በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ትክክለኛ ውሳኔ ማድረግ የምትችለው እንዴት ነው?

ትክክለኛ ውሳኔ ማድረግ የምትችለው እንዴት ነው?

ትክክለኛ ውሳኔ ማድረግ የምትችለው እንዴት ነው?

የጥንቷ እስራኤል ንጉሥ የነበረው ሰሎሞን “ጠቢብ . . . ከመስማት ጥበብን ይጨምራል” በማለት ተናግሮ ነበር። አብዛኞቻችን የሌሎችን ምክር ችላ በማለታችን ብቻ ማስተዋል የጎደለው ውሳኔ አድርገን ሊሆን ይችላል።—ምሳሌ 1:5

ሰሎሞን ካቀናበራቸው “ሦስት ሺህ ምሳሌዎች” ውስጥ የተወሰዱት እነዚህ ቃላት ከሌሎች ምሳሌዎች ጋር በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ተመዝግበዋል። (1 ነገሥት 4:32) እነዚህን ምሳሌዎች በመማርና በሥራ ላይ በማዋል ጥቅም ማግኘት እንችል ይሆን? አዎን። ምሳሌዎቹ “ጥበብንና ተግሣጽን ለማወቅ፣ የእውቀትንም ቃል ለማስተዋል፣ የጥበብን ትምህርት ጽድቅንና ፍርድን ቅንነትንም ለመቀበል” ይረዱናል። (ምሳሌ 1:2, 3) ትክክለኛ ውሳኔ ለማድረግ የሚረዱንን በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተመሠረቱ አምስት መመሪያዎች እስቲ እንመልከት።

ውሳኔህ የሚያስከትለውን ዘላቂ ውጤት አስብ

አንዳንድ ውሳኔዎች በሕይወታችን ላይ ትልቅ ለውጥ የሚያስከትሉ ናቸው። ስለሆነም ውሳኔህ ምን ውጤት እንደሚያስከትል ከወዲሁ ለመገመት ሞክር። ለጊዜው የምታገኘው ጥቅም ወደፊት ሊያጋጥሙህ የሚችሉትን ችግሮች እንዳታይ ሊጋርድብህ አይገባም። ምሳሌ 22:3 “ብልህ ሰው ክፉን አይቶ ይሸሸጋል፤ አላዋቂዎች ግን አልፈው ይጐዳሉ” በማለት ያስጠነቅቃል።

ውሳኔህ የሚያስከትላቸውን የአጭር ጊዜም ሆነ የረጅም ጊዜ ውጤቶች በወረቀት ላይ በዝርዝር መጻፉ ጠቃሚ ሊሆን ይችላል። ለምሳሌ ያህል፣ አንድን የሥራ መስክ ስትመርጥ የሥራውን አስደሳችነትና ዳጎስ ያለ ደመወዝ የሚያስገኝ መሆኑን ትመለከት ይሆናል። ሆኖም ወደፊት ምንም እድገት የማይገኝበት ቢሆንስ? ከጊዜ በኋላ ከወዳጅ ዘመዶችህ ርቀህ ወደ ሌላ አካባቢ እንድትዛወር የሚያስገድድህ ይሆን? ውሎ አድሮ ለጤና ችግር የሚያጋልጥህ ወይም አሰልቺ ከመሆኑ የተነሳ ለተስፋ መቁረጥ የሚዳርግህ ቢሆንስ? ጥቅሙንና ጉዳቱን ካመዛዘንክ በኋላ ሚዛን የሚደፋውን ምረጥ።

ጊዜ ሰጥተህ አስብበት

ሳይታሰብበት በጥድፊያ የተደረገ ውሳኔ ችግር ሊያስከትል ይችላል። ምሳሌ 21:5 “የትጉህ አሳብ ወደ ጥጋብ ያደርሳል ችኩል ሰው ሁሉ ግን ለመጉደል ይቸኩላል” በማለት ያስጠነቅቃል። ለምሳሌ ያህል በወረት ፍቅር የተያዙ አፍላ ወጣቶች ተጣድፈው ትዳር ከመመሥረታቸው በፊት ጊዜ ሰጥተው ሊያስቡበት ይገባል። ካለበለዚያ በ18ኛው መቶ ዘመን መጀመሪያ አካባቢ የኖረው ዊልያም ኮንግሪቭ የተባለ ጸሐፊ ተውኔት “ተጣድፈን ካገባን የብዙ ዘመን ጸጸት እናተርፋለን” በማለት የተናገረው ሐቅ በእነርሱ ላይ ይፈጸማል።

ይሁን እንጂ ጊዜ ሰጥቶ በጉዳዩ ላይ ማሰብ ሲባል ዛሬ ነገ እያሉ ማዘግየት ማለት አይደለም። አንዳንድ ጉዳዮች በጣም አስፈላጊ ከመሆናቸው የተነሳ በተቻለ መጠን ቶሎ ውሳኔ ሊደረግባቸው ይገባል። ያለ ምክንያት ዛሬ ነገ እያሉ ማጓተት በእኛም ሆነ በሌሎች ላይ ትልቅ ኪሳራ ሊያስከትል ይችላል። ውሳኔ የሚያስፈልገውን ጉዳይ ያለ በቂ ምክንያት ማዘግየት በራሱ ውሳኔ ነው፤ ምናልባትም የተሳሳተ ውሳኔ።

ምክር ለመቀበል ፈቃደኛ ሁን

ፍጹም ተመሳሳይ የሆኑ ሁኔታዎች ሊኖሩ ስለማይችሉ ሁለት ሰዎች አንድ ዓይነት ችግሮች ቢያጋጥሟቸው የሚመሳሰሉ ውሳኔዎችን ለማድረግ ያላቸው አጋጣሚ ጠባብ ነው። ቢሆንም ሌሎች ከእኛ ጋር የሚመሳሰል ሁኔታ ሲያጋጥማቸው ምን ውሳኔ እንዳደረጉ ማወቁ ጠቃሚ ነው። ስለ ውሳኔያቸው መለስ ብለው ሲያስቡ ምን እንደሚሰማቸው ጠይቃቸው። ለምሳሌ ያህል አንድን የሥራ ዓይነት ከመምረጥህ በፊት በዚህ መስክ የተሰማሩ ሰዎችን ስለ ሥራው ጥሩም ሆነ መጥፎ ጎኖች እንዲነግሩህ ጠይቃቸው። በዚህ የሥራ መስክ በመሰማራታቸው ምን ጥቅሞች አግኝተዋል? ምንስ እንቅፋቶች ወይም ችግሮች አጋጥመዋቸዋል?

ንጉሥ ሰሎሞን “ምክር ከሌለች ዘንድ የታሰበው ሳይሳካ ይቀራል፤ መካሮች በበዙበት ዘንድ ግን ይጸናል” በማለት አሳስቦናል። (ምሳሌ 15:22) እርግጥ ነው፣ ከሌሎች ተሞክሮ ለመማር ምክር ስንጠይቅ ውሳኔ የማድረጉ ኃላፊነት የእኛው መሆኑንና ኃላፊነቱን የምንሸከመው ራሳችን እንደሆንን መገንዘብ ይኖርብናል።—ገላትያ 6:4, 5

ሕሊናህን አዳምጥ

ሕሊና ሕይወታችንን ለመምራት ከምንጠቀምበት መሠረታዊ ሥርዓት ጋር የሚስማሙ ውሳኔዎች እንድናደርግ ሊረዳን ይችላል። ይህ ለአንድ ክርስቲያን ሕሊናውን በአምላክ አስተሳሰብ መቅረጽ ማለት ነው። (ሮሜ 2:14, 15) የአምላክ ቃል “በመንገድህ ሁሉ እርሱን እወቅ፣ እርሱም ጎዳናህን ያቀናልሃል” በማለት ይናገራል። (ምሳሌ 3:6) እርግጥ በሚገባ የሰለጠነ ሕሊና ያላቸው ሁለት ሰዎች በአንዳንድ ጉዳዮች ላይ የተለያየ አመለካከት ሊኖራቸውና ውሳኔያቸው ሊለያይ ይችላል።

በአምላክ ቃል ውስጥ በቀጥታ የተወገዙ ድርጊቶችን በሚመለከት ግን የሰለጠነ ሕሊና ያላቸው ሰዎች እንዲህ ያለ የውሳኔ ልዩነት አይታይባቸውም። ለምሳሌ ያህል አንድ ወንድና ሴት ሕሊናቸው በመጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ ሥርዓት ያልሰለጠነ ከሆነ ትዳር ከመመሥረታቸው በፊት ምን ያህል እንደሚጣጣሙ ለማወቅ አብረው ለመኖር ይወስኑ ይሆናል። እንዲህ ማድረጋቸው ተጣድፈው ስኬታማ ያልሆነ ትዳር ከመመሥረት እንደሚያድናቸው በማሰብ ጥሩ ውሳኔ እንዳደረጉ ይሰማቸው ይሆናል። ሕሊናቸውም ላይወቅሳቸው ይችላል። ሆኖም አምላክ ስለ ጾታና ስለ ትዳር ያለውን አመለካከት የሚያውቅ ማንኛውም ሰው እንዲህ ባለው ዘላቂነት የሌለውና ሥነ ምግባር የጎደለው ግንኙነት ውስጥ ለመግባት አይወስንም።—1 ቆሮንቶስ 6:18፤ 7:1, 2፤ ዕብራውያን 13:4

ውሳኔህ ሌሎችን የሚነካው እንዴት ነው?

የምታደርገው ውሳኔ ብዙውን ጊዜ ሌሎችን ይነካል። ስለሆነም ከወዳጆችህ፣ ከዘመዶችህ ከሁሉም በላይ ደግሞ ከአምላክ ጋር ያለህን ውድ ዝምድና ሊያበላሽብህ የሚችል መጥፎ ውሳኔ ላለማድረግ ተጠንቀቅ። ምሳሌ 10:1 “ጠቢብ ልጅ አባቱን ደስ ያሰኛል፤ ሰነፍ ልጅ ግን ለእናቱ ኀዘን ነው” በማለት ይናገራል።

በሌላ በኩል ደግሞ አንዳንድ ጊዜ በጓደኛ ምርጫህም ረገድ ውሳኔ ማድረግ እንዳለብህ ልትገነዘብ ይገባል። በምሳሌ ለማስረዳት ያህል ቀድሞ የነበረህ ሃይማኖታዊ አመለካከት ከመጽሐፍ ቅዱስ ጋር እንደሚጋጭ ስትገነዘብ አስተሳሰብህን ለማስተካከል ትወስን ይሆናል። ወይም አኗኗርህን አዲስ ከተማርካቸው መለኮታዊ መመሪያዎች ጋር ለማስማማት ስትል ሥር ነቀል የባሕርይ ለውጥ ለማድረግ ትወስን ይሆናል። አንዳንድ ጓደኞችህ ወይም ዘመዶችህ በዚህ ላይደሰቱ ይችላሉ፤ ሆኖም አምላክን የሚያስደስት እስከሆነ ድረስ ጥሩ ውሳኔ እንዳደረግህ ሊሰማህ ይገባል።

ማስተዋል የሚጠይቅ ትልቅ ውሳኔ

ብዙዎች ባይገነዘቡትም የሕይወት ወይም የሞት ምርጫ በእያንዳንዱ ሰው ፊት ተደቅኗል። በ1473 ከዘአበ በተስፋይቱ ምድር ድንበር ላይ ሰፍረው የነበሩት የጥንት እስራኤላውያን ተመሳሳይ ምርጫ ቀርቦላቸው ነበር። የአምላክ ቃል አቀባይ የነበረው ሙሴ እንዲህ አላቸው:- “በፊታችሁ ሕይወትንና ሞትን በረከትንና መርገምን እንዳስቀመጥሁ እኔ ዛሬ ሰማይንና ምድርን በአንተ ላይ አስመሰክራለሁ፤ እንግዲህ አንተና ዘርህ በሕይወት ትኖሩ ዘንድ ሕይወትን ምረጥ፤ እግዚአብሔርም ለአባቶችህ ለአብርሃምና ለይስሐቅ ለያዕቆብም እንዲሰጣቸው በማለላቸው በምድሪቱ ትቀመጥ ዘንድ፣ እርሱ ሕይወትህ የዘመንህም ርዝመት ነውና አምላክህን እግዚአብሔርን ትወድደው ትጠባበቀውም ቃሉንም ትሰማ ዘንድ ምረጥ።”—ዘዳግም 30:19, 20

የመጽሐፍ ቅዱስ ትንቢትና የዘመን አቆጣጠር ‘በሚያስጨንቅ ዘመን’ ውስጥ እንደምንኖርና ‘የዚህ ዓለም መልክ ተለዋዋጭ እንደሆነ’ ያሳያሉ። (2 ጢሞቴዎስ 3:1፤ 1 ቆሮንቶስ 7:31) አስቀድሞ በትንቢት የተነገረው ለውጥ ይህ በመፈራረስ ላይ የሚገኘው አሮጌ ሥርዓት በአምላክ አዲስ የጽድቅ ሥርዓት ሲተካ ፍጻሜውን ያገኛል።

አሁን የምንገኘው በዚህ አዲስ ዓለም ደፍ ላይ ነው። በአምላክ መንግሥት አገዛዝ ሥር በምድር ላይ ለዘላለም ከሚኖሩት መካከል ትገኝ ይሆን? ወይስ የሰይጣን ሥርዓት ከምድር ላይ ሲደመሰስ አብረህ ትጠፋ ይሆን? (መዝሙር 37:9-11፤ ምሳሌ 2:21, 22) ልትከተለው የሚገባውን መንገድ የመወሰኑ ኃላፊነት የራስህ ሲሆን ይህ ውሳኔ የሕይወትና የሞት ጉዳይ ነው። ትክክለኛውን ውሳኔ ማድረግ እንድትችል እርዳታ ብታገኝ ደስ አይልህም?

ሕይወትን መምረጥ አምላክ የሚፈልግብንን ብቃቶች መማርን ይጨምራል። አብዛኞቹ አብያተ ክርስቲያናት እነዚህን መስፈርቶች በትክክል ሳያስተምሩ ቀርተዋል። መሪዎቻቸው ሕዝቡ የሐሰት ትምህርቶችን እንዲያምኑና አምላክን የሚያሳዝኑ ድርጊቶችን እንዲፈጽሙ በማድረግ በተሳሳተ ጎዳና መርተዋቸዋል። አምላክን “በመንፈስና በእውነት” ለማምለክ በግለሰብ ደረጃ ውሳኔ የማድረግን አስፈላጊነት ከማስተማር ችላ ብለዋል። (ዮሐንስ 4:24) በመሆኑም ብዙ ሰዎች አምላክን የሚያመልኩት በመንፈስና በእውነት አይደለም። ኢየሱስ ግን ምን እንዳለ ተመልከት:- “ከእኔ ጋር ያልሆነ ይቃወመኛል፣ ከእኔ ጋርም የማያከማች ይበትናል።”—ማቴዎስ 12:30

የይሖዋ ምሥክሮች ሰዎች ስለ አምላክ ቃል የተሻለ እውቀት እንዲኖራቸው ለመርዳት ፈቃደኞች ናቸው። በግለሰብ ደረጃም ይሁን በቡድን ለሰዎቹ አመቺ በሆነው ጊዜና ቦታ መጽሐፍ ቅዱስን በቋሚነት ያስጠናሉ። ከዚህ ዝግጅት ለመጠቀም የሚፈልጉ ሰዎች በአቅራቢያቸው የሚገኙትን የይሖዋ ምሥክሮች ማነጋገር ወይም ለዚህ መጽሔት አዘጋጆች መጻፍ ይችላሉ።

እርግጥ አንዳንዶች አምላክ ከእነርሱ ምን እንደሚፈልግ መሠረታዊ እውቀት አግኝተዋል። የመጽሐፍ ቅዱስን እውነተኝነትና እምነት የሚጣልበት መሆኑን ይቀበሉ ይሆናል። ያም ሆኖ ግን ብዙዎቹ ራሳቸውን ለአምላክ ለመወሰን ዛሬ ነገ እያሉ ያመነታሉ። ለምን? ጥቂት ምክንያቶችን መጥቀስ ይቻላል።

ራስን ለአምላክ የመወሰንን አስፈላጊነት አልተገነዘቡ ይሆን? ኢየሱስ “በሰማያት ያለውን የአባቴን ፈቃድ የሚያደርግ እንጂ፣ ጌታ ሆይ፣ ጌታ ሆይ፣ የሚለኝ ሁሉ መንግሥተ ሰማያት የሚገባ አይደለም” በማለት በግልጽ ተናግሯል። (ማቴዎስ 7:21) የመጽሐፍ ቅዱስ እውቀት ብቻውን በቂ አይደለም፤ ተግባርም አስፈላጊ ነው። በዚህ ረገድ ጥንት የነበረው የክርስቲያን ጉባኤ አርዓያ ይሆነናል። በመጀመሪያው መቶ ዘመን ስለነበሩ አንዳንድ ሰዎች እንዲህ ተብሎ ነበር:- “ስለ እግዚአብሔር መንግስትና ስለ ኢየሱስ ክርስቶስ ስም እየሰበከላቸው ፊልጶስን ባመኑት ጊዜ፣ ወንዶችም ሴቶችም ተጠመቁ።” (ሥራ 2:41፤ 8:12) በመሆኑም አንድ ሰው የአምላክን ቃል ከተቀበለ፣ ካመነበትና አኗኗሩን ከአምላክ የሥነ ምግባር መስፈርቶች ጋር ካስማማ ራሱን ወስኖ እንዳይጠመቅ ምን ያግደዋል? (ሥራ 8:34-38) እርግጥ ነው፣ በአምላክ ዘንድ ተቀባይነት ለማግኘት እንዲህ ያለውን እርምጃ የሚወስደው በፈቃደኝነትና ከልቡ ተነሳስቶ መሆን ይኖርበታል።—2 ቆሮንቶስ 9:7

አንዳንዶች ደግሞ ራሳቸውን ለአምላክ ለመወሰን የሚያበቃ እውቀት እንደሌላቸው ይሰማቸው ይሆናል። ይሁን እንጂ በሕይወቱ ውስጥ አዲስ ጎዳና መከተል የጀመረ ማንኛውም ሰው መጀመሪያ ላይ የሚኖረው እውቀት ውስን ነው። ‘ስለ ሞያዬ ዛሬ ያለኝ እውቀት በጊዜ ሂደት ያገኘሁት ሳይሆን ድሮም የነበረኝ ነው’ ሊል የሚችል ማን ይኖራል? ራስን ለአምላክ ለመወሰን የሚያስፈልገው ስለ መጽሐፍ ቅዱስ ትምህርቶችና መመሪያዎች መሠረታዊ እውቀት ማግኘትና በእነርሱ ለመመራት ልባዊ ፍላጎት ማዳበር ብቻ ነው።

አንዳንዶች ራሳቸውን ለአምላክ ከመወሰን ወደ ኋላ የሚሉት ቃላችንን መጠበቅ ቢያቅተንስ በሚል ፍርሃት ይሆን? በሰዎች የእርስ በርስ ግንኙነት ውስጥ የገባሁትን ቃል መጠበቅ ቢያቅተኝስ ብሎ መፍራት ያለ ነገር ነው። ለምሳሌ ትዳር መሥርቶ ልጆች ለመውለድ የሚያስብ ሰው በተወሰነ መጠን ብቁ እንዳልሆነ ይሰማው ይሆናል፤ ይሁን እንጂ የሚገባው ቃል ኪዳን ኃላፊነቱን ለመወጣት አቅሙ የፈቀደውን ሁሉ እንዲያደርግ የሚገፋፋ ኃይል ይሆንለታል። በተመሳሳይም አዲስ መንጃ ፈቃድ ያወጣ አንድ ወጣት የመኪና አደጋ ያጋጥመኝ ይሆን ብሎ መስጋቱ ያለ ነው። በተለይ በእድሜ ከገፉ አሽከርካሪዎች ይልቅ ወጣቶች ይበልጥ ለአደጋ እንደሚጋለጡ ማወቁ ፍርሃቱን ሊያባብስበት ይችላል። ሆኖም ይህን ማወቁ በጥንቃቄ እንዲያሽከረክር ስለሚያደርገው ጠቃሚ ሊሆን ይችላል። መንጃ ፈቃድ ከማውጣት ወደ ኋላ ማለቱ ግን መፍትሔ ሊሆን አይችልም።

ሕይወትን ምረጥ!

መጽሐፍ ቅዱስ በጊዜያችን ያለው የፖለቲካ፣ የኢኮኖሚና የሃይማኖት ሥርዓት እንዲሁም የሥርዓቱ ደጋፊዎች በቅርቡ ከምድር ገጽ ተጠራርገው እንደሚጠፉ ይናገራል። ሆኖም በሕይወት ለመትረፍ ውሳኔ ያደረጉና ከውሳኔያቸው ጋር ተስማምተው የሚኖሩ ሰዎች ከጥፋቱ ይድናሉ። እነዚህ ሰዎች በአዲሱ ዓለም ውስጥ ለሚቋቋመው ኅብረተሰብ እንደ መሠረት በመሆን ምድርን ወደ መጀመሪያው የአምላክ ዓላማ ይኸውም ወደ ገነትነት በመለወጡ ሥራ ይካፈላሉ። በአምላክ አመራር ሥር ሆነህ በዚህ አስደሳች ሥራ ለመካፈል አትፈልግም?

የምትፈልግ ከሆነ የአምላክን ቃል ለማጥናት ውሳኔ አድርግ። አምላክን ለማስደሰት እንድትችል መለኮታዊ ብቃቶቹን ለመማር እንዲሁም በሥራ ላይ ለማዋል ወስን። ከሁሉም በላይ ደግሞ በውሳኔህ እስከ መጨረሻው ለመግፋት ቁርጥ አቋም ይኑርህ። በአጭሩ ሕይወትን ምረጥ!

[በገጽ 4 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ከባድ ውሳኔ ከማድረግህ በፊት በቂ ጊዜ ሰጥተህ አስብበት

[በገጽ 5 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ማንኛውንም ሥራ ከመምረጥህ በፊት ሌሎችን አማክር

[በገጽ 7 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

አሁን አምላክን ለማገልገል የወሰኑ ሰዎች ወደፊት ምድርን ገነት በማድረጉ ሥራ ተካፋይ ይሆናሉ