በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ታማኝ ክርስቲያን ሴቶች—በአምላክ ፊት ውድ ናቸው

ታማኝ ክርስቲያን ሴቶች—በአምላክ ፊት ውድ ናቸው

ታማኝ ክርስቲያን ሴቶች—በአምላክ ፊት ውድ ናቸው

“ውበት ሐሰት ነው፣ ደም ግባትም ከንቱ ነው፤ እግዚአብሔርን የምትፈራ ሴት ግን እርስዋ ትመሰገናለች።”ምሳሌ 31:30

1. ይሖዋ ለውበት ያለው አመለካከት ከዓለም የተለየ የሆነው እንዴት ነው?

 ይህ ዓለም ለውጫዊ ውበት ከፍተኛ ግምት የሚሰጥ ሲሆን ይበልጡን ደግሞ ለሴቶች መልክ ልዩ ትኩረት ይሰጣል። ይሖዋ ግን በዋነኝነት ትኩረት የሚያደርገው ዕድሜ እየጨመረ ሲሄድ ውበቱ ይበልጥ ሊደምቅ በሚችለው በውስጣዊው ማንነታችን ላይ ነው። (ምሳሌ 16:31) በዚህም ምክንያት መጽሐፍ ቅዱስ ለሴቶች የሚከተለውን ምክር ሰጥቷል:- “ለእናንተም ጠጉርን በመሸረብና ወርቅን በማንጠልጠል ወይም ልብስን በመጐናጸፍ በውጭ የሆነ ሽልማት አይሁንላችሁ፣ ነገር ግን በእግዚአብሔር ፊት ዋጋው እጅግ የከበረ የዋህና ዝግተኛ መንፈስ ያለውን የማይጠፋውን ልብስ ለብሶ የተሰወረ የልብ ሰው ይሁንላችሁ።”—1 ጴጥሮስ 3:3, 4

2, 3. በመጀመሪያው መቶ ዘመን ሴቶች ለምሥራቹ መስፋፋት ምን አስተዋጽኦ አድርገዋል? ይህስ በትንቢት የተነገረው ምን ተብሎ ነበር?

2 በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የተጠቀሱ በርካታ ሴቶች ከላይ የተገለጸው ዓይነት ሊመሰገን የሚገባው መንፈስ አሳይተዋል። በመጀመሪያው መቶ ዘመን ከእነዚህ ሴቶች አንዳንዶቹ ኢየሱስንና ሐዋርያቱን የማገልገል መብት አግኝተው ነበር። (ሉቃስ 8:1-3) ቆየት ብሎም ክርስቲያን ሴቶች ቀናተኛ ወንጌላውያን ሆነው አገልግለዋል፤ ሌሎች ደግሞ ሐዋርያው ጳውሎስን ጨምሮ ግንባር ቀደም ሆነው ለሚያገለግሉት ክርስቲያን ወንዶች ከፍተኛ ድጋፍ ሰጥተዋል። አንዳንዶች በቤታቸው የጉባኤ ስብሰባ እንዲካሄድ እንኳ በመፍቀድ ግሩም የሆነ የእንግዳ ተቀባይነት መንፈስ አሳይተዋል።

3 ይሖዋ ከዓላማው አፈጻጸም ጋር በተያያዘ ሴቶች ጉልህ ድርሻ እንዲኖራቸው እንደሚያደርግ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ አስቀድሞ ተነግሯል። ለአብነት ያህል፣ በኢዩኤል 2:28, 29 ላይ ወንዶችና ሴቶች እንዲሁም ወጣቶችና አረጋውያን መንፈስ ቅዱስን እንደሚቀበሉና የአምላክን መንግሥት ምሥራች በማሰራጨቱ ሥራ እንደሚካፈሉ ትንቢት ተነግሮ ነበር። ይህ ትንቢት መፈጸም የጀመረው በ33 እዘአ በጰንጠቆስጤ ዕለት ነበር። (ሥራ 2:1-4, 16-18) በመንፈስ የተቀቡ አንዳንድ ሴቶች ትንቢት እንደመናገር ያሉ ተዓምራዊ ስጦታዎች ተሰጥተዋቸው ነበር። (ሥራ 21:8, 9) ታላቅ መንፈሳዊ ሠራዊት የሆኑት እነዚህ ታማኝ እህቶች በቅንዓት ባከናወኑት አገልግሎት በመጀመሪያው መቶ ዘመን ክርስትና በፍጥነት እንዲስፋፋ አስተዋጽኦ አድርገዋል። እንዲያውም በ60 እዘአ ገደማ ሐዋርያው ጳውሎስ ምሥራቹ “ከሰማይ በታች ባለው ፍጥረት ሁሉ ዘንድ” እንደተሰበከ ጽፏል።—ቆላስይስ 1:23

ባሳዩት ድፍረት፣ ቅንዓትና እንግዳ ተቀባይነት የተመሰገኑ ሴቶች

4. ጳውሎስ በመጀመሪያው መቶ ዘመን የክርስቲያን ጉባኤ ውስጥ የነበሩትን በርካታ ሴቶች ለማመስገን በቂ ምክንያት ነበረው የምንለው ለምንድን ነው?

4 አንዳንድ ሴቶች ያከናወኑትን አገልግሎት ካደነቁ ሰዎች መካከል ሐዋርያው ጳውሎስን እንደ ምሳሌ መጥቀስ ይቻላል። በዛሬው ጊዜ የሚገኙ ክርስቲያን የበላይ ተመልካቾችም እንዲሁ ቀናተኛ የሆኑ ሴቶች የሚያከናውኑትን ሥራ ከፍ አድርገው ይመለከቱታል። ጳውሎስ በስም ከጠቀሳቸው ሴቶች መካከል ‘በጌታ ሆነው የሚደክሙት ፕሮፊሞናና ጢሮፊሞሳ’ እንዲሁም ‘በጌታ እጅግ የደከመችው የተወደደች ጠርሲዳ’ ይገኙበታል። (ሮሜ 16:12) ጳውሎስ ስለ ኤዎድያንና ሲንጤኪን ሲጽፍ “በወንጌል ከእኔ ጋር አብረው ተጋድለዋል” ብሏል። (ፊልጵስዩስ 4:2, 3) ጵርስቅላም ከባለቤቷ ከአቂላ ጋር በመሆን ከጳውሎስ ጎን አገልግላለች። እርሷና አቂላ ለጳውሎስ ሲሉ ‘ነፍሳቸውን ለሞት በማቅረባቸው’ ጳውሎስ “የአሕዛብም አብያተ ክርስቲያናት ሁሉ የሚያመሰግኑአቸው ናቸው እንጂ እኔ ብቻ አይደለሁም” ብሎ ለመጻፍ ተገፋፍቷል።—ሮሜ 16:3, 4፤ ሥራ 18:2

5, 6. ጵርስቅላ በዛሬው ጊዜ ለሚገኙ እህቶች መልካም አርዓያ የምትሆነው በየትኞቹ መንገዶች ነው?

5 ጵርስቅላ ቅንዓትና ድፍረት እንድታሳይ አስተዋጽኦ ያደረገው ምንድን ነው? ጵርስቅላ አንደበተ ርቱዕ የነበረው አጵሎስ አዲስ የተገለጠውን እውነት እንዲገነዘብ በመርዳት ረገድ ለባለቤቷ ድጋፍ እንደሰጠችው የሚናገረው የሐዋርያት ሥራ 18:24-26 ዘገባ ፍንጭ ይሰጠናል። ከዚህ በግልጽ ለመመልከት እንደሚቻለው ጵርስቅላ የአምላክን ቃልና የሐዋርያትን ትምህርት በትጋት ትከታተል ነበር። በዚህም የተነሳ በአምላክና በባለቤቷ ዘንድ ውድ እንድትሆንና በጥንቱ ጉባኤ ውስጥም በአክብሮት እንድትታይ ያስቻሏትን ግሩም ባሕርያት አዳብራለች። መጽሐፍ ቅዱስን በትጋት የሚያጠኑትና ይሖዋ ‘በታማኙ መጋቢ’ በኩል የሚያቀርበውን መንፈሳዊ ምግብ የሚመገቡት በዛሬው ጊዜ ያሉ በርካታ ትጉ ክርስቲያን እህቶችም ከእርሷ ባልተናነሰ ሁኔታ ውድ ናቸው።—ሉቃስ 12:42

6 አቂላና ጵርስቅላ ለየት ያለ የእንግዳ ተቀባይነት መንፈስ ነበራቸው። ጳውሎስ በቆሮንቶስ አብሯቸው ድንኳን ይሰፋ በነበረ ጊዜ ያረፈው በእነርሱ ቤት ነበር። (ሥራ 18:1-3) ባልና ሚስቱ ወደ ኤፌሶን፣ በኋላም ወደ ሮም በሄዱ ጊዜም የእንግዳ ተቀባይነት መንፈስ ማሳየታቸውን የቀጠሉ ሲሆን በቤታቸው የጉባኤ ስብሰባ እንዲካሄድም ፈቅደዋል። (ሥራ 18:18, 19፤ 1 ቆሮንቶስ 16:8, 19) ንምፉንና ማርቆስ የተባለው የዮሐንስ እናት ማርያምም እንዲሁ በቤታቸው የጉባኤ ስብሰባ እንዲካሄድ ፈቅደዋል።—ሥራ 12:12፤ ቆላስይስ 4:15

በዛሬው ጊዜ የሚገኙ ውድ ሀብቶች

7, 8. በዛሬው ጊዜ ያሉ በርካታ ክርስቲያን ሴቶች ምን የሚያስመሰግን ቅዱስ አገልግሎት አከናውነዋል? ስለ ምን ጉዳይስ እርግጠኞች መሆን ይችላሉ?

7 በመጀመሪያው መቶ ዘመን እንደነበረው ሁሉ ዛሬ ያሉ ክርስቲያን ሴቶችም በአምላክ ዓላማ አፈጻጸም በተለይም በወንጌላዊነቱ ሥራ ቁልፍ ሚና ይጫወታሉ። እነዚህ እህቶች እንዴት ያለ መልካም ስም አትርፈዋል! በ2002 በሞት እስካንቀላፉበት ጊዜ ድረስ ይሖዋን ከ50 ለሚበልጡ ዓመታት በታማኝነት ያገለገሉትን እህት ግዌንን እንመልከት። ባለቤታቸው እንዲህ ይላሉ:- “ግዌን በቀናተኛ ወንጌላዊነቷ በከተማችን በሰፊው የታወቀች ነበረች። ማንኛውም ሰው ከይሖዋ ፍቅርና ካዘጋጃቸው ተስፋዎች ተጠቃሚ ሊሆን እንደሚችል ታስብ ነበር። ተስፋ ስንቆርጥ ከምትሰጠን ፍቅራዊ ማበረታቻ በተጨማሪ ለአምላክ፣ ለድርጅቱና ለቤተሰባችን የምታሳየው ታማኝነት አብረን ባሳለፍነው አርኪና አስደሳች የሕይወት ዘመን ሁሉ ለእኔም ሆነ ለልጆቻችን ትልቅ ድጋፍ ሆኖልናል። የእርሷ አለመኖር በጣም አጉድሎብናል።” እህት ግዌንና ባለቤታቸው በትዳር ዓለም 61 ዓመታት አሳልፈዋል።

8 አቅኚዎችና ሚስዮናውያን የሆኑ በአሥር ሺዎች የሚቆጠሩ ትዳር ያላቸውም ሆኑ ነጠላ እህቶች ለሕይወት በሚያስፈልጓቸው መሠረታዊ ነገሮች ረክተው በመኖር ሕዝብ በሚበዛባቸው ከተሞችና ገለልተኛ በሆኑ ክልሎች የመንግሥቱ መልእክት ሰባኪ ሆነው ያገለግላሉ። (ሥራ 1:8) ብዙዎች ይሖዋን ይበልጥ በተሟላ መልኩ ለማገልገል ሲሉ ቤት ንብረት የማፍራት እንዲሁም ልጆች የመውለድ አጋጣሚያቸውን መሥዋዕት አድርገዋል። ተጓዥ የበላይ ተመልካች ሆነው የሚያገለግሉ ባሎቻቸውን በታማኝነት የሚደግፉ ሴቶችም አሉ። ሌሎች በሺዎች የሚቆጠሩ እህቶች ደግሞ በዓለም ዙሪያ በሚገኙ የቤቴል ቤቶች ያገለግላሉ። የራሳቸውን ጥቅም መሥዋዕት ያደረጉት እነዚህ እህቶች የይሖዋን ቤት በክብር ከሚሞሉት ‘ከአሕዛብ ሁሉ የተመረጡ ዕቃዎች’ መካከል እንደሚቆጠሩ ምንም ጥርጥር የለውም።—ሐጌ 2:7

9, 10. ክርስቲያን ሚስቶችና እናቶች የተዉትን ግሩም ምሳሌ አስመልክቶ አንዳንድ የቤተሰባቸው አባላት አድናቆታቸውን የገለጹት እንዴት ነው?

9 እርግጥ ነው፣ አብዛኞቹ ክርስቲያን ሴቶች የቤተሰብ ኃላፊነቶች አሏቸው። ያም ሆኖ ከመንግሥቱ ጋር ለተያያዙ ጉዳዮች ቅድሚያ ይሰጣሉ። (ማቴዎስ 6:33) አንዲት ነጠላ የሆነች አቅኚ እህት እንዲህ ስትል ጽፋለች:- “የዘወትር አቅኚ እንድሆን ትልቅ አስተዋጽኦ ያበረከተው የእናቴ የማይናወጥ እምነትና ግሩም ምሳሌነቷ ነው። እንዲያውም በአቅኚነት ሳገለግል ጥሩ የአገልግሎት ጓደኛዬ ነበረች።” አምስት ትልልቅ ሴቶች ልጆች ያሉት አንድ አባት ስለ ባለቤቱ ሲናገር እንዲህ ይላል:- “ቤታችን ሁልጊዜ ንጹሕና ሥርዓታማ ነበር። ባኒ ቤተሰባችን በመንፈሳዊ ግቦች ላይ እንዲያተኩር ለመርዳት ስትል ቤታችን ቀለል ያለና ኮተት ያልበዛበት እንዲሆን ታደርግ ነበር። በገንዘብ አያያዝ ረገድ ጠንቃቃ መሆኗ ለ32 ዓመታት ያህል የሙሉ ጊዜ ሥራ መሥራት ሳያስፈልገኝ ለቤተሰባችንና ለመንፈሳዊ ጉዳዮች ሰፋ ያለ ጊዜ ለመስጠት አስችሎኛል። ባለቤቴ ታታሪ ሠራተኛ የመሆንን አስፈላጊነትም ለልጆቻችን አስተምራቸዋለች። ምስጋና ሊቸራት የሚገባት ሴት ናት።” በአሁኑ ወቅት ባልና ሚስቱ በይሖዋ ምሥክሮች ዋና መሥሪያ ቤት ያገለግላሉ።

10 ትልልቅ ልጆች ያሉት አንድ ባል ሚስቱን በተመለከተ እንዲህ ሲል ጽፏል:- “ሱዛን አምላክንና ሰዎችን በጥልቅ የምታፈቅር እንዲሁም አሳቢ፣ የሌሎችን ችግር እንደራሷ የምትመለከትና ሐቀኛ በመሆኗ በጣም አደንቃታለሁ። አቅማችን በፈቀደ መጠን ለይሖዋ ምርጣችንን ልንሰጠው ይገባል የሚል አመለካከት አላት። የአምላክ አገልጋይና የልጆች እናት እንደመሆኗ መጠን ያሉባትን ኃላፊነቶች ስትወጣ ይህንን ሥርዓት ተግባራዊ ታደርጋለች።” ይህ ወንድም ሚስቱ በምታደርግለት እርዳታ እየታገዘ በርካታ መንፈሳዊ መብቶች ማግኘት ችሏል። ከእነዚህም መካከል በሽምግልና፣ በአቅኚነት፣ በተተኪ የወረዳ የበላይ ተመልካችነት እንዲሁም በሆስፒታል አገናኝ ኮሚቴ ውስጥ ማገልገል ችሏል። እንደነዚህ ያሉት ሴቶች በባሎቻቸው፣ በእምነት ባልደረቦቻቸውና ከሁሉ በላይ ደግሞ በይሖዋ ዘንድ ምንኛ ውድ ናቸው!—ምሳሌ 31:28, 30

ባል የሌላቸው ውድ ሴቶች

11. (ሀ) ይሖዋ ታማኝ ለሆኑ ሴቶች በተለይም ለመበለቶች እንደሚያስብ ያሳየው እንዴት ነው? (ለ) መበለት የሆኑ ክርስቲያኖችና ባል የሌላቸው ሌሎች ታማኝ እህቶች ስለ ምን ነገር እርግጠኞች መሆን ይችላሉ?

11 ይሖዋ የመበለቶች ደህንነት እንደሚያሳስበው ደጋግሞ ገልጿል። (ዘዳግም 27:19፤ መዝሙር 68:5፤ ኢሳይያስ 10:1, 2) ዛሬም ቢሆን አልተለወጠም። ይሖዋ ለመበለቶች ብቻ ሳይሆን ነጠላ ለሆኑ እናቶች እንዲሁም በፍላጎታቸውም ይሁን ተስማሚ ክርስቲያን ባል ባለማግኘታቸው ምክንያት በነጠላነት ለሚኖሩ ሴቶችም በጥልቅ ያስባል። (ሚልክያስ 3:6፤ ያዕቆብ 1:27) አንቺም ደጋፊ የሆነ ክርስቲያን ባል ሳይኖራቸው ይሖዋን በታማኝነት ከሚያገለግሉት ሴቶች አንዷ ከሆንሽ በአምላክ ዘንድ ውድ እንደሆንሽ እርግጠኛ መሆን ትችያለሽ።

12. (ሀ) አንዳንድ ክርስቲያን እህቶች ለይሖዋ ታማኝ መሆናቸውን ያሳዩት እንዴት ነው? (ለ) አንዳንድ እህቶቻችን ከምን ዓይነት ስሜት ጋር ይታገላሉ?

12 ‘በጌታ ብቻ’ እንዲያገቡ ይሖዋ የሰጠውን ምክር በታማኝነት በመከተላቸው ምክንያት ያላገቡ ክርስቲያን እህቶቻችንን እንደ ምሳሌ እንውሰድ። (1 ቆሮንቶስ 7:39፤ ምሳሌ 3:1) መጽሐፍ ቅዱስ “ለታማኝ ሰው [ይሖዋም] ታማኝ” እንደሆነ ማረጋገጫ ሰጥቷቸዋል። (2 ሳሙኤል 22:26 አ.መ.ት) ያም ሆኖ ለብዙዎቹ በነጠላነት መኖር ከባድ ነው። አንዲት እህት እንዲህ ትላለች:- “በጌታ ብቻ ለማግባት የወሰንኩ ቢሆንም እንኳ ጓደኞቼ ግሩም የሆኑ ክርስቲያን ወንዶችን ሲያገቡ እኔ ግን ነጠላ ሆኜ በመቅረቴ ብዙ ጊዜ አንብቻለሁ።” አንዲት ሌላ እህት ደግሞ እንዲህ ትላለች:- “ይሖዋን ለ25 ዓመታት ያህል አገልግዬዋለሁ። እስከ መጨረሻው ድረስ ለእርሱ ታማኝ ለመሆን የቆረጥኩ ቢሆንም ብዙውን ጊዜ የብቸኝነት ስሜት ሆድ ያስብሰኛል።” አክላም “እንደ እኔ ያሉ እህቶች ማበረታቻ በጣም ያስፈልጋቸዋል” ብላለች። እንደ እነዚህ ያሉትን ታማኝ እህቶች እንዴት ልንረዳቸው እንችላለን?

13. (ሀ) የዮፍታሔን ሴት ልጅ ለመጠየቅ ይሄዱ ከነበሩት እስራኤላውያን ምሳሌ ምን እንማራለን? (ለ) በጉባኤያችን ለሚገኙ ነጠላ እህቶች አሳቢነታችንን ማሳየት የምንችልባቸው ሌሎች መንገዶች ምንድን ናቸው?

13 አንድ ጥንታዊ ታሪክ እነዚህን እህቶች መርዳት የምንችልበትን አንዱን መንገድ ይጠቁመናል። የዮፍታሔ ሴት ልጅ ባል የማግባት አጋጣሚዋን በፈቃዷ ስትተው መሥዋዕትነት እየከፈለች እንደሆነ ሕዝቡ ተገንዝቦ ነበር። እርሷን ለማበረታታት ምን አደረጉ? “የእስራኤልም ሴቶች ልጆች በዓመት በዓመቱ እየሄዱ የገለዓዳዊውን የዮፍታሔን ልጅ በዓመት አራት ቀን ሙሾ እንዲያወጡ [“እንዲያመሰግኑ፣” የ1879 እትም] በእስራኤል ዘንድ ልማድ ሆነ።” (መሳፍንት 11:30-40) በተመሳሳይ እኛም የአምላክን ሕግ በታማኝነት ለሚታዘዙ ነጠላ እህቶች ልባዊ አድናቆታችንን ልንገልጽላቸው ይገባል። a አሳቢነታችንን በምን ሌላ መንገድ መግለጽ እንችላለን? እነዚህ ውድ የሆኑ ታማኝ እህቶች በአገልግሎታቸው መጽናት እንዲችሉ እንዲደግፋቸው ይሖዋን በጸሎታችን ልንለምነው ይገባል። ይሖዋም ሆነ መላው የክርስቲያን ጉባኤ በጥልቅ እንደሚወዷቸውና ከልብ እንደሚያደንቋቸው ልናረጋግጥላቸው ይገባል።—መዝሙር 37:28

ነጠላ የሆኑ ወላጆች ሊሳካላቸው የቻለው እንዴት ነው?

14, 15. (ሀ) ነጠላ የሆኑ ክርስቲያን እናቶች ይሖዋ እንዲረዳቸው መጠየቅ ያለባቸው ለምንድን ነው? (ለ) ነጠላ የሆኑ እናቶች ከጸሎታቸው ጋር የሚስማማ እርምጃ ሊወስዱ የሚችሉት እንዴት ነው?

14 ነጠላ ወላጆች የሆኑ ክርስቲያን ሴቶችም በርካታ ፈታኝ ሁኔታዎች ያጋጥሟቸዋል። ሆኖም ከመጽሐፍ ቅዱስ መመሪያዎች ጋር በሚስማማ መንገድ ልጆቻቸውን በማሳደግ ረገድ የይሖዋን እርዳታ መጠየቅ ይችላሉ። ነጠላ ወላጅ ከሆንሽ በሁሉም መስኮች እናትም አባትም ልትሆኚ እንደማትችዪ እሙን ነው። ያም ሆኖ ይሖዋን በእምነት ከጠየቅሽው ያሉብሽን በርካታ ኃላፊነቶች መወጣት እንድትችዪ ይረዳሻል። ጉዳዩን በምሳሌ ለማስረዳት ያህል:- ከገበያ የገዛሻቸውን ዕቃዎች የያዘ ከባድ ዘንቢል ራቅ ብሎ ወደሚገኘው ቤትሽ መውሰድ አለብሽ እንበል። መጓጓዣ መጠቀም ስትችዪ ዘንቢሉን ተሸክመሽ በእግርሽ ለመሄድ ትመርጫለሽ? እንደማታደርጊው የታወቀ ነው! በተመሳሳይም ይሖዋ እንዲረዳሽ መጠየቅ እየቻልሽ ከባድ የሆኑ ስሜታዊ ሸክሞችን ብቻሽን ለመሸከም አትሞክሪ። እንዲያውም ይሖዋ እርዳታ እንድትጠይቂው አበረታትቶሻል። መዝሙር 68:19 ‘ሸክማችንን በየዕለቱ የሚሸከምልን . . . ጌታ ይባረክ’ ይላል። [አ.መ.ት] በተመሳሳይም 1 ጴጥሮስ 5:7 ‘እርሱ ስለ እናንተ ያስባልና የሚያስጨንቃችሁን ሁሉ በእርሱ ላይ ጣሉት’ የሚል ግብዣ አቅርቦልሻል። እንግዲያው ችግሮችና የሚያስጨንቁ ነገሮች ሲከብዱብሽ ‘ሳታቋርጪ’ በመጸለይ ሸክምሽን በሰማይ በሚኖረው አባትሽ ላይ ጣዪው።—1 ተሰሎንቄ 5:17፤ መዝሙር 18:6፤ 55:22

15 ለምሳሌ፣ እናት ከሆንሽ ልጆችሽ በትምህርት ቤት ከእኩዮቻቸው ሊደርስባቸው የሚችለው ተጽዕኖ ወይም አቋማቸውን በተመለከተ ሊያጋጥማቸው የሚችለው ፈተና እንደሚያሳስብሽ የታወቀ ነው። (1 ቆሮንቶስ 15:33) ስለ እነዚህ ጉዳዮች መጨነቅሽ ተገቢ ነው። ሆኖም ጸሎት የሚያሻቸው ጉዳዮችም ናቸው። እንዲያውም ልጆችሽ ወደ ትምህርት ቤት ከመሄዳቸው በፊት፣ ምናልባትም የዕለቱን ጥቅስ አብራችሁ ካነበባችሁ በኋላ ስለ እነዚህ ጉዳዮች አንስተሽ እነርሱ ባሉበት ለምን አትጸልዪም? ከልብ የመነጩና ነጥቡን ለይተው የሚጠቅሱ ጸሎቶች የልጆችሽን ልብ ሊነኩ ይችላሉ። ከሁሉ በላይ ደግሞ የአምላክን ቃል በልጆችሽ ልብ ውስጥ ለመትከል በትዕግሥት ጥረት ስታደርጊ የይሖዋን እርዳታ የማግኘት አጋጣሚ ይኖርሻል። (ዘዳግም 6:6, 7፤ ምሳሌ 22:6) ‘የይሖዋ ዓይኖች ወደ ጻድቃን እንደሆኑና ጆሮዎቹም ለጸሎታቸው ክፍት እንደሆኑ’ አትዘንጊ።—1 ጴጥሮስ 3:12፤ ፊልጵስዩስ 4:6, 7

16, 17. (ሀ) አንድ ልጅ እናቱ ስላሳየችው ፍቅር ምን ብሏል? (ለ) እናትየው የነበራት መንፈሳዊ አመለካከት በልጆቿ ላይ ተጽዕኖ ያሳደረው እንዴት ነው?

16 የስድስት ልጆች እናት የሆነችውን የኦሊቫን ምሳሌ እንመልከት። አማኝ ያልሆነው ባለቤቷ የመጨረሻ ልጃቸው እንደተወለደች ቤተሰቡን ትቶ ቢሄድም ኦሊቫ ልጆቿን በአምላክ መንገድ የማሠልጠኑን ኃላፊነት በፈቃደኝነት ተቀበለች። አሁን 31 ዓመት የሆነውና በክርስቲያን ጉባኤ ውስጥ ሽማግሌና አቅኚ ሆኖ የሚያገለግለው ዳረን የተባለው ልጅዋ በዚያን ጊዜ የአምስት ዓመት ልጅ ነበር። ይባስ ብሎ ደግሞ ዳረን አሁንም ድረስ በሚቸገርበት የጤና እክል መጠቃቱ የኦሊቫን ጭንቀት የሚያባብስ ነበር። ዳረን የልጅነት ሕይወቱን በማስታወስ እንዲህ ሲል ጽፏል:- “ሆስፒታል አልጋዬ ላይ ቁጭ ብዬ የእማዬን መምጣት በጉጉት የምጠባበቅበትን ጊዜ አሁንም ድረስ አስታውሰዋለሁ። እማዬ አጠገቤ ትቀመጥና መጽሐፍ ቅዱስን በየዕለቱ ታነብልኝ ነበር። ከዚያም ‘ይሖዋ እናመሰግንሃለን’ የሚለውን የመንግሥቱን መዝሙር ትዘምርልኛለች። b ይህንን መዝሙር አሁንም ድረስ በጣም እወደዋለሁ።”

17 ኦሊቫ ልጆቿን ብቻዋን ብታሳድግም በይሖዋ ላይ ያላት ትምክህትና ለእርሱ ፍቅር ማዳበሯ እንዲሳካላት ረድተቷታል። (ምሳሌ 3:5, 6) ለልጆቿ ያስቀመጠችላቸው ግቦች መንፈሳዊ አመለካከት እንደነበራት ያሳያሉ። ዳረን እንዲህ ብሏል:- “እማዬ የሙሉ ጊዜ አገልግሎት ግብ እንድናወጣ ሁልጊዜ ታበረታታን ነበር። በዚህም ምክንያት እኔና ከአምስቱ እህቶቼ አራቱ ወደ ሙሉ ጊዜ አገልግሎት ገባን። ሆኖም እማዬ ስለ እነዚህ ነገሮች ፈጽሞ በጉራ ተናግራ አታውቅም። የእርሷን ግሩም ባሕርያት ለመኮረጅ ከፍተኛ ጥረት እያደረግሁ ነው።” እርግጥ ነው፣ ሁሉም ወላጆች እንደ ኦሊቫ ልጆቻቸው የአምላክ አገልጋዮች ላይሆኑ ይችላሉ። ሆኖም አንዲት እናት በመጽሐፍ ቅዱስ መመሪያዎች መሠረት ለመኖር የምትችለውን ሁሉ ካደረገች ይሖዋ እንደሚመራትና ፍቅራዊ ድጋፍ እንደሚያደርግላት እርግጠኛ መሆን ትችላለች።—መዝሙር 32:8

18. ይሖዋ በክርስቲያን ጉባኤ በኩል ያደረገልንን ዝግጅት እንደምናደንቅ ማሳየት የምንችለው እንዴት ነው?

18 አምላክ ከሚሰጠን ድጋፍ አብዛኛውን የምናገኘው ከክርስቲያን ጉባኤ ነው። ጉባኤው ቋሚ በሆነ የመንፈሳዊ ማዕድ ፕሮግራም፣ በክርስቲያናዊ ወንድማማችነትና በመንፈሳዊ በጎለመሱ “ስጦታ የሆኑ ወንዶች” አማካኝነት ድጋፍ ይሰጠናል። (ኤፌሶን 4:8 NW) ታማኝ የሆኑ ሽማግሌዎች “ወላጆች የሌላቸውን ልጆች ባልቴቶችንም በመከራቸው” ለሚያስፈልጋቸው ነገር ልዩ ትኩረት በመስጠት በጉባኤ ውስጥ ያሉትን በሙሉ ለመገንባት ጠንክረው ይሠራሉ። (ያዕቆብ 1:27) እንግዲያው ፈጽሞ ራሳችሁን ሳታገልሉ ከአምላክ ሕዝቦች ጋር ተጣብቃችሁ ኑሩ።—ምሳሌ 18:1፤ ሮሜ 14:7

ተገዢነት—ማራኪ የሆነ ባሕርይ

19. ሚስት ለራስነት ሥልጣን መገዛቷ የበታች እንድትሆን አያደርጋትም የምንለው ለምንድን ነው? የትኛው የመጽሐፍ ቅዱስ ምሳሌ ለዚህ ማስረጃ ይሆነናል?

19 ይሖዋ ሴትን የፈጠራት የወንድ ማሟያ እንድትሆን ነው። (ዘፍጥረት 2:18) በዚህም ምክንያት ሚስት ለባሏ ተገዢ መሆኗ ከእርሱ የምታንስ አያደርጋትም። ከዚህ ይልቅ በርካታ ተሰጥኦዎቿንና ችሎታዎቿን ከአምላክ ፈቃድ ጋር በሚስማማ መንገድ ለመጠቀም አጋጣሚ ስለሚሰጣት ያስከብራታል። ምሳሌ ምዕራፍ 31 በጥንቷ እስራኤል የምትኖር ልባም ሚስት የምታከናውናቸውን የተለያዩ ተግባሮች ይዘረዝራል። የተቸገሩትን ትረዳ፣ ወይን ትተክል እንዲሁም መሬት ትገዛ ነበር። በእርግጥም፣ “የባልዋ ልብ ይታመንባታል፣ ምርኮም አይጐድልበትም።”—ቁጥር 11, 16, 20

20. (ሀ) አንዲት ክርስቲያን ሴት ከአምላክ ያገኘቻቸውን ችሎታዎች ወይም ተሰጥኦዎች እንዴት ልትጠቀምባቸው ይገባል? (ለ) አስቴር ምን ግሩም ባሕርያት ነበሯት? ይህስ ይሖዋ እንዲጠቀምባት ያስቻለው እንዴት ነው?

20 ቦታዋን የምታውቅና ፈሪሃ አምላክ ያላት ሴት ከባሏ ልቃ ለመታየት ወይም ከእርሱ ጋር ለመፎካከር አትሞክርም። (ምሳሌ 16:18) ዓለማዊ ግቦችን ሥራዬ ብላ በማሳደድ የራሷን ጥቅም ለማሟላት አትሯሯጥም። ከዚህ ይልቅ ከአምላክ ያገኘችውን ተሰጥኦ ሌሎችን ማለትም ቤተሰቧን፣ ክርስቲያን ባልንጀሮቿን፣ ጎረቤቶቿንና ከሁሉ በላይ ደግሞ ይሖዋን ለማገልገል ትጠቀምበታለች። (ገላትያ 6:10፤ ቲቶ 2:3-5) በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሚገኘውን የንግሥት አስቴርን ምሳሌ እንመልከት። ማራኪ ውበት የነበራት ቢሆንም ልኳን የምታውቅና ለሥልጣን የምትገዛ ሴት ነበረች። (አስቴር 2:13, 15) ካገባች በኋላም ከእርሷ በፊት ከነበረችው ከንግሥት አስጢን በተቃራኒ ባሏን በጥልቅ ታከብረው ነበር። (አስቴር 1:10-12፤ 2:16, 17) ከዚህም በላይ አስቴር ንግሥት ከሆነችም በኋላ እንኳ በዕድሜ የሚበልጣትን የአጎቷን ልጅ መርዶክዮስን በአንዳንድ አስፈላጊ ጉዳዮች ረገድ ትታዘዘው ነበር። ይህ ሲባል ግን አስቴር ደካማ ነበረች ማለት አይደለም! አይሁድን ለማጥፋት ሴራ የጠነሰሰውን ኃያሉንና ጨካኙን ሐማን በድፍረት አጋልጣዋለች። ይሖዋ ሕዝቡን ከጥፋት ለመታደግ አስቴርን በከፍተኛ ሁኔታ ተጠቅሞባታል።—አስቴር 3:8 እስከ 4:17፤ 7:1-10፤ 9:13

21. አንዲት ክርስቲያን ሴት በይሖዋ ዓይን ይበልጥ ውድ መሆን የምትችለው እንዴት ነው?

21 በግልጽ ለመመልከት እንደሚቻለው በጥንት ጊዜም ይሁን ዛሬ ለአምላክ ያደሩ ሴቶች ይሖዋንና የእርሱን አምልኮ በሙሉ ልባቸው ደግፈዋል። በመሆኑም ፈሪሃ አምላክ ያላቸው ሴቶች በይሖዋ ዓይን ውድ ናቸው። ክርስቲያን እህቶች፣ ይሖዋ ‘ለበጎ ሥራ ሁሉ የተዘጋጃችሁ’ ይበልጥ ጥራት ያለው የክብር “ዕቃ” እንድትሆኑ በየጊዜው በመንፈሱ አማካኝነት እንዲቀርጻችሁ ፍቀዱለት። (2 ጢሞቴዎስ 2:21፤ ሮሜ 12:2) የአምላክ ቃል እንደነዚህ ስላሉት ውድ የሆኑ የይሖዋ አምላኪዎች ሲናገር “ከእጅዋ ፍሬ ስጡአት፣ ሥራዎችዋም በሸንጎ ያመስግኑአት” ይላል። (ምሳሌ 31:31) እናንተም እንደዚህ የሚባልላችሁ እንድትሆኑ እንመኛለን።

[የግርጌ ማስታወሻ]

a አድናቆታችንን መግለጽ የምንችልበትን መንገድ በተመለከተ የመጋቢት 15, 2002 መጠበቂያ ግንብ ገጽ 26-28⁠ን ተመልከት።

b ይህ መዝሙር በይሖዋ ምሥክሮች በተዘጋጀው ለይሖዋ የውዳሴ መዝሙር ዘምሩ በተባለው ቡክሌት ላይ የሚገኘው መዝሙር 212 ነው።

ታስታውሳለህ?

• በመጀመሪያው መቶ ዘመን የኖሩ አንዳንድ ክርስቲያን ሴቶች በይሖዋ ዓይን ውድ የሆኑት ለምን ነበር?

• በዘመናችን የሚኖሩ ብዙ እህቶች በይሖዋ ዓይን ውድ እንዲሆኑ ያደረጋቸው ምንድን ነው?

• ይሖዋ ነጠላ የሆኑ እናቶችንና ባል የሌላቸውን ሌሎች እህቶች የሚደግፈው በምን መንገዶች ነው?

• አንዲት ሴት ለራስነት ሥልጣን ልባዊ አክብሮት እንዳላት ማሳየት የምትችለው እንዴት ነው?

[የአንቀጾቹ ጥያቄዎች]

[በገጽ 17 ላይ የሚገኝ ሣጥን]

ልናሰላስልባቸው የሚገቡ ምሳሌዎች

በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የተጠቀሱ የእምነት ምሳሌ የሚሆኑ ሌሎች ታማኝ ሴቶችን ማወቅ ትፈልጋላችሁ? ከሆነ ከዚህ በታች የቀረቡትን ጥቅሶች እንድታነብቡ እንጋብዛችኋለን። በእነዚህ ግለሰቦች ታሪክ ላይ በምታሰላስሉበት ጊዜ በሕይወታችሁ ውስጥ ይበልጥ ልትሠሩባቸው የምትፈልጓቸውን መሠረታዊ ሥርዓቶች ለማስተዋል ሞክሩ።—ሮሜ 15:4

ሣራ:- ዘፍጥረት 12:1, 5፤ 13:18ሀ፤ 21:9-12፤ 1 ጴጥሮስ 3:5, 6

ለጋስ የሆኑ እስራኤላውያን ሴቶች:- ዘጸአት 35:5, 22, 25, 26፤ 36:3-7፤ ሉቃስ 21:1-4

ዲቦራ:- መሳፍንት 4:1 እስከ 5:31

ሩት:- ሩት 1:4, 5, 16, 17፤ 2:2, 3, 11-13፤ 4:15

ሱነማዊቷ ሴት:- 2 ነገሥት 4:8-37

ከነዓናዊቷ ሴት:- ማቴዎስ 15:22-28

ማርታና ማርያም:- ማርቆስ 14:3-9፤ ሉቃስ 10:38-42፤ ዮሐንስ 11:17-29፤ 12:1-8

ጣቢታ:- ሥራ 9:36-41

የፊልጶስ አራት ሴቶች ልጆች:- ሥራ 21:9

ፌቤን:- ሮሜ 16:1, 2

[በገጽ 15 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

የአምላክን ሕግ በታማኝነት የሚታዘዙ ያላገቡ እህቶችን እንደምታደንቋቸው ትገልጹላቸዋላችሁ?

[በገጽ 16 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ልጆች ወደ ትምህርት ቤት ከመሄዳቸው በፊት ስለ ምን ነገር ጠቅሶ መጸለይ ይቻላል?