወደ እውነት ስለሳበኝ በጣም አመሰግነዋለሁ!

[በገጽ 25 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ከሞድ ኮዳና ከባለቤታቸው ጋር። ከፊት በኩል በስተ ግራ ያለሁት እኔ ነኝ

[በገጽ 27 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

በ1953 በያንኪ ስታዲየም ከጃፓን ከመጡ ሚስዮናውያን ጋር። በስተ ግራ ዳር ላይ ያለሁት እኔ ነኝ

[በገጽ 28 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

በቤቴል፣ ከባለቤቴ ከጁንጂ ጋር