በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ሽልማቱን ለማግኘት ራስን የመግዛት ባሕርይ አሳዩ

ሽልማቱን ለማግኘት ራስን የመግዛት ባሕርይ አሳዩ

ሽልማቱን ለማግኘት ራስን የመግዛት ባሕርይ አሳዩ

“የሚታገልም ሁሉ በነገር ሁሉ ሰውነቱን ይገዛል።”—1 ቆሮንቶስ 9:25

1. በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎች ከኤፌሶን 4:22-24 ጋር በሚስማማ መንገድ ምን እርምጃ ወስደዋል?

 የተጠመቅህ የይሖዋ ምሥክር ከሆንህ የዘላለም ሕይወት ሽልማት በሚያስገኝ ውድድር ውስጥ ለመካፈል እንደምትፈልግ ለሕዝብ አሳውቀሃል። የይሖዋን ፈቃድ ለማድረግም ተስማምተሃል። ብዙዎቻችን ራሳችንን ለይሖዋ ከመወሰናችን በፊት ይህ ውሳኔያችን ከልብ የመነጨና በአምላክ ዘንድ ተቀባይነት የሚያስገኝልን እንዲሆን በሕይወታችን ላይ ጉልህ ለውጦችን ማድረግ አስፈልጎን ነበር። ሐዋርያው ጳውሎስ እንደሚከተለው በማለት ለክርስቲያኖች የሰጠውን ምክር ተግባራዊ አድርገን ነበር:- “ፊተኛ ኑሮአችሁን እያሰባችሁ እንደሚያታልል ምኞት የሚጠፋውን አሮጌውን ሰው አስወግዱ፣ . . . ለእውነትም በሚሆኑ ጽድቅና ቅድስና እንደ እግዚአብሔር ምሳሌ የተፈጠረውን አዲሱን ሰው ልበሱ።” (ኤፌሶን 4:22-24) በሌላ አነጋገር ራሳችንን ለአምላክ ከመወሰናችን በፊት ተቀባይነት የሌለውን የቀድሞ አኗኗራችንን እርግፍ አድርገን መተው ነበረብን።

2, 3. 1 ቆሮንቶስ 6:9-12 የአምላክን ሞገስ ለማግኘት ሁለት ዓይነት ለውጦች ማድረግ እንዳለብን የሚያሳየው እንዴት ነው?

2 የይሖዋ ምሥክር ለመሆን የሚፈልጉ ሁሉ አውልቀው ሊጥሏቸው ከሚገቡት የአሮጌው ሰውነት ክፍሎች ውስጥ አንዳንዶቹ በአምላክ ቃል ውስጥ በቀጥታ የተወገዙ ናቸው። ጳውሎስ ለቆሮንቶስ ክርስቲያኖች በጻፈው ደብዳቤ ላይ አንዳንዶቹን እንዲህ ሲል ጠቅሷል:- “ሴሰኞች ቢሆኑ ወይም ጣዖትን የሚያመልኩ ወይም አመንዝሮች ወይም ቀላጮች ወይም ከወንድ ጋር ዝሙት የሚሠሩ ወይም ሌቦች ወይም ገንዘብን የሚመኙ ወይም ሰካሮች ወይም ተሳዳቢዎች ወይም ነጣቂዎች የእግዚአብሔርን መንግሥት አይወርሱም።” አክሎም የመጀመሪያው መቶ ዘመን ክርስቲያኖች የሚፈለግባቸውን የባሕርይ ለውጥ እንዳደረጉ ሲናገር “ከእናንተም አንዳንዶቹ እንደ እነዚህ ነበራችሁ” ብሏል። ነበራችሁ እንጂ ናችሁ እንዳላለ ልብ በል።—1 ቆሮንቶስ 6:9-11

3 ጳውሎስ “ሁሉ ተፈቅዶልኛል፣ ሁሉ ግን አይጠቅምም” በማለት ተጨማሪ ለውጦች ማድረግ እንደሚያስፈልግም ገልጿል። (1 ቆሮንቶስ 6:12) ስለሆነም በጊዜያችን የይሖዋ ምሥክሮች ለመሆን የሚፈልጉ ብዙ ሰዎች በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ባይወገዙም ምንም እርባና በሌላቸው ነገሮች ከመካፈል መቆጠብ አስፈላጊ መሆኑን ይገነዘባሉ። እነዚህ ነገሮች ጊዜያችንን ሊሻሙብንና የላቀ ጠቀሜታ ያላቸውን ግቦች ከመከተል ሊያዘናጉን ይችላሉ።

4. ራሳቸውን ለአምላክ የወሰኑ ክርስቲያኖች በየትኛው የጳውሎስ ሐሳብ ይስማማሉ?

4 ራሳችንን ለአምላክ የምንወስነው በሙሉ ፈቃደኝነት እንጂ ትልቅ መሥዋዕትነት የሚጠይቅብን ይመስል ቅር እያለን መሆን አይኖርበትም። ራሳቸውን ለአምላክ የወሰኑ ክርስቲያኖች ጳውሎስ የክርስቶስ ተከታይ ከሆነ በኋላ “ስለ እርሱ ሁሉን ተጐዳሁ፣ ክርስቶስንም አገኝ ዘንድ፣ . . . በእርሱ እገኝ ዘንድ ሁሉን እንደ ጒድፍ እቈጥራለሁ” በማለት በተናገረው ሐሳብ ይስማማሉ። (ፊልጵስዩስ 3:8) ጳውሎስ የአምላክን ፈቃድ ለማድረግ ሲል እርባና የሌላቸውን ነገሮች እርግፍ አድርጎ ትቷል።

5. ጳውሎስ በድል ያጠናቀቀው የትኛውን ሩጫ ነው? እኛስ እንደ እርሱ ሊሳካልን የሚችለው እንዴት ነው?

5 ጳውሎስ መንፈሳዊ ሩጫውን ሲሮጥ ራስን የመግዛት ባሕርይ አሳይቶ ነበር። ስለሆነም በሩጫው ማገባደጃ ላይ እንዲህ ለማለት ችሏል:- “መልካሙን ገድል ተጋድዬአለሁ፣ ሩጫውን ጨርሼአለሁ፣ ሃይማኖትን ጠብቄአለሁ፤ ወደ ፊት የጽድቅ አክሊል ተዘጋጅቶልኛል፣ ይህንም ጻድቅ ፈራጅ የሆነው ጌታ ያን ቀን ለእኔ ያስረክባል፣ ደግሞም መገለጡን ለሚወዱት ሁሉ እንጂ ለእኔ ብቻ አይደለም።” (2 ጢሞቴዎስ 4:7, 8) እኛስ አንድ ቀን እንዲህ ለማለት እንበቃ ይሆን? ክርስቲያናዊ ሩጫችንን እስከ ፍጻሜው በጽናት እየሮጥን ራስን የመግዛት ባሕርይ በእምነት የምናሳይ ከሆነ እንደ ጳውሎስ ለማለት እንበቃለን።

መልካም ለማድረግ ራስን መግዛት ያስፈልጋል

6. ራስን መግዛት ሲባል ምን ማለት ነው? ይህንን ባሕርይ ማሳየት የምንችልባቸው ሁለት መንገዶች የትኞቹ ናቸው?

6 በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ “ራስን መግዛት” ተብለው የተተረጎሙት የዕብራይስጥና የግሪክኛ ቃላት ጥሬ ፍቺያቸው አንድ ሰው በራሱ ላይ ያለውን ሥልጣን ያመለክታል። እነዚህ ቃላት ብዙውን ጊዜ መጥፎ ነገር ከማድረግ ራስን መቆጠብ የሚል ሐሳብ ያስተላልፋሉ። ይሁን እንጂ መልካም ሥራዎች መሥራትም ቢሆን በተወሰነ መጠን ራስን መግዛት እንደሚጠይቅ ግልጽ ነው። ፍጹም ያልሆኑት የሰው ልጆች መጥፎ እንዲያደርጉ የሚገፋፋ ዝንባሌ ስለወረሱ ሁለት ዓይነት ትግል ከፊታቸው ተደቅኖባቸዋል። (መክብብ 7:29፤ 8:11) መጥፎ ነገር ላለማድረግ እየታገልን መልካም ሥራ ለመሥራት ራሳችንን ማስገደድ ይኖርብናል። እንዲያውም መልካም ለማድረግ ራስን ማስገደድ ከመጥፎ ነገር መራቅ ከምንችልባቸው መንገዶች አንዱ ነው።

7. (ሀ) እንደ ዳዊት ሁሉ እኛም ምን ለማግኘት መጸለይ ይኖርብናል? (ለ) ራስን የመግዛት ባሕርይ እንድናዳብር የሚረዳን ስለ ምን ነገሮች ማሰላሰላችን ነው?

7 በግልጽ ለማየት እንደሚቻለው ራሳችንን ለአምላክ ስንወስን የገባነውን ቃል ለመፈጸም የምንፈልግ ከሆነ ራስን የመግዛት ባሕርይ ማዳበራችን የግድ አስፈላጊ ነው። እኛም ልክ እንደ ዳዊት “አቤቱ፣ ንጹሕ ልብን ፍጠርልኝ፣ የቀናውንም መንፈስ በውስጤ አድስ” ብለን መጸለይ ይኖርብናል። (መዝሙር 51:10) ከሥነ ምግባር አኳያ ስህተት ከሆኑና ለአካላዊ ጉዳት ከሚዳርጉ ነገሮች መራቅ የሚያስገኛቸውን ጥቅሞች ማሰላሰል እንችላለን። ከእነዚህ ነገሮች አለመራቅ ከባድ የጤና ችግሮች ሊያስከትልብን፣ ከሌሎች ጋር ያለንን ግንኙነት ሊያሻክርብንና ያለ ዕድሜያችን እንድንቀጭ ሊያደርገን እንደሚችል አስብ። በሌላ በኩል ደግሞ ይሖዋ ሕይወታችንን እንድንመራበት የሰጠንን መመሪያ መከተል የሚያስገኛቸውን በርካታ ጥቅሞች አስብ። ልብ ተንኮለኛ መሆኑን ግን መዘንጋት አይኖርብንም። (ኤርምያስ 17:9) ልባችን የይሖዋን የሥነ ምግባር መስፈርቶች መከተል ያለውን አስፈላጊነት አሳንሶ ለማቅረብ የሚያደርጋቸውን ሙከራዎች ለማሸነፍ ቆራጥ መሆን አለብን።

8. ብዙዎቻችን ከተሞክሮ ምን ተምረናል? ምሳሌ ስጥ።

8 ደካማ የሆነው ሥጋችን ያለንን የቅንዓት መንፈስ ሊያቀዘቅዝብን እንደሚሞክር ብዙዎቻችን ከተሞክሮ አይተናል። የመንግሥቱን የስብከት ሥራ እንደምሳሌ አድርገን እንመልከት። ሰዎች ሕይወት አድን በሆነው በዚህ ሥራ ለመካፈል ፈቃደኛ መሆናቸው ይሖዋን ያስደስተዋል። (መዝሙር 110:3፤ ማቴዎስ 24:14) ለብዙዎቻችን አደባባይ ወጥተን መስበክን መማር ቀላል አልነበረም። ቀላል መስሎ የታየንን ከመከተል ይልቅ ሥጋችንን ‘እየጎሰምን ማስገዛት’ ጠይቆብናል፤ ምናልባት አሁንም እንዲህ ማድረግ ያስፈልገን ይሆናል።—1 ቆሮንቶስ 9:16, 27፤ 1 ተሰሎንቄ 2:2

“በነገር ሁሉ” ራሳችሁን ትገዛላችሁ?

9, 10. ‘በነገር ሁሉ ራስን መግዛት’ ምንን ይጨምራል?

9 መጽሐፍ ቅዱስ ‘በነገር ሁሉ ራሳችንን እንድንገዛ’ የሚሰጠን ምክር ቁጣችንን ከመቆጣጠርና ከሥነ ምግባር ውጪ ከሆኑ ነገሮች ከመቆጠብ የበለጠ ነገርንም እንደሚጨምር ያሳያል። በእነዚህ ዘርፎች ራሳችንን መግዛት እንደቻልን ይሰማን ይሆናል። በእርግጥ ተሳክቶልን ከሆነ የምንደሰትበት በቂ ምክንያት አለን። ሆኖም ራስን የመግዛት ባሕርይ ማሳየት አስፈላጊ በሆነባቸው ሌሎች መስኮችስ እንዴት ነን? ለምሳሌ ያህል፣ የምንኖረው በአንጻራዊ ሁኔታ ከፍተኛ የኑሮ ደረጃ ባለው የበለጸገ አገር ውስጥ ነው እንበል። አላስፈላጊ በሆኑ ነገሮች ላይ ገንዘብ ላለማባከን ጠንቃቆች መሆን አይኖርብንም? ልጆች የገንዘብ አቅሙ ስላላቸውና ስለወደዱት ብቻ ያዩትን ሁሉ መግዛት እንደሌለባቸው ወላጆች ሊያሰለጥኗቸው ይገባል። እርግጥ ነው፣ እንዲህ ያለው ሥልጠና ውጤታማ እንዲሆን ከተፈለገ ወላጆች ራሳቸው አርዓያ ሆነው መገኘት አለባቸው።—ሉቃስ 10:38-42

10 አንድ ነገር የምንፈልገው ወይም የሚያስፈልገን ቢሆንም እንኳን ያለዚያ መኖር መቻል መንፈሰ ጠንካራ ሊያደርገን ይችላል። እንዲሁም ያሉንን ቁሳዊ ነገሮች እንድናደንቅና ወደው ሳይሆን በሁኔታዎች አስገዳጅነት የተነሳ የሚያስፈልጓቸውን ነገሮች ሳያገኙ ለሚኖሩ ሰዎች እንድናዝንላቸው ያደርገናል። እርግጥ ነው፣ ልከኛ የሆነ አኗኗር “ራስህን አስደስት” ወይም “ለአንተ የሚገባው ምርጥ ምርጡ ነው” እንደሚሉት ካሉ ሰፊ ተቀባይነት ያገኙ አስተሳሰቦች ጋር አይጣጣምም። የማስታወቂያው ዓለም ደግሞ የፈለጉትን ነገር ወዲያው ገዝቶ ራስን ማስደሰትን ያበረታታል። እንዲህ የሚያደርገው ግን በንግድ ለሚያገኘው ትርፍ ሲል ነው። ይህ ሁኔታ ራሳችንን ለመግዛት የምናደርገውን ጥረት ሊያደናቅፍብን ይችላል። በበለጸገ የአውሮፓ አገር የሚታተም አንድ መጽሔት በቅርቡ እንዲህ ብሎ ነበር:- “ድህነት ሥር በሰደደባቸው አገሮች የሚኖሩ ሰዎች ተገቢ ያልሆኑ ዝንባሌዎቻቸውን ለመቆጣጠር ከባድ ውስጣዊ ትግል የሚጠይቅባቸው ከሆነ ወተትና ማር በሚፈስባቸው ሀብታም አገሮች ውስጥ የሚኖሩትማ ምንኛ የባሰ ትግል ይጠይቅባቸዋል!”

11. ባለን መርካትን መማር ጠቃሚ የሆነው ለምንድን ነው? ይህን ፈታኝ የሚያደርገው ምንድን ነው?

11 እንዲኖረን የምንፈልገውንና በእርግጥ የሚያስፈልገንን መለየት ከባድ ከሆነብን ማስተዋል የጎደለው ነገር ከማድረግ የሚያግዱንን እርምጃዎች መውሰዳችን ጠቃሚ ሊሆን ይችላል። ለምሳሌ ያህል በሆነ ባልሆነው ገንዘብ የማባከንን ዝንባሌ ለማስወገድ ከፈለግን በዱቤ ምንም ላለመግዛት ቁርጥ ውሳኔ ማድረግ ወይም ገበያ በምንወጣበት ጊዜ የተወሰነ ገንዘብ ብቻ መያዝ እንችላለን። ጳውሎስ “ኑሮዬ ይበቃኛል ለሚለው ግን እግዚአብሔርን መምሰል እጅግ ማትረፊያ ነው” ሲል እንደተናገረ ታስታውስ ይሆናል። ይህን ያለበትን ምክንያት ሲናገር “ወደ ዓለም ምንም እንኳ አላመጣንምና፣ አንዳችንም ልንወስድ አይቻለንም፤ ምግብና ልብስ ከኖረን ግን፣ እርሱ ይበቃናል” ብሏል። (1 ጢሞቴዎስ 6:6-8) እኛስ ባለን እንረካለን? ቀላል ሕይወት መኖር እንዲሁም ከልክ በላይ ለራስ ምኞት በማደር የሚመጣን ማንኛውንም አላስፈላጊ ሸክም ማስወገድ መንፈሰ ጠንካራነትና ራስን መግዛት ይጠይቃል። ይሁን እንጂ ባለን የመርካት ዝንባሌ ልንማረው የሚገባን ትምህርት ነው።

12, 13. (ሀ) በክርስቲያናዊ ስብሰባዎች ላይ ራሳችንን መግዛት የሚኖርብን በየትኞቹ ሁኔታዎች ነው? (ለ) ራስን የመግዛት ባሕርይ የምናሳይባቸው ሌሎች ዘርፎች የትኞቹ ናቸው?

12 በጉባኤና በትልልቅ ስብሰባዎች ላይ መገኘትም በተለየ መንገድ ራስን መግዛት ይጠይቃል። ለምሳሌ ያህል፣ በስብሰባ ወቅት ሐሳባችን እንዳይባዝን ከፈለግን ራሳችንን መግዛት ይፈለግብናል። (ምሳሌ 1:5) ተናጋሪውን በትኩረት ከማዳመጥ ይልቅ አጠገባችን ከተቀመጡት ጋር እያንሾካሾክን ሌሎችን ላለመረበሽ ራሳችንን መግዛት ይኖርብናል። ስብሰባው ከመጀመሩ በፊት መድረስ እንድንችል ፕሮግራማችንን ማስተካከልም ራስን መግዛት ይጠይቃል። ከዚህም በላይ ለስብሰባዎች የምንዘጋጅበትን ጊዜ ለማመቻቸትና ተሳትፎ ለማድረግ ራስን መግዛት ያስፈልጋል።

13 በትናንሽ ነገሮች ራሳችንን የምንገዛ ከሆነ ከባድ ጉዳዮች ሲያጋጥሙን ራሳችንን ለመግዛት ያለን ችሎታ ይጠናከራል። (ሉቃስ 16:10) በመሆኑም የአምላክን ቃል እንዲሁም በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተመሠረቱ ጽሑፎችን ለማንበብ፣ ለማጥናትና በተማርናቸው ነገሮች ላይ ለማሰላሰል ራሳችንን መገሠጻችን በጣም አስፈላጊ ነው። ተገቢ ያልሆኑ ሥራዎችን፣ ጓደኞችን፣ አስተሳሰቦችንና ልማዶችን በተመለከተ ራሳችንን መገሠጻችንና ለአምላክ አገልግሎት ልናውለው የሚገባንን ውድ ጊዜ ሊሻሙብን በሚችሉ እንቅስቃሴዎች ላለመካፈል ራሳችንን መግዛታችን በጣም ጠቃሚ ነው። በይሖዋ አገልግሎት መጠመዳችን በእርሱ ዓለም አቀፋዊ ጉባኤ ውስጥ ያገኘነውን መንፈሳዊ ገነት ሊያሳጡን ከሚችሉ ነገሮች ይጠብቀናል።

ራሳችሁን በመግዛት በመንፈሳዊ ጎልምሱ

14. (ሀ) ልጆች ራስን መግዛት የሚማሩት እንዴት ነው? (ለ) ልጆች ገና በሕፃንነታቸው ራስን መግዛት መማራቸው ምን ጥቅሞች አሉት?

14 ከአንድ አራስ ልጅ ራስን የመግዛት ባሕርይ አንጠብቅም። የልጆችን ባሕርይ በሚያጠኑ ባለሞያዎች የተዘጋጀ አንድ በራሪ ጽሑፍ እንዲህ ይላል:- “ራስን መግዛት በደመነፍስ የምናንጸባርቀው ወይም ድንገት የምንላበሰው ባሕርይ አይደለም። አራስ ልጆችና የሚድኹ ሕፃናት ራስን መግዛትን ለመማር የወላጆች አመራርና ድጋፍ ያስፈልጋቸዋል። . . . ልጆች በትምህርት ዓለም ሳሉ ከወላጆች በሚያገኙት እርዳታ እየታገዙ ራስን የመግዛት ባሕርይ እያዳበሩ ይሄዳሉ።” የአራት ዓመት ዕድሜ ባላቸው ልጆች ላይ የተደረገ አንድ ጥናት እንደሚያሳየው በተወሰነ መጠን ራስን መግዛት የተማሩ ልጆች “ከአዳዲስ ሁኔታዎች ጋር በቀላሉ የሚላመዱ፣ ተወዳጅ፣ አዲስ ነገር ለማወቅ ጉጉት ያላቸው፣ በራሳቸው የሚተማመኑና እምነት የሚጣልባቸው ሆነው ያድጋሉ።” ራስን የመግዛት ባሕርይ ገና ያላዳበሩት ደግሞ “ብቸኛ፣ በቀላሉ ተስፋ የሚቆርጡና ግትር ይሆናሉ። ለተጽዕኖዎች በቀላሉ የሚንበረከኩ ከመሆኑም በላይ ጥረት የሚጠይቁ ከበድ ያሉ ነገሮችን ይሸሻሉ።” በግልጽ ለማየት እንደሚቻለው ልጆች ወደፊት ሲያድጉ ስኬታማ መሆን እንዲችሉ ራስን መግዛት መማር ይኖርባቸዋል።

15. ራስን አለመግዛት ምንን ያመለክታል? በአንጻሩ መጽሐፍ ቅዱስ የትኛውን ግብ እንድንከተል ያበረታታናል?

15 እኛም በተመሳሳይ የጎለመስን ክርስቲያኖች ለመሆን ራሳችንን መግዛት መማር ይኖርብናል። ራሳችንን መግዛት የሚሳነን ከሆነ በመንፈሳዊ ሕፃናት ነን ማለት ነው። መጽሐፍ ቅዱስ ‘በአእምሮ የበሰላችሁ ሁኑ’ በማለት ያሳስበናል። (1 ቆሮንቶስ 14:20) ግባችን “የእግዚአብሔርን ልጅ በማመንና በማወቅ ወደሚገኝ አንድነት፣ ሙሉ ሰውም ወደ መሆን፣ የክርስቶስም ሙላቱ ወደሚሆን ወደ ሙላቱ ልክ” መድረስ ነው። ለምን? “እንደ ስሕተት ሽንገላ ባለ ተንኰል በሰዎችም ማታለል ምክንያት በትምህርት ነፋስ ሁሉ እየተፍገመገምን ወዲያና ወዲህም እየተንሳፈፍን ሕፃናት” እንዳንሆን ነው። (ኤፌሶን 4:12-14) ራስን መግዛት ለመንፈሳዊነታችን በጣም አስፈላጊ እንደሆነ ግልጽ ነው።

ራስን የመግዛት ባሕርይ ማዳበር

16. ይሖዋ ራስን የመግዛት ባሕርይ እንድናዳብር የሚረዳን እንዴት ነው?

16 ራስን የመግዛት ባሕርይ ለማዳበር መለኮታዊ እርዳታ የሚያስፈልግ ሲሆን ይህን እርዳታም በቀላሉ ማግኘት እንችላለን። የአምላክ ቃል ልክ እንደ መስታወት ምን ለውጦችን ማድረግ እንደሚያስፈልገን የሚያሳየን ከመሆኑም በላይ እነዚህን ለውጦች እንዴት ማድረግ እንደምንችልም ምክር ይሰጠናል። (ያዕቆብ 1:22-25) እኛን ለመርዳት ምንጊዜም ዝግጁ የሆኑ አፍቃሪ ወንድሞችና እህቶችም አሉን። የጉባኤ ሽማግሌዎችም በግለሰብ ደረጃ እርዳታ በማድረግ አሳቢነት ያሳዩናል። ይሖዋ ራሱ በጸሎት ከለመንነው ቅዱስ መንፈሱን አትረፍርፎ ይሰጠናል። (ሉቃስ 11:13፤ ሮሜ 8:26) ስለሆነም እነዚህን ዝግጅቶች በአድናቆት እንጠቀምባቸው። በገጽ 21 ላይ ያሉት ሐሳቦችም ሊረዱህ ይችላሉ።

17. በምሳሌ 24:16 ላይ ምን ማበረታቻ እናገኛለን?

17 ይሖዋ እርሱን ለማስደሰት የምናደርገውን ጥረት በአድናቆት እንደሚመለከተው ማወቁ ምንኛ የሚያጽናና ነው! ይህ ደግሞ ራሳችንን ለመግዛት ይበልጥ ጥረት እንድናደርግ ሊያነሳሳን ይገባል። በተደጋጋሚ ጊዜያት ሳይሳካልን ቢቀር እንኳን ተስፋ ልንቆርጥ አይገባንም። “ጻድቅ ሰባት ጊዜ ይወድቃልና፣ ይነሣማል።” (ምሳሌ 24:16) ይሖዋን ለማስደሰት በቻልን ቁጥር በራሳችን ደስ ልንሰኝ ይገባናል። ይሖዋም እንደሚደሰትብን እርግጠኞች ልንሆን እንችላለን። አንድ ወንድም ራሱን ለይሖዋ ከመወሰኑ በፊት ሲጋራ ሳያጨስ አንድ ሳምንት ባሳለፈ ቁጥር ራሱን በመግዛቱ ባጠራቀመው ገንዘብ አንድ ጠቃሚ ነገር በመግዛት ራሱን ይሸልም እንደነበር ተናግሯል።

18. (ሀ) ራሳችንን ለመግዛት የምናደርገው ተጋድሎ ከምን ጋር የተያያዘ ነው? (ለ) ይሖዋ ምን ማበረታቻ ሰጥቶናል?

18 ከሁሉም በላይ ራስን መግዛት ከአእምሮና ከስሜት ጋር የተያያዘ እንደሆነ መዘንጋት አይኖርብንም። “ወደ ሴት ያየ ሁሉ የተመኛትም ያን ጊዜ በልቡ ከእርስዋ ጋር አመንዝሮአል” የሚሉት የኢየሱስ ቃላት ይህን ያስገነዝቡናል። (ማቴዎስ 5:28፤ ያዕቆብ 1:14, 15) አእምሮውንና ስሜቶቹን የሚቆጣጠር ሰው መላ ሰውነቱን መግዛት አይሳነውም። ስለዚህ መጥፎ ነገር ላለማድረግ ብቻ ሳይሆን መጥፎ ነገር ላለማሰብም ያደረግነውን ቁርጥ ውሳኔ እናጠናክር። መጥፎ ሐሳቦች ወደ አእምሯችን ሲመጡ ቶሎ እናስወጣቸው። በጸሎት አማካኝነት ዓይናችን በኢየሱስ ላይ እንዲያተኩር በማድረግ ከፈተና መሸሽ እንችላለን። (1 ጢሞቴዎስ 6:11፤ 2 ጢሞቴዎስ 2:22፤ ዕብራውያን 4:15, 16) ራሳችንን ለመግዛት አቅማችን የፈቀደልንን ሁሉ ስናደርግ በመዝሙር 55:22 ላይ የሚገኙትን “ትካዜህን በእግዚአብሔር ላይ ጣል፣ እርሱም ይደግፍሃል፤ ለጻድቁም ለዘላለም ሁከትን አይሰጠውም” የሚሉትን ቃላት ተግባራዊ እናደርጋለን።

ታስታውሳለህ?

• ራስን መግዛት ማሳየት የምንችልባቸው ሁለት መንገዶች የትኞቹ ናቸው?

• ‘በነገር ሁሉ ራስን መግዛት’ ሲባል ምን ማለት ነው?

• በዚህ ጥናታችን ላይ ራስን የመግዛት ባሕርይ ማዳበርን አስመልክቶ ከቀረቡት ሐሳቦች ውስጥ አንተን የነካህ የትኛው ነው?

• ራስን መግዛት የምንማረው ከመቼ ጀምሮ ነው?

[የአንቀጾቹ ጥያቄዎች]

[በገጽ 21 ላይ የሚገኝ ሣጥን/ሥዕል]

ራስን የመግዛት ባሕርይ ለማዳበር

በትናንሽ ጉዳዮችም ራስን መግዛት ተማር

ራስን መግዛት አሁንም ሆነ ወደፊት የሚያስገኛቸውን ጥቅሞች አስብ

አምላክ ባወገዛቸው ነገሮች ፋንታ እንድናደርግ ያበረታታንን ነገሮች አድርግ

ተገቢ ያልሆኑ ሐሳቦች ወደ አእምሮህ ሲመጡ ወዲያው አስወጣቸው

አእምሮህ በመንፈሳዊ በሚያንጹ ሐሳቦች እንዲሞላ አድርግ

በመንፈሳዊ የጎለመሱ ክርስቲያኖች የሚያደርጉልህን እርዳታ በደስታ ተቀበል

ከሚፈትኑ ሁኔታዎች ሽሽ

ፈተና በሚያጋጥምህ ጊዜ አምላክ እንዲረዳህ ጸልይ

[በገጽ 18, 19 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ራስን መግዛት መልካም እንድናደርግ ያነሳሳናል