ሊታመን የሚችል ሰው ይኖር ይሆን?
ሊታመን የሚችል ሰው ይኖር ይሆን?
በ1989 የበርሊኑን ቅጥር መውደቅ ተከትሎ በሚገባ ተጠብቀው የነበሩ ብዙ ምስጢሮች ይፋ ወጡ። ለምሳሌ ያህል፣ ሊዲያ a የተባለች ሴት በምሥራቅ ጀርመን በሶሻሊስት አገዛዝ ወቅት ሽታዚ የተባለው የመንግሥት የደህንነት አገልግሎት የግል ሕይወቷን የሚመለከት መረጃ ሰብስቦ እንደነበረ ደረሰችበት። ሊዲያ ይህንን ስትሰማ ቢገርማትም ለስለላ ድርጅቱ መረጃውን ያቀበለው ባሏ መሆኑን ስታውቅ ግን ክፉኛ ደነገጠች። ገመናዋን ያወጣው ሙሉ እምነቷን ልትጥልበት የሚገባት ባሏ ነበር።
የለንደኑ ዘ ታይምስ መጽሔት እንደዘገበው አረጋዊው ሮበርት ሐኪማቸውን “በጣም ያከብሩት፣ ያደንቁትና ይተማመኑበት” ነበር። ሐኪሙ “የደግነትና የርኅራኄ አቀራረብ” እንደነበረው ይነገርለታል። ከዚያም ሮበርት በድንገት ሞቱ። የሞቱት ልባቸው ድንገት ቀጥ ብሎ ወይም በአንጎላቸው ውስጥ የደም መፍሰስ አጋጥሟቸው ይሆን? አይደለም። ጉዳዩ የሚመለከታቸው ባለ ሥልጣናት ሐኪሙ ሮበርትን ለማየት ወደ ቤታቸው በሄደበት ወቅት እርሳቸውም ሆኑ ቤተሰቦቻቸው ሳያውቁ የሚገድል መድኃኒት እንደወጋቸው ገለጹ። ሮበርት ሙሉ እምነት በጣሉበት ሰው እንደተገደሉ ግልጽ ነው።
ሊዲያና ሮበርት አስደንጋጭ የሆነ የእምነት ማጉደል ወንጀል የተፈጸመባቸው ሲሆን ይህም ከባድ መዘዝ አስከትሎባቸዋል። በሌሎች ሁኔታዎች ውጤቱ ያን ያህል አስከፊ ላይሆን ይችላል። ያም ሆኖ በምናምነው ሰው መከዳት የሚያጋጥም ነገር ነው። አንድ ታዋቂ የጀርመን የምርምር ተቋም አልንስባከር ያርቡክ ደር ዴሞስኮፒ 1998-2002 በሚል ርዕስ ያወጣው ሪፖርት እንዳሳየው በአንድ ጥናት ላይ ከተሳተፉት መካከል 86 በመቶ የሚሆኑት ባመኑት ሰው ተከድተዋል። ምናልባት አንተም ተመሳሳይ ሁኔታ አጋጥሞህ ይሆናል። እንግዲያው ኖይ ጹኧርከር ጻይቱንግ የተባለ አንድ የስዊዝ ጋዜጣ በ2002 እንደዘገበው “በኢንዱስትሪ በበለጸጉት ምዕራባውያን አገሮች እምነት ሊጣልባቸው የሚገቡ ዝምድናዎች ላለፉት በርካታ ዓመታት እየተዳከሙ መምጣታቸው” እምብዛም አያስደንቀንም።
ለመገንባት ረጅም ጊዜ ቢወስድም በአንድ ጀምበር ሊጠፋ ይችላል
መተማመን ምንድን ነው? አንድ መዝገበ ቃላት እንደሚገልጸው መተማመን ማለት “[እምነት የተጣለባቸው ሰዎች] ሐቀኞችና እውነተኞች መሆናቸውንና ሆን ብለው የሚጎዳንን ነገር እንደማያደርጉ ማመን ነው።” በአንድ ሰው መተማመን ቀስ በቀስ የሚመጣ ቢሆንም ይህ እምነት በቅጽበት ሊጠፋ ይችላል። በዛሬው ጊዜ ያመኑት ሰው እንደከዳቸው የሚሰማቸው ብዙዎች በመሆናቸው ሰዎች በሌሎች ላይ እምነት ለመጣል ፈቃደኛ ባይሆኑ ሊያስደንቀን ይገባል? በ2002 በጀርመን ታትሞ በወጣ ጥናት መሠረት “በሌሎች ላይ መሠረታዊ እምነት የሚጥሉ ወጣቶች ከሦስት አንድ እንኳን አይሆኑም።”
እንግዲያው ራሳችንን እንደሚከተለው ብለን ልንጠይቅ እንችላለን:- ‘በእርግጥ ልንተማመንበት የምንችል ሰው አለ? የመከዳት አጋጣሚ እያለ በአንድ ሰው ላይ እምነት መጣል ያዋጣል?’
[የግርጌ ማስታወሻ]
a ስሞቹ ተቀይረዋል።
[በገጽ 3 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
በአንድ ጥናት ላይ ከተሳተፉት መካከል 86 በመቶ የሚሆኑት ባመኑት ሰው ተከድተዋል